አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 02 March 2018

አዲስ አበባ የካቲት 23/2010 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከማድረግ አኳያ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበለትን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊነት ላይ በጥልቀት ከተወያየ በኋላ በምክር ቤቱ ከተገኙ 490 አባላት መካከል በ395 የድጋፍ ድምጽ፣ በ88 ተቃውሞ እንዲሁም በ7 ድምጸ ተአቅቦ አጽድቆታል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ እንዲሁም የሕዝብን ሠላምና ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ እየተስፋፋ መምጣቱን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ዛሬ ለምክር ቤቱ አባላት አብራርተውላቸዋል። 

በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የተነሳም በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የሕብረተሰቡ ክፍሎች መንግሥት የሕግ ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግላቸው በተለያዩ መድረኮች መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

በሕገ መንግሥቱ ላይ የተጋረጠውን አደጋ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት መከላከልና መቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማውጣት ማስፈለጉን አቶ ጌታቸው አንስተዋል።

አዋጁ መጽደቁ ተገቢና ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑንም ኢዜአ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል።

ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በአገሪቷ በነበረው የፀጥታ ችግር ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሉ አተገባበሩ ላይ ክፍተቶች የነበሩ በመሆኑ ይህ እንዳይደገም ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የጅባትና የኖኖን ሕዝብ በመወከል የመጡት አቶ አበበ ከፈኒ እንዳሉት ከዚህ ቀደም በነበረው አዋጅ ላይ በተለይ የሰብአዊ መብት አያያዝ ጥሰቶችና በዴሞክራሲ መብቶች ዙሪያም የአተገባበር ክፍተቶች የታዩበት በመሆኑ የአካባቢው ሕዝብ እንደ ስጋት ሲያነሳ መቆየቱን ገልጸዋል።

የሕዝቡንም ጥያቄ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ለማቅረብ መሞከሩን ገልጸው፤ “እያንዳንዱ የፓርላማ አባል በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን መብት በመጠቀም ለሕዝብ ይበጃል ያለውን ሀሳብ የመደገፍ መብት ያለው በመሆኑ ከዚህ አንፃር በአብላጫ ድምጽ አዋጁ ሊጸድቅ ችሏል” ነው ያሉት።

አዋጁ መጽደቁን ተከትሎ በየደረጃው ያለው የመንግሥት መዋቅር፣ ሕዝቡና ወጣቱ ከአላስፈላጊ ስህተት እራሱን በመጠበቅ አዋጁና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትሎ ተግባራዊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

ከደቡብ ክልል ሕዝቦች የተወከሉት የምክር ቤቱ አባል አቶ ናስር ካንሱ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ የፀጥታ ሁኔታ በጥያቄ ውስጥ በመሆኑ አዋጁ ለመታወጅ አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

መንግሥትም የሕዝቡንና የወጣቱን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ይዞ በመሥራት ላይ ባለበት ሁኔታ ያንን እንኳን ለመተግበር አስቸጋሪ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል።

“በመሆኑም በአገሪቷ የተፈጠረውን ይህን ችግር ለመፍታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጁ ታሪካዊ ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ከሱማሌ ክልል ሕዝብን በመወከል የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ወይዘሮ ካይዝ አብደላ አገሪቷ አሁን ካለው የፀጥታ ችግር አኳያ የአዋጁ መጽደቅ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጴጥሮስ ወልደሰንበት እንዳሉት አዋጁ መውጣቱ ከሕገ መንግሥቱ አኳያ ተገቢ ነው።

“በአገሪቷ አሁን ያለው የፀጥታ ሁኔታ በመደበኛ የሕግ ሂደት የሚፈታ ባለመሆኑ ዜጎች የመዘዋወር መብታቸው ተነፍጓል፤ መንገዶች ተዘግተው ከንብረት ውድመት እስከ ሕይወት ሕልፈት አደጋ ተፈጽሟል” ነው ያሉት።

በመሆኑም ችግሩን ለመፍታትና ዜጎችን ለመታደግ መንግሥት የወሰደው እርምጃ አግባብነት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የአገሪቷ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 (ሀ) የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚታወጅ ይደነግጋል።

ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰትም፣ የፌዴራሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን እንዳለውም ይገልጻል።

 

Published in ፖለቲካ

አምቦ  የካቲት 23/2010 በአምቦ ከተማ የከተሞች የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር ተግባራዊ ባለመደረጉ ተጠቃሚ መሆን አልቻልንም ሲሉ በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

 የአምቦ ከተማ ነዋሪ አቶ ክፍሌ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ ለማሻሻል የዘረጋው የምግብ ዋስትና መርሃ ግብር በከተማዋ ተግባራዊ ባለመደረጉ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም ።

 በተለይ መርሃ ግብሩ የመስሪያ ቦታና የመንቀሳቀሻ ካፒታል ድጋፍ የሚደረግበት በመሆኑ ከልምና ሕይወታቸው ያላቅቀናል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

 ወጣት ልደት ምስጋና በበኩሏ በልጅነቷ ከቤተሰቦቿ በመለየቷ እስካሁን ድረስ አዳጋች ሕይወት ለመግፋት መገደዷን አስታውሳለች።

 በችግር ምክንያት ለልመና ሕይወት መዳረጓን የምትናገረው ወጧቷ፣ በአሁኑ ወቅት ከሦስት ልጆቿ ጋር በችግር ውስጥ መሆኗን ነው የገለጸችው።

 የምግብ ዋስትና መርሃ ገብሩ በከተማው ቢጀመር የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንደሚያደርጋት ጠቁማ፣ መርሃ ግብሩ በፍጥነት እንዲጀመር ጠይቃለች።

 የአምቦ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዲልጋሱ በበኩላቸው፣ የተነሳው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን አምነዋል።

 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተቀረጸው መርሃ ግብር በተለያዩ ምክንያቶች በከተማዋ ተግባራዊ ሳይሆን መቆየቱን አስታውሰዋል።

 መርሃ ግብሩ እንዳይተገበር ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ ግልጽ የአሰራር  አቅጣጫ  አለመቀመጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀድመው ወደ ትግበራ የገቡት ከተሞች ተሞክሮ አለመወሰዱም መርሀ ግብሩ እንዳይተገበር አስተዋጽኦ ማድረጉን አመልከተዋል።

 በተያዘው ዓመት  የመርሃ ግብሩ  ተጠቃሚዎችን የመለየት ሥራ በማጠናቀቅና ከመንግስት በጀት በማስለቀቅ ወደሥራ ለመግባት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መርምሮ  አጸደቀ።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባደረገው ስብሰባ የአዋጁን አስፈላጊነት ከመረመረ በኋላ በ395 ድምጽ ድጋፍ፣88 ተቃውሞ እና በ7 ድምጸ ተአቅቦ አጽድቆታል።

አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መንግስት ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ የመከላከልና የመጠበቅ፣ የአገርን ሰላምና ደህንንነት ለማስከበር በሚል መጽደቁ ይታወሳል።

በተጨሪም የህዝቦችን አንድነትና እኩልነት እውን በማድረግ የዜጎችን በነፃነት የመዘዋወር መብት ለመጠበቅ ፣ በመረጡት ቦታ የመኖርና ሀብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ መሆኑንም ተጠቁሞ ነበር።

ስለሆነም ምክር ቤቱ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ 1 ( ሀ) መሰረት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን አረጋግጧል።

አዋጁ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ከየካቲት 09/2010 ዓ.ም ጀምሮ የጸና ይሆናል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጸደቀ።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአገሪቱ ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ህገ መንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ ለመታደግ በሚል የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወቃል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጌታቸው አምባዬ የአዋጁን ዝርዝር ሁኔታ ለምክር ቤቱ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ በተከሰተው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ዜጎች ህገ-መንግስቱ ያጎናጸፋቸውን መብቶች አንዳይጠቀሙ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

በሰውና ንብረት ላይ አደጋ ማድረስ፣ ዜጎችን ማፈናቀል፣ የመንግስት አገልግሎት ተቋማትን ማውደም፣ የኢንቨስትመንት ተቋማትን ማጥቃትና ሌሎች ህገወጥ እንቅስቃሴዎች በስፋት የተንጸባረቁ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አብራርተዋል።

እነዚህን ችግሮች በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርዓት መቀልበስ እንዳልተቻለ የገለጹት አቶ ጌታቸው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን በመገንዘብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው አዋጁን በሚመለከት የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አቅርበዋል።

ከምክር ቤቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ጠቅላይ አቃቤ ህጉ ማብራሪያ ሰጥተውባቸዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ በቡድን ሆኖ መንቀሳቀስን በሚመለከት ለተቀመጠው አንቀጽ ግልጽ መመሪያ ይወጣል።

የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን መዝጋት በሚመለከት ለተነሳ ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።

ወቅታዊ ሁኔታውን በመጠቀም በአገሪቱ ውስን ሃብት በሆነው መሬት ላይ ህገወጥ ድርጊት መበራከቱን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው "የመሬት ጉዳይ ህግ የማስከበር አንዱ አካል ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

በዛሬው የምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ 490 አባላት የተገኙ ሲሆን፤ አባላቱ ሰፊ ክርክር ካደረጉ በኋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በ395 የድጋፍ ድምጽ፣ በ88 ተቃውሞና በሰባት ድምፀ ተአቅቦ አጽድቆታል።

አዋጁም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከታወጀበት ከየካቲት 09 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የፀና ይሆናል።

Published in ፖለቲካ

ነገሌ የካቲት 23/6/2010 የጉጂ ዞን ፖሊስ ከ900 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የኮንትሮባንድ እቃ ትላንት በቦሬ ከተማ መያዙን አስታወቀ፡፡ 

 በዞኑ ፖሊስ የህግ ማስከበር አስተባባሪ ኮማንደር ኤደን ዱባ እንዳሉት የኮንትሮባንድ እቃው በህብረተሰቡ ጥቆማ የተያዘው ታርጋ ቁጥር ኮድ 3 - 24025 በሆነ የቤት መኪና ከሻኪሶ ከተማ ወደ መሀል አገር በመጓጓዝ ላይ እንዳለ ነው፡፡

 ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል 2 ሺ 980 የሞባይል ቀፎዎችና የተለያዩ ጫማዎች ይገኙበታል፡፡

 ''ፖሊስም የተያዘውን የኮንትሮባንድ እቃ ለነገሌ ቦረና ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያ በማስረከብ አሽከርካሪውንና ተሽከርካሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን እያጣራ ነው'' ብለዋል፡፡

 የዞኑ ህዝብ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለማጋለጥ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

 ባለፉት ስድስት ወራት ከሞያሌ በጉጂ ዞን በኩል ወደ መሀል አገር ሲጓጓዝ የነበረ 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የኮንትሮ ባንድ እቃ በዞኑ የፖሊስ አባላት መያዙን አስታውቀዋል፡፡

 ከተያዙት የኮንትሮ ባንድ እቃ መካከል በዋናነት 134 ቴሌቪዢኖች፣ ሽቶ፣ የተለያዩ ልባሽ ጨርቆች፣ 300 ጀሪካን ዘይት 22 ሞተር ሳይክሎችና ሌሎችም እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2010 ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስኮች እያስመዘገበች ያለውን እድገት ለማስቀጠል ዜጎች በቀደምት ጀግኖቿ ፅናት በጸረ ድህነት ትግሉ ላይ ሊረባረቡ እንደሚገባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ተናገሩ።

122ኛው የአድዋ ድል በዓል ጀግኖች አርበኞች፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የውጭ አገራት አምባሳደሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በምኒልክ አደባባይ ተከብሯል።

ከንቲባ ድሪባ ኩማ "የአድዋ ድል አፍሪካዊያንና መላው ነጻነት ወዳድ ህዝቦች በኢትዮጵያ አማካኝነት ታሪካቸውን የቀየሩበትና የ'ይቻላል' መንፈስ የተጎናጸፉበት ደማቅ ድል ነው" ብለዋል።

ቀደምት የአገሪቷ ጀግኖች ውድ ዋጋ በመክፈል ያስገኙት አንጸባራቂ ድልና ለጥቁር ህዝቦች ነጻነት የከፈሉት መስዋዕትነትም ትልቅ ነው።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን እንደ ጀግኖች አርበኞቹ አገሪቷ አሁን ለጀመረችው የልማትና የእድገት ጉዞ ቀጣይነት መረጋገጥ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያን ህዳሴ ከግብ ማድረስ የሚቻለው የአገሪቷ ሰላም በአስተማማኝ መልኩ ሲረጋገጥና ህብረተሰቡም በሙሉ አቅሙ በየተሰማራበት መስክ ሲንቀሳቀስ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአካባቢን ሰላም በመጠበቅና የተጀመሩትን የልማት ጉዞ በማስቀጠል ረገድ "መላ የአገሪቱ ህዝቦች በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋል" ሲሉም አክለዋል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር አለማየሁ አበበ በበኩላቸው፤ አድዋ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም ህዝቦች በሙሉ በተለይም ለጥቁር ህዝቦች "አዲስ ምዕራፍ የከፈተና ለተገፉና ለተጨቆኑ ህዝቦች ነጻነት ያጎናጸፈ ነው" ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

ወልዲያ የካቲት 23/2010 የወልድያና አካባቢው ነዋሪዎች የረዢም ዓመታት ጥያቄ የነበረው የኤሌክትሪክ መብራት ኃይል አቅርቦት ችግር መፈታቱ ተገለፀ፡፡

የወልድያ ከተማ መብራት ሃይል የደንበኞች አገልግሎት ስራአስኪያጅ አቶ ዮናስ ጌታቸው እንደገለፁት ችግሩ የተፈታው ከወልዲያ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 40 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ ተጨማሪ ትራንስፎርመር ተተክሎ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ነው፡፡

ቀደም ሲል የወልድያ ንኡስ ጣቢያ በሚያመነጨው 11 ሜጋዋት የህብረተሰቡን ፍላጎትና አቅርቦት ማመጣጠን ባለመቻሉ ተደጋጋሚ የሃይል መቆራረጥ ይከሰት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ህብረተሰቡ ተደጋጋሚ ጥያቄ በማቅረብ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው ከተዘረጋው ከፍተኛ የሃይል መስመር ላይ ተጠልፎ ወደዚሁ ትራንስፎርመር የገባው የኤሌክትሪክ ሃይል የአካባቢውን የመብራት ችግር መፍታት እንዳስቻለ ገልፀዋል።

አሁን አገልግሎት የጀመረው የሃይል ምንጭ በፊት ከነበረውን 11 ሜጋዋት ወደ 51 ሜጋዋት በማሳደግ ችግሩን እንደሚያቃልል አረጋግጠዋል፡፡

ከዚህም በፊት በሃይል እጥረት ምክንያት ተከልክለው የነበሩ በርካታ ሃይል ፈላጊ አመልካቾችን ለማስተናገድ ምዝገባ መጀመሩን አቶ ዮናስ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በወልድያ ከተማ የወፍጮ ቤት ባለቤት ወይዘሮ አቻሽማን ክቡር በሰጡት አስተያየት በተደጋጋሚ ይፈጠር በነበረው የሃይል መቆራረጥ ወፍጮአቸው ለተደጋጋሚ ብልሽት ይዳረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

በዚህም ምክንያት ከወፍጮው ቋት ውስጥ የገባ እህል እስከ ሁለት ቀን ከዚያው ይቆይ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

አሁን የተደረገው የሃይል ማስፋፊያ ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን በመጠገን የሚተዳደሩት አቶ ባየው ዓለሙ በበኩላቸው ያለማቋረጥ በሚከሰት የሃይል መቆራረጥ በርካታ ቴሌቪዥንና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እየተበላሹ ለጥገና ወደ እርሳቸው እንደሚመጡ ገልፀዋል።

መብራት ሃይል የህብረተሰቡን ተደጋጋሚ ቅሬታ አይቶ ያደረገው የሃይል ማስፋፊያ ችግሩን ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አስተያየት ሰጭው ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አድዋ የካቲት 23/2010 የዓድዋን ድል መልካም እሴቶች ለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች መጠቀም እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ አሳሰቡ።

122ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የከተማው ነዋሪዎች በተገኙበት አድዋ ላይ በድምቀት ተከብሯል።

መታሰቢያ በዓሉ ''የአድዋ ድል የአብሮነትና የአሸናፊነት ተምሳሌት'' በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተከበረው።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ድሉ ለኢትዮጵያዊያን የሉዓላዊነት መገለጫ፣ ለአፍሪካዊያንም የነጻነት ትግል ድፍረትና ቁርጠኝነትን ያስተማረ እንዲሁም ለመላው ጥቁር ህዝብ የብሄርተኝነት ቅስቀሳ ያገለገለ ታልቅ ድል ነው።

"ከመላው የአገሪቷ አካባቢዎች ወደ አድዋ የዘመቱ ቅደመ አያቶቻችን በመካከላቸው የነበረውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው ለአገራቸው አንድነት ዘብ ቆመዋል" ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

"የአገር ጉዳይ ከእያንዳንዱ ግለሰብ ፍላጎት በላይ ነው" ያሉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፤ በጦርነቱ የታየውን መልካም እሴት በመያዝ ለአገር ሠላምና መረጋጋት መስራት ይገባል ሲሉም ነው አጽንኦት የሰጡት።

የአገሪቷን ሠላምና መረጋጋት የሁላችንም ኃላፊነት በማድረግ ለአገር ጉዳይ በጋራ መቆም እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የአድዋ ድል እሴቶችን በአርዓያነት በመውሰድ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍና አገር ለማስከበር ቃል የምንገባበት በዓል መሆኑንም አውስተዋል።

"አገር የምትቀጥለው ሠላም ሲኖር ነው" ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችም በአድዋ ድል የነበሩ መልካም እሴቶችን እንደ ተሞክሮ መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ወጣቱ ትውልድ አባቶች ያስተላለፉትን አገር በመጠበቅና ለአገሪቷ ሠላምና መረጋጋት በመስራት የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ማስቀጠል ይኖርባቸዋልም ብለዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም በበኩላቸው "ታላቁን የዓድዋ ድል በመዘከር፣ ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላፍና ለአፍሪካዊያን መዳረሻ በማድረግ ለገቢ ምንጭነትና ለአገር ገጽታ ግንባታ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

ድሉ የተገኘበትን ታሪካዊ ሥፍራ ለማልማትና የምርምር ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ ፕሮጀክቶች መቀረጻቸውን ገልጸው፤ ለፕሮጀክቶቹ እውን መሆን ሁሉም ዜጋ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ሚኒስትሯ።

የትግራይ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት የዓድዋን ተራሮች ለማልማትና የድሉን ታሪክ ለመዘከር ለሚሰሩ ማናቸውም ፕሮጀክቶች ክልሉ ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 23/2010 ትውልዱ የአድዋን ድል ተምሳሌት በማድረግ ለአገር ዕድገትና ልማት በመትጋት ድህነትን ማሸነፍ እንደሚጠበቅበት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።

122ኛው የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይና አዋሬ አካባቢ በሚገኘው የአድዋ ድልድይ በድምቀት ተከብሯል።

ኢዜአ በበዓሉ አከባበር ላይ የታደሙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባል ሻምበል ሰለሞን ባንታዬሙሉ "የአሁኑ ትውልድ የአድዋን ድል ተምሳሌት በማድረግ ድህነትን በጋራ ለማሸነፍ መሥራት ይገባዋል" ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት መንፈስ ለአገሩ ጠንክሮ በመሥራት ራሱንም አገሩንም ማልማት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

ወጣት ወርቅአገኘሁ ዘውዱ አድዋ ላይ የተመዘገበው ድል ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከሰሩ አገራቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑን ጠቁሟል።

የአሁኑ ትውልድም የአባቶቹን የአንድነት መንፈስ በመውረስና ልዩነቶቹን ወደ ጎን በመተው ለአንድ አገር ዕድገት ማሰብ እንደሚገባውም ወጣቱ ገልጿል።

የበዓሉ ታዳሚ የነበረው ኮሜዲያን አሰፋ ተገኝ በበኩሉ ወጣቱ በአድዋ ድል የታየውን የአንድነት መንፈስ ለአገሩ ልማት በጋራ በመረባረብ መድገም አለበት ባይ ነው።

በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ሚስ ቪልማ ቶማስ እንደገለጹት የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን የአንድነት መንፈስ በመላበስ ጠላትን ያሸነፋበት እንደሆነና ይህ የድል መንፈስ አገሪቷ በቀጣይ ድህነትን በማሸነፍና ልማት እንዲመጣ ለማድረግ ለምታደርገው ጥረት ብርታት ሊሆን ይገባል።

122ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን ''አድዋ የአብሮነትና የአሸናፊነት ተምሳሌት'' በሚል መሪ ሃሳብ እየተከበረ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዳማ የካቲት 23/2010 የሰላም እሴቶች በመጠቀም የሀገር አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ከመንግስት ጋር በመሆን እንደሚሰሩ የኃይማኖት መሪዎች ገለጸ።

ከአሮሚያ ክልል የተወጣጡ የኃይማኖቶች መሪዎችና የፀጥታ ዘርፍ አካላት የተሳተፉበት የሰላም እሴት ግንባታ መድረክ በአዳማ ከተማ አባገዳ አደራሽ ተካሄዷዋል።

በመድረኩ ከተሳተፉት መካከል የአምቦ ከተማ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ  ቄሲስ ደረጀ ፀጋዬ "መንግስትና የኃይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ ነበራዊ ሁኔታ ላይ ተግባብተን የሰላምና የልማቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሁላችንም መሆን አለበት" ብለዋል።

መንግስትና የእምነት ተቋማት ተቀናጅተው የወጣቶች፣ሴቶችና የሌሎችንም የህዝብ አደረጃጀቶች ላይ በትብብር መስራት እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

ለዘመናት የዘለቀው የሀገሪቱ ህዝቦችና ኃይማኖቶች የአብሮነት፣መቻቻልና መከባበር ባህል ለሰላምና ለልማት ቀጣይነት አስፈላጊ በመሆኑ ከመንግስት ጋር በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በአዳማ የተዘጋጀው መድረክ የኃይማኖት መሪዎች በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩና የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ለማስቻል መሆኑን የገለፁት ደግሞ በአርሲ ዞን የሽርካ ወረዳ የኃይማኖት መሪ ሼህ ዳዊድ ሙሐመድ ናቸው።

ዘመን ተሻጋሪ የኃይማኖቶችና የህዝቦች የመቻቻል እሴት አሁን በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች የመፍትሄው አንዱ አካል በማድረግ የወጣቶች ጥያቄ ከስሜት በፀዳ መልኩ  በአግባቡ ምላሽ እንዲያገኝ የሚደግፉ መናቸውን ገልጸዋል።

ሀገሪቱ  ወደ ነበረችበት ሰላም እንዲትመለስ የኃይማኖት መሪዎች፣የሀገር ሽማግሌዎችና መንግስት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ምክትል ጠቅላይ ፀሐፊ አቶ ሁሉፍ ወልደስላሴ በበኩላቸው የኃይማኖት መሪዎችና የመንግስት አካላት  የሰላም እሴቶችን በመጠቀም ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በሚቻልበት ላይ ለመምከር መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

"ኃይማኖት ነክ የሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር ፣የወጣቶች የዴሞክራሲ፣የልማትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በየደረጃው የሚገኙ የኃይማኖት ተቋማት ባሳተፈ መልኩ ከመንግስት ጋር በቅንጅት ተረባርበን ለመፍታት ጭምር ነው" ብለዋል።

"የኦሮሞ ህዝብ ለሌሎች ምሳሌ የሆነ የእርቅና የሰላም እሴት አለው" ያሉት አቶ ሁሉፍ ይህን እሴት በመጠቀም አሁን ሀገሪቱ ካጋጠማት ችግር ለመውጣት ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት  ጉዳዮች ሚኒስቴር የኃይማኖትና የእምነት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ጌታዋ ዳስታ እንዳመለከቱት በሀገሪቱ  ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ የባህል፤ የኃይማኖት መቻቻልና የአብሮነት እሴትን ማዳበር ይገባል።

የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ መንግስትና የኃይማኖት መሪዎች ቅድሚያ ለሰላም ሰጥተው  በጋራ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መድረኩ መመቻቸቱን ገልጸዋል።

ችግሮቹን ለመፍታት ከኃይማኖት መሪዎች ጋር አብሮ ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱን የተናገሩት ዳይሬክተር ጀነራሉ "የውይይት መድረኩ  እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ ይወርዳል "ብለዋል።

ለሶስት ቀናት የቆየውና ዛሬ በተጠናቀቀው መድረክ በአሮሚያ ክልል ከሚገኙ ወረዳዎች የተወጣጡ ከ400 በላይ የተለያዩ ኃይማኖቶች መሪዎችና የፀጥታ ዘርፍ አካላት ተሳትፈዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን