አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 14 March 2018

ጋምቤላ መጋቢት 5/2010 በጋምቤላ ክልል ለማህፀን በር ካንሳር አጋላጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑ ተጠቆመ።

ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀንን በማስመልከት በማህፀን በርና በጡት ካንሰር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ተሳታፊዎች ለኢዜአ በሰጡት አስታያየት በክልሉ ለማህጸን በር ካንሰር አጋላጭ የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ቢኖሩም በሽታውን ለመከላከል የተሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው።

የቅድመ ካንሰር የምርመራ አገልግሎትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ዝቅተኛ መሆን ለእዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ኛቦር ባንዳክ በሰጡት አስተያት ከብዙ ወንዶች ጋር ወሲብ መፈጸም፣ ያለድሜ ጋብቻ ፣ ትንቦሆ ማጨስና ሌሎችም ምክንያቶች ለማሕፀን በር ካንሰር እንደሚያጋልጡ በመድረኩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በክልሉ የሚፈፀሙ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ የውርስ ጋብቻና ሌሎች ጎጂ ልማደዊ ድርጊቶች ለማህጸን በር ካንሰር አጋላጭ ተብለው ከተጠቀሱ ችግሮች መካከል ስለሆኑ ተገቢ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ይሁንና በሽታውን ለመከላከል እየተሰጠ ያለው የማህጸን በር ካንሳር ምርመራና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በሚፈለገው መጠን እየተከናወኑ አለመሆኑን ተናግረዋል።

" ለማህጸን በር ካንሰር መንስኤዎች ናቸው ተብለው የተጠቀሱት አጋላጭ ሁኔታዋች በሕብረተሰቡ የሚፈጸሙ በመሆናቸው የመከላከሉ ሥራ በተወሰነ አካል ብቻ ውጤታማ ሊሆን አይችልም " ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ  አቶ ነብዩ ማሞ ናቸው።

በሽታውን ለመከላከል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመው ፣ በተለይም የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የቅድመ ካንሰር ምርመራ አገልሎትን ተደራሽ በማድረግ በኩል ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በጋምቤላ ሆስፒታል የተቋረጠው የቅድመ የማህጸን በር ካንሳር ምርመራ አገልግሎት በፍጥነት ሊጀምር እንደሚገባም አቶ ነብዩ ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ሆስፒታል የአዋላጅ ነርስ ባለሙያ አቶ ኦማን ኦኬሎ በሰጡት አስተያየት ለተወሰኑ ወራት በሆስፒታሉ ተጀምሮ በነበረው የቅድመ ማህጸን በር ካንሳር ምርምር ከተጠቀሙ ሴቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ለችግሩ የተጋለጡ እንደነበሩ ጠቁመዋል።

በመሆኑም በክልሉ ካሉት አጋለጭ ሁኔታዎች አኳያ በሽታውን የመከላከሉ ሥራ ተገቢ ትኩረት እንደሚያስፈልገው ነው ባለሙያው የገለጹት።

የጋምቤላ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቻንኮት ቶክ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ይሰጥ የነበረው የቅድመ ማህጸን በር ካንሰር ምርመራ አገልግሎት በመሳሪያ ብልሽት ምክንያት መቋረጡን ገልጸዋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ሆስፒታሉ የተባለሸውን የመመርመሪያ መሳሪያ በማስጠገን አገልገሎቱን በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለማስጀመር ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጀምስ ቦል በበኩላቸው ከእዚህ ቀደም በክልሉ የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል ምርመራውን ተደራሽ በማድረግም ሆነ ግንዛቤን በማሳደግ በኩል ብዙም የተጠናከረ ሥራ አለመሰራቱን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በጋምቤላ ሆስፒታልና በኢታንግ ጤና ጣቢያ ብቻ ተወስኖ የነበረውን የቅድመ ምርመራ አገልግሎት ወደ ሌሎች የገጠር ሆስፒታሎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

Published in ማህበራዊ

መጋቢት 5/2010 የጀርመን ፓርላማ አንጌላ ሜሪከል ለአራተኛ ጊዜ የሀገሪቱ መራሂተ መንግስት እንዲሆኑ መረጠ።

ሜሪከል ከሀገሪቱ የወግ አጥባቂና የግራ ዘመም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ጥምር መንግስት መመስረታቸው ይታወሳል።

የጀርመን ፓርላማ ዛሬ ባካሄደው ምርጫ ሜሪከል 364 ድጋፍ፣ 315 ተቃውሞና ዘጠኝ ድምፀ ተዓቅቦ በማስተናገድ ነው በድጋሚ በመራሂተ መንግስትነት የተመረጡት።

ሜሪከል በድጋሚ መራሂተ መንግስት ሆነው ለመመረጥ በትንሹ 355 የፓርላማ አባላትን  ድምፅ ማግኘት ይጠበቅባቸው ነበር።

ዛሬ በተደረገው የፓርላማ ምርጫ  ሜሪከል ያገኙት ድምፅ እሳቸው የሚመሩት የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን እና ተጣማሪው ሶሺያል ዴሞክራቲክ ፓርቲዎች በርካታ አባላት ድጋፍ እንዳልሰጧቸው ያሳያል ነው የተባለው።

ጥምር ፓርቲዎች በጀርመን ፓርላማ ቡንደስታግ በድምሩ 399 ወንበር አላቸው።

ባለፈው ወር የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን እና ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ አመራሮች የጥምር ፓርቲ መንግስት ለመመስረት መስማማታቸው ይታወሳል።

የሜሪከል ፓርቲ በመስከረም ወር በተካሄደው የጀርመን የፓርላማ ተወካዮች ምርጫ ከአጠቃላይ 709 መቀመጫዎች ውስጥ ያገኘው 246 ብቻ ሲሆን የሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ደግሞ 153 ወንበሮችን አሸንፏል።

 

ምንጭ፦አናዶሉ

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2010 በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ሰርቶ በመለወጥ ህልማቸው ላይ  ስጋት መደቀኑን አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ ሴቶች ገለጹ፡፡

ወጣት ማንአለኝ አስማማው በቡራዩ ከተማ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች ማምረት ተደራጅታ ሥራ ከጀመረች አራት ዓመታትን አስቆጥራለች።

"በስራዬ ተግቼ ትልቅ የመሆን ህልም አለኝ" የምትለው ወጣቷ አሁን በአገሪቷ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ህልሟ እውን እንዳይሆን ሊያደርግ እንደሚችል ስጋት አሳድሮባታል።

ያለውን መልካም አጋጣሚና ሰላም ተጠቅማ  ከሦስት መሰሎቿ ጋር ተደራጅታ ከ15 ሺህ ብር ካፒታል በመነሳት በመቶ ሺህ የሚቆጠር ኃብት ማካበቷን ገልጻለች።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቷ እየተከሰተ ባለው አለመረጋጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው ምርቶቻቸውን መሸጥ እንዳልቻሉ ነው የተናገረችው፡፡

ወጣት ማንአለኝ በተለይም በሰሞኑ ግርግር ምክንያት ምርቶቿን መሸጥ እንዳልቻለች ገልጻ "በሠላም እጦት በይበልጥ ተጎጂዎች እኛ ሴቶች በመሆናችን ሠላማችንን ልንጠብቅ ይገባናል" ብላለች።

የአዲስ አበባዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ትዕግስት ደረሰም "በተፈጠሩ አሰራሮችና ሴቶችን በሚያበረታቱ ዕቅዶች ቀዳሚ ተጠቃሚ ሆነናል" ይላሉ።

በዚህም ከራሳችን አልፈን ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠር "ከማጀት ወደ አደባባይ የሚወጡ እንስቶችን የማብዛት ራዕይ ሰንቀናል" የሚሉት ወይዘሮዋ በአገሪቷ የሚስተዋለው አለመረጋጋት ህልማቸውን እንዳያጨልመው መስጋታቸውን አልሸሸጉም።

ሰላም ወዳድ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላሙን ለማደፍረስ ለሚጥሩ ኃይሎች በር መክፈት እንደሌለበት የተናገሩት ደግሞ ወጣት መሰለች ገብረጻዲቅና ወይዘሮ ልዩነሽ መገርሳ ናቸው።

በሰላም መጥፋትና በሁከት የመጀመሪያዎቹ ተጎጂዎች ሮጠው የማያመልጡ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን አቅም መገንባትና የሙያ ማኅበር ማቋቋም እንደሚያስፈልግ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተናገሩ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው የባለሙያው ቁርጠኝነት ማነስ እንጂ በሙያዊ አቅም ግንባታ ዘርፍ ሰፊ የክህሎት ክፍተት የለም ብለዋል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው የክልሎችና የፌዴራል ተቋማት የህዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኃላፊዎች እንዲሁም የባለድርሻ አካላት የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ፎረም ዛሬም ቀጥሏል።

በትናንትናው መድረክ ከተሰነዘሩ ሃሳቦች መካከል በኮሙኒኬሽን ባለሙያው ሙያዊ ክፍተት መኖሩ "በአገር ገጽታ ግንባታ፣ በወቅታዊ ጉዳዮችም ሆነ በጋራ መግባባት ዙሪያ የመረጃ መለዋወጥና ማሰራጨት ሂደቱ ሰፊ ክፍተትና መደናገር ፈጥሯል" የሚለው ይገኝበታል።

የቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ግርማ "የአገር ገጽታን ለመገንባትና አገሪቷ ያሏትን ሀብቶች ለማስተዋወቅ የባለሙያው ዕውቀትና ክህሎት ክፍተት አለ" ይላሉ።

ክፍተቱን ለመድፈን በዓለም አቀፍ የሕዝብ ግንኙነት ኤጀንሲና በተግባቦትና ጋዜጠኝነት ትምህርት ዘርፍ ብቻ ትኩረት ያደረጉ ተቋማት እንደሚያስፈልጉ ነው የገለጹት።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጤና ኮሙኒኬሽንና ጤና ትምህርት ዳይሬክተር አቶ አህመድ ኢማኖም የአቶ ስንታየሁን ሃሳብ ይጋራሉ።

አሁን ላይ አገሪቷ የደረሰችበትን ዕድገትና ፍላጎት የሚመጥን የመረጃ ተደራሽነት ለመፍጠር የተግባቦት ባለሙያዎች ማኅበርና አማካሪ ተቋማት እንደሚያስፈልጉም ይገልጻሉ።

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ደግሞ የባለሙያዎችን አቅም ለመገንባትና በአገር ውስጥ የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና  ለገጽታ ግንባታ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ እንዲያደርሱ ለሚዲያና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ተደጋጋሚ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ይናገራሉ።

የተሻለ የኮሙኒኬሽን ስራ ለመስራት ባለሙያዎችን በክህሎትና ዕውቀት ማጎልበት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ከአጫጭር ስልጠናዎች ባሻገር በ2ኛና 3ኛ ዲግሪ በአገር ውስጥና በውጪ ትምህርት እንዲከታተሉ በማድረግ የክህሎት ክፍተቱን ለመሙላት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ ከ50 በላይ ባሙያዎች በህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ኮሙኒኬሽን ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መግባታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

ስለሆነም በዘርፉ ለሚስተዋለው የመረጃ ፍሰት ችግር ምክንያቱ ባለሙያው ባለው ዕውቀትና ክህሎት ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ ለማድረስ ቁርጠኝነት ማጣት ነው ባይ ናቸው።

የኮሙኒኬሽን ባለሙያው ክህሎቱን ተጠቅሞ በተግባር ምን ያህል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባም ነው የገለጹት።

ሚኒስትሩ የባለሙያዎች ማኅበርና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ተቋም ስለማቋቋም የተነሳውን ሃሳብ እንደሚደግፉትም ገልጸዋል።

ነገር ግን በቅድሚያ አሁን ያለውን አገራዊ ስኬት ለዓለም ህብረተሰብ ለማስተዋወቅ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን በመጠቀም በተገቢው ሁኔታ ተናቦ መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል በመረጃ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ ቀውስ መፍጠሩ በሚነገርለት ማህበራዊ ሚዲያ በቂ ክህሎትና ስልጠና እንደሚያስፈልግ አቶ ስንታየሁ ግርማና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ መኮንን ኃይሉ ይናገራሉ።

ለዚህም ዶክተር ነገሪ ስለ ማህበራዊ ሚዲያው የሚነሱ ጉዳዮች "የባለሙያው ድክመት እንጂ የዕውቀትና ክህሎት ክፍተት አይደለም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ መጋቢት 5/2010 በያሉበት አካባቢ ሰላማዊ ኑሮን ለማስቀጠል በሚደረገው  ጥረት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አስተያየታቸውን የሰጡ ሴቶች ገለጹ፡፡

በክልሉ ከፋ ዞን የቦንጋ ከተማ ነዋሪ  ወይዘሮ አስማረች ሀይሌ ለኢዜአ  እንዳሉት በቅርቡ በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች ተከስቶ በነበረው ሁከት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በመግታት በዕለት ተለት እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮባቸው ነበር።

በተለይ ለስራ ጉዳይ ወደ ሀዋሳ በተጓዙበት ወቅት መንገድ በመዘጋቱ በግንባታ ላይ በሚገኘው የቦንጋ ጭዳ መንገድ ፈታኝና አድካሚ የሆነ ጉዞ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

"ለሀገር ሰላም፣ ለልማትና ቤተሰብ ለማስተዳደር ሴቶች ወሳኝ ሚና አላቸው "ያሉት ወይዘሮ አስማረች  ችግር ሲፈጠርም በቅድሚያ ተጠቂ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ለሀገር ሰላምና የህዝቦችን ደህንነት ለማስጠበቅ ለወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊነት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

በሸካ ዞን ማሻ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ካህኔ ገመዳ በበኩላቸው ችግር በሚኖርበት ጊዜ ተጎጂዎቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ሰላማዊ ኑሮን ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንደሚወጡ አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም በአካባቢያቸው አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በግላቸው ከሚያደርጉት አስተዋጽኦ በተጨማሪ በልማት ቡድናቸው የጸጥታና የሰላምን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚወያዩ ጠቁመዋል፡፡

’’የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መውጣት  በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ የፀጥታ  ችግሮች እንዲቆሙ አድርጓል፤ ህብረተሰቡም ያለስጋት የእለት ተእለት ስራውን እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል’’ ብለዋል፡፡

የጂንካ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ተማሪ በእምነት ኢሳያስ በበኩሏ ሰላም ከሌለ ህጻናት በመልካም ስነምግባር ታንጸውና ተገቢውን እንክብካቤ አግኝተው ማደግ አይችሉም ብላለች።

ሰላም ትልቅ ዋጋ አለው ያለችው ተማሪ በእምነት በተለይ ህጻናት ስለሚረከቧት ሀገር ጥሩ አመለካከት ከሌላቸው በስነ ልቦናቸው ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ተናግራለች፡፡

እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባትና በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን መንግስትም ሆነ ህብረተሰቡ የየራሳቸውን ስራ ሊሰሩ ይገባል ብላለች፡፡

በጋሞጎፋ ዞን ጎፋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑትና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ወይዘሮ ሮማን ጋሻው በአካባቢያቸው ሁከት እንዳይነሳ በሴቶች ልማት ቡድን ስር በሰላም ዙሪያ በማወያየት እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ መንግስት ችግሩን ለማስወገድ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት እንዳገዘ ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደሴ መጋቢት 5/2010 በደሴ ከተማ ከህግ አግባብ ውጭ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ የግል የጤና ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ፡፡

 በከተማ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ የጤናና ጤና ነክ ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ሙስጠፋ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት በጤና ተቋማቱ ላይ እርምጃ የተወሰደው ከትክክለኛ ተቋማት መድኃኒት መግዛታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ያላቀረቡ፣  የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት ሲሸጡ የተገኙ ናቸው፡፡

 በህገ ወጥ ተግባር ተሰማርተው በተገኙ  ሰባት የመድኃኒት መደብርና የመድኃኒት ቤቶች እንዲሁም አንድ መካከለኛ ክልኒክም ከመጋቢት 2/2010 ዓ.ም.  ጀምሮ መታሻጋቸውን አስታውቀዋል።

 "በመመሪያው መሰረት ባለሙያዎቹ  እስከ ሁለት ዓመት ድረስ በሙያቸው እንዳይሰሩ የታሸጉት የጤና ተቋማት ደግሞ ምንም ዓይነት የህክምና አገልግሎት እንዳይሰጡ ይደረጋል" ብለዋል።

 ጊዜያቸው ያለፈበቸው መድኃኒቶች በአስወጋጅ ኮሚቴ እንደሚወገዱ ያመለከቱት አስተባባሪው  በታሸጉት መድኃኒት ቤቶች ያሉት ህጋዊ መድኃኒቶች ለሌሎች የጤና ተቋማት እንደሚከፋፈልም ጠቁመዋል፡፡

 የከተማው አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስቻለው ተሾመ በበኩላቸው በደሴ ለሸማቾች ሊሰራጩ የነበሩ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የፈሳሽና ደረቅ ምግቦች እንዲሁም የመዋቢያ ምርቶች መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡

 ከክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ከተውጣጣ ቡድን ጋር በመሆን ለአንድ ሳምንት ባደረጉት የቁጥጥር ስራ 289 ሊትር የተበላሹና የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ለስላሳ መጠጦች፣ጭማቂ ፣ወተት፣ እርጎ እንዲሁም 323 ኪሎ ግራም ብስኩትና ቼኮሌት መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

 በህገ ወጥ ድርጊቱ ተሰማርተው በተገኙ አስር ነጋዴዎች ላይም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እና የንግድ ቤቶቻቸውን እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

 "ኅብረተሰቡም ፈሳሽና ደረቅ ምግቦችን ሲገዛ የተመረቱበትንና የአገልግሎት ጊዜያቸው የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ማየትና ጥንቃቄ ማድረግ  እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

 ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች የሚሸጡ ግለሰቦችንም በመጠቆም  እንዲተባበርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 በደሴ ዙሪያ ወረዳ  የቦሩ ሜዳ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ኪዳኔ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ምግቦችና መጠጦች በተለይ በህጻናትና በሌሎች ህመሞች ህክምና በሚወስዱ ሰዎች ላይ ከከባድ የጤና ችግር  ሊያስከትል  እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡

 የመዋቢያ ምርቶችም ጊዜያቸው ካለፈ በቆዳ፣ በፀጉርና በአጥንት ላይ የከፋ ጉዳት ስለሚያደርሱ ሸማቹ ህብረተሰብ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 5/2010 የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ከኡጋንዳው ኬሲሲኤ ጋር ላለበት የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመልስ ጨዋታ ነገ ወደ ካምፓላ ያቀናል።

 በተመሳሳይ ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ከግብጹ ዛማሌክ ጋር የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ነገ ወደ ካይሮ እንደሚያቀና ታውቋል።

 ቅዱስ ጊዮርጊስና ኬሲሲኤ የፊታችን ቅዳሜ በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ ስታር ታይምስ ስታዲየም ከቀኑ አስር ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

 የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ምኒሊክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት ቡድኑ 19 ተጫዋቾችንና ስምንት የልዑካን ቡድን አባላትን ይዞ ወደ ካምፓላ ያቀናል።

 ከልዑካኑ ጋር 30  ደጋፊዎችም ወደ ስፍራው እንደሚጓዙም ጠቁመዋል።

 የክለቡ ተጫዋቾች ከጨዋታው በፊት በተጋጣሚው ቡድን ሜዳ ልምምድ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

 ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ለመልሱ ጨዋታ ተጫዋቾቹ ልምምድ ሲያደርጉ እንደቆዩ አቶ ምኒሊክ አስረድተዋል።

 ተጫዋቾቹ በአዲስ አበባ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ዛሬ ማለዳ ሲያከናውኑ ተጨዋቾቹ በሙሉ በተሳካ ሁኔታ ልምምድ መጨረሳቸውን ገልጸዋል።

 የፊታችን እሁድ ለህክምና ወደ ጀርመን የሚያቀናው ሳላሃዲን ሰኢድ፣ እንዲሁም የመሐል ክፍል ተጫዋቹ ናትናኤል ዘለቀ ከጉዳት በኋላ ልምምድ እየሰራ ቢሆንም ለጨዋታ ዝግጁ ባለመሆኑ ወደ ካምፓላ አያቀኑም።

 አጥቂው አሜ መሐመድ ጉዳት ላይ በሚገኘው ሳላሃዲን ሰኢድ እንደተካ ጠቁመዋል።

 ተጫዋቾቹ የማሸነፍ ስነልቦና እንደያዙና ጨዋታውን አሸንፈን ወደ ምድብ ድልድል መግባት የሚያስችል ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

 ከሳምንት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ የተጠናቀቀ ሲሆን በአጠቃላይ በደርሶ መልስ የሚያሸንፈው ቡድን ወደ ምድብ ድልድሉ ይገባል።

 በተመሳሳይ ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ከግብጹ ዛማሌክ ጋር የመልስ ጨዋታውን ለማድረግ ነገ ማታ 21 ተጫዋቾችና ሌሎች ልዑካንን ይዞ ወደ ካይሮ እንደሚያቀና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ወሲሶ ገልጸዋል።

 ጨዋታው የፊታችን እሁድ ከቀኑ አስር ሰአት ላይ ይደረጋል።

 የክለቡ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ከተወሰኑ ተጫዋቾች ቀለል ያለ ህመም በስተቀር ሁሉም ተጫዋቾች በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

 ከሶስት ቀናት በፊት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወላይታ ድቻ ከወልዲያ ጋር ጨዋታውን ባደረገበት ወቅት በዛብህ መለዮና ሃይማኖት ወርቁ ጉዳት ያጋጠማቸው ሲሆን ጉዳቱ ቀለል ያለ በመሆኑ ጨዋታውን ማድረግ እንደሚችሉ የክለቡ የህክምና ባለሙያዎች ወስነዋል።

 ቶጎዋዊው አጥቂ ጃኮ አራፋትና እሸቱ መና መጠነኛ የሆድ ህመም እንዲሁም ያሬድ ዳዊት የወባ ህመም ምልክት የታየበት ሲሆን የህክምና ባለሙያዎች ድጋፍ በማድረጋቸው ተጫዋቾቹ በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ። 

 ተጫዋቾቹ ለመልስ ጨዋታው ዝግጅት ይረዳቸው ዘንድ በሶዶ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርጉ እንደቆዩና በጠንካራ የማሸነፍ ስነልቦና ላይ እንደሚገኙ ነው አሰልጣኝ ዘነበ የተናገረው።

 በመጀመሪያው ጨዋታ የተጋጣሚው ቡድን ዛማሌክ ከክንፍ የሚሻገሩ ኳሶችን በመጠቀም ጎል ለማስቆጠር ሲያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ በመግታት ማሸነፋቸውን ገልጸው በመልሱ ጨዋታ ይህንኑ በመድገም ውጤት ይዘው ለመውጣት እንደሚሞክሩ ተናግረዋል።

 "ተጫዋቾቼ ዛማሌክን አሸንፈን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ እንችላለን የሚል ከፍተኛ ሞራል አላቸው" ብለዋል።

 ቡድኑ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉን ያስታወሱት አሰልጣኝ ዘነበ ተጫዋቾቹ እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎች ጥሩ ተሞክሮና ልምድ እንዳገኙ አስረድተዋል።

 ከሳምንት በፊት ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ በወላይታ ድቻ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት የተጠናቀቀ መሆኑ ይታወሳል።

Published in ስፖርት

መቱ መጋቢት 5/2010 በየመስኩ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ሊረጋገጥ የቻለው ሰላም በመስፈኑ በመሆኑ ለሰላማቸው ዛሬም ትኩረት እንደሚሰጡ በመቱ ከተማ ሴት ሠራተኞች ገለጹ፡፡  

አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሴቶች እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸው ሊረጋግጥ የቻለው በሀገሪቱ በሰፈነው ሰላም ነው።

አስተማማኝ ሰላም መኖሩ በህገ መንግስቱ በተረጋገጡላቸው መብቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የመቱ ከተማ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሳሊያ ሙዘሚል እንዳሉት ባለፉት 26 ዓመታት ሴቶች ከወንዶች እኩል በሀገሪቱ ልማት ላይ ተሳታፊ በመሆን የድርሻቸውን ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

በሀገሪቱ የተጀመረው ፈጣን ልማት መጠናከር ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ስለሚያደርግ በአካባቢያቸው ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በሰላም እጦት በዋናነት የሚጎዱት ሴቶችና ሕጻናት በመሆናቸው ለአስተማማኝ ሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩም አስገንዝበዋል።   

"ሴቶች ከወንዶች እኩል የመሬት ባለቤት እንዲሆኑና በሥራ ዕድል ፈጠራ ተሰማርተው ራሳቸውን መለወጥ የቻሉት በነበረው አስተማማኝ ሰላም ነው" ያሉት ደግሞ የኢሉአባቦር ዞን አስተዳደር ሠራተኛ ወይዘሮ ምንታምር ሸጋው ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ ሰላምና ልማት ቀጣይነት ባለው መልኩ መረጋገጡ በትምህርት ቤቶች የሴት ተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምርና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ ማድረጉንም አመልክተዋል።

" ህገ መንግስቱ ለሴቶች የሰጠውን መብት በመጠቀም በትምህርትና ስልጠና ራሴን በማብቃት እስከ አመራር ደረጃ ደርሻለሁ " ያሉት ወይዘሮ ምንታምር፣ እንደእርሳቸው ሌሎችም ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለሰላም ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ሴቶች ፌዴሬሽን ኃላፊ ወይዘሮ ጽጌ ረጋሳ በበኩላቸው፣ ሴቶች በፖለቲካው መስክ ወደ አመራር ቦታ በመምጣት ከወንዶች እኩል የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ጽጌ እንዳሉት፣ አስተማማኝ ሰላሙ ሴቶች በተጎናጸፉት ህገ መንግስታዊ መብት ተጠቅመው የመሬት ባለቤትነታቸውን እንዲያረጋግጡና ከወንዶች እኩል ለግብርናው ልማት ዕድገት የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ አስችሏል።

"ህገመንግስቱ ባጎናጸፈኝ መብት በመጠቀም ያለ ምንም ተጽዕኖና ጫና በማንኛውም ሥራ ላይ ከወንዶች እኩል የበኩሌን እየተወጣሁ ነው” ያሉት ወይዘሮ ጽጌ፣ ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

Published in ፖለቲካ

ሐረር መጋቢት 5/2010 የድሬ ብድርና ቁጠባ ተቋም ያመቻቸላቸውን የገንዘብና የተሽከርካሪ ብድር አገልግሎት እራሳቸውን ለመቻል እንደረዳቸው በሐረር ከተማ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ገለጹ፡፡

ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መካከል በከተማው የቀበሌ 17 ነዋሪ ወጣት ስሜነህ ተፈራ  እንደገለጸው  ተቋሙ  ባመቻቸው የብድርና የቁጠባ አገልግሎት በመጠቀም ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ባለቤት መሆን ችሏል፡፡

የተሸክርካሪው ባለቤት መሆን  የቻለው 40 በመቶ በመቆጠብና  ቀሪውን ገንዘብ በሶስት  ዓመት ውስጥ ከፍሎ በማጠናቀቅ ነው፡፡

" ተጨማሪ ሌላ ብድር ወስጄም በንግድ ስራ ተሰማርቻለሁ፣ ተሽከርካሪዋንም ሌላ ሰው እንዲሰራበት  በመቅጠር የስራ ዕድል ፈጥሬያለሁ፤ በዚህም ራሴን ችያለሁ፤ ቤተሰቤንም እየረዳሁ እገኛለሁ"ብሏል፡፡

ተቋሙም ከሌሎች የብድርና ቁጠባ ተቋም ለየት የሚያደርገው አማራጮችን በማቅረብ ወጣቱ በፈለገበት እንዲሰማራ ማድረጉ እንደሆነ የተናገረው ወጣቱ " ይህም በሁሉም አካባቢ  ቢዘወተር ለወጣቱ የስራ መነሳሳትን ይፈጥራል"  ሲል ገልጿል።

የሸንኮር ወረዳ ነዋሪ አቶ ዱላ ማኖቼ በበኩላቸው 30 ሺህ ብር በመቆጠብ ከተቋሙ 150 ሺህ ብር በብድር   ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 10 ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ የገላ መታጠቢያ አስገንብተው ለአገልግሎት በማብቃት ገቢ እያገኙበት ነው፡፡

" በአሁኑ ወቅትም 125 ሺህ ብር መመለስ ችያለው ፤ ከሶስት ወር በኋላም ሙሉ ለሙሉ ብድሬን አጠናቅቃለሁ፤ ልጅም እያስተማርኩበት በመሆኑ ተጠቃሚ አድርጎኛል"ብለዋል።

በተቋሙ የሐረር የቅርንጫፍ  ስራ አስኪያጅ አቶ ከዲር መሀመድ ተቋሙ በአካባቢው ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ  1 ሺህ 288 ነዋሪዎች ከ36 ሚሊዮን  800 ሺህ ብር በላይ የገንዘብና የተሽከርካሪ የብድር አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱን ካገኙት መካከል 105 ባለሶስት እግርና የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ተሽከርካሪዎች  በብድር የወሰዱ ናቸው፡፡

አቶ ከዲር እንዳመለከቱት ከመካከላቸውም  34ቱ የመክፈያ ውላቸው ሳይደርስ በአንድ ዓመት ውስጥ ብድራቸውን በመመለስ ንብረቱን የግላቸው ማድረግ ችለዋል።

ተቋሙ በተጨማሪም በወለድና ከወለድ ነፃም የብድር አገልግሎት በመስጠት ሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ላልተወሰነ ጊዜ በሐረሪ ክልል ትራንስፖርት ባለስልጣን የታገደው የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ሰሌዳ በስራቸው ላይ እንቅፋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ችግሩ እየተፈታ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ መጋቢት 5/2010 በሀገሪቱ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ሴቶችን በዘላቂነት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ማረጋገጥ እንደሚገባ አስተያየታቸውን የሰጡ የመቀሌ ከተማ ሴቶች ገለጹ።

አዲሱ ትውልድ ለሰላም መጠናከር ዘብ እንዲቆም የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑም ተመልክቷል።

በየዓመቱ የሚከበረውን የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ ሴቶች እንዳሉት፣ በሰላምና ሰላም በሚታጣበት ወቅት ይበልጥ ተጠቃሚና ተጎጂ ሴቶች ራሳቸው ናቸው።  

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በመቀሌ ከተማ የሚኖሩት ታጋይ ወርቅነሽ በሽር እንዳሉት፣ በሀገሪቱ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ብቻ ሳይሆን ሀገርና ህዝብን ጠብቆ ለማቆየትም ሰላም የጎላ ፋይዳ አለው።

ሰርቶ መለወጥ፣ ያሰቡትን ማሳካትና ከልማቱም ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ ሰላምን በዘላቂነት ለማስጠበቅ በተለይ ሴቶች በግንባር ቀደምነት ተዋናይ ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ላለፉት ዓመታት በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ሰላምና ልማት በብዙ መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑን በመገንዘብ በተለይ እናቶች ልጆቻቸውንና ወጣቱን ትውልድ ስለሰላም ዋጋ ማስተማር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የሰላም ዋጋ በቀላሉ መታየት የለበትም ያሉት ታጋይ  እሰይነሽ  ኪሮስ በበኩላቸው፣ ሰርቶ መግባትም ሆነ ሀብት ማፍራት የሚቻለው ሀገር ሰላም ስትሆን በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚንቀሳቀሱ አመልክተዋል።

ሰላማቸው ከደፈረሰ የተለያዩ ሀገራት እርስ በርስ ከመጋጨትና ልማትን ከማጥፋት ውጪ የሚቀሰም መልካም ነገር እንደሌለ የገለጹት ታጋይ እሰይነሽ፣ ሰርቶ ለመለወጥና የወለዱት ለመሳምም ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሴቶች የሰላም እጦት በሀገርና በዜጎች ላይ በተለይ በሴቶች ላይ የሚያስከትላቸውን የተለያዩ ችግሮች ለልጆቻቸው በማስረዳት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል።

 “ እናት ስለሰላም ማስተማር ከቤቷ ነው መጀመር ያለባት። በትጥቅ ትግል ወቅት በሀገሪቱ ሰላም እንዲረጋገጥና የዜጎች መብት እንዲከበር ልጇን ለትግል በክብር የሸኘች ናት። አሁንም ወጣቱ ትውልድ ወጥቶ ለመግባትና ሰርቶ ለማደር የሰላምን አስፈላጊነት ተረድቶ ሰላሙን ጠብቆ እንዲቆይ ሁሌም ልታስተምር ይገባል።’’

ከሃገር መከላከያ ሠራዊት በጡረታ መሰናበታቸውን የሚናገሩት ሻለቃ ደስታ ወረደ በበኩላቸው፣  በሀገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ በተደረገ የትጥቅ ትግል የወጣትነት ጊዜያቸውን በጦርነት አውድማ ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ትውልድ በተለይ ሴቶች በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሰላምን ዋጋ በአግባቡ በመረዳት ለሰላማቸው በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

“ቤተሰብ የሀገር መሰረት፤ እናትም ደግሞ ዋነኛ የቤተሰብ ምሰሶ ናት” ያሉት ሻለቃ ደስታ፣ እናቶች ልጆቻቸው የሰላም አስፈላጊነትን እንዲረዱ ሁሌም የማስተማር ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በወይይት መደረኩ ላይ የተገኙት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሕዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ ሴቶች በሀገሪቱ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲረጋገጡ በትጥቅ ትግሉ ወቅት የጎላ ሚና እንደነበራቸው አስታውሰዋል።

ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ወደኋላ እንዳይመለስ አሁንም ግንባርቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።     

"በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተረጋገጠውን የሴቶችን እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማጎልበት የአገርን ሰላም ዘላቂ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል ወይዘሮ ሮማን።

ለእዚህም ወጣቱ ትውልድ የሰላምን አስፈላጊነት ተገንዝቦ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ በኩል ከሴቶች በፊት ሊቀድም የሚችል ሌላ ኃይል አለመኖሩን ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን