አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 12 March 2018

ጎንደር መጋቢት 3/2010 በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በዘመናዊ መንገድ ሰብስቦ ማስወገድ የሚችል ማሽን ዛሬ በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ።

 በአማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተገዛው ይኸው ማሽን አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በሰዓት 5 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገኝ የእምቦጭ አረም የማስወገድ አቅም አለው፡፡

 በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ጎመንጌ በተባለው የሃይቁ  ዳርቻ ዛሬ በተካሄደው ስነ-ስርአት የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተርር በላይነህ አየለ እንደተናገሩት በሃይቁ ላይ የተጋረጠውን የእምቦጭ አረም ስጋት ለመቀነስ በርካታ ተግባራት  እየተከናወኑ ነው፡፡

 እየተከናወኑ ካሉት ተግባራት መካከልም በህዝቡ ተሳትፎ የሚካሄደው የማስወገድ ስራ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን የክልሉ ባለሀብቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማትና በውጪ የሚኖሩ ተወላጆችም እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

 ''አማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከቻይና ሀገር ያስመጣው የእምቦጭ አረም መሰብሰቢያ ማሽን ስራ እንዲጀምር መደረጉ የባለሀብቶች ተሳትፎ አንዱ ማሳያ ነው'' ብለዋል፡፡

 የክልሉ መንግስት ተመሳሳይ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በቅርቡ የተቋቋመው የጣና ፈንድም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ድጋፎችን በማስተባበር ሃይቁን ለመታደግ ሰፊ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 አማጋ ላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ተወካይ አቶ ፍቅሬ ፎጌ የጣና ሐይቅ ከክልሉ አልፎ የሀገር ሀብት እንደመሆኑ ድርጅቱ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ማሽኑን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ስራ እንዲጀምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

 ማሽኑ በሰአት 5ሺ ካሬ ሜትር ሃይቁን የወረረውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ አቅም እንዳለው ገልፀው ማሽኑ ለተከታታይ 30 ሰዓት ያለእረፍት የመስራት አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

 የፌደራል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ሃይቁን ለመታደግ እየተደረገ ላለው ርብርብ በምርምር፣ በፋይናንስና በቁሳቁስ ጭምር ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

 በዚህ አመት ብቻ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ''በስሩ የሚገኙ ኢንስቲትዩቶችም የሀይቁን ብዝሃ ሕይወት ለመታደግ የሚያስችሉ ምርምሮች እያካሄዱ ይገኛሉ'' ብለዋል፡፡

 የማእከላዊ ጎንደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው ሃይቁን በሚያዋስነው በጎንደር ዙሪያ ምእራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች ከ167ሺ በላይ አርሶ አደሮች በእምቦጭ አረም ማስወገድ ስራ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ 

 ሃይቁን የወረረውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ላለፉት 5 አመታት ጉልበታችንን አፍሰናል ያሉት ደግሞ የሀይቁ አዋሳኝ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አበረ ሽፈራው ናቸው፡፡

 ''የማሽኑ መምጣት ድካማችን ይቀንሰዋል ብለን ተስፋ አድርገናል'' ያሉት አርሶአደር አበረ ከችግሩ ስፋት አኳያ በአንድ ማሽን የሀይቁን አረም ማስወገድ የማይቻል በመሆኑ ተጨማሪ ማሽን ተገዝቶ ሊመጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 በማሽኑ የማስጀመሪያ ስነ ሰርአት ላይ ከፌደራል፣ ከክልልና ከማእከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

 ማሽኑን በግዢ ለአበረከተው ለአማጋ የግል ድርጅት የክልሉ መንግስት ያዘጋጀው የእውቅና ምስክር ወረቀትና ዋንጫ ለድርጅቱ ተወካይ በስጦታ ተበርክቷል፡፡

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2010 ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር የኢኮኖሚ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር መሐመድ እድሪስ ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደሩ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ከአራት ዓመት በፊት ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ስትራቴጂክ ሰነድ መፈራረማቸው አስታውሰዋል።

ሰነዱ በመከላከያ፣ በፀጥታ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በይበልጥ ተባብረው መሥራት የሚያስችላቸው ነው።

ሁለቱ አገሮች በድንበር አካባቢ፣ በንግድ መስመሮችና በወደቦች ላይ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መገንባታቸው በኢኮኖሚ ለመተሳሰር የሚያደርጉትን ጥረት እያፋጠነው እንደሚገኝ አምባሳደር መሐመድ ገልጸዋል።

ጅቡቲ ሁለንተናዊ ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ ተናግረዋል።  

አገሮቹ በመሠረተ ልማት ለመተሳሰር የተፈራረሟቸው ስምምነቶች እየተተገበሩ ስለመሆኑ የኢትዮ-ጂቡቲ የባቡር ፕሮጀክት ጥሩ ማሳያ እንደሆነ አምባሳደር ፋራህ ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ለማስተሳሰርና የንግድ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ ጠቀሜታ እንዳለው አውስተዋል።

ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን ለማስገባት የተጀመረው ሁለተኛው የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክት ከአንድ ወር በኋላ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ጠቁመዋል። 

ከአዲስ አበባ ጅቡቲ የተገነባው የባቡር ፕሮጀክት በአገሮቹ መካከል የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም አምባሳደሩ አንስተዋል።                     

በአገሮቹ መካከል የንግድ እንቅስቃሴውንም ለማሳደግ ጅቡቲ ፍላጎት እንዳላት ገልጸው፤ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ፣ ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን የወጪ ገቢ ንግድ ማጠናከሩም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

“ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ብዙ ነገር ትማራለች” ያሉት አምባሳደር መሐመድ፤ ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሠላም ለማስጠበቅ ያላትን ሚና አድንቀዋል።  

በቀጣይም የሶማሊያ፣ የደቡብ ሱዳን እንዲሁም የቀጠናው ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ጅቡቲና ኢትዮጵያ የጀመሩትን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።  

ሰሞኑን በጅቡቲ እና ‘ዲፒ ዎርልድ’ በተሰኘው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ኩባንያ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ እንደሌለው አምባሳደር መሐመድ እድሪስ ገልጸዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መልካም ቢሆንም ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አምባሳደሩ ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2010 በሴቶች ባለቤትነት የተያዙና የሚመሩ የአነስተኛና መካከለኛ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች ብዛት እጅግ አናሳ መሆኑ ተገለጸ።

ሴቶችን በአነስተኛና መካካለኛ አምራቾች ዘርፍ ለማበረታታትና ለመደገፍ የተዘጋጀ አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

የዓለም የሴቶች ቀንን በማስመልከት በተዘጋጀ በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ30 በላይ ሴት የአነስተኛና መካካለኛ ማምረቻ ኢንደስትሪ አምራቾች የተሳተፉበት ሲሆን እስከ መጋቢት ሰባት ድረስ ይካሄዳል።

በአውደ ርዕዩ ሴት አምራቾች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ አምራቾች የልምድ ልውውጥ ለማድረግና እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ሌሎች ተግባራት የሚካሄዱበት መሆኑም ተገልጿል።

በኢንደስትሪ ሚኒስቴር የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በሴቶች ባለቤትነት የተያዙና የሚመሩ መካከለኛ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች 16 በመቶ ሲሆኑ፤ የአነስተኛ ማምረቻው ደግሞ 22 በመቶ መሆኑን ያሳያል።

ኢንዱስትሪዎቹ በወንዶች ባለቤትነት ከሚመሩት አንጻር ሲታዩ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ የአመራረት ዘዴ የሚጠቀሙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ አነስተኛ የምርት ውጤት ያላቸውና አዝጋሚ የሽግግር ዕድገት የሚያስመዘግቡ መሆናቸውም ተመልክቷል።

ከነዚህም በአብዛኛው በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት እንዲሁም በግብርና ውጤቶች ላይ እሴት በሚጨመሩ ስራዎች ላይ የተገደቡ መሆናቸውን ነው ጥናቱ የሚያስቀምጠው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አግላቸው ሀዲስ የማምረቻ ዘርፉን ለመደገፍ በሚንስቴሩ በዘርፉ የሚሰማሩ ሁሉም ባለሀብቶችን የሚደግፍ ዳይሬክቶሬትና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ መቋቋማቸውን አንስተዋል።

የሴት አምራቾች የአቅም ግንባታ ስልጠና ፣ የልምድ ልውውጥ፣ሴቶችን ወደ ዘርፉ የሚስገቡ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ስራዎች፣ተቋማት ሴቶችን መደገፍ እንደ ዋና ስራቸው በእቅዳቸው አካተው እንዲሰሩ የማድረግ ጅምር ስራዎች ቢኖሩም ብዙ ቀሪ ስራዎች አሉ ብለዋል።

በቀጣይም እነዚሀን ስራዎች በስፋትና በተጠናከረ መልኩ በመስራት የሴት አነስተኛና መካካለኛ አምራቾችን ቁጥር ለማሳደግ መታቀዱን ገልጸዋል።

የማምረቻ ዘርፉ ፈታኝ በመሆኑም የሴቶች ያላሰለሰ ጥረትና የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ርብርብ አስፋላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ መጋቢት 3/2010 በአዳማ ከተማ እሬቻ ቀበሌ በሚገኘው ኩሪፍቱ ሪዞርት ላይ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ አዳጋ በንብረት ላይ ጉዳት ማስከተሉን የከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ዛሬ ከቀኑ 4፡30 ሰዓት ተኩል አካባቢ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ በሪዞርቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ በሪዞርቱ ውስጥ የነበረው ንብረት ሙሉ በሙሉ መውደሙን ምክትል ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልጸዋል።

ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ሕብረተሰቡ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ የፖሊስ አባላት ከፍተኛ ርብርብ በማድረጋቸው እሳቱ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

በተጨማሪም አደጋውን ለመቆጣጠር ከሞጆ ደረቅ ወደብ፣ ከቢሾፍቱ አየር ኃይል፣ ከትራክተር ፋብሪካና የከተማው መስተዳድር የእሳትና አደጋ መከላከያ ሠራተኞች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸውን ምክትል ኢኒስፔክተር ወርቅነሽ አስረድተዋል።

አደጋው በአካባቢው የነበረው ትራንስፎርመር ፈንድቶ የኤሌክትሪክ ኬብል በሳር ቤቶች ላይ በመውደቁ የተነሳ የተከሰተ መሆኑንም ገልጸዋል።

በቃጠሎው የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳይ ለማወቅ ኮማንድ ፖስት፣ ፖሊስና የሪዞርቱ ባለቤት በማጣራት ላይ መሆናቸውንም ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2010 አምስት መቶ አርባ  ስራ አጥ ወጣቶች የመስሪያ፣ መሸጫና ማሳያ ቦታ መስጠቱን በአዲስ አበባ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ገለጸ።

ቦታውን ያገኙት ከስደት ተመላሾች፣በቆሼ አካባቢ የቆሻሻ መደርመስ አደጋ ደርሶባቸው የተረፉና ሌሎች በክፍለ ከተማው የሚኖሩ ስራ አጥ ወጣቶች ናቸው።

በክፍለ ከተማው የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መቆያ ላሌ እንደተናገሩት መንግስት ስራ አጥነትን ለመቀነስ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የመስሪያ፣ የመሸጫና የማሳያ ቦታ አዘጋጅቶ ለተደራጁ ስራ አጦች ማስተላለፍ አንዱ ነው።

በዕጣ የመስሪያ፣ የመሸጫና የማሳያ ቦታ ያገኙት 540 ስራ አጥ ወጣቶች ምንም አይነት ስራ የሌላቸው ከዚህ በፊት የመስሪያ ቦታ ያልወሰዱ መሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

ስራ ፈላጊ ወጣቶች በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በከተማ ግብርና፣ በእንጨትና ብረታብረት ስራ፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች እንዲሁም በአገልግሎት ዘርፍ ተደራጅተው ሙያዊ  ስልጠና የተሰጣቸው መሆኑን አቶ መቆያ ገልጸዋል።

ሰልጣኞች በሰለጠኑበት የሙያ ዘርፍ የብቃት ምዘና ፈተና ወስደው ብቁ ስለመሆናቸው የብቃት ማረጋገጫ የተሰጣቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከመስሪያ፣ መሸጫና ማሳያ ቦታዎቹ በተጨማሪ ለስራ ማስኬጃ የብድር አቅርቦት ለወጣቶቹ መመቻቸቱን ገልጸዋል።

ወጣቶቹ ብድር ለመውሰድ የሚጠየቁ መስፈርቶችን በማሟላት የሚያስፈልጋቸውን የገንዘብ መጠን በየወረዳቸው በማቅረብ የብድር ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ  ወጣቶቹ ወደ ስራ ገብተው ውጤታማ እንዲሆኑ ተገቢው ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል።

በ2009 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ከሳውዲ አረቢያ ወደ አገሯ የተመለሰችው ወጣት ሙሉ ረጋሳ  በበኩሏ "የእድሉ ተጠቃሚ መሆን በመቻሌ ከምንም በላይ ደስተኛ ነኝ በአገሬ ሰርቼ እራሴን ለመለወጥ ተዘጋጅቻለሁ" ብላለች።

ለሌሎች ወጣቶችም በሰው አገር ስደትን ከመመኘት በአገር ላይ ሰርቶ መቀየር እንደሚቻልም መልዕክቷን አስተላልፋለች።

ሌላኛው የእድሉ ተጠቃሚ ወጣት ዘካሪያስ ጩባሮ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ተደራጅቶ ለመስራት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሲሞክር መቆየቱን ገልጾ አሁን ባገኘው እድል መደሰቱን ተናግሯል።

Published in ኢኮኖሚ

አርባ ምንጭ መጋቢት 3/2010 ህብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስፈላጊነት በሚገባ ተገንዝቦ ለተግባራዊነቱ የድርሻውን እንዲወጣ በማድረግ በኩል የምክር ቤት አባላት  ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው የጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት አፌ ጉባኤ ገለጹ።

የዞኑ መስተዳደር 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።

የምክር ቤቱ አፌ ጉባኤ ወይዘሮ ልሳኔወርቅ ካሳዬ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት የምክር ቤት አባላት በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ ይዘው የወከላቸውን ህዝብ የማስረዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት የተሰጠው አካላት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የምክር ቤቱ አባላት ህዝቡን በማስተባበር የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ትናንት የተጀመረው የዞኑ መስተዳደር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የ9ኛ መደበኛ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ መርምሮም ከነማሻሻያው በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የጋሞ ጎፋ ዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ የአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የስድስት ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ምክር ቤቱ በሪፖርቱ ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከወጣው መረሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2010 ሁለተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ነገ በሐዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ይጀመራል።

ከመጋቢት 4 እስከ 8 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር 10 የቦክስ ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን የኢትዮጵያ የቦክስ ፌደሬሽን በዘንድሮው ዓመት ከሚያካሂዳቸው የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድሮች ሁለተኛው ነው።

በፌደሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር እንዲሁም ከደቡብ ክልል የተውጣጡ ናቸው።

ክለቦቹ 12 የወንዶችና ስድስት የሴቶች ተወዳዳሪዎችን ይዘው እንደሚቀርቡ የተናገሩት አቶ ስንታየው ተወዳዳሪ ክለቦች ከሁሉም ክልሎች ያልተገኙት የቦክስ ክለብ የሌላቸው በመሆኑ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በውድድሩ ላይ በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም ግጥሚያ የሚካሄድ ሲሆን፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ባሉ ክብደቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ ብለዋል።

ይህንን ውድድር እንደሌሎቹ ስፖርቶች በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ለማካሄድ ይህንን ውድድር እንደመነሻ ለመጠቀም መታቀዱን አቶ ስንታየሁ ተናግረዋል።

ውድድሩ ሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው የአፍሪካ የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩ ቦክሰኞችን ለመምረጥና ለመመልመል እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

በውድድሩ በየክብደቱ ምርጥ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሚረዳ አስረድተዋል።

የዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድር በታህሳስ ወር 2010 ዓ.ም እንደተካሄደ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የቦክስ ፌደሬሽን ቀጣዮቹን ሁለት የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ሻምፒዮና በሚያዝያና ሰኔ ወር 2010 ዓ.ም ላይ እንደሚያካሂድ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት ለወታደሮች ይሰጥ ነበር።

በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። በአዲስ አበባ ከተማ ስፖርቱ መለመድና መስፋፋት ጀመረ።

የክለቦች ምስረታም በዛው ወቅት የተጀመረ ሲሆን፤ በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ።

Published in ስፖርት

ባህር ዳር መጋቢት 3/2010 መላው የስፖርት ቤተሰብ ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ።

ከአምስት ሺህ 700 በላይ ስፖርተኞች የሚሳተፉበት 6ኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ጨዋታ በባህር ዳር ብሔራዊ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን ተጀምሯል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ወለላ መብራቱ ውድድሩ ሲጀመር እንተናገሩት የክልሉ መንግስት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደውና ትናንት የተጀመረው 6ኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ጨዋታ ለክልሉና ለሀገሪቱ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የጎላ ድርሻ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል። 

በህዝቦች መካከል ሰላምን፣ አንድነትን፣ ወዳጅነትን፣ መከባበርና መደጋገፍን ለማጠናከር ስፖርት የጎላ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝም ወይዘሮ ወለላ አስረድተዋል።

" ስፖርት የጾታ፣ የብሔርና መሰል አስተሳሰቦችን የማያስተናግድ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠ ተግባር በስፖርት ማዘውተሪያዎች እየተስተዋለ ይገኛል" ብለዋል።

ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስም ተሳታፊ ስፖርተኞች፣ ባለሙያዎች፣ ደጋፊዎችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭ ወጣቶች ስፖርታዊ ጨዋነትን ለማወክ የሚንቃሳቀሱ ኃይሎችን በማጋለጥ ከመንግስት ጎን ሆነው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።  

ስድስተኛው የመላው አማራ ስፖርታዊ ጨዋታን በተጋባዥነት ተገኝታ የከፈተችው ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ ስፖርት በህዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠርና ወንድማማችነት እንዲጎለብት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን ገልጻለች።። 

ተሳታፊ ስፖርተኞችም በሚያደርጉት ውድድር ማሸነፍንም ሆነ መሸነፍን በፀጋ በመቀበል እርስ በእርስ ስፖርትዊ ጨዋነትና ልምዶችን መለዋወጥ እንደሚገባቸው አስረድታለች።

ከስፖርታዊ ውድድሩ ጎን ለጎንም የመጣችሁበትን አካባቢ ወግና ባህል ከማስተዋወቅና ከማሳደግ ባለፈ ይበልጥ አንድነታችሁን ልታጠናክሩ ይገባል ሲሉም መክረዋል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ክብረት መሀሙድ በበኩላቸው በአስተዳደሩ ጥረትና የክልሉ መንግስት በሚያደርገው ድጋፍ ከተማዋን ለማዘመን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም የቱሪዝም ፍሰቱ እያደገ እንዲሄድ ከማድረጉ በላይ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉን ተናግረዋል። 

"በሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች የስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያደፈርሱ አመለካከቶች እየታዩ በመሆኑ የከተማዋ ሕዝብ ሊከላከላቸው ይገባል" ብለዋል።

በስድስተኛው የመላው አማራ ጨዋታ ለመሳተፍ ወደከተማው የመጡ የስፖርት ልዑካን ተሳታፊዎች በቆይታቸው የኦሎምፒክ ስፖርት መርህን በመላበስ አንድነትና ፍቅርን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በውድድሩ መክፈቻ ላይ የተገናኙት የባህር ዳርና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እግር ኳስ ክለቦች ባደረጉት ጨዋታም የአዊ እግር ኳስ ክለብ 5 ለ 2 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ከትናንት ጀምሮ እስከ መጋቢት 16 በሚካሄደው የመላው አማራ ስፖርታዊ ውድድርም እግር ኳስና አትሌቲክስን ጨምሮ 18 ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚካሄዱ ታውቋል።

Published in ስፖርት

ወልዲያ መጋቢት 3/2010  በሰሜን ወሎ ዞን በአይን ሞራ ግርዶሽና ትራኮማ የተጠቁ 3ሺህ 600 ህሙማን በተደረገላቸው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ማየት መቻላቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

 የመምሪያው የዓይነ ስውርነት መከላከል ባለሙያ አቶ አስፋው ጎበዜ እንደገለጹት ህሙማኑ ብርሃናቸው የተመለሰው ባለፉት ሰባት ወራት በወልድያ፣ በቆቦ፣ በላልይበላ ሆስፒታሎችና በጤና ጣቢያዎች በመደበኛና በዘመቻ መርሀግብር በተደተገላቸው የቀዶ ህክምና አገልግሎት ነው።

 በበሽታዎቹ የሚያዙ ሰዎች በግንዛቤ እጥረት ወደ ህክምና ተቋም በወቅቱ መምጣት ባለመቻለቸው ህክምናውን አስቸጋሪ እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል ።

 በወልድያ ሆስፒታል የዓይን ቀዶ ህክምና ባለሙያ አቶ አብርሃም አረጋዊ በበኩላቸው በሆስፒታሉ የቀዶ ህክምና ከተደረገላቸው 1ሺህ 750 ህሙማን በተጨማሪ ለ3ሺህ 250 ህሙማን የተለያየ የአይን ህክምና ተሰጥቷል ።

 የግልና የአካባቢ ንጽህናን መጠበቅ፣ በተለይ ለትራኮማ ክትባት መውሰድና ቫይታሚን ኤ ያሉባቸውን ምግቦች መመገብ የአይን ህመሞችን አስቀድሞ ለመከላከል መፍትሄ መሆናቸውን መክረዋል ።

 በመቄት ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሰጠችኝ አያሌው በሰጡት አስተያየት በዚህ አመት በወልድያ ሆስፒታል ለሁለት አይናቸው ሁለት ጊዜ በተደረገላቸው የቀዶ ህክምና የአይናቸው ብርሀን መመለሱን ተናግረዋል ።

 ከራያ ቆቦ ወረዳ ወደ ሆስፒታሉ የመጡ ወይዘሮ ዘነቡ ካሳው በበኩላቸው "በተደረገልኝ የቀዶ ህክምና በሞራ ግርዶሽ ለሁለት አመት ማየት ተስኟቸው የቆዩ ሁለት አይኖቼ ማየት ችለዋል " ብለዋል ።

 "ከዓይን ቆቤ በሚበቅል ፀጉር ከሚያስከትልብኝ ሲቃይ ለመገላገል በየጊዜው በወረንጦ እየነቀልኩ ለ40 አመት ቆይቻለሁ " ያሉት አቶ ፈንታየ ገብሬ በበኩላቸው በህክምና ከበሽታው መዳን እንደሚቻል በማወቃቸው በሆስፒታሉ የአይን ቆብ ህክምና ለማድረግ ወረፋ እየጠበቁ መሆናቸውን አስረድተዋል ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 3/2010 ጃፓን በኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ከ600 ሚሊዮን  ብር በላይ ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች።

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ ፤ አገሪቱ በኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ እና ለሌሎች ሰብአዊ ድጋፍ የሚውል 628 ሚሊዮን 368 ሺህ ብር በአለም አቀፍ ተቋማት በኩል ድጋፍ አድርጋለች።

ድጋፉ ኢትዮጵያ ከድህነት ለመውጣት ላቀደቻቸው የዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት፣ለስደተኞች ድጋፍ እንዲሁም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለመስጠት የሚውል ነው።

የኢትዮጵያውያንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በማሳደግ የተሻለ ህይወት አንዲኖራቸውና በራሳቸው ጥረት እንዲለወጡ ለማድረግ ጃፓን የአቅም ግንባታና የቴክኒክ ድጋፍ እንደምታደርግም ተገልጿል።

ጃፓን እስከ መጋቢት 2018 መጨረሻ ከሰሃራ በታች ላሉ አገሮች 145 ነጥብ 45 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግ ተገልጿል።

በተጨማሪም የጃፓን በአፍሪካ አህጉር መረጋጋት እንዲኖርና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በሚደረገው እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነች በመግለጫው ተጠቁሟል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን