አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 11 March 2018

አዲስ አበባ የካቲት 2/2010 ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን 2 ለ1 በማሸነፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የእግር ኳስ ዋንጫ ሻምፒዮን ሆኗል።

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ዘንድሮ ለአምስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የእግር ኳስ የዋንጫ ውድድር ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ፍጻሜውን አግኝቷል።

የሲዳማ ቡናው ትርታዬ ደመቀ በ31ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠረው ጎል መሪ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ቡና ከእረፍት መልስ አቡበከር ነስሩና ቶማስ ስምረቱ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ጨዋታውን ለማሸነፍ ችሏል።

ቀደም ሲል ለደረጃ በተደረገው ጨዋታ ኢትዮ - ኤሌክትሪክ በሀቢብ ከማልና በባህሉ ተሻገር ጎሎች ደደቢትን 2 ለ0 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።

በውድድሩ አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና የ50 ሺ ብር ቦንድ፣ ዋንጫና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልሟል።

ሁለተኛና ሦስተኛ የወጡት ሲዳማ ቡናና ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በተከታታይ የ35ሺ ብር ቦንድና የ15 ሺ ብር ቦንድ እንዲሁም የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

ሽልማቱን የሰጡት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ይገዙ፣ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ጁኔዲን በሻ እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ናቸው።

 

Published in ስፖርት

ደብረ በርሃን መጋቢት 2/2010 በሀገሪቱ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚደረገው ጥረት በየቤተ እምነቶቻቸው ተከታዮቻቸውን በማስተማር የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የአንጎለላ ጠራ ወረዳ የሃይማኖት አባቶች ገለፁ።

ከሁከትና ብጥብጥ የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ ህበረተሰቡ ችግሮችን በሰከነና በተረጋጋ መንገድ በመወያየት መፍታት እንዳለበትም የሃይማኖት አባቶቹ አሳስበዋል።  

የወረዳው የሃይማኖቶች የጋራ የሰላም የምክክር ጉባኤ ጽህፈት ቤት ሰብሳቢ ቄስ ዮሐንስ መለሰ የሃይማኖቶች የጋራ የምክክር መድረክ ጉባኤ በጫጫ ከተማ ሲካሄድ እንደገለፁት በሀገሪቱ አንዳንድ ቦታዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት መልሶ የሚጎዳው ዜጎችንና የሀገር ልማትን ነው።

ወጣቶች ችግሮቻቸውንና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በተገቢው መንገድ በማቅረብ  ከብጥብጥና ከሁከት መንገዶች መራቅ እንዳለባቸውም መክረዋል።

በሀገሪቱ የተጀመረው የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመንግስት በኩልም የወጣቶችን ጥያቄ በማዳመጥ ተገቢውን መልስ መስጠት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሁሉንም ህዝብ ሰላማዊ እንቅስቃሴ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለውጤታማነቱ ህዝቡን ስለ ሰላም ዋጋ በማስተማር ከመንግስት ጋር ተባብረው እንደሚሰሩም አመልክተዋል።

"ህዝቡ ወደ ቀደሞ ግብረ ገባዊ ምግባሩ እንዲመለስ ሃይማኖታዊ አስተምህሮውን መሰረት በማድረግ ግንዛቤ ፈጠራ ላይ በስፋት እንሰራለን" ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ ።

በመቻቻልና ተከባብሮ የመኖር እሴቶቻችንን በማጠናከር በአብሮነት የማደግ ባህላችንን ማጎልበት እንጂ ብጥብጥና ሁከት አይጠቅመንም ያሉት ደግሞ የጉባኤው ጸሐፊ አቶ መሐመድ ከድር ናቸው።

የሀገሪቱ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆንና ዜጎች ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀሱ በየቤተ እምነቶቻቸቸው ያሉ ተከታዮቻቸውን በማስተማር ለሀገሪቱ ልማት መፋጠን እንደሚሰሩ ጨምረው ተናግረዋል።

የወረዳው አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዘላቂ መፍትሔ ትግበራ ባለሙያ አቶ ወጋየሁ ገድሌ በበኩላቸው የሀይማኖት አባቶቹ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ ያደርጉት ጥረት በአካባቢው ግጭቶች እንዲቀንሱ አግዟል ብለዋል።

አሁንም በየቤተ እምነቶቻቸው ተከታዮቻቸውን ስለ ሰላም አስፈላጊነትና ሁከትና ብጥበጥ የሚያስከትለወን ጉዳት በማስተማር የአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ አጥብቀው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

Published in ፖለቲካ

ባህር ዳር መጋቢት2/2010 በአማራ ክልል በመጪው የመኽር ወቅት ለኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ንግድ የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን በብዛትና በጥራት ለማምረት ኩታገ ጠምን መሰረት ያደረገ የእርሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

መጪው የመኽር እርሻ የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ፍሰሃ ወልደሰንበት በእዚህ ወቅት እንደገለጹት የአርሶ አደሩን ልማዳዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ በመቀየር በኩል አበረታች ለውጥ እየተመዘገበ ነው።

በእዚህም አርሶ አደሩ በተደራጀ አግባብ እንዲንቀሳቀስ ከማድረግ ባለፈ በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እርስ በእርሱ ልምድ የሚለዋወጥበት ዕድል ተፈጥሯል።

ባለፈው የመኽር ወቅት በተደረገ እንቅስቃሴ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዋና ዋና ሰብሎች በኩታ ገጠም እንዲለማ መደረጉን ጠቁመው፣ በአጠቃላይ ከለማው 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬትም 100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ገልፀዋል።

በቀጣዩ የመኽር ወቅትም 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ካለፈው ዓመት በ10 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት ለማምረት መታቀዱን ጠቁመዋል።

ከሚለማው መሬት ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በዘመናዊ መንገድ በኩታ ገጠም የሚለማ ሲሆን በእዚህም ለኢንዱስትሪዎችና ለውጭ ንግድ የሚውል 45 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ነው።

"ግቡ እንዲሳካም የምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ማድረስና ተገቢው ሙያዊ ስልጠናና ድጋፍ ከአመራሩ ይጠበቃል" ብለዋል።

የምስራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፈንታሁን አቢታ በበኩላቸው በ2009/10 የምርት ዘመን 15 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልፀዋል።

በእዚህ የምርት ዘመንም ግብዓቶችን በመጠቀምና ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴን በማስፋት 20 ሚሊዮን ኩንታል መረት ለመሰብሰብ ከወዲሁ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

"ዕቅዱ እንዲሳካ ምርጥ ተሞክሮዎችን ከማስፋት ባለፈ ምርጥ ዘር እንዲሁም ማዳበሪያ በበቂ መጠን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ጥረት ይደረጋል" ብለዋል።

" የአካባቢው የእርሻ መሬት ለአሲደማነት በመጋለጡ ለዲከረንስና ባህር ዛፍ ልማት እየዋለ ነው" ያሉት ደግሞ በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አንክሻ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙላቱ ጌትነት ናቸው።

በመሆኑም በቀጣዩ የክረምት ወቅት አሲዳማ መሬትን በማከም የተሻለ ምርት ለመሰብሰብና የመሬቱን ለምነት ለመመለስ ከወዲሁ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጨመሮ የዞንና የወረዳ አመራሮች ተሳትፈዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መጋቢት2/2010 ዶክተር ማህሌት ይገረሙ የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ሃኪም ናቸው። ተመራማሪ፣ አስተማሪ፣ የህክምና ባለሙያ፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሴት ተመራማሪዎች ቡድን አባልና መስራች እንዲሁም እናት ናቸው።

እነዚህን ሁሉ ኃላፊነቶች የተሸከሙት እኚህ እንስት "ሴት በተፈጥሮ በተሰጣት ጸጋ ሁሉንም መስራትና መሆን ትችላለች" የሚል ጽኑ ዕምነት አላቸው።

በራስ መተማመናቸው በቀላሉ ከፊታቸው ላይ የሚነበብባቸው ዶክተር ማህሌት ላለፉት አስራ ሶስት ዓመታት ለአገራቸው በህክምናው ዘርፍ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስና ፍሬውን ለማብዛት በምርምር ዘርፍ ከራሳቸው አልፈው ብዙ ወጣቶችን ይዘው ለመውጣት ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር ራዕይ ሰንቀዋል።

ከአንድ አመት ተኩል በፊት 16 የሙያ አጋሮቻቸውን በመያዝ በሴቶች ጤና ዙሪያ የምርምር ስራ የሚያደርግ የተመራማሪዎች ቡድን ካቋቋሙ ሶስት እንስቶች መካከል አንዷ ናቸው።

የእነዚህ ወጣት ሴት ተመራማሪዎች ቡድን በአጭር ጊዜ ፍሬ አፍርቶ በቅድመ ካንሰር ምርመራ፣ በወሊድ ጊዜ የእናቶች ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን አሁን ካለው ነበራዊ ሁኔታና ሌሎች ጥናቶችን አበርክተዋል።

እነዚህ ሴቶች በአገሪቱ በአብዛኛው በወንዶች የተያዘውን የጥናትና ምርምር ስራ እንዲዳፈሩ የትናንት ማንነታቸው ስንቅ እንደሆናቸው ይናገራሉ። ''ማህበረሰብ በተለይም ደግሞ ቤተሰብ ለሴቶች የነገ ማንነት ወሳኝ ሚና አላቸው'' ይላሉ።

''አባቶች ሴት ልጆቻቸው ብቁ ሆነው እንዲወጡ ለማስቻል ትኩረት መስጠት አለባቸው'' የሚሉት ዶክተር ማህሌት ''አባት በሴት ልጁ የሚተማመን ከሆነ ሌላው ህብረተሰብ የዛ ነጸብራቅ ይሆናል'' ባይ ናቸው።

''ለእኔ ውጤታማነት ከእናቴ ጎን የአባቴ ድጋፍና ክትትል ነው "አባቴ አንቺ ከእኔ በላይ ነሽ፣ ታውቂያለሽ፣ ከሁሉም ትበልጫለሽ" እያለ ስላሳደገኝ በራስ የመተማመን መንፈሴን ጨምሮታል'' ብለዋል።

ዶክተር ማህሌት ባላቸው ሰፊ ኃላፊነት እንዳይደክሙ ብርታት የሆናቸው የአባታቸው ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ያላቸው ሰፊ የወደፊት ራዕይ ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ።

መንግስት የሴት ጤና ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ ሰፊ ጥረት አድርጎ በአገሪቱ ከሚገኙት አጠቃላይ የጤና ባለሙያዎች ውስጥ የሴቶች ድርሻ ከ50 በመቶ በላይ ቢሆንም በከፍተኛ የተመራማሪነት ደረጃ ላይ ማድረስና ለሃላፊነት ማብቃት ላይ ተጨማሪ ጥረት ይጠይቃል።

ሁሉም በሃላፊነት ቦታ ላይ ያለ ሰው በስሩ በርካታ ሰዎችን የማፍራት ሃላፊነት ስላለበት ሴቶች ለከፍተኛ ተመራማሪነት ደረጃና ለሃላፊነት እንዲበቁ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዲን ዶክተር ምትኬ ሞላ እንደገለጹት፣ የኮሌጁ የሴት ተመራማሪዎች ቡድን ለፖሊሲ አውጪዎች ድጋፍ የሚሆኑ ምርምሮችን እያካሄዱ ነው።

በተለይ የተማሩ ሴቶች ለሌሎች አርአያ መሆንና ብዙ አቅም ያላቸውን ሴቶች ለመፍጠር ጥረት ማድረግ አለባቸው። ''እኛ ሴቶች በህይወቴ ለአገሬ ምን አደረኩ አርአያነቴ ምንድነው የሚለውን መልሰን መሄድ አለብን'' ብለዋል።

''መምህሮቼና ቤተሰቦቼ "ትችያለሽ ብለው ለዚህ አብቅተውኛል እኔም የእነሱን አርአያ ለመከተልና የወጣት ሴቶችን አቅም ለመጠቀም ቡድኑን ለመመስረት ሃሳብ አፍልቄያለሁ'' ብለዋል።

በአገር ደረጃ  ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ያላቸውን ሴቶች የመጠቀም አቅማችን ዝቅተኛ በመሆኑ አቅሙን ለመጠቀም የሚያስችል መንገድ መከተል ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ዕድል ሁል ጊዜ ለተዘጋጀ ሰው ክፍት እንደሆነች የሚያምኑት ዶክተር ምትኬ ሁሉም የተሰጠው ጸጋ ስላለው ለዛሬ ባይሳካለት ለነገ መሳካቱ ስለማይቀር ተስፋ በመሰነቅ መትጋት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቤተሰብም ልጆቹን በይቻላል መንፈስ ቢያሳድግና ለነገ አገር ገንቢ ትውልድና በራሷ የምትተማመን ሴት ለመፍጠር ይረዳታል ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

ሽሬእንዳስላሴ መጋቢት 2/2010 በሃገሪቱ የተከሰተውን አለመረጋጋት ወደ ቀደመው ሰላም ለመመለስ ለወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ በሽሬ እንዳስላሴ የሚገኙ የህወሃት ነባር ሴት ታጋዮች ገለጹ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በከተማው በተከበረበት ወቅት የከተማው ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ መብራት ለገሰ "በአገራችን እየተከሰተ ባለው ሁከትና ግርግር ግንባር ቀደም ተጠቂዎች ሴቶችና ህጻናት ናቸው" ብለዋል።

"ድህነትና ኋላ ቀርነትን ለማጥፋት የሰላም መረጋገጥ ወሳኝ ነው" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ ዛሬ አገራችን ውስጥ እየተስተዋለ ያለውን የሰላም መደፍረስ ለመቀልበስ ሴቶች በተደራጀ መልኩ እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

የሴቶች ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ የሚችለው ሰላም ሲሰፍን ብቻ በመሆኑ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የትግራይ ሰሜናዊ ዞን የሴቶች ማህበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ  ወይዘሮ አበባ ኪሮስ ናቸው።

ለሰላም መስፈን የዞኑ ሴቶች ማህበር አባላት የድርሻቸውን ለመወጣትና የመሪነት ሚናቸውን ለመጫወት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በንግድ ሥራ የተሰማሩት ሌላዋ ነባር የህወሓት ታጋይ ወይዘሮ አለምፀሃይ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው"በሁለቱም ፆታዎች የጋራ መስዋእትነት በአገራችን እየተረጋገጠ ያለውን የሰላምና ልማት ጉዞ ለማስቀጠል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከፍተኛ ሚና አለው" ብለዋል።

በሃገሪቱ የተከሰተውን ያለ መረጋጋትና ብጥብጥ ለማስቆም የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውጤታማ እንዲሆን ሴቶች አካባቢያቸውን በመጠበቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

"የደርግ ስርዓትን ለመደምሰስ በተካሄደው የትጥቅ ትግል አካሌ ቢጎድልም አሁንም በቀረው አካሌ ራሴን ለመቻል ሰላም ያስፈልገኛል" ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ነባር ታጋይ ወይዘሮ ሮማን መብራህቶም ናቸው።

መንግስትና ህብረተሰቡ የሃገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት ላይም የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አርባ ምንጭ መጋቢት 2/2010 በጋሞ ጎፋ ዞን አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የሚያቀርቡት ሪፖርት ተጨባጭና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሊሆን እንደሚገባ የዞኑ ምክር ቤት አስታወቀ።
የጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በዞኑ በገጠርና በከተማ የተከናወኑ የልማትና መልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ያደረጉትን ምልከታና ያገኙትን መረጃ መሰረት አድርገው ከአስፈጻሚው አካል ጋር ተወያይተዋል።
የምክር ቤቱ ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዞኑ በምዕራብ አባያ፣ ዲታና አርባምንጭ ከተማ አስተዳደር በምልከታ፣ በህዝብ ውይይትና ከአስፈጻሚው ያገኘውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የደረሰበትን የግምገማ ግብረ መልስ ለዞኑ አስፈጻሚ አካላት አቅርቧል።
ግብረመልሱን ያቀረቡት የኮሚቴው አባል አቶ ቦረና ቦኖ እንደተናገሩት አስፈጻሚ አካላት ለምክር ቤቱ የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ እውነታ ጋር በእጅጉ የራቁ ናቸው።
ባለፈው ዓመት የዞኑ ግብርና መምሪያ ለምክር ቤቱ ባቀረበው ዓመታዊ ሪፖርት በዞኑ በሁሉም ወረዳዎች የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ተገንብተውና በቁሳቁስ ተሟልተው ወደስራ መግባታቸውን ቢገለጽም በዲታ ወረዳ ብቻ አምስት ማዕከላት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ድረስ ስራ አለመጀመራቸውን በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን በማሳያነት ገልጸዋል።
"በአርባምንጭ ከተማ ሴቶች በ80 የልማት ቡድን ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸው ቢገለጽም በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉት የልማት ቡድኖች 15 መሆናቸውንና በዚህም አብዛኞቹ በአደረጃጀታቸው ወደ ስራ እንዳልገቡ ተመልክተናል" ሲሉም አስረድተዋል።
በገዜ ጎፋ፣ ኦይዳና ሳውላ ከተማ አስተዳደር ምልከታ ያደረገው በምክር ቤቱ የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት ለምክር ቤቶች የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች የተደራጁና ምክር ቤቶችን የሚመጥኑ አለመሆናቸውን አስረድቷል።
ግብረ መልሱን ለአስፈጻሚው አካል በጽሁፍ ያቀረቡት የኮሚቴው አባል አቶ ግርማ ዋሼ እንዳሉት ምልከታ ያደረጉባቸው ወረዳዎች የበጀትና የፋይናንስ አጠቃቀም ችግሮች አሉባቸው፡፡
አስፈጻሚ አካላት ጉድለቶችን እንዲያርሙ በተሰጣቸው ማሳሰቢያ መሰረት አለመተግበራቸውንም በምልከታ መረጋገጡን ገልጸዋል።
በተለይ በኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ፣ በገቢዎችና ፋይናንስ ሴክተሮች በገቢ አሰባሰብ፣ በብድር ስርጭትና በክፍያ አፈጻጸም ከፍተኛ የአሰራር ጥሰት መኖሩንና በዚህም ብዙ ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት ሲጉላላ ማየታቸውን ተናግረዋል።
የዞኑ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ልሳነ ወርቅ ካሳዬ በበኩላቸው አስፈጻሚ አካላት በየሴክተራቸው የሚታቀዱ ዕቅዶችና ክንውኖች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውን በኃላፊነት ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።
በየጊዜው ለምክር ቤቱ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶችም ተጨባጭና ህዝቡ ሊቀበላቸው የሚገቡ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በይዘት፣ በቁጥርና በትክክለኛነት የሚያጠራጥሩ ሪፖርቶችን የሚያቀርቡ አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር ምክር ቤቱ መዘርጋቱንም አፈጉባኤዋ ገልጸዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢሳያስ እንድሪያስ በበኩላቸው "ምክር ቤቱን የማይመጥኑና ተአማኒነታቸው የሚያጠራጥሩ ሪፖርቶችን የሚያቀርቡ አስፈጻሚ አካላት በምክር ቤቱ አሰራር ይጠየቃሉ" ብለዋል።

 

Published in ፖለቲካ

ዲላ መጋቢት 2/2010 በዞኑ የተሚሰተዋሉ የአፈፃፀም ጉድለቶችን ለማረም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ክትትል አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አባላት ገለፁ ፡፡

የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት አራተኛ ዙር 13ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል ፡፡

በጉባኤው ባለፉት ስድስት ወራት የሴክተር መሰሪያ ቤቶችን የሥራ ክንውን በመገምገም በድክመትና በጥንካሬዎች  በስፋት መክሯል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በዚህ ወቅት እንዳሉት በአስፈጻሚ አካላት የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ጉድለቶችን ለማረም የሚጠበቅባቸውን ድጋፍና ክትትል አጠናክረው ይቀጥላሉ። 

የዞኑ የምክር ቤት አባልና የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አቶ ታደሰ ደያሶ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በበጀት አመቱ መጀመሪያ የሚሰጣቸውን ሥራ እንዲያሳኩ በቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት ድጋፍና ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በጉባኤው ላይ የዞኑን አርሶ አደሮች ከሚያመርቱት ምርት የላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት በመልካም የታዩ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡

ቡና አብቃይ አርሶ አደሮችን የላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ከሁለት ሄክታር በላይ መሬት ያላቸው 150 የሚሆኑ አርሶ አደሮች ፈቃድ አውጥተው በስማቸው እስከውጭ ድረስ ቡና መላክ እንዲችሉ መደረጉን ገልጸዋል።

በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራትም አበረታች ለውጥ እያመጡ ስለመሆናቸው በጉባኤው መገምገሙን ነው አቶ ታደሰ የገለጹት፡፡

በአንጻሩ "ከገቢ አሰባሰብ፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የማምረቻና የመሸጫ ቦታ በማቅረብ፣ ህገ-ወጥ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ከመቆጣጠርና ለጎዳና ተዳዳሪነት የሚጋለጡ ሕጻናት ቁጥርን በመቀነስ በኩል የተከናወኑ ተግባራት ክፍተት እንዳለባቸው ተገምግሟል" ብለዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባልና የመሰረተ ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጉሴ አሰፋ በሚፈለገው ልክ ወጣቶችን ወደስራ ያለማስገባት፣ የገቢ አሰበሰብ ማነስ ፣ የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መቋረጥና መሰል ክፍተቶች እንዳሉ መለየቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የዓመቱ የገቢ አሰባሰብ ዕቅድ እስከ ግማሽ ዓመቱ 30 በመቶ ብቻ መሆኑ በመሰረተ ልማት ግንባታዎችና ሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አስረድተዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋ በበኩላቸው በስድስት ወራት ውስጥ ዝቅተኛ አፈፃፀም የነበራቸው ሴክተር መሰሪያ ቤቶችን ለመደገፍና የታዩ ጉድለቶችን በቀሪ ጊዜያት ለማካካስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ፡፡

የባለሙያዎች እጥረት በዞኑ ለታየው ዝቅተኛ የገቢ አሰባሰብ አንዱ ምክንያት መሆኑን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው ክፍተት ባለባቸው ቦታዎች ባለሙያዎችን የማሟላት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ምክር ቤቱ ለሁለት ቀናት ባካሄደው አራተኛ ዙር 13ኛ መደበኛ ጉባኤው የዞኑን የፍትሕ፣ የመንገድና ትራንስፖርት እንዲሁም የፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ ኃላፊዎችን ሹመት አፅድቋል ፡፡  

 

Published in ፖለቲካ

መጋቢት 2/2010 የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ  ስብሰባውን ዛሬ ጀምሯል፡፡

በስብሰባውም ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በታህሳስ ባካሄደውና 17 ቀናት በፈጀው ስብሰባ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች በየብሔራዊ ድርጅቶች እንዴት እንደፈፀሙ ይገመግማል።

አገሪቷ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታና የጥልቅ ተሃድሶውን አፈፃፀም መነሻ በማድረግ ስራ አስፈፃሚው ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ያሉበትን ደረጃ ገምግሞ ቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ።

ስብሰባው እንደተጠናቀቀም የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ተጠርቶ በቅርቡ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡት የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ኃይለማሪያም ደሳልኝን የሚተካ ሰውም ይመረጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ የመለክታል።

Published in ፖለቲካ

ጎንደር የካቲት 2/2010 ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማጠናከርና በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ዩኒቨርሲቲው "ሴቶች በኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ"  በሚል ያዘጋጀውን የሁለት ቀናት ሀገር አቀፍ የምክክር አውደ ጥናት በመካሄድ ላይ ነው፡፡

በምክክር መድረኩ መክፈቻ ላይ በዩኒቨርሲቲው የስርዓተ ጾታና ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ጴጥሮስ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው ሴት ተማሪዎችን በማብቃት በኩል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

የሴት ተማሪዎችን የትምህርት ተሳትፎ ለማጠናከር ተቋሙ የማጠናከሪያ ትምህርት መርሃ ግብር በመዘርጋት በዚህ ዓመት ብቻ 3ሺህ 666 የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ አከናውኗል፡፡

ሴት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ሊገጥሟቸው የሚችሉ ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮችን ለማቃለል ለ7 ሺህ 431 ተማሪዎች የሕይወት ክህሎት ስልጠናና የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

የገንዘብ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች በኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ዩኒቨርሲቲው 4ሺህ ለሚጠጉ ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በተለይ አዲስ ሴት ተማሪዎች በቆይታቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው አቅም ለመፍታት እንዲችሉ አደረጃጀት በመፍጠር ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ሴቶችን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ  ጾታዊ መድልዎ እንዳይደርስባቸው የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

"የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገሪቱ የጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ የስርአተ ጾታ መድልዎን ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት ማገዝ አለባቸው" ያሉት ደግሞ በምክክር መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አምባሳደር ዶክተር ገነት ዘውዴ ናቸው፡፡

መገናኛ ብዙሀን እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች በማህበረሰቡ ዘንድ ሴቶችን ከወንዶች አሳንሶ የመመልከት የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በመለወጥ በኩል የለውጥ ኃይል መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ሴቶች በኢትዮጵያ ኪነጥበብ የሚታዩበት ሁኔታ፤ በዘርፉ ሴቶች የነበራቸው ሚናና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚዳስሱ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከጀርመን የባህል ማዕከል ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት ባዘጋጀው  መድረክ ላይ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራኖች እንዲሁም በኢትዮጵያ የጀርመንና የቤልጂየም አምባሳደሮችን ጨምሮ ታዋቂ የሀገር ውስጥ የኪነጥበብ ሰዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መጋቢት 2/2010 ሰላምና አንድነታችንን ጠብቀን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ሁላችንም የበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን ስትል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አምባሳደር ወይዘሪት ሩታ አያሌው ተናገረች።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ጋር በጋራ ያዘጋጀው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአምባሳደርነት ውድድር ተካሄዷል።

በውድድሩ ዘጠኙም ክልሎችና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችን የወከሉ እንስቶች ተሳታፊ ነበሩ።

እያንዳንዱ ክልልና የከተማ አስተዳደር ከዚህ በፊት ባካሄዱት ውድድር ከአንድ እስከ ሶስት የወጡ ወይዛዝርት በውድድሩ የተካፈሉ ሲሆን፤ አማራ ክልልን የወከለችው ሩታ አያሌው ውድድሩን በማሸነፍ የግደቡ አምባሳደር ሆናለች።

ሩታ አያሌው ውድድሩን በማሸነፏ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል እንደምትሆንም ተገልጿል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ  ታገል ቀኑብህ እንዳሉት፤ የውድድሩ ዋና ዓላማ ሴቶች በግድቡ ላይ ያላቸውን ሚና ይበልጥ ማጎልበት ነው።

“ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሰፊ ቅስቀሳና መረጃ አንዲሰጡ ለማድረግና በእውቀት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለህበረተሰቡ እንዲሰጡ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው።"ብለዋል፡፡

"በግድቡ ዙሪያ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ቆንጆ ናቸው" ያሉት አቶ ታገል፤ በዚህ ምክንያት ውድድሩ የቁንጅና ከሚለው ይልቅ 'የታለቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አምባሳደርነት ውድድር' የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ጠቁመዋል።

"ውድድሩ ሴቶች ያላቸውን ተፈጥሯዊ ክህሎት ተጠቅመው የግድቡን ሁለንተናዊ ፋይዳ አንዲያስተዋውቁ ይረዳል" ያሉት ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ ናቸው።

የውድድሩ አሸናፊ ወጣት ሩታ አያሌው በበኩሏ ኢትዮጵያዊያን ከሶስት ሺህ ዘመን በላይ ታሪክ ያላቸው ህዝቦች መሆናቸውን አውስታ፤ "አንድነታችንን በመጠበቅ ግድቡን እንጨርሳልን" ስትል ለግድቡ እውን መሆን ያላትን እምነት ገልጻለች።

ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋርም ሆነ በተናጥል በምታደርገው እንቅስቃሴ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ እንደምታስተዋውቅም ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በውድድሩ አንደኛ ለወጣችው የ35 ሺህ ብር ቦንድ ያበረከተ ሲሆን፤ ሁለተኛና ሶስተኛ ለወጡት እንደ ቅደም ተከተላቸው የ25 ሺህ እና 15 ሺህ ብር ቦንድ ሽልማት አበርክቶላቸዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን