አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 10 March 2018

ሽሬእንዳስላሴ መጋቢት 1/2010 የተመቻቸላቸውን የብድር ገንዘብ  በአነስተኛ የንግድ ሥራዎች ላይ በማዋል ኑሮአቸውን እየለወጡ መሆናቸውን በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች ገለጹ።

ሴቶችን በገንዘብ ለማገዝ የተቋቋመው የአደዳይ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የሽሬ እንዳስላሴ ቅርንጫፍ ከ5 ሺህ ለሚበልጡ ሴቶችን የብድር ገንዘብ ተጠቃሚ ማድረጉ ተመልክቷል።

ከተቋሙ ከሦስት ዓመት በፊት 30 ሺህ ብር ብድር መውስዳቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ለምለም ገብረሚካኤል፣ በከተማው ውስጥ በሸቀጣ ሸቀጥ የንግድ ሥራ ተሰማርተው ባገኙት ገቢ ዛሬ ላይ የተሻለ ኑሮ እየመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የወሰዱትን ብድር በመመለስም  ከሚያገኙት ገቢ  ከሃያ ሺህ ብር በላይ ቆጥበዋል።

ወይዘሮ አለምፀሃይ ይህደጎ በበኩላቸው ከሶስት ዓመት በፊት ከተቋሙ 30 ሺህ ብር ብድር ወስደው በእህል ንግድ እንደተሰማሩ አመልክተው ቀደም ሲል ከእጅ ወደ አፍ የነበረውን ኑራቸው አሁን ላይ መሻሻሉን ገልጸዋል፡፡

ሦስት ልጆቻቸውን የትምህርት ወጪያቸውን ችለው በየዓመቱ ከሚያገኙት ገቢ ከአሥር ሺህ ብር በላይ በቁጠባ እንደሚያስቀምጡም አመልክተዋል።

ወጣት ብርዛፍ አሰፋ በሰጠችው አስተያየት በተያዘው ዓመት ከፋይናንስ ተቋሙ በወሰደችው የብድር ገንዘብ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የሴቶች የውበት ሳሉን ከፍታ ኑሯዋን ለማሻሻል ጠንክራ እየሰራች መሆኑን ተናግራለች፡፡

የተቋሙ የሽሬ እንዳስላሴ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ አስገዶም በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት ለ225 ሴቶች ከ4 ሚሊዮን 400ሺህ ብር በላይ በብድር ማከፋላቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ሴቶች ያገኙትን የብድር ገንዘብ ስራ ላይ በማዋል 3ሚሊዮን 200ሺህ ብር መቆጠባቸውንም ጠቅሰዋል።

ቅርንጫፉ ባለፉት አምስት ዓመታት 5ሺህ 100 ሴቶችን ከ27 ሚሊዮን ብር በላይ በብድር በማከፋፈል ተጠቃሚ ማድረጉንም ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

 ጎንደር መጋቢት 1/2010  መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ብድር በመታገዝ በተሰማሩበት የስራ መስክ ከራሳቸው ተርፈው ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን በሰሜን ጎንደር ዞን  አዲአርቃይ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ የወጣቶች ገለፁ።

 በብድር የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ መጀመራቸውንም ወጣቶቹ ተናግረዋል ።

 ወጣት አበበ ገብረዋሃድ እንደገለፀው ስራ ፍለጋ ከሱዳን፣ ግብጽና እስራኤል ተሰዶ ቢቆይም የስደት ህይወት አስቸጋሪ ስለሆነበት ወደ ትውልድ ሀገሩ ተመልሷል ።

 ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ባገኙት  594ሺህ ብር ተዘዋዋሪ ብድር በመታገዝ የጠጠር ማምረቻ አቋቁመው ስራ መጀመራቸውን ተኗግሯል ።

 "ባቋቋምነው የጠጠር ማምረቻ ከራሳችን በተጨማሪ ለሌሎች 23 የአካባቢው ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረናል" ያለው ወጣቱ ከተበደሩት ገንዘብ ውስጥ 11ሺህ ብር መመለሳቸውን ገልጿል።

 "ከዚህ ቀደም ስራ አጥ ነበርኩ፤ አሁን ግን የጠጠር ማምረቻ ማህበሩ በፈጠረልኝ የስራ ዕድል በማሽን ኦፕሬተርነት ተቀጥሬ በወር 4ሺህ ብር ክፍያ እያገኘሁ ነው" ያለው ደግሞ ወጣት ወልዳይ ጉኡሽ ነው፡፡

 ወጣቱ እንዳለው በተሰማረበት የስራ መስክ ተጠቃሚ ሆኗል ።

 የአዲአርቃይ የዳቦ አምራቾች ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት እያያው ተስፋዬ በበኩሉ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት ባገኙት 240ሺህ ብር ብድር ታግዘው ስራ መጀመራቸውን ተናግሯል ።

 "በአሁኑ ወቅት በቀን 700 ዳቦ እያመረትን ለአዲአርቃይ ከተማ ነዋሪዎች እያቀረብን ነው " ብሏል።

 "ከራሳችን ተርፈን ለሌሎች አምስት ወጣቶች ስራ ዕድል ፈጥረናል" ያለው ወጣት እያያው በማህበሩ ስም ከተበደሩት ገንዘብ ውስጥ 14ሺህ ብር  መመለሳቸውን ገልጿል።

 የማህበሩ የዳቦ መጋገሪያ ባህላዊ በመሆኑ ወደ ዘመናዊ ለማሳደግ የሚያስችላቸውን የሊጥ ማቡኪያ ማሽን ለመግዛት ተጨማሪ ብድር እንዲፈቀድላቸው ጥያቄ አቅረበው እየተጠባበቁ መሆናቸውንም ጠቅሳል።

 በቢሮና በቤት ዕቃዎች የእንጨት ስራ ማህበር ከተደራጁ ወጣቶች መካከል ወጣት እንዳለው ምስጋናው እንዳለው  ከሶስት ጓደኞቹ ጋር ተደራጅተው 200ሺህ ብር ብድር አግኘተው ወደ ስራ ገብተዋል ።

 " በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የእንጨት ውጤቶችን አምርተን ለህብረተሰቡና ለመንግስታዊ ተቋማት በሽያጭ እያቀረብን ነው" ያለው ወጣት እንዳለው ከወሰዱት ብድር ውስጥ 14ሺህ ብር መመለሳቸውን ገልጿል።

 የአዲአርቃይ ወረዳ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለምሰገድ ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ለወረዳው ከተመደበው 14 ሚሊዮን ብር ውስጥ 6 ሚሊዮኑ ተለቆ ስራ ላይ መዋሉን ተናግረዋል ።

 "የብድር ገንዘቡ በሀምሳ ኢንተርፕራይዞች ለተደራጁ 58 ወጣቶች ተሰጥቷል" ያሉት ኃላፊው ወጣቶቹ ገንዘቡን በመጠቀም በእንጨት ስራ፣ በዳቦ ጋገራ፣ በጠጠር ማምረቻና በሌሎችም ዕድገት ተኮር በሆኑ የሙያ መስኮች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

 የብድሩ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ውጤታማ የሆኑ 11 ማህበራት 219ሺህ ብር የመጀመሪያ ዙር ብድራቸውን መመለሰቸውንም ጠቁመዋል።

 ኃላፊው እንዳመለከቱት ወደ ስራ ለገቡ ወጣቶችና ማህበራት የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የገበያ ትስስር በመፍጠር ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰሩ ናቸው፡፡

 እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ በቀሪው 8 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር በ46 ማህበራት ለተደራጁ 322 ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብረሀን/ደብረማርቆስ መጋቢት 1/2010 በተያዘው በጋ ወራት በመጀመሪያ ዙር በመስኖ ካለሙት ቀይ ሽንኩርት ሽያጭ እስከ 168 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን  በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የቀወት ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

 በምስራቅ ጎጃም ዞን ደግሞ  አርሶ አደሮች በአነስተኛ መሬት ላይ በገበያ አዋጪ  ሰብል በመስኖ እያለሙ መሆናቸው  ተመልክቷል።

 በቀወት ወረዳ የሌን ቀበሌ  አርሶ አደር ደጀኔ ኃይሉ እንደገለፁት በተያዘው ዓመት በመስኖ በመታገዝ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት ቀይ ሽንኩርት 90 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።

 " ከምርቱ ሽያጭ 168 ሺህ ብር ገቢ አግኝቻለሁ"ብለዋል ።

 በወረዳው በብርብራና ገልገሎ ቀበሌ ወጣት አርሶ አደር መለሰ አበበ እንዳለው  ዘንድሮ  በግማሽ ሄክታር መሬት በመስኖ ካለማው ቀይ ሽንኩርት 96 ኩንታል ምርት ማግኘት ችሏል።

 ከምርት ሽያጭ 143 ሺህ ብር ገቢ ማግኘቱን ጠቅሶ በሌላ ሩብ ሄክታር መሬት 9 ኩንታል ማሽላ ማምረቱንም ጠቁሟል።

 በመደበኛው የዝናብ ወቅት ከሚያመርቱት ሰብል በተጨማሪ በበጋ መስኖ በማልማት ተጨማሪ ገቢ የማግኘት ልምዱን እያጎለበተ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

 እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጿ በተያዘው  ዓመት በቀበሌ ደረጃ በተቋቋመ የግብይት ማዕከል አማካኝነት ምርታቸውን በመሸጣቸው ከዚህ  ቀደም በደላሎች ይደርስባቸው የነበረው አላስፈላጊ ኪሳራ በመቅረቱ ተጠቃሚ ሆነዋል ።

 በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ባለሙያ ወይዘሮ ሉምታየ ዘነበ እንዳመለከቱት   በበጋው ወቅት በመጀመሪያው ዙር በመስኖ ከለማው 86 ሺህ 897 ሄክታር መሬት 3ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ  ኩንታል ምርት ተገኝቷል።

 በልማቱ ከተሳተፉ 245 ሺህ አርሶ አደሮች መካከል 31ሺህ ሴቶች ናቸው።

 አርሶ አደሩ በመስኖ ከሚያለማው  የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተገቢዉን ዋጋ እንዲያገኝ እየተሰራ መሆነ የገለጹት ደግሞ በዞኑ የንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ግብይት ባለሙያ አቶ ተስፋየ ታደሰ ናቸው፡፡ 

" በዚህ ዓመት ልማቱ በስፋት በሚካሄድባቸው ወረዳዎች 19 የግብይት ቡድኖችን በማደራጀት በማዕከላት በውል ግብይት በመፈፀም አምራቹ ከምርቱ እንዲጠቀም ማድረግ ተችሏል" ብለዋል።

 በተያዘው በጋ ወቅት በመስኖ ከለማው አትክልትና ፍራፍሬ 118 ሺህ 178 ኩንታል ምርት በገበያ ትስስር በ113 ሚሊዮን ብር ግብይት መፈፀሙንም ጠቁመዋል።

 በተመሳሳይ በመስርቃ ጎጃም ዞን ደግሞ አርሶ አደሮች በበጋው ወቅት መስኖን በመጠቀም በአነስተኛ ማሳ ላይ በገበያ አዋጪ የሆነ የተለያየ ሰብል በማልማት የተሻለ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆናቸው ተገልጿል።

 በደጀን ወረዳ የየትኑራ ቀበሌ አርሶ አደር ባያብል ምስጋናው በሰጡት አስተያየት በበጋው ወቅት በባህላዊ መንገድ የወንዝ ውሀ በመጥለፍ በግማሽ ሄክታር ማሳ ላይ ቀይ ሽንርት፣ አብሽና ምስር በማልማት ላይ እንደሚገኙ ተናገረዋል።

 " ከምርት ሽያጭ እስከ 60 ሺህ ብር አገኛለሁ ብየ እጠብቃለሁ" ያሉት አርሶ አደሩ ቀደም ባሉት ጊዜያት በመስኖ ካለሙት ምርት ሽያጭ ካገኙት ገቢ ውስጥ 80 ሺህ ብር መቆጠባቸውን አመልክተዋል፡፡

 ኩሬ በመቆፈር በአነስተኛ መሬት እያለሙ ካለው የጓሮ አትክልትና ሰብል ምርት ሽያጭ የተሻለ ገቢ አገኛለሁ ብለው እየሰሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በወረዳው የገልገሌ ቀበሌ አርሶአደር አላምረው ጫኔ ናቸው፡፡ 

 በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ ልማት ባለሙያ አቶ አያሌው ገሌ እንዳሉተ አርሶ አደሩ የከርሰና የገጸ ምድር ውሃን በመጠቀም በመጀመሪያው ዙር ካለማው መሬት 1ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ  ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል።

 " በቅመማቅመም፣ ስራስርና የጓሮ አትክልት  ከተሸፈነው 127 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 15 ሺህ ሄክታር ላይ ቀድሞ የደረሰ ምርት ተሰብስቧል"

ብለዋል ።

 በልማቱ 200 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ጠቁመው  ከልማቱ 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል ።

 በዞኑ ባለፈው ዓመት በመስኖ ከለማው 117 ሺህ ሄክታር መሬት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል  ምርት መገኘቱም ተመልክቷል።

Published in ኢኮኖሚ

ድሬደዋ መጋቢት1/2010 የከተሞች የምግብ ዋስትና  መርሃ ግብር ኑሯቸውን ለማሻሻል እየረዳቸው መሆኑን በድሬዳዋ አስተዳደር አስተያየታቸውን የሰጡ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

በድሬደዋ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎቹ መካከል ወይዘሮ  ሃምዲያ መሐመድ ለኢዜአ እንዳሉት መንግስት የፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማ አረንጓዴ ልማት ስራ ተሰማርተው በሚያገኙት ገንዘብ  ይቸግራቸው የነበረው የቤት ክራይና የልጆቻቸውን  ወጪ በመሸፈን ኑሯቸውን ለማሻሻል እየረዳቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስድስት ልጆች እናት እንደሆኑ የተናገሩት ወይዘሮ  ኑሪያ ሁሴን በበኩላቸው መንግስት ለደሃ በማሰብ ያደረገላቸው ድጋፍ ኑሮቸውን ለመለወጥ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አመልክተዋል፡፡

በአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ላይ ተሰማርተው በሚያገኙት ገንዘብ ኑሯቸው እየተሻሻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ልብስ በማጠብ ፣እንጨት ከጋራ በመሰብሰብ በሚያገኙት ጥቂት ገንዘብ ኑሯቸውን ለመምራት ተቸግረው እንደነበረ አስታውሰው በመርሃ ግብሩ ከታቀፉ ወዲህ ልጆቻቸውን ጭምር ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ከሚያገኙት ገቢ በሚቆጥቡት ገንዘብ  ተደራጅተው ወደ ተሻለ ገቢ ማስገኛ ሥራ ለመሰማራት እንደሚፈልጉ ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ ለዚህም  ካለው የኑሮ ውድነት ጋር የሚጣጣም ክፍያ እንዲደረግላቸውም ጠቁመዋል፡፡             

በፌደራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የምግብ ዋስትና ዘርፍ ተጠባባቂ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን አሰፋ " ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር በ11 ከተሞ የተጀመረው መርሃ ግብር ከ190ሺ በላይ የደሃ ደሃ ዜጎችን ተጠቃሚ አድርጓል "ብለዋል፡፡

ከነዚህ መካከል 68 በመቶ  ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

እነዚህ ዜጎች በከተማ ግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት ፣ በከተማ ፅዳትና ውበት፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ፣ በመሠረተ ልማት ተሰማርተው ተጠቃሚ ከሆኑባቸው ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪ ለችግር የተጋለጡና የመስራት አቅም የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም  በቀጥታ በመደገፍ እንዲጠቀሙ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

እስካሁን በተከናወኑት ስራዎች የህብረተሰቡን ኑሮ ከማሻሻል ባለፈ  ከተሞችን ምቹና ፅዱ ማድረግና ከጎርፍ ሥጋት መቀነስ እንደሚቻል ጅምር  ተስፋ የተስተዋለባቸው መሆኑን አቶ ሰሎሞን ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ጅምር ተግባራት ለማጠናከር  250ሺ  ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማታዊ ሴፍትኔት የልማት ሥራዎች በሁለት ቢሊዮን ብር በጀት ዘንድሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ ሰሎሞን አመልክተዋል፡፡

የተጠቃሚዎች ምልመላና የመለየት ስራ  እየተጠናቀቀ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የነዋሪዎችን የክፍያ መጠን ለማሻሻል የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው  ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ የደህንነትና የሥራ ቁሶች በግዥ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በሀገሪቱ 11 ከተሞች ለተጀመረው  የምግብ ዋስትና  መርሃ ግብር ማካሄጃ  ከተመደበው ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት 150 ሚሊዮን ዶላር ሲሸፈን ከአለም ባንክ ደግሞ  300 ሚሊዮን  ዶላር በብድር የተገኘ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

መቀሌ መጋቢት 1/2010 የመቀሌ ዩኒቨርስቲ የአይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በቅድመና ድህረ ምረቃ መርሀ ግብር በተለያዩ የህክምና ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 362 ባለሙያዎች ዛሬ አስመረቀ።

ኮሌጁ ካስመረቃቸው መካከል 157ቱ በመጀመሪያ ዲግሪ በህክምና ዶክተርነት የሰለጠኑ ሲሆኑ ከነዚሁ ውስጥ 50ዎቹ ሴቶች ናቸው ።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ክንደያ ገብረህይወት በምረቃው ላይ እንደተናገሩት ኮሌጁ በመጀመሪያ ዲግሪ ካስመረቃቸው የህክምና ዶክተሮች በተጨማሪ በተለያዩ የህክምና አይነቶች 38 ስፔሻሊስት ሀኪሞችም ይገኙበታል።

ከነዚሁ ውስጥም ሁለቱ በሽንት ቱቦ፣ ፍኛና ኩላሊት ህክምና በሳብ ስፔሻሊቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመረቁ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የጤና ዘርፎች 167 ባለሙያዎች በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሀኑ ምሩቃን የሙያውን ስነ ምግባር በማክበር ሀገሪቱ በጤና ዘርፍ ላስቀመጠችው ዘላቂ ግብ ሰኬታማነት ጠንክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል ።

ሚኒስትሩ አያይዘው እንዳሉት የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ከተያዙ የትራንስፎርሜሽን አጀንዳዎች አንዱ የመረጃ አብዮት ነው።

ይህንን በስራ ለመተርጎም በአገር አቀፍ ደረጃ በ240 ወረዳዎች፣በ1ሺህ 875 ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ለኤሌክትሮኒክስ የህክምና መረጃ ምዝገባና ክትትል በሚያመች መንገድ የመረጃ መርብ እየተዘረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል።

በዘርፉ ተጨማሪ ስራዎችን ለማከናወንና የመረጃ ቋቶችን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው የመረጃ አብዮት ዋነኛ አላማ የጤና ስርዓቱን ከማዘመን ባለፈ መረጃን መሰረት ያደረጉ የጤና መርሀ-ግብሮችን መንደፍ  እንደሆነ ተናግረዋል።

ከተመራቂ ሀኪሞች መካከል ዶክተር ጎይተኦም ካህሳይ እንደገለጸው በሙያው ስነምግባር እና በገባው ቃል ኪዳን መሰረት ሁሉንም ወገኑን በእኩልነት ለማገልገል ተዘጋጅቷል።

ሌላዋ ወጣት ተመራቂ ዶክተር ሚሻ አባይነህ በበኩሏ "የህክምና ሙያ ዘር ሃይማኖት ቋንቋ እና ሌሎችም ነገሮች ሳይገድቡት ለሁሉም እኩል አገልግሎት መስጠትን የግድ የሚል ነው" ብላለች።

ለሙያዋ እና ለህብረተሰቡ ታማኝ በመሆንም በስራ ዘመኗ የሚጠበቅባትን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ማድረጓንም ተናግራለች።

Published in ማህበራዊ

ለይኩን አሰፋ /ኢዜአ/

መከላከልን መሰረት ያደረገው የኢትዮጵያ ጤና ፖሊሲ ላለፉት ሁለት አሥር ዓመታት አበረታች ውጤቶች ተገኝቶበታል። የተገኘውን ስኬት ለማጠናከርም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የትምህርት ቤት ጤናና ስርዓተ ምግብ መርሀ ግብር በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። የመርሀ ግብሩ ዋነኛ ዓላማ በሽታን በመከላከሉ ረገድ ተማሪዎች ዘላቂ የባህሪ ለውጥ እንዲያመጡ ለማገዝ ሲሆን የተለያዩ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለይቶ ህክምና መስጠትንም ያካትታል።     

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ይፍሩ ብርሃን መርሀ ግብሩን ለማስጀመር በተደረገው ዝግጅትና በሚኖረው ጠቀሜታ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።             

ኢዜአ-በአገር አቀፍ ደረጃ የትምህርት ቤት ጤናና የስርዓተ ምግብ መርሃ ግብር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፤ በአሁኑ ወቅት ምን ደረጃ ላይ ነው?  

ፕሮፌሰር ይፍሩ- የትምህርት ቤት ጤናና ስርዓተ ምግብ ፕሮግራም በአጠቃላይ በአገሪቷ እንዲተገበር ነው የታቀደው። በአገራችን የትምህርት ቤት ጤና አገልግሎት በክሊኒክ ደረጃ በተወሰኑ አካባቢዎች ሲሰጥ እንደነበር ይታወቃል።ይህ አዲስ ያዘጋጀነው የትምህርት ቤት ጤናና ስርዓተ ምግብ መርሀ ግብር ግን በጣም ሰፊ ነው፤ አሥር  ማዕቀፎችም ያሉት ነው። በአጠቃላይ በአገርም ይሁን በክልል ደረጃ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበታል። በትምህርት ሚኒስቴርና ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል። ይህ ብዙ ሰው የወደደው መርሃ ግብር በሽታን በመከላከልና የጤና ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ለይቶ በማከም ላይ ትኩረት ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ግን ስለ ራሳቸው ጤና የሚያውቁ፤ የራሳቸውን ጤና እራሳቸው የሚጠብቁና ራሳቸውን ከበሽታ የሚከላከሉ ትውልድ በመፍጠር ላይ ትልቅ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ፤ በጤናው ላይ ትልቅ ግንዛቤ የያዘ ትውልድ መፍጠር ነው የዚህ መርሀ ግብር ዋና ዓላማ። 

የመርሀ ግብሩ አጠቃላይ የዶክመንት ማዕቀፍ ተዘጋጅቷል፤ተገምግሟል፤ እሱ እያለቀ ነው። ከዚያ በመቀጠል ወደየክልሎቹ አውርደነው በተለይ ሙከራ የምናደርግባቸው ትግራይ፣አማራ፣ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ላይ የሙከራ ትግበራ እያካሄድን ነው ያለነው። በተለይ በትግራይና አማራ ፈጥኖ ሄዷል ባለሙያዎች እየሰለጠኑ ነው ያሉት። ለትምህርት ቤት አመራር አባላት መረጃ እየተሰጠ ነው፤ መርሃ ግብሩን የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው ያለው። በአጠቃላይ በሙከራ ጊዜው የሚጠበቀው ከ 400 እስከ 500 ትምህርት ቤቶችን ማካተት ነው። ይህንን ካካተትንና የዚህን ውጤት ካየን በኋላ በአገር አቀፍ ደረጃ ትግበራውን እንጀምራለን።

በትግበራው ቅድመ አንደኛ ደረጃ የሚባሉትን ጭምር ከያዝናቸው 37 ሚሊዮን የሚሆኑ ተማሪዎች ናቸው በትምህርት ሚኒስቴር ተመዝግበው ያሉት። ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ ያለውን ብቻ ከተመለከትን ደግሞ ወደ 25 ሚሊዮን የሚሆነው ሕዝባችን ትምህርት ቤት ነው። ሁሉንም ከወስድናቸው አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ሕዝባችን ትምህርት ቤት ነው ማለት ነው። የግልም ትምህርት ቤት ይሁን የመንግሥት ትምህርት ቤት ሁሉንም ለመድረስ ነው እኛ እቅዳችን በተያዘው እቅድ መሰረት በ 5 ዓመት ውስጥ ሁሉንም ትምህርት ቤት እንደርሳለን።

ኢዜአ -መርሃ ግብሩ ምን ምን ጉዳዮችን ነው ያቀፈው ተማሪዎችስ እንዴት ነው ተጠቃሚ የሚሆኑት?      

ፕሮፌሰር ይፍሩ- ትምህርት ቤቶች ሊኖራቸው ከሚያስፈልጉ ነገሮች አንዱ እንደ ክሊኒክ የሚያገለግል የጤና ማዕከል ነው። የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት የተለያየ የጤና ችግር ያለባቸውና የሌለባቸው ተማሪዎች የሚለዩት በነዚህ የጤና ማእከላት ወይም ክሊኒኮች ነው። አብዛኛው አገልግሎት የሚሰጠው በትምህርት ቤት ጤና ማዕከላት በመሆኑ እጅግ አስፈላጊ ናቸው። እስካሁን ወደ 8 ሺህ ትምህርት ቤቶች አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል በቂ ቦታ እንዳላቸው ለይተናል። ሌሎች ትምህርት ቤቶች ግን አገልግሎቱ የሚሰጥበት ቦታ ያስፈልጋቸዋል። እነሱም እንዲያዘጋጁ እየተደረገ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ በጣም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ ካለ ግን የሚያስፈልገውን ገንዘብ እያፈላለግን  ግንባታም ጭምር በየ ትምህርት ቤቶቹ እናካሂዳለን። በዚህ መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ቦታ እንዲዳረስ እቅድ ተይዟል።       

የመርሀ ግብሩን አሥር ማዕቀፎች በአጠቃላይ በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን። አንደኛው የጤና ችግር ያለባቸውን ለይቶ ማከም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መከላከልና ግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ ያተኮረ ነው። የመጀመሪያው አስፈላጊ አገልግሎቶችን በየትምህርት ቤቱ ከማቅረብ ጀምሮ ህክምናውን እስከመስጠት ያደርሳል። በእውቀት ላይ የተመሰረተ የሄልዝ ፕሮሞሽን ኤንድ ፕሪቬንሽን በሚል አንድ ክንፍ አለ።  ሁለተኛውና በመከላከልና ጤና ማበልጸግ ላይ የሚሰራውን በምናይበት ጊዜ ትኩረት ከምናደርግባቸው ውስጥ አንዱ በወጣትነት እድሜ ላይ ያሉ ተማሪዎች ለጤናቸው አደጋ የሆኑ ወይም ጤናቸው ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ነገሮችን እንዴት ማወቅ እንደሚችሉ ነው። ቀድመው ማወቅ መቻላቸው  ብዙ የጤና ችግር ሊያመጡ የሚችሉ የጤና ጠንቆችን ለመከላከል የሚያስችል አቅም ይፈጥራል። ስለሆነም በቀላሉ ራሳቸውን ከበሽታ መከላከል የሚችሉበትን የህይወት ክህሎት የሚያዳብሩበት፣ በሽታን እንዴት መከላከል እንደሚቻል በተግባር በትምህርት ቤት እንዳሉ የሚለማመዱበትን ያካተተ ነው።  

በሽታን አስቀድሞ መከላከል  

ፕሮፌሰር ይፍሩ- በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ ተማሪዎችን ከሚያጠቃው ውስጥ አንዱ ትራኮማ/ዓይን ማዝ/ ነው። አገራችን በዓለም ካለው  የትራኮማ ብዛት አጠቃላይ 43 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ ነው። ይሄ ትራኮማ ደግሞ የሚከሰተው በቀላሉ ዓይንና ፊትን በውኃ ባለመታጠብ ነው። በውኃ ቢታጠቡ ይህን በሽታ ሙሉ በሙሉ መከላከል ይቻላል። ስለዚህ በየትምህርት ቤቱ ውኃ እንዲኖር በማድረግ ተማሪዎች ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርት ከመጀመራቸው በፊትና ትምህርት ጨርሰው ሲወጡ እጅና ፊታቸውን መታጠብ ባህል እንዲያደርጉ፤ ይህንንም ወደ ቤተሰቦቻቸው ሲወስዱት በየ ቤቱ ባህል እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው።  እጅና ፊትን መታጠብ ማለት ትራኮማን ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ብዙ የባክቴሪያ በሽታዎችን፣ብዙ ዓይነት የቫይረስ በሽታዎችን መከላከልም ጭምር ስለሆነ። በእጅ የሚተላለፉ በሽታዎች በርካታ በመሆናቸው እነዚህን በሽታዎች ለመከላከል እጅና ፊትን መታጠብን  እንዲለማመዱና ባህል እንዲያደርጉት ማድረግ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው።

በተለይ እድሜያቸው ከ 5 እስከ 10 የሆኑ ህጻናት ላይ የሚሰራ ስራ ውጤታማነቱ ከፍተኛ ነው። በዚህ እድሜ የሚያገኙት ግንዛቤና እውቀት ወደ ፊት በአፍላ ወጣትነትና በአዋቂነት ዘመናቸው ሁሉ ጤናማ ይህወት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ስለዚህ በዚህ እድሜ ላይ እያሉ እንዲያውቁ የሚፈለገው ነገር ስለ ጾታዊ ግንኙነትና ስለሚያመጣው አደጋ፣ በተለይ ከ 20 ዓመት በፊት ግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ከአባለዘር በሽታ አኳያ፣ ከካንሰር፣ ከአላስፈላጊ እርግዝናና ውርጃ እንዲሁም ከሌሎችም ችግሮች አኳያ የሚኖሩ ተጽእኖዎችን ቀድመው እንዲያውቁ ከተደረጉ ሲፈጽሟቸው አይገኙም።  

በአገራችን ከፍተኛ ችግር እየሆነ የመጣው ሌላው ጉዳይ የዕጽ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ነው። አልኮል፣ትንባሆ፣ሽሻና ሀሺሽ  በጤና ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ወጣቶቹ ቀድመው  እንዲያውቁት በማድረግ ወደዚያ እንዳይገቡ ማድረግ አንዱ ዓላማ ነው። በአሁኑ ሰዓት በተለይ በከተሞች አካባቢ የአዕምሮ ህመምተኞች በብዛት እየተመዘገቡ ነው፤ ብዙ ሆስፒታሎች ላይ ብዛት ያላቸው የአዕምሮ ህመምተኞች እየመጡ ነው። ህመምተኞቹ ወደኋላ ታሪካቸው ሲታይ አብዛኞቹ የነዚህ እጾች ተጠቃሚዎች ናቸው። በሌላው ዓለምም ይህ ነገር ደጋግመን የምንሰማው ነው። ብዙዎቹ እራሳቸውን የሚያጠፉት የዕጽ ተጠቃሚዎች ናቸው። እኛ አገርም መረጃው የለም  እንጂ ይህ ነገር ከባድ ችግር ነው። ስለዚህ እጽ መጠቀም ሊያደርስ የሚችለውን የጤና ችግር በህይወታቸው ሊያመጣ የሚችለውን ቀውስ እንዲያውቁ ማድረግ ሌላው ጉዳይ ነው።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል   

ፕሮፌሰር ይፍሩ- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አሁን በከተሞች አካባቢ እንደ ወረርሽኝ እየተከሰቱ ነው። እንደ ስኳር፣ ኩላሊት፣ የልብ በሽታ፣ የደም ስር በሽታ፣ ሪህ  አይነት በሽታዎች አብዛኞቹ ጤናማ የአመጋገብ ስርአት ካለመከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ካለ ማድረግ፣ የአካባቢ ንጽህና ካለ መጠበቅና ጭንቀት ከማብዛት የሚመጡ ናቸው። ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ማስተካከል ከተቻለ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል ይቻላል። በሽታዎች አንዱ ከአንዱ ጋር የተያያዙ ናቸው። በተለይ የስኳር በሽታ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው። አሁን  አገራችን ካላት ሕዝብ  ቁጥር ጋር ሲታይ ከሰሀራ በታች ካሉት አገሮች መሪነቱን ይዛ ነው ያለችው። አብዛኛው የኛ ሕዝብ ይህን ያህል ወፍራም ሆኖ አይደለም፤ ነገር ግን አንዱ ትልቅ ችግር የዓመጋገብ ስርዓታችን ነው። ሕዝባችን  የዓመጋገብ ሥርዓቱ በተለይ በከተሞች አካባቢ የፋብሪካ ወጤቶች ላይ ብዙ ትኩረት ይደረጋል፤ የተፈጥሮ ምግቦችን የመተው ነገሮች እየበዙ መጥተዋል። ከዚያም አልፎ በተለይ በከተሞች አካባቢ እንቅስቃሴ ከማድረግ ይልቅ ብዙ ሰው ከቤት ወደ መኪና ከመኪና ወደ ቤት ባህል እየሆነ ነው። ይሄም አንዱ ሌላው ችግር ነው። ለኬሚካሎች መብዛት እየተጋለጥን ነው። ስለሆነም ተማሪዎች ስለነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማወቅ አለባቸው። ጤናማ አመጋገብ ምንድ ነው? ፣ጤናማ ህይወት ምንድ ነው? አካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል ማድረግ ምንድነው፤ የሚያመጣው ጠቀሜታስ? የሚሉትን ሁሉ እንዲያውቁ ይደረጋል። እዚህ ላይ የሚሰራው ሥራ በተግባር ትምህርቶችም ጭምር የተደገፈ እንዲሆን ይደረጋል። 

ችግር ያለባቸውን ለይቶ አገልግሎት መስጠት   

ፕሮፌሰር ይፍሩ- አገራችን በብዙ ቦታ ከምግብ አለመመጣጠን ጋር ተያይዞ የመቀጨጭና የዕድገት ማነስ፣ የመቀንጨር፣  እንዲሁም የደም ማነስ በልጆች እና በእናቶች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይታያል። ማይክሮና ማክሮ ኒውትረንት የምንላቸው አሉ። የሁለቱ አይነት የጤና ችግሮች ይስተዋላሉ። ስለዚህ ከአመጋገብ ጋር  በተያያዘ የተከሰቱ የጤና ችግሮችን እንለያለን፤ እኛ ስንለይ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ የመመገብ ስርዓቱን እየሄደበት ነው በሰፊው። እኛ ማንኛው ልጅ ምን አይነት የጤና ችግር ወይም የስርዓተ ምግብ መጓደል አለበት የሚለውን ስንለይ እነሱ ደግሞ ወደ አገልግሎት መስጠት ይሄዳሉ ማለት ነው።

ሌላኛው አገራችን ላይ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘውና ብዙ ልጆችን የሚያጠቃው የተለያዩ ጥገኛ ተዋህሲያን አንጀት ውስጥ መገኘት ነው። እነዚህ ጥገኛ ተዋህሲያን ህጻናትን ለመቀንጨር የመዳረግ አቅማቸው እጅግ ከፍተኛ ነው። በብዛት የሚታወቁት እንደ ወስፋት፣መንጠቆ ትል፣ ብልሀርዚያ የመሳሰሉትን በመለየት እነዚህን የሚያጠፋ መድሃኒቶችን እንሰጣቸዋለን። በዚህም የሚመገቡት ምግብ ወደ ሰውነታቸው እንዲሄድና እድገታቸውም እየተስተካለ ሆኖ ትምህርት የመቀበል ብቃታቸው እየጨመረ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ የማብቃት ሥራ የምንሰራበት ነው። 

ሴቶች ደግሞ ከሥነ ተዋልዶ ጋር የተያያዙ ሰፊ የጤና ችግሮች አሉባቸው። ቀላል ምሳሌ ብጠቅስ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ብዙ ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት የሚቀሩበት ባስ ሲልም ትምህርት የሚያቋርጡበት። ይህ ግን በቀላሉ የሚታከምና መስተካከል የሚችል ነው። እዚያው ትምህርት ቤት ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ጤናቸው እንዲጠበቅና ትምህርታቸውን መከታተል እንዲችሉ ማድረግ ስለሚቻል ይህንን ሁሉ ያካተተ አገልግሎት እንሰጣለን። ያልተፈለጉ እርግዝናዎች እንዳይከሰቱ በተመሳሳይ የሚሰጡ አገልግሎቶች ይኖራሉ።

ከዚህ ጋር አብሮ ሊጠቀስ የሚገባው እስካሁን ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን ኤች አይ ቪ እንዳለባቸው ይገመታል። አብዛኞቹ ደግሞ በወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ናቸው። አብዛኞቹ ወጣቶች ደግሞ ትምህርት ቤት ነው ያሉት። ኤች አይ ቪን ለመከላከል ከተፈለገ ትልቅ ስራ መሰራት ያለበት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው። ስለዚህ ሁሉንም ተማሪዎች በተለይ ዕድሜያቸው አፍላ ወጣትና ከዛ በላይ የሆኑ ተማሪዎችን እንዲመረመሩ በማድረግ ችግሩ ያለባቸው ተማሪዎች ካሉ  የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ አምራችና ጤናማ ዜጋ ሆነው እንዲቀጥሉ የኤች አይቪ ምርመራ በሰፊው እናካሂዳለን።

ክትባትን በትምህርት ቤት ተደራሽ ማድረግን በተመለከተ 

ፕሮፈሰር ይፍሩ -ከክትባት ጋር በተያዘዘ ክትባት በአገራችን አሁን እየተሰጠ ያለው በየጤና ጣቢያዎች፣በጤና ኬላዎች፣በተወሰኑ ሆስፒታሎች ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ቤት ለቤት የሚሰጥበት ሁኔታም አለ። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ከክረምት ውጪ ልጆቹ ያሉት  ትምህርት ቤት ነው። ሌላው ነገር ደግሞ  እድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ላሉ ህጻናት የሚሰጡትን ክትባቶች ሁሉም አያገኙም።  ብዙ ክትባቱን ያላገኙ ልጆች እንደነበሩ በቅርብ የተሰራው አገር አቀፍ ጥናት አሳይቷል። እነዚህን ክትባቶች ግን እድሜያቸው ከአንድ ዓመት ካለፈም በኋላ  እስከ 18 ዓመት ድረስ መስጠት ይቻላል። ስለዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ አንድም ልጅ አናጣም ማለት ነው። አንድም ልጅ ሳይከተብ የሚያድግ ወይም ደግሞ ክትባት የሚያልፈው ልጅ አይኖርም ማለት ነው ይሄ አንዱ መርሀ ግብር ነው

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች በየ እድሜያቸው የማጅራት ገትር ፣የመንጋጋ ቆልፍና ሌሎችም ክትባቶች በትምህርት ቤት እያሉ መስጠት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በጣም ውጤታማ ነው የሚያደርገን ልጆችም ክትባት እንዳያመልጣቸው ይሄ ጥሩ መርሀ ግብር ነው።

ሌላው ህጻናት በተለይ በገጠሩ አካባቢ  ብዙ ጊዜ ወደ ሀኪም ቤት የሚወሰዱት ምናልባት ከትምህርት ቤት የሚያስቀራቸው ህመም ሲያጋጥማቸውና አልጋ ሲይዙ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ሌሎች የጤና ችግሮች አሉ፤ አልጋም ሳያሲዙ እየጎዷቸው ትምህርታቸውን እንዳይማሩ የሚያደርጋቸው። ለዕድገታቸውም ለትምህርት ቅበላቸውም ብዙ ጉዳት የሚያደርሱ የጤና ችግሮች አሉ። እነዚህን የጤና ችግሮች በቀላሉ በመለየት እዛው ህክምና መስጠት ይገባል። አንድ ምሳሌ ብጠቅስ አሁን በአገራችን ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ የልብ በሽተኞች አሉ። አብዛኞቹ በሽተኞች ከጉሮሮ ላይ ከሚፈጠር ኢንፌክሽን ወደ ልብ የሚሄድና ልብ ላይ ጉዳት በማድረሱ የሚመጣ ነው። ይሄንን ኢንፌክሽን ግን በቀላሉ በመድሃኒት መከላከል ይቻላል። እነዚህ ልጆች ጉንፋን ነው፤ ቀላል ነው ችግሩ እየተባለ በወቅቱ አገልግሎት ሳያገኙ የልብ ችግር ተጠቂ የሚሆኑት። ሌሎች የቆዳ ላይ ኢንፌክሽኖች የሚፈጠሩ አሉ እነዚህ ኢንፌክሽኖች ቀላል ነው እየተባለ ግን ያ ኢንፌክሽን እስከ ኩላሊት ይሄድና ኩላሊት እንዳይሰራ እስከ ማድረግ ድረስ ችግር ሊያደርስ ይችላል።

የማየትና የመስማት ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች ልየታ  

ፕሮፈሰር ይፍሩ - በየገጠሩ ትምህርት ቤት ሲኬድ አንድም መነጽር ያደረገ ልጅ አይታይም። ያ ማለት ግን ሁሉም የማየት ችግር የለበትም ማለት አይደለም። በመነጽር መስተካከል የሚችሉ የእይታ ችግር ያለባቸው እጅግ በጣም ብዙ ልጆች በጊዜ ሊደረስላቸው ባለመቻሉ ከትምህርት ቤት ይቀራሉ፤ ወይ ደግሞ የመጀመሪያውን ወንበር ለማግኘት ሲታገሉ ይታያል። በዚህም ትምህርታቸው ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ስለዚህ ሁሉንም ተማሪ እንለያለን፤ የማየት ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ካሉ እይታቸውን የሚያስተካክል መነጽር እንዲደርሳቸው ለማድረግና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ለማድረግ መሥራት የመርሀ ግብሩ ሌላው ዓላማ ነው። 

የመስማት ችግር ያለባቸው ልጆችም በየትምህርት ቤቱ አሉ። የመስማት ችግር ያለበት ልጅ ደግሞ ትምህርት መከታተል እንዴት አስቸጋሪ ሊሆንበት እንደሚችል መገመት ይቻላል ። ስለዚህ የመስማት ችግር ያለበት ካለ፣ የማየት ችግር ያለበት ካለ፣የተለያዩ ኢንፌክሽኖች ወይም ደግሞ ከበድ ያሉ እንደ ቲቢ፣ወባና ሌሎችም ችግሮች ያሉባቸውን ልጆች  በመለየት በያሉበት ትምህርት ቤት ጤና ማእከል ውስጥ  ማከምና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ ማድረግ ይቻላል። መርሀ ግብሩ ከዚህ አኳያ በጣም ሰፊ ነው። የወደፊቱን ትውልድ መቅረጽና ጤናማ ህይወት እንዲኖረው ማድረግ ቀላል ነገር አይደለም።

የትምህርት ቤት ጤናና ስርዓተ ምግብ መርሀ ግብር አንዱ ጥሩ ነገር፤ አብዛኞቹ ቀድሞ በተለያዩ ቦታ ተበታትነው ያሉ አገልግሎቶች በነጻ የሚሰጡ መሆናቸውና ትምህርት ቤትም አሁን አገልግሎቱን ስንጀምር በነጻ የሚሰጥ መሆኑ ነው። ስለዚህ በነጻ መሆኑ በራሱ ብዙዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል። እንደ አገር ደግሞ  ጤናማ፣ ለአገር የሚያስብ፣ አምራች የሆነ ትውልድ እንደመፍጠር ጥሩ ነገር የለም። ስለዚህ ከዚህ አኳያ የአጭር ጊዜና የረዥም ጊዜ ግብ ይዞ የተነሳ መርሀ ግብር ነው።

ኢዜአ-መርሃ ግብሩ ሙሉ በሙሉ መቼ ተግባራዊ ይሆናል?  

ፕሮፈሰር ይፍሩ - በአጠቃላይ ከ500 ትምህርት ቤቶች በማይበልጡት ላይ ነው በሙከራ ደረጃ እንዲተገበር እያሰብን ያለነው። የነሱን ውጤት እናይና ከዚያ እያሰፋን እንሄዳለን በትልቁ እንጀምራለን ማለት ነው። የማሰልጠኛ ቁሳቁስ አሉ፤ እነሱንም እየሞከርን ነው ያለነው፤ የተለያዩ መዛግብት አሉ እነሱን እየሞከርን ነው ያለነው። የትምህርት ቤት ጤናና ስርዓተ ምግብ መርሃ ግብር አዲስና ሰፊ ስራ የሚጠይቅ ስለሆነ ያንን ወደ ተግባር ስናዞረው በፊት ኀብረተሰቡ ውስጥ ይሰራ የነበረ፤ ጤና ተቋም ውስጥ ይሰሩ የነበሩ ነገሮችን አቀናጅተናቸዋል፤ ወደ አንድ አምጥተናቸዋል። ስለዚህ  ወደ ትልቁ የአገር አቀፍ ሙሉ ትግበራ ከመሄዳችን በፊት የዚህን ውጤት ማየት ይገባል። በኛ እቅድ መሰረት መርሀ ግብሩ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2019 በትልቁ እንጀምራለን ብለን ነው የምናስበው።   

ኢዜአ የመርሀ ግብሩ ማስፈጸሚያ በጀት ከየት ነው የሚመጣው? 

ፕሮፈሰር ይፍሩ -መርሀ ግብሩ በመንግሥት ደረጃ የተለየ በጀት የተያዘለት አይደለም።አንደኛ አብዛኞቹ ያሉ ፕሮግራሞችን ነው አቀናጅተን ያመጣናቸው፤ ሁለተኛ ለዚህ ፍላጎት ያሳደሩ አጋር ድርጅቶች አሉ። ፕሮግራሙን ወደውታል ከነሱ የተወሰኑ ድጋፎች ያገኘናቸው አሉ። የግል ፊል አንትሮፒ ድጋፍ የሚሰጡ አንድ ሚሊዮን ዶላር ሰጥተውናል። በሂደት ሌሎች አሉ መስመር ላይ ያሉ ማለት ነው ከመንግሥትም ከአጋር ድርጅቶችም ብዙ ነገር ይጠበቃል።

ኢዜአ-መርሀ ግብሩ የታሰበውን ውጤት እንዲያመጣ ከጉዳዩ ተዋንያኖች ምን ይጠበቃል? 

ፕሮፈሰር ይፍሩ -ይሄን መርሀ ግብር የምንተገበረው ክትምህርት ሚኒስቴር ጋር  በመተባበር ነው። ወደ ታችም ስናወርደው ትምህርት ቤቶች በዚህ ፕሮግራም ላይ መተባበር ይጠበቅባቸዋል። መርሀ ግብሩን በባለቤትነት መያዝን ይጠይቃል። ለየትምህርት ቤቶቹ ቅርበት ያለው የወረዳ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ይህንን መርሀ ግብር በባለቤትነት የሚያስኬደው ይሆናል። ሁሉም የተማሪዎች የጤና ችግሮች እዚያው ትምህርት ቤት ጤና ጣቢያ ውስጥ ይፈታሉ ማለት አይደለም፤ አንዳንዶቹ ቅርብ ወዳለ ጤናጣቢያና ሆስፒታል መላክን ይጠይቃሉ። ስለዚህ እነዚያ ትምህርት ቤቶችና በአካባቢው ያሉ ጤና ተቋማት መተባበርን ይጠይቃል። 

በየትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ያሉ አስተዳደር ሰራተኞች፣ መምህራንና ተማሪዎች ሊተባበሩ ይገባል። በተለይ የጤና ማበልጸግ ሥራዎችን አብረን ነው የምንሰራቸው። መምህራን ለተማሪዎች አርአያ ሆነው እንዲሰሩ ይጠበቃል፤ ምክንያቱም ከ5 እስከ 10 ዓመት ባለው እድሜ ውስጥ ተማሪዎች አዕምሯቸው ውስጥ የተቀረጸ ነገር በይህወት ዘመናቸው አብሯቸው ነው የሚኖረው። በቃል ከሚነገራቸው የሚያዩትን ነው የሚተገብሩት። ስለዚህ እያዩት የሚያጨስ አስተማሪ ካለ ስህተት ነው አጠቃላይ የመምህሩ ባህሪ ተማሪው ላይ ይገለጻል ስለዚህ መምህራን ለተማሪዎች ምሳሌ መሆን ይኖርባቸዋል። 

ኢዜአ-የመርሀ ግብሩ ቀጣይነት እንዴት ይታያል? 

ፕሮፈሰር ይፍሩ-ይሄ መርሀ ግብር ስሙ እንደሚለው ፕሮጀክት አይደለም። በሆነ ጊዜ ተተግብሮ በሆነ ጊዜ የሚቆም አይደለም። ትውልድ እንደሚቀጥለው ሁሉ አዲስ ትውልድ ይመጣል። ትምህርት ቤት ደግሞ ያው አዲስ ተማሪ  ሁል ጊዜ ነው የሚመጣው። ስለሆነም የአገልግሎቱ  ዘላቂነት ያለው ነው፤ አይቆምም። አሁን እኛ ሦስተኛ እግር ነው የምንለው አንዱ ማህበረሰብ ውስጥ የምንሰራው አለ። ሌላው ደግሞ ጤና ተቋማት ውስጥ የምንሰራው አለ። ሦስተኛው ደግሞ አሁን ትምህርት ቤት ውስጥ የምንሰራው ነው። ስለዚህ ይሄ ዘላቂ ነው የሚቆም ነገር አይደለም። በሰፊው የምንሄድበት እንጂ እያነሰ የሚመጣ ወይም ደግሞ የአንድ ሰሞን ሥራ አይደለም በየጊዜው እያሳደግነው የምንሄደው መርሀ ግብር ነው።

ኢዜአ - ጊዜዎን ሰውተው ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን!

ፕሮፌሰር ይፍሩ- እኔም አመሰግናለው!        

 

 

 

Published in ዜና ሐተታ

 አዲስ አበባ መጋቢት 1/2010 'ኢትዮጵያ አገሬ ናት' የሚል ሁሉ ለሰላም መስፈንና ለአንድነት በጋራ ሊቆም እንደሚገባ ለኢዜአ  አስተያየታቸውን  የሰጡ  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች  ተናገሩ፡፡

 ሰላም የሁሉም  ነገር መሰረት ነው  ያለችው  ተማሪ  ኤልሳቤጥ ፈቃደ   ተማሪው፣ ተመራማሪው፣ አርሶ አደሩ፣ ሁሉም በአንድነት አገርን  ተረባርቦ  ማሳደግና  ሰላምን መጠበቅ ይኖረበታል ብላለች፡፡

 ይሁን እንጂ አሁን  እየተስተዋለ ያለው ተማሪው  ተረጋግቶ ትምህርቱን   እንዳይማር ፣ ነጋዴው  በሰላም ወጥቶ  እንዳይገባ    እሆነ  መሆኑንም ትናገራለች  ፡፡

 በመሆኑም ስለተሰማራበት ስራ ሳይሆን ስለ ሰላም እጦትና ወጥቶ ስለመግባቱ እንዲያስብ መገደዱን ነው  የምትናገረው  ተማሪዋ፡፡

 "ሰላም ካለ የምታስበው ስለ ማደግ ነው" የምትለው ተማሪዋ "ሰላም ከሌለ ግን የምታስበው ስለ ግል ህይወትህ ብቻ ይሆናል" ትላለች።

 አገር የምታድገው በመግባባትና በመመካከር በመሆኑ መንግስት ህዝቡን ሊያዳምጥ፤ ህዝቡም መንግስትን ሊገነዘብ እንደሚገባም  ገልጻለች።

 "ሰላም ሁሉ ነገር ነው፣ እዚህ ተረጋግተን ብዙ ሆነን በጋራ እየኖርን የምንማረው ሰላም ስላለ ነው፣ የምንሰማቸው አንዳንድ ነገሮች በመጠኑም ቢሆን እየረበሹን ነው" ያለው ደግሞ ተማሪ አዲሱ አለሙ ነው።

 አገርን እመራለሁ የሚል ማንኛውም የፖለቲካ አካል በመግባባትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንጂ ህዝብን በመከፋፈል መሆን የለበትም፤ አሁን የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ መስራት ይጠበቅበታል ብሏል።

 ተማሪ ዘሪሁን ሰቦቃ በበኩሉ ለአገር አንድነት ሁሉም ሰው ሃላፊነት ስላለበት ሰላማዊ ከመሆን ጀምሮ ሌሎችን ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ ይኖርበታል ይላል።

 ለአገር አንድነትና እድገት መሰረቱ መግባባት ስለሆነ  የፖለቲካዊ  እንቅስቃሴ ሲደረግ    በመግባባትና  ለአገር  በሚጠቅም  መልኩ  ሊሆን እንደሚገባውም  ነው የተናገረው፡፡

 ለኢትዮጵያ አንድነትና እድገት ቀና አስተሳሰብ ያለው አካል ሁሉ ቅድሚያ ለአገራዊ አንድነትና ሰላም ሊሰጥ እንደሚገባም ነው ተማሪዎቹ በአስተያየታቸው የገለጹት።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መጋቢት 1/2010 የማበረታቻ ሽልማትና እውቅና መስጠት ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን መነሳሳትን እንደሚፈጥርላቸው ተማሪዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ ፈንድ በየዓመቱ የሚያካሂደውን በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች የስኮላርሺፕ እውቅናና የገንዝብ ሽልማት ዛሬ አበርክቷል።

ለ21ኛ ጊዜ በተካሄደው የእውቅናና የገንዘብ ሽልማት ከተለያዩ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት መስኮች የተውጣጡ 25 ተማሪዎች የተሸለሙ ሲሆን ዘጠኙ ሴቶች ናቸው።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች እንደገለጹት ሽልማቱ በቀጣይ ችግር ፈቺ ምርምር ለማካሄድ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሞራል ስንቅ ሆኗቸዋል።

የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ተማሪው ዘሪሁን ሰቦቃ እንደሚለው የእውቅና ሽልማቱ ለትምህርቱ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥና ለአገር የሚጠቅም ምርምር ለመስራት እንዲነሳሳ የሚያደርግ የቤት ስራ ነው።

"ነገሮች ሳይመቻቹለት ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም እውቅናን ያተረፈውን የፕሮፌሰር አክሊሉ ለማን ፈለግ ለመከተል አነሳስቶኛል" ነው ያለው።

"ጎበዝ ተማሪዎች የሚያስፈልጋቸውን በመረዳት ለትምህርት ግብዓት ማሟያ የኪስ ገንዘብና ለውጤታቸው እውቅና መሰጠቱ ነገ እንደ ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ ምሳሌ የሚሆን ትውልድ ለመቅረጽ የሚያስችል ነው" ያለችው ደግሞ የሂሳብ ተማሪዋ ኤልሳቤጥ ፈቃደ ናት።

በትምህርታቸው ግንባር ቀደም ሆነው በገንዘብ እጥረት የትምህርት ቁሳቁሶችን ለማሟላት የሚቸገሩ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሳ ይህ አይነቱ ሽልማት አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እንዲያሟሉ ከማስቻሉ በላይ "ጠንክሮ የመስራት ሞራል ያመጣል" ብላለች።

በየዓመቱ የሚካሄደው የሞራል ማበረታቻ "እንደ ፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ እኔስ ለአገሬ ምን ላበርክት ብሎ የሚያስብ ዜጋ ለመቅረጽ ቀስቃሽ መሳሪያ ነው" ያለው ደግሞ የሜዲካል ራዲዮሎጂ ተማሪው አዲሱ አለሙ ነው።

ከኪስ ገንዘብ ድጎማ ባለፈ ለተማሪዎች 'አይዟችሁ በርቱ' የሚለው መልዕክት ተጨማሪ ጉልበት እንደሚሆንም አስረድቷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ  የፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ ፈንድ ዋና አስተባባሪ ፕሮፌሰር ዘመድ አስፋው ፈንዱ ወጣቱ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን እንዲፈጥር ታስቦ የተቋቋመ መሆኑን ገልጸዋል።

ፈንዱ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ለሚያስመዘግቡ ተማሪዎች ስኮላርሺፕ ወይም የትምህርት ግብዓቶችን ማሟያ የኪስ ገንዘብ እንዲሁም የምርምር ስራ ለሚሰሩ ተማሪዎች ድጋፍና ምክር ይሰጣል እንደ ፕሮፌሰር ዘመድ ገለጻ።

ከምስረታው ጀምሮ የፈንዱ ተጠቃሚ የሆኑ ተማሪዎችም ከዩኒቨርሲቲው እንደወጡ በዩኒቨርሲቲው ከረዳት ተመራማሪ እስከ ከፍተኛ ተመራማሪ ደረጃ ድረስ ለአገሪቱ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሚገኙ ነው ያስረዱት።

ተመራማሪዎችን ለማፍራት ድጋፉን እያደረገ የሚገኘው የፕሮፌሰር አክሊሉ ለማ ፈንድ እስካሁን ለ490 ተማሪዎች የስኮላርሺፕ ድጋፍ የሰጠ ሲሆን 52ቱ ሴቶች ናቸው።

Published in ማህበራዊ

 

                   ዳግም መርሻ (ኢዜአ)

 አለም አቀፍ የሴቶች ቀን  በአያሌ ሀገራት በየአመቱ እ.አ.አ ማርች 8 (መጋቢት 29) በድምቀት ይከበራል። በአሉ ህብረተሰቡ  ስለ ሴቶች ጾታዊ ማንነት ተገቢውን ክብር በመስጠት፣ እንዲሁም ሴቶች በህይወታችን ውስጥ ያላቸውን ሚናና አስተዋጽኦ በተለያየ መልኩ አስበውት የሚውሉበት ቀን ነው። አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሴቶች በሁለንተናዊ የሰው ልጆች ሀይወት ውስጥ ስላላቸው ወሳኝ የሆነ ሚና ፍቅርና አክብሮትን በመግለጽ እንደ የሀገሩ ባህልና ስርአት ይከበራል። በአሉ በአለም ዙሪያ የሚከበረው በተለያዩ ዝግጅቶች ሲሆን ይኽውም በኪነ-ጥበብና ስነ ጥበብ ዝግጅቶች፣ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ በአሉን አስመልክቶ በሚደረጉ ንግግሮችና መልእክቶች፣ በእግር ጉዞዎች፣ በሰላማዊ ሰልፎች፣ በዎርክሾፖችና ኮንፍራንሶች…ወዘተ በመታጀብ ነው።

የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን ክብረ በአል አመጣጥ በዋነኝነት ከሁለት ታሪከዊ ክስተቶች ጋር ተያያዥነት እንዳለው ይታመናል። የመጀመሪያው ታሪካዊ መነሻ እ.አ.አ ከ1907-1908 በአሜሪካ ኒው ዮርክ ቁጥራቸው 15,000 የሚሆነ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ሴት ሰራተኞች Hunger March የሚል መፈክር ይዘው ያደረጉት ሰላማዊ ተቃውሞ ሲሆን፣ ተቃውሟቸውም የተራዘመ የስራ ሰአታቸው በቀን ወደ አስር ሰአት እንዲያጥር፣ የተሻለ ክፍያ እንዲኖር፣ ምቹ ያልሆኑ የስራ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ፣ የመምርጥ መብትን...ወዘተ የተመለከቱ ጉዳዮች ነበሩ።

እንዚህን የጾታዊ መብትና እኩልነት ጥያቄዎችን ለማሰብና ብሎም የተነሱት የመብትና የእኩልነት ሀሳቦችን በመጋራት በአሜሪካ የሶሻሊስት ፓርቲ የሴቶች ብሄራዊ ኮሚቴ (Woman’s National Committee) ቴሬዛ ማሊኪል በምትባል እንስት ሀሳብ አመንጪነት በቀጣዩ አመት የአሜሪካ የሴቶች ቀን (Woman’s Day) ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ 1909 ጀምሮ በብሄራዊ ደረጃ እንዲከበር ተወሰነ።

ሌላው የለአለማቀፉ የሴቶች ቀን ክብረ በአል እንደመነሻ ሆኖ የሚወሰደው ታሪካዊ አጋጣሚ ደግሞ እ.አ.አ በ1910 በዴንማርክ ኮፐን ሀገን በተካሄደው ሁለተኛው የሶሻሊስት የሴቶች ኮንፍረንስ የጀርመን ሶሻሊስት ሴቶች ተወካይና የሶሻሊስት ርዮት አቀንቃኟ ክላራ ዜትኪን በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፍትሀዊ ያልሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ሚዛናዊነት የጎደለው የስራ ክፍፍልን እንደመነሻ በመውሰድ ሴቶች የኢኮኖሚና የፖለቲካ መብቶቻቸው እንዲረጋገጥ የሴቶች ቀን በየአመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ኖሮት እንዲከበር ለጉባኤው  ባቀረበችው ሀሳብ ከ17 ሀገሮች በመጡ የሠራተኞች ማህበራት፣ የሶሻሊስት ፓርቲዎች፣ የሴት ሠራተኞች ክበብ ተወካዮች ዘንድ ድጋፍ ማግኘቱ ነው፡፡

በመሆኑም በኮፐን ሀገን ኮንፈረንስ ውሳኔ መሠረት በቀጣዩ አመት ማለትም እ.አ.አ ማርች 19 ቀን 2011 ዓ.ም የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን በኦስትሪያ፣ በዴንማርክ፣ በጀርመን እና በሲውዘርላንድ በሰላማዊ ሰልፍና ልዩ ልዩ ትእይንቶች መከበር ጀመረ፡፡ እነዚህ በአሎች ሲነሱ የነበሩ መፈክሮችም ከመምረጥና መመረጥ መብቶችም አልፎ ጾታን ማእከል ያደረጉ መድልኦዎችና ልዩነቶች እንዲወገዱ የሚጠይቁ ነበሩ።

ይህ በአል በተከበረ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ በተነሳ የእሳት ቃጠሎ 146 የሚሆኑ የፋብሪካው ሰራተኞች ውስጥ አብዛኞቹ ስደተኛ የሆኑ ሴት ሰራተኞች  የቃጠሎው  ሰለባ ሆኑ፡፡ ይህን አደጋ ተከትሎ ብዙ ኢንዱስትሪዎችና ፋብሪካዎች በደረሰባቸው ግፊትና ተጽእኖ ለሰራተኞቻቸው የስራ ሁኔታዎችን እንዲያሻሽሉ የተገደዱበት ሆኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ  ጎንለጎን የሞቱትን ሰራተኞች በየአመቱ በሚከበረው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የበአሉ አካል ሆነው ታስበው እንዲውሉ አደጋው ምክንያት ሊሆን ችሏል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በቀደሙት ጊዜያት ይከበሩ በነበሩት የአለም አቀፍ ሴቶች ቀን ክብረ በአላት ላይ ይነሱ የነበሩት ጭብጦች በአመዛኙ ከሴት ሰራተኞች መብትና እኩልነት ጥያቄዎች ጋር ተያያዥነት የነበራቸው ርእሶች ነበሩ።

በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን መከበር የተጀመረው በጁለያን ከላንደር ፌብሩዋሪ 1913 ነው። ያንጊዜ  የመጀመሪያው የአለም ጦርነት አ.አ.አ በ1914 መፈንዳቱን ተከትሎ በጦርነቱ ብዙ ወታደሮች በማለቃቸው በሩሲያና አውሮፓ ሴቶች ጦርነቱን በመቃወምና የሴቶችን የአንድነት ስሜት ለማሳየት እ.አ.አ  ማርች 8 ቀን 1914 ታላቅ የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ። እነዚህ ሰላማዊ ሰልፎች በአጠቃላይ በአውሮፓ ውስጥ እስከ 1916 ድረስ ዘልቀዋል፡፡

በሂደትም በግሪጎሪያን አቆጣጠር ማርች 8 ቀን 1917 ዓ.ም የአንደኛው የአለም ጦርነት ገና ባልተጠናቀቀበት ሁኔታና በሩሲያ አብዮት ዋዜማ  የሩሲያ ሴቶች ጦርነቱ ባስከተለው ሞትና የንብረት ውድመት ዙሪያ በቂ ተሞክሮና ግንዛቤ ሊይዙ የቻሉበት ሁኔታ ስለነበር ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍና ተቃውሞ የተደረገበተ ጊዜ ነበር። የሰላማዊ ሰልፎቹና ተቃውሞዎች ማጠንጠኛ ያደረጉት ዋና ዋና ጉዳይ የህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ማሽቆልቆል፣ የመሰረታዊ የምግብ አቅርቦት መጓደል እና የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት ነበር። የተቃውሞዎቹ ዋነኛ ተዋናዮች ሴቶች ይሁኑ እንጂ ወንዶችም የተቃውሞ ሰልፎቹ ተካፋይ የሆኑበት ሁኔታ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ተቃው  ይመራ የነበረው በሩሲያ የሴቶች መብት አቀንቃኝ በነበረችው  አልክሳንድራ ኮሎንታየ በምትባል ሲሆን ሰልፉ “ዳቦና ሰላም” የሚል ቀዳሚ መልእከት ከዳር እስከዳር በማስተጋባት ከላይ ከተጠቀሱት የኢኮኖሚ ጥያቄዎች በተጨማሪ በወቅቱ የነበረውን ጦርነትና ውድመት አምርረው ተቃወሙ። ተቃውሞው ከተደረገ ከአራት ቀናት ቦኋላም የሩሲያ ዛር ሥልጣኑን እንዲለቅ አስገዳጅ ሁኔታ በመፈጠሩ ሥልጣኑን ለቀቀ። በምትኩ ወደስልጣን የመጣው የሽግግር መንግስትም የሴቶች የመምረጥ መብትን ሊቀበል ቻለ። ይህን ታረካዊ ሰለማዊ ሰልፍና ተቃውሞ ለማሰብም ሶቭየት ዩንየን ከማርች 8 ቀን 1922 ዓ.ም ጀምሮ የሴቶች ቀን በዓል ታሰቦ እንዲውል ውሳኔ አስተላልፏል።

የተጋጋለው የሴቶች ቀን ተፋፍሞ ባለበት በመቀጠሉ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን  እ.አ.አ በ1975 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት  እውቅና እስኪያገኝ ድረስ በተለያዩ አህገራት በሚገኙ የሶሻሊስት ንቅናቄ ቡድኖችና ባብዛኞቹ ኮሚኒስት ሀገሮች እንደ ብሄራዊ በአል ሲታሰብ ቆይቷል።

አሁን ባለንበት ጊዜ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተለያዩ ሀገራት ሲከበር ሴቶች በተለያዩ መስኮች ያስመዘገቧቸውን ድሎች በመዘከርና በማሰብ የመሆኑን ያህል በአሉ በአንዳንድ ሀገሮች በተቋውሞዎችና ባልተሟሉላቸው መብቶች ዙሪያ ጥያቄዎችን የሚስተናገድበት ነው። ለአብነትም የአለፈው አመት የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 ሲከበር በአሜሪካና በሌሎች ሀገራት በሚለዮን የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች አደባባይ በመውጣት ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራፕ መመረጥ ጋር በማያያዝ የሴቶች መብት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ በተለይም ከጾታዊ ጥቃት፣ እኩል የከፍያ ስርአትና የጤና እንክብካቤ ጋር የያያዙ ጉዳዮች እንዲሻሻሉና እንዲለወጡ ጥቄያቸውን ያሰሙበት ሁኔታ ነበር።

ቀኑ በሌሎች ሀገሮችም ሲከበር ከሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ ከጾታ ጥቃት፣ ከእኩልነትና ከሴቶች መብቶች ጋር የተያያዙ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ በሴቶች የሚነሱበትና ጎልተው የሚደመጡበት ነው። ያም ሆኖ ቀኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ ሀገሮች ከአመት አመት ጥንካሬ እያገኘ በመሄድ በታሪክ ለቀኑ መታወስ በምክንያትነት የሚጠቀሱ የሴቶችን ታሪካዊ ትግሎችና የተከፈሉ መስእዋትነቶችን የሚዘከርና የሚታወስ ከመሆኑ ጎን ለጎን ሴቶች በማህበራዊ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በሌሎች መስኮች ያስመዘገቧቸው ስኬቶች የሚወደስበትና እውቅና የሚሰጥበት እለት ነው። በሌላ በኩል ቀኑ ሴቶች በቀጣይነት መልስ ላላገኙ ጥያቄዎቻቸው የተለያዩ አካላትን ትኩረትና ተሳትፎ ባካተተ መልኩ በተለያየ ደረጃ መፍትሄ እንዲለዋወጡ ብሎም ወደ መፍትሄ አቅጣጫ እንዲጓዙ የሚያስችል እድል የሚፈጥርላቸው ቀን ነው።

እንግዲህ ዘንድሮም አንጋፋዋ ማርች 8 በአለም አቀፍ ደረጃ ለ107 ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ 42ኛ ጊዜ “በተደራጀ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን” በሚል መልእክት እየተከበረ ሲሆን፣ ቀኑ ሲታሰብ የሀገራችን ሴቶች ያሳለፉትን እና እስካሁንም በተሟለ መልኩ መፍትሄ ያላገኘውን ጾታን መሰረት ያደረገ ኢ-ፍትሃዊነት በተለይ ባለንበት ዘመን እየሰማን ያለነውን አስከፊ የሆነውን የሴቶች ጥቃትና የመብት መጓደል በመቃወምና ለእነዚህ ችግሮች የተሻለ መፍትሄ የሚያስገኙ ጥረቶች ይደረጉ የሚል ሀሳብ በማቅረብ ነው፡፡

 

 

Published in ዜና ሐተታ

የደም ግብር ታዛቢ መልክዓ ምድሮች

አየለ ያረጋል /ኢዜአ/

በነጫጭ ቀለማት ያሸበረቁ ካቦች ይስተዋላሉ፤ ከዙሪያ ገባ ጎራማይሌ ተራሮች ግርጌ። ዕልቆ ቢስ ትዕይንቶች በዘመናት ጅረት ፈሰዋል፤ ሠርቀው ሰርገዋል። እነኚህ ግዑዛን የአይን ዕማኝ ኮረብታዎች ግን ጥንትም እንደነበሩ አሉ፤ የትዕይንቱን ዑደቱ እየታዘቡ። ባሳለፍነው አንድ ምዓተ ዓመት እንኳን ስንቱን ተመለከቱ! ብቻ አጀብ ነው! ይሄው ከ122 ዓመታት በፊት በዙሪያቸው ተዳፋታማና ሜዳማ ስፍራዎች የደም ግብር ሲበላ አስተዋሉ። ከሰሞኑ ደግሞ እንደኔ በርካታ ካቦች በነጫጭ ቀለማት ሲቀልሙ ተመለከቱ። ቁጥቋጦዎች ሲራቆቱ ምድረ በዳዎች ሲጎፍሩ አይተዋል። የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ንጋት  ጀምሮ በፆመ ሁዳዴ የደም ግብር ሲበላ ነበሩ፤ ዛሬም ግብሩ የተበላባቸውን ስፍራዎች(መካነ መቃብሮች) እያዩ ነው። የአድዋ ተራሮችን ያክል ሕያው የታሪክ ምስክር ማን አለ! ዘመን አይሽሬ መልክዓ ምድሮችን ያክል!

ይሄው ከሰሞኑ 122ኛውን የአድዋ ጦርነት ድላችንን ዘከርን። በዚያች ተዓምረኛ ዕለት በአድዋ ተራሮች መንደር መድፎች አጓርተዋል፣ መትረየሶች አሽካክተዋል፣ እሳት ወርዷል፤ ጥይት ዘንቧል፣ ጎራዴ ተመዟል፣ ጦር ተሰብቋል! ምን አለፋን በጥቅሉ የክቡር ሰብዓ ዘሮች ደም ተገብሯል። የአድዋን ድል ህያውነት፣ እንቆቅልሽነት፣ አድማስ ዘለል ታሪክነት፣ የዓለም ነጸብራቅነት፣ አፍሪቃዊነት፣ ኢትዮጵያዊነት አልዘረዝርም። /“አሁንም አሁንም ለበላይ---” እንዳለው ዘፋኙ ስለ አድዋ(በቂ ነው ባይባልም) ብዙ ተብሏል አሁንም አሁንም ቢባልለት ግን አይጋነንም።/

ከዚያ ይልቅ የደራሲና ጋዜጠኛ ነብይ መኮነን ስንኞች(ስውር ስፌት) ልዋስ!

“አድዋ የደም ግብር ነው፤አበው የለኮሱት ቀንዲል

አድዋ የአፍሪካ ዱካ ነው፤ አበሽ የከተበው ፊደል

ላጥፋህ ቢሉት መች ይጠፋል፤ ጠላት በልቶ ያፈራ ተክል

ለዛሬም ታሪክ ነው፣ ‘ነገም ሌላ ቀን ነው’ ለሚል----”

አድዋን ጂጂና ቴዲ አፍሮ በዘፈኖቻቸው፣ እነ ፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ በፊልማቸው፣ እነ ግራዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት በተውኔታቸው፣ ጸጋዬ ገብረ መድህንና መሰሎቹ በቅኔያቸው፣ ሌሎች የኪነ ጥበብ ሰዎች በየመክሊቶቻቸው፣ የታሪክ ሊቃውንትም በጥናታቸው አውስተውታል፤ በዘመኑ አሳሾችም ሆነ በአሜሪካና አውሮፓ ጋዜጦች ተነግሮለታል። ለመሆኑ እኛ (ባለታሪኮች) ድፍን 122 ዓመታት ያስቆጠረውን አኩሪ ድላችንና የአብሮነት አርማችን ተግባብተንበታል! በተገቢው ሁኔታ ዘክረነዋል! ቋሚ መዘከርስ እስካሁን ለምን አልቆመለትም! የጽሁፌ መንደርደሪያና መድረሻም ‘ዝክረ አድዋ’ ነው!

ዝክረ አድዋ

“ጥቁር ሕዝቦች ከነጮች ጋር ያደረጓቸው ጦርነቶች ብዛት የትየሌለ ነው” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤምሬትስ ፕሮፌሰሩ ባህሩ ዘውዴ። (ፕሮፌሰሩ በዘንድሮው ክብረ በዓል በአድዋ ተገኝተው ነበር፣ ስለ ዝክረ አድዋ አስፈላጊነትና ታሪካዊ ፋይዳ በጽሁፋቸው አንስተዋል፤ በተለይም ለኢዜአ በጉዳዩ ላይ ሀሳብ ሰንዝረዋል)። “አንድም ጦርነት ግን በነጮች ላይ ድል አልተጎናጸፈም፤ ከወርቃማው የአድዋ ድል በስተቀር”። አድዋ አዲስ የታሪክ ምዕራፉ ሲከፍት በአንጻሩ ነባር አስተሳስብ ሰብሯል፤ የጥቁሮች የበታችነት ስሜትና የነጮች የበላይነት አስተሳስብ ለመጀመሪያ ጊዜ በአድዋ ተራሮች ግርጌ ተሽሯል።

ፕሮፌሰሩ ‘ኢትዮጵያዊያን ለምን አሸነፉ’ ለሚለው አራት መልሶች አሏቸው። የመጀመሪያው ከቅድመ አድዋ ጦርነቶች ያልታዬ ህብረት በአድዋ ጦርነት ወቅት መጥቷል። ከዳር እስከ ዳር ሁሉም አካባቢ ህዝብ ምንም አይነት ልዩነት ሳይገድበው ወደ አድዋ ተምሟል። በኤርትራና በትግሬ የነበሩ ለጠላት አድረው የነበሩ እንደነ ደጃዝማች ባሕታ ሐጎስና ራስ ስብሐት መሰል መሳፍንት ከዳግማዊ አጼ ምኒልክ ጐን ተሰልፈዋል።

በአጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ዘመን የተገኘው ወታደራዊ ልምድን ደግሞ ለጦርነቱ በድል መወጣት በሁለተኛ ምክንያትነት ይጠቅሱታል። ሶስተኛው የአጼ ምኒልክ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት ነው። በየጊዜው በርካታ የወቅቱ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች ገብተዋል። (በነገራችን ላይ በአድዋ ጦርነት በኢትዮጵያና በፋሽስት ጣሊያን መካከል የነበረው የጦር መሳሪያ ልዩነት እምብዛም ነው፤ ‘ኢትዮጵያን በኋላቀር የጦር መሳሪያ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያ ጦር አሸነፉ’ በሚባለው ተረክ ፕሮፌሰር ባህሩን ጨምሮ በርካታ የታሪክ ምሁራን አይስማሙበትም፤ ንጉሱ በርካታ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ወደ ኢትዮጵያ ቀድመው ገብተው ስለነበር። በእርግጥ ከ40 ዓመታት በኋላ በ5 ዓመቱ ጦርነት ፋሸስት ኢጣሊያ አውሮፕላን ይዛ ስትመጣ ኢትዮጵያ ግን ጦርና ጎራዴ ይዛ ጠብቃለች)                     

አራተኛው ምክንያት ደግሞ “የኢትዮጵያዊያን ታክቲካዊ የበላይነት ነው” ይላሉ። ዳግማዊ ምኒልክ በጦርነቱ ወቅት የተጠቀሙበት ስልት(ለምሳሌ የባሻ አውዓሎምን ስለላ ልብ ይሏል) ጠላትን በተሳሳተ ስሌት የመራና ጠላት በቀላሉ በወገን ጦር እንዲከበብ ያደረገ ነበር  ነው የሚሉት። በኢጣሊያ ወገን ከዘመቱ አራት ጀነራሎች መካከል አንደኛው ከመሸሹ ውጭ ሁለቱ በጦርነቱ ተገድለዋል፣ አንደኛውም ተማርኳል።

የአድዋ ድል ዘመናዊነት እንዲስፋፋ፣ የባቡር፣ ስልክ፣ ትምህርት፣ ፖስታ፣ ቴሌ፣ መንገድና ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉ፤ ኢትዮጵያ የትኛውም አፍሪካዊ አገር ያላገኘውን የራሷን የፖለቲካ ኢኮኖሚ እንድትመራ ያስቻላት ድል ነው። ቀድሞውኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይዘት ቢኖረውም በኋላ ግን የአፍሪካዊያን የነጻነት እንቅስቃሴ ምልክት ሆኗል፤ የ‘ኢትዮጵያዊነት’ ጽንሠ ሃሳብ። እናም አድዋ ለ’ኢትዮጵያዊነት’ እና ለ’ፓን አፍሪካዊነት’ ጉዞ መሰረት ሆኗል፤ ቅኝ ግዛት እጣፈንታ አለመሆኑን አብስሯል፣ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛት ቀንበር ሲላቀቁ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማትን ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ተሻምተዋል። ኃያላኑ የምዕራብ አገራት ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ ከፍተው ለኢትዮጵያ ነጻና ሉዓላዊነት ‘አሜን’ ብለው ዕውቅና ሰጥተዋል።

ሌላም አለ፤ ከአድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያዊያን የጀግንነት፣ የአገር ፍቅር፣ የአገር ሉዓላዊነት የማይበገር ወኔና ስነ ልቦና እሴቶችን አዳብሯል። ለአብነትም በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ፣ በደርግ ዘመን በነበረው የሶማሊያ ወረራ እንዲሁም በባድመ የነበረው የኢትዮጵያዊያን ኅብረት ከአድዋ የተገኘ የአብሮነትና አይበገሬነት እሴት መሆኑን የታሪክ ምሁሩ ያብራራሉ። በርግጥ ኢትዮጵያዊያን በአድዋ ጦርነት ርህራሄንና ሰብዓዊነትን ለነጭ ፋሽስት አስተምረዋል።

“አድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት” እንዲል የዘንድሮው መፈክር የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኅብረትና አንድነት ጥግ ድረስ የታዬበት ይህ ድል በተገቢው ሁኔታ አልተዘከረም። አድዋ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረው በ1923 ዓ.ም በድሉ ሰባተኛ ዓመት የዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ምረቃ ዕለትና የአጼ ኃይለሥላሴ ንግስና ዋዜማ ዕለት ነው። ከ1934 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ ብሔራዊ በዓል ተደርጎ በየዓመቱ መታሰብ ጀመረ። 100ኛ እና 103ኛ ክብረ በዓሉ በድምቀት መከበሩን ይገልጻሉ። ‘እንኳን እንደ አድዋ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ድል ቀርቶ በርካታ ትናንሽ ጦርነቶች እንኳን መታሰቢያ የጦር ሙዚዬም ገንብተዋል’ የሚሉት ፕሮፈሰር ባህሩ፤ ለዚህ “ኢትዮጵያዊያን አንዱ ይህን ታሪካዊ ታላቅ ድል እስካሁን ቋሚ መታሰቢያ መገንባት አለመቻላችን ሊያሳፍረን ይገባል”ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ስለ ጦርነቱ ተዋናዮች እንዲህ ይላሉ። “ከዳር እስከ ዳር ነው የተነሳው። ያኮረፈም ሳይቀር ገብቷል። ያኮረፈም ቢሆን በምንም መልኩ አያገባኝም ያለ የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረም። ከወለጋ እስከ ሀረር፣ ከኤርትራ እስከ ሲዳሞ። ኤርትራ ውስጥ በኢጣሊያን ቅኝ ግዛት የነበረችው ኤርትራ እንኳን በደጃች ባሕታ ሐጎስ የሚመራ አመጽ ማካሄድ ችላለች። ያ ኢትዮጵያዊ ስሜት ነው። በቅኝ ግዛት ስር የነበሩት እንኳን። እና ዋናው የአድዋ እሴት ይሄ ነው።”

ወጣቱ ትውልድ ከአድዋ እሴቶች ‘አንድነትን’ ሊወርስ ይገባል ባይ ናቸው። “አንድነት ባይኖር፤ ያ! ሁሉ ኢትዮጵያዊ ባይተባበር ኖሮ ይህን አይነት ድል ሊገኝ አይችልም። የዚያ ውጤት ነው” ይላሉ። አያቶች በክንዳቸው መከዳነት፣ በአጥንታቸው ምሰሶነትና በደማቸው ቡኬት በኅብረት በማገራትና አስከብረው ባቆዩዋት አገር የልጅ ልጆች በአድዋ ታሪካቸው እንኳን የጋራ መግባባት ፈጥረዋል? ለሚለው መጠይቅ ፕሮፌሰር ባህሩ ‘መግባባት ቢኖርም በቂ አይደለም! ይበልጥ ይሰራበት” የሚል አስተያየት አላቸው።

“የጋራ መግባባት አለ፤ ይቀረዋል፣ የበለጠ መሰራት አለበት። ግን አሁን ጅማሬው ጥሩ ነው ፣ የጋራ መግባባት አለ፤ እስካሁን ድረስ ይሄ መግባባት አልነበርም ማለት ይቻላል”።

የዝክረ አድዋ ተስፋችን

ባለፈው ዓመት ከተከበረው 121ኛው የድሉ መታሰቢያ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ነበር። በዓሉ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ታቦ ምቤኪን ጨምሮ የአገሪቷ ርዕሰ ብሔርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት ነበር በአድዋ ከተማ በድምቀት የተከበረው። የአድዋ ድል ሕያውነት ባሳለፍነው ዓመት ተነስቷል፣ ብዙ ተብሏል። የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጽንሰ ሃሳብም ተነስቷል። ዘንድሮስ? 122ኛው መታሰቢያ ቀን ባሳለፍነው ሳምንት ሲከበር በተመሳሳይ  ርዕሰ ብሔሩ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ተገኝተዋል። የአድዋ ድል ሕያውነት አስተጋብተዋል። “የድሉን መልካም እሴቶች ለወቅታዊ የሰላምና መረጋጋት ፍላጎታችን መጠቀም ይገባል” ብለዋል።

ሁለቱንም ክብረ በዓላት በቦታው ተገኝቼ እንደታዘብኩት የአከባበር ሂደቱ መሻሻል የታየበት ይመስላል። ለአብነትም ባሳለፍነው ዓመት የአድዋን ድል እንዲገኝ በመሪነት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱን ስም ማውሳት ነውር ይመስል ነበር። በወቅቱ የአውሮፓና የአሜሪካ ጋዜጦች ሳይቀር ያወደሳቸው፣ ጣሊያኖች በሮም አደባባይ “አበጀህ ምኒሊክ! አበጀሽ ጣይቱ!” እያሉ ሰልፍ የወጡላቸው የዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ስምም በንግግር አድራጊዎችና ድራማዊ ተውኔቶች ተነስተዋል። (በርግጥ ከባለፈው አመት አኳያ አልኩኝ እንጂ በንግግር አድራጊዎች ንጉሱና ንግስቲቱ የሚለው ሚዛን ይደፋል፤ በበዓሉ ዋዜማ በተከፈተው የፎቶ ዓውደ ርዕይም የበርካታ አርበኞች ፎቶ ለዕይታ ቢቀርብም የንጉሠ ነገሥቱና የእቴጌጣይቱ ምስል አልነበረም)።

የክልሎች መገናኛ ብዙሃንም በአንድ ታሪክ ላይ የተለያዩ ይዘቶችን ከማስተጋባት ባለፈ  ለታሪካዊ ለድሉ ተገቢውን ሽፋን ያልሰጡ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንደነበሩ ሲወራ እንደነበር አይዘነጋም። በዚህ ዓመት አከባበሩ ግን በርካታ መገናኛ ብዙሃን በስፍራው ተገኝተው ሽፋን ሰጥተዋል። ለዝክረ አድዋ መነሳሳት የፈጠረው ጉዞ አድዋም በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ በአደባባይ  ተመስግኗል። በዘንድሮው የአምስተኛው ዙር የአድዋ ተጓዦች (አንዲት ታሪካዊ ውሻን ጨምሮ) በስፍራው ተገኝተው “ኢትዮጵያዊነት ይለምልም” ብለዋል። እና ምናልባት በጋራ ታሪካችን ላይ እየተግባባን ይሆን ያሰኛል!

(በነገራችን ላይ ለአድዋ ድል በዓል መታሰብ በአዲስ ንቅናቄ የፈጠሩት የ’ጉዞ አድዋ’ ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ ሲካሄድ አንድ አስገራሚ ክስተትም ተመዝግቧል። ተጓዦቹ የ45 ቀናት በእግር ጉዟቸውን ከአዲስ አበባ ጀመሩ። ጉዞው ከአድዋ ታሪክ ጋር ቁርኝት ያላቸውን ሰፍራዎች በመጎብኘት ዳግማዊ ምኒልክና የፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ የትውልድ ስፍራ(አንጎለላ) ደረሱ። ታሪካዊቷ ውሻም በፈቃዷ ወጣቶችን ተከትላ አድዋ ተራሮችን ጎበኘች። የበዓሉ ዕለትም ተጓዦችን ተከትላ ስትቦርቅ ተስተዋለች። አድዋንም ተሳልማ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰች። ‘እንኳን ሰው ውሻም…’ ብለን እንተርት እንዴ?) 

ሌላው የዘንድሮ መታሰቢያ ክብረ በዓል የድሉ ቋሚ መታሰቢያነት በአድዋ የሚገነቡ ሶስት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ ላይ እያሉ መከበሩ ነው። የመጀመሪያው ባሳለፍነው ዓመት በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ላይ የነበረው የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፤ ለፕሮጀክቱ በመንግስት 200 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ማስታወቃቸው አይዘነጋም። የዲዛይን ስራውና ሌሎች ተግባራት መጠናቀቃቸው ተነግሯል።

ሌላው ደግሞ  ‘የአድዋ ድል መታሰቢያ ዓለም አቀፍ ሙዚዬም’ ግንባታ ፕሮጀክት ነው። የመሰረት ደንጋይ ከመቀመጥ አልፎ የመሬት ክለላ ስራዎች ተከናውነዋል። የዲዛይን ስራው በኢትዮጵያ አርክቴክቸሮች ማኅበር እየተሰራ ነው። ፕሮፖዛሉ በመሰራት ላይ ሲሆን፤ ቀጣይ ገንዘብ ማሰባሰብ ስራ እንደሚከናወን ተገልጿል። ይህ ሙዚዬም የፋሽስት ጣሊያን አሰብ መግባት ጀምሮ ከቅደመ አድዋ የነበሩ ጦርነቶችና ታሪካዊ ሁነቶችን የሚይዝ ተቋም እንደሚሆን ተገልጿል። ፕሮጀክቱን በዋናነት የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚን ወክለው በስፍራው የተገኙት ፕሮፌሰር ባሕሩ ለዚህ ድል “የቋሚ መዘክር አስፈላጊነቱ ጥርጥር የለውም” ይላሉ።

ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለወራት መሰራቱን አደረጃጀቱና ይዘቱን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ ተወስዶ “የአድዋን ታሪካዊ ግዝፈት በሚመጥን ሁኔታ እንዲገነባ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው” ብለዋል። ውጫዊና ውስጣዊ ገጽታዎች የሚኖሩት ይህ ቤተ መዘክር ‘ምንድብድብ’ በተሰኘው የእጅ በጅ ውጊያ በተካሄደበት ስፍራ ይገነባል። (ውስጣዊ ስዕላዊና ቁሳቁሶችን ሲይዝ ውጫዊ ገጽታው የፍልሚያ ቦታዎችን የሚይዝ ነው)

ሶስተኛው ደግሞ በክልሉ መንግስት መሪነት ‘የአድዋ ተራሮችና የአድዋ ድል ቱሪዝም ፕሮጀክት’ በይፋ መመረቁ ነው። ወደ 258 ሚሊዮን ወጭ የተገመተለት ይህ ፕሮክት በውስጡ አስር የተለያዩ ተግባራትን አካቷል። ለምሳሌ በአድዋ ከተማ ጣሊያኖች በቆንስላነት ሲጠቀሙበት የነበረውን ሕንጻ ቤተ መዘክር ይደረጋል፣ የባሻ አውዓሎም ሃረጎት ሐውልት ይገነባል፣ የራስ አሉላ አባነጋ መቃብር ሐውልት ይታደሳል፤ የብዝሐ ሕይወት ፓርክ ይከለላል፣ በተራራ ላይ ተንሳፋፊ ጋሪዎች፣ ባሎኖች፣ የቱሪስት ማረፊያዎች፣ የእግርና ፈረስ ጉብኝት አገልግሎቶች፣ የመካነ መቃብር ስፍራዎች ልማት ጥቂቶቹ ናቸው። ከሁለት ወራት በፊት የተጀመረው የዚህ ፕሮጀክት እንቅስቃሴም እስካሁን በርካታ መካነ መቃብሮች ተለይተው ታጥረዋል። (ቀደም ሲል ነጫጭ ቀለማት ያልኳቸው ካቦች ከጠላትም ከወገንም መቃብሮች ናቸው)።  ከነዚህም መካከል

“አድዋ ስላሴን ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው…”

የተባለለት የአድዋው ጀግና የፊታውራሪ ገበየሁ ገቦ(ጎራው ገበየሁ) የተሰዋበት ስፍራ ላይ ጊዜያዊ መታሰቢያ ሐውልት ይገኛል። በጠላት ወገን ደግሞ የጀኔራል ዳቦር ሜዳ ሐውልት ለመገንባት መቃብሩ በጊዜያዊነት ታጥሯል። የአድዋን ተራሮች የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በማልማትና ብዝሃ ሕይወቱን በመጠበቅ ታሪካዊ ሥፍራውን በዓለም አቀፉ የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት (ዩኔሰኮ) ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ማቀዱን የተለያዩ የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ገልጸዋል።

የሆነው ሆኖ በሚገነቡ ሶስት ፕሮጀክቶች (በተለይ ቤተ መዘክሩ ዓለም አቀፋዊ ነውና) በግንባታና በሚይዛቸው ነገሮች ዙሪያ የተለያዩ ወገኖችን አስተያየት ማስተናገዱ አልቀረም።

የመጀመሪያዊ የግንባታዎች ‘ኢትዮጵያዊነት’ ወይም አገራዊ ባህል አንጸባራቂነታቸው ነው። የኢትዮጵያ ፊልም ሰሪዎች ማህበርን በመወከል በስፍራው የተገኘው አርቲስት ደሳለኝ ስዩም የቤተ መዘክሩ አርክቴክቸራል ዲዛይን ሊታሰብበት ይገባል ባይ ነው። ምንም እንኳን ቅኝ ባንገዛም ኪነ ሕንጻው የውጭ ባህል ካንጸባረቀ ሌላ ‘የባህል ቅኝ ግዛት’ በመሆኑ ግንባታው አገራዊ ለዛ ሊላበስ እንደሚገባ ነው ያብራራው። የታሪኩ ባለቤቶች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነውና ሁሉንም ህዝቦች ተሳትፎ፣ ባህልና ማንነት ወካይ መሆን እንዳለበትም እንዲሁ። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከአክሱም እስከ ጎንደር ዘመነ መንግስት የኪነ ሕንጻ ጥበባት የተገለጠባቸው ድንቅ ቅርሶች ባለቤት አገር ናት ይላል።

በሌላ በኩል የአድዋ ተራሮች ሲለሙ፣ ቤተ መዘከር ሲገነባ የተወሰኑ የጦር ተዋናዮች መታሰቢያ እንደሚኖራቸው ቢገለጽም ‘የእነ እገሌስ’ የሚሉም አልጠፉ። ለአብነትም ደራሲት የምወድሽ በቀለ ተከታዩን ትላለች። “እቴጌ ጣይቱ ልጅ የላትም፤ ግን ትልቅ ስራ የሰራች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጸሀይ ናት። ለእሷስ ከሚሰራው ነገር ምስሏ ያለበት መሰራት የለበትም?”።

ዓለም አቀፍ ሙዚዬሙ ከአጼ ካሌብ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ጀምሮ እስከ ባድመ ጦርነት ያለውን የጦርነት ታሪካችንን የሸከፈ የጦር ሙዚዬም መሆን አለበት የሚል ሃሳብ የሚያነሱም አሉ።

ለአድዋ ድል መንስኤ የሆነው የውጫሌ ውል የተፈረመበት ይሥማ ንጉስ፣ የእቴጌ ጣይቱ ብልሀትና የጦር ስትራቴጂ የታየበት እንዳየሱስ፣ ከአድዋ ጦርነት ቀደም ብሎ ፊታውራሪ ገበየሁ ታላቅ ጀብዱ የሰሩበት የአምባላጌ ጦር ሜዳና መሰል ታሪካዊ ሥፍራዎች ከአድዋ ጋር ተሳሰረው መልማት እንዳለባቸው ያነሱም አልጠፉ። በዚህ ረገድ ፕሮፌሰር ባህሩ “ በእንዳየሱስ ጣሊያኖች የሰሩትን ያህል ኢትዮጵያን አልሰሩም። ጣሊያን ለራሳቸው መታሰቢያ ወደኋላ አይሉም። እኛ ግን በገዛ አገራችን አልሰራንም። የውጫሌ ውል ጣጠኛ ውል ቢሆንም ቢያንስ ታሪካችን ስለሆነ ልንዘክረው ይገባል” ነው ያሉት።

ዞሮ ዞሮ ሁሉንም ፍላጎት ማሳካት ባይቻልም ቢያንስ እንደመንደርደሪያ ጀግኖቻችንን ከዘከርን፣ ታሪካችንን ካወሳን፣ ወደፊትም ተግባቦታችን ተጠናክሮ፣ ኢትዮጵያዊነት ለምልሞ ብሩህ ዘመን ይመጣ ይሆናል።

ምናልባት እነዚህና መሰል ተግባራት ሲከናወኑ ቋሚ መዘከር በማቆም ከታሪክ ተወቃሽነት ያድናል። ሉላዊ ድላችንን መዘከሩ በታሪካችን መኩራት ነው! ሰማዕታትን ማክበር ነው! የአብሮነት እሴቶችን መንገር ነው!!

Published in መጣጥፍ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን