አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 01 March 2018

ጎንደር የካቲት 22/2010 ወጣቱ ትውልድ የቀደምት አባቶቹን የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ በመዘከር ለሀገር አንድነትና ሰላም በጋራ ሊቆም እንደሚገባ ምሁራንና አባት አርበኞች ተናገሩ፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ ማህበረሰብ አባላትና የጎንደር ከተማ ጀግኖች አርበኞች 122ኛውን የአድዋ ድል በአል በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ በጋራ  አክብረዋል፡፡

በበአሉ ላይ የተገኙት አባት አርበኛ ሃምሳ አለቃ ወርቁ መኮንን እንደተናገሩት የአድዋ ድል ለወጣቱ ትውልድ አንድነትን ፍቅርን ለጠላት አይበገሬነትንና ለሀገር መስዋእት መሆንን የሚያስተምር ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ አሻራ ነው፡፡

የጎንደር ዩንቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶክተር አስራት አጸደወይን ''የአደዋ ድል የማንነታችንና የቀደምት ስልጣኔያችን መገለጫ ህያው ታሪካችን ነው'' ሲሉ ተናግረዋል፡፡

''የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በመላው አለም የሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ድል ነው'' ያሉት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ወጣቱ ትውልድ ከዚህ የታሪክ ማህደር በርካታ ቁምነገሮች ሊማር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ ምክትል ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ በበኩላቸው የአድዋን ድል ከመዘከር ባለፈ ወጣቱ ትውልድ የራሱን ታሪክ ሰርቶ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ አለበት፡፡

በአድዋ ጦርነት ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ  ያቀረቡት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር ዶክተር ፈንታሁን አየለ በበኩላቸው በአድዋ ጦርነት የሴቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ለጀግኖች አባቶቻችን ድል መቀዳጀት ሴቶች ስንቅ በማቀበል ቁስለኛ በማግለል የጦር ሰፈር በመጠበቅ ካደረጉት የጀግንነት ውሎ በሻገር በውጊያ ግንባር ጭምር በመሰለፍ የከፈሉት መስዋእትነት በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡

''ዝክረ አድዋ'' በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በአል ላይ እለቱን የሚዘክሩ የሙዚቃና የድራማ ትእይንቶች የቀረቡ ሲሆን˝በአድዋ ድል የሴቶች ተሳትፎ’’ በሚል ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጓል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  የካቲት 22/2010 አሁን አሁን የተለያዩ ሱስ አስያዥ ዕፆችን የመጠቀም ነገር እየሰፋ፤ ከበድ ያለ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ቀውስም እያስከተለ፤ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ለተለያዩ ጉዳቶች እየዳረገ ይገኛል።

በተለይም ወጣቱ ለጫት፣ ለሲጋራና ከዛም ከፍ ሲል ለሌሎች አደንዛዥ ዕፆች ሱሶች እየተዳረገ ሲሆን ችግሩ በተለይ በነገው አገር ተረካቢ  ትውልድ ላይ የሚያደርሰውን የስነ ልቦናና የጤና ችግር አስከፊነት መገመት አያዳግትም።

አቶ ተመስገን ወልዴ ይባላሉ፤ ወደ ሱስ ከገቡ ረጅም ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ይናገራሉ። በአቻ ግፊት፣ዘና ለማለት እንዲሁም የማወቅ ጉጉትን ለማርካት በሚል በተለያዩ ሱሶች መጠመዳቻውንም ይናገራሉ።

ይሁንና ወደ ሱስ መግባታቸው ከትዳራቸው፣ ከልጃቸው ብሎም ከማህበረሰቡ እንዲገለሉ ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ።

በዚህም ከፍተኛ የስነ ልቦና ስብራት እንደደረሰባቸውንና የእድሜያቸውን ግማሽ ባላስፈለጊ ድርጊት ውስጥ ማሳለፋቸውን ያወሳሉ።

ይሁንና ከችግሩ በመላቀቅ ለመለውጥና ወደ ቤተሰባቸውና ማህበረሰቡ ለመቀላቀል ፍላጎት ያላቸው በመሆኑ፤ ከሱስ ለማገገም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እየተሰጠ ያለውን የሱስ ማገገም ህክምና ለማግኘት መወሰናቸውን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ምህረቱ ዘውዱ በትምህርት ደረጃው ባለዲግሪ ቢሆንም በሱስ ምክንያት ግን እራሱን መለወጥ ባለመቻሉ ምክንያት ለጉዳት መዳረጉን ያስረዳል።

ይሁንና ከሁለት ወራት በፊት  በፍቃደኝነት ወደ ሆስፒታሉ  በመምጣት የህክምና አገልግሎት እያገኘ እንደሆነና በዚህም ለውጥ ማምጣቱን ገልፆ ባለሙያዎች የሚያደርጉለት ድጋፍና ክትትል ለውጥ እንዲያመጣ እንደረዳው ይገልጻል።

አቶ ካሳሁን ኪሮስ በበኩላቸው በሱስ መጠመዳቸው ከስራቸው ለመፈናቀል ምክንያት እንደሆነና ለብዙ ችግር እንደዳረጋቸው በማስታወስ በፍቃደኝነት ወደ ማገገሚያ ማዕከሉ ለመምጣት መወሰናቸውን ይናገራሉ።

ወጣቶች በሱስ ከመጠመድ ተቆጥበው ቤተሰቦቻቸውን፣ ህብረተሰቡንና አገራቸውን በመጥቀም ረገድ የጎላ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ታካሚዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

አደገኛ ዕፆችን የመውሰድ ልማድ በዓለም ላይ በእጅጉ እየተስፋፋ መምጣቱን በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያመላክታሉ።

በአደገኛ ሱሶች የተጠመዱ ሰዎች ምርታማነታቸው በመቀነሱ ሳቢያ ለገቢ መቀነስ፣ የሕክምና ወጪ መጨመርና ለወንጀል ድርጊቶች ያላቸውን ተጋላጭነት እንደሚጨምረው ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ ችግሩን ለመከላከል ከጥቂት ዓመታት በፊት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከሱስ የማገገም ህክምና ተክፈቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅም ከገቡበት ሱስ ለመውጣት በፍቃደኝነት የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይገልፃል።

በሆስፒታሉ የህክምና አገልግሎት ምክትል ኃላፊ ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ እንደገለጹት፤ በማዕከሉ ከዚህ ቀደም ለህክምና አገልግሎቱ የሚያገለግሉ ክፍሎች ውስን ነበሩ።

በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ እየተሰጠ ያለው ከሱስ የማገገም ህክምና ከ10 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በዓመት በአማካኝ ከስልሳ በላይ ታካሚዎች አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ከሆስታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2010 በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ በህክምና ስህተት ጉዳት ለደረሰበት ኢትዮጵያዊ ህጻን የተወሰነውን የ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሪያል ካሳ ለማስፈጸም እየሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሳኡዲ አረቢያ ጤና ጥበቃ የሃኪሞች ስህተት ማቅረቢያ ቦርድ በኢትዮጵያዊው ህጻን መሀመድ አብዱልአዚዝ ላይ የተፈጸመውን የህክምና ስህተት ተከትሎ ካሳ እንዲከፈል ያሳለፈው ውሳኔ ተግባራዊ እንዲደረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል።

በጅዳ የሚገኘው የኢፌድሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በጉዳዩ ዙሪያ የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ.ም ከሃገሪቱ የህክምና ቦርድ እና መካ ከሚገኘው የሃገሪቱ ጤና ጥበቃ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጋር መነጋገሩ ተገልጿል።

በዚህም በህፃኑ ላይ ለደረሰው አካላዊ ጉዳት ሆስፒታሉ የ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሪያል የካሳ ክፍያ እንዲፈጸም የተላለፈው ውሳኔ እንዲፈፀም ኦርጂናል ሰነድ እንዲያቀርብ በአገሪቱ ጤና ጥበቃ መጠየቁ በመግለጫው ተጠቁሟል።

የህክምና ስህተቱን የፈጸመው ሆስፒታል ካሳ እንዲከፍልና ውሳኔውን ተፈፃሚ ለማድረግ ለመካ ሪጅን የጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት ኦርጂናል ሰነዱን እንዲያቀርብ ለየካቲት 25 ቀን 2010 ዓ.ም ተቀጥሯል።

የቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ውሳኔው እንዲፈፀም ጉዳዩን ከሳዉዲ መንግስት አካላት ጋር የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል

 

 

Published in ማህበራዊ

የካቲት 22/2010 በቡራዩ ከተማ  በ708 ሚሊዮን በር ወጪ  የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤት እያስገነባ መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር  ገለጸ፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂ ጌታሁን መኩሪያ የአካባቢው ማህበረሰብ ፕሮጀክቱን በእኔነት ስሜት እንዲደግፈው እና እንዲጠብቀው አደራ ብለዋል፡፡

በአካባቢው የሚገነባው ትምህርት ቤት በአገሪቱ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎች የሚማሩበትና ጥሩ አስተሳሰብ ይዘው አንዲያድጉ የሚደረግበት እንደሚሆንም ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ  አገሪቱን ሊያስጠሩ የሚችሉ ፤በዓለም ላይ ተወዳደሪ የሆኑና እውቀት ያላቸው እንዲሁም የተለያዩ የግኝት ስራዎችን የሚሰሩ ተማሪዎች የሚፈሩበት እንደሚሆንም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የከተማ ነዋሪውም አሁን እየደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማጠናከር ለትምህረት ቤቱ ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርግ  ጥሪ አቅርበዋል።

መንግስት በ708 ሚሊዮን ብር እያስገነባ ያለው ይህ ትምህርት ቤት ግንባታ በዚህ ዓመት የተጀመረ ሲሆን በአንድ ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ግንባታው እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2010 122ኛው የአድዋ ድል በዓል በአዲስ አበባ በምንሊክ አደባባይና አድዋ ድልድይ በድምቀት እንደሚከበር ተገለፀ

ኢትዮጵያን ጥቁር ህዝብ ከቅኝ አገዛዝ መላቀቅ እንደሚቻል ያስተማሩበት የአድዋ ድል በአገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የጣሊያንን ሰራዊት ድል ባደረገችበት የአድዋ ተራራ ነገ ይከበራል።

በመዲናዋ አዲስ አበባም በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በከተማ አስተዳደሩ አዘጋጅነት በምኒልክ አደባባይና በአድዋ ድልድይ በድምቀት እንደሚከበር ነው የከተማይቱ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያስታወቀው።

በቢሮው የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ከፍተኛ ባለሙያ መምህር መክበብ ገብረማርያም ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት የመዲናዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ፣አባት አርበኞች፣ወጣቶችና የከተማዋ ነዋሪዎች በተገኙበት በምኒሊክ አደባባይ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ትርዒቶች ይከበራል።

ምኒሊክ አደባባይ የሚደረገው ስነ-ስርዓት ከተጠናቀቀ በኋላም ጣልያንን ያሸነፉት አርበኞች የተሻገሩበት ቦታ ላይ አዋሬ አደባባይ አካባቢ የሚገኘው የአድዋ ድልድይ በመሄድ አባት አርበኞች በወቅቱ እንዴት ድልድዩን ተሻግረው እንደሄዱ የሚያሳይ ትርዒት እንደሚቀርብ መምህር መክበብ ተናግረዋል። 

የዳግማዊ ምንሊክ ሀውልት እድሳት እየተደረገለት ቢሆንም ለበዓሉ ድምቀት ሲባል አጥሩ ተነስቶ ለእይታ ክፍት ይሆናል ብለዋል።

የአጥሩ መነሳት በጥገናው ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ እንደማይፈጥርበት እና ከበዓሉ ማግስት ጥገናው እንደሚቀጥል ገልፀዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2010 በኦሮሚያ ክልል የጤና ሽፋኑን ለማሳደግ 60 አምቡላንሶች ተገዝተው አገልግሎት መስጠት መጀመራችውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

ተጨማሪ የ540 አምቡላንሶች ግዥ እየተከናወነ መሆኑም ተገልጿል።

የግዥ ሂደታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቁትም ሆኑ በግዥ ሂደት ላይ ያሉ አምቡላንሶች የክልሉን የጤና ሽፋን በማሳደግና በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ከፍ በማድረግ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸውም ተጠቁሟል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት ለተገዙት 60 አምቡላንሶችና በግዥ ሂደት ላይ ላሉ 540 አምቡላንሶች 600 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል።

ለአምቡላንሶች ግዥ የክልሉ መንግስት  200 ሚሊዮን ብር፣ ከህዝቡ የተዋጣ 100 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 300 ሚሊዮን ብር ነው መከናውኑም ተገልጿል፡፡

በግዥ ሂደት ላይ ያሉት 540 አምቡላንሶች እስከሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ አገር ውስጥ  ገብተው ለአገልግሎት እንደሚበቁም ዶክተር ደረጄ ገልጸዋል።

የሚገዙት አምቡላንሶች ሰፊ የህብረተሰብ ክፍል በሚኖርባቸው፣የመንገድና የህዝብ ማጓጓዣ እጥረት ባለባቸው፣በድርቅ የተጎዱና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ሰዎች በሚገኙባቸው አካበቢዎች እንደሚሰራጩ ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ቦረና፣ ጉጅ፣ ምዕራብ ጉጅ፣ምስራቅና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እንደሚከፋፈሉ የቢሮ ሀላፊው ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በክልሉ 500 አምቡላንሶች መኖራውን በማስታወስ እነዚህ ሲጨመሩ የአምቡላንሶችን ቁጥር ከ1 ሺህ በላይ እንደሚያደርሰውም ጠቁመዋል።

በክልሉ የእናቶች በጤና ጣቢያ የመውለድ መጠን 70 በመቶ መድረሱን ያስታወሱት ዶክተር ደረጀ በቤታቸው የሚወልዱ እናቶች በጤና ጣቢያ እንዲወልዱ ለማድረግ አምቡላንሶቹ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል  ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

ቡራዩ የካቲት 22/2010 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለቡራዩ ከተማ ነዋሪዎች በሁለት ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አስመረቀ።

ፕሮጀክቱ በአካባቢው ይስተዋል የነበረውን የውሃ አቅርቦት ችግር እንደሚፈታላቸው ነዋሪዎቹ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

2 ሚሊዮን ብር የፈጀውን የዚህን ፕሮጀክት ግንባታ በተቋራጭነት ወስዶ ያከናወነው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት መሆኑም ታውቋል።

የንፁህ ውሃ አቅርቦቱ ከዚህ በፊት የነበረውን የውሃ ችግር ይቀርፍልናል ሲሉ ነው ኢዜአ ያነጋገራቸው የቡራዩ ከተማዋ ነዋሪች የተናገሩት።

ከዚህ በፊት በአካባቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ ለማግኘት ከግማሽ ሰዓት እስከ  አንድ ሰዓት የእግር ጉዞ ይወስድብን የነበረውን ድካም ያስቀርልናል ብለዋል ነዋሪዎቹ።

በቡራዩ ከተማ የገፈርሳ ጉጄ አካባቢ ነዋሪ  ወይዘሮ ዳዶ ወቅቶላ ከዚህ በፊት የወንዝ እና የምንጭ ውሃ እንደሚጠቀሙ ገልጸው ይህም በልጆቻቸው እና በራሳቸው ጤና ላይ ጉዳት እንዳደረሰባቸው ተናግረዋል።

አሁን የንጹህ መጠጥ ውሃ ማግኘታቸው ችግሩን እንደሚቀርፍላቸው ተናግረው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በአካባቢው የሚያስገነባው የልዩ ተሰጥኦ ትምህርት ቤት ሲጠናቀቅ እንደሚንከባከቡ ገልጸዋል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አልማዝ ወዳጆ በበኩላቸው ከዚህ በፊት የንጹህ መጠጥ ውሃ ለመቅዳት ረጀም ርቀት እንደሚሄዱና እሱንም ለመግኘት ብዙ ሰልፍ ስለሚኖረው ብዙ ጊዜ እንደሚወስድባቸው ጠቁመዋል።

ለምግብ ማብሰያነትና ለሌሎች ነገሮች የሚገለገሉበትን ውሃ ከወንዝ ለመቅዳትም ረጅም ርቀት መጓዝ የግድ እንደነበር በማስታወስ አሁን ግን ይህ ሁሉ ችግር ይፈታልናል ነው ያሉት ወይዘሮ አልማዝ።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆኑ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

የማህበረሰብ የውሃ ችግር ለመቀነስ የተገነባውን የውሃ ፕሮጀክት የአካባቢው ነዋሪዎችና አመራሮች በተገኙበት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2010 የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ ተራዘመ።

ምርጫ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ ለመወያየት የፊፋ ልዑክ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ተገለጸ ።

የፌደሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ጸሐፊ  አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፊፋ በትናትናው ዕለት ለፌደሬሽኑ በላከው ደብዳቤ አማካኝነት ምርጫው ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።

ባለፈው ጥር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን ለፊፋና ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ ቀድሞ እንዲያሳውቅ ቢጠየቅም ባለማሳወቁ ምክንያት ምርጫው ሊራዘም መቻሉን ፊፋ በላከው ደብዳቤ ማሳወቁንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ምርጫው የሚካሄድበት ቀንና በአጠቃላይ የፌደሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አጀንዳ ቀድሞ ለክልል እግር ኳስ ፌደሬሽኖች አለመድረሱ  ምርጫው እንዲራዘም ያደረገው ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ምርጫ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማድረግ በሚቻልበት ዙሪያ ለመወያየት የፊፋ ልዑክ መጋቢት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።

የፊፋ ልዑክ በምርጫው ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን ይፋ እንደሚደረግ ነው አቶ ሰለሞን ያብራሩት።

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ማህበር የውይይቱ መካሄድ በምርጫው ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ምርጫው ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ በላከው ደብዳቤ ላይ ጠቅሷል።

Published in ስፖርት

የካቲት 22/2010 ትውልዱ አንድነቱን በማጠናከር አገሩን በማሳደግና በመጠበቅ የአድዋን ድል ሊደግመው እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

122ኛው የአድዋ ድል በአል አስመልክቶ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡

የበአሉ ተሳታፊ የሃይማኖት አባት መምህር ሊቀ አድባር ተገኝ  በሰጡት አተያየት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አገራችን በውጭ ሃይል እንዳትወረር ውድ ህይወታቸውን ሰውተው ለዛሬዋ ታላቅ ቀን አብቅተውናል፡፡

ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመንቀሳቀስ ያስገኙትን ድል የአሁኑ ትውልድ በሚገባ በመረዳት  የትላንት ጀግኖች ያወረሱትን ነጻና የተከበረች አገር መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ሌላው የበአሉ ተሳታፊ የአዲስ አበባ አረጋውያን ማህበር ፕሬዘዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሌ አባቶቻችን እጅ ለእጅ ተያይዘው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ኩራት የሆነ ድል አስመዝግበዋል ፡፡

አባቶቻችን ያስረከቡንን አገር በአንድነት በመጠበቅና የተጀመሩትን የልማት ስራዎች ከዳር በማድረስ የኢትዮጵያን ህዳሴ ማብሰር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በአድዋ የተገኘው ድል በልማት እንዲደገም የአገሪቷን ሰላም በመጠበቅ ሁሉም የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ እንደሚገኝ የተናገረው ደግሞ የኤፌድሪ መከላከያ ሰራዊት አባል ኮለኔል ካህሳይ በርሄ ነው፡፡

በአድዋ ድል የተገኘውን የኢትዮጵያ ጀግንነት ታሪክ በልማት ለመድገምና የአገሪቱን ሰላም ለመጠበቅ ሰራዊቱ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የአድዋ ድል እጅግ የሚያኮራ መሆኑን የጠቀሰው ወጣት ይበልጣል አሰፋ ለዚህ ላበቁን አያት ቅድመ አያቶቻችን ምስጋናና ክብር እንደሚገባቸው ተናግሯል፡፡

ሰንደቅ አላማችን የበለጠ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ወጣቱ ከፍተኛ ሃላፊነት ያለበት በመሆኑ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል ነው ያለው ወጣት ይበልጣል፡፡

የአድዋን ድል አስመልክቶ ጥናት ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚክ ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ጌታቸው አድዋ የብሄር ብሄረሰቦች በጋራ የስገኙት ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ ድል መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ዛሬም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ልክ እንደ አድዋው ድል በአንድነቱ በመጽናትና በመተባበር አገሩን መጠበቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አፈጉባኤ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን  በበኩላቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በባዶ እግሩ በርካታ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ በኋላቀር መሳሪያ ድል ያደረገበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የበለጸገችና ሰላሟ የተጠበቀች አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ዜጎች የውጭም ሆነ የውስጥ ጠላቶች ሰለባ እንዳይሆኑ እጅ ለእጅ ተያይዘው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
የአድዋ ድል በዓል ነገ በአዲስ አበባ ሚኒሊክ አደባባይ ይከበራል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

ፍቼ የካቲት 22/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ በዞኑ የትምህርት ባለድርሻ አካላት ተናገሩ።

የዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፍት ቤት ከዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች ከተውጣጡ 630 የትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በፍቼ ከተማ መክሯል።

በወቅቱም ባለደርሻ አካላቱ በትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍንና የትምህርት ጥራት አንዲጠበቀ ለሰላምና መረጋጋት ቅድሚያ ትኩረት ሰጠተው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።  

ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎቹ  መካከል የግራር ጃርሶ ወረዳ የሃገር ሽማግሌ የሆኑት ኮሎኔል ገዝሙ ጋዲሳ  እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን እያወኩ መጥተዋል።

በትምህርት ቤቶች ውስጥ  ንብረት የማጥፋትና የስርቆት ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን ጠቅሰው እንዲህ አይነት የስነ ምግባር ችግር በቀጣይ እንዲታረም ወጣቶችን በመምከርና በመገሰጽ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በየትምህርት ቤቱ ተግባራዊ የተደረገው የትምህርት ጥራት ፓኬጅ ስኬታማ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሰሩም አመልከተዋል።

በተለይ ሕብረተሰቡ ለተቋማቱ እያደረገ ያለው የገንዘብ፣ የጉልበትና የእወቀት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር የተለየ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም አመልክተዋል ።

የጅዳ ወረዳ ተሳታፊ መምህር ፈይሴ ዘውዴ በበኩሏ በጥሩ ስነ-ምግባር የታነፀ ዜጋ ለማፍራት በሚከናወኑ ተግባራት የራሷን ኃላፊነት እንደምትወጣ ተናግራለች።

አንዳንዴ በትምህርት ቤቶች የሚስተዋለው ሁከትና ግርግር የመልካም አስተዳደር እጦትና ብልሹ አስራር ውጤት መሆኑን የገለፀችው መምህር ፈይሴ፣ በቀጣይ ለመፍትሄው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደምትሰራ ተናግራለች ።

የአብቹ  ሚኣ ወረዳ ወላጅ መምህር ሕብረት ተወካየ አቶ ተስፋዬ  መኮንን  በበኩላቸው በቀላሉ ሊፈቱ በሚችሉ ጥቃቅን ችግሮች በመነሳሳት  ንብረትን ማውደምና የትምህርት ጊዜ ማባከን ተገቢነት አንደሌለው አመልክተዋል።

የህዝቡን ፍላጎትና ጥያቄዎች ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የዞን መስተዳድሮች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሲቪክ ማህበራት እርስ በእርስ  ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ መምህራንና ወላጆች ትምህርት ቤቶች ወጣቶች በስነ -ምግባርና በእውቀት ታንጸው የሚወጡበት ጠንካራ ተቋማት እንዲሆኑ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል ።

የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን አልዩ በምክክር መድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ትምህርት ለሀገር እድገትና ልማት ወሳኝ መሳሪያ በመሆኑ ሕብረተሰቡ በእውቀት፣ በጉልበትና በቁሳቁስ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ ኃይሎችንም መምከርና ማስተማር የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ።

የክልሉ መንግስት የሕብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ አንዲያደርጉ አስገንዝበዋል ።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን