አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 09 February 2018

አዲስ አበባ የካቲት2/2010 በዐብይ ጾም የሃይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች የሠላም አጀንዳ ዕለታዊ ሥራቸው እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንዲሁም የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት አብያተ ክርስቲያናት የፊታችን ሰኞ የሚጀመረውን ዐብይ ጾምን አስመለክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ የዐብይ ጾምን አስመልክቶ ለእምነቱ ተከታዮች ባስተላለፉት መልእክት "ወርሃ ጾም መንፈሳዊ ኃይላችንን የምናጎለብትበት፣ ጥላቻ፣ የእርስ በእርስ ጥርጣሬን የምናደክምበትና የምናስቀርበት ነው" ብለዋል።

በዚህ የጾም ወቅት ምእመኑ ለአገሪቱ አንድነት፣ ለሕዝቦች ልማትና ብልጽግና እንቅፋት የሚሆኑ እንዲሁም ለሕይወትና ንብረት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ግጭቶችን ለማረም እንዲጸልዩ ጠይቀዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በተለይም ወጣቱ በዚህ ቅዱስ ወርሃ ጾም ወደ ልቡ ተመልሶ ነገሮችን አርቆ ማየት ይኖርበታል ነው ያሉት።

ምዕመናን ከግጭት፣ ጥላቻና መለያየት በመራቅ የሠላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና ይቅር ባይነትን ባህል በማሳደግ ስለ ሃይማኖትና አገራዊ ዘላቂ ጥቅሞች አብዝቶ በመጸለይ መፍትሄ የሚያበጅበት ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።

በየአካባቢው ያሉ የሐይማኖት መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች በጾሙ ወቅት የሰላም አጀንዳን እለታዊ ስራ አድርገው ወጣቱን ትውልድና ህዝቡን እንዲመክሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በፆሙ ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች አቅም በፈቀደ መጠን የተራቡትን በማጉረስ፣ የተራቆቱትን በማልበስ ጾሙን እንዲያሳልፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ -ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌልም የጾሙን መግቢያ አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት አማኞች በዓበይ ጾም ወቅት ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ሰላም ከልብና በእውነተኛ ስሜት መጾምና መጸለይ ይገባቸዋል ብለዋል።

"ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ሁሉ በጥበብ  ፍትህ እንዲሰጡና እውነተኛ የሕዝብ የጋራ ጥቅም የሚያመጣ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲወስኑ በጾምና በጾሎት መትጋት ይገባል" ብለዋል።

ይህ ታላቅ የጾምና የጾሎት ወቅት የሰው ክብር የሚጠበቅበት፣ ፍትህና ሰላም የሚሰፍንበት ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተለይ ካቶሊካዊያን ጾሙን የሚጾሙት ከሀሜት፣ ከቅናት፣ ከክፋት፣ ከቂም በቀል፣ ከጥላቻና ከብጥብጥ በመራቅ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ብቻ ሳይሆን ወደ ባልንጀራችን ለመቅረብም ሊሆን እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የዓብይ ጾም የካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ይጀመራል።

 

 

Published in ማህበራዊ

መካነ ሠላም የካቲት 2/2010 በደቡብ ወሎ ዞን ለሚ ሮቢቴ ከተማ በ14 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ከጀርመን የኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተሰራው ፕሮጀክቱ፤ በወጊዲ ወረዳ ጣዬ፣ አቦቴ እና ሰፈር ቀበሌዎች የሚገኙ ከ6 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ለሚቀጥሉት 30 ዓመታት ተጠቃሚ ያደርጋል።

በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የቦረናና ወጊዲ ፕሮጀክቶች ስራ አስኪያጅ አቶ አዳነ ንጉሴ እንደገለጹት፤ የለሚ ሮቢቴን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ለማጠናቀቅ ሁለት ዓመት ፈጅቷል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሆኑት ነዋሪዎችም ፕሮጀክቱ ከውሃ ወለድ በሽታዎችና ውሃ ፍለጋ ከሚያባክኑት ጊዜና ድካም እንደታደጋቸው ነው የገለፁት።

በኢትዮጵያ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ዋና ኃላፊ ሚስተር ፒተር ሪነር እንዳሉት፤ ድርጅቱ በሀገሪቱ ላለፉት 36 ዓመታት የተለያዩ የልማት ተግባራትን አከናውኗል።

በግብርና፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ የውሃ ልማት፣ ትምህርት፣ የጤናና የጽዳት አገልግሎት እንዲሁም የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ከ5 ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በተቀናጀ የገጠር ልማት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ እንደሆኑም ነው የገለጹት።

በቀጣይ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ጥናትና ምርምሮችን መሰረት ያደረጉ የተቀናጀ የገጠር ልማት ስራዎችን ድርጅቱ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ድርጅቱ በወጊዲ ወረዳ ከንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ባሻገር የክትባት፣ የዓይን ህክምና፣ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ነው የተነገረው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 2/2010 ፈዋሽነታቸው በቤተ ሙከራ በተረጋገጡ 12 ዕፅዋት ላይ መድኃኒት እየቀመመ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት በባህል ህክምና ዙሪያ ፈዋሽነት አላቸው በሚባሉ እጽዋት ላይ ባደረገው ጥናት በቤተሙከራ የተረጋገጡ 70 እጽዋት መለየቱን ገልጿል።

በኢኒስቲትዩቱ የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ አሸንፍ ታደለ እንደገለጹት፤ የባህል መድኃኒቶች ለህብረተሰቡ የሚሰጡት ጥቅም ከፍተኛ ነው።

በዚህም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ለመድኃኒትነት ይጠቅማሉ ተብለው የሚገመቱ አንድ ሺህ እጸዋት መኖራቸውን በጥናቱ አመላከተዋል።

ከእነዚህ እጽዋት መካከል ፈዋሽነታቸው በቤተሙከራ ተረጋግጦ ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ ያላቸው 70 እጽዋት  መለየታቸውንም ገልጸዋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት ከእነዚህ ለተለያዩ በሽታዎች መድኃኒትነት አላቸው ከተባሉት 70 እጽዋት ውስጥ 12ቱ ውጤታማነታቸው ተረጋግጦ በቅመማ ደረጃ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

የጠጅ ሳር ዘይት፣ ሞሪንጋ (ሽፈራው)፣ ነጭ አዝሙድ፣ ብርብራ (አሳ ማስገሪያ) እና ነጭ ባህርዛፍ እጽዋት የመድኃኒት ቅመማ እየተካሄደባቸው ካሉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

ኢኒስቲትዩቱ በቀጣይም በተለይ በአዳዲስ  ፈዋሽ መድኃኒቶች ላይ ለሚያደርጋቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ስኬት ከዩኒቨርሲቲዎችና ከክልል የምርምር ተቋማት ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የአለም የጤና ድርጅት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2016 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው 80 በመቶ የሚሆኑ የእስያና የአፍሪካ አገራት ህዝቦች የባህል መድኃኒት ተጠቃሚ ናቸው።

 

 

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ የካቲት 2/2010 ኦሲፒ የተባለ የሞሮኮ ኩባንያ ሶስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በሆነ ወጪ  በድሬዳዋ የማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት እየተዘጋጀ መሆኑን ተገለጸ፡፡

የኩባንያው ባልደረቦች በፋብሪካው ግንባታ ዙሪያ ከድሬደዋ አስተዳደር የስራ ኃላፊዎች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የኩባንያው ከፍተኛ ኢንጂነር  ሐናን  አህመድኑር እንዳስታወቁት ኩባንያው በአካባቢው ሥነ-ምህዳር ላይ ተፅዕኖን በሚቀንስ መንገድ  በአምስት ዓመት  ውስጥ የፋብሪካንው  ግንባታውን  በማጠናቀቅ ማምረት ይጀመራል፡፡

በ300 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈውን የማዳበሪያ ፋብሪካውን ለመገንባት ከድሬደዋ አስተዳደር ጋር ስምምነት በማድረግ ለግንባታው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

"ፋብሪካው በዓመት ሁለት ሚሊዮን 400ሺህ ቶን ማዳበሪያ በማምረት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል" ብለዋል፡፡

በግንባታው ሂደት 1ሺህ 200 ሰዎች በጊዜያዊና ፋብሪካው ማምረት ሲጀምር ደግሞ ለ500 ሰዎች ቋሚ የሥራ ዕድል ያስገኛል ተብሏል፡፡ 

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው የዚህ ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ዕውን እንዲሆን አምና የሞሮኮ ንጉሱ ኢትዮጵያ  ተገኝተው ከጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የጋራ ልማት ለማከናወን የተስማሙበት  ውል ውጤት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"በአፍሪካ ደረጃ የመጀመሪያ የሚሆነው የማዳበሪያ ፋብሪካ ሀገሪቱ  ከውጭ የምታስገባውን ብዛት ያለው ማዳበሪያ በቀላሉ በማግኘት የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ያግዛል" ብለዋል፡፡

ፋብሪካው ማምረት ሲጀምር የቴክኖሎጂ  እውቀት ለመቅሰም እንደሚያስችል የጠቆሙት ከንቲባ ኢብራሂም የግብርና ምርትን በማሳደግ የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግሩ እውን እንዲሆን የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡  

ፋብሪካው በአካባቢው ላይ ሊያደርሰው የሚቻለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል የግምገማ ጥናት ለማካሄድ እንቅስቃሴ መጀመሩም ታውቋል፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲሰ አበባ የካቲት 2/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ  የቻይና ጉአንግዡ ባዪዩን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ባዘጋጀው የደንበኞች አውደ ርዕይ ላይ ከአስር ምርጥ ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች ውስጥ በማሸነፍ ተሸለመ፡፡

የአፍሪካ ትልቁ የጭነት ማጓጓዣ (ካርጎ) የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የጭነትና ማጓጓዣ አገልግሎት "የወጪና ገቢ ጭነት ማጓጓዣ ሽልማትን" ጥር 30 ቀን 2010 በቻይና ተቀብሏል።

የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማያርም፤ አየር መንገዱ በቻይና ምርጥ አስር ዓለም አቀፍ ካርጎ አጓጓዥ ውስጥ አሸናፊ በመሆኑ ደስታቸውን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ የጭነት ማጓጓዣ ትራንስፖርት አገልግሎት የአየር መንገዱን የ2025 ራዕይን ተግባራዊ በማድረግ ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። 

አየር መንገዱ የቻይና- አፍሪካ የአየር ኢንቨስትመንትና ንግድ ግንኙነትን በመደገፍ የመሪነት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ አጠቃላይ የማጓጓዣ ትራንስፖርት (ካርጎ) የ13 በመቶ ድርሻ እንዳላትም "ጉአንግዡ ባዪዩን" በተባለው የቻይናው ዓለም አቀፍ አየር መንገድ በተካሄደው ዓውደ ርዕይ ተገልጿል። 

አየር መንገዱ በአዲስ አበባ የሚገኘው ካርጎ ተርሚናል ብቻ በዓመት አንድ ሚሊዮን ቶን የመያዝ አቅም እንዳለው ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

ድርጅቱ በ44 ዓለም አቀፍ የጭነት ማጓጓዣ አውሮፕላኖች በአምስት አህጉሮች የጭነት አገልግሎትን የሚሰጥ ሲሆን ይህም የወጭና ገቢ ንግዶችን በማቀላጠፉ ረገድ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።     

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ የካቲት 2/2010 ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮችን አምሮ በመታገል የክልሉን ህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ እንደሚሰራ የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ( ጋህአዴን )አስታወቀ፡፡

የጋህአዴን ድርጅታዊ ኮንፍረንስ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የድርጅቱ ሊቀመንበር ጋትሉዋል ቱት በኮንፈረንሱ መክፈቻ  ወቅት እንደገለጹት ባለፈው ዓመት ተካሄዶ በነበረው የጥልቅ  ተሀድሶ ግምገማ ወቅት  በህዝብ የተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ድርጅቱ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን አዘጋጅቶ  ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡

በዚህም አበረታች ውጤቶች  መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የክልሉን መንግስት የሚመራው ጋህአዴን የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳዳር ጥያቄዎችን ለመመለስ የጀመራቸውን ጥረቶች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ በህዝቡ ለተነሱት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የተጀመሩት ስራዎች በተፈለገው ፍጥነት እንዳልተጓዙ አመልክተዋል።

በክልሉ  በተለይም የወጣቶችንና የሴቶችን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ ረገድ ሰፊ ስራን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ ወቅት የተለዩ የኪራይ ሰብሳቢነት፣የጠባብ ብሔረተኝናትና የብልሹ አሰራር ችግሮችን በመታገል በኩልም የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ የድርጅቱ ሊቀመንበር ተናግረዋል።

የድርጅቱ አመራሮችና መላ አባላቱ በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና  የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የህዝብ ንቅናቄ በመፈጠር ጠንክርው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳሰበዋል።

ድርጅቱ ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮችን አምሮ በመታገል በሁሉም ዘርፍ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰራ ለቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ 

ኮንፈረንሱ ከጥልቅ ተሀድሶው በኋላ የታዩ ውጤቶችንና ውስንነቶችን በመለየት ድርጅቱ በቀጣይ ለሚያከናውናቸው ስራዎች የተሻለ ግብዓት የሚገኝበት በመሆኑ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች የነቃ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል፡፡

የጋህአዴን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኡቡያ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በክልሉ በተካሄዱ የልማትና የፀረ- ድህነት ትግል ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ሆኖም ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራሮች በህዝቦች ተጠቃሚነትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ውስጥ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

"ለተጀመረው የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ እንቅፋት የሆኑ ብልሹ አሰራርና የኪራይ ሰብሳቢነትን እኩይ ተግባር ጠንክሮ መታገል ያስፈልጋል" ብለዋል።

ትናንት ማምሻውን የተጀመረውና  ለአራት ቀናት የሚቆየው ኮንፍረንሱ ድርጅቱ ባከናወናቸው ስራዎችና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።

ከ700 በላይ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች በኮንፍረንሱ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ

ሀዋሳየካቲት2/2010 በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች የሚያደርሱትን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል በተሰራው ሥራ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።  

በሲዳማ ዞን የምትገኘው ዳራ ወረዳ ባለፉት ስድስት ወራት ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች የሚያደርሱትን አደጋ በመቀነስና ሁሉም የሞተር አሽከርካሪዎች የአደጋ መከላከያ ቆብ እንዲጠቀሙ በማድረግ ሞዴል ሆና ተመርጣለች።  

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ለወረዳዋ ትናንት ባዘጋጀው የዕውቅና ስነ ስነስርዓት ላይ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ኮማንደር ታደለ ዋርዩ እንዳሉት ከባለሁለት እግር ተሽከርካሪ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የተሰራው ስራ ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡

ለእዚህም በዳራ ወረዳ ባለፉት ስድስት ወራት በባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ አንድ ቀላል ጉዳት ብቻ መድረሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በክልሉ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ጉራጌ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ዳውሮ፣ ከፋ፣ ሸካና ሲዳማ ዞኖች እንዲሁም ኮንታ ልዩ ወረዳ በሰሩት ሥራ በስድስት ወራት ውስጥ በእያንዳንዳቸው ከ100 እስከ 50 ይደርስ የነበረውን አደጋ በማውረድ ከ43 እስከ 1 ማድረስ ተችሏል፡፡

ከፍተኛ የሞተር ሳይክል ቁጥር ያለበት ሲዳማ ዞን በሚገኙ ወረዳዎች አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ሁለትና ከሁለት ሰው በላይ ጭነው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ መኖሩን አስታውሰው በዞኑ የዳራ ወረዳ ከአንድ ተሳፋሪ በላይ ባለመጫን ሞዴል መሆኗን ተናግረዋል፡፡

የዳራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ በበኩላቸው ወረዳውን ከሚያዋስኑ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በመሆን በህገ ወጥ የሞተር ሳይክል እንቅስቃሴ፣ በግጭት አፈታትና ወንጀል መከላከል ላይ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ  ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ታደሰ በበኩላቸው በባለ ሁለት እግር አሽከርካሪዎች ላይ አንዳንድ ያልተገቡ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።

ከሁለትና ሦስት ሰው በላይ ጭኖ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ መንዳት፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ሰሌዳ የሌላቸው ህገወጥ ተሽከርካሪዎች ይዞ  መንቀሳቀስ እንዲሁም ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ መንዳት ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሀ ጋረደው በበኩላቸው የባለሁለት እግር ሞተር ብስክሌት በራሱ ስጋት አለመሆኑን ነው የገለጹት።

"እያደገ ያለውን የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በመደገፍና በሕብረተሰቡ መካከል የሚደረገውን ሁሉንም ማህበራዊ እንቅስቃሴ በማፋጠን በኩል ዘመኑ ካመጣቸው ተሽከርካሪዎች አንዱ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ይገባል" ብለዋል።

በዳራ ወረዳ የባለሁለት እግር አሽከርካሪዎች በጥንቃቄ በማሽከርከርና በመጠቀም ለሰው ልጅ ሕይወት ዋጋ ሰጥተው ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ሥራ በመስራት የሚያኮራ ተግባር መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በወረዳው በተለይ ከባለ ሁለት እግር ተሽከርካሪ ጋር በተያያዘ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በማስቀረት የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በተከናወነው ተግባር ውጤት እንዲመጣ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አንድ የትራፊክ ፍሰት ባለሙያ የምክትል ሳጅንነት የማዕረግ እድገትና የገንዘብ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡

የዳራ ወረዳ ነዋሪና የባለሁለት አግር አሽከርካሪ የሆኑት አቶ አጌኛ ጥበበ በበኩላቸው ቀደም ሲል የአደጋ መከላከያ ቆብ መጠቀም ስላለው ፋይዳ ግንዛቤ እንዳልነበራቸው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በማንኛውም ጊዜ የአደጋ መከላከያ ቆብ ከማድረግ ባለፈ ከአንድ ሰው በላይ ሳያሳፍሩ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በማሽከርከር አደጋን ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ህገወጥ የሞተር ተሽከርካሪዎች ወደወረዳው እንዳይገቡም በማህበራቸው አማካኝነት በመከታተል ህገወጦች ሲኖሩ ለመንግስት አሳልፈው እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ለፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊና አንድ ባለሙያ የገንዘብ ሽልማት ሲሰጥ ለወረዳው ዘመናዊ የሞተር ሳይክል ሽልማት እንዲሁም  የማህበረሰብ ፖሊሲ አገልግሎትን ለማጠናከር የ100 ሺህ ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

በደቡብ ክልል በተያዘው ዓመት ስድስት ወራት ከደረሰ 786 የትራፊክ አደጋ ውስጥ 244 በባለ ሁለት እግር ሞተር ሳይክል የተከሰተ ነው።

በባለ ሁለት ተሽከርካሪ በደረሰ በእዚህ አደጋም 80 ሰዎች የሞት፤ 160 ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘውን መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

ዲላ የካቲት 2/2010 በጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየንና በሰረንደም የገበያ ማዕከል ማህበር መካከል ለዓመታት የቆየው የኢንቨስትመንት መሬት ይገባኛል ክርክር በእርቅ ተቋጨ፡፡

ዕርቁን አስመልክቶ በዲላ ከተማ በተካሄደ የማጠቃለያ መርሀ-ግብር ላይ እንደተገለጸው የይገባኛል ክርክሩ በ2009 ዓ.ም መስከረም ወር በዞኑ ተፈጥሮ ለነበረው ሁከትና ግርግር ማቀጣጠያ ሰበብ ሆኖ ነበር፡፡

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ እንዳሉት በዲላ ከተማ ለሰረንደም የገበያ ማዕከል ማህበር እና ለይርጋጨፌ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን በተደራቢ ካርታ በተሰጠው የኢንቨስትመንት መሬት ምክንያት ሁለቱ ወገኖች ላለፉት ስድስት ዓመታት የይገባኛል ክርክር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

በወቅቱ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር በዞኑ በህዝቦች መካከል የነበረው አንድነትና መቻቻል እንዲላላ ማድረጉን ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው በተከናወኑ የዕርቀ-ሠላምና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች ሁኔታው ሊቀለበስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ በተካሄደ ዞንአቀፍ የእርቀ-ሠላም መድረክ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የይገባኛል ክርክሩ በሽምግልና እንዲፈታ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ሁለቱም ወገኖች ተስማምተው ጉዳያቸው በእርቅ ሊቋጭ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ዕርቀ-ሠላሙ እንዲሳካ የሰረንደም የገበያ ማዕከል ማህበር አባላት ቅድሚያ ለሠላምና አንድነት ትኩረት በመስጠት መሬቱን ለዩኒየኑ በመልቀቃቸውና አስታራቂ ሽማግሌዎችም ዋጋ ከፍለው ሲያደራድሩ በመቆየታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ህዝቡ አለመግባባቶችን በምክንያታዊነትና በሰከነ መንገድ ተወያይቶ የመፍታት ልምድን በማዳበር ለፀረ-ሠላም ኃይሎች አፍራሽ አጀንዳ ዕድል ሳይሰጥ ለዘላቂ ሠላም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዲላ ከተማ ከንቲባ አቶ ይመኑ ዳካ በበኩላቸው ሁለቱም ወገኖች መንግስት የንግዱን ማህበረሰብ ለማበረታታትና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በልማታዊ አስተሳሰብ የመሬት ጥያቄ ያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ለህዝቡ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት ሰላማዊ መንገድን በመምረጣቸው ሁለቱም ወገኖች አሸናፊዎች ናቸው" ያሉት ከንቲበው፣ የኢንቨስትመንት መሬቱ የተሰጠው ዩኒየንም ሆነ ተለዋጭ መሬት የሚሰጠው የሰረንደም የገበያ ማዕከል ማህበር ፈጥነው ወደ ልማቱ እንደገቡ አስገንዝበዋል።

ላለፉት ስድስት ዓመታት በክርክሩ ምክንያት ያባከኑትን ጊዜ ለማካካስ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

ሁለቱን ወገኖች ካደራደሩ ሽማግሌዎች መካከል አቶ አበበ ቢራራ ተከራካሪ ወገኖቹ ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ያሳዩት ፍላጎት ለእርቁ በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ ጠቀሜታ እንደነበረው ገልጸዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ አመራር አካላት ለሚነሱ አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ይሰጡ የነበረው ፈጣን ምላሽ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረጉን አምልከተዋል፡፡

አቶ አበበ እንዳሉት ሁለቱን ወገኖች ለዓመታት ሲያከራክር የቆየውና በኋላም ለግጭት ማቀጣጠያ ሰበብ የሆነው ጉዳይ መንስኤ በወቅቱ የነበረው አመራር የፈጠረው ስህተት ነው።

"ሁላችንም ለፀብ የሚዳርጉ ምክንያቶችን በማስወገድ ዘላቂ ሠላማችንን ማስጠበቅ ይኖርብናል" ብለዋል፡፡

"በመሬቱ ጉዳይ የህግ ባለመብቶች ብንሆንም ሽማግሌዎች ያቀረቡልንን ጥያቄ በመቀበል ለዘላቂ ሠላም ስንል ቦታውን ለዩኒየኑ ትተናል" ያሉት ደግሞ የሰረንደም የገበያ ማዕከል ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተካ በረዳ ናቸው፡፡

የይርጋጨፌ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታከለ ማሞ በበኩላቸው፣ የይገባኛል ጥያቄው በ2009 መስከረም ወር በዞኑ ተከስቶ ለነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ባይሆንም ግለሰቦች እንደማባባሻ የተጠቀሙበት መሆኑን አስታውሰዋል።

በዚህም መሬቱ ቢሰራበት ሊያስገኝ ከሚችለው ጥቅም በላይ በንብረትና በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ታከለ "በክርክር ያባከናቸውን ዓመታት መመለስ ባንችልም ይህን ማካካስ በሚያስችለን መልኩ ፈጥነን ወደ ልማት ሥራው እንገባለን" ሲሉም አመለክተዋል፡፡

በእርቅ ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ የተከራካሪ ወገኖች አባላት፣ የሃይማኖትና የባህል አባቶች፣ የአመራር አካላትና ከየወረዳው የመጡ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለሽምግልናው ሂደት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦችም በመርሃ ግብሩ ላይ የምስጋናና ዕውቅና ሽልማት መበርከቱን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

Published in ማህበራዊ


መቀሌ የካቲት 2/2010 በሁመራ ከተማ የተዘጋጀ የመላው ትግራይ ጨዋታዎች ላይ በክለብ ደረጃ የብስክሌትና ለመጀመሪያ ጊዜ ደግሞ የውሃ ዋና ውድድር እየተካሄደ ነው።

በብስክሌት ውድድሩ በሁለቱም ፆታ የጉና፣ የትራንስ ኢትዮጵያ፣ የመሰቦ ሲሚንቶ ፣ የብሩህ ተስፋ፣ የመቐለ ፣ የወልዋሎ ፣ የሰላም ቆርቆሮና ደስታ አልኮል ክለቦችን በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

በማውንቴ ብስክሌት ሴቶች 30 ኪሎ ሜትር በሸፈነ የዙር ውድድር መቅደስ አሰፋ ከመቐለ ፣ ትርሓስ ዳንኤል ከወልዋሎ እና ሜላት ዮሐንስ ከመቐለ በቅደም ተከተል ከአንደኛ እስካ ሶስተኛ በመውጣት አሸንፈዋል፡፡

በወንዶች 50 ኪሎ ሜትር ርቀት በሸፈነው ተመሳሳይ ውድድር ደግሞ አማኑኤል ሓዱሽ ከወልዋሎ አንደኛ ፣ፀጋዘአብ ብርሃነ ከወልዋሎ፣ ይትባረክ ታጀበ ከደስታ አልኮል ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አሸናፊ ሆነዋል፡፡

እንዲሁም በኮርስ ብስክሌት ሴቶች 45 ኪሎ ሜትርና በወንዶች የ50 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍኑ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በውጤቱም በሴቶች ሰላም ገብረህይወትና መርሃዊት ደስታ ከመስፍን ኢንጂነሪንግ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ፣ሱዛን ተወልደ ደግሞ ከመቐለ ከተማ ሶስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በወንዶች ደግሞ የብሩህ ተስፋ፣ ጉናና የትራንስ ኢትዮጵያ ክለብ ተወዳዳሪዎች ተከታትለው በመግባት አሸንፈዋል፡፡

በሌላ በኩል ለመጀመሪያው ጊዜ የተዘጋጀ የትግራይ የውሃ ዋና ውድድር ከትናንት ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን በወንዶች የ14 ወረዳዎች በሴቶች ደግሞ የአምስት ወረዳዎች ተወዳዳሪዎችን እየተሳተፉ ነው።

በዚህም የ50 ሜትር፣ የ100 ሜትር እና የ1ሺህ 500 ሜትር ነፃ ቀዘፋ፣ የደረት ፣ የቢራቢሮና የ100 ሜትር ዱላ ቅብብል የማጣሪያ ውድድሮች በሁለቱም ፆታዎች እየተካሄደ ይገኛል።

በ1 ሺህ 500 ሜትር ነፃ ቀዘፋ በወንዶች መካከል በተደረገው የፍፃሜ ውድድር አክሱም ከተማን ወክሎ የተወዳደረው ወጣት ዮናስ ርጥበይ በ24 ደቂቃ በ48 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆኗል።

ሰቲት ሁመራ ከተማን ወክሎ የተወዳደረው ወጣት አስመሮም አብርሃ ደግሞ በ28 ደቂቃ ከ10 ሰከንድ በመግባት ሁለተኛ ፣ በ28 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ በመግባት ሦስተኛ የሆነው ደግሞ የፀገዴ ወረዳ ተወዳዳሪው ወጣት ፋንታሁን አስናቀ ነው።

በሁመራ ከተማ ጥር27/2010ዓ.ም. የተጀመረው የመላው ትግራይ ጨዋታዎች በእስካሁኑ ቆይታ ከብስክሌትና ከውሃ ዋና ሌላ የእጅ ኳስ ፣ ቅርጫት ኳስ፣ የቼዝና የእግር ኳስ ውድድሮች በወረዳዎች መካከል ማጣሪያዎች ተካሄደዋል።

በወንዶች እግር ኳስ በወረዳዎች መካከል የተካሄዱ ውድድሮችን ያለመመጣጠን ችግር የታየ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ አንዳንድ ወረዳዎች በተገቢው ሳይዘጋጁ ለተሳትፎ ብቻ የቀረቡ በመሆናቸው ጨዋታውን አደብዝዞታል።

በዚሁ ውድድር ዓድዋ ከተማ ታህታይ ማይጨው ወረዳን ስምንት ለአንድ ፣ ኮረም ከተማ ደግሞ እንዳመሆኒ ወረዳን አስር ለባዶ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል፡፡

በቅርጫት ኳስ ሴቶች ዓድዋ ከተማ አክሱምን 30 ለ17 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

በተመሳሳይ በወንዶች መካከል በተደረገው ጨዋታ ኢሮብ ወረዳ አዲግራት ከተማን 32 ለ28 ፣ ፣ አክሱም ከተማ ማይጨው ከተማን 36 ለ14 በሆነ ውጤት ረትተዋል።

በጨዋታው በሁለቱም ፆታ የተሳተፉ ከ6 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች በ18 የስፖርት ዓይነቶች እየተፎካከሩ ነው፡፡

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ የካቲት 2/2010 በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ከነገ በስቲያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደቡብ ሱዳኑ ዋኡ ሳላም ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ የሚመሩት ዳኞች ዛሬ አዲስ አበባ  ይገባሉ።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ምንሊክ ግርማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ዳኞቹ ዛሬ ከሰአት  ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ይደርሳሉ።

ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት የሚመሩት እና ሁለቱ ረዳት ዳኞች ብሩንዲያዊ ሲሆኑ የጨዋታው ኮሚሽነር ከኬንያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የመሐል ዳኛው ጂዮርጂስ ጋቶ በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ደረጃ በማጫወት ልምድ ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የተጋጣሚው ቡድን ዋኡ ሳላም ቡድን ኃላፊዎች ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር ትናንት በጨዋታው ዙሪያ መነጋገራቸውንና ክለቡ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በተያያዘም ክለቡ ለእሁዱ ጨዋታ የተመነውን የስታዲየም መግቢያ ዋጋ ይፋ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ክቡር ትሪቡን አንድ ሺህ ብር፣ጥላ ፎቅ 200 ብር፣ ከማን አንሼ በወንበር 100 ብር፣ ከማን አንሼ ያለ ወንበር 50 ብር፣ ካታንጋ 30 ብር እንዲሁም ሚስማር ተራና ዳፍ ትራክ በተመሳሳይ 20 ብር መሆናቸውን አቶ ምንሊክ አብራርተዋል።

የመግቢያ ዋጋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ዓመት በሻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታውን ሲያደርግ ከነበረው ምንም ለውጥ እንደሌለውም አመልክተዋል።

ትኬት ለመቁረጥ የስታዲየም በሮች ከስድስት ሰአት ጀምሮ እንደሚከፈቱና ከጨዋታው በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡም አክለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በባለፈው ዓመት የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር የምድብ ድልድል ውስጥ በመግባት በኢትዮጵያ እግር ኳስ አዲስ ታሪክ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን