አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 08 February 2018

መቱ/የነቀምቴ የካቲት 1/2010 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ያሳለፈውን ውሳኔ በመደገፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ በመቱና በነቀምቴ ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

ነዋሪዎቹ በሁለቱ ከተሞች ለሚገኙ የኢዜአ ሪፖርተሮች እንዳሉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትን የሚመራው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስቀመጠው አቅጣጫ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ልማትና እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል ነው፡፡

በመቱ ከተማ የዜሮ ሁለት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ወንድሙ ደበላ  የድርጅቱ ውሳኔ የወጣቱን  የልማት  ጥያቄዎች ለመመለስ እንደሚስችሉ እምነት እንዳለው ተናግሯል፡፡

በክልሉ እየተነሱ ያሉ የልማት ተሳታፊነትና የወጣቶች ተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ  ለማበርከት ዝግጁ እንደሆነም ገልጿል።

በመቱ የሚኖረው የኢሉአባቦር ዞን ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ወጣት ታጠቅ ከፍያለው በበኩሉ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች የክልሉን ብሎም የሀገሪቱን የህዝቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከፌዴሬሽኑ አባላት ጋር በመሆን ለተግባራዊነቱ እንደሚረባረቡም ጠቅሷል።

ድርጅቱ "በኢንቨስትመንት ስም  የህዝብና የመንግስት መሬት መመዝበሩንና ይህንንም ለማስተካከል እንደሚታገል ማሳወቁ የሚበረታታ ነው" ብሏል  ወጣት ታጠቅ፡፡

የነቀምቴ ከተማ ነዋሪና በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ የምዕራብ ችሎት አቃቤ ሕግ አቶ ደረጃ አበበ በሰጡት አስተያየት ደግሞ " የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ለሕዝብ  ጥያቄ መልስ ሊሰጡ የሚችሉ ናቸው "ብለዋል፡፡

ለውሳኔው ተግባራዊነት ከድርጅቱ ጎን ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በነቀምቴ ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሰባት ነዋሪ ወይዘሮ ሣዲያ አብዱል ቃድር በበኩላቸው  "በመግለጫው የተመለከተው የድርጅቱ ውሳኔዎች በርካታ ጥቅሞች የሚያመጡ በመሆናቸው ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊደግፈውና ሊተገብረው ይገባል "ብለዋል ።

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ  የኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክተር ዶክተር ዘለቀ ተሸመ  "ውሳኔው ኦሮሞ  ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ሕዝቦች መብት የሚያስከብር በመሆኑ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች ልዩነት ሳይፈጥር ለተግባራዊነቱ መስራት ይኖርበታል "ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ደሣለኝ  ውሳኔው ትልቅና የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ በመሆኑ  እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2010 የህብረት ስራ ማህበራት ከአምራቾች ጋር ቀጥታ የገበያ ትስስር በመፈጠሩ የደላሎች ጣልቃ ገብነት እየቀነሰ መምጣቱን የህብረት ስራ ማህበራት ገለጹ።

አምስተኛው ሀገር አቀፍ የህብረት ስራ ሲምፖዚየም ዛሬ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ተጀምሯል።

ለሰባት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዚህ ሲምፖዚየም ላይ የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖችና የዘርፉ ምሁራን እየተሳተፉ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የህብረት ስራ ማህበራት አባላትና አመራሮች እንደሚሉት ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት የነበረው በአምራችና በህብረት ስራ ማህበራት መካከል ጣልቃ ሲገቡ የነበሩ ደላሎች መረብ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

የህብረት ስራ ማህበራት የአምራቹንና የዩኒየኖችን  ችግር በመረዳት ዩኒየኖች ቀጥታ ከአምራቹ እንዲገዙ ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠራቸው ነው ይላሉ።

በኦሮሚያ ክልል የጉሜ አዳማ ህብረት ስራ ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ለማ እንደሚሉት መንግስት ችግሩን አጥንቶ ግብይቱ ቀጥታ በገበሬውና በዩኒየኖች መካከል እንዲሆን ስላመቻቸ ቀደም ሲል ያለአግባብ ይጠቀሙ የነበሩት ደላሎችና ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ጣልቃ ገብነት ቆሟል።

ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በቆጂ ከማይካ ሁለገብ ህብረት ስራ ማህበር የመጡት አቶ ነጌሶ ዋሌ በበኩላቸው አምራቹ እንዳይጠቀም ጥቃቅን ነጋዴዎችና ደላሎች በመሀል ይገቡ እንደነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የቀጥታ ግብይት ስለተመቻቸ የነበረው ጣልቃ ገብነት ማቆም ብቻ ሳይሆን መንግስትና ዩኒየኖች የውጪ ገበያ ሰብረው ገብተው የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ መስራት አለባቸው ብለዋል።

የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር የህብረት ስራ ማህበራት አገሪቱን ከድህነት ለማላቀቀ አይነተኛ መፍትሄ በመሆናቸው ለአምራቹና ሸማቹ ህብረተሰብ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ተጨማሪ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ከ82 ሺህ በላይ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት 381 የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች እንዳሉ ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎባ/ ጅማ/ነገሌ/ ጊምቢ /ፍቼ የካቲት1/6/2010 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ለማጎልበት ገንቢ ሚና እንዳለው የአምስት ከተሞች ነዋሪዎች ገለፁ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ሪፖርተሮች የሰጡት የባሌ ሮቤ፣ የአጋሮ፣ የያቤሎ፣ የጊምቢና የፍቼ ከተሞች ነዋሪዎች እንዳሉት የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ አገራዊና ክልላዊ ጠቀሜታው የላቀ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማበርከት ተዘጋጅተዋል።

በሮቤ ከተማ የጨፌ ዶንሳ ቀበሌ ነዋሪ መምህር ግዛው ከበደ ድርጅቱ በመግለጫው ያስቀመጠው አቅጣጫ በሀገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በማጠናከር የሕዳሴ ጉዞን ለማሳካት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል በማለት ገልፀዋል፡፡

"ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አብዱረህማን ሀሰን በበኩላቸው ኦህዴድ በተለይ በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና በውጭ ሀገር ከሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ጋር አብሮ ለመስራት አቅጣጫ ማስቀመጡ የድርጅቱን ብስለትና አርቆ አሳቢነት ያሳያል" ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የሀገሪቱን የፖለቲካ ስነ- ምህዳር በማስፋት በኩልም ጉልህ ድርሻ ስለሚኖረው ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ነው የገለጹት።

 አቶ ሱልጣን መሀመድ የተባሉ የአጋሮ ከተማ ቀበሌ 03 ነዋሪ በበኩላቸው “ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል፣ ሰላምና ፍትህ እንዲሰፍን ኦህዴድ ያወጣውን መግለጫ ወደ ተግባር መቀየር ይኖርበታል" ብለዋል፡፡

ኦህዴድ የኦሮሞ ሕዝብ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በመተባበር የሀገሪቱን ቀጣይ ጉዞ የማቅናት ሚናውን እንዲያጠናክር ያስተላለፈውን ጥሪ በመቀበል ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ሌላው የአጋሮ ከተማ ነዋሪ ወጣት ምስጋናው ሰለሞን በበኩሉ ወጣቶች ሰላማዊ የትግል ስልት እንዲከተሉ በማስተማር የዴሞክራሲ ባህልን ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ማዕከላዊው ኮሚቴው በትኩረት ማያቱ እንዳስደሰተው ገልጿል፡፡

ኦህዴድ የወጣቱን ችግር ለመፍታትና አብሮ ለመስራት እያደረገው ያለውን ጥረት እንደሚደግፍም ወጣት ምስጋናው ተናግሯል።

በድርጅቱ መግለጫ ላይ የተላለፈው የሰላምና የልማት ጥሪ ወቅቱን ጠብቆ ለህዝብ የተሰጠ የተግባር ምላሽ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቦረና ዞን ያቤሎ ወረዳ የጮቃሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኪያቶ ጫጩ ናቸው።

የክልሉ ሕዝብ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመተሳሰብና በመረዳዳት ለሰላምና ለልማት እንዲሰራ የተላለፈው ውሳኔና ጥሪ ልዩነትን በማስወገድ መቀራረብን የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል።

የጊምቢ ከተማ ነዋሪ አባ ገዳ ተሊላ ቦጃ በበኩላቸው "ኦህዴድ ሰሞኑን የሰጠው መግለጫ አገራዊ አንድነትን በማጠናከር ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለተጀመረው ሁለንተናዊ የዕድገት በጋራ እንዲሰለፉ የሚቀሰቅስ ነው" ብለዋል።

"የአንድን ብሔር የበላይነት አግዝፎ ሌላውን አሳንሶ የማየት አስተያየት የማያዛልቅና ሊታረም የሚገባው መሆኑን ያመላከተ መግለጫ ነው" ሲሉም አባ ገዳው ተናግረዋል።

ዜጎች ሰላምና ፍትሕ በሰፈነበት አገር በደስታ እንዲኖሩ ከማዕከላዊ ኮሚቴው የተላለፈውን ጥሪ ተቀብለው ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ኦህዴድ የሕዝቡን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የጀመረውን የለውጥ ጉዞ እንደሚደግፉና ለተፈጻሚነቱም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ የፍቼ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የታሪክ መምህር ወይዘሮ ወይንሸት ደፋር ናቸው፡፡

"ወጣቶች ከኃይል በፀዳ መልኩ ሰላማዊ ትግል እንዲያካሂዱ የተላለፈውን ጥሪ ተቀብለን ለተግባራዊነቱ ከድርጅቱ ጐን እንሰለፋለን ያለው" ደግሞ የፍቼ ከተማ ወጣት ማህበር ተወካይ ዘሪሁን ዳሞታ ነው።

በተለይ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዲሳካም የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2010 የቦሌ ለሚ ቁጥር አንድና ሁለት የኢንዱስትሪ መንደር የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ኮርፖሬሽን ለኢንዲስትሪ ፓርክ ልማት ሲባል ከመኖሪያ ቀዬአቸው የሚነሱ አርሶ አደሮችን የሚደግፍና መልሶ የሚያቋቋም የስራ ዘርፍ በማደራጀት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።

ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ለቦሌ ለሚ ቁጥር አንድና ሁለት የኢንዱስትሪ መንደር የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ደረጃውን የጠበቀና ከወራት በፊት ተጠናቆ ስራ የጀመረ አንድ መዋዕለ ህጻናትና ግንባታቸው ያልተጠናቀቁ የከብትና የዶሮ ማርቢያ ሼዶችን አስመርቋል።

መዋዕለ ህጻናቱ በቦሌ ወረዳ 11 'ቦሌ ለሚ 'ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የተገነባ ሲሆን 12 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ተገልጿል።

የቤት እንስሳት ማርቢያ ሼዶቹ 10 ሚሊዮን ብር የፈጁ ሲሆን ተጠናቀው ለተጠቃሚዎቹ ለመተላለፍ የሁለት ወራት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯል።

በኮርፖሬሽኑ የተወዳዳሪነትና ስራ ፈጠራ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተሰማ ገዳ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ ለኢንዱስትሪ መንደር ግንባታው ከቀዬአቸው የተነሱ አርሶ አደሮች በሰፈሩበት አዲስ አካባቢ እንዳይቸገሩ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን እያሟላ ነው።

አርሶ አደሮቹ በማህበር ተደራጅተው ከብት እያደለቡ እንዲጠቀሙ 30 በሬዎች እንደተሰጧቸውና የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የተፋሰስ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ለምረቃ የበቃው መዋዕለ ህጻናት በአካባቢው የሚኖሩ 320 አባና እማወራ ልጆችን በበቂ ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚችልም ተናግረዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የአካባቢው ነዋሪዎች በአካባቢያቸው ህጻናት የሚማሩበት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰው የተገነባው ትምህርት ቤት ችግራቸውን እንደፈታላቸው ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እንደሚሉት የእንስሳት ማርቢያ ሼዶቹ ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቃቸው ለአርሶ አደሮች አልተላለፉም።

ግንባታው የሚከናወንበት ስፍራ በማሳ የተከለለና ወደ አካባቢው የሚወስድ መንገድም ባለመኖሩ ሼዶቹን በቶሎ ለማጠናቀቅ እንቅፋት መፍጠሩን ነው የተናገሩት።

አሁን ላይ በማሳዎቹ ላይ የነበረው ምርት እስኪሰበሰብ ተቋርጦ የነበረው የሼዶች ግንባታ ስራ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ወረዳው ከባለ ማሳዎች ጋር በመመካከር ወደ አካባቢው የሚያስገባ መንገድ ለመዘርጋት ቃል መግባቱንም አቶ ተሰማ አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2010 እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 746 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ በይቅርታ እንደሚለቀቁ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ገለጸ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ በተለያዩ ወንጀሎች የተፈረደባቸውና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የሚገኙ ግለሰቦች ጉዳያቸው እየታየ እንዲለቀቁ መወሰኑ ይታወቃል።

በይቅርታ የሚለቀቁት ሰው በመግደል፣ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ፣ የአገር ኢኮኖሚ ለማውደም በመሳተፍ፣ ህገ መንግስቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ያልተሳተፉ እንደሆኑም አስታውቋል።

በዚሁ መሰረት በፌደራል ደረጃ በሽብር፣ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሀይማኖት አክራሪነትና በተለያዩ ወንጀሎች የእስር ቅጣት ተላልፎባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 417 ታራሚዎች በይቅርታ ይለቀቃሉ ተብሏል።

በይቅርታ ከሚለቀቁ ታራሚዎች መካከልም 298ቱ በፌደራል ማረሚያ ቤት የሚገኙ ሲሆኑ 119ኙ በአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል።

እንዲለቀቁ ከተወሰነላቸው መካከል በሽብር ወንጀል ተከሰው በማረሚያ ቤት የሚገኙት እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌ ይገኙበታል።

በተመሳሳይ ጉዳያቸው በህግ በመታየት ላይ የነበሩ 329 ተጠርጣሪዎችም ክሳቸው እንዲቋረጥ ተወስኗል።

ከእነዚህ መካከልም 278 በፌደራል፣ 33 በትግራይና 18ቱ በአማራ ክልል የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎችና ክስ የተቋረጠላቸው ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ይለቀቃሉ።

የታራሚዎቹ ዝርዝር በይቅርታ ቦርዱ አማካኝነት ለአገሪቱ ፕሬዚዝዳንት ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ ወደ ኅብረተሰቡ ይቀላቀላሉ ነው የተባለው።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በወሰነው መሰረት ቀደም ሲል የአማራና የኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ 6 ሺህ 376 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች በይቅርታ ተለቀዋል።

Published in ፖለቲካ

የካቲት 1/2010 ኢትዮዽያ የልማት ፕሮጀክቶቿ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረጓ በምጣኔ ሃብታዊ እድገት የመሪነት ደረጃውን ከኬንያ እንድትረከብ ማድረጉን የኬንያው ስታንዳርድ ዲጂታል በድረ ገጹ አስነብቧል።

ዘገባው በአፍሪካ የኮንስትራክሽን አዝማሚያ ላይ ክትትል በማድረግ ሪፖርት የሚያወጣውን ዴሎይት የተሰኘ ተቋም የ2017 ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ነው ይህን ያለው::

ኢትዮዽያ ለእያንዳንዱ ኢንቨስትመንት ከምትመድበው በጀት ውስጥ 40 በመቶውን ለቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስታውል፥ ኬንያ ግን 20 በመቶውን ብቻ እንደምትመድብ ተጠቅሷል።   

እኤአ በ2016 በአካባቢው ግዙፍና ፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ያስመዘገበችው ኢትዮዽያ በምጣኔ ሃብታዊ እድገቷ አሁንም ከኬንያ ቀዳሚ ሆና እንደምትቀጥል ዘገባው አመላክቷል።

ኬንያ በ2016 እና 2017 መካከል በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች የነበሯት ቢሆንም፥ በተጠቀሱት ዓመታት በኢትዮዽያ እየተካሄዱ የነበሩ ፕሮጀክቶች ከኬንያ በእጥፍ እንደሚበልጡ የዴሎይት ሪፖርት አሳይቷል።

በተጠቀሱት ጊዜያት በኬንያ እየተካሄዱ ከነበሩት የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የትራንስፖርት ዘርፉ 53 በመቶ ሲይዝ የማዕድን ዘርፉ 23 በመቶ፣ ሪል ስቴት 14 በመቶ እንዲሁም የውሃ ፕሮጀክቶች ደግሞ ስድስት በመቶ መያዛቸውን ነው መረጃው ያመላከተው።

ኢትዮዽያ በአሁኑ ወቅት በቢሊዮኖች በሚቆጠር ዶላር  ታላቁ የህዳሴ ግድብን እና የኮይሻ የውሃ ሃይል ማመንጫን እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኗም ተጠቅሷል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ባወጣው ሪፖርት የኢትዮዽያ ኢኮኖሚ በሃገር ውስጥ ጥቅል ምርት(GDP) ጭምር ከኬንያ እንደሚበልጥ አመላክቷል።

በአጠቃላይ ዓመታዊ የዕቃዎችና የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት ኢትዮጵያ 73 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ስታስመዘግብ፥ ኬንያ ግን ያስመዘገበችው 69 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አሳይቷል።

በአፍሪካ የዴይሎቴ የመሰረተ ልማትና ካፒታል ፕሮጀክቶች ሃላፊ ዢያን ፒየር ላበስካግኔ “በእውነት ኢትዮዽያውያን መልካም ስራ እየሰሩ ነው፤ በአንፃራዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምንም ተነስተው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።” ሲሉ መናገራቸውን የስታንዳርድ ዘገባ ያሳያል።

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ የካቲት 1/2010 የግብር ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ባደረጉ ባለሙያዎችና የገቢ ደረሰኝ ሳይጠቀሙ በተገኙ ነጋዴዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መውሰዱን የወላይታ ዞን ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።፡

በግማሽ የበጀት ዓመቱ በዞኑ የሰበሰበው ገቢ ከእቅዱ በ73 ሚሊዮን ብር ያነሰ መሆኑም ተመልከቷል ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መንግስቱ ትግሮ እንደተናገሩት በራስ አቅም ገቢ በመሰብሰብ በታክስ ስርዓቱ አሰራር ላይ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው፡፡

የዞኑ ገቢ የማመንጨት አቅም አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ አንዳንድ ስነ ምግባር የጎደላቸው ባለሙያዎችና ህገ -ወጥ ነጋዴዎች መኖር በግማሽ የበጀት ዓመቱ የሚጠበቀው ገቢ በአግባቡ እንዳይሰበሰብ ምክንያት ሆኗል ።

ለዚህ ምክንያት በሆኑ 16 ባለሙያዎችና የገቢ ደረሰኝ ባልተጠቀሙ 46 ነጋዴዎች ላይ  የቅጣት እርምጃ መወሰዱን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር በህገ-ወጥ መንገድ በታተመ ደረሰኝ መንግስትን ማግኘት የነበረበትን የግብር ገቢ ያሳጡ አራት ባለሙያዎች ከስራ ታግደው ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቀሪዎቹ ደረሰኝ በማበላለጥ፣ሰነድ በማጭበርበርና መሰል ተግባራት በፈጸማቸው አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

ደረሰኝ ሳይጠቀሙ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 34 ነጋዴዎች ከአንድ ሚሊዮን 700ሺህ ብር በላይ ገቢ እንዲያደርጉ መደረጉን ያመለከቱት  አቶ መንግስቱ ውዝፍ ዕዳ ለመክፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ 12 ነጋዴዎች ሀብታቸው ታግዶ ጉዳያቸው በህግ እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።

" በግብርና ታክስ አሰባሰብ ያልተፈቱ ችግሮችን በመለየትና የሚፈጸሙ ማጭበርበሮች ላይ የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ በቀሪው ጊዜ የተሻለ አፈጿጸም ለማስመዝገብ ይሰራል"ብለዋል።

ጽህፈት ቤቱ የግማሽ በጀት ዓመቱን የሰራ አፈፃፀም ከባለድርሻ አካላት ጋር በገመገመበት መድረክ  ለታማኝ ግብር ከፋዮች የዋንጫና የዕውቅና ሰርተፊከት ሸልማል ።

ከተሸላሚዎች መካከል የሌዊ ጠቅላላ የህንጻ ስራ ተቋራጭ አስተባባሪ አቶ ከበደ ተካ በሰጡት አስተያየት " የመንግስትን ገቢ በተገቢው መልኩ ማስገባት ጥቅሙ ለራስ ነው" ብለዋል፡፡

ሌላው በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በሸቀጣሸቀጥ ንግድ የተሰማሩት አቶ ካቢሶ ካጫሮ በበኩላቸው የሚጠበቅባቸውን የግብር ገቢ በወቅቱ በመክፈል ተሸላሚ እንደሆኑ ጠቅሰው ሁሉም የግብር ግዴታውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 463 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 390 ሚሊዮን ብር ሰብሰቧል።

በበጀት ዓመቱ ከ926 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱም ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2010 ኢትዮጵያ የተወሰደባትን የጤፍ አዳቃይነትና ዱቄት አዘገጃጀት መብት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፈራሽ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ኢትዮጵያ በጤፍ ሃብት ላይ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ እና ጽህፈት ቤቱ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ  መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ በጤፍ ጀነቲክ ሀብት የአርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ላይ ከሆላንዱ 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል ቢቪ' ኩባንያ ጋር እ.ኤ.አ ሚያዝያ 2005 ስምምነት መፈራረማቸው ይታወቃል።

በስምምነቱ መሰረትም ኩባንያው ኢትዮጵያ በጤፍ ላይ የምታደርገውን ምርምር ለመደገፍ፣ ለግብርና ባለሙያዎች ነፃ የትምህርት እድል ለመስጠት፣ ጤፍ በአውሮፓ ምድር ሲዘራ በሄክታር 10 ዩሮ ለመክፈልና ኩባንያው ከተጣራ ትርፉ በዓመት 5 በመቶ ወይም ከ20 ሺህ ዩሮ ያላነሰ ገንዘብ መስጠት ነበረበት።

ነገር ግን ኩባንያው ስምምነቱን ወደ ጎን በመተው በጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት ፓተንት እና 'አዲና'፣ 'አያና' እንዲሁም 'ተስፋያ' በተባሉ ሶስት የጤፍ ዝርያዎች ላይ እ.ኤ.አ በ2003 ከአውሮፓ ፓተንት ጽህፈት ቤት የአዳቃይነት መብት አግኝቷል።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሶስት ሺህ ዓመት በፊት ጀምሮ ስትጠቀምበት የነበረውን የጤፍ አዘገጃጀት በስሟ ወደ አለም ገበያ ይዛ እንዳትገባ ተደርጋለች።

የጽህፈት ቤቱ ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን ጤፍ የባለቤትነት መብት በማስመለስ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በሚኒስትሮች ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩትና ሌሎች የመንግስት ተቋማት የተውጣጣ የሚኒስትሮች ኮሚቴ የቴክኒክ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚቴው ፓተንቱን ፈራሽ ወይም ውድቅ ለማድረግ መክሰስ፣ ምርቱን ወደ ገበያ ይዞ ገብቶ መከሰስ፣ ወይም ደግሞ በዲፕሎማሲ መፍታት የሚሉትን አማራጮች መለየታቸውን አስታውቀዋል።

አገሪቱ ከጤፍ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያዋጣውን አካሄድ በመከተል በአንድ ዓመት ውስጥ ፓተንቱ ፈራሽ እንደሚደረግ ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተሩ ሒደቱን ተናግረዋል።

ለዚህም ኮሚቴው ግልፅ አሰራር ዘርግቶ እያንዳንዱ የኮሚቴ አባል መስሪያ ቤት የየራሱን የስራ ድርሻ ወስዶ የቴክኒክ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤትም የተሰጠውን የቴክኒክ ስራ በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ ለኮሚቴው ያቀርባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሶስት ሚሊዬን ሄክታር መሬት በተለያዩ የጤፍ ዝርያዎች የሚሸፈን ሲሆን ከስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎችም በጤፍ ምርት  ላይ ይሳተፋሉ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 1/2010 የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ የ2018 የቶታል የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጉዞውን በመጪው እሁድ ከደቡብ ሱዳኑ ዋኡ ሳላም ጋር በሚያደርገው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ይጀምራል።

የኢዜአ ሪፖርተር ክለቡ ለጨዋታው እያደረገው ያለውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኙንና ደጋፊዎቹን አነጋግሯል።

የክለቡ ምክትል አምበል አዳነ ግርማ ለጨዋታው ልምምድና ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልጿል።

የሻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ ደጋፊውና ተጫዋቾቹ በጉጉት የሚጠብቁት በመሆኑ ጥሩ ዝግጅት እንዳደረጉና ቡድኑም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።

በጉዳት ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቁ ተጫዋቾች ወደ ልምምድ መመለሳቸው ለክለቡ ትልቅ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው አዳነ የገለጸው።

ለእሁዱ ጨዋታ "ጠንካራውን ጊዮርጊስን ጠብቁ" ያለው አዳነ የደቡብ ሱዳንን ቡድን ለማሸነፍ ጥረት እናደርጋለን ብሏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለፈው ዓመት ለነበረው የሻምፒዮንስ ሊግ ግስጋሴ ወሳኝ ሚና ከነበራቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው የክለቡ ተከላካይ አስቻለው ታመነ ዘንድሮ ካለፈው ዓመት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ማቀዳቸውን ተናግሯል።

ክለቡ ባለፈው ዓመት በካፍ የሻምፒዮንስ ሊግ 16 ውስጥ በመግባት በአገሪቷ እግር ኳስ አዲስ ታሪክ መስራቱን አስታውሶ ዘንድሮም የተሻለ ግስጋሴ ለማድረግ እንደሚጫወቱ ገልጿል።

ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ ከሲዳማ ቡና ተዛውሮ ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ሙሉአለም መስፍን በቅጽል ስሙ ዴኮ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።

በእሁዱ ጨዋታ ለቡድኑ ማሸነፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት የተቻለውን ለማድረግ መዘጋጀቱን ነው የተናገረው።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባለፈው ሳምንት ክለቡ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ካደረገው ጨዋታ ጊዜ ጀምሮ  ለሻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ የሚያበቃውን ዝግጀት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ክለቡ በፕሪሚየር ሊጉ የነበረበትን ድክመት በማረም ለእሁዱ ጨዋታ ጠንካራ ቡድን ይዞ ለመቅረብ ሲሰራ መቆየቱንም ገልጿል።

''ተጋጣሚያችን በሻምፒዮንስ ሊጉ ያለውን ልምድ በመጠቀም የእሁዱን ጨዋታ ለማሸነፍ ጥረት እናደርጋለን፤ ክለቡ ልምድ የለውም ብለን አነስተኛ ግምት አንሰጠውም'' ብሏል ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ልምምዱን በሚያደርግበት የቦሌ ወረዳ 3 የወጣቶች ማዕከል ያገኘናቸው ደጋፊዎች ለእሁዱ ጨዋታ ከእነሱ የሚጠበቀውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ክለቡን በህብረ ዝማሪ በማነቃቃት ዋነኛ የሆነው ይድነቃቸው አሸናፊ በቅጽል ስሙ አቼኖ ለእሁዱ ጨዋታ ደጋፊው የሚጠበቅበትን ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግሯል።

በአይነቱ ለየት ያለ የአጨፋፈር ስልት ማዘጋጀታቸውንና ቡድናቸው ከደቡብ ሱዳኑ ቡድን ጋር ሲጫወት ባማረ ህብረ ዝማሬ እንደሚያበረታቱት ገልጿል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የእሁዱ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ የመልስ ጨዋታውን የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ.ም በደቡብ ሱዳን ጁባ ስታዲየም ያደርጋል።

የደቡብ ሱዳኑ ዋኡ ሳላም ያለፈው ዓመት የአገሪቷ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ነው፤ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲሆን ከዚህ በፊት በአፍሪካ የኮንፌደሬሽን ዋንጫም ተወዳድሮ ያውቃል።

Published in ስፖርት

ሀዋሳ የካቲት1/2010 በደቡብ ክልል ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ ለመከላከል በተደረገው ጥረት ለውጥ ቢታይም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና በሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዋና ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አቅናው ካውዛ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ ተላላፊ በሽታዎችን አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ከዓመት ዓመት በመሻሻሉ የበሽታዎቹ ጫና እየቀነሰ መጥቷል።

በአንጻሩ እንደ ስኳር፣ ካንሰር፣ የልብና ከደም ቧንቧ ጋር የተያያዙ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ብዙ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረጉ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በክልሉ የበሽታዎቹ መስፋት ከከተሞች እድገት፣ የአመጋገብ ስርዓትና የኑሮ ዘይቤ መለወጥ ጋር ተከትሎ የመጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

አንደ አቶ አቅናው ገለጻ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ ቅባትና ስኳርን አብዝቶ መውሰድ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ጫት፣ አልኮልና ትንባሆን አዘውትሮ መጠቀም ለበሽታዎቹ የመጋለጥ ዕድልን የሚያባብሱ ምክንያቶች ናቸው።

የበሽታዎቹን ስርጭትና ጫና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨረ መምጣቱን ገልጸው፣ በክልሉ 25 ሺህ 530 ሰዎች ባለፉት ስድስት ወራት የስኳር በሽታ እንደተገኘባቸው ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በተመሳሳይ ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች በደም ግፊትና 1 ሺህ 286 ሴቶችና ወንዶች ደግሞ በማሕጸን በር፣ በጡትና በፕሮስቴት ካንሰር በሽታ ተይዘው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

"ተላላፊ በሽታዎችን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥረን ሳንጨርስ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ጣምራ ጫና ፈጥረውብናል" ሲሉም ስጋታቸውን ገልፀዋል።

በክልሉ በ67 ጤና ተቋማት የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ቅድመ ምርመራና ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

በተጨማሪም በዲላ፣ አርባ ምንጭ፣ ዱራሜና ሃዋሳ ሪፈራል ሆስፒታሎች በማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስት ኃኪሞች በመታገዝ ሕክምናው በተጠናከረ መንገድ እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

በበሽታዎቹ መምጫና መከላከያ መንገዶች ላይ ሕብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረውና በምርመራ ራሱን እንዲያውቅ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ አቶ አቅናው ገለጻ በአብዛኛው የክልሉ ጤና ተቋማት በሽታዎቹን ማከም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን