አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 07 February 2018

ባህርዳር ጥር 30/2010 የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ባለፉት ሁለት ዓመታት ባካሄደው የምርምር ሥራ 17 የሰብል ዝርያዎችን በማውጣትና በማላመድ ለአርሶ አደሮች ማሰራጨቱን አስታወቀ።

የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩ ይታፈሩ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ለአርሶ አደሩ የተሰራጩት የሰብል ዝርያዎች በኢንስቲትይቱና በስሩ በሚገኙ የግብርና ምርምር ማዕከላት የወጡ ናቸው።

በብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው ለአርሶ አደሩ ከተለቀቁት 10 የሰብል ዝርያዎች መካከል ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ የምግብ ገብስ፣ ማሽላ፣ አተር፣ ቦሎቄ፣ አብሽ፣ ነጭ አዝሙድና ሌሎችም ይገኙበታል።

ዝርያዎችን የማላመድ ሥራ የተከናወነላቸው ደግሞ የዳቦና የማካሮኒ ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተርና መሰል የሰብል ዝርያዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመት መጨረሻ ተቋሙ በምርምር ለማውጣት በዕቅድ ከያዛቸው መካከልም ባለፉት ሁለት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት አብዛኞቹን በምርምር ማውጣቱን አመልክተዋል።

በምርምር የወጡት የሰብል ዝርያዎች ድርቅና በሽታን ተቋቁመው ፈጥነው በመድረስ ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ መሆናቸውንም ዶክተር ብሩ አስረድተዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በኢኒስቲትዩቱ ሥር ያለው የአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል ከሌሎች የምርምር ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ያወጣው “ሕብር-1” የተሰኘ የተሻሻለ የጤፍ ዝርያም በሄክታር እስከ 27 ኩንታል ምርት መስጠት ይችላል።

ይህም በአካባቢው ካለው ዝርያ የ47 በመቶ የምርት ጭማሪ እንዳለው ነው የገለጹት።

“ጎንደር-1” የሚል ስያሜ የተሰጠው የሰሊጥ ዝርያ በሄክታር በአማካይ ዘጠኝ ኩንታል ምርት የሚሰጥ ሲሆን ከአካባቢው ዝርያ ከዕጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ዶክተር ብሩ ተናግረዋል፡፡

ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል የወጣ “አለነ” የተባለ የማሽላ ዝርያም በሄክታር 47 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥና ከአካባቢው ዝርያም የ41 በመቶ የምርት ጭማሪ እንዳለው አስረድተዋል።

ዝርያው ቀድሞ የሚደርስ ከመሆኑ በላፈ የወፍ ጥቃትን በመቋቋም ለቆቦ፣ ጨፋ፣ ጃሬና ተመሳሳይ እርጥበት አጠር ቦታዎች ተስማሚ መሆኑን ተናግረዋል።

" የዋግ ነሽ " የተባለ የአተር ዝርያ ደግሞ ለሰሜን ወሎ፣ ለዋግ-ህምራና ተመሳሳይ ዕርጥበት አጠር ለሆኑ አካባቢዎች ተስማሚና በአማካኝ 23 ኩንታል ምርት በሄክታር ይሰጣል።

ከአካባቢው ዝርያም የ45 በመቶ የምርት ጭማሪ እንዳለው ዶክተር በሩ አመልክተዋል።

ከ22 እስከ 25 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ ሁለት የነጭ አዝሙድ ዝርያዎችም ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

እነዚህ ዝርያዎች ለደምቢያ፣ ጣቁሳ፣ ሲሪንቃና ተመሳሳይ የአየር ጠባይ ላላቸው አካባቢዎች ተስማሚ እንደሆኑም አስረድተዋል።

በያዝነው ዓመትም 181 የሰብል፣ የእንስሳትና የደን ዝርያዎችን በምርምር ለማውጣት ኢንስቲትዩቱ የምርምር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።  

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ጥር30/2010 ለአራት ቀናት በመቀሌ ሲካሄድ የቆየው የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የአምስተኛ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የተለያዩ ሹመቶችንና አዋጆችን በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሆነው ባለፈው ዓመት ተሹመው የነበሩት አቶ አማኑኤል አሰፋን የፍትህ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ነጋ አሰፋን የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ረዳኢ ሓለፎም የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ  ሆነው ተሹመዋል።

እንዲሁም በሁለት የቢሮ ኃላፊዎች ሲመራ የነበረው የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በዶክተር አትንኩት መዝገቦ ብቻ እንዲመራ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን ሹመት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።

ከተሿሚዎቹ መካከል የፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ አማኑኤል አሰፋ  እንደገለጹት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ከባልደረቦቻቸው ጋር በትጋት ለመስራት ተዘጋጅተዋል።

መንግስት መገናኛ ብዙሃንን ለማጠናከር እያካሔደ ባለው ስራ ላይ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት አቶ ረዳኢ ሓለፎም ናቸው።

ህዝብ ሊያገኘው የሚገባውን መረጃ በተሟላ መልኩ ከማቅረብ ጎን ለጎን ከመንግስት ጋር በመሆን ለሃገሪቱ የህዳሴ ጉዞ መሳካት እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ የ574 ሚልዮን 727ሺህ 671 ብር ተጨማሪ በጀት ያጸደቀ ሲሆን በጀቱ ከፌዴራል መንግስት በብድርና ከተለያዩ ገቢዎች የተገኘ መሆኑን በምክር ቤቱ የበጀትና ኦዲት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ንጉሰ ለገሰ ረቂቅ አዋጁን አስታውቀዋል።

በክልሉ ያጋጠመውን የበጀት እጥረት ለማቃለል የውሃ ሃብትና የኮንስትራክሽን፣መንገድና ትራንስፖርት ቢሮዎች ከዚህ ቀደም ላሰሩዋቸው ስራዎች ያልተከፈለ እዳ ማወራረጃ የሚውል መሆኑንም አቶ ንጉሰ አስረድተዋል።

ከዚሁ ውስጥ 556ሚልዮን የሚሆነው ለካፒታል በጀት ሲሆን ቀሪው ለመደበኛ በጀት የሚውል መሆኑንም ታውቋል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ወረዳዎች ተመድበው የሚሰሩ 38 ዳኞችን ሹመት ተቀብሎ በማፅደቅ ጉባኤውን አጠናቋል።

 

Published in ፖለቲካ

መቀሌጥር 30/2010 የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት  አምስተኛ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ውሎው አራት ሹመቶችንና ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

ምክር ቤቱ የጻደቀው ሹመት የክልሉ ፍትህ ቤሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ ፣የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ነጋ አሰፋ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ደግሞ አቶ ረዳኢ ሃለፎምን ሾሟል።

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪ የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቦ እንዲሆኑ ወስኗል።

እንዲሁም በተለያዩ ቦታዎች የሚሰሩ የ38 ዳኞችን ሹመት ያጸደቀ ሲሆን ከ574 ሚሊዮን 700 መቶ ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ በጀት በማጽደቅ ጉባኤው ተጠናቋል።

Published in ፖለቲካ

ጅግጅጋ ጥር 30/2010 መንግስት በነጻ የፈቀደላቸውን የተጓዳኝ በሽታዎች መድኃኒት በካራማራ ሆስፒታል ማግኘት ባለመቻላቸው መቸገራቸውን በጅግጅጋ ከተማ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ተናገሩ፡፡

ሆስፒታሉ በበኩሉ ችግሩ የተፈጠረው የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒቶቹን ባለማቅረቡ መሆኑን ገልጿል፡፡

"መንቃት ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ማህበር" ምክትል ሊቀመንበር ወይዘሮ ቤተልሔም ተስፋዬ ከፀረ ኤች አይ ቪ መድኃኒት በተጨማሪ ለተጓዳኝ በሽታ የሚሰጥ መድኃኒት በሆስፒታሉ ባለመኖሩ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

"ብዙዎቹ የማህበሩ አባላት መድኃኒቱን የመግዛት አቅም ስለሌላቸው በጊዜ ታክመው መዳን ሲችሉ ለህመም እየተዳረጉ ነው" ብለዋል።

የነጻ መድኃኒቱ ተገልጋይ ከሆኑት መካከል አቶ አፈወርቅ እሽቱ በበኩላቸው በሆስፒታሉ ቀደም ሲል በነፃ ይቀርቡ የነበሩ መድኃኒቶችን በአሁኑ ወቅት እያገኙ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

" መድኃኒት ቤት ሄዳችሁ ግዙ ከማለት ውጪ የተጓዳኝ በሽታ መድኃኒቶችን በነጻ አናገኝም " ሲሉም ተናግረዋል።

የካራማራ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሰዒድ አብዲላሂ በሰጡት ምላሽ በደማቸው የኤች.አይ.ቪ ቫይረስ ያለባቸው ሰዎች በሆስፒታሉ የሚሰጠው የፀረ ኤች.አይ.ቪ መድኃኒት ሕክምና በአግባቡ እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይሁንና መንግስት ለታካሚዎች በነፃ የሚያቀርበው የተጓዳኝ በሽታ መድኃኒት ከኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ባለመቅረቡ ምክንያት ችግሩ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ችግሩ እንዲፈታ ከአንድም ሁለት ጊዜ ለኤጀንሲው ቢያሳውቅም በኤጀንሲው በኩል ፈጣን ምላሽ ባለመሰጠቱ ምክንያት መድኃኒቱን ለተጠቃሚዎች በነጻ ማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ሰዒድ እንደገለጹት፣ በተቋማት መካከል በተፈጠረ ችግር ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖች ለጉዳት መዳረግ ስለሌለባቸው ከኤጀንሲው ጋር በመነጋገር በቀናት ጊዜ ውስጥ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል፡፡

በካራማራ ሆስፒታል የፀረ ኤች.አይ.ቪ ሕክምናና ምርመራ ክፍል ኃላፊ ሲስተር ትህትና በላይ በበኩላቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተጓዳኝ በሽታዎች አስፈላጊ የሆኑ መድኃኒቶች ባለመኖራቸው ሕሙማን መድኃኒቶቹን ከውጪ እንዲገዙ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ የስርጭት ክፍል ባለሙያ አቶ ታሪኩ ታምሬ በበኩላቸው መድኃኒቶች ዕቅድን መሰረት አድርገው እንደሚገዙ ገልጸዋል።

ኤች.አይ.ቪ በደማቸው ያለባቸው ሰዎች በዋናነት "ኮትሪ ሞክሳዞሊ" የተባለና በሽታ የመከላከል አቅም እንዳይዳከም የሚረዳ መድኃኒት እጥረት እንደሌለ ገልጸዋል።

የካራማራ ሆስፒታል ይህንንና መሰል መድኃኒቶችን እንዲቀርቡለት በመድኃኒቶች መጠየቂያ ላይ ፍላጎቱን በወቅቱ ባለማሳወቁ መድኃኒቶቹን ማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

" ሆስፒታሉ ፍላጎቱን በወቅቱ ካለማሳወቅ ባለፈ ጥቅም ላይ ለዋሉ መድኃኒቶች ወቅቱን ጠብቆ ሪፖርት አያቀርብም " ያሉት አቶ ታሪኩ ፣ መድኃኒቶቹ በውድ ዋጋ የሚመጡ በመሆናቸው ለምን እንደዋሉ ትክክለኛ ሪፖርት በጊዜ ማቅረብ አንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 30/2010 በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ የማምረት ዓቅም ቢፈጠርም ጥቅም ላይ የዋለው ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ተገለጸ።

የብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የ2010 በጀት ዓመት የንዑስ ዘርፍ የግማሽ ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርቅነህ ደሳለኝ እንዳሉት በግማሽ ዓመቱ በዘርፉ ከቀረቡት ምርቶች 64 ነጥብ 8 በመቶው ከውጭ በገቡ ምርቶች ተሸፍኗል።

ምርቶቹን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት 23 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገም ገልጸዋል።

በአገር ወስጥ በዘርፉ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ዓቅም መፈጠሩን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን ባለው ሂደት አገልግሎት ላይ የዋለው ዓቅም ከ30 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቁመዋል።

የውጭ ምንዛሪ፣ የኃይል አቅርቦትና የስራ ማስኬጃ በጀት እጥረት እንዲሁም የጉምሩክና ሎጂስቲክስ አገልግሎት መጓተት የተፈጠረውን አቅም አሟጦ ጥቅም ላይ ለማዋል እንዳይቻል ማነቆ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እንደሚሰራ አቶ ወርቅነህ ተናግረዋል።

የኢንስቲትዩቱ የዕቅድ፣ የፖሊሲ ጥናትና መረጃ ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ዓባይ በበኩላቸው ዘርፉ በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ሆኖ በግማሽ ዓመቱ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች 23 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘቱን ገልፀዋል።

በተጠቀሰው ጊዜ ለመጀመሪ ጊዜ የአልሙኒየም ፕሮፋይልና የቤት እቃዎችን ወደ ውጭ መላክ መጀመሩንም አክለዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ጥር 29/2010 በደቡብ ጎንደር ዞን ደብረታቦር ከተማ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ምረቃና ጉብኝት ተካሄደ፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ በተገኙበት ዛሬ ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የድንጋይ ንጣፍ እና የጠጠር መንገድ ይገኙበታል፡፡

እንዲሁም የዳግማዊ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ባለአንድ ፎቅ ቤተ መጻህፍት ፣ ለቢሮ አገልግሎት የሚውል የተለያዩ ክፍሎችና አዳራሽ ያሉት  የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር ህንፃም እንዲሁ፡፡

በከተማዋ አደባባይ የተገነባውና ሰባት ነጥብ አምስት ሜትር ከፍታ ያለው የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሐውልትም ከተመረቁት ወስጥ አንዱ ነው፡፡

ከምረቃውም ሌላ በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው የደብረታቦር ሆስፒታል ቤተ ሙከራ በዕለቱ የክብር እንግዶች ተጎብኝቷል፡፡

ሆስፒታሉ ያለበትን የህክምና ቁሳቁስ እጥረት ለማሟላት የሚያግዙ 20 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው እቃዎች ከደብደታቦር ዩኒቨርስቲ በስጦታ መበርከቱን የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ደጀን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ተጠናቀው የተመረቁትና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት እነዚህ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ 313 ሚሊዮን ሲሆን የተሸፈነውም በህዝብና በመንግስት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

ፕሮጀክቶቹ  የዞኑንም ሆነ የከተማዋ  አስተዳደር ለህብረተሰቡ የሚሰጡትን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል አመቺነት እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡ 

በምረቃና ጉብኝት ስነስርዓቱ ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  አቶ ያለው አባተ ፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የከተማው ህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጊምቢ ጥር 30/2010 በምዕራብ ወለጋ ዞን ቦጂ ድርመጂ ወረዳ ትናንት በደረሰ  የተሽከርካሪ አደጋ  የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንና በዘጠኝ ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

 አደጋው የደረሰው የሰሌዳ ቁጥር ኮድ -3 65434 አ.አ. የሆነ የጭነት አይሱዙ ተሽከርካሪ ከነጆ ከተማ ወደ ቢላ ከተማ ከ70 በላይ ሰዎችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ እንዳለ  ዲላ በሚባል የገጠር ቀበሌ ሲደርስ በመገልበጡ ነው ።

 የዞኑ ትራፊክ ፖሊስ ቁጥጥር ዲቪዝዮን ኃላፊ ኢንስፔክተር አብዱረዛቅ ምትኩ እንደገለፁት ትናንት ማምሻውን 12 ሰዓት አካባቢ መሆኑና መንስኤውም  እየተጣራ ነው፡፡ 

 በአደጋው ህይወቱ ካለፈው ሌላ በአምስት ሰዎች ከባድ እና አራት ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳትደርሷል ።

 የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በነጆ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ያመለከቱት  ኢንስፔክተሩ 150 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት መውደሙንም ጠቅሰዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲሰ አበባ ጥር 30/2010 አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የኤሌክትሮኒክ ቲኬት /ኢ-ቲኬቲንግ/ የክፍያ አሰራር ለመጀመር ይዞት የነበረው ዕቅድ እያስገነባ ባለው ዴፖ ምክንያት መጓተቱን ገለፀ።

ድርጅቱ ዘመናዊው የኢ-ቲኬቲንግ የክፍያ አሰራር በመስከረም 2010 ዓ.ም. እንደሚጀምር ገልጾ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ተግባራዊ አላደረገውም።

የኢ-ቲኬቲንግ ክፍያ አሁን አገልግሎት ላይ ያለውን የወረቀት ቲኬት የሚተካ ሲሆን አውቶቡሱ ላይ በሚገጠም ማሽን አማካኝነት የሚተገበር አሰራር ነው።

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ኃይሉ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዘመናዊው አሰራር ተግባራዊ መሆን ያልቻለው በተመሳሳይ ወቅት እየተካሄደ በሚገኘው የአውቶቡሶች ዴፖ ግንባታ ምክንያት ነው።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ድርጅቱ የኢ-ቲኬት አሰራሩን ለመተግበር አስቀድሞ ያካሄደው ጥናት ጎን ለጎን የሚያከናውነውን የዴፖ ግንባታ ታሳቢ ያደረገ አልነበረም።

የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት የቁጥጥር ማዕከላት ከዴፖዎቹ ጋር ተጣጥመው መገንባት ያለባቸው በመሆኑና የዴፖዎቹ ግንባታም ባለመጠናቀቁ አገልግሎቱ መዘግየቱን ተናግረዋል።

በግንባታ ሂደት ላይ ከሚገኙት አራት ዴፖዎች እስካሁን የሸጎሌና የየካ ግንባታ እየተጠናቀቀ በመሆኑ የኢ-ቲኬት አሰራሩን በዚህ ዓመት ለመጀመር የሚያስችል ሙከራ ይደረጋልም ብለዋል።

ድርጅቱ የኢ-ቲኬቲንግ ስራውን ለመጀመር በዘርፉ ብቃት ያላቸው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ቅጥር በማከናወን በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎቱ ድርጅቱ ለትኬት ማሳተሚያ የሚያወጣውን ወጪ ከማስቀረቱ ባሻገር ተጠቃሚዎች ትኬት በመቁረጥ ሂደት የሚያባክኑትን ጊዜና እንግልት ያስቀራል።

አሰራሩ ክፍያ ሳይፈጽሙ የሚጓዙ መንገደኞች ሲያጋጥሙ መውረድ የማያስችልና የተሳፋሪውንም ሆነ የድርጅቱን ጥቅም የሚያስጠብቅ መሆኑንም ተገልጿል።

አንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት ከ70 ዓመት በላይ ያስቆጠረ የህዝብ ማመላለሻ ሲሆን ከ500 በላይ በሆኑ አውቶቡሶቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Wednesday, 07 February 2018 22:11

'የጤናው ዘርፍ ፈተና........ '

አስቴር ታደሰ (ኢዜአ)                     

አንድ አባባል አለ፤ ‘መድሃኒት ያድናልም ይገላልም’ የሚል። ዛሬ አለም ከደረሰችበት የስልጣኔ ጣሪያ ጋር አብሮ የሚሄድ የዘመነና እጅግ ፈዋሽ መድሃኒት እየተመረተ ለገበያ እየዋለ በርካታ ግለሰቦች ጤናቸውን መጠበቅ ችለዋል። የተሻለ የመፈወስ ዓቅም ያላቸው መድሃኒቶች ለገበያ መብቃታቸውን የሰው ልጅ የመኖር እድሜ ጣሪያ ከፍ እንዲል አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው። መድሃኒት የማዳኑን ያህል የከፋ ጉዳት የሚያደርስም ሊሆን ይችላል።

መድሃኒት ጥራቱን ጠብቆ ካልተመረተ የመፈወስ አቅሙ መዳከም ብቻ ሳይሆን ለጤና መቃወስ የሚዳርግ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ብዙ ነው። የመድሃኒት የፈዋሽነት ዓቅም መዳከም መንስዔዎች ብዙ ቢሆንም መድሃኒት ከሚያመርቱ ተቋማት ውጪ በህገወጥ መንገድ ተመርተው ወደገበያ መቀላቀላቸውና የሃሰተኛ መድሃኒት አምራቾች መበራከት ነው። በቅርቡ የአለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ላይ ሃሰተኛ መድሃኒት የቀጣዩ ጊዜ የህብረተሰብ ጤና ስጋት ምንጭ ሊሆን እንሚችል አመላክቷል።

በአለም ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ከመጣው ቴክኖሎጂ ጋር ተያይዞ የተሻሻሉና የሰው ልጆችን ስቃይ ቀንሰው  ህይወትን የሚታደጉ መድሃኒቶችይፈበረካሉ። መንግስታትም መድሃኒቶች እንዲመረቱና ሕዝቦቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ አኳያ ጠንካራ የሚባል ስርአት ይዘረጋሉ። እነዚሁ አገሮች በዓመት ለመድሃኒት ግዥ በቂ የሚሆን በጀት መድበው የመድሃኒት አቅርቦቱ ተደራሽ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ። መንግስታቱ  ለግዥ ብቻ ሳይሆን ለመድሐኒት የምርት ሒደት ድጋፍ ለማድረግም ትኩረታቸው ከፍ ያለ ነው። የዚህ ድጋፍ ውጤትም የአንድን አገር የጤና አገልግሎት በማሳደግና በተለያዩ ሕመሞች ተይዘው የሚሞቱ ሰዎችንም ቁጥር ከመቀነሱም ባሻገር የገቢ ምንጭን ያሳድጋል።

መድሐኒት በበቂ ሁኔታ መመረቱ ደግሞ ታማሚዎች የከፋ ችግር ውስጥ ከመግባታቸው በፊትና ከገቡም በኋላ በፍጥነት እንዲፈወሱ ያደርጋል፤ በምድር ላይ የሚኖሩበትን እድሜም ወይም የእድሜ ጣራቸውን በማራዘም ረገድ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ ያበረክታል።

ነገር ግን በተቃራኒው በአሁኑ ወቅት ባደጉትም ሆነ ባላደጉት አገሮች ከደረጃ በታች የሆኑ መድሃኒቶች በስፋት እየተሰራጩ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት እያሳሰበ ነው። ድርጅቱ በዚሁ መስክ በቅርቡ ባወጣው መረጃ የሐሰት ወይም ተመሳስለው የተመረቱ መድኃኒቶች ሕገወጥ ንግድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከጦር መሳሪያ ሽያጭ ቀጥሎ ትልቅ ገንዘብ የሚዘዋወርበት እየሆነ መምጣቱን ነው ያስታወቀው።

በዚህ መስክ አምራቾችና ጅምላ አከፋፋይ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አዘዋዋሪዎች፣ ቸርቻሪዎችና ተጠቃሚዎች ያሉበት ሲሆን፣ በተለይ የአዘዋዋሪዎቹ ብዛትና አቅም ከፍተኛ መሆኑ ችግሩን ስር የሰደደ እንዲሆን አድርጎታል። እነዚህ አካላት በየአገሮቹ ፖሊሲና ሕግ እስከማስቀየር የሚደርስ ጡንቻ አላቸው፡፡ ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ወይም አንድ አካል በአግባቡ እንዳይንቀሳቀስና እንዲዳከም ማድረግ የሚያስችል ተግባራትን ለማካሔድም አቅም እንዳላቸውም የድርጅቱ መረጃ ይጠቁማል።

ሆኖም  ሪፖርቱ በዓለም በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙት የአፍሪካ አገሮች የሐሰት ወይም ተመሳስለው የተሠሩና ከደረጃ በታች የሆኑ፣ ጥራታተውን ያልጠበቁ መድኃኒቶች እየተሰራጩ መሆኑን አረጋግጬያለሁ ብሏል። የዚህ ድርጊት ወትሮም በፈተና የተተበተበውን የጤና አገልግሎት የበለጠ በማወሳበሰብ ነገሩን ሁሉ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ያደርገዋል።

በሐሰትና ከደረጃ በታች በሆኑ መድሐኒቶች ምክንያት በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ብቻ 72 ሺሕ ሕፃናት ከሳንባ ምች፣ 69 ሺሕ አዋቂዎች ደግሞ ከወባ በሽታዎች መዳን አቅቷቸው ሞተዋል፡፡ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ከሚቀርቡ መድኃኒቶች አንድ አሥረኛ ያህሉ የውሸት፣ በሽታን የማያድኑና ጥራታቸውም ከደረጃ በታች መሆናቸውን ድርጅቱ እንደደረሰበት ይጠቅሳል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በቅርቡ እንደገለጹት፤ የውሸት መድኃኒት የዓለም ፈተና ነው። በተለይ እአአ ከ2013 ወዲህ በአብዛኛው ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሐሰትና ከደረጃ በታች የሆኑ መድኃኒቶች ገበያ ላይ ስለመዋላቸውና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ስለመሆናቸው ነው፡፡

በዚህም ሳቢያ ከ2013 ወዲህ ብቻ ለድርጅቱ 1 ሺ 500 የሐሰት ወይም የጥራት ደረጃቸው የወረዱ መድኃኒቶች ስለመገኘታቸው ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ከእነዚህ ሃሰተኛ መድኃኒቶች ውስጥ ሕዝብ በአብዛኛው የሚጠቀምባቸው ፀረ ተዋህስያን (አንቲባዮቲክስ) ይገኙበታል፡፡ በተለይ በመካከለኛና በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ አገሮችን የሚፈትነውን ወባ ለመቆጣጠር ከሚውሉ መድኃኒቶችም የሐሰት መድሃኒት ስለመኖሩ ተደጋጋሚ መረጃ ለድርጅቱ ደርሷል።

ለድርጅቱ ከደረሱ ከነዚህ ጥቆማዎች ውስጥ 42 በመቶው ከአፍሪካ፣ 21 በመቶው ከአሜሪካ እንዲሁም 21 በመቶው ከአውሮፓ ናቸው፡፡ ለድርጅቱ የቀረበው ሪፖርት በዓለም ይሰራጫል ከሚባለው የሃሰት መድኃኒት ቅንጣት ያህሉ ብቻ መሆኑም ነው የተጠቆመው፡፡ ከምዕራብ ፓስፊክ ደግሞ ስምንት በመቶ፣ ከምሥራቅ ሜዲትራኒያን ስድሰት በመቶ እንዲሁም ከደቡብ ምሥራቅ እስያ ሁለት በመቶ ብቻ ሪፖርት መደረጉም ችግሩ ግዙፍ ቢሆንም መረጃው በትክክል እንደማይደርስ ነው የተገለፀው።

በዓለም ጤና ድርጅት የመድኃኒትና ክትባት ተደራሽነት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ማሪኒላ ሲማው እንደሚሉት፣ የሐሰት መድኃኒቶች የሚያደርሱት ጉዳት በሕሙማኑና በታማሚዎች ላይ ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም በሽታን እየተላመደ ያስቸገረውን ባክቴሪያ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ላይ የተጋረጠ ፈተና ነው፡፡ መድኃኒት የማዳን ኃይሉ እየቀነሰ በመጣበት በዚህ ወቅትም የውሸትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመድኃኒት ዓይነቶች እየተሠራጩ መሆናቸው ለጤናው ዘርፍ ፈታኝ ሆኗል፡፡

በተለይ በታንዛኒያና በናይጄሪያ የሐሰትና ተመሳስለው የተሰሩ መድኃኒቶች ዝውውር ከአሥር በመቶ በላይ በመሆኑ የችግሩ ስፋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ ባለሥልጣን የመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ እንደሚሉት፤ በአገራችን ችግሩን ለመከላከል የተለያዩ መድኃኒቶች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ቁጥጥር ይደረጋል። መድኃኒቱ ለገበያ ከመሠራጨቱ በፊት የላቦራቶሪ ጥራት ምርመራ እንደሚካሔድና ገበያ ላይም ከዋለ በኋላም የድህረ ገበያ ቅኝት እንደሚሠራና የሐሰትና ተመሳስለው የተመረቱ ወይም ደረጃቸውን ያልጠበቁት እንደሚለዩ ይናገራሉ፡፡

ባለሥልጣኑ ባደረገው ምርመራም፣ በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ጋምቤላ ክልል አንድ የፀረ የወባ መድኃኒት የሀሰት ወይም ተመሳሳይ ሆኖ ተገኝቶ ነበር፡፡ በወቅቱ መድኃኒቱ በኮንትሮባንድ አዲስ አበባ  እንደገባና ጋምቤላ ውስጥ ሲሸጥ እንደተገኝም ነው የገለጹት።

ባለሥልጣኑ በተለይ ኅብረተሰቡ በብዛት የሚጠቀምባቸው ፀረ ተዋህስያን፣ ፀረ-ወባና ሌሎችም “ችግር ሊያመጡ ይችላሉ” የሚባሉ መድኃኒቶችን በመለየትና በላቦራቶሪ በመመርመር ችግር ያለባቸው ከሆኑ ለገበያ እንዳይቀርቡና ከቀረቡም ወዲያው እንዲሰበሰቡ ያደርጋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንደሚለው፣ ተመሳስለውም ሆነ ከደረጃ በታች የሚሠሩት መድኃኒቶች ሕብረተሰቡ ይጠቀምባቸዋል ተብለው የሚገመቱት መድኃኒቶች ብቻ ሳይሆኑ የካንሰር መድኃኒቶችን ጨምሮ በውድ ዋጋ የሚገዙትንም ያካትታል፡፡

“የመድኃኒቶችን ትክክለኛነትና ፈዋሽነት ማረጋገጥ እንደ አገር ከፍተኛ ወጪና ባለሙያ የሚጠይቅ ነው” ይላሉ አቶ ገዛኸኝ፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ ከመንግስት የሚመደብለትን በጀት ጨምሮ የሕብረተሰቡን  ጤና ለመጠበቅ ከተለያዩ መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል።

የሐሰተኛ መድኃኒቶች ዝውውር ደረጃ ይለያይ እንጂ በሁሉም አገሮች የሚከሰት ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ የወባ በሽታ መድኃኒቶች እስከ 65 በመቶ ድረስ የሚሆኑት ተመሳስለው በመሠራታቸው በየዓመቱ ከ100 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ሰዎች መዳን ሲችሉ ፈዋሽ ያልሆነ ነገር እየወሰዱ ለህልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡

በዓለም ደረጃ በወባ በሽታ ብቻ እስከ 450 ሺሕ ሰዎች በየዓመቱ እንደሚሞቱ ሲገመት፣ ይህም ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ችግር ነው፡፡ በታዳጊ አገሮች የወባ መድኃኒት፣ ለባክቴሪያ ኢንፌክሽን የሚያገለግሉ ፀረ ተዋህሲያን እና የወሊድ መከላከያዎች፣ በአሜሪካ ደግሞ የኮሌስትሮል መድኃኒቶች ተመሳሳለው ተገኝተዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የምግብና የመድኃኒት አስተዳደር በ1995 ዓ.ም. በውጭ አገር ተመርተው ወደ አሜሪካ ከገቡት መድኃኒቶች 18 ሚሊዮን ኪኒን የሐሰት ሆነው መገኘታቸውን አስታውቆ ነበር፡፡ ሃሰተኛ ሆነው ከተገኙት ውስጥ ለካንሰር፣ ለአካል መቆጣት፣ ለአለርጂ፣ ለአስም ተብለው የተዘጋጁ ናቸው፡፡

በታዳጊም ሆነ በበለጸጉት አገሮች ለስኳር በሽታ የሚሆኑ ኢንሱሊኖችን ጨምሮ ለከፍተኛ የደም ግፊት የሚሆኑ መድኃኒቶችም የሀሰት እየሆኑ መገኘታቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያመላክታል፡፡ ድርጅቱ ባደረገው ፍተሻ ከበቆሎ ዱቄት ወይም ከድንች የተሰሩ የወባ መድሐኒት ተብለው ለገበያ መቅረባቸውንና በመድሐኒቶቹ ላይ የተለጠፈው መግለጫ እውነት እንደሚመስል ይህም በሽታን መከላከል ሳይቻል ቀርቶ ለሞት ወይም ለከፍተኛ ጉዳት ይዳርጋል።

የሐሰት መድኃኒቶች ላይ ጎጂ ኬሚካሎችም እንደሚጨመሩ ይህም ጉበት እንደሚያቃጥል፣ ኩላሊትን እንደሚያውክ፣ አዕምሮን እንደሚያቃውስና የደም ሴሎችን እንደሚያበላሽም የአለም ጤና ድርጅት በድረ ገጹ አስነብቧል፡፡ ሃሰተኛ መድሃኒት በማምረት ገንዘብ የሰበሰቡ ራስ ወዳዶች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ የጤና እክል ለሚያጋጥማቸው የሰው ልጆች ሞት መንስዔ እየሆኑ ነው። የሃሰተኛ መድሃኒት ስርጭት እየተባባሰ መምጣትም ለጤና ዘርፍ ፈተና ነው።

 

በመሆኑም ይሕንን ችግር ለመከላከል አኳያ መንግስት ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ መድሐኒቶችንም ሆነ አገር ውስጥ የሚመረቱት ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር፣ ክትትልና ፍተሻ የበለጠ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጠናከር ይኖርበታል። ሕብረተሰቡም የሚያደረገውን የቁጥጥር ስራ በመደገፍ ቢሳተፍና  በተለይም መድሐኒቶችን ሲገዛ ጥንቃቄ ቢያደርግ ፤ የመድሃኒት መሸጫ መደብር ባለሙያዎችና ባለንብረቾችም ትክክለኛ የሆኑና ፈዋሽነታቸው

የተረጋገጠ መድሃኒቶችን ለሕብረተሰቡ ቢያቀርቡ አለ አግባብ የሚጠፋውን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት መታደግ ይቻላል።

 

Published in ዜና ትንታኔ

አዲስ አበባ ጥር 30/2010 ኢትዮጵያ የቡድን 77 እና ቻይና /የናይሮቢ ቻፕተር/ ሊቀመንበርነት ከፓኪስታን ተረከበች።

የሊቀመንበርነቱን ቦታ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መረከባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አምባሳደር ዲና በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ውስጥ ቡድኑ ለታዳጊ አገራት ድምጽ መሰማት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ ነው።

በቀጣይም ቡድኑ በተባበሩት መንግስታት ስርዓት ውስጥ የታዳጊ አገሮችን ጥቅም ለማስጠበቅና ድምጻቸውን በጋራ ለማሰማት የሚያደርገው ሚና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጋላጭነት ፎረም ሊቀመንበር እንደመሆኗ የተባበሩት መንግስታት ፕሮግራም ለአየር ንብረት ተጋላጭ የሆኑ አገራት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት በሚሰራቸው ስራዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደምትሰራ አስታውቀዋል።

በተባበሩት መንግስታት ቀጣይነት ያለው የልማት ዕቅድ ከግብ እንዲደርስም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አምባሳደር ዲና ተናግረዋል።

ቡድን 77 እና ቻይና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የታዳጊ አገራት ህብረት ሲሆን ዋና ዓላማቸውም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ በጋራ መስራት ነው።

ቻይና በቡድን 77 እና በቻይና ሙሉ አባል ሳትሆን የቡድኑ የቅርብ አጋር በመሆኗ ቡድኑ 'ጂ77 እና ቻይና' በመባል ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን