አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 06 February 2018
Tuesday, 06 February 2018 23:28

የበኩር ልጆች

                               በጥላሁን አያሌው / ኢዜአ/

የማለዳው ጉም ከጥቅጥቁ ደን እንደ እንፋሎት እየተትሎገሎገ ይወጣል፡፡ጉሙ በእያንዳንዱ እድሜ ጠገብ ረጃጅም ዛፎች አናት ላይ ሲረብብ ሲታይ ከሣር ጎጆ ጣሪያ የሚወጣ ጭስ ይመስላል፡፡

በስሱ እየተመጠነ የሚወጣው አየር ይሰባሰብና ሕብረት ሰርቶ አቅም ሲፈጥር ደግሞ ዓይን ይይዛል፡፡ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ ሁሉ "ነፋስ ሲያብርም ግዘፍ ይሰራል" ያስብላል፡፡

እንደጥጥ የነጻው ጉምም በቦንጋ ሰማይ ላይ እንዳሻው ይምነሸነሻል፡፡ቦንጋ ማለዳውን በጉም ትታጠናለች፡፡ከረቂቅ ነፋስነት ወደ ቀልብ ሳቢ ትዕይንት የሚለወጠው ጉምም ከጥጥ ባዘቶ ይጸድላል፡፡

የተክሎች እስትንፋስ፤የዛፎች በረከት፤ የተፈጥሮ ጸጋ የሆነው አየር አንዴ ሲጠቀለል እንደገና ሲከፋፈል በከተማዋ አድማሳት ላይ ልዩ ትርኢቱን ያሳያል፡፡ተፈጥሮ ንጋት ላይ ራሷን ቬሎ ታለብሳለች፡፡ራሷን በራሷ ስትሞሽርም ትታያለች፡፡

ቦንጋ ማለዳ አትነቃም አረፋፍዳ ነው የምትበራው፡፡ ጽልመቱ በንጋት፤ ጉሙ በማለዳ ጮራ በመተካት ላይ ሲሆን፤ በጉም ጋቢ ተከናንበው ጸድለው ያረፋፈዱት የከተማዋ ከፍታማ ቦታዎችም እየወገጉ ነው፡፡

ጉሙን ተከትላም የማለዳ ቀስተ ደመና ከቀኝና ግራ ባሉት የተራራዎች አናት ላይ እግሮቿን ተክላለች፡፡ በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያሸበረቀችውን የጠዋት ቀስተ ደመና በአርምሞ ሳስተውልም አንዳች ነገር ውስጤን ነዘረኝ፡፡

አሻግሬ ሳይም በአረንጓዴ ቢጫና ቀይ ደማቅ ቀለማት የተዋበ ሰፊ በር ታዬኝ፡፡ በበሩ መሀልም ማለፍን ተመኘሁም፡፡

የምንገኘው ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ካፋ ዞን ቦንጋ ከተማ ነው፡፡ ቦንጋ የዕውቀት ጮራ ካረገዘች ሁለት ዓመታትን አስቆጥራለች፡፡ ዛሬ ትወልዳለች፡፡ እልልልል ይባልላታል፡፡

ሰንጋ ታርዶ ፍሪዳው ተሰቅሏል፡፡ ጠጁ ተጥሎ መዓዛው ያውዳል፡፡ ሁሉ ሙሉ ሁሉ ዝግጁ ሆኖ ተሰናድቷል፡፡

የሚታየው ሁነትም ባገሩ የተከበረና ተወዳጅ ለሆነ ለአንድ ሀገር ባለሟል ኢትዮጵያዊ ድግስ ለማውጣት የሚደረግ ርብርብ ይመስላል፡፡

ሰው ሁሉ ከወዲያ ወዲህ ይጣደፋል፡፡ ሁሉም በሥራ ላይ ነው፡፡ ሁሉም ፊት ላይ የሚታየው ደስደስ ነው፡፡

የከተማው ነዋሪ አጠቃላይ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲን ቤቴ ብሏል፡፡ ቤቱን  ትቶ የዩኒቨርሲቲው ቅጽር ግቢ ውስጥ ነው ያለው፡፡ እናቶች ሽር ጉዱን ተያይዘውታል፡፡ ወገባቸውን አስረው ለሥራ ታጥቀው እሚበላ እሚጠጣውን እያሰናዱ ነው፡፡

አባቶችም በፊናቸው የተንጣለለ ማለፊያ አዳራሽ አዘጋጅተዋል፡፡ የሰሩት አዳራሽም ስፋቱ ፈረስ ያስጋልባል፡፡

መለስተኛ ስታዲያም በሚመስለው አዳራሽ በወንበር ተሞልቷል፡፡ እንደየእንግዶቹ ዓይነት በተለያየ መልክ ነው ወንበሮቹ የተሰደሩት፡፡ የክብር እንግዶች ሐይማኖት አባቶች የሀገር ሽማግሌዎች ከፊት፤ የተማሪችና የተማሪ ወላጆች ከቀኝ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ በስተግራ ቦታቸው ነው፡፡ ለሁሉም ታዳሚዎች መርሀ ግብሩን ተንፈላሰው ዘንተው የሚታደሙበት ሁኔታ ተመቻችቶላቸዋል፡፡

ቀኑ ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ ገቢ ተማሪዎቹን የሚቀበልበትና የዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍ የሚመረቅበት ዕለት ነው፡፡

ዝግጅቱ ደግሞ የቦንጋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ወደ ልጅ እግሩ ጀማሪ ዩኒቨርሲቲያቸው የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን አቀባበል የሚያደርጉበት ልዩ ፕሮግራም፡፡

ነዋሪዎቹ ዓዲስ ገቢ ተማሪዎችን የበኩር ልጆቻችን ብለዋቸዋል፡፡

ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡት እንግዳ ተማሪዎች በጉጉት ይጠበቃሉ፡፡ ፍጹም ቤተኝነት እንዲሰማቸውም ነዋሪዎቹ  ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ሰፊ ዝግጅት አድርገዋል፡፡

አቶ ዓለሙ ገብሬ በቦንጋ ከተማ የ01 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የዩኒቨርሲቲው የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች ድጋፍ በማድረግ አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ቀበሌያቸው ከ13ሺህ ብር በላይ ለተማሪዎች አቀባበል አዋጥቷል የቀበሌው ነዋሪ ባዋጣው ገንዘብም አንድ ሰንጋ በሬና ሃይላንድ ውሀ በመግዛት አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በድግስ ለመቀበል ሽር ጉድ ላይ ናቸው ፡፡

የእናት አንጀት አይጨክንም ባንወልዳቸውም ልጆቻችን ናቸው፡፡ ትምህርቱን ጨርሰው ወደ ወላጆቻቸው እስኪመለሱ እኛ አለንላቸው ያሉት የ03 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሽታዬ አብደልኑር ናቸው፡፡

ልጆቹ ለአጉል ድርጊትና ለሱስ እንዳይዳረጉም ከአሁኑ የሱስ ቤቶች እንዳይስፋፉ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት ነው ሲሉ አወጉኝ፡፡

የተደረገለት አቀባበል ከጠበቀው በላይ ነው ለተማሪ ነብዩ ደምሴ ከኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ነው የመጣው ይህን ያህል ኪሎሜትር ተጉዞ ቦንጋ ሲደርስ ግን ባልጠበቀውና ሆኑ በሚመለከተው አቀባበል ረክቷል፡፡

የእንግድነት ስሜት እንዳይሰማው ያደረገው የህዝቡ አቀባበል በሁሉም አካባቢዎች ለተመደቡ ተማሪዎች እንዲህ በሆነ ሲል ተመኘ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው መረዳዳት ነው መተጋገዝ አለሁልህ መባባል ነው ይህን ሁሉ በቦንጋ ህዝብ ውስጥ መመልከቱ አስደስቶታል፡፡

እንዲህ ላከበረኝና ለመከረኝ እንደ እንቁላል በጥንቃቄ እንደሚይዘኝ ለነገረኝ ህዝብ በትምህርቴ ስኬታማነት ውለታውን ለመክፈል ተዘጋጅቻለሁ ነው ያለው፡፡

ዶክተር ጴጥሮስ ወ/ጊዮርጊስ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት የአዲሱ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ እሳቸውም የከተማዋ ነዋሪ ለተማሪዎቹ ያደረገው አቀባበል አስደምሟቸዋል፡፡

በግንባታው ላይ በንቃት በመሳተፍ የበረከተው ሳያንስ ዛሬ ደሞ ከኪሱ ያለውን እየመዘዘ የዩኒቨርሲቲውን የመጀመሪያ ልጆች በፍቅር መቀበሉ ልባቸው በደስታ እንዲርድ ማድረጉን ሊደብቁት አልቻሉም፡፡

ይህን ለኢትዮጵያ ሳንባ ንጹህ አየር የሚለግስ ተፈጥሮ ባለቤት የሆነ ህዝብን ለመጥቀም ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት ላይ በትኩረት ይሰራ ሲሉ ለህዝቡ ውለታ ቃል ገቡ፡፡

ትምህርት ዓለም አሁን ለደረሰችበት ዕድገትና ለውጥ እንድትበቃ ተተኪ የሌለው ሚና የተጫወተ ዘርፍ ስለመሆኑ እማኝ ያማያሻው ጉዳይ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

የሰለጠኑ ሀገራት ዜጎቻቸው በዕውቀት የተካኑና የበቁ እንዲሆኑ የትምህርት ፍላጎታቸውን በማሟላትም አሁን ያሉበት ልዕልናቸውን ማግኘት ችለዋልም ብለዋል፡፡

በ1987 ዓም የተቀረጸው የሀገራችን የትምህርት ፖሊሲ ፍትሀዊ የትምህርት ተደራሽነት እንዲኖርና የተማረ ህብረተሰብ በመገንባት ወደ ዕድገት ጎዳና ለሚደረግ ጉዞ መንደርደሪያ መሰረት የጣለ ነው ብለዋል፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲም የዚህ የትምህርት ፖሊሲ ፍትሀዊነትን ማሳያና ማረጋጋጫ ስለመሆኑ በመግለጽ ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ማህበረሰብ የዘመናት ጥያቄን የመለሰ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፍትሀዊነትን ከማረጋገጥ ባሻገር ሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስፈልጋን የሰለጠነና የተማረ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት ግብና አቅጣጫ ተከትሎ የተገነባ ተቋም ነው ያሉት ደግሞ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙበትን አካባቢ መሰረት በማድረግና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ያሉት ዶ/ር ጥላዬ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲም ሰፊ ሥራ ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰላም ደሴቶች  በምክንያትና በውይይት የሚያምን ህብረተሰብ ማዕከል በመሆናቸው ሰላማዊ የመማር ማስተማር እንዲኖርም ማረጋገጥ ይገባልም ብለዋል፡፡

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ እኤአ በ2030 በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም በአፍሪካ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግንባር ቀደም ሆኖ መገኘት ራዕዩ ነው!!!

ሀገራዊ ህዳሴን ለማሳለጥና ለማረጋገጥ እንዲሁም የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ትምህርት በትምህርት የታገዘ ዕውቀት እንላለን፡፡ በዕውቀት ህቡዕ ይገለጣል ሩቁ ይቀርባልና፡፡

ቸር እንሰንብት

Published in ዜና ሐተታ

ባህር ዳር ጥር 29/2010 በደቡብ ጎንደር ዞን በቢራ ገብስ ልማትና ዘር ብዜት ሥራ መሳተፍ የጀመሩ አርሶ አደሮች የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናገሩ።

 የጎንደር ብቅል ፋብሪካም በተያዘው በጀት ዓመት እስካሁን ድረስ 70 ሺህ ኩንታል የብቅል ገብስ ከአርሶ አደሮች መረከቡን ገልጿል።

 በዞኑ እስቴ ወረዳ የዱርጌ ማሽንት ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃን ይመር ትላንት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በቢራ ገብስ ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ስድስት ዓመት ሆኗቸዋል።

 ባለፈው ዓመት ከአራት ሄክታር በላይ መሬት አልምተው ያገኙትን 94 ኩንታል የቢራ ገብስ ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ በማስረከብ ከ104 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 በ2009/2010 የምርት ዘመን መሬቱን ለማፈራረቅ በሚል ድንች ቢያለሙም ገቢያቸው ከቢራ ገብሱ አንጻር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

 "ዘንድሮ ከድንቹ ጎን ለጎን ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ አልምቼ ከሰበሰብኩት 15 ኩንታል የቢራ ገብስ 17 ሺህ 850 ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል።

 በምርት ዘመኑ ከቢራ ገብስ ዘር ብዜትና ልማት ያገኙትን 22 ኩንታል ለአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝና ለጎንደር ብቅል ፋብሪካ ማስረከባቸውን የገለጹት ደግሞ የላይ ጋይንት ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አለምነው ውቤ ናቸው።

 ከዚህም 28 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

 እንደ አርሶ አደር አለምነው ገለጻ፣ በቢራ ገብስ ልማትና ዘር ብዜት ሥራ መሳተፍ ከጀመሩ ካለፉት ሰባት ዓመታት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከገቢያቸው ከ115 ሺህ ብር በላይ በባንክ መቆጠብ ችለዋል። 

 የቢራ ገብስ ልማት አዋጭ በመሆኑ በመጪው የመኽር ወቅት አብዛኛው መሬታቸውን በቢራ ገብስ ሸፍነው በማልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ ተዘጋጅተዋል።

 የጎንደር ብቅል ፋብሪካ የቢራ ገብስ ምርትና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ አቶ አደባባይ ፀጋው በበኩላቸው፣ ፋብሪካው በዚህ ዓመት 230 ሺህ ኩንታል የቢራ ገብስ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል።

 "በምርት ዘመኑ ከመኽርና በመስኖ ከለማው 90 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ የብቅል ገብስ ከአርሶ አደሮች ኩንታሉን በአንድ ሺህ 190 ብር ለመግዛት አቅዶ እስካሁን የ70 ሺህ ኩንታል ግዥ ፈፅሟል" ብለዋል።

 " ፋብሪካው በዕቅድ የያዘውን የቢራ ገብስ ከአርሶ አደሩ ሙሉ በሙሉ ሲያሰባስብ ከውጭ ለቢራ ገብስ ግዥ ሊያወጣ የሚችለውን አምስት ሚሊዮን ዶላር " የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚችልም አስረድተዋል።

 በቀጣይም አርሶ አደሮች የውጭ ምንዛሬን ሙሉ በሙሉ ለማስቀረት ጥራቱን የጠበቀ የብቅል ገብስ በጥራትና በብዛት አምርተው በተሻለ ዋጋ ለፋብሪካው  በማስረከብ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

 እንደ አቶ አደባባይ ገለጻ፣ ፋብሪካው ባለፈው ዓመት ከአምራች አርሶ አደሮች 85 ሺህ ኩንታል የጥራት ደረጃው የተረጋገጠለት የብቅል ገብስ ከአርሶ አደሮች ተረክቦ ጥቅም ላይ አውሏል።

 ከአማራ ከልል ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2009/2010 የምርት ዘመን በክልሉ በቢራ ገብስ ከለማው 15 ሺህ 273 ሄክታር መሬት ከ290 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 29/2010 በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ የችርቻሮ ሱቆችና ስጋ ቤቶች ተጠቃሚውን በሚዛን እንደሚያታልሉ የኢትዮጵያ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን  ጥናት ይፋ አድርጓል፡፡

በመዲናዋ የሚገኙ 110 የግልና የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የችርቻሮ ሱቆችና ስጋ ቤቶች በናሙናነት ተካተዋል።

ምልከታ ከተደረገባቸው 12 የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ስጋ ቤቶች መካከል አስሩ፤ ከ21 የግል ስጋ ቤቶች መካከል ደግሞ 11ዱ የሚዛን ጉድለት ችግር ታይቶባቸዋል።

በባለስልጣኑ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ሞላ እንደገለጹት የክብደት ልኬት መዛባት  ሸማቹ  በከፈለው ገንዘብ ልክ የሚገባውን ጥቅም እንዳያገኝ እያደረገው ነው።

በቀጣይ ድንገተኛ ፍተሻዎችን በማድረግ ጉድለት በሚታይባቸውና የልኬት መሳሪያዎች ማረጋገጫ እውቅና ሳያገኙ ወደ ስራ የሚገቡ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያስታወቁት፡፡

ሸማቹ  ግዢ በሚፈጽምበት ጊዜ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ጠቁመው መሰል የማታለል ድርጊቶች ሲያግጥሙት በ8478 ነፃ የስልክ መስመር ለባለስልጣኑ እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።

Published in ማህበራዊ

ጭሮ 29/2010 በሀገሪቱ የተረጋገጠው የፌደራሊዝም ሥርዓት ተጠብቆ እንዲቆይ ከወጣቱ ብዙ እንደሚጠበቅ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አፈጉባዔዎች ፎረም አስታወቀ።

የዞኑ ምክርቤት አፈጉባዔዎች ፎረም ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ ጀማል ለኢዜአ እንዳሉት በአገሪቱ የተዘረጋው የፌዴራሊዝም ስርዓት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቃቸው እንዲማሩና እንዲዳኙ ዕድል ሰጥቷል።

የፌደራሊዝም ሥርአቱ ብሔር በሔረሰቦች በማንነታቸው እንዲኮሩ፣ በአካባቢያቸው ልማት እንዲሳተፉና ከውጤቱም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ፣ በሀገሪቱ በየዘርፉ ለተመዘገበው እድገት ጉልህ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል።

የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲሁም አልፎ አልፎ የሚታየው ጽንፈኝነትና ግጭት በአሁኑ ወቅት የሥርአቱ አደጋ እየሆኑ ስለመምጣታቸው ወጣቶች ሊገነዘቡ እንደሚገባም አፈጉባኤዋ አመልክተዋል።

ፌደራሊዝም የሀገራቱ ህዝቦች ሃይማኖታቸውንና ባህላቸውን እንዲያሳድጉና ጠብቀው እንዲቆዩ መንገድ የከፈተ መሆኑን ወጣቶቹ ተረድተው ለስርዓቱ ቀጣይነት የድርሻቸውን ሊወጡ አንደሚገባ ገልጸዋል።

ማንኛውንም ጥያቄያቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከማቅረብ ባለፈ በየዘርፉ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ማስቀጠልና በሚከናወኑ የልማት ሥራዎችም ተሳታፊና ተጠቀሚ መሆን እንዳለባቸው ጨምረው አመልክተዋል።

"በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለሚኖሩባት ኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው" ያሉት ደግሞ የፎረሙ ፀሐፊ አቶ ጀማል መሀመድ ናቸው፡፡  

"ወጣቱ የስርዓቱ አደጋ የሆኑትን ችግሮች ተገንዝቦ ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን በመቆም ለሀገር አንድነትና እድገት የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት" ብለዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ትዝታ ስዩም በበኩላቸው የተጀመረው የሰላምና የማረጋጋት ሥራ እንዲጠናከር መንግስት የህዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ ከመመለስ ባለፈ የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ዘላቂ በሆነ መንገድ ማረጋገጥ እንዳለበት አመልክተዋል ።

ወጣቱ ትውልድ ተገቢ ወዳልሆነ ድርጊት የሚመሩትን አፍራሽ ኃይሎች በቀዳሚነት መታገል እንዳለበት የተናገሩት ሌላው  የከተማው ነዋሪ አቶ ደመረው አለማየሁ  ናቸው ።

ወጣቱ በሕብረተሰቡ መካከል ልዩነትና ግጭት ለመቀስቀስ ለሚጥሩ አካላት ትኩረት ሳይሰጥ በብዙ መስዋዕትነት የተረከበውን ሀገርና የተረጋገጠውን የፌደራል ስርዓት ጠብቆ ማቆየት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ ጥር 29/2010  የወለጋ ዩኒቨርሲቲ  የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ  በአካባቢው ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እያደረገ ያለው ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሆን እቅድ አዘጋጅቶ በምሥራቅ ፣በምዕራብ፣በቄለም፣እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች ነው፡፡

 በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና ኢንዱስትሪ  ትስስር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ትፍስህት ሰለሞን እንደገለጹት ተቋሙ በስሩ በሚገኙ   ኮሌጆች አማካኝነት ከአንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የትምህርት ጥራት መጓደል ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል፡፡

 በተለይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣በተፈጥሮ ሳይንስና በሒሳብ የትምህርት ዓይነቶች መምህራን የተለያዩ የማስተማር ዘዴዎችን በመጠቀም ተማሪዎችን ለማብቃት እንዲችሉ ተከታታይ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 ተማሪዎች በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በዩኒቨርሲቲው በመገኘት በተግባር የተደገፈ ልምምድ እንደሚያደርጉ ዶክተር ትፍስህት አመልክተዋል፡፡ 

 የተግባር ልምምድ ከሚያደርጉባቸው መካከል ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬንሽን ቴክኖሎጂና  የኤሌክትሪክ ስራዎች  ይገኙበታል፡፡

 በዩኒቨርስቲው የቋንቋዎች ጥናትና የጋዜጠኝነት ተቋም መምህር አቶ ዘሪሁን ቡሊ በበኩላቸው ተቋሙ  የተለያዩ ፕሮጀክቶችን  ቀርፆ የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት በአራቱ የወለጋ ዞኖች እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለማሻሻልና የትምህርት አሰጣጡን ተማሪ ተኮር ለማድረግ ለመምህራን የተለያዩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

 በተያዘው የትምህርት ዘመንም ከሁለተኛው  ሴሚስተር ጀምሮ የሚደረገው የአቅም ግንባታ ድጋፍ ይቀጥላል፡፡

 የዳሎ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ታሢሣ ጎበና በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርሲቲው መምህራን በትምህርት ቤቱ በመገኘት ለተማሪዎች የሒሳብና የፊዚክስ ማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

 በተጨማሪም  15 ኮምፒዩተሮች እና 100 የተማሪ ወንበሮች  በስጦታ ከዩኒቨርስቲው ማግኘታቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

 ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን ለማብቃት በሚያደርገው ድጋፍ ከትምህርት ቤቱ ተሰጥኦ ያላቸው ተመርጠው  በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ውድድር   ሦስት ተማሪዎች  መሸለማቸውን ጠቁመዋል፡፡

 የትምህርት ቤቱ የአስረኛ  ክፍል ተማሪ ታሪኩ ተፈራ ዩኒቨርሲቲው በሚያደርግለት ድጋፍ የእህል ማበጠሪያ ማሽን ሞዴል በማዘጋጀት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተደረገው ውድድር ላይ መሳተፉን ተናግሯል፡፡

 በዚህም አምስተኛ  ደረጃን በማስመዝገብ  የገንዘብ ሽልማት ማግኘቱና ይህም  ለፈጠራ ስራው ይበልጥ እንዲነሳሳ ማበረታቻ እንደሆነው አመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 29/2010 ስድስት ክልሎች በ2010 በጀት ዓመት ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ የተመደበውን ተዘዋዋሪ ብድር አለመውሰዳቸውን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስታወቀ።

ትግራይ፣ አማራ፣ ሃረሪ፣ አዲስ አበባ፣ አፋርና ጋምቤላ የተመደበላቸውን ተዘዋዋሪ በጀት ያልወሰዱ ክልሎች ናቸው።

የፌደራሉ መንግስት በ2010 ዓ.ም ለወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ አምስት ቢሊዮን ብር መመደቡ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በግማሽ ዓመቱ ክልሎቹ የወሰዱት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ያህሉን ብቻ መሆኑን ነው የገንዝብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትሩ ዶክተር አብርሃም ተከስተ ለኢዜአ የገለጹት።

በዚህ ዓመት ከጸደቀው 5 ቢሊዮን ብር ውስጥ ክልሎቹ የተጠቀሙት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ገልጸው ይህም በአፈጻጸም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ክልሎቹ የተመደበላቸውን በጀት አለመውሰዳቸው የመንግሥትን የስራ እድል ፈጠራ ስራ አፈጻጸም ዝቅተኛ እንዳደረገውም ተናግረዋል፡፡

መንግስት ባለፈው ዓመት የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ 10 ቢሊዮን ብር መድቦ ወደ ስራ ቢገባም በአንዳንድ ክልሎች የአጠቃቀም ክፍተት መኖሩን አንስተዋል።

የጸደቀውን የወጣቶች ተዘዋዋሪ በጀት ማቅረብና ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ማከፋፈል የመስሪያ ቤታቸው ኃላፊነት ቢሆንም  ስድስቱ ክልሎች የተፈቀደላቸውን በጀት ለመጠቀም ምንም አይነት ጥያቄ እንዳላቀረቡ ነው ያብራሩት።

ሚኒስትሩ እንዳብራሩት ክልሎቹ የተፈቀደላቸውን በጀት ያልተጠቀሙበትን ምክንያት ለማወቅ የሚመለከተው አካ የማጣራት ስራ እየተሰራ ነው፡፡

ክልሎቹ የተመደበላቸውን በጀት ጥቅም ላይ በማዋል የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መረባረብ እንዳለባቸውም ዶክተር አብርሃም ተከስተ  አሳስበዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 29/2010 በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላትን የሚያስተሳስር "ቢውልዲንግ ኢንፎርሜሽን ሞዴል" የተሰኘ ቴክኖሎጂ ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተነገረ።

 የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ለማስፋት ለ20 የዘርፉ ባለሙያዎች የአሰልጣኝነት ስልጠና እየሰጠና የፖሊሲ ዝግጅትም እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

 ከአሜሪካ የመነጨው ይህ ቴክኖሎጂ በእንግሊዝና በሩቅ ምስራቅ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑም ተነግሯል።

 ቴክኖሎጂው የግንባታው ባለቤት፣ የስራ ተቋራጩ፣ አማካሪውና ግብዓት አቅራቢዎች በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስችልም ነው።

 የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋ አሻ ለኢዜአ እንደገለጹት ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአንድ ህንጻ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቅንጅትና በመናበብ እንዲሰሩ ያደርጋል። 

 ከግንባታ በፊት ህንጻው ምን እንደሚመስል፣ የሚያስፈልጉት የግብዓት ዓይነቶች፣ የኤሌክትሪክ፣ የፍሳሽ መስመሮችና ለዚሁ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በቅድሚያ በመለየትና በማሳየት በግንባታ ሂደት የሚከሰትን አላስፈላጊ ወጪ ያስቀራል፤ ጊዜም ይቆጥባል።

 በግንባታ ወቅት በህንጻው ላይ የዋጋ፣ የዲዛይንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ቢከሰት ባለድርሻ አካላቱ በተመሳሳይ ጊዜ ስለ ለውጡ እንዲያውቁ ማድረግም ያስችላል እንደ ዶክተር አረጋ ገለፃ።

 ይህም አንድ የኪነ-ህንጻ ባለሙያ በሚሰራው ህንጻ ላይ የተወሰነ ለውጥ ሲያደርግ ለውጡን ለህንጻው ባለቤትና ለኮንትራክተሩ በማሳየት የሚፈጀውን ገንዘብና ጊዜ ለማወቅ ይረዳል ነው ያሉት።

 የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ለማስፋት የአሰልጣኞች ስልጠና በመውሰድ ያሉ ባለሙያዎች ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ ሌሎችን በማሰልጠን ቴክኖሎጂው ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፉ የበለጠ እንዲሰርፅ የማድረግ ሥራ ይሰራሉም ብለዋል።

 በመንግስት በኩል ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በሚኖራቸው ግንባታዎች ላይ ቴክኖሎጂውን ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር አረጋ ገልጸዋል።

 በዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉትን የሙስናና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ይቻላል የሚል እምነት መኖሩን ተናግረዋል።

 የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምርጥ ተሞክሮዎችን፣ ወጪ ቆጣቢና የተሻሻሉ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ለማሻሻል የተቋቋመ ተቋም ነው።

አዲስ አበባ ጥር 29/2010 የጤና ተቋማትን ደረጃ በአገራዊ የጤና መስፈርቶች መሰረት በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን የአዲስ አበባ የምግብ፣ መድሃኒትና የጤና እክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ገለፀ።

 የጤና ተቋማቱ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ፍቃድ ሲያወጡ በደረጃ ተለይተው ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ አሰራር መተግበሩ ይታወቃል።

 የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምጸሀይ ጳውሎስ ለኢዜአ እንደገለጹትም በተያዘው ዓመት የጤና ተቋማቱን ደረጃ በአገራዊ የጤና መስፈርቶች መሰረት የማሟላቱ ስራ ውጤታማ እየሆነ ነው።

 የህክምና መሳሪያዎችና ግብዓቶችን ማሻሻል፣ ብቃት ያለው የሰው ኃይል ማሟላትና በቂ የቦታ ይዞታን ከመስፈርቶቹ መካከል ጠቅሰዋል።

 መስፈርቶቹን አሟልተው በሚሰጣቸው ነጥብ 75 በመቶና ከዛ በላይ ያስመዘገቡ ተቋማት አረንጓዴ፣ ከ50-75 የሚያገኙ ቢጫ፣ ከ50 በታች የሆኑት ደግሞ ቀይ ደረጃ እንደሚሰጣቸው አብራርተዋል።

 በመስፈርቶቹ የሚመዘኑት በአዲስ አበባ የሚገኙ ከመጀመሪያ ደረጃ ክሊኒክ እስከ አጠቃላይ ሆስፒታል ድረስ ያሉ የጤና ተቋማት ናቸው።

 በዚሁ መስረት በ2010 ዓ.ም ሁሉም የጤና ተቋማት በአረንጓዴ ደረጃ ላይ እንዲገኙ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ነው ምክትል ዳይሬክተሯ የገለጹት።

ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ ደረጃ ላይ ይገኙ የነበሩት 64 በመቶ ያህሉ የጤና ተቋማት ሲሆኑ በዚህ ዓመት አሃዙ ወደ 95 በመቶ አድጓል።

የጤና ተቋማቱ የውስጥ ጥራት ቁጥጥር እንዲያደርጉ መደረጉና በየጤና ተቋማቱና በባለስልጣኑ ለባለሙያዎች የተሰጡ ስልጠናዎች ለተመዘገበው ውጤት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በቢጫ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙት 5 በመቶ የሚሆኑ የጤና ተቋማትም ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

ባለፈው ዓመት 30 የጤና ተቋማት በቀይ ደረጃ ውስጥ እንደነበሩም ወይዘሮ አለምፀሃይ አንስተዋል።

በተደረገው ተከታታይ ቁጥጥርና ክትትል ከእነዚህ ተቋማት መካከል ሶስቱ የነበሩባቸውን ችግሮች ማስወገድ ባለመቻላቸው አገልግሎት መስጠት እንዲያቋርጡ መደረጉን ተናግረዋል።

ቀሪዎቹ 27 ተቋማት ደረጃቸውን ማሻሻል በመቻላቸው በአሁኑ ወቅት በቀይ ደረጃ የሚገኝ ተቋም የለም ነው ያሉት።

ወደ ስራ ለሚገቡ አዳዲስ የጤና ተቋማት ፍቃድ የሚሰጠው መስፈርቶቹን ሙሉ በሙሉ ሲያሟሉና አረንጓዴ ደረጃ ላይ ሲገኙ ብቻ  እንደሆነም አስታውቀዋል።

በመዲናዋ ከመጀመሪያ ደረጃ ክሊኒክ እስከ አጠቃላይ ሆስፒታል ባለው ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ 1 ሺህ 74 የግልና የመንግስት የጤና ተቋማት ይገኛሉ።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ጥር 29/2010 በትግራይ ክልል በአንዳንድ ተቋማት የሚቀርበውን የሀሰት ሪፖርት ለመከላከል አህዛዊ መረጃዎችን የሚያሰባስብ ኤጀንሲ እንደሚቋቋም የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በክልሉ ምክርቤት 4ኛ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት የክልሉ የስድስት ወራት የሥራ እንቅስቃሴ አስመልከተው ከምክርቤቱ አባለት ለተነሱት ጥያቄዎች ትናንት ምላሽ ሰጥተዋል።

ዶክተር ደብረጽዮን በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ በተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ሪፖርቶች ከእውነት እየራቁ መጥተዋል፤ ይህ ደግሞ እየተደረገ ላላው የጸረ ድህነት ትግል እንቅፋት እየሆነ መጥቷል።

እንደ ርዕሰ መስታዳድሩ ገለጻ ከዚህ ቀደም አንድ ሰው የተሰራውንና ያልተሰራውን ስራ በአግባቡ ለይቶ ትክክለኛ ነገሩን ያሳይ የነበረው ተነሳሽነት በአሁኑ ወቅት እየተቀየረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በውሸት ላይ ተመስርተው የሚዘጋጁ ሪፖርቶች የሚደረገውን የፀረ ድህነት ትግል እንደሚያደናቅፉና ህዝቡ በተባለው ልክ ሳይጠቀም እንደተጠቀመ  የሚያደርግ በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት በባለሙያዎች የሚመራ አሀዛዊ መረጃዎችን የሚያሰባስብ ተቋም በኤጀንሲ ደረጃ በክልሉ እንደሚቋቋመም ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፣ ባለፉት የግምገማ መድረኮች በአንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች በውሸት ተደጋግፎ ወደ ስልጣን የመምጣት ፍላጎት በስፋት እንዳለ ታውቋል።

ይህን ችግር ለማረም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ቢሮዎች በራሳቸው የሚያቀርቡትን ሪፖርት ሳይሆን ሦስተኛ ወገን ይዞት የሚቀርበውን ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት እንዲቀርብ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።

በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት የሁሉም ቁርጠኛነት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፣ መንግስት ከመቼውም ጊዜ በላይ ለዚህ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው በውይይት ወቅት የተነሱ ጉዳዮችን በመስክ ምልክታ ለማረጋገጥ ሙከራ በሚያደርጉበት ወቅት በሪፖርት የሚገለጸውና በተጨባጭ መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚለያይበት አጋጣ በርካታ መሆኑን ተናግረዋል። 

ከምክር ቤቱ አባላት መካካል የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲስተር ገነት ደስታ እንዳሉት፣ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባካሄዱት የመስክ ምልክታ በሪፖርት እየቀረበ ያለውን ያህል አይደለም።

በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጠቃሚ አድርገናል ያሏቸው ሴቶች በተገለጸው ልክ አለመሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ማረጋገጣቸውን አመልክተዋል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ደክተር ገብረመስቀል ታረቀ በበኩላቸው፣ ባለፈው ዓመት በክልሉ ውስጥ አምስት ሺህ ተማሪዎች ማቋረጣቸው የሚገልጽ ሪፖርት ቀርቦ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁንና ባለፈው መስከረም ወር ባካሄዱት የመስክ ምልከታ 88 ሺህ ተማሪዎች የችግሩ ሰለባ መሆናቸው በተጨባጭ መረጋገጡን ተናግረዋል።

በየጊዜው የውሸትና ተጋነው የሚቀርቡ ሪፖርቶችን ለመከላከል የክልሉ መንግስት በቀጣይ ኤጀንሲ ለማቋቋም ያቀደው የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ለስራው ውጤታማነት የሁሉም ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።   

የምክር ቤቱ አባላት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የቀረቡትን የስድስት ወር ሪፖርት ከገመገሙ በኋላ ትናንት ማምሻው በሙሉ ድምፅ ማጽደቃቸው ታውቋል።

በዛሬው እለትም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድቤትና የዋና ኦዲተር ሪፖርቶችን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመምከር ላይ መሆናቸውን የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

Published in ፖለቲካ

 ሀዋሳ ጥር 29/2010 የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት መክፈላቸው የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ያለስጋት ለማከናወን እንዳስቻላቸው በደቡብ ክልል የሃዲያ ዞን ሞዴል ግብር ከፋዮች ተናገሩ፡፡

11ኛው የገቢ ሳምንት "የታክስ ትንራንስፎርሜሽን ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል በሃዲያ ዞን ሆሳዕና ከተማ ተከብሯል።

በሆሳዕና ከተማ በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ መስፍን ጀምበሩ እንዳሉት ሰርተው ከሚያገኙት ገቢ የሚከፍሉት ግብር ለአካባቢውና ለሀገር ልማት እንደሚውል በመገንዘባቸው ግብራቸውን በአግባቡ ይከፍላሉ፡፡

በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት በየወሩ በቫት ብቻ ከ90 እስከ 120 ሺህ ብር ለመንግስት ገቢ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

የሚጠበቅባቸውን ግብር በሰዓቱና በታማኝነት መክፈላቸው ኩራት እንዲሰማቸው ከማድረጉም ባለፈ ከመንግስት ተቆጣጣሪዎች ሥራቸውን ሳይደበቁ ያለፍርሃትና ጥርጣሬ እንዲሰሩ ያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየዓመቱ ከ250 እስከ 320 ሺህ ብር ግብር እንደሚከፍሉ የገለጹት አቶ መስፍን፣ በእዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት ሞዴል ግብር ከፋይ በሚል በመንግስት እውቅና እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በሆቴልና በግንባታ ሥራ የተሰማሩት አቶ በረከት ፀጋዬ በበኩላቸው፣ በግማሽ ዓመት ውስጥ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግብር በመክፈላቸው መሸለማቸውን ተናግረዋል፡፡

" ግብርን በወቅቱ በመክፈል ግዴታን መወጣት ትልቅ የአእዕምሮ እረፍት ይሰጣል " ያሉት አቶ በረከት ፣ ሁሉም ሰው ልማት ያለ ግብር  የሚታሰብ አለመሆኑን በመረዳት ኃለፊነቱን እንዲወጣ  አስገንዝባዋል።

በመንግስት የተሰጣቸው እውቅና እንዳስደሰታቸውና ለቀጣይ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንዳንድ ነገዴዎች ላይ የሚስተዋለው ለሸማቾች ደረሰኝ ያለመስጠት ችግር ሊታረም እንደሚገባ ገልጸዋል።

እንደ አቶ በረከት ገለጻ፣ በግብር አሰባሰብ ላይ ያለውን የግንዛቤና የአስተሳሰብ ችግር ለመቅረፍ መንግስትና ነጋዴው እንዲሁም ሁሉም የህብረሰተሰብ ክፍል ተቀራርበው መስራት ይኖርባቸዋል።

የሃዲያ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በበኩላቸው እንዳሉት ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ የታክስ ስርዓት ለመፍጠር በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ግብርን በታማኝነትና በወቅቱ የሚከፍል ግብር ከፋይ እየተፈጠረ ነው፡፡

የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ እያደገ ቢመጣም አኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ መሰብሰብ እንዳልተቻለና  ለልማት የሚወጣውን ወጭ ከመሸፈን አንጻርም ብዙ ስራ እንደሚቀር ተናግረዋል፡፡

የዞኑ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን በማዘመን ስምንት አዳዲስ ቅርንጫፎ  ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ እየሰራ መሆኑንም አቶ ስንታየሁ አመልክተዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ በበኩላቸው የ2010 የገቢ ሳምንት የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነትን ትግል በማጠናከር፣ ጠንካራ የታክስ ስርዓት በመፍጠር፣ ለልማታዊ ባለሃብት ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠትና ህገ ወጥ ተግባራትን በብቃት በመከላከል እንደሚከበር ገልጸዋል።

አቶ ንጉሴ እንዳሉት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዓመት መጨረሻ የክልሉ ገቢ ከአጠቃላይ የክልሉ ምርት ገቢ ጋር ሲጻጸር 16 በመቶ እንዲያመነጭ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

ለዚህም ህገ ወጥ ንግድ፣ ግብር የማጭበርበርና የቫት ደረሰኝ ያለመስጠት ችግሮችን በመፍታት የህዝቡን የልማት ጥያቄ መመለስ እንደሚገባ  እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

11ኛው የገቢ ሳምንት በውይይት፣ በእግር ጉዞና በተለያዩ ዝግጅቶች የተከበረ ሲሆን ሞዴል ግብር ከፋዮችና የተቋሙ ምርጥ ፈጻሚዎችም ሽልማትና እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን