አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 05 February 2018

አዲስ አበባ ጥር 28/2010 ለሰባት ቀናት የሚቆየው አምስተኛው አገር ዓቀፍ የህብረት ስራ ማህበራት  ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም የፊታችን ሐሙስ በአዲስ አበባ ይከፈታል።

"የህብረት ስራ ማህበራት ግብይት ለፍታዊ ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ በተመለከተ የፌደራል ህብረትራ ስራ ኤጀንሲ  ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ኤግዚቢሽንና ባዛር በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማዕከል፣ ሲምፖዚየሙ ደግሞ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ የሚካሄድ ይሆናል።

የኤግዚቢሽኑና ሲምፖዚየሙ ዓላማ የህብረት ስራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን ከሸማቾች፣  የአዲስ አበባ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት፣ የግብርና ምርት አቀነባባሪዎችና ከላኪዎች እንዲሁም በአጠቃላይ ከግብይት ተዋናዮች ጋር  ቀጥተኛ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ነው።

280 የህብረት ስራ ማህበራት፣100 የግብርና ምርት አቀነባባሪዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካለላት በሚሳተፉበት በዚህ መድረክ ከ10ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርቶች  ለሸማቹ ማህበረሰብ  በተመጣጣኝ ዋጋ  በቀጥታ የግብይት ትስስር ሽያጭ ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ከ100 ሺህ  ኩንታል በላይ  የግብርና ምርቶች  የግብርና ምርት ከሚሸምቱ  የአዲስ አበባ ሸማች የህብረት ስራ ማህበራትና የግብርና ምርት አቀነባባሪ ኢንዱስትሪዎች ጋር  ቀጥተኛ የገበያ ትስስር የሚፈጠርበት እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ  አስገንዝበዋል።

በሲምፖዚየሙ  ውጤታማ የሆኑ የህብረት ስራ ማህበራት  ልምድና ተሞክሯቸውን የሚያካፍሉበትና የህብረት ስራ ትምህርት የሚሰጡ  ዩኒቨርሲቲዎች በዘርፉ የሰሯቸው  የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል።

ኤግዚቢሽኑንና ባዛሩን 70 ሺህ ሰዎች እንደሚጎበኙትም ይጠበቃል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጥር 27/2010 መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ ወደ ስራ የገቡ የአዲስ አበባ ወጣቶች የምርት ማሳያና መሸጫ ቦታ ችግር እንዳጋጠማቸው ገለጹ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ችግሮቹን  ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 እንጨትና የብረታ ብረት   ውጤቶችን ለማምረት የተደራጁ ወጣቶች ስራ አስኪያጅ ታምራት ጦይንቻ ለኢዜአ እንዳለው ለስድስት ተደራጅተው ባገኙት 150 ሺህ ብር ብድር ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ወጣቱ እንደሚለው ምርታቸውን ተሯሩጠው እየሸጡ የተሻለ ገቢ እያገኙ ቢሆንም የመስሪያ ቦታቸው ለገበያ ምቹ ባለመሆኑ ምርታቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ተቸግረዋል፡፡

ሌላው አስተያት ሰጪ ወጣት አባቴነህ ከበደም እርሱና ጓደኞቹ ሰፈር ውስጥ ያለስራ ቁጭ ብለው ይውሉ እንደነበር ገልጾ አሁን ባገኙት የሙያ ስልጠና፣ የመስሪያ ቦታና ብድር ለስምንት ተደራጅተው ወደ ስራ መግባታቸውን ተናግሯል፡፡

ዘርፉ ጠንክሮ ለሚሰራ አዋጭ መሆኑን በተግባር  እያዩ መምጣታቸውንም ገልጿል፡፡

ለስራቸው እንቅፋት የሆነባቸው የማሳያና መሸጫ ቦታ እጥረቱ ቢቀረፍላቸው ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ወጣቱ የተናገረው፡፡

ወጣት እጸገነት በቀለ እንዳለችው ደግሞ ከአራት አጋሮቿ ጋር ተደራጅተው ባገኙት 150 ሺህ ብር ብድር በአልባሳት ንግድ ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተሰጣቸው ቦታ ለማምረቻ እንጂ ለመሸጫ  ምቹ ባለመሆኑ ማህበሩ መበተኑን ነው የተናገረችው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ቦታዎች አስተዳደርና ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ግዴና ኃይለስላሴ  መንግስት ባለው አቅም የብድር አቅርቦት፣ የስልጠናና የመስሪያ ሼድ  እያሟላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ያም ቢሆን ከፈላጊው ቁጥር አንጻር የመሸጫና ማምረቻ ቦታ ለመስጠት አዳጋች በመሆኑ ሌሎች አማራጮች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ለአብነትም የማሳያና የመሸጫ ቦታ ያገኙ ማህበራት ከኢንተርፕራይዞች የሚረከቧቸውን ምርቶች ብቻ እንዲሸጡ የሚያስገድደው መመሪያ ተሻሽሎ 20 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ቀላቅለው እንዲሸጡ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ማህበራቱ በመሸጫና ማሳያ ማዕከላት ውስጥ ቀላል የስራ መሳሪያዎችን አስገብተው በከፊል የማምረት ስራ እንዲሰሩባቸው መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

የጎላ ችግር የሚስተዋልባቸውን የመሸጫና የማሳያ ህንጻዎች በጥናት ለይቶ ወደ ሌላ ቦታ የመቀየር ስራ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት፡፡

ከምንም በላይ ግን ወጣቱ ያሉትን አማራጮች አሟጦ በመጠቀም በራሱ ጥረት ተወዳዳሪነቱን ማሳደግና ገበያውን ማስፋት እንዳለበት መክረዋል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተመደበው 419 ሚሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ከ37 ሚሊዮን የሚበልጠው ብር  ለ173 ኢንተርፕራይዞች መሰጠቱን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ጥር 27/2010 በጋምቤላ ክልል የስፖርቱን ዘርፍ የማስፈፀም አቅም በማጎልበት ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳደር ጋትሉዋክ ቱት  አስታወቁ፡፡

የክልሉ የልዩ ልዩ   ስፖርት ውድድር  በጋምቤላ ከተማ አስተናጋጅነት ዛሬ ተጀምሯል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ በውድድሩ  በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት ዘርፉ ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ባሻገር ተወዳዳሪዎች በአንድ መድረክ ተገናኝተው የራሳቸውን ባህልና ወግ ከማሳየት  ባለፈ የስፖርተኞች የመቻቻልና የመከባበር እሴትን ለማሳደግ ያግዛል፡፡

በተለይም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና የማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋፋት መንግስት ትኩረት አድረጎ ይሰራል፡፡

ለዚህም ስኬታማነት ሁሉም በጋራ መረባረብ እንዳለበትም ጠቅሰዋል፡፡

በየአካባቢው የሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ የተሻሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም ውጤታማነት ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ መፈጸም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ 

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቴኩዌይ ጋች በበኩላቸው ምርጥ  ስፖርተኞችን  ለመለየት ውድድሩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በውድድሩ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ተወዳዳሪዎች በትግራይ ክልል ለሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች ክልሉን በመወከል እንደሚወዳደሩም  ጠቅሰዋል፡፡

በመክፈቻውም የተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮች የተካሄዱ ሲሆን በእግር ኳስ ጋምቤላ ወረዳ ጋምቤላ ከተማን ሶስት ለአንድ  አሽንፏል፡፡

በውድድሩ ከተለያዩ የክልሉ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደር የተወጣጡ  ከስድስት መቶ በላይ ተወዳዳሪዎች እንደሚሳተፉ  አዘጋጅ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

እስከ የካቲት 10/2010ዓ.ም በሚቆየው በዚህ ውድድር እግር ኳስን ጨምሮ የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች እንደሚካሄዱ ታውቋል፡

 

Published in ስፖርት

መቀሌ ጥር 28/2010 ስፖርታዊ ውድድሮች የሰላም የልማትና የአንድነት ማስተማሪያ መድረኮች ሆነው እንዲቀጥሉ ሁሉም የድርሻውን መስራት እንዳለበት የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

ዘጠነኛው የመላው ትግራይ ወረዳዎች ስፖርት ውድድር ትላንት ማምሻውን በሁመራ ከተማ ተጀምሯል።

የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ኪሮስ ንጉስ በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት ስፖርታዊ ውድድሩ ወጣቶች ወንድማማችነት፤ፍቅርና አንድነታቸውን የሚያረጋግጡበትና ባህልና ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት መድረክ ነው።

''በጨዋታው ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት ክልላችን ዘንድሮ በሚያዘጋጀው ስድስተኛው የመላው ኢትዮጵያ ጨዋታዎች የሚሳተፉ ብቁ ተወዳዳሪዎች ይመረጥሉ" ብለዋል።

በመክፈቻው በተካሄደው የሴቶች 5ሺህ ሜትር ውድድር ገነት ሳህለ ከእንደርታ ወረዳ አንደኛ፤ሂወት ተወልደ ከአክሱም ሁለተኛ፤አመተ ብርሃን ገብሩ ከእንደርታ ሶስተኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በአንድ ሺህ 500 ሜትር መስማት የተሳናቸው ወንዶች ውድድር አንደኛ ሓጎስ በርሀ ከዓዲግራት፣ የማነ መብራህቱ ከደጉዓ ተምቤን ሁለተኛ አሰፋ ገብረህይወት ከአንደርታ ሶስተኛ በመሆን አሸንፈዋል።      

በውድድሩ ከ49 ወረዳዎች የተወከሉ ከ5ሺህ 700 በላይ ወንድና ሴት ስፖርተኞች በአትሌቲክስ፤ በተለያዩ የኳስ ጨዋታዎች፤የቤት ውስጥ ውድድሮች፤የዋና ውድድሮችና በፓራሊምፒክ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በመክፈቻው ላይ የስፖርቱ ደጋፊ የአካባቢውና የክልሉ ነዋሪዎችን ጨምሮ የሱዳን ከሰላ ክፍለ ሃገር ወደልሂለው ዞንና ገዳሪፍ ክፍለ ሃገር የሽወክ ዞን አስተዳዳሪዎችና ተወካዮች በክብር እንግዳነት ተገኝተዋል።

Published in ስፖርት

ባህርዳር ጥር 28/2010 በህብረተሰቡ ዘንድ የሚከበሩ ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅና በማልማት ለሰላምና ለልማት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

የሰባት ቤት አገው ባህላዊ የፈረስ ትርኢት "ለሰላምና ልማት-አይሞሎ " በሚል መሪ ሀሳብ ትናንት በእንጅባራ ከተማ ተካሄደ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ በዚህ ወቅት እንዳሉት ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና ታሪካቸውን በእኩልነት እንዲጠበቁና እንዲያለሙ እየተሰራ ነው።

"በብዛህነታችን ውስጥ ያሉ አንድነታችንንና አብሮነታችንን የሚያጎሉ የተናጠልና የጋራ እሴቶችና ባህሎች ለዘላቂ ሰላምና ልማት ልንጠቀምባቸው ይገባል" ብለዋል።

በተለይም በህዝቡ ዘንድ ታላቅ አክብሮት ያላቸው የግጭት አፈታቶች፣ የግልግል፣ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶች የመረዳዳት፣ የመከባበርና የመቻቻል ተጠቃሽ እሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

እነዚሁ እሴቶች በመጠበቅ  ለሀገሪቱ ቀጣይ እድገት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

የሰባት ቤት አገው የፈረስ ባህላዊ ትርኢት ለ78 ዓመታት ሳይበረዝ እንዲዘልቅ ያደረገውም የህዝቡ ባህሉንና እሴን ጠብቆ ማቆየቱንም አበረታትዋል።

የፈረስ ባህላዊ ትርኢትም ለቱሪስቶች በአግባቡ በማስተዋወቅ ለመስህብ አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው በህዝቡ ዘንድ ተጠብቀው የሚኖሩ ባህላዊ ሃብቶች  በማልማትና በመጠበቅ ለቱሪዝም ልማት እንዲውል እየተሰራ መሆኑን ገልዋል፡፡

"የሰባት ቤት አገው የፈረስ ማህበር የጥንት ባህሎችን ከመጠበቅ ባለፈ አካባቢያዊ ችግሮችን በራስ አቅም በመፍታት  ትምህርት የሚወሰድበት ባህላዊ አሴት ነው "ብለዋል።

በቀጣይም ማህበሩን ባህላዊ ጥንካሬውን ይዞ እንዲቀጥልና ለቱሪዝም ልማት አገልግሎት እንዲውል ለማስተዋወቅ የተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የ78ኛ ዓመቱ የሰባት ቤት ፈረሰኞች ማህበር በዓል ከጥር 23/2010 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱን የገለፁት ደግሞ የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየን ብርሃን ናቸው።

ማህበሩ ጀግኖች አባቶች የሀገራቸውን  ዳር ድንበር ከጠላት ለማስጠበቅ በፈረስ ያደረጉትን ትግልና የከፈሉትን መስዋትነት በማስታወስ በየዓመቱ እንደሚከበር  ጠቅሰዋል፡፡

የሰባት ቤት አገው ፈረሰኞች ማህበር አለቃ ጥላየ አየነው በበኩላቸው ማህበሩ 48 ሺህ 200 አባላት እንዳሉት ጠቅሰው የተሰረቁ ንብረቶችን በማስመለስ፣ የተጣላን በማስታረቅና የተቸገሩን በመርዳት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ማህበሩ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በዞን ደረጃ ከስድስት ሺህ 200 በላይ አስፈፃሚ አካላት እንዳሉት ጠቁመዋል፡፡

የሰባት ቤት አገው ባህላዊ ዝግጅቶች የተካሄዱት በፈረስ ትርኢት፣ በፓናል ውይይት፣ በአውደ ርኢ ፣ በሙዚቃና በሌሎችም ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ ነው፡፡

የክልሎች እና  የፌደራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በበዓሉ  የተገኙ ሲሆን ለዝግጅቱ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት  ሽልማት ተበርክቷል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር28/2010 በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመቐለ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከትናንት በስቲያ እንዲካሄድ መርሃ ግብር ቢወጣለትም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታውን ወደ ነገ አስተላልፏል።

የነገው ጨዋታ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት መቐለ ከተማ ደግሞ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ ለሁለቱ ቡድኖች በጣም ወሳኝ ነው።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ እስካሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን፤ መቐለ ከተማ በ21ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት ከሊጉ ለጥቂት ከመውረድ የተረፈው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ቡድን ዘንድሮም ተደጋጋሚ ሽንፈትን በማስተናገድ ላይ ይገኛል።

በዚህም ምክንያት ክለቡን ሲያሰልጥኑ የነበሩትን ብርሃኑ ባዬን በማሰናበት ታህሳስ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የለቀቁትን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ተክቷል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወራጅ ቀጣና ለመውጣት የግድ ቀጣይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይጠበቅበታል። ከዚህ አኳያ የነገው ጨዋታ ለክለቡ ወሳኝ ነው።

በዮሐንስ ሳህሌ የሚሰልጥነውና ሊጉን ዘንድሮ የተቀላቀለው መቐለ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል። በሊጉም የደረጃ ሰንጠረዥ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የመቐለ ከተማው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በአምስት ጨዋታዎች ቡድናቸውን እንዳይመሩ በፌዴሬሽኑ በመቀጣታቸው ምክንያት በነገው ጨዋታ አይገቡም።

አሰልጣኙ ክለባቸው ከ10 ቀናት በፊት ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 1ለ0 ባሸነፈበት ጨዋታ ቡድናቸውን ከሚመሩበት ክልል ወጥተው ወደ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ቦታ በመሄድ የሲዳማ ቡናውን ምክትል አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ሰድበዋል በመባሉ ነው የቅጣቱ ውሳኔ የተላለፈባቸው።

ከተጣለባቸው የጨዋታ ቅጣት በተጨማሪ አራት ሺ ብር እንዲከፍሉም ተወስኖባቸዋል።

በሌላ የሊጉ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በአርባምንጭ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይደረጋል።  

በ14ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ መርሃ ግብር ሊካሄድ የነበረው የጅማ አባ ጅፋርና የወላይታ ድቻ ጨዋታ ወደ የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ተራዝሟል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጪው እሁድ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ከደቡብ ሱዳኑ ዋኡ አልሰላም ጋር ባለበት ጨዋታ ምክንያት ከአዳማ ከተማ ጋር ሊያደርገው የነበረውም ጨዋታ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ይሆናል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመወዳደር ላይ የሚገኘው ወልዲያ ከተማ ቀሪ ጨዋታዎቹ ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፋቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

በዚህም መሰረት በ14ኛው ሳምንት ወልዲያ ከደደቢት ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል።

በ14ኛ ሳምንት መከላከያ ከሲዳማ ቡና ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ጎል ሲጠናቀቅ፤ ክልል ላይ በተደረገ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ሀዋሳ ከተማን አንድ ለባዶ አሸንፏል።

ከትናንት በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከተማን ሶስት ለሁለት ማሸነፍ ችሏል።

የፕሪሚዬር ሊጉን የደረጃ ሠንጠረዥ ደደቢት በ25 ነጥብ ሲመራ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ አዳማ ከተማና መቐለ ከተማ በተመሳሳይ 21 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከሁለት እስከ አምስት ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡

የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በዘጠኝ ጎል ሲመራ፤ ኦኪኪ አፎላቢ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክና አል ሀሰን ካሉሻ ከጅማ አባጅፋር በተመሳሳይ ሰባት ጎሎች ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።

 

 

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ጥር 28/2010 ኢትዮጵያ የ2020 የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና ቻን ውድድር ለማዘጋጀት ዓርማ ተረከበች። 

የአገር ውስጥ የሊግ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የአፍሪካ የቻን ውድድር ላለፉት ሦስት ሳምንታት ሲካሄድ ቆይቶ ትናንት መቋጫውን አግኝቷል።

አዘጋጇ ሞሮኮ ናይጄሪያን አራት ለዜሮ በማሸነፍ የ2018ቱ የአፍሪካ እግር ኳስ አገራት ሻምፒዮን ቻን ዋንጫን አንስታለች።

የዋንጫ ሽልማቱ በተሰጠበት ወቅት የአፍሪካ እግር ኳስ አገራት ሻምፒዮና ቻን በ2020 ለማስተናገድ ካፍ እድሉን የሰጣት ኢትዮጵያ የዘንድሮውን ውድድር ካዛጋጀችው ሞሮኮ እጅ አዘጋጅነቷን የሚያበስር ዓርማ ተቀብላለች።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ጁነዲን ባሻ እና የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ፀሐፊ ሠለሞን ገብረሥላሴ  በ2020 ዋንጫውን ኢትዮጵያ የምታዘጋጅበትን  ዓርማው ከአፍሪካ የእግር ኳስ ኮንፌደሬሽንና ከሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ተቀብለዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ አገሪቷ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ለመፈተሽ በቀጣይ ሁለት ወራት የተቆጣጣሪ ቡድን እንደሚልክ በጥር ወር መጀመሪያ አሳውቋል።

በመሐመድ አምስተኛ ስታዲየም በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ሞሮኮ ከጨዋታ ብልጫ ጋር በሰፊ የጎል ልዩነት በማሸነፍ አገሯ ላይ ዋንጫውን አስቀርታለች።

ሞሮኮአዊ ተጫዋች አዩብ ኤልካቢ  በአጠቃላይ በውድድሩ ያስቆጠረውን ጎል ዘጠኝ በማድረስ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ጨርሷል።

ከትናንት በስቲያ በማራካሽ ስታዲየም በተደረገው የደረጃ ጨዋታ ሱዳን ሊቢያን በመለያ ምት አራት ለሁለት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በመደበኛው 90 ደቂቃ አንድ ለአንድ የወጡት ቡድኖች በተጨማሪው ሰላሳ ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው ነው ወደ መለያ ምት ያመሩት።

የሱዳኑ ግብ ጠባቂ አክራም ኤልሀዲ ሁለት የመለያ ምቶችን በማዳን ቡድኑ ሶስተኛ ደረጃን እንዲይዝ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

በቻን ውድድር በተደረጉ 32 ጨዋታዎች 59 ግቦች መረብ ላይ ያረፉ ሲሆን በየጨዋታው በአማካይ 1 ነጥብ 8 ጎል ተቆጥሯል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ካፍ በአጠቃላይ በውድድሩ ለተሳተፉ 16 አገራት ያስመዘገቡትን ውጤት መሰረት በማድረግ የ1 ነጥብ 25 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አበርክቷል።

ኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደውን ውድድር ለማስተናገድ ከሁለት ዓመት በፊት መመረጧ ይታወሳል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ጥር 28/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ ቺካጎ ከተማ የቀጥታ በረራ አገልግሎት ሊጀምር ነው።

በረራው ከግንቦት 23 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ የሚጀምር ሲሆን፤ አፍሪካን ከቺካጎ ጋር የሚያገናኝ የመጀመሪያ በረራ እንደሆነም ተገልጿል።

ወደ ከተማዋ በረራ የሚያደርገው አውሮፕላን ቦይንግ 787 እንደሚሆን ታውቋል።

የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደገለጹት፤ በረራው ወሳኝ የሚያስብለው በአየር ትራንስፖርት ያለውን የትስስር ክፍተት በመሙላት አፍሪካንና ቺካጎን የሚያገናኝ የቀጥታ በረራ ነው።

በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በረራው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰት በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል።

በአሜሪካ የሚገኘው የስታር አሊያንስ አጋር የሆነው ዩናይትድ አየር መንገድ ወደሚገኝበት የቺካጎ ከተማ የሚጀመረው በረራ ከአየር መንገዱ ጋር በትብብር እንደሆነ አመልክተዋል።

በበረራው አማካኝነት አሜሪካንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ያሉትን ከ55 በላይ መዳረሻዎች በማስተሳሰር ተሳፋሪዎች ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙና ምርቶቻቸውን ማጓጓዝ እንደሚችሉ ነው አቶ ተወልደ ያብራሩት።

የቺካጎ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሜሪካ አራተኛው እንዲሁም በደቡብና ሰሜን አሜሪካ አህጉሮች ሰባተኛ መዳረሻው እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ኒውዮርክ፣ ዋሺንግተን ዲሲና ሎስ አንጀለስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ የሚያደርግባቸው የአሜሪካ ከተሞች ናቸው። በተጨማሪም ወደ ካናዳ ቶሮንቶና ብራዚል ሳኦፖሎ ከተሞች በረራውን ያደርጋል።

አየር መንገዱ በመጋቢት ላይ ወደአርጄንቲና ርዕሰ መዲና ቦነስ አይረስ በረራ እንደሚጀምር ከአየር መንገዱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አሜሪካ እ.አ.አ በ1998 በረራ እንደጀመረ የአየር መንገዱ የፕሬስ መግለጫ ያመለክታል።

አየር መንገዱ በአምስት አህጉሮች ከ100 በላይ የበረራና የካርጎ መደረሻዎች አሉት።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 28/2010 በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማስፈን “የአገሪቷ የፖለቲካ ኃይሎች ቁርጠኝነት ሊኖራቸው ይገባል” ሲሉ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተናገሩ።

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነትን በተመለከተ በመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ ስብሰባ እየተካሄደ ነው።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን /ኢጋድ/ አባል አገሮች የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በስብሰባው ላይ “በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከቃል በዘለለ በተግባር ቁርጠኝነትን ማሳየት ይገባል” ብለዋል።

በተለይም ደግሞ ሁሉም የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች እውነተኛ የሆነና ጠንካራ ቁርጠኝነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው የገለጹት።

እነዚህ ቡድኖች አልያም ደግሞ አባሎቻቸው የጠራ ግብና ፖለቲካዊ ፍቃደኝነት በማሳየት ለፈጠሩት ችግሮች አፋጣኝ እልባት መስጠት እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት።

በዚህም ደግሞ ሁሉም የሚመለከተው አካላት በአገሪቷ የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ በሚሆንበት አግባብ ላይ የራሱን አዎንታዊ ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።

ይህንንም ለማድረግ ደግሞ አገሪቷ አሁን ላይ ሰላም በማጣት እየደረሰባት ያለውን ችግርና የአገሪቷን ጥቅም ከግምት ማስገባት ሁነኛ መፍትሄው መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህም በአገሪቷ የጋራ ጥቅምን ሊያመጣ የሚችል መፍትሄ ላይ ለመረባረብ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ለአስር ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስብሰባ በደቡብ ሱዳን ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ላይ በስፋት ይመክራል ተብሏል።

ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ ውሳኔ የተላለፈበትን የተኩስ አቁም ስምምነት ዳግም ተግባራዊ ሊሆን በሚችልበት ጉዳይ ላይ ምክክር ይደረጋልም ነው የተባለው።

በተመሳሳይ የደቡብ ሱዳን ሽግግር መንግሥት ማብቂያን ተከትሎ ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድም የተወሰነው ውሳኔ ላይም ውይይት ይደረጋል።

Published in ፖለቲካ

ጥር 27/2010 የሃገሪቱን የቱሪዝም ሃብቶችና እያደገ የመጣውን የሆቴል ኢንደስትሪ ይበልጥ በማስተዋወቅ የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነቷን ማሳደግ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎች የስራ ሃላፊዎች ተናገሩ፡፡

የራዲሰን ብሉ ዓለም አቀፍ ሆቴል ማርኬቲንግና ኮምዩኒኬሽን ማናጀር አቶ ሚካኤል ግርማ እንደተናገሩት ለ30ኛው የህብረቱ ጉባዔ የሆቴሉ 212 ክፍሎች በጉባኤው ታዳሚዎች አስቀድመው ተይዘው ነበር፡፡

ይህን መሰሉ አገልግሎት ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የምታገኝበትን መልካም አጋጣሚ ይዞ እንደሚመጣ ገልጸው የሆቴሉ ሰራተኞችም ዳጎስ ያለ የአገልግሎት ክፍያ ማግኘታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

አቶ ሚካኤል እንዳሉት ሆቴሉ የአምስት ሃገራት መሪዎችንና  ሌሎች ታዳሚዎችን ያስተናገደ ሲሆን ለእንግዶቹ የሀገሪቱን አመጋገብ፣ አልባሳትና ጌጣጌጦች የማስተዋወቅ ስራ ሰርቷል፡፡

የሆቴሎች አገልግሎት በአመታዊ ጉባኤ  ብቻ ጥገኛ መሆን እንደሌለበት ገልፀው የሃገሪቱን የኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ለማሳደግ እንደ ናይሮቢና ሩዋንዳ የኮንቬንሽን ማዕከላት አገልግሎቶች ሊኖሩ ይገባልም ብለዋል፡፡

የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል የፋይናንስ ዳይሬክተሩ አቶ ኢሳኢያስ ግደይ በበኩላቸው ጉባኤው ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣም መፍጠሩን ገልፀዋል ፡፡

ለሆቴሉ እንግዶች ከተማዋን የማስጎብኘት፣ የሬስቶራንት ቅኝትና ከስብሰባ መልስም የሙዚቃ ዝግጅት እንደነበር ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

“ጉባኤው የዓለም ዐይን ወደ አዲስ አበባ እንዲያተኩር በማድረግ ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ለኢንቨስትመንት መንሸራሸር መልካም አጋጣሚ” ይፈጥራልም ነው ያሉት፡፡

ኤምባሲዎች ፣ ቆንስላዎችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሃገሪቱ መሰል ዓለም ዓቀፍ ጉባዔዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳላት የማስተዋወቅ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ከ90 በመቶ በላይ ደንበኞቻቸው የውጪ ሃገራት ዜጎች በመሆናቸው መገኛኛ ብዙሃን የሃገሩቱን በጎ ገፅታ የማስተዋወቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

በኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና የውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር  አቶ ገዛኸኝ አባተ እንዳሉት ሃገሪቱ እያመዘገበች ያለው የኢኮኖሚ  እድገት ለባህልና ቱሪዝሙ እድገት በጎ አስተዋፅ አለው፡፡

“አሁን ዲፕሎማቶቻችን የባህል ዲፕሎማሲ ላይ ልዩ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ነው” ያሉት አቶ ገዛኸኝ በስራቸው ስኬታማ የነበሩ ዲፕሎማቶች እውቅና እንደተሰጣቸውም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመስተንግዶም ይሁን ከፀጥታ አኳያ በስኬት የተወጣችው የህብረቱ ጉባኤም ሌሎች ድርጅቶች ጉባዔዎቻቸውን  ወደ ሃገሪቱ እንዲያመጡ በር የሚከፍት መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት ጋር በመወዳደር የአፍሪካ የቱሪዝም ምክርቤትንና   የዩኔስኮን የማይዳሰሱ ቅርሶች ጉባኤ ጨምሮ ሌሎች የፖስታ፣ የአይ ሲ ቲ ፣ የንግድና የቡና ጉባኤዎችን ማስተናገዷን ገልጸው ይህም የሀገሪቱ ከንፈረንስ ቱሪዝም እያደገ ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን