አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 03 February 2018

አዲስ አበባ  ጥር 26/2010 በአዲስ አበባ ለልማት ተነሺዎች በሚል በመጠባበቂያነት የተቀመጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህገወጦች እየተሰበሩ ለሌላ አገልግሎት እየዋሉ ነው።

በአዲስ አበባ የካቲት 2008  በተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቆጠራ ከተለዩ 102 ሺህ 331 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ 90 ቤቶች ተሰብረው ግለሰቦች በህገ ወጥ መልኩ ይኖሩባቸው እንደነበር መረጋገጡ ይታወሳል።

ኢዜአ ችግሩ ከሁለት ዓመት በኋላ ተፈቷል አልተፈታም የሚለውን ለመለየት በከተማዋ የጋራ መኖሪያ ቤት ከተገነባባቸው አካባቢዎች መካከል በተወሰኑት ላይ ምልከታ አካሂዷል።

በዚህም በሰሚት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከስቱዲዮ እስከ ባለሶሰት መኝታ ቤቶች ላለፉት አራት አመታት አሁንም ክፍት ሆነው እንደቆዩ ባደረግነው ምልከታ አረጋግጠናል።

እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና ሱቆች ተሰብረው ህገወጦች ሲገለገሉባቸውና አልባሌ ተግባራት ሲፈጸምባቸው ከማየት ባለፈ የቆሻሻና የሌሎች ቁሳቁሶች ማጠራቀሚያ ሆነው ቆይተዋል።

በአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ የጋራ መኖሪያ ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ልሳነወርቅ ከልለው ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ምላሽ ለልማት ተነሺዎች ተብለው በተጠባባቂነት ክፍት ሆነው የሚቆዩ ቤቶች አሉ።

ነገር ግን ለእነዚህ ቤቶች የሚደረግላቸው ጥበቃ በቂ ነው ብለው እንደማያስቡ ገልጸው፤ ይህም በአስተዳደሩ ብቻ  የሚፈጸም አለመሆኑንና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

''እያንዳንዱን ክፍት ቤት የምንቆጣጠርበት ዘመናዊ አሰራር አለን ማለት አይቻልም'' ያሉት አቶ ልሳነወርቅ የጋራ መኖሪያ ቤቱን በቅርበት ከሚያውቋቸው ኮሚቴዎች ጋር በመሆን ቤቶቹን እንዲቆጣጠሩ አሰራር እየተፈጠረ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በተደረገው ቆጠራ ከተገኙት ከፍት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ለመምህራን የተላለፉ ሲሆን አሁንም ለልማት ተነሺዎች የተያዙና ጨረታ ወጥቶባቸው ሰው ሳይወዳደርባቸው የቀሩ ሱቆች አሉ።

ለልማት ተነሺዎች የሚሰጡት ቤቶች በቁጥር ደረጃ ምን ያህል ናቸው? ብለን ለጠየቀናቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ''ዛሬ ላይ የተናገርነው ለነገ አያገለግልም በየጊዜው ቁጥሩ ይለዋወጣል'' ብለዋል።

ኤጀንሲው ለህብረተሰቡ ሳይተላለፉ የቀሩና በመጠባበቂያነት ለልማት ተነሺዎች የተያዙ ክፍት ቤቶችን የማስተዳደር ሃላፊነት በአዋጅ እንደተሰጠው ይታወቃል።

 

Published in ኢኮኖሚ

መቱ ጥር 26/2010 ከቡና በተጓዳኝ ከሚያለሙት የሻይ ተክል ምርት ሽያጭ የገቢ አቅማቸው እያደገ መምጣቱን በኢሉአባቦር ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የአሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ ።

በወረዳው 159 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ በሻይ ተክል መሸፈኑ ተመልክቷል።

በወረዳው በሻይ ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት ከምርት ሽያጭ እያገኙት ያለው ተጨማሪ ገቢ  በኑሯቸው ላይ የተሻለ ለውጥ እንዲያመጡ አግዟቸዋል ።

በወረዳው ኦንጋ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አለም ገላዬ እንዳሉት በመደበኛት ከሚያመርቱት ቡና በተጓዷኝ ከሁለት ሄክታር በሚበልጥ መሬት የሻይ ተክል እያለሙ ነው ።

የጉመሮ ሻይ ልማት የምርት ማሳደጊያ በብድር በማቅረብና በባለሙያ ምክር በመስጠት በሚያደርግላቸው የቅርብ ድጋፍ በመታገዝ ልማቱን እያካሄዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል ።

"ድርጅቱ የማለማውን የሻይ ምርት ስለሚረከበኝ የገበያ ችግር የለብኝም " ያሉት አርሶ አደር አለም፣ አንዱን ኪሎ ግራም የሀገር ውስጥ ሻይ በሦስት ብር ከ50 ሣንቲም የውጭውን ደግሞ በአራት ብር ከ10 ሣንቲም ሒሳብ እየተረከባቸው መሆኑን ተናግረዋል ።

"በየአመቱ ከሻይ ምርት ሽያጭ ከ80 ሺህ ብር በላይ ገቢ አገኛለሁ፤ ገበዬ እያደገ በመመጣቱ ይስራ መስኬን በማስፋት በንግድ መስክ ተሰማርቻለሁ " ሲሉ በኑሯቸው ላይ የተሻለ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልፀዋል ።

ከአራት ዓመታት ወዲህ አምስት ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ በሻይ ተክል ልማት ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸው አየተለወጠ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በወረዳው የጉመሮ አቦ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር እንዳለ ብርሀኑ ናቸው፡፡

በዞኑ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን የሻይና ቅመማ ቅመም ልማት ባለሙያ አቶ ቡላ ገብሬ በበኩላቸው በወረዳው 234 ቡና አምራች አርሶ አደሮች በተጓዳኝ በሻይ ተክል ልማት ሥራ እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

"በሻይ ተክል ልማት ከተሸፈነው 159 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ውስጥ 110 ሄክታሩ ምርት እየሰጠ ነው " ብለዋል።

ተሳታፊ አርሶ አደሮች ባለፈው ዓመት ያገኙትን 153 ሺህ ኩንታል የሻይ ምርት ለጉመሮ ሻይ ልማት ድርጅት አቅርበው ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውንም አስታውሰዋል።

እንደ ባለሙያው ገለፃ በአርሶ አደሩ ደረጃ የተጀመረውን የሻይ ተክል ልማት በማስፋፋት ተጠቃሚነቱን የማሳደግ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ጥር 26/2010 በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ልባዊ ሃዘን እንደተሰማው የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት አስታወቀ።

ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ ተከስቶ በነበረው ግጭት የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉንም አመልክቷል።

በመግለጫው እደተገለጸው፣ በአማራ ክልል የህዝቦችን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ባለፉት ዓመታት ብርቱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱንና በዚህም የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል።

ይሁን እንጂ እያደገ የመጣውን የህዝቡን የልማት ፍላጎት መሰረት ተደርጎ በየወቅቱ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ፈጥኖ መመለስ ባለመቻሉ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ግጭት እየተገባና ይህም ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።

ከእርካታ እጦት እየተከሰቱ ባሉ ቅሬታዎችና ብሶቶች የተፈጠረው ግጭትም የክልሉን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ግስጋሴ ፈተና ውስጥ መጣሉን መግለጫው አስታውቋል።

በቅርቡ በወልዲያ፣ ቆቦና መርሳ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭትም በ13 የአካባቢው ነዋሪዎችና በሁለት የፀጥታ ኃይሎች ላይ የሞት አደጋ አድርሶ ማለፉን ጠቅሷል።

ምክር ቤቱ በጠፋው ውድና የማይተካ የሰው ሕይወት ጥልቅ ሃዘን የተሰማው መሆኑን ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ይመኛል ብሏል መግለጫው።

ህዝቡን በማስከፋት ለቅሬታ ያበቁትን የልማትም ሆነ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አትቷል።

ምክር ቤቱ ያወጣው መግለጫ አያይዞ እንደገለጸው፣ ተከስቶ የነበረውን አለመረጋጋት ወደነበረበት ለመመለስ በተሰራው ሥራ ከሰላም ፈላጊው ህዝብ፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከወጣቶች ጋር በመተባበር አንፃራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል።

በግጭቶቹ የሰው ሕይወት ከማጥፋትና ንብረት ማውደም በዘለለ በህዝቦች መካከል ለዘመናት ፀንቶ የኖረ አብሮነትንና አንድነትን የሚንዱ ድርጊቶች መስተዋላቸውንም መግለጫው አመልክቷል።ክስተቶቹ በምንም መንገድ የአካባቢውን ህዝቦች የማይወክሉ ተግባር ናቸው።

በዚህ ጥፋት ለህዝብ ጥቅም የተገነቡና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ የመንግስት ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ሁሉም ውድመቶች ሊከሰቱ የማይገቡ አሳፋሪ ድርጊቶች ናቸው፡፡

ግጭቱ የህግ የበላይነትን ከመጣሱ ባለፈ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ሕይወት አናግቷል፤ በተወሰኑ አካባቢዎች ስጋትና ውጥረት እንዲነግስ ማድረጉንም መግለጫው አትቷል።

"የአማራ ክልል ሕዝቦች እርስ በእርሳቸውም ሆነ ከሌሎች የሀገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር አኩሪ ባህልና ጥብቅ ትስስር ያላቸውም ናቸው" ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው።

በቀጣይም መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ የክልሉ መንግስት አጥብቆ አንደሚሰራና በግጭቱ በቀጥታ ተሳታፊ የነበሩ አካላትም በቀጣይ በህግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ መስተዳደር ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ አብራርቷል።

የምክር ቤቱ ሙሉ መግለጫ ከእዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርቧል-

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት የደረሰውን ጥፋት አስመልክቶ ከክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት (ካብኔ) የተሰጠ መግለጫ

በክልላችን ሁለተናዊ ልማት ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የህዝቡን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ዘርፈ ብዙ ተግባር በመንግስትና በመላው ህብረተሰብ የተቀናጀ ጥረት ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የሀገራችንንም ሆነ የክልላችንን ተስፋ ያለመለሙ ለውጦችና ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይህም ውጤት ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት የራሱን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ መጥቷል፡፡ በቀጣይነትም ይህንኑ የህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግና ለማስፋት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው በመንግስት በኩል የህዝቡን እርካታ በሚፈለገው መጠን ያለማረጋገጥ ድክመቶች እየተፈታተኑን ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የህብረተሰቡ እርካታ እጦት ፣ ቅሬታ እና ብሶት ወደ ግጭት እያመራ ዋጋ እያሰከፈለን ይገኛል፡፡

ሰፊው የክልላችን ህዝብ የአገራችን ህገ-መንግስታዊ ስርዓት በፈቀደለት መሠረት ከኋላ ቀርነት ተላቆ ከድህነት ለመውጣት በትጋት በሚረባረብበት በአሁኑ ወቅት ይህንኑ ሰላማዊ እንቅስቃሴውንና የማህበረ ኢኮኖሚያዊ ልማት ግስጋሴውን የሚገቱ ፈተናዎች እየተደቀኑበት ነው፡፡ ሰሞኑን በክልላችን በተለይም በወልዲያና አካባቢዉ የተከሰተው የፀጥታ መደፍረስና የሠላም መናጋት የክልሉን መስተዳድር ምክር ቤት በእጅጉ አሳስቦታል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ወልዲያ ከተማ ቀደም ሲል በወልዲያ እና በመቀሌ ከተማ የእግር ኳስ ደጋፊዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም የቃና ዘገሊላ በዓል በሚከበርበት ዕለት በበአሉ ታዳሚዎችና በህግ አስከባሪ አካላት መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት ውድመት የተከሰተ ሲሆን ውሎ ሲያድርም ግጭቱ በቆቦ እና መርሳ ከተሞች የቀጠለ በመሆኑ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ አልፏል፡፡ ከሁሉም በላይ በወልዲያ፣በቆቦና በመርሳ ከተሞች ነዋሪዎች 13 ፤ ከፀጥታ ሃይሉ 2 በድምሩ የ15 ወገኖቻችን ህይወት ማለፉ ከፍተኛ ሃዘንና ቁጭት ፈጥሮብናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ መስተዳድር ምክር ቤቱ ከሁሉ አስቀድሞ በጠፋው ውድና መተኪያ የሌለው የሰው ህይወት ከልብ የተሰማውን ጥልቅና መሪር ሃዘን እየገለፀ ለተጐጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ይመኛል፡፡

የተከሰቱ ግጭቶች መሠረታዊ መነሻ ምክንያቶቻቸው የህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎች እንዲሁም ቅሬታዎችና ብሶቶች መደማመርና ሳይፈቱ መዋል ማደራቸው ሲሆን በየደረጃው ተገቢውን ምላሽ በወቅቱ ካለመስጠት ጋር የተያያዙም ናቸው፡፡ የክልሉ መንግስት በአሁኑ ወቅት እነዚህን ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ከምንጊዜውም በላይ ጥረት እየደረገና በትኩረት እየጠሰራ ይገኛል፡፡

የክልሉ መንግስት በወልዲያ ከተማ ጉዳቱ ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ በልዩ ትኩረት በርዕሰ መስተዳድሩ መሪነት በቦታው በመገኘት ቅድሚያ የዜጐችን ህይወት ለመታደግና ግጭቱን ለማስቆም ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በጋራ ተረባርቧል፡፡ በዚህም የህብረተሰቡ ቀና እና አስተዋይነት የተሞላበት ተሳትፎ ተጨምሮበት አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ ክስተት ከጥፋት ውጪ የሚገኝ አንዳችም ትርፍ ካለመኖሩም በላይ አንዳንዶቹ የግጭት አዝማሚያዎች የህዝቦችን ፀንቶ የኖረ አብሮነትንና አንድነትን በሚጐዳ መልኩ የተከሰቱ መሆናቸውና የመንግስት ተቋማትና የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች እና ድርጅቶች ላይ ያነጣጠረ መሆኑ የዜጐች ሀብትና ንብረት በአጭር ጊዜ እንዲወድም አድርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ክስተት ግን በምንም መንገድ ቢሆን ግጭቱ የተከሰተባቸውን የአካባቢ ህዝቦች የማይወክል ተግባር ነው፡፡

በዚህ ጥፋት ለህዝብ ጥቅም የተገነቡና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ የመንግስት ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ ሁሉም ውድመቶች በዚህ ዘመን ሊታዩ የማይገቡ አሳፋሪ ድርጊቶች ናቸው፡፡ ግጭቱ የህግ የበላይነትን ከመጣሱ የተነሳ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ህይወት አናግቷል፤ ስጋትና ውጥረት እንዲነግስ አድርጓል፡፡

የአማራ ክልል ህዝቦች እርስ በርሳቸውም ሆነ ከሁሉም የአገራችን ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር አኩሪ ባህልና ጥብቅ የሆነ ትስስርንና አብሮነትን ጠብቀው መኖርን የሚያውቁና በዚህም የሚገለፅ ማንነት ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ የእነዚህ እሴቶች ባለቤት የሆኑት የወልዲያና አካባቢው ነዋሪዎችም ግጭቶቹ ከተከሰቱ በኋላ በአካባቢው የህግ ጥሰትና ስርዓት አልበኝነት በመንገሱ የራሳቸውም ሆነ የመንግስት ሃብትና ንብረት ከዘረፋና ከጥፋት እንዲድን እንዲደረግ ለመንግስት ጥሪ ከማቅረባቸውም ባለፈ በሚችሉት አቅም ሁሉ የተጎዱትን ወገኖች በመደገፍና ከፖሊስ ጎን ሆነው ፀጥታውን በማስከበርና አጥፊዎችን ለህግ እንዲቀርቡ በመተባባር ላይ ናቸው፡፡

ከዚህ ሌላ በአካባቢው ግጭት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በቦታው በመገኘት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በማወያየት ችግሮች በውይይትና በጋራ የሚፈቱ መሆናቸውን በመተማመን በአካባቢው የተፈጠረው ሁከት በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶችና በመላ ህብረተሰቡ ትብብር ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ የማድረግ ሥራ በመሰራት ላይ ነው፡፡ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በሰላም እና የህግ የበላይነት ጉዳይ ላይ መተማመን በመጀመሩ በአሁኑ ጊዜ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ለህግ እየቀረቡ ከተሞቹም ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ መግባት የጀመሩ ሲሆን መንገዶችም ተከፍተው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡

የክልሉ መስተዳደር ምክር ቤት በተሻሻለው የብሄራዊ ክልሉ ህገ መንግስት አንቀፅ 56 ንዑሱ አንቀፅ (1) መሠረት የክልሉ ከፍተኛ አስፈፃሚ እና አስተዳደራዊ አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡ የህገ መንግስቱ አንቀፅ 58 ንዑስ አንቀፅ (6) እንደሚደነግገው መስተዳድር ምክር ቤቱ በክልሉ ውስጥ ህግና ስርዓት መከበሩን የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት ያለውን ወቅታዊ አቋም እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-

============================================

  1. በወልዲያ ከተማ ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሃይማኖት ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት የተፈፀመውን ድርጊት በሚመለከት ምንም እንኳን አንዳንድ ቡድኖች የሀይማኖቱ ስርዓት በማይፈቅደው መልኩ ተንኳሽ ተግባራት መፈፀማቸው ስህተት መሆኑን ብናምንም ፤ መነሻው ምንም ይሁን ምን የተፈፀመው የሰው ግድያም ሆነ በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የተደረገ ተኩስ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት በሚካሄድበት እና ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅትና ቦታ ፀጥታ ያደፈረሱም ይሁን በስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች ላይ ጥይት የተኮሱ፣ ሰው የገደሉ፣ ልዩ ልዩ ጉዳት ያደረሱ አካላት ጉዳዩ በዝርዝር ተጣርቶ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡
  1. ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም በወልዲያ ከተማ የደረሰውን ጉዳት መቃወምና በመሰለው መንገድ ማውገዝ ህገ-መንግስታዊ መብት ቢሆንም ይህንን በወልዲያ ከተማ የተፈጠረውን ግጭት በምክንያትነት በመጠቀም በዕለቱም ሆነ በተከታዮቹ ቀናት ዜጎች በያዙት አመለካከትም ሆነ ማንነታቸው ላይ በመመስረት የደረሰው ጥቃት ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ተግባር በመሆኑ የሰው ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ኢንቨስትመት እንዲወድም ፣ የግለሰቦችና የመንግስት ሃብትና ንብረት እንዲቃጠል፣ እንዲዘረፍና በልዩ ልዩ መንገድ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ፣ በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያስተባበሩም ሆነ የተሳተፉ በህግ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ በግጭቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ክህብረትሰቡ ጋር በመተባበር እንዲቋቋሙ ይደረጋል፡፡
  1. በህብረተሰቡ የተነሱ በአመራር አካላት፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በፍትሃዊ ተጠቃሚት የሚገለፁ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በዝርዝር ተለይተው በቅደም ተከተል የህብረተሰቡን ተሳትፎ ባረጋገጠ አኳኋን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡
  2. በወልዲያና በአካባቢው የተፈጠረው ግጭት ያደረሰው ጉዳት አሁን ከደረሰው በላይ እንዳይሆንና አድማሱን እንዳያሰፋ የፀጥታ ሃይሎች ያደረጉት ርብርብ የሚያስመሰግናቸው ሲሆን በታጋሽነትና በወገናዊነት ስሜት፣ የፀጥታውን ችግር ለመቅረፍ ለከፈሉት መስዋዕትንት እና ላደረጉት መልካም እንቅስቃሴ መስተዳደር ምክር ቤቱ ላቅ ያለ ምስጋናውን ይገልፃል፡፡
  1. በወልዲያ፣ በቆቦ፣ በመርሳና በእነዚህ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ በተለይም የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ያሳዩት ርብርብ አክብሮታችን ላቅ ያለ መሆኑን እየገለፅን በቀጣይም ህብረተሰቡን ሠላሙን ለማስከበርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እንደተለመደው ሁሉ ከክልሉ የፖሊስና የፀጥታና ሃይል ጐን ተሰልፎ እንዲንቀሳቀስ የክልሉ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በቀጣይም መንግስት የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ እና ሃብት፣ ንብረት ያወደሙ ማናቸውንም ወገን መረጃ ላይ ተመስርቶ ከክልሉ በተወከሉ ሙያተኞችና አመራራሮች ደረጃ እያጣራ በመሆኑ ይህ እንደተጠናቀቀ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድና ይህንን በግልጽ ለህብረተሰቡ የሚሣውቅ መሆኑን ሲያረገግጥ የህብረተሰቡንም ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አጥብቆ እንደሚሠራ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡

በመሆኑም ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብም በየአካባቢው ከልማት ሥራው ሳይቋረጥ በአብሮነት መንፈስ የሰላም ባለቤትነት ተግባሩን ለአፍታም ቢሆን ሳይዘነጋ ከፀጥታ ሃይሉ ጐን በመቆም ሰላም ለማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ በቀጣይነት እንዲወጣ አበክሮ ያሳስባል፡፡

ጥር 25 ቀን 2010 ዓ.ም

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳደር ምክር ቤት

 

Published in ፖለቲካ

አዲሰ አበባ ጥር 26/2010 የማታ ትምህርትን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለማስቀጠል መንግስት ፈጣን መፍትሔ እንዲያስቀምጥ መምህራን ጠየቁ።

ለማታ ክፍለ ጊዜ መምህራን የሚከፈለው ክፍያና በሱም ላይ የተጣለው ግብር አለመመጣጠን ደግሞ መምህራኑ በዋናነት የሚያነሱት ችግር ነው።

የማታ ትምህርት  በቀኑ መርሃ ግብር የሚሰጠውን ትምህርት መከታተል ላልቻሉ ዜጎች በአማራጭነት እውቀት እንዲገበዩ እድል የሚሰጥ በመሆኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ትምህርት ቤቶችና አካባቢዎች ሲሰራበት መቆየቱ ይታወሳል።

ይሕ ደግሞ መንግሰት ለሁሉም ዜጎች በተለይ የመጀመሪያ ትምህርትን ለማስፋፋትና ተደራሽ ለማድረግ ያቀደውን ግብ ከሚያሳካበት መንገድ አንዱ ሲሆን በርካታ ዜጎችም ራሳቸውን እንዲለውጡ የሚያስችል ነው።

ነገር ግን በአገሪቱ በተለይ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በማታው መርሃ ግብር የሚሰጠውን ትምህርት አስመልክቶ ምንም አይነት መመሪያና ደንብ እንደሌለ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተያዘው ዓመት በተለይም በአዲስ አበባ በርካታ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የማታ ትምህርት  መስጠት አቁመዋል፤ ቀሪዎቹም በመጪው ዓመት መርሃ ግብሩን ለማስቀጠል እንደሚያዳግታቸው ነው የሚገልጹት።

ከዚህ ውስጥም የበሻሌ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ ዜና ተፈሪ እንደሚሉት የማታ ትምህርት ደመወዝ  ላይ ተደራራቢ ግብር በመጣሉ ሳቢያ ትምህርቱን ማስቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

ችግሩን መንግስት መፍትሔ ካልሰጠው የማታ ትምህርት በአጠቃላይ ወደ መቆሙ እየሔደ ነው ያሉት ርእሰ መምህሩ፤ በአሁኑ ወቅት መምህራኑ እያስተማሩ ያሉት በፈቃደኝነት እንጂ በተጠቃሚነት መንፈስ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

በዚሁ ትምህርት ቤት ለበርካታ አመታት በሒሳብ መምህርነት የቆዩት መምህር ጌታቸው ተክሌ የማታ ትምህርት በተለይ ቀን መማር የማይችሉ ዜጎች በዝቅተኛ ክፍያ እውቀት የሚገበዩበትና እራሳቸውን የሚያሻሽሉበት መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚከፈለው ክፍያ ግን አነስተኛ ነው ይላሉ።

በዚህ ትምህርት ቤት በአሁኑ ወቅት በማታው መርሃ ግብር የሚያስተምሩ መምህራን በመታጣቱ ከሌሎች ትምህርት ቤቶች እንዲመጡ እየተደረገ ሲሆን እነዚህም ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር ቀጥተኛ ሙያ የሌላቸው ናቸው። ይህም ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ተግዳሮት እንደሆነ ነው የሚገልጹት።

የዶክተር ሐዲስ አለማሁ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርእሰ መምህር አቶ አለማየሁ ገሰሰ በበኩላቸው የማታ ትምህርት ፕሮግራም ላይ የሚጣለው ግብር ከደመዋዛቸው ጋር ተደምሮ ከፍተኛ በመሆኑ መምህራን ለማስተማር ፍላጎት እንዲያጡ እያደረገ ነው ይላሉ።

የማታ ትምህርት ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ባልተናነሰ መንገድ መሰጠት ቢኖርበትም በአሁኑ ወቅት በክፍያው ዝቅተኛነት ምክንያት ከድካም ውጭ ትርፍ ስለሌለው ለማስተማር ፍላጎት የለንም የሚሉት የዚሁ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር አሰበ ጥላሁን ናቸው።

የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ በበኩላቸው እንደ ሀገር የማታ ትምህርት ትልቅ ስጋት ውስጥ የወደቀ ዘርፍ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ማህበሩ ያለው የተደራራቢ ግብር ጉዳይ እንዲፈታ ለማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጀምሮ በየደረጃው ያሉና የሚመለከታቸው አካላት መፍትሔ እንዲሰጡ ማሳወቁን ነው የገለጹት።

ችግሩ በአዲስ አበባ ብቻም ሳይሆን በመላው አገሪቱ የሚታይ በመሆኑ ተግዳሮቶቹን ለመፍታት መንግስት መፍትሔ ማስቀመጥ ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።

የማታ ትምህርትን አስመልክቶ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን ለማወቅ ኢዜአ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮን ለማነጋገር ያደረግው ተደጋጋሚ ጥረት  አልተሳካም።

Published in ማህበራዊ

ጭሮ ጥር 26/2010 ያላቸውን ልምድና ክህሎት ተጠቅመው በመስራት ኑሮቸውን ለመቀየር ቢፈለጉም በድጋፍ ማጣት እንዳልቻሉ  በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ  ከስደት የተመለሱ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከተመላሾች መካከል ወጣት አህመድ አሊዩ ለኢዜአ እንዳለው ከጓደኞቹ ጋር ሳዑዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ በመውጣት ያሳለፉት ህይወት ስቃይ የበዛበት ነበር፡፡

በሳዑዲ አረቢያ ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ያለምንም ጥሪት መንግስት ባደረገለት ድጋፍ ባለፈው ዓመት ወደሀገሩ መመለሱን ተናግሯል፡፡

" ከመጣን በኋላ ባለን ክህሎትና ባካበትነው ልምድ ተደራጅተን እንደምንሰራና ድጋፍ እንደሚደረግልን ቃል ሲገባልን ተስፋ አድርገን ነበር፤ ሆኖም የተመቻቸ ድጋፍ  ባለመኖሩ መቸገራቸውን ነው ወጣቱ የገለጸው፡፡

ወይዘሮ አሊፋ ሼህ አደም የተባሉት ከሰደት ተመላሽ በሰጡት አስተያየት ከሶስት ዓመት በላይ የአረብ ሀገር  ቆይተው በመንግስት ድጋፍ ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ የሰሩትንና የለፉበትን ጥሪት እንኳን ሳይወስዱ ባዶ እጃቸውን እንደተመለሱ ተናግረዋል፡፡

" የተሻላ ነገር አገኛለሁ ብዬ ሶስት ልጆቼን በትኜ በእጄ ያለኝንም ጨርሼ ተመለስኩ ፤ነገር ግን እንደመጣን   ትደራጃላችሁ ፤ የመስሪያ ቦታ ይሰጣችኋል፤ የገንዘብ ድጋፍም ይደረግላችኋል ስንባል ሰርቼ እቀየራለው ብዬ ተስፋ ባደርግም ላለፉት አስር ወራት ምንም የተደረገልን ነገር የለም" ብለዋል፡፡

ከጓደኞቹ ጋር በ2004 እያንዳንዳቸው ለደላላ 30 ሺህ ብር ከፍለው በጅቡቲ በኩል  ሳዑዲ አረቢያ እንደገቡ የተናገረው ደግሞ ወጣት ናሲር አብደላ ነው፡፡

" እንደተመለስን 1 ሺህ 800 ብር ተሰጥቶን ለወደፊት ድጋፍ ይደረግላችኋል ተብለን ተመዘግበን ነበር ነገር ግን በዛው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ"  ብለዋል፡፡

የዞኑ  የሥራ እድል ፈጠራና የከተሞች ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ህሊና መካ ለቅሬታዎቹ በሰጡት ምላሽ በምዕራብ ሐረርጌ ከሚገኙት 751 ከስደት ተመላሾች መካከል ለ265 የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡

የስራ እድል ለተፈጠረላቸውም  በ53 ማህበራት በማደራጀትም ከ450ሺ ብር በላይ የብድር ገንዘብና የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በከተማ ደረጃ  በቂ የሆነ የማምረቻና የመሸጫና ቦታ አለማመቻቸታቸው እንዲሁም በገጠር ደግሞ በተለያየ የልማት ስራ የለማውን መሬት ለወጣቶቹ ለማስተላለፍ አንዳንድ አመራሮች  ፍቃደኛ አለመሆን ሁሉንም ተመላሸች ወደ ስራ ለማስገባት እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው ኃላፊው የተናገሩት ፡፡

ከስደት  ተመላሾቹ ጥቂት የማይባሉት በከተማ ነው መስራት ያለብን የሚል አመለካከትና ሥራን የመናቅ ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው አሁን ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት   ችግሩን ለመፍታት  እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጎባ ጥር26/2010 ከአምስት ዓመታት በፊት የግንባታ ሥራው የተጀመረው የ "ወቾ " ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በመጓተቱ መቸገራቸውን በባሌ ዞን የሲናና ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ ፡፡

የዞኑ የመስኖ ልማት ባለስልጣን በበኩሉ በችግሩ  ውስጥ እጃቸው ያለበትን አካላት ለህግ አቅርቦ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል ፡፡

በወረዳው የወልተኢ ወቾ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ በከር እንደገለጹት ከዚህ በፊት በአካባቢያቸው የሚፈሰውን የ”ቶጎና”ን ወንዝ በመጥለፍ በበህላዊ መልኩ ከሚያለሙት የመስኖ እርሻ አትክልትና ፍራፍሬ ሽያጭ በአንድ ዙር እስከ 15 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ አስታውሰዋል፡፡

መንግስት በ2004 ዓ.ም በበህላዊ መልኩ የሚጠቀሙትን መስኖ ወደ ዘመናዊ በመቀየር የተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥርና ተጠቃሚነት እጨምራለሁ በሚል የጀመረው ፕሮጀክት ሳይጠናቀቅ እስከዛሬ መጓተቱን ተናግረዋል ፡፡

"በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቃቃል የተባለው የመስኖ ፕሮጀክት በወቅቱ ባለመጠናቀቁ የተነሳ በበህላዊ መንገድ እንጠቀም የነበረውን መስኖ አሳጥቶናል" ሲሉም ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል ፡፡ 

ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ጄይላን ኡስማን በበኩላቸው "ፕሮጀክቱ መጓተቱ ብቻ  ሳይሆን አሁንም ድረስ ተስፋ የሚሰጥ የመፍትሄ ሀሳብ አለመኖሩ አሳዛኝ" ነው ብለዋል ፡፡

መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ ምልሽ እንዲሰጠን እንፈልጋለን ሲሉም ጠይቀዋል።

ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ መንግስት በተለያዩ ቦታዎች የሕብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግርና መንስኤዎችን በመፍታት ምላሽ እየሰጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት ይህ ፕሮጀክት ከነችግሩ ዘመናትን መሻገሩ አግባብ አይደለም ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ መሐመድ ሀሰን ናቸው፡፡

ጉዳዩ የሚመለከታቸው በየደራጃው የሚገኙ የመንግስት አካላት ችግራችንን ሊፈቱልን ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የሲናና ወረዳ መስኖ ልማት ባለስልጣን ኃላፊ ተወካይ አቶ ከበደ ደጀኔ ሕብረተሰቡ የሚያነሳው ቅሬታ አግባብነት እንዳለው አምነው የፕሮጀክቱ የግንባታ ጨረታ በዞን ደረጃ መሰጠቱ ችግሩን በወረዳ ደረጃ ለመፍታት እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል ፡፡

ተወካዩ እንዳሉት ከ50 ሄክታር በላይ መሬት በባህላዊ መንገድ ሲያለማ የነበረው መስኖ በዘመናዊ መልኩ በማሰደግ ከ100 ሄክታር በላይ እንዲያለማ ታስቦ  የ"ወቾ " መስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ ተጀምሯል።

ፕሮጀክቱ እስካሁን ባለመጠናቀቁ የአካባቢው ማህበረሰብ እንደ ትልቅ የመልካም አስተዳደር ችግር በየጊዜው እያነሳው መሆኑን ለዞንና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ ጊዜያት ቢያሳውቁም ምላሽ አለማግኘታቸውን አስረድተዋል ፡፡  

የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ሙዘየን አቡበከር በበኩላቸው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሕብረተሰቡ የሚያነሰው ቅሬታ አግባብ መሆኑን ገልጸዋል።

በወቅቱ የነበሩ የሥራ ኃላፊዎች ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሳይጠናቀቅ ለፕሮጀክቱ የተያዘውን በጀት በመክፈላቸው ችግሩ መፈጠሩን ተናግረዋል።

አቶ ሙዘየን  እንዳሉት በ2004 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረውና በአንድ ዓመት ዕድሜ ውስጥ ይጠናቀቀል ተብሎ የነበረው የመስኖ ፕሮጀክት የተያዘለት በጀት ሙሉ በሙሉ መከፈሉን የፋይናንስ ሰነዶች ያሳሉ፡፡

በህግ አግባብ መታየት ያለበት ሁኔታ ተጣርቶ ለህግ የሚቀርብ መሆኑን ጠቁመው፣ "የፕሮጀክቱን ቀሪ ሥራ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር ሌላ በጀት አፈላልጎ ለማስጨረስ እየተሰራ ነው" ብለዋል ፡፡

የኦሮሚያ ክልል የመስኖ ልማት ባለስልጣን ምክትል ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሁሴን ስለጉዳዩ በስልክ ለኢዜአ እንደተናገሩት ችግሩን ለመፍታት ፕሮጀክቱ ያለበትን ደረጃ የሚያጣራ ባለሙያ ሰሞኑን ወደ ስፍራው መለካቸውን ገልጸዋል።

ከስፍራው የሚመጣላቸውን ሪፖርት መሰረት በማድረግ የድጋፍና የእርምት እርምጃዎች እንደሚወስዱም ተናግረዋል ፡፡

በባሌ ዞን በተለያዩ የመስኖ አማራጮች በዓመት 40 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት እየለማ መሆኑን ከዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 26/2010 "መገናኛ ብዙኃን በሙገሳ ወይም በጥላቻ ላይ የተንጠለጠለ ዘገባ ከመስራት መቆጠብ አለባቸው" ሲሉ ፕሬዘዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ የፋና ቴሌቪዥን መደበኛ ስርጭት በይፋ ሲመረቅ ባስተላለፉት መልዕክት መገናኛ ብዙኃን "በአጉል ሙገሳ ወይም በጥላቻ ላይ የተንጠለጠለ ዘገባ" ከመስራት መቆጠብ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙኃን ሚዛናዊ፣ ተዓማኒና፣ለሀገር ሁለንተናዊ ጥቅሞች እንዲቆረቆሩም ፕሬዘዳንቱ አሳስበዋል።

መንግስት ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ የመገናኛ ብዙኃን ለሀገር ልማትና ዲሞክራሲ ጉዞ የሚኖራቸውን አስተዋፅኦ በመገንዘብ ዘርፉ እንዲጎለብት በህገ መንግስቱ ለተቀመጠው ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ተግባራዊነት ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረጉን ተናግረዋል።

በዚህም የህትመትም ሆነ የብሮድካስት መገናኛ ብዙኃን ቁጥር መጨመሩን ጠቅሰው የመገናኛ ብዙኃኑ መጨመር ለሀገራችን የወደፊት ጉዞ በጎ ሚና የሚኖራቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በማንሳት መላው ህብረተሰብ ለአንድ ሃገራዊ  አላማ እንዲሰለፍ መልካም አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙኃን መልካም ተግባራት እንዳሉ ሆነው በቅርብ ጊዜ ግን ከስነ ምግባርና ከሙያዊ መለኪያዎች አንፃር በርካታ ችግሮች እንደሚስተዋልባቸውም ገልፀዋል።

"አንዳንዶቹ ጥሩ መስሎ የሚታያቸውን ብቻ በማድነቅና በማጉላት ሲሰሩ፤ ሌሎቹ ደግሞ የተሰራውንና ያለውን መልካም ነገር ለመዘገብ ፍላጎት እንዳላሳዩ" ግልፅ ነበር ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ሁለቱም ጫፎች ጥርጣሬን እንጂ የህዝብ አመኔታ እንዳላስገኙ አውስተው፣ ይህ ደግሞ ጉዳት አንጂ ጥቅም እንደማያስገኝ ተናግረዋል።

በመሆኑም መገናኛ ብዙኃኑ "በሙገሳ ብቻ ወይንም በጥላቻ ብቻ ከመጠመድ ይልቅ በህዝብ ዘንድ አመኔታን ለማትረፍና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስገኘት የሚሰሩ መሆን አለባቸው" ብለዋል።

ለህዝብ ታማኝ መገናኛ ብዙኃን እንዲፈጠሩ የማድረግ ሃላፊነቱ የመንግስት ብቻ ሳይሆን በሙያው ውስጥ ያሉ የአመራሮችና ጋዜጠኞች ሚና መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

በሙያው ተፅእኖ ለማሳረፍ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክር አካልን በመታገል "ከህዝብና ከሀገር ጥቅም በላይ የሚያስበልጡት እንደሌለ ማሳየት" አለባቸው ብለዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትም ከተመሰረተ ጀምሮ በአንፃራዊ መልኩም ቢሆን የተለያዩ ሀሳቦች የሚንሸራሸሩበት መድረክ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው ወደፊትም ሙያዊ ስነ ምግባር በተላበሰ መልኩ የብዝኃነት ድምፆች የሚሰሙበት ተቋም እንዲሆን መስራት አለበት ብለዋል።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዱ ይመስል በበኩላቸው በአሁን ዘመን ወቅታዊ መረጃ የሰውን ህይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዝ ከመሆኑ ሌላ ጥፋትንና ውድመትን ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመዋል።

"በመረጃ ስርጭት ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወቱት መገናኛ ብዙኃን ተልዕኮና ሃላፊነትም በዚህ ማዕቀፍ መታየት አለበት" ብለዋል።

ፋና ቴሌቪዥንም በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘና ከቀረፃ እስከ ስርጭቱ ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ለሀገራችን የቴሌቪዥን ስርጭት ስርዓት እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል" ብለዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሬዲዮ ፋና በሚል ስም በ1987 ዓ.ም የተመሰረተና ተደራሽነቱን በየጊዜው እያሳደገ ያለ ተወዳጅ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም  ነው።

አዳማ ጥር 26/2010 የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ የተለያዩ ማዳበሪያዎችን በስፋት አገልግሎት ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር ገለጸ።

በበጀት ዓመቱ በስፋት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚደረጉት ማዳበሪያዎች የተፈጥሮ፣ ፍሳሽ፣ ምጥንና ውህድ ማዳበሪያን ጨምሮ ስድስት ዓይነት ማዳበሪያዎች ናቸው።

ማዳበሪያዎቹን ጥቅም ላይ ለማዋል፣ በሄክታር የሚያስፈልገውን መጠን ለመለየትና አጠቃቀሙን ለመወሰን የሚያስችል የምክክር መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።  

በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር የሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ባለሙያ አቶ ፋኖሴ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት ሀገሪቷ ከ50 ዓመታት በላይ በሁለት አይነት ማዳበሪያ ብቻ ተወስና በመቆየቷ የእርሻ መሬት ለምነት መቀነስና የአፈር ንጥረ ነገር መመናመን ተስተውሏል።

"የእርሻ መሬት ተገቢውን ምርት እንዲሰጥ 13 አይነት ንጥረ ነገር የያዘ መዳበሪያ ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ፋኖሴ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በዘላቂነት ለማስቅጠል በመላ ሀገሪቷ የአፈር ለምነት ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

ለእዚህም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ደቡብ፣ ሶማሌ፣ አፋርና ሐረሪ ክልሎች በተደረገው የአፈር ለምነት ጥናት ውጤት መሰረት የእርሻ መሬቱ ከስድስት አይነት በላይ ማዳበሪያ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

በ2010/2011 የበልግ ወቅት በስፋት አገልግሎት ላይ አንዲውሉ የሚደረጉት ማደባሪያዎች ብዛት ያላቸው የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን የያዙ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

ባለሙያው አንዳሉት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የተፈጥሮ ሀብት መመናመን አፈር በጎርፍ እንዲሸረሸርና የመሬት ለምነትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ በማድረግ ላይ ነው።

"ለአካባቢ አየር፣ ለእርሻ መሬትና ለሕብረተሰቡ ጤንነት ተስማሚ የሆኑ ደረጃቸውን የጠበቁ የማዳበሪያ አይነቶች አገልግሎት ላይ ከመዋላቸው በፊት ደረጃ ማውጣትና የአጠቃቀም መጠኑን መወሰን ይገባል" ብለዋል።

እንደ አቶ ፋኖሴ ገለጻ፣ የተለዩና ደረጃ የወጣላቸው መዳበሪያዎች ከየአካባቢው የግብርና ስነ ምህዳር ጋር ተስማሚ መሆናቸው በ40 ሺህ የአርሶ አደር ሠርቶ ማሳያ ማዕከላት ላይ ተሞክረው ሙሉ በሙሉ ውጤታማ መሆናቸው ተረጋግጧል።

በመሆኑም ማዳበሪያዎቹን በስፋት አገልግሎት ላይ ለማዋል  አምስት የማዳበሪያ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ተቋቋመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ነው የገለጹት።

መዳበሪያዎቹን የማስተዋወቅ፣ በአጠቃቀሙ ላይ የአርሶ አደሩን ክህሎትና ግንዛቤውን የማሳደግ ሥራ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ድረስ በልማት ጣቢያ ሠራተኞች፣ በዘርፉ ባለሙያዎችና አመራሮች አማካኝነት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአፈር ውስጥ ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን ጠብቀው የሚያቆዩ መዳበሪያዎችን አገልግሎት ላይ ለማዋል የምክክር መድረኩ ጠቃሚ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር የግብርናና የስነ ምግብ ደረጃዎች መዳቢ ባለሙያ አቶ ኃይለገብረኤል ለማ ናቸው።

አቶ ኃይለገብረኤል እንዳሉት ለሰብል፣ ለአትክልትና ፍራፍሬ፣ ለአበባ ምርቶችና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉና 13 ንጥረ ነገሮችን የያዙ ስድስት አይነት ማዳበሪያዎች በአሁኑ ወቅት ተለይተው ደረጃ ወጥቶላቸዋል።

ደረጃው የተቀመጠላቸው ከአካባቢ ሁኔታ ፣ ከአየር ንብረት፣ ከህበረተሰቡ ጤና፣ ከስነምህዳርና ከመሳሰሉት ጋር ተቃኝተው መሆኑንም አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ከኬሚካል ኢንዱስትሪዎች፣ ከግብርና ምርምር እንዲሁም ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚንስቴር የተወጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳተፊ ሆኖዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 25/2010 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንባታቸው የዘገየ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲፋጠን የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን የ2010 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃጸምን ዛሬ ገምግሞ ግብረ መልስ ሰጥቷል።

ጅማ፣ ባህር ዳር እና ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች በተያዘላቸው ጊዜ ግንባታቸው እየተከናወነ አለመሆኑ ቋሚ ኮሚቴ ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ የፓርኮችን ግንባታ ለማፋጠን በሁለተኛው ሩብ ዓመት የታዩ መሻሻሎች የተሻለ ቢሆንም በበጀት ዓመቱ ቀሪ ጊዜያት ፓርኮችን ሰርቶ ለማጠናቀቅ ኮርፖሬሽኑ የግንባታ ሥራውን ማፋጠን እንዳለበት አሳስበዋል።

በተጨማሪም የተገነቡ ፓርኮችን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ማስገባት፣ የፓርኮች አካባቢ ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ማድረግ፣ ወደ ፓርኩ የሚገቡ የአገር ውስጥ ባለኃብቶችን ቁጥር ማሳደግም ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች እንደሆኑም አስምረውበታል 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳሬክተር አቶ ሲሳይ ገመቹ የተሰጠው ግብረ መልስ ጠቃሚ ግብዓት መሆኑን ጠቅሰው ለአፈጻጸሙ መዘግየት የኮንትራክተሮችና የወሰን ማስከበር ችግር በዋናነት አንስተዋል 

የአማካሪ ድርጅቶች ድክመት እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ ውስጣዊ አቅም ማነስ ተጨማሪ ምክንያቶች እንደሆኑም ገልጸዋል።

በዚህ ምክንያት በአንድ ዓመት ይጠናቀቃል የተባለው የጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የማጠናቀቂያ ጊዜው ቢያልፍም አፈጻጸሙ ግን ገና 45 በመቶ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።

በዚህ በጀት ዓመት መጀመሪያ ግንባታቸው የተጀመረው የባህር ዳርና ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ አፈፃጸማቸው 5 በመቶ ብቻ ነው ብለዋል።

ኮርፖሬሽኑ ችግሩን ለመፍታትና ግንባታቸውን ለማፋጠን በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዕቅድ ክለሳ በማድረግ በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ተቋሙ ስራውን ለማፋጠን ግንባታውን ከሚያከናውኑት ኮንትራክተሮችና አማካሪዎች ጋር ስምምነት ላይ በመድረሱ በዚህ ዓመት የሼድ፣ መሰረተ ልማት ሥራዎችን የማጠናቀቅ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

 

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አሶሳ ጥር 26/2010 በመተከል ዞን የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች በንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት መቸገራቸውን ገለጹ።

በከተማው ከአራት ዓመት ወዲህ የመጠጥ ውሃ እጥረት እየተባባሰ ቢመጣም መፍተሄ ሊሰጠው ባለመቻሉ ለጤና ችግር እየተጋለጡ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል ።

ወይዘሮ ፅጌ ዮሐንስ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የሚሰራጨው የቧንቧ ውሃ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ የሚደርሳቸው በመሆኑ ተቸግረዋል።

የጉድጓድና የወንዝ ውሃ ቀድተው ለመጠቀም በመገደዳቸው ከነቤተሰባቸው የጤና እክል እየገጠማቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሆቴል ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ በላቸው አምሳሉ በበኩላቸው "የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረቱ በንግድ ሥራዬ ላይ ተፅዕኖ እያሳደብኝ ይገኛል" ብለዋል።፡

ያቋቋሙት ሆቴል የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ሊጎበኙ የሚመጡ እንግዶች የሚያርፉበት ቢሆንም በውሃ እጥረቱ ደንበኞችን በአግባቡ ለማስተናገድ እየተሳነው መምጣቱን ጠቁመዋል።

የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አበጀ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  ከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ እየቀረበ ያለው ከአስር ዓመት በፊት በተገነባ የውሃ ተቋም አማካኝነት መሆኑን ገልጸዋል።

በየጊዜው እያደገ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር አቅርቦቱና ፍላጎቱ ባለመጣጣሙ እጥረቱ መከሰቱን ተናግረዋል።

በክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ የግንባታ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ደረጀ አቀና በበኩላቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረቱን ለመፍታት ከሁለት ዓመት በፊት የተጀመረው የሦስት ጥልቅ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሥራ በአሁኑ ወቅት መጠናቀቁን ተናግረዋል ።

“የውሃውን ስርጭት ለማስጀመር አስፈላጊ የሆኑ የቧንቧ መስመር ዝርጋታና ተጓዳኝ ሥራዎች የዲዛይን ሥራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል

በ2011 አጋማሽ ድረስ ሥራው ተጠናቆ አገልግሎቱ እንደሚጀምር ተናግረዋል።

እስከዚያው ድረስ ፍትሀዊነቱን ጠብቆ ውሃን በፈረቃ ከማከፋፈል ሥራ ተጠናክሮ አንደሚቀጠል  የገለፁት አቶ ደረጀ፣ ህብረተሰቡም የሚያገኘውን ውሀ በቁጠባ እንዲጠቀም አስገንዘበዋል ።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን