አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 02 February 2018

መቀሌ ጥር 25/2010 በመቀሌ ከተማ ከሳምንት በላይ ሲካሄድ የቆየው የህወሓት የክልልና የከተማ ከፍተኛ አመራሮች ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የለያቸውን ችግሮች ለማስተካከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን በመውሰድ ተጠናቀቀ።

ለ11 ቀናት የተካሄደው ኮንፈረንስ ትናንት ሲጠናቀቅ ስምንት ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ፤ 26ቱ ደግሞ በከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ወሳኔ ተላልፎባቸዋል።

በህወሓት ጽህፈት ቤት የክልል ስታፍ አስተባባሪ አቶ ተካ መንገሻ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በግመገማው ከባድ ጥፋት የተገኘባቸው ሁለት የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከስራቸው እንዲነሱና ስምንቱ ከባድ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

የመቀሌ ከተማ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመንፈስቅዱስ ፍስሃ በበኩላቸው ስድስት የክፍለ ከተሞች  ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲንሱና 18ቱ ደግሞ በከፍተኛ ማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ ውሳኔ የተላለፈባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"ከመቀሌ ከተማ ከሰባት ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ከ160 በላይ ከፍተኛ አመራሮች በግምገማው ተሳትፈዋል" ብለዋል።

የክልልና የመቀሌ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ባኬሄዷቸው ግምገማዎች በሌሎች አመራሮች ላይ ጉዳያቸው ተጣርቶ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ውሳኔ ማሳለፋቸውን ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።

የክልል ከፍተኛ አመራሮች ያካሄዱትን ግምገማ  የመሩት የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ሀዱሽ ዘነበ እንደገለጹት እያንዳንዱ አመራር ህዝብን ከማገልገል አኳያ የነበሩበት ችግሮችን በጥልቀት አይቶ ለማስተካከል መስራት አለበት።

የመቀሌ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ግምገማቸውን ሲያጠናቅቁ ባወጡት ባለ አስር ነጥብ የአቋም መግለጫ የበደሉትን ህዝብ በአግባቡ እንደሚያገለግሉ አረጋግጠዋል።

በሚካሄዱ የልማት ስራዎች የህዝቡ ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲረጋገጥ በተኩረት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

የከተማው ምክትል ከንቲባና የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ብርሃነ ገብረኢየሱስ በበኩላቸው "የግምገማ መድረኩ እራሳችንን በጥልቀት ያየንበት ነበር" ብለዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ዘርትሁን ደስታ በሰጡት አስተያየት ግምገማው ህዝብን ከማገልገል ይልቅ በግል ፍላጎት ተውጠው መቆየታቸውን ራሳቸውን ያዩበት እንደነበር ተናግረዋል።

በመቀሌ ከተማ የዓይደር ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ገብረጻዲቅ እንዳሉት በግምገማው ከህዝብ ጥቅም አንጻር ምን ሲሰሩ እንደነበር ራሳቸውን እንደፈተሹ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አርባ ምንጭ ጥር 25/2010 የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአንድን ሃይማኖት ሰላምና ስሜት የሚነካ ያልተገባ አስተምህሮ አካሂዷል ባለው ግለሰብ ላይ የሰባት ወር እስራት ቅጣት አሳለፈ።

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት በግለሰቡ ላይ ዛሬ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው ተከሳሹ በሌላ የእምነት ተቋም የሚከናወን ሃይማኖታዊ ስርዓትን ሰላም የሚጎዳ አስተምህሮ ማካሄዱ በማስረጃ በመረጋገጡ ነው።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ባስቻለው ችሎት በንባብ እንዳስታወቀው፣ ዐቃቤ ህግ በግለሰቡ ላይ ያቀረበውን ”የአንድን ሃይማኖት ሰላምና ስሜት የመንካት″ ክስ በዝርዝር ሲመረምር ቆይቷል።

ተከሳሹ ተመስገን ምትኩ ከራሱ እምነት ውጪ የሌሎችን እምነት ሰላምና ስሜት የሚነካ ተግባር መፈጸሙን ክዶ ቢከራከርም ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ማስረጃ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ ተረጋግጧል።

ድርጊቱ በወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት ከ10 ቀን እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ መቀጮ የሚያስቀጣ መሆኑን ችሎቱን የመሩት ዳኛ ጠቅሰዋል።

ሆኖም ፍርድ ቤቱ የወንጀሉን አፈጻጸም፣ የደረሰውን ጉዳት፣ የተከሳሹን የቤተሰብና የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ተከሳሹ ያቀረበውን የቅጣት ማቅለያ ግምት ውስጥ በማስገባት ወንጀሉን በመካከለኛ ደረጃ መፈረጁን አመልክተዋል።

ተከሳሹ ውሳኔው በገንዘብ መቀጮ እንዲሆን ያቀረበውን ሀሳብ እንዲሁም ዐቃቤ ህግ ግለሰቡ ወንጀል የፈፀመው ቀደም ስል በሚያመልከው እምነት ላይ በመሆኑ ” ክህደት ነው″ በሚል ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል። 

በዚህም የተፈጸመው ወንጀል በህጉ ከተቀመጠው የገንዘብ መቀጮ ቅጣት ከፍ ያለ በመሆኑና ከከፍተኛው የሁለት ዓመት እስራት ቅጣት ያነሰ በመሆኑ ሌሎችንም ያስተምራል በሚል ግለሰቡ በሰባት ወር እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል።

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ጥር 25/2010 በትግራይ ክልል ደረጃ የተዘጋጀው የልዩ ልዩ ስፖርት ውድድር የፊታችን እሁድ በሁመራ ከተማ እንደሚጀመር የክልል ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው ህዝባዊ መሰረት ያለው ስፖርት ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ሓዱሽ እንደገለጹት በ19 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሄደው ውድድር ዓላማው ለሀገር አቀፉ ጨዋታዎች ክልሉን ወክለው የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመመረጥ ነው፡፡

ለ18 ቀናት በሚቆየው ውድድር በክልሉ ውስጥ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባለፈ ወጣቶች ባህልና ልምድ እንዲለዋወጡ ለማስቻል ጭምር እንደሆነ ዳይሬክተሩ  አመልክተዋል፡፡

በውድድሩ በክልሉ ከ51 ወረዳዎች የሚወከሉ  ከ6ሺህ 700 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ከነዚህም 1 ሺህ 782 ሴቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

በመጪው እሁድ በሁመራ ለሚጀመረው የክልሉ ስፖርት ውድድር ሜዳዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ዝግጅቶች መጠናቀቃቸውም ተገልጿል፡፡

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ጥር 25/2010 ወጣቶች በስሜታዊነት ተነሳስተው እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ ጥያቄያቸው በምክንያታዊነት አስተሳስብና ለአገር ልማት በሚበጅ አኳሃን እንዲያቀርቡ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ጠየቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አገሪቷ ባለፉት በርካታ ዓመታት በነበራት ሠላምና መረጋጋት የኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች በማስመዝገብ ህዝቦቿን ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻለች አውስተዋል።

በትራንስፖርት፣ በቤቶች ግንባታ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በኃይል አቅርቦትና መሰል መስኮች የተጀመሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም ከፈጠሩት ሰፊ የሥራ ዕድል ባሻገር ወደፊት የአገሪቷን ነባራዊ ሁኔታ ከመሰረቱ የሚቀይሩ የልማት ፕሮጀክቶች በመተግበር ላይ ናቸው ብለዋል።

ይሁንና ከአመርቂ ድሎች ጎን ለጎን አሁንም 22 ሚሊዮን ዜጎች ከድህነት ወለል በታች እንደሚገኙና የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥርም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ህዝቦችን ለምሬት የዳረጉ የሠላም፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳድር እጦት እንዲሁም የኪራይ ሰብሳቢነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

መንግሥትም የችግሮቹ መሰረታዊ ምንጭ የገዥው ፓርቲ ውስጣዊ ክፍተት እንደሆነ በማመን ለዓመታት የተጠራቀሙ የሠላም፣ የፍትሕ፣ የዴሞክራሲና የሕዝብ ተጠቃሚነት ቅሬታዎችን ለመፍታት እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው ብለዋል።

ይሁንና መንግስሥት ችግሮችን በሕዝብ ተሳትፎ ለመፍታት በቁርጠኝነትና ተግባራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ባለበት ወቅት በአንዳንድ ከተሞች የዜጎች ሕይወት ህልፈት እንዲሁም በግለሰቦችና በመንግሥት የአገልግሎት ተቋማት ላይ ውድመት ያስከተለ ድርጊት መፈጸሙ አገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴውን የሚያደናቅፍ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣትም "በኅብረተሰብ ደረጃ ሁለንተናዊ የአስተሳስብ ለውጥ ማምጣት ግድ ይላል" ሲሉ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል።

ወጣቶች በስሜታዊነት ተነሳስተው እርምጃዎችን ከመውሰድ ይልቅ በምክንያታዊነት አስተሳስብ ለአገር ልማት የሚበጀውን አቅጣጫ መከተል ይገባቸዋል ብለዋል።

ስለሆነም ወጣቶች ማንኛውንም ጥያቄያቸውን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና አገራዊ ስሜት እንዲያቀርቡ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የእርስ በርስ ጥላቻና ጥቃት አገር ለማፍረስ የሚፈልጉ አካላት እንጂ ለየትኛውም ወገን ስለማይጠቅም በአንድነትና በመከባበር እሴት ወጣቶች አርቀው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ስለሆነም ወጣቶች በፈጠራና በሳይንስና ቴክኖሎጂ በመላቅ ለችግሮች የመፍትሔ አካል መሆን እንጂ አገሪቷ የተፈጥሮ ኃብቷን እንዳትጠቀም ለሚፈልጉ ኃይሎች መጠቀሚያ መሆን እንደሌለባቸውም አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ዜጎች ለብጥብጥና ሁከት ከሚለቀቁ የተዛቡ መረጃዎች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚገባቸው ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ከጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ከተሞች የተቀሰቀሰው ግጭት በአሁኑ ሰዓት አንፃራዊ ሠላምና መረጋጋት መስፈኑን ገልጸው፤ ለግጭቱ መንስኤ የሆነ የፀጥታ አካልም ሆነ ሌላ ዜጋ በሕግ ተጠያቂ ይደረጋል ብለዋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 25/2010 አዲስ አበባን ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የተጀመረው ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻ ነገ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚቀጥል የከተማዋ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ።

ዘመቻው "እኔ አካባቢዬን አጸዳለሁ እናንተስ?" በሚል መሪ ሀሳብ ባለፈው ኅዳር ተጀምሯል።

የመላውን ኅብረተሰብ ቀጣይ ተሳትፎ ለማረጋገጥ ዘመቻው ነገም ለሦስተኛ ጊዜ  እንደሚካሄድ ኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በዘመቻው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመዲናዋ ከንቲባ፣ የካቢኔ አባላትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ተወካዮች በተገኙበት በልደታ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ አንድ፣ ቀጠና አንድ አካባቢ ይካሄዳል።

በዕለቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በአረንጓዴ ልማትና ጽዳት ሞዴል የሆኑ እንደሚጎበኙና የችግኝ ተከላም እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።

በተመሳሳይ ቀን በሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ አስተባባሪነት በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ በሚካሄደው የፅዳት ሥራም አትሌቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ የፅዳት ዘመቻ ህዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በይፋ መጀመሩ ይታወቃል።

 

Published in ማህበራዊ

ጊምቢ ጥር 25/2010 በምዕራብ ወለጋ ዞን ስድስት  ጤና ጣቢያዎችን ወደ ሆስፒታል ደረጃ በማሳደግ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ለማጠናከር  እየተሰራ ነው፡፡

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ከድር ሙዘይን ለኢዜአ እንደተናገሩት ጤና ጣቢዎቹ ወደ ሆስፒታል ደረጃ ለማሳደግ ከ2008 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የማስፋፊያ ግንባታቸው እየተካሄደ ነው፡፡

ከእነዚህም በሰዮ ኖሌና ሀሩ ወረዳዎች   የማስፋፊያ ግንባታቸው አሁን ላይ 92 በመቶ ፤  የእናንጎና ጉደቱ ባቦም ፕሮጄክቶች ደግሞ  70 በመቶ  መድረሱን  ገልጸዋል።

ከ40 በመቶ በላይ መሄድ ያልቻሉት የገባ ደፊኖ እና ጉሊሶ የጤና ተቋማት ፕሮጄክቶች በግንባታ ጥራት ችግር መቋረጣቸውን ጠቁመዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ግንባታውን ከሚያከናውኑት ተቋራጮች  ጋር በተደጋጋሚ ውይይት ተደርጎ መፍትሄ ባለመምጣቱ ውላቸውን አቋርጠው ለሌላ ተቋራጭ ለመስጠት በሂደት ላይ ይገኛል።

ግንባታቸውን በማጠናቀቅም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ አገልገሎት እንዲሰጡ ከወዲሁ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ  የጎሪ እና እናንጎ ጤና ጣቢያዎች ተጠናቀው ስራ መጀመራቸውም አመልክተዋል፡፡

ቀላል የቀዶ ጥገና አገልግሎትም በእነዚሁ ጤና ጣቢያዎችና ሆስፒታሎች ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንደሚፈጠር አቶ ከድር ጠቅሰዋል፡፡

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት የጤና ተቋማት ተጠናቀው  ስራ ሲጀምሩ ህብረተሰቡ በቅራቢያው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል፡፡

በተለይም የወሊድ አገልግሎት ለማግኘት የነበረውን እንግልት በመቀነስ እናቶች በአከባቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡

የሀሩ ወረዳ ነዋሪው አቶ እውነቱ ቤኛ በሰጡት አስተያየት በአቅራቢያቸው እየተገነባ የሚገኘው የጤና ተቋም ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት እስከ ጊምቢ ከተማ በመሄድ ህክምና ለማግኘት የሚያወጡት ወጪና ጊዜ እንደሚቀንስላቸው የሚጠብቁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጉሊሶ ከተማ ነዋሪ አቶ መልካሙ ሰንበታ በበኩላቸው የከተማቸውን ጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ የተጀመረው ስራ በማፋጠን ለአገልገሎት እንዲበቃ  የሚመለከተው አካል ትኩረት መስጠት እንዳለበት ጠቁመዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 25/2010 ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዓላማዎችን በማስፈጸም ረገድ ግንባር ቀዳም ሚና እየተወጣች መሆኗን ተገለጸ።

ኢጋድ እንደ አውሮፓውያን የጊዜ ቀመር በ1986 ድርቅና የበረሃ መስፋፋት መከላከልን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ቀጣናዊ ኅብረት ነው።

ከምሥረታው አሥር ዓመት በኋላ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ከተማ በተደረገ ጉባዔ ዓላማውን ሰፋ በማድረግ አሁን የሚጠራበትን ስያሜ ያገኘ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኬነያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኡጋንዳ ደግሞ የድርጅቱ አባል አገራት ናቸው።

ቀጣናውን በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር፣ ሠላምና መረጋጋትን ማስፈን፣ አባል አገራት ከሚገጥማቸው ሰብዓዊ ቀውስ መታደግና ድርቅን ለመቋቋም ቀጣይነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ማከናወን ድርጅቱ ካነገባቸው ዓላማዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው።

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂካዊ ጥናት ኢንስትቲዩት የውጭ ፖሊሲ ትንተና ክፍል ኃላፊ አቶ መላኩ ሙሉዓለም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ የኢጋድን ዓላማዎች ከግብ ለማድረስ በርካታ ተጨባጭ ተግባራትን አከናውናለች።

በተለይ የአካባቢውን አገራት በኤሌክትሪክ ኃይልና በመንገድ የመሰረተ ልማት በማስተሳሰር በኩል ኢትዮጵያ የላቀ አስተዋጽኦ ማደረጓን በማሳያነት ጠቅሰዋል። 

ይህ ደግሞ ኢጋድ ቀጣናውን በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር ያስቀመጠውን ዓላማ ስኬታማ እንዲሆን የሚያግዝ ተግባር እንደሆነ ነው ኃላፊው የተናገሩት።

ቀጣናው አለመረጋጋት በተደጋጋሚ እንደሚስተዋልበት የጠቀሱት አቶ መላኩ ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት፣ በአፍሪካ ኅብረትና በኢጋድ ጥላ ሥር የሠላም አስከባሪ ኃይል በማዋጣት የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ በማስጠበቅ በኩል ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣች ነው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው ኢትዮጵያ ከቀጣናው አገራት ጋር ካላት የመንግሥት ለመንግሥት ግንኙነት ባለፈ በህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ አገራት ከግጭት ለመውጣትና ከወጡም በኋላ የድህረ-ግጭት ድጋፍ በማድረግ በኩል አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያደረገች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራት ሕዝቦች በግጭት ወቅት በሚገጥማቸው ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት ከለላ ሲፈልጉ በማስጠጋት ስሟ በመልካም የሚጠራ አገር መሆኗንም ገለጸዋል።

ኢጋድ ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም ካስቀመጠው ዓላማ አንፃርም ኢትዮጵያ ለሌሎች አገራት ምሳሌ በሚሆን መልኩ የአካባቢ ጥበቃ ስራ በማከናወን ላይ መሆኗን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አባል አገራት 230 ሚሊዮን ሕዝብ ያቀፈ ክፍለ አሕጉራዊ ቀጣና ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 25/2010 ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚያጋጥሟትን ችግሮች ለመፍታት እየወሰደች ያለውን እርምጃ የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አደነቀ።

በአውሮፓ ኅብረት የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በአውሮፓ ፓርላማ የአፍሪካ፣ የካሪቢያንና ፓስፊክና የአውሮፓ ፓርላማ ልኡክ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ስለ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ እንዳስታወቀው አምባሳደር ተሾመ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ብቻ ከመመልከት ይልቅ ሙሉ ገጽታዋን መረዳት ጠቃሚ መሆኑን አብራርተዋል።

ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች በአገሪቱ የተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶችና እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ግልጽ አድርገዋል።

እንዲያም ሆኖ ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በማለፍ ለውጥ የማስመዝገብ ብቃት እንዳላት ነው ለፓርላማ አባላቱ ያስረዱት።

የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር በማሰብ መንግሥት በወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ በሚፈቅደውና ለዚሁ ሲባል በተዘጋጀው መስፈርት መሰረት በክስ ሂደት ላይ ያሉት ጭምር ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

ማብራሪያውን ያደመጡት የኅብረቱ ፓርላማ አባላትም የመንግሥትን ጥረት በመገንዘብ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ማየት ተገቢ መሆኑን ነው የገለጹት።

የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ምክትል ሰብሳቢ በቅርቡ ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውንና በኢኮኖሚው መስክ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች እያመጣች መሆኗን የፓርላማው አባላት ገልጸዋል።

በፖለቲካውና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የተጀመሩት ሥራዎችም ሊጠናከሩ እንደሚገባና መንግሥት በቅርቡ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን ለመፍታት የወሰደውን እርምጃ እንደሚያደንቁም ይፋ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በቀጣናው የሠላም ማስጠበቅ ሂደት ትልቅ ኃላፊነት እየተወጣች፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ያለች አገር መሆኗንም በመድረኩ ተነስቷል።

በፀረ-ሽብር ትግሉም የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ከዓለም ዓቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የበኩሏን ሚና በመጫወት ላይ እንደምትገኝም የፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።

በፀረ-ሽብር ትግሉ የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር እያበረከተች ያለው አስተዋጽኦ የጋራ ተጠቃሚነትን እያስገኘ መሆኑም ተገልጿል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ 25/2010 ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ የሚካሄደው ዓመታዊ ከተማ አቀፍ የባሕል ሳምንት ዛሬ በአዲስ አበባ እግዚቢሽን ማዕከል ተጀመረ።

የከተማ ሳምንቱ "ባሕላችን ለሠላምና አንድነታችን" በሚል መሪ ሐሳብ እስከ መጪው እሁድ የሚካሄድ ነው።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ረመዳን አሸናፊ በመክፈቻው ላይ እንዳሉት የባህል ሳምንቱ የመዲናዋ ነዋሪ ከአገር በቀል እሴቶች፣ ቋንቋና ባሕሎች ጋር እንዲተዋወቅ የሚያግዝ ነው።

ሕዝቡ ይበልጥ እንዲቀራረብና እንዲተዋወቅ፣ የአብሮነት ባሕልን በማጠናከር አንዱ የሌላውን ማንነት እንዲያከብር ግንዛቤ የሚያሰፋ እንደሆነም  ገልጸዋል።

ለዘመናት የቆዩትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጽኑ የአብሮነት እሴቶች ለማስቀጠልም የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የጋራ ርብርብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሚኒስተር ዴኤታው ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረፃዲቅ ሐጎስ በበኩላቸው ሳምንቱ የከተማዋ ነዋሪዎች ይበልጥ የሚቀራረቡበትና ለሠላምና አብሮነት ያላቸውን ኅብረት የሚያጠናክሩበት ነው ብለዋል።

ሳምንቱ ወጣቱ የኪነ-ጥበብ ሙያውን እንዲያሳድግና እንዲበረታታ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር በባሕል ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች የሚተዋወቁበት መድረክ ነው።

በተጨማሪም ሳምንቱ በጎ ባሕሎች ወደ ቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ በትጋት መስራትን፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መከላከልና በሕዝቡ ግንዛቤ መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው መሆኑን ተናግረዋ።

የኪነ-ጥበቡ ዘርፍ ባለሙያዎች የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለእይታ ያቀረቡ ሲሆን የተሻሉ የፈጠራ ሥራዎችን ያቀረቡ የሚሸለሙበትና የሚበረታቱበት ይሆናል ብለዋል

በዚህ የባሕል ሳምንት ኪነ-ጥበባዊ ውድድሮች፣ ሲምፖዚየሞችና ልዩ ልዩ የመዝናኛ ዝግጅቶች እየቀረቡ ሲሆን፤ ከ200 በላይ ተቋማት የባሕል ውጤቶቻቸውን ለእይታ አብቅተዋል።

አልባሳት፣ የቆዳ ውጤቶች፣ የባሕል ማዕከላት ምርቶች፣ የሸክላና የዕደ ጥበብ ውጤቶች እንዲሁም የተለያዩ ጌጣጌጦችን የሚያመርቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ተሳታፊ ሆነዋል።

በዚህ የባሕል ሳምንት የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የሚያጎለብቱ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም ታውቋል።

 

Published in ማህበራዊ

ፍቼ ጥር 25/2010 ለህብረተሰቡ  ፍትሃዊ አገልግሎት እንዳይደርስ ማነቆ እየሆነ ያለውን ሃሰተኛ ማስረጃ  ለመቆጣጠር እየተሰራ መሆኑን በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ፐብሊክ ሰርቪስና  የሰው ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት  ገለጸ።

 የጽህፈት ቤቱ  ኃላፊ አቶ ደረጄ ሰማ  እንዳሉት በዞኑ 13 ወረዳዎችና ከተሞች በዝውውር  ፣ ለእድገትና የትምህርት እድል  ተጠቃሚ ለመሆን  ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡

 የህክምና ፣የጋብቻና የልደት ጨምሮ ሌሎችም የሀሰት ማስረጃዎች የሚያቀርቡ ግለሰቦች በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ እገልግሎት  የመስጠት አቅም እንደሌላቸው ነው ያመለከቱት፡፡

 በዚህም ምክንያት ለህብረተሰቡ  ፍትሃዊ አገልግሎት እንዳይደርስ ማነቆ ነው፡፡

 ችግሩን ለማስወገድ ባለፉት ስድስት  ወራት  በርካታ የግንዛቤ   ማስጨበጫ  ስልጠናዎችና ውይይቶች መደረጋቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

 ሆኖም   ራስን አጋልጦ የሚመጣን   የስራ ቦታ ላይ ለመመደብ  ያለው ፍቃደኝነት ዝቅተኛ ነው፡፡

 ለዚህም ኃላፊው በማሳየነት የጠቀሱት በዞኑ ካሉት 21 ሺህ 465  የመንግስት ሰራተኞችና የስራ ኃላፊዎች  መካከል  በተደረገው ማጣራት ግማሽ  የሚጠጉት አጠራጣሪ የትምህርት ማስረጃዎች እንዳላቸው ቢለይም ራሳቸውን አጋልጠው ወደ ህጋዊ መስመር ለመግባት የፈቀዱት ግን  ከ310 አይበልጡም፡፡

 መፈራራት ፣ያልተገባ የጥቅምና አድሏዊ አሰራር ችግሩ እንዳይፈታ  በምክንያትነት የጠቀሱት ኃላፊው  በጽህፈት ቤቱ በኩል ያለው ቅንጅት  ማጣትና የተደራጀ የመረጃ  አያያዝ ጉድለት  አስተዋፅኦ ማድረጉንም ጠቁመዋል ።

 ይህም ሆኖ  በተደረገው ማጣራት አለአግባብ ሀሰተኛ ማስረጃ አቅርበው ለተገኙ  ሰራተኞች ይከፈል የነበረው ከ3 ሚሊዮን ብር  በላይ ገንዘብ  ዘንድሮ  ማዳን መቻሉን አመልክተዋል፡፡

 በህገ ወጥ መንገድ የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ለመቆጣጠር ፣ አቅምና ችሎታ ያላቸውን ግለሰቦች ከሙያቸው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ  እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

 የዞኑ አስተዳዳር ተወካይና የካቢኔዎች ምክር ቤት ኃላፊ  አቶ አባቡ ወርዶፋ በዞኑ ጥቂት የማይባሉ በህገወጥ  ማስረጃ ተጠቃሚ የሆኑ እንዳሉ  ጠቅሰው   በአስተደደሩ በኩል  ስርዓት ለማስያዝ ደረጃ በደረጃ በማጣራት ለማስተካከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

 ከጥረቶቹ መካከል  የሃሰት ማስረጃ  ተጠቃሚው ራሱን አጋልጦ  በሚመጥነው የሰራ ደረጃና ደመወዝ መመደብን ጠቅሰዋል፡፡

 ህዝብን ለማገልገል  ህጋዊና እውነተኛ  መሆኑን ዋና  መስፈርት  በማድረግ በወንጀል  የሚጠየቁበት  አስተዳደራዊና ህጋዊ  አሰራር ተከትሎ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ከሚመለከታቸው  የፍትህ አካላት ጋር  እየተሰራ እንደሚገኝ  አመልክተዋል ።

 አቶ አባቡ እንዳሉት በተለይ አንድ አገልጋይ  ታማኝነትና  ሕጋዊነትን ተላብሶ እንዲሰራ  ከግንዛቤ ማስጨበጥ ጀምሮ እየተሰራ ነው፡፡

 በቀጣይም ግልፅነት  ያለው አሰራር  በመዘርጋት  በህገወጥ መንገድ  ለመጠቀም  የሚፈልጉ  አካላት ከህገ-ወጥ ደርጊታቸው እንዲታቀቡ  ሕጋዊ አሰራሮች እንደሚጠናከሩም  አስታወቀዋል፡፡

 በዞኑ ትምህርት ጽህፈት ቤት የትምህርት ባለሙያ አቶ ግርማ አደም በበኩላቸው "ለስራ ብቁ የሆኑ ሙያተኞችን በአቅምና ችሎታቸው በመመደብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለሕዝቡ እንዲሰጥ ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃ ወሳኝ ነው" ብለዋል፡፡

 በቡድንና በተናጥል የሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ተግባራትን በተቀናጀ መልኩ መታገል እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

 እራሳቸውን አጋልጠው አርአያ የሆኑ ግለሰቦች በድርጊታቸው በመፀፀት  ለሌሎች ማስተማሪያ በመሆናቸው ተገቢውን ስልጠናና ድጋፍ ተደርጎላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባ የተናገረችው ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ  ወጣት ተናኜ  ዳምጤ ነች ።

 በፍቼ ከተማ ከተማ የቀበሌ ዜሮ አራት  ሊቀመንበር አቶ ቸርነት ታደሰ እንደገለፁት ህገ ወጦች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሚያደርሱትን በደሎች ለመከላከል ለግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡

 አጥፊዎችም በህግ መጠየቅ  እንዳለባቸውና   ወደ ስራው ከተሰማሩ  በኋላ ሳይሆን ችግሩን ገና በትምህርት ቤት ደረጃ መፈታት እንዳለበትም  ጠቁመዋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን