አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 14 February 2018

ጎባ/ጊምቢ የካቲት 7/2010 የሰላም አለመኖር የሚያስከትለውን ጉዳት በመረዳት ወጣቱ ጥያቄውን በሰለጠናና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ማቅረብ እንደለበት  በባሌ ጎባ አስተያየታቸውን የሰጡ የህብረተሰብ ክፍሎች አመለከቱ፡፡

በባሌና በምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች ተቋርጦ የነበረው  የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት  ዛሬ ተጀምሯል፡፡

በጎባ ከተማ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ነዋሪዎች መካከል የሀገር ሽማግሌ የሆኑት  አቶ አህመድ ከንፈልቻ እንደገለጹት በአካባቢያቸው ባለፉት ሁለት ቀናት የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት  የአካባቢው ህብረተሰብ ተቸግሮ መቆየቱን ጠቅሰው ወጣቱ የሰላምን ትልቅ ዋጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ጥያቄውን በህጋዊ አግባብ በማቅረብ ለሰላም ዘብ መቆም እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በከተማው የምዕራብ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አብዱልአዚዝ ከድር በበኩሉ የክልሉ መሪ ድርጅት ኦህዴድ ህዝቡ የሚያነሳውን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚደነቅ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ እንዳለው በተለይ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባስቀመጠው  አቅጣጫ መሰረት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሌሎችም ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲፈቱ መደረጉ መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል የሚያከብር መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ  ነው፡፡

መንግስት የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ  እየፈታ ባለበት በአሁኑ ወቅት የገበያና  የትራንስፖርት አገልግሎት ማቋረጥ መልሶ ራሱ ህዝቡን የሚጎዳ ተግባር እንደሆነ ጠቅሷል፡፡

የንግድ እንቅስቃሴና የትራንስፖርት አገልግሎት ማቆም ወደ ሁከትና ብጥብጥ በመቀየር በግለሰቦች ንብረት ላይ ጉዳት የማድረስ ተግባር ከኦሮሞ ህዝብ ባህልና ወግ ያፈነገጠና የሚወገዝ ተግባር እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የምስራቅ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አለማየሁ ከበደ ናቸው፡፡

"ወጣቱ  በሀገሪቱ ለዘመናት የተገነባው አብሮ የመኖር እሴቱ እንዳይናድ በማድረግ ረገድ  የሰላም አምባሳደር በመሆን የመሪነት ሚና ሊጫወት ይገባልም "ብለዋል። 

የባሌ ዞን የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳኒ ራሺድ "ሮቤና ጎባ ከተሞችን ጨምሮ በተወሰኑ ወረዳዎች ውስጥ ቆሞ የነበረው የንግድና የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ዛሬ ተጀምሯል"ብለዋል ፡፡ 

አቶ ሳኒ ወጣቱ የክልሉ መንግስት  የህዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄዎች በመለየት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት  እየሰራ መሆኑን በመረዳት ሌላ ዓላማ ያላቸው ሰዎች መሳሪያ ከመሆን መቆጠብ እንደለበት አሳስቧል ፡፡

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ እና  ሌሎችም ከተሞች ላለፉት ሁለት ቀናት ተቋርጦ የነበረው የንግድና ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩን የዞኑ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አብዮት ዳንኤል ገልጸዋል፡፡

አገልግሎቱ የተጀመረው ዛሬ ከምሳ ሰዓት በፊት በሁሉም ከተሞች ህዝቡ ከአመራር ጋር ባደረገው  ውይይት የጋራ መግባባት ላይ በመደረሱ ነው፡፡

በጊምቢ  የንግድ ድርጅቶች ተከፍተዋል፤ የከተማው የታክሲ ትራንስፖርት አገልገሎት መጀመራቸውን የጠቀሱት ኃላፊዋ  በ20 ወረዳዎች ከተሞችም በተመሳሳይ ወደ ነበሩበት ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ኃላፊዋ አመልክተዋል።

በጊምቢ ከተማ በንግድ ስራ የሚተዳደሩት አቶ አደራ ግርማ በሰጡት አስተያየት ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሰላም በመመለሷ የንግድ ድርጅታቸውን ከፍተው  መስራት እንደጀመሩ ተናግረዋል።

በቀን ስራ ኑሯቸውን እንደሚመሩና  የአምስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ አዱኛ ገነቲ   ላለፉት ሁለት ቀናት ከነቤተሰቦቻቸው ተቸግረው ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም  አሁን ላይ አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ለነገ ስራ ተስፋ አድርገው  እየተዘጋጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ለስራ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ጊምቢ መጥተው የሚመለሱበት የትራንስፖርት አገልግሎት በማጣት ተቸግረው እንደነበር የተናገሩት ደግሞ  አቶ ቶማስ ብሩ ናቸው፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱ በመጀመሩ ደስተኛ መሆናቸውንና ወደ አዲስ አበባ ለመሄድ የሚያስችላቸውን የአውቶብስ ቲኬት ማግኘታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የጊምቢ ከተማ ከንቲባ አቶ ተፈሪ መኮንን ህዝቡ መብትና ግዴታውን አውቆ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴው በመመለሱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት7/2010  በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ወደ ውጭ አገራት የሚደረገውን ጉዞ ለመቀነስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ሆስፒታሎች ገለጹ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ አገር አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን በማስፋት የውጭ አገር ህክምናን ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብሏል።

የካንሰር፣ የኩላሊትና ሌሎች የውስጥ አካላት ንቅለ ተከላ፣ የመገጣጠሚያና የህብለ ሰረሰር፣ የልብና የጭንቅላት ቀዶ ሕክምናዎችን  ለማግኘት ኢትዮጵያዊያን ወደ ውጭ አገራት ለመሄድ እንደሚገደዱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ታይላንድ፣ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ቱርክ፣ የመካካለኛው አውሮፓና የደቡብ እስያ አገራትም ታካሚዎች ከሚሔዱባቸው መካከል ይጠቀሳሉ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በርካታ የህክምና አይነቶች ውጭ አገር ከሚሰጡት በተመሳሳይ ደረጃ መስጠት መጀመሩን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሆስፒታሎች ኃላፊዎች ይገልጻሉ።

የሃሌሉያ አጠቃላይ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሚካኤል ጥላሁን በአዳዲስ መሳሪያዎች የታገዙ ህክምናዎችን በሆስፒታሉ በመጀመርና ከውጭ አገር ባለሙያዎችን በማስመጣት ህሙማን በአገር ውስጥ እንዲታከሙ እየተደረገ ነው ይላሉ።

ለአብነትም ሙሉ የሳምባ ምርመራና ህክምና ማከናወን የሚያስችል በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የሆነ ህክምና በቅርቡ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የአዲስ ህይወት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ካሳሁን ኪሮስም በአገር ውስጥ የማይሰጡ የነበሩ አዳዲስ የህክምና አይነቶች እየተሰጡ በመሆኑ በውጭ አገር ህክምና የሚያስፈልጋቸው የህመም አይነቶች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል።

የነርቭ፣ የአንጀት፣ የሽንት ቧንቧ፣ የኩላሊትና ሌሎች ውስብስብ ቀዶ ሕክምናዎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ታግዘው ከሚሰጡት መካከል ጠቅሰዋል።

ከውጭ አገራት ሆስፒታሎች ጋር በመስራት የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማስፋት ስራዎች እንደሚሰሩም አክለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የውጭ አገር ሕክምናን ለመቀነስ በአገር አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን የማስፋት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስታውቋል።

በሚኒስቴሩ የክሊኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር ተወካይ ዶክተር ይበልጣል መኮንን እንደገለጹት የጤና አገልግሎቱን ጥራትና ተደራሽነት ለማሻሻል በአገር አቀፍ ደረጃ የስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎት ለማስፋፋት ንድፈ ካርታ እየተዘጋጀ ነው።

ለንድፈ ካርታ ዝግጅቱም በአገሪቱ የሚያስፈልጉ የስፔሻሊቲ ሕክምና አገልግሎቶችን የመለየትና ለማዳረስ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል፣ የመሰረተ ልማት ስራዎችና የመሳሪያዎች ግብዓት ጥናት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተሰጠ ያለው የኩላሊት እጥበትና ንቀለ ተከላ ሕክምና ወደ ውጭ አገራት የሚደረገውን ጉዞ በመቀነሱ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የተገኘው ተሞክሮና ልምድ የሌሎች አካላት ንቅለ ተከላ ሕክምና ለመጀመር ጠቃሚ ነው ብለዋል።

"በሕክምና ሳቢያ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት እንዲቻል ደረጃቸውን የጠበቁ ሆስፒታሎች በአገር ውስጥ እንዲከፈቱ እናበረታታለን" ያሉት ደግሞ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አበበ አበባየሁ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተገነቡ 40 እንዲሁም በውጭና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተገነቡ ስምንት ሆስፒታሎች እንደሚገኙ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 7/2010 የበጀት ዓመቱ አገር አቀፍ የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በተያዘው ወር እንደሚጀመር ተገለፀ።

የምገባ ፕሮግራሙ በዓመቱ መጀመሪያ ተግባራዊ ሳይሆን የቆየው በበጀት አለመለቀቅ ምክንያት መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከዚህ ወር ጀምሮ ለሚካሄደው የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ከ289 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን የሚኒስቴሩ የትምህርት ቤት ምገባ አስተባባሪ አቶ መኳንንት ዳኘው ገልጸዋል።

በዚህም በቅድመ መደበኛና በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ቁርስ እንዲመገቡ ይደረጋል።

ከተመደበው በጀት ለኦሮሚያ ክልል 107 ሚሊዮን 94 ሺህ 109 ብር፣ ለሶማሌ ክልል 52 ሚሊዮን 440 ሺህ 396 ብር የተሰጠ ሲሆን መነሻውም ባለፈው ዓመት በክልሎቹ የተከሰተው ድርቅ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት ለፕሮግራሙ የያዘው በጀት መከፋፈሉንና ክልሎችም ምገባውን ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ደቡብ ክልል በራስ አቅም 20 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ ከ144 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመመገብ ላይ መሆኑን የጠቀሱት አቶ መኳንንት ከፌዴራል በተለቀቀለት በጀት ተጨማሪ 400 ሺህ ችግረኛ ተማሪዎችን በቅርቡ መመገብ እንደሚጀምር ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተሰማ ዲማ ከፌዴራል መንግስት በተመደበው 48 ሚሊዮን ብር “ከመጪው የካቲት 15 ጀምሮ ከ400 ሺህ በላይ ተማሪዎችን መመገብ እንጀምራለን” ሲሉ አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ሸምሰዲን ሙሀመድ ክልሉ በመደበው 10 ሚሊዮን ብር ችግረኛ ተማሪዎችን ለመመገብ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በተጨማሪም ከፌዴራል መንግስት በተመደበው ከ679 ሺህ ብር በላይ በጀት 10 ሺህ ያህል ተማሪዎችን ከየካቲት 19 ጀምሮ መመገብ ይጀመራል ብለዋል።

የሚኒስቴሩ የትምህርት ቤት ምገባ አስተባባሪ አቶ መኳንንት ሌሎቹም ክልሎች የምገባ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ክልሎች ለፕሮግራሙ የተመደበውን በጀት ለታለመለት ዓላማ ማዋላቸውን የሚከታተልና ድጋፍ የሚሰጥ ግብረ-ኃይል በፌዴራልና በክልል ደረጃ ተቋቁሞ እየሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የምገባ ፕሮግራሙ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ለማበረታታት፣ ለትምህርት አቀባበል መሻሻል፣ መጠነ ማቋረጥና መድገምን ለመቀነስና ለተማሪዎች አካላዊና አእምሯዊ እድገት ጉልህ አስተዋጾ እንዳለው ታምኖበታል።

ለአምራቾችና አቅራቢዎች የስራ እድል በመፍጠር ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋልም ተብሏል።

ፕሮግራሙ ወጥ በሆነ መንገድ እንዲመራ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑንና በቅርቡም ተግባራዊ እንደሚደረግ አቶ መኳንንት ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት7/6/2010 በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በየሚሲዎኖቹ በሚጀመረው የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት፣ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት እና የመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንዲያካሂዱ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።

 በመሆኑም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ምዝገባውን ለማካሔድ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ ላይ ናቸው።

 የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለኢዜአ እንደተናገሩት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን የልደት፣ የጋብቻና የሞት ሁኔታዎች ለመመዝገብ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች ተጠናቀው ስልጠናዎች እየተሰጡ ነው።

 ይህም ኢትዮጵያዊያኑ ባሉበት አገር የልደት፣ የጋብቻና የሞት ሁኔታዎቻቸው በየሚሲዎኖቹ የክብር መዝገብ ላይ እንዲያርፍ በማድረግና ማስረጃዎችን በመስጠት ከእንግልት እንዲድኑ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

 ሚኒስቴሩ አገልግሎቱን ለመጀመር በዋናው መስሪያ ቤት 40 ሰራተኞች ስልጠና የወሰዱ ሲሆን በየሚሲዮኖቹም ተመሳሳይ የክህሎት ስልጠና በቅርቡ እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።

 በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ የሆኑና ለምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶች እንዲሁም የምስክር ወረቀቶችን ጨምሮ የክብር መዝገቦችም ለየሚሲዮኖቹ መሰራጨታቸውን አስታውቀዋል።

 በፌዴራል የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የጥናት፣ የምርምርና የአሰራር ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ መኮንን እንዳሉትም ምዝገባው ከአገር ውጪም እንዲሰጥ ለሚኒስቴሩና ለሌሎችም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እንዲያካሂዱ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል።

 በዚሁ መሰረት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ የምዝገባ ጣቢያዎችን ከፍቶ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ስራውን ለመጀመር አስፈላጊ ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ ነው ብለዋል።

 ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት፣ ለባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትና  ለመከላከያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ሰነዶች ዝግጅት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል።

 ምዝገባው ለአገሪቱ ትልቅ መረጃ ነው፤ ከዚሁ መረጃ በመነሳትም ፖሊሲዎችን ለማውጣት፣ ደንቦችን ለማስቀመጥና መመሪያዎችን ለማዘጋጀት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ነው ያሉት። 

በመላው አገሪቱ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በ2009 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  የካቲት 7/6/2010 ቅዱስ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታውን ነገ ከአዳማ ከተማ ጋር ያደርጋል።

 ጨዋታው ከቀኑ 11 ሰአት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።

 የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ14ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር  መሰረት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረበት የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ቅደመ ዝግጅትና ጨዋታ ምክንያት መራዘሙ ይታወሳል።

 ከቻምፒዮንስ ሊጉ ጨዋታ ዝግጀት መልስ ቡድኑ ነገ ላለበት የፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ዝግጅት ማድረጉን የክለቡ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከነገው ጨዋታ በተጨማሪ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ሐዋሳ ላይ ከሐዋሳ ከተማ ጋር፣ የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም ከደደቢት ጋር የሚያደርጋቸው ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች አሉት።

 ክለቡ በሊጉ በአሁኑ ሰዓት በ21 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ያሉትን ተስተካካይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ከቻለ የሊጉ መሪ የመሆን እድል ይኖረዋል።

 በአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ የሚሰለጥነው አዳማ ከተማ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ያለው አጀማመር ጥሩ የሚባል ሲሆን እስካሁን ባደረጋቸው 14 ጨዋታዎች 22 ነጥብ በመሰብሰብ በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል።

 በዘንድሮው ዓመት በሜዳው አይበገሬነቱን እያሳየ ያለው አዳማ ከተማ እስካሁን በአዳማ አበበ በቂላ ስታዲየም ባደረጋቸው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሽንፈትን አላስተናገደም።

 በነገው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።

 የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ደደቢት በ28 ነጥብ አንደኛ፣ መቐለ ከተማ በ25 ነጥብ ሁለተኛ፣ ጅማ አባጅፋር አዳማ ከተማና ፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 22 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

Published in ስፖርት

አምቦ የካቲት 7/2010 ከሰብል ልማት ሥራቸው ጎን ለጎን በዓመት ለሁለት ጊዜ ከሚያመርቱት የማር ምርት ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን በንብ ማነብ ሥራ የተሰማሩ የምዕራብ ሸዋ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡ 

የቶኬ ኩታዬ ወረዳ አርሶ አደር ሞቱማ ዱጋሳ እንደገለጹት በንብ ማነብ ሥራ በመሰማራት በዓመት ሁለት ጊዜ ከሚቆርጡት ማር  ከአንድ የንብ ቀፎ በአማካይ እስከ 30 ኪሎ ግራም ምርት እያገኙ ነው፡፡

ከአንድ የምርት ስብሰባ የሚያገኙትን ማር በመሸጥ ብቻ ከ28 ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

የደንዲ ወረዳ አርሶ አደር ነገሪ ቶልቻ በበኩላቸው በዘመናዊ የንብ ቀፎዎች በመታገዝ እያከናወኑት ካለው የንብ ማነብ ሥራ በሚያገኙት ገቢ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ቀደም ሲል ከአንድ ባህላዊ የንብ ቆፎ ያገኙ የነበረው የማር ምርት ከአምስት ኪሎ ግራም የማይበልጥ እንደነበርና በባህላዊ ዘዴ የሚመረተው ማር ጥራት ዝቅተኛ በመሆኑ በገበያው የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በዘመናዊ የንብ ማነብ ቀፎ መጠቀም ከጀመሩ ወዲህ ከአንድ ቀፎ ከ28 እስከ 30 ኪሎ ግራም ማር በማግኘት በብዛትና በጥራት ተጠቃሚ በመሆናቸው ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የምዕራብ ሸዋ ዞን የእንስሳት ሀብት ጤናና ገበያ ልማት ጽህፈት በበኩሉ በዞኑ ከሰብል ልማት በተጓዳኝ በንብ ማነብ ሥራ ከተሰማሩ ከ19 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መካከል ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ማር ተሰብስቧል።

በጽህፈት ቤቱ የንብ ሃብትና ሀር ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ለቺሳ አንዳሉት ምርቱ የተሰበሰበው ከ103 ሺህ 588 ዘመናዊ፣ የሽግግርና ባህላዊ ቀፎዎች ነው፡፡

እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻም ከ1 ሚሊዮን 727 ሺህ ኪሎ ግራም ባላይ ማር ለማምረት መታቀዱንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አርባ ምንጭ የካቲት 7/2010 በአካባቢው በሚገኙ ጥብቅ ደኖችና ፓርኮች ይዞታዎች ውስጥ የሚነሳ የሰደድ እሳት ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን የጋምጎፋ ዞን  አካባቢ ጥበቃና ደን ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ኩማ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ በተለይ በማዜና ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርኮች እንዲሁም  ጉጌ ተራራ ስር የሚነሱ ቃጠሎዎች ብርቅዬ በሆኑ የዱር እንስሳትና እጽዋት ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው።

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ካለው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በተጓዳኝ  ለቃጠሎ ምክንያት በሆነው የሰደድ እሳት ክስተት መንስኤዎችና መከላከያ መንገዶች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱ እየተካሄደ ያለው በልማት ቡድኖችና  በአንድ ለአምስት አደረጃጀቶች አማካኝነት እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በዚህም በቅርቡ በማዜ ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተነሳው እሳት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በህዝብ ትብብር ፈጥኖ መቆጣጠር መቻሉን ጠቅሰዋል ።

የዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን  ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ካምቦ ዴሮ በበኩላቸው በአካባቢው ብሔራዊ ፓርኮችና ጥብቅ ደኖች ውስጥ ለሚነሳው ቃጠሎ በአብዛኛው ከሰው ንክኪ ጋር የተያያዘ መሆኑን አስታውቀዋል።

"ህብረተሰቡ  አዲስ ሳር  ያበቅላል በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እሳት በመልቀቅ፣ በህገ ወጥ ከሰል ማክሰልና ማገዶ ፍለጋ ለቃጠሎ መፈጠር ተጠቃሽ ምክንያቶች ናቸው " ብለዋል ።

ድርጊቱን ለመከላከል እየተከናነ ካለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በተጨማሪ ህገ ወጦችን ለመከላከል የሚደረገው ጥበቃ የተጠናከረ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።

Published in አካባቢ

ድሬደዋ የካቲት 7/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  አሁን ለደረሰበት ደረጃ የሰራዊቱ  አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ  የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የሰራዊቱ አባላት "የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሰላማችን ምንጭ ነው"  በሚል መሪ ሀሳብ ለህዳሴው ግድብ መሳካት የሚከፍሉትን መስዋዕትነት የፀና መሆኑን የሚገልጽ የሰልፍ ስነስርዓት ትናንት አካሂደዋል፤ ሠራዊቱ ለግድቡ መሳካት እያደረገ ለሚገኘው አስተዋጽኦ ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡

በዚህ ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ  ኢብሂራም ዑስማን የኢፌዴሪ የሠራዊት አባላትና የፀጥታ ኃይሎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  መሳካት ሌት ተቀን እያበረከቱ ያሉትን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡

ግድቡ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የሰራዊቱ  አስተዋፅኦም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ድጋፍ እስከግድቡ ፍጻሜ ድረስ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

በኢፌዴሪ አየር ኃይል የምስራቅ አየር ኃይል ምድብ አባል ጆይክ ይድነቃቸው ታፈሰ በበኩላቸው ሠራዊቱ ለግድቡ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

" እኔ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ለግድቡ ዕውን መሆን የምሰስተው ነገር የለም " ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ዳይሬክተር  ኮማንደር ብንያም ፍቅሩ " ሠራዊት ለግድቡ ግንባታ ቦንድ ከመግዛት ባሻገር እያከናወነ ለሚገኘው አበረታች ሥራ ሀገራዊ ዕውቅና መስጠቱ የሚበረታታ ነው" ብለዋል፡፡

ዕውቅናው ሰራዊቱ ለበለጠ ሥራና ውጤት እንደሚያነቃቃው ኮማንደሩ ጠቅሰዋል፡፡

በስነስርዓቱ ወቅት የህዳሴ ግድብ ግንባታ የድሬዳዋ የህዝብ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከፈለኝ አበራ በየደረጃው የሚገኘው የአስተዳደሩ ነዋሪ ለግድቡ ግንባታ እስከ አሁን ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በአስተዳደሩ የሚገኙ የአየር ኃይል የምሥራቅ አየር ኃይል ምድብ ፣  የድሬዳዋ ፖሊስ አባላትና አመራሮች በስነስርዓቱ ተሳትፈዋል፡፡

ሠራዊቱ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለውን  አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዋንጫ ሽልማት መዘጋጀቱም ታውቋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 7/2010 አስራ ሁለተኛው የናይል ቀን በዓል የካቲት 15 በኢትዮጵያ እንደሚከበር የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡    

ቀኑ በኢትዮጵያ ሲከበር ለሦስተኛ ግዜ ሲሆን ሚኒስቴሩ ከናይል (አባይ) ተፋሰስ አገራት ጋር በጋራ የሚያዘጋጀው ነው።

''ናይል የጋራ ኃብት ለዘላቂ ልማት ተባብሮ መስራት'' በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በሚከበረው በዚሁ በዓል ላይ የኢኒሼቲቩ አባል አገራት ይሳተፉበታል።

በዚህም የተፋሰሱ አገራት የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት፣ የኢኒሼቲቩ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚታደሙ ነው ሚኒስቴሩ የገለጸው፡፡          

ቀኑ የሚከበረው የካቲት 15 ቀን 1991 ዓ.ም በታንዛንያ ዳሬሰላም የናይል የትብብር ጅማሮ በተጋሪ ሀገሮቹ የተመሠረተበትን ዕለት ለመዘከር ነው፡፡

በበዓሉ ላይ በወንዙ ዙሪያ የተፋሰሱ አገራት ኃብቱን በጋራ ለመጠቀም እንዴት መስራት አለባቸው?፣ያሉ ችግሮች ምንድ ናቸው? በቀጣይ ምን መደረግ አለበት? በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት እንደሚመክር ይጠበቃል።  

በናይል ወንዝ ዘላቂ የውኃ አስተዳደርና ልማት የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩርና ''ለውጤታማ የናይል ትብብር የፖለቲካ ቁርጠኝነትን የሚያጎለብቱ አማራጮች''  በሚል መሪ ሀሳብ ሲምፖዚየም እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡ 

በበዓሉ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣የተፋሰሱ አገራት የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ተጋባዥ እንግዶች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። 

የማርሽ ባንድ፣የኪነጥበብ ሥራዎች፣የሕጻናት መዝሙሮች በዕለቱ ከሚቀርቡ ዝግጅቶች መካከል እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል። 

ኢትዮጵያ፣ግብጽ፣ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ኬኒያ፣ሩዋንዳ፣ደቡብ ሱዳን፣ሱዳን ፣ታንዛኒያና ኡጋንዳ የተፋሰሱ አባል አገራት ናቸው። 

 

 

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 7/2010 በደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት መንግሥት ለሁሉም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ጀምስ ፒ ሞርጋን ገለጹ።

በደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲት እና በተቀናቃኛቸው ዶክተር ሬክ ማቻር መካከል በተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ቢፈረምም በስምምነታቸው መቀጠል አልቻሉም።

በዚህም የተነሳ ደቡብ ሱዳናዊያን ሰላምና መረጋጋት ከራቃቸው ሰንብተዋል። 

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በገለልተኛ ወገን እንዲሁም በኢጋድ አደራዳሪነት ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ቢፈረሙም ተግባራዊ ባለመሆናቸው ሁለተኛው ምዕራፍ ድርድር በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ድርድሩ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ አንደኛው በተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ መግባባት፤ ሁለተኛው ደግሞ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሥልጣን ክፍፍል ማድረግ ነው።

የአገሪቷን ሁኔታና የድርድሩን ሂደትና ግብ በማስመልከት ኢዜአ በኢትዮጵያና በጅቡቲ የደቡብ ሱዳንን አምባሳደር እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት፣ የኢጋድና የመንግሥታቱ ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ቋሚ ተወካይ ከሆኑት ጀምስ ፒ ሞርጋን ጋር ቆይታ አድርጓል።

አምባሳደር ሞርጋን እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያለውን ግጭት ለማስቆምና ዘላቂ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን መንግሥት ለመላው ተቃዋሚ የፖለቲካ አባላት የሥልጣን ክፍፍል ለማድረግ ፍላጎት አለው።

ለችግሩ እልባት ለመስጠት መንግሥት የልዑካን ቡድኑን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁለተኛው ምዕራፍ የእርቅ መድረክ መካሄድ ጀምሯል።

“በደቡብ ሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ ለመስማማት መንግሥት ዝግጁ ነው፤ ሁሉም በዚህ እንዲስማማም ውይይቱ ተጀምሯል” ነው ያሉት አምባሳደሩ።

በአደራዳሪው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) አማካኝነትም ችግሩን ለመፍታት የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር ሀሳብ በመቅረቡ መንግሥት ይህን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። 

 “ሁለት የተለያዩ ወታደራዊ ኃይል ያለው አገር የለም” ያሉት አምባሳደር ሞርጋን፤ ከሁሉም ወታደራዊ ቡድኖች የተውጣጣ አንድ ብሔራዊ ወታደራዊ ኃይል ለማቋቋም መግባባቱ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። 

"ደቡብ ሱዳናዊያን ዴሞክራሲን ተርበዋል፤ መሪያቸውንም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጥ ይፈልጋሉ፤ በመሆኑም ይህን ለማድረግ መጀመሪያ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን በዘላቂነት የተኩስ አቁም ስምምነቱ ላይ መግባባት ያስፈልጋል" ብለዋል።

በአገሪቷ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ነፃ ምርጫ ለማካሄድ መጀመሪያ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ከኢጋድና ሌሎች ገለልተኛ ወገኖች የቀረበውን ሀሳብ መንግሥት እንደሚቀበልም አምባሳደር ሞርጋን ገልጸዋል። 

በአገሪቷ ሙሉ በሙሉ ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነና የሕዝብ ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውሳኔ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት እንደሚመሰረትም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለድርድሩ እንደ ኢጋድ አባልነትም እንደ ጎረቤትም ላበረከተችው ትልቅ አስተዋጽኦ አምባሳደሩ ምስጋና አቅርበዋል።

ደቡብ ሱዳናዊያን ጥር 28 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የጀመሩት ሁለተኛ ምዕራፍ ድርድር አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በተካሄደው ስምምነት ሁለቱ ወገኖች በሥልጣን ክፍፍል ላይ መስማማታቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በዚህም የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ቡድን 53 በመቶ የሚሆነውን የካቢኔ ወንበር፤ የዶክተር ሬክ ማቻር ቡድን ደግሞ 33 በመቶ እንዲይዝ መወሰኑ የሚታወስ ነው። 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን