አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 13 February 2018

ጋምቤላ የካቲት 5/2010 የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል የክልሉን መንግስት የሚመራው  የጋምቤላ ህዝቦች አንድነት ዴምክራሲያዊ ንቅናቄ / ጋህአዴን / አስታወቀ።

በጋምቤላ ከተማ ለአራት ቀናት ሲካሄድ የቆየው  የጋህአዴን ድርጅታዊ  ኮንፍረንስ  የአቋም መግለጫ በማውጣት ትናንት ተጠናቋል።

በዚሁ አቋም መግለጫ እንደተመለከተው የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች፣ አድርባይነት ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የህዝብ ወገንተኝነት መሸርሸር በድርጅቱ የጥልቅ ተሀድሶ ወቅት የተለዩ ችግሮች ነበሩ፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የተለዩት እነዚህን ችግሮች በመፍታት የህዝቡን  ጥያቄዎችን ለመመለስ በተከናወኑት ስራዎች ለውጦች ቢኖሩም በተፈለገው ልክ እንዳልሆነ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በአቋም መግለጫው አውስተዋል።

በተለይም የመሬት አስተዳደርና አቅርቦት፣ የመንግስት በጀት አስተዳደር፣የትምህርት ጥራት፣ የፍትህ አገልግሎትና የንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚስተዋሉት ችግሮች ዛሬ ላይም የድርጅቱ ፈተናዎች ሆነው እንዳሉም ተጠቁሟል።

የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ ችግሮችንና በህዝቡ እየተነሱ ያሉትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት የተጀመረውን ስራ አጠናክረው ለመቀጠል  አመራሮችና አባላቱ  ቃል ገብተዋል።

የወጣቶችና የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጡ ስራ  ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫ አድረገው  ለመንቀሳቀስ መዘጋጀታቸውንም በአቋም መግለጫቸው አረጋግጠዋል፡፡

በክልል ለተጀመሩ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የህዳሴ ጉዞ መሰናክል እየሆኑ ያሉትን የሙስናና ብልሹ አሰራር ፣የአድርባይነት፣ የጠባብነትና ሌሎች ችግሮችን አምርረው ለመታገልም ቃል ገብተዋል።

በክልሉ ያለውን ሰላምና ልማትን በዘላቂነት በማስቀጠል  የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች ሌላው የድርጅቱ አመራርና አባላት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ከድርጅቱ አመራሮች መካከል ዶክተር ሎው ኡቡፕ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት የጤናና የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑት ስራዎች  አበረታች ቢሆኑም በጥራት ረገድ ከፍተኛ ክፍተቶች እንዳሉ  ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማስቀረት በሁሉም መስክ   ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ያመለከቱት ደግሞ  ሌላው የድርጅቱ አመራር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ናቸው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ጋትሉዋክ ቱት በኮንፈረንሱ ማጠቃለያ  "በየደረጃው የሚገኙ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በህዝቡ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

 

Published in ፖለቲካ
Tuesday, 13 February 2018 23:43

ገደብ የሌለው ባለ ራዕይ

          በአቢብ አለሜ/ኢዜአ/

መሃል አዲስ አበባ ካዛንችስ አካባቢ ነኝ።ከውጪ ለሚያያት አልፎ ሂያጅ ደሳሳ መሳይ በሯ ላይ የሳር ክፍክፍ ያለባት ቤት ውስጥ እግሬ ገብቷል።

በዚህች ቤት መገኘቴ ያላንዳች አይደለም፤ ትልቅ ጉዳይ ነበረኝ። የኢትዮጲያን ሙዚቃ ለዓለም መድረክ በማስተዋወቅ ላይ ያለ አንድ የባሕል ቡድን መሪና ተወዛዋዠን ስለ ኪነ ጥበብ ለማውጋት ነበር።

ፈንድቃ የሚል ጽሑፍ ከሳር ክፍክፉ ላይ ማንበቤን ሳስታውስ እውን ከዚህ ቤት ነው ይሄንን ያህል ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ሙዚቀኞች መፍለቅ የቻሉት ስል ራሴን ጠየቅሁ።

ፈንድቃ ለሚለው ቃል ስቃ፤ ተደስታ፤ ዘና ባለ ስሜት ሆና፤ ፊቷን በፈገግታ ሞልታ የሚል ክርክር አልባ ትርጓሜ ሰጥተነው ልናልፍ እንችላለን።

ነገር ግን ፈንድቃ በጎጃምና በጎንደር መካከል የምትገኝ ቦታ ሥያሜ ነው። ታድያ ምሽት ቤቱ ይህንን ስያሜ እንደያዘ ለ27 ዓመታት ባሕላዊ ሙዚቃን በማቅረብ የዘለቀ፤ የኢትዮጲያን ቀደምት ባሕላዊ የአዝማሪ ሙዚቃ ለቀሪው ዓለም በማስተዋወቅ የተጓዘ ትልቅ ባህላዊ የምሽት ቤት ነው።

ጠባቧንና ምሽት ላይ መውጫ መግቢያ የሚጠፋባትን ነገር ግን ቱባ ባህል የሚቀዳባትን የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት አቋርጠን ያሸበረቁ ባሕላዊ እቃዎችና ስእሎችን እያየን ከመላኩ በላይ ጋር ወደ ጓሮ በር አለፍን።

ወደ ጓሮ ያቀናነው ልንነጋገርበት ያሰብነውን ጉዳይ ዘወር ብለን ሳንረበሽ ለመከወን እንዲያመቸን በማሰብ ነበር።

ወደ ጀርመን ለመሄድ ሲጣደፍ ነበር በተጣበበ ጊዜ ውስጥ ያገኘሁት። ጸጉሩ የቀድሞ አርበኛ መሳይ ነው። ጠጋ ብላችሁ ስታወሩት ደግሞ ያ ቴሌቪዢን ላይ ወይም በአካል ሲጨፍርና ሲወዛወዝ ያያችሁት ወጣት አይመስላችሁም። ትሑት፤ፈገግታና እርጋታ የሞላው ሆኖ ታገኙታላችሁ።

ቁጭ ብለን መጨዋወት ጀምረናል። ከተቀመጥንበት ጎን ፈንጠር ብለው ማሲንቆ የያዙ ወጣቶች ጢሪሪሪ--- ጢሪሪሪ እያደረጉ ይገርፉታል። ለምሽት መርሀ ግብራቸው ልምምድና ጥናት ላይ መሆናቸው ነው።

መላኩ ማሲንቆ ወደ ያዘ አንድ ታዳጊ ወጣት እያመላከተ "እየው ይሄንን ልጅ" አለኝ፤ ልጁ 15 ዓመት ገደማ የሚሆነው ቀይ ለግላጋ ነው። "ከላሊበላ ነው መንገድ ላይ ሲጫወት አግኝቼው ያመጣሁት አሁን ጎበዝ ተጫዋች እየሆነ ነው" አለኝ። የኪነ ጥበብ ተተኪዎችን የማፍራት ጽኑ ፍላጎት እንዳለውም አወጋኝ።

እየተጨዋወትሁ ያለሁት ለ20 ዓመታት ያህል በፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት ውስጥ ተወዛዋዥ ሆኖ የሰራና አሁን ላይ "ኢትዮ ከለር" የተሰኘ ባሕላዊ የሙዚቃ ባንድን መስርቶ፤ ቤቱን በአዲስ መልክ በማስፋፋት በባለቤትነት እየሰራ ካለው የሙዚቃ ሰው፣ ዳንሰኛና ተወዛዋዠ መላኩ በላይ ጋር ነው።

መላኩ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ነው፡፡ የትኛውም ትምህርት ቤት ገብቶ ውዝዋዜን አልተማረም። ከእስክስታ ጋር ያስተዋወቁት ልዩ ልዩ የህዝብ በዓላት፣ ጥምቀትና ሠርግ ቤቶች ናቸው፡፡ የእርሱን የህይወት ታሪክ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዳሰውታል። አምስት ዶክመንተሪ ፊልሞች ተሰርተውለታል፡፡

በፈንድቃ የባህል ምሽት ቤት 12 ዓመታት በታዳሚ ሽልማት ብቻ ሰርቷል። ሌላ ቦታ ተቀጥሮ መስራት ቢችልም ነፍሱ ጋር የተጣባችው እስክስታ ከፈንድቃ እንዲርቅ አልፈቀደችለትም።

በኋላም የኢትዮጵያ ባህልና ማንነት ሳይበረዝና ሳይከለስ ዓለም እንዲያውቀው የማድረግ ትልቅ ውጥን ይዞ ተነሳ፡፡ ተሳክቶለትም ወጣት አዝማሪዎችን ከቴአትር ቤትና ከፈንድቃ የባሕል ምሽት እየወሰደ በአሜሪካ፤ በአውሮፓ፤ በአፍሪካ፤ በሩቅ ምስራቅ አገራት ተዘዋውሮ አገሩን በስፋት አስተዋውቋል።

ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኪነ ጥበብ አውደ ርዕይ ማሳያ ማዕከል መስርቶ የስዕል፤ የቅርጻ ቅርጽና የንድፍ ስራዎቻቸውን ማሳየትና ማስተዋወቅ የሚፈልጉ ግለሰቦችና ወጣቶች በየወሩ ስራዎቻቸውን በነጻ እንዲያቀርቡበት አድርጓል።

በዚህ የኪነ ጥበብ ማሳያ ማዕከል ቀድሞ ስራዎችን የሰሩና አሁን በጡረታ ላይ ያሉ የኪነ ጥበብ ሰዎች፤ እንዲሁም መድረክ ያጡ በርካታ የፈጠራ ስራዎች ያሏቸው ወጣቶች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ዕድል ተመቻችቶላቸዋል።

በዚህ ማዕከል በወር አንድ ጊዜ ስለ ንባብ  ውይይት የሚደረግበትና የግጥም ዝግጅቶች የሚቀርቡበት መድረክ በማዘጋጀትም ሕብረተሰቡ ለንባብና ለኪነ ጥበብ ያለው ስሜት እንዲነሳሳ እያደረገ ይገኛል።

ጭፈራን በራሱ መንገድ መጫወት እንደሚያስደስተው የሚናገረው የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ባለቤት መላኩ በላይ "በሰውነቴ እንቅስቃሴና በጭፈራዬ ሁኔታዎችን እገልጻለሁ"ይላል። ሲጨፍር በሰውነቱ ጊዜን፤ ሀዘንን፤ ደስታን፤ ችግርን፤ እለታዊ ሁኔታውን መግለጽ እንደሚያስደስተውም ይናገራል።

በሰው ውስጥ ያለውን ስሜት፣ያስደሰተውን ጉዳይና ልዩ ልዩ ሁነቶችን በራሱ መረዳት መጠን ከምንም አይነት ድምጽ ጋር አዋህዶ በውዝዋዜ መግለጽ መቻሉ የመላኩ ትልቁ ችሎታው ተደርጎ ይወሰድለታል።

ለዚህም መርካቶ ምናለሽ ተራ አካባቢ ካሉ ብረት ቀጥቃጮች ጋር የሰራው ውዝዋዜ፤ ስሜትን አንዴት አድርጎ ከድምጽ ጋር ማዋሐድ እንደሚቻል አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።

"አሁን" የሚል ስያሜ በሰጠው በዚህ ዝግጅቱ ላይ ሁሉም ብረት ቀጥቃጮች የራሳቸውን ስራ እየሰሩ፤ ትልቁ ስራና ሐላፊነት ድምጽን ሙዚቃ የማድረጉ ተግባር ደግሞ በተወዛዋዡ ላይ የወደቀ እዳ ነበር።

የብረትና በርሜል ድምጽን ወደ ሙዚቃነት መቀየር ከባድ እንደሆነ ቢታወቅም እኔ ግን ስሜቴንና ሙዚቃን ለማገናኘት ተጠቅሜበታለሁ ይላል።"የሰውነት ቋንቋ ሙዚቃን ሰዎች አውቶቡስ ላይ ሲሄዱ፤ መብራት ሲሰሩና ሌሎች ተግባራትን ሲከውኑ መስራቱንም ይናገራል።

እሱ በተወዛዋዥነትና በመሪነት ኢትዮ ከለር ባንድ ደግሞ አጃቢ በመሆን በርካታ ሙዚቃዎችን ለዓለም ህዝብ አቅርቧል፤ አሁንም እያቀረበ ይገኛል።

በነዚህ ስራዎቹ የራስን ቀለም ለማሳየት ይረዳው ዘንድም የአገሪቷን የተለያዩ ሙዚቃዎች ባሕርያትና ምንነት ጥናት ማድረጉንም ይናገራል።

ይሁን እንጂ የብሔረሰብ ሙዚቃዎችን እንደ ማሕበረሰቡ አድርጎ መስራት ባይቻልም እንኳን የኢትዮጲያን ሙዚቃ፣ ባሕል፤ ታሪክ ማንነቱን ሳይለቅ በራሱ መንገድ ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቁን ይገልጻል።

ኢትዮጵያ የረሀብና የችግር መግለጫ ተደርጋ መጠቀሷ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን በመጥቀስ ይህንን መጥፎ ምስል ለመቀየር ትልቅ ስራ ሰርተናል ሲል በኩራት ይናገራል።

አሁንም ገና ብዙ ስራዎች የሚጠበቁን በመሆናቸው በሙዚቃ አማካኝነት እየሰራን ያለነውን የገጽታ ግንባታ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ይላል።

መላኩ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያቀረባቸው የሙዚቃ ስራዎች በርካታ የውጪ ሀገራት ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና በሙዚቃው፤ በአኗኗሩ፤ በኪነ ጥበቡ ላይ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ ምክንያት መሆኑንም አጫውቶኛል።

ከማንም፤ ምንም ነገር እንደማይጠብቅና ሁልጊዜ ከለውጥና ከአዳዲስ ነገሮች ጋር በፈጠራ መንገድ መጓዝ እንደሚያስደስተው ይናገራል። "ለምወደውና ላመንኩበት ነገር መኖር የሕይወቴ መርኅ ነው" ይላል።

"ራእይ ማብቂያና ገደብ የለውም" የሚለው መላኩ አሁንም በቻይና፤ በርሊን፤ ሮም፤ ፓሪስ፤ ቶኪዮና ኒዮርክ የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ቅርንጫፍ ከፍቶ ኢትዮጲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ሕልም አለው።

በየክፍላተ አህጉራቱ ሁሉ ፈንድቃ የባሕል ምሽት ቅርንጫፍ እንዲኖረው እፈልጋለሁ የሚለው መላኩ ቀጣይ በናዝሬት፤ ባሕርዳር፤ በደብረ ማርቆስ፤ ጎንደር፤ ላሊበላ፤ ሐዋሳ፤ አርባ ምንጭና በሌሎችም አካባቢዎች ከፍቶ ባሕልንና ማንነትን ማስተዋወቅና፤ የሕብረተሰቡን የኪነ ጥበብ ፍላጎት የማርካት ብርቱ ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል።

ፈንድቃን በሀገር ውስጥ የማስፋፋቱ ዋና ምክንያትም በተለያዩ አካባቢዎች ላሉ ወጣት አርቲስቶች እድሉን ለማመቻቸት፤ ለሙዚቃ ያላቸውን ፍላጎት ለማነሳሳት፤ ያላቸውን ነገር እንዲወዱት ለማድረግ፤ ያደጉበት ባሕል ትልቅ ዋጋ እንዳለው እንዲገነዘቡ ለማስቻል መሆኑን ይናገራል።

ተተኪ ወጣቶችን ለማፍራት ያለውን ጽኑ ፍላጎት እውን ለማድረግ ሁነኛ አማራጭ መሆኑንም ያብራራል። ፈንድቃ ኢላማ አድርጎ የተነሳው ባሕልን በኪነ ጥበብ ለማበልጸግ ነው የሚለው መላኩ ሁልጊዜ ራሳችንን መመልከትና ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ አትኩረን መስራት ይገባናል ይላል።

ኢትዮጵያ ብዙ የሚያኮራ ባሕል፣ ታሪክ፤ ሙዚቃና ማንነት ያላት አገር በመሆኗ እነዚህን ሀብቶቿን ለማጉላትና ለማስተዋወቅ በኪነ ጥበብ ዘርፍ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚቻልና እንደሚገባም ጭምር ይገልጻል።

በዚህ ረገድ አዝማሪዎች እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ያብራራል። አንድነት፤ ቁጭት፤ ፍቅር፤ ሰላም፤ ተስፋ፤ ደስታ፤ ብልጽግና፣ ማስታረቅ፤ ታሪክን ስለመጠበቅ፤ ጎጂ ነገሮችን ስለመቅረፍ፣ አገርን ስለመጠበቅ ወዘተ ያሉ ጉዳዮች አዝማሪዎች ልዩ ትኩረት አድርገው የሚሰሩባቸው ጭብጦች መሆናቸውን በማሳያነት ያነሳል።

ይሁን እንጂ አዝማሪዎች ከሙዚቃ አድማጩና ተመልካቹ የሚያገኙት ገንዘብ ሕይወትን ለመደጎም የሚበቃ ባለመሆኑ በፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ውስጥ የሚሰሩ አዝማሪዎችን በወር 2ሺሕ ብር እየከፈላቸው ይገኛል።

ዓለም አቀፍ እውቅናና ተፈላጊነት ያለው ፈንድቃ የባሕል ምሽት በሰራቸው አያሌ ስራዎች በፈረንሳይ የባሕል ሚኒስቴር የክብር ሜዳልያ ሽልማትና እውቅና ተበርክቶለታል።

"እያገኘን ያለነው ዓለም አቀፍ እውቅና ቢያስደስትም መንግስት ሀገራዊ ባሕልን ለመደገፍ የሚያደርገው እንቅስቃሴ አናሳ መሆኑ ግን ያሳዝነኛል" የሚለው መላኩ ለባህልና ኪነጥበብ ትኩረት መሰጠት አለበት ይላል።

ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፈንድቃን እንደማያውቀው በመጥቀስ ዓለም አቀፍ ብዙኋን መገናኛ የሆኑት ቢቢሲ፤ ሲኤንኤን እና ሌሎችም እየመጡ  ሲዘግቡ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት አለመስጠቱ  እንደሚያሳፍረውም ገልጿል።

ለ20 ዓመታት ባሕልን፤ ሙዚቃን፤ ኪነ ጥበብንና ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ብዙ የተጓዘው መላኩ በርካታ ችግሮችን በግሉ ተቋቁሞ አልፏል። "መንግስት ምን ችግር አለብህ ብሎ ቢጠይቀኝና ቢረዳኝ የት በደረስኩ ነበር" ሲልም ቁጭት አዘል ጥያቄውን ያክላል።

እኔም "ራእይ ማብቂያና ገደብ የለውም" የሚለው መላኩ ተተኪ ወጣቶችን በማፍራትም ሆነ ኪነ ጥበብን በማስተዋወቅ ረገድ ሊሰራ ያሰበው እንዲሳካለት በመመኘት ቱባ ባህል የሚቀዳባትን የፈንድቃ የባሕል ምሽት ቤት ተሰናብቼ ወጣሁ።

 

Published in መጣጥፍ

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 እስክንድር ነጋና አንዱዓለም አራጌን ጨምሮ 746 ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋረጦ ነገ እንደሚለቀቁ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ገለጸ።

በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጉርሜሳ አያና፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጌቱ ጋሩማ፣ አቶ ተስፋዬ ሊበን እና አቶ በየነ ሩዳ ክሳቸው ተቋርጦ ዛሬ ተለቀዋል።

ታራሚዎቹ እና ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ እንዲለቀቁ የተደረገው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ጉዳያቸው ሕጉ በሚፈቅደው መሰረት እየታየ እንዲለቀቁ በወሰነው መሰረት ነው።

ይቅርታ የሚደረግላቸው ሰው በመግደል፣ ከባድ የአካል ጉዳት በማድረስ፣ የአገር ኢኮኖሚ ለማውደም በመሳተፍ፣ ህገ መንግስቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር ወንጀል ያልተሳተፉ ፍርደኞችና ተከሳሾች እንደሆነ ተገልጿል።

በዚሁ መሰረት በፌደራል ደረጃ በሽብር፣ በሁከትና ብጥብጥ፣ በሀይማኖት አክራሪነትና በተለያዩ ወንጀሎች ክሳቸው በሒደት ላይ የሚገኙና የእስር ቅጣት ተላልፎባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ 417 ታራሚዎች ነገ ከማረሚያ ቤት ይወጣሉ።

በተመሳሳይ ጉዳያቸው በህግ በመታየት ላይ የነበሩ 329 ተጠርጣሪዎችም የተሃድሶ ስልጠናውን ጨርሰው ነገ እንደሚለቀቁ ገልጿል።

 

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር የካቲት 6/2010 በሀገሪቱ  ተራቁቶ የነበረ  ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር  በላይ  መሬት በደን መሸፈኑ የአካባቢ፣ የደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ አስታወቀ።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የክልሎች  የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሰድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የሚገመግም መድረክ  በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ውቅት በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  የተራቆተ መሬትን በደን የመሸፈን ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረገው ጥረትም አካባቢያዊ ስነ ምህዳር መሰረት ያደረገ ችግኝ መተከሉን ጠቁመው በዚህም ከአንድ ሚሊዮን 300ሺህ ሄክታር  በላይ  ሄክታር በላይ መሬት በደን  መሸፈኑን ተናግረዋል።

የተራቆተ መሬት ለይቶ መልሶ በደን የማልበስ ስራ በሀገሪቱ በስፋት የሚከናወነው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መሆኑን ጠቁመዋል።

የተፋሰስ ስራዎች ዘላቂነት ያለው ለውጥ ለማምጣት በሚያስችል መልኩ እንዲፈፀሙ በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያ የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንዳለባቸውም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ባለፈው ክረምት በ664 ሺህ ሄክታር በተራቆተ መሬት ላይ የተተከለው  ሶስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን  ችግኝ ውስጥ  70 በመቶ መጽደቁን የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የደን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ከበደ ይማም ናቸው።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጀመሪያ 15 ነጥብ አምስት በመቶ የነበረውን የሀገሪቱን የደን ሽፋን በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 20 በመቶ ለማድረስ ግብ መያዙንም አስታውቀዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳላት የሚተከል ችግኝ  የመፅደቅ ምጣኔ እንዲጨምር  አርሶ አደሩ ተገቢ  ጥበቃና እንክብካቤ ማደረግ የሚያስችለው  ተከታታይ የግንዛቤ  ስራ እየተከናወነ ነው።

"በሀገሪቱ የደን ውድመትን ለመቀነስም በግማሽ ዓመቱ ከ535 ሺህ የሚበልጡ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ለተጠቃሚዎች እንዲሰራጭ ተደርጓል" ብለዋል።

በመጪው የክረምት ወቅትም ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት ላይ ለማልማት የችግኝ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል።  

የአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና ዱር እንስሳት ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ በበኩላቸው ከአካባቢው ጋር ፈጥኖ የሚላመድ የደን ችግኝ  አርሶ አደሩ አልምቶ እንዲጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በተለይ፣ በአዊና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች የሚገኙ አርሶ አደሮች ደንን በስፋት በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደጀመሩም ጠቅሰዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው የገምገማው መድረክ የሚኒስቴሩና የሁሉም ክልሎች ያለፉት ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት እንደሚካሄድ ተመልክቷል።

 

 

 

Published in አካባቢ

ጭሮ የካቲት 6/2010 በአካባቢያቸው ባጋጠማቸው የንፁህ የመጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶና ጭሮ ወረዳዎች አስተያየታቸውን የሰጡ  ነዋሪዎች ገለጹ።

በጭሮ ወረዳ የጋራንጉስ  ቁጥር ሁለት ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል  ወይዘሮ ሙሉካ ዩያ እንዳሉት በአካባቢው ጎልብቶ የነበረው  ምንጭ በመድረቁ የሶስት ሰዓት መንገድ በመጓዝ የኩሬ ውሃ  እየቀዱ ለመጠቀም ተገደዋል።

"ከነ ቤተሰቤ ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ ለመጠጣት በመገደዳችን  ለውሀ ወለድ በሽታ ተጋልጠናል" ያሉት ወይዘሮ ሙሉካ ችግሩ በተለይ በህጻናት ላይ እንደሚብስ ተናግረዋል ።

መምህር ካሳሁን መርጋ በበኩላቸው የንፁህ መጠጥ ውሀ እጦት ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።

"መምሀራን አንድ ባለ 20 ሊትር ጀሪካን ውሃ በ20 ብር እየገዛን እየተጠቀምን ነው " ያሉት መምህሩ ወሀ ፍለጋ በየእለቱ ረዥም መንገድ በመጓዝ  የመማር ማስተማር ስራው እየተስተጓጎለ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ በሚኤሶ ወረዳ የሁሴ ቀበሌ ነዋሪ ተማሪ ብርሃን ኪዳኑ እንደገለጸው  ቤተሰቦቹን ለመርዳት ንጽህ የውሃ ለመቅዳት ሲል ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል።

በወረዳው የሀሙስ ገበያ ጤና ጣቢያ ሲስተር ኢየሩስ ደምሴ በሰጡት አስተያየት በየቀኑ ከሚመጡ ታካሚዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ንፅህናው ባልተጠበቀ ውሀ በመጠጣት ህመም ያጋጠማቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የዞኑ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጁዋር ጠሃ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው የውሀ ችግር በመኢሶና ጭሮ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ወረዳዎች መኖሩን ገልጸዋል።

በወረዳዎቹ  ከዚህ ቀደም  የጎለበቱ ምንጮች ውሀ የማመንጨት አቅማቸው በመቀነሱ ችግሩ መከሰቱን ጠቁመዋል ።

"ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በሁለቱም የወረዳ ቀበሌዎች የተጀመሩ የአንድ ጥልቅ ጉድጓድ ቁፋሮና የአንድ ምንጭ ማጎልበት ስራዎች በበጀት እጥረት መቋረጣቸው ለውሀ እጦቱ መባባስ ሌላው ምክንያት ነው" ብለዋል ።

ችግሩ በከፋባቸው ቦታዎች ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት አስር ቦቴ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው የውሀ እደላ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል ።

እንደ አቶ ጁዋር ገለጿ የተቋረጠውን የውሀ ተቋማት ስራ ለማስጀመር ለኦሮሚያ  የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሃብት ልማት ቢሮ የበጀት ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  የካቲት 6/2010 ኢትዮጵያ የአፍሪካን ግጭቶች አስመልክቶ በመንግሥታቱ ድርጅት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ አዎንታዊ ጫና እያሳደረች መሆኑን በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ ዶክተር ተቀዳ አለሙ ገለጹ።  

 ዶክተር ተቀዳ አገሪቷ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው አንድ ዓመት ያከናወነቻቸውን ሥራዎች አስመልክቶ ከኢዜአ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። 

 ዶክተር ተቀዳ ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ውስጥ የአፍሪካን ጉዳይ በአንክሮ ስትከታተል መቆየቷን ነው የተናገሩት።

 በፀጥታው ምክር ቤት ከተመረጠችበት ጊዜ ጀምሮ ከአህጉሪቱ አባል አገራት ጋር በመሆን የጋራ አቋም በማንጸባረቅ እየሰራች መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 በተለይም በአፍሪካ የጸጥታ ችግር በሚታይባቸው አገራት ምክር ቤቱ በሚያስተላልፈው ውሳኔ ላይ አዎንታዊ ጫና በማሳደር ጥረት እያደረገች መሆኑን ጠቁመዋል።

 ግጭት በተከሰተባቸው በተለይም በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳንና በዳርፉር አካባቢዎች እስካሁን በምክር ቤቱ የተላለፉትን ውሳኔዎች ለአብነት አንስተዋል።

 በቀጣይም የሱዳንና የሶማሊያ ጉዳይ ምክር ቤቱ ትኩረት የሚያደርግባቸው የአህጉሪቱ የጸጥታ ጉዳዮች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

 በምክር ቤቱ በተለይም ሠላምና ደህንነትን በተመለከተ በርካታ አስቸጋሪ ጉዳዮች ተገናዝበው ውሳኔዎች መተላለፋቸውን አስረድተዋል።

 ዶክተር ተቀዳ "በምክር ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፍ ከባድ ሆኗል፤ ይህ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የፖለቲካ ሁኔታና የኃይል ሚዛን መለወጥን ተከትሎ የመጣ ነው" ብለዋል።

 ያም ሆኖ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በምክር ቤቱ ከነበራት አባልነት በላቀ ሁኔታ ኃላፊነቷን በአግባቡ እየተወጣች መሆኑን ነው የገለጹት።

 በተለይም በጸጥታ ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ወታደር ከሚያዋጡ አገራት መካከል ቀዳሚውን ደረጃ መያዟንና በዚህም በምሳሌነት እንደምትጠቀስ አስረድተዋል።

 በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካ ውስጥ ልዩነት መፍጠር የምትችል አገር እንደሆነችም ጠቅሰዋል።

 ኢትዮጵያ በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ስትሆን የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

 ከዚህ ቀደም እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ከ1968 - 1969 እንዲሁም ከ1989 - 1990 ድረስ ለሁለት ጊዜ በአባልነት አገልግላለች።

Published in ፖለቲካ

በሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች በተያዘው የበጋ ወቅት አርሶ አደሩን በማሳተፍ ከ65ሺህ  ሄክታር በላይ  የተጎዳ መሬትን ለማልማት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን  የደን ልማት ባለሙያ አቶ መሀመድ አብደላ እንደገለጹት እስከ የካቲት 20/2010ዓ.ም በሚቆየው የልማት ስራ በጥናት በተለዩ 543 ተፋሰሶች ውስጥ ስራው የሚከናወን ሲሆን 388 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

እየተካሄዱ ካሉት ስራዎች መካከል የማሳና የጋራ ላይ እርከን ፣ የእርጥበት መቆያ ፣ ፣የክትር ስራ እና የውሃ ማሰባሰቢያ ኩሬ ቁፋሮ ይገኙበታል።

በዋድላ ወረዳ የቀበሌ ዜሮ ሁለት  አርሶ አደር ሰጠ በላይ በሰጡት አስተያየት የተከለሉ ቦታዎችን የአካባቢያዊ ህግ በማውጣት ከሌሎች ጋር በመሆን የመጠበቅና የመንከባከብ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች  የተጎዳው መሬት እያገገመ መሆኑን ጠቅሰው ልማቱ በተሰራባቸው የወል ይዞታዎችና የማሳ ዳር መሬት ለእንስሳት መኖ እየጠቀማቸው  መሆኑን ገልፀዋል።

ተፋሰስን መሰረት በማድረግ በተደጋጋሚ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  አርሶ አደሩ ተጠቃሚ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በላስታ ወረዳ የቀበሌ 23  ነዋሪና የተፋሰስ ኮሚቴ ጸሐፊ አርሶ አደር እንዳየነው ወርቀልኡል ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በሰሜን ሸዋ ዞን በ931 ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው እየተከናወነ እንደሚገኝ የገለፁት ደግሞ በዞኑ ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም የስራ ሂደት መሪ አቶ ጌታነህ ሳህለ ማሪያም ናቸው።

በተፋሰሶች ውስጥም 35 ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንና  ከ437 ሺህ በላይ ህዝብ እየተሳተፈበት እንደሚገኝ አስታውቀዋል ፡፡

በሚለማው  መሬት ላይ በመጪው  የክረምት ወቅት የሚተከል  350 ሚሊዮን የእንስሳት መኖና  የደን ችግኝ እየተዘጋጀም መሆኑም ጨምረው አመልክተዋል፡፡

 

Published in አካባቢ

ደሴ የካቲት 6/2010 በደሴ ከተማ በተለምዶ ፒያሳ ጨው ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሰዓታት በፊት የተነሳ ከባድ የእሳት ቃጠሎ ለጊዜው ቁጥራቸው ባልታወቀ ቤቶች ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑንፖሊስ ገለጸ።

በከተማው አንደኛ ፖሊስ ጣቢያ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ጌታቸው ምህዬ እንደገለጹት ከጥቂት ሰዓት በፊት የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በአካባቢው ቤቶች ላይ ሰፊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል።

የቃጠሎም መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ገልጸው በአሁኑ ሰዓት የኮምቦልቻ እና የደሴ ከተሞች እሳት አደጋ መከላከል ግብረ-ኃይል አደጋውን ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው እንደተመለከተው የእሳት ቃጠሎው እየቀነሰ ቢሆንም በትንሹ ከ10 ያላነሱ ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የአደጋው የጉዳት መጠንና ዝርዝር መረጃ እንደደረሰን እናስታውቃለን።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 የኢትዮጵያና አርጀንቲና የሁለትዮሽ ግንኙነት በሁሉም መስኮች ሊጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ከአርጀንቲና አቻቸው አምባሳደር ፔድሮ ዴልጋዱ ጋር ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው መክረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የሁለቱን አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጎልበት የሁለትዮሽና የባለብዙ ዘርፍ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ሊጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህም አገራቱ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በግብርና፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአየር ትራንስፖርት መስኮች ለመስራት የጀመሯቸውን ሰምምነቶች ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተያዘው የአውሮፓዊያን ዓመት መጋቢት 8 ወደ አርጀንቲና ቀጥታ በረራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአገራቱን ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ጉልህ ድርሻ ይጫወታል ብለዋል።

የአርጀንቲና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ፔድሮ ዴልጋዱ በበኩላቸው አገራቸው የቡድን 20 (ጂ-20) ፕሬዚዳንት መሆኗን ጠቅሰው ሁለቱ አገራት በዓለም አቀፍ፣ በመንግስታቱ ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ ገልጸዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በግብርና እንዲሁም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተባብረው በሚሰሩበት ሁኔታ ላይ መነጋገራቸውንም አክለዋል።

አርጀንቲና ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት መስራት እንደምትሻ መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ጄኔራል ዳይሬክተር አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል።

አርጀንቲና በኢትዮጵያ ያላትን ኤምባሲዋን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2013 በድጋሚ መክፈቷ ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010 በኦሮሚያ ክልል በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ የ121 ድርጅቶችን ፈቃድ መሰረዙን  የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት በውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ ያከናወናቸውን ተግባራት የተመለከተ መግለጫም ሰጥቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አሰፋ ኩምሳ እንደገለጹት ቢሮው የድርጅቶችን ፈቃድ  የሰረዘው ባለፈው አንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ  ቢሮ ሊታረሙ ይችላሉ ብሎ የገመገማቸውን ከ200 በላይ ድርጅቶች በጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ማለፉንም አቶ አሰፋ አስታውቀዋል፡፡

ፈቃዳቸውን የተነጠቁት 121 ድርጅቶች የመንግስት ግብር የሚያጭበረብሩ፣ ለኅብረተሰቡ ጤንነት ደንታ የሌላቸው፣ ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል የማይፈጥሩና ፈቃዳቸውን ተገን አድርገው ኮንትሮባንድ የሚሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

 በማዕድን ዘርፍ የአካባቢውን ኅብረተሰብና መንግስትን ተጠቃሚ ለማድረግ ፈቃድ ካወጡ በኋላ ስራቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ድርጅቶች  መሆናቸውንም ጨምረው  ተናግረዋል

ሌሎች የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ከ200 በላይ ድርጅቶችም በተሰጣቸው ፍቃድ መሰረት ካልሰሩ በቀጣይ የመንግስትና የህዝብ ንብረት ለመጠበቅና በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሲባል እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

የቁጥጥርና ክትትል ስርዓት ደካማ እንደነበር የጠቀሱት ኃላፊው እስካሁን ለተፈጠረው ችግር ከፌዴራል እስከ ታችኛው የዘርፉ አመራርና ባለሙያ ተጠያቂ እንደሆነም የቢሮ ኃላፊ አመልክተዋል፡፡

በክልሉ ከ715 በላይ ድርጅቶች በማዕድን ዘርፍ ፈቃድ አውጥተው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም አብዛኞቹ ስራቸውን የሚያከናውኑት በህገ ወጥ መንገድ እንደሆነ መታወቁን  ጠቁመወዋል

በሌላ በኩል  በዘረፉ ባለፉት ስድስት ወራት  ከ52 ሺህ በላይ ወጣቶች በማዕድን ዘርፍ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸውና ከአምስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን  የቢሮው ኃላፊ አቶ አሰፋ ኩምሳ አስታውቀዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን