አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 12 February 2018

አዲስ የካቲት 5/2010 ኩዌት ለኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶች ድጋፏን እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የአገሪቷ አምባሳደር ራሽድ ፋሌህ አል ሀጂሪ ገለጹ።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኩዌት ኤምባሲ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት የሚያካሂደውን ሰባተኛውን የስፖርት ቀን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አምባሳደር ራሽድ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት "አገራቸው በኢትዮጵያ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ጥረት ከሚያደርጉ አገራት በዋነኛነት ትጠቀሳለች"።

በኩዌት የልማት ፈንድ በኩል በአገሪቷ በመሰረት ልማት በተለይም በመንገድ ግንባታና በገጠር የኤሌትሪክ ሃይል የማስፋፋፊያ ፕሮጀክቶች ስራዎች የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል።

በቅርብ ጊዜ በትግራይ አክሱም ከተማ እየተካሄደ ላለው የውሃ ልማት ፕሮጀክትም የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ኩዌት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለችውን የልማት ስራዎችና እንቅስቃሴዎች በመገንዘብና የምታደርገውንም ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል።

አገራቸው በተያዘው ዓመት በተለያዩ መስኮች ለአፍሪካ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ እቅድ እንዳላትና ኢትዮጵያም በዚሁ ድጋፍ ተጠቃሚ እንደምትሆን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

ገንዘቡ በአህጉሪቷ ለሚከናወኑ የመሰረተ ልማት፣የኢንቨስትመንት፣የምግብ ዋስትና፣ትምህርት፤ ለጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚውልም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያና ኩዌት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የገለጹት አምባሳደሩ የየአገራቱ ባለስልጣናትም ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ከጥቂት ወራቶች በፊት ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ሰአት ሁለቱ አገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል መሆናቸውንና ይህም በአህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በትብብር እንዲሰሩ ምቹ አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በባህረ ሰላጤው ያለው ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የኩዌት ኤሚር ሼክ ጃበር አል አህመድ አል ሳባህ እያደረጉት ያለውን የዲፕሎማሲ ጥረት መደገፏ በጉዳዩ ላይ ያላትን ጠንካራ አቋም እንደሚያሳይ ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመራ የጋራ የሚኒስትሮች ስብሰባ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በዲፕሎማሲው መስክ ያላቸውን ጠንካራ ግንኙነት በንግድና ኢንቨስትመንቱም እንዲጠናከር አገራቸው እንደምትሰራ አስታውቀዋል።

የኩዌት መንግስት የአገሪቷ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደምታበረታታ አምባሳደር ራሽድ አብራርተዋል።

በመጪው ቅዳሜ የሚካሄደው 7ተኛው የስፖርት ቀን አላማ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዲፕሎማቶች፣ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና የኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ቤተሰባዊ መንፈስን መፍጠር እንደሆነም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ኩዌት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1967 ሲሆን ሁለቱ አገራት እ.አ.አ በ1997 በየአገራቱ ኤምባሲ ከፍተዋል።

ኢትዮጵያ ቡና፣ሰሊጥ፣የቁም እንስሳት፣አበባና የአትክልት ምርቶችን ወደ ኩዌት ስትልክ በአንጻሩ መድሐኒት፣የብረታ ብረት ውጤቶች፣የግንባታ እቃዎችና ነዳጅ ታስገባለች።

Published in ማህበራዊ

በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ/ ኤድስን ስርጭት ለመግታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት  የእቅዳቸው አካል በማድረግ  ሊሰሩ እንደሚገባ  ተመለከተ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልገሎቱ የጋምቤላ ሪጀን ሰራተኞች በፍቃደኝነት የተመሰረተ የኤች አይ ቪ/ ኤችአይቪ/ኤድስ የምክርና የደም ምርመራ አካሂደዋል።

በዚህ  ወቅት የክልሉ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ኡሞድ አኳይ እንደተናገሩት የበሽታውን ስርጭት የመከላከሉና የመቆጣጠሩ ስራ በአንድ ተቋም ብቻ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።

በሽታውን ለመግታትና ለመቆጣጠር የመንግስትም ሆነ የግል የልማት ሴክተር መስሪያ ቤቶች የመከላከሉ ስራ በልማት እቅዳቸው ውስጥ አካተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገለግሎት በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን ለመወጣት እራሱን የቻለ ጽህፈት ቤት ከፍቶ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት በአርአያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሰው ሀብት ስራ አስፈፃሚ አቶ እሱባለው ጤናው በበኩላቸው የመስሪያ ቤቱ  ሰራተኞች ስለበሽታው ያላቸውን ግንዛቤ  በማሳደግ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን  እየተወጡ  መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት የዓለም የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ቀንን  በማስመለከት ሰራተኞቹ  በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምክርና የደም ምራመር አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።  

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኤች አይ ቪ / ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ በዳሶ መስሪያ ቤታቸው  በሽታውን ለመከላከል እንደ አንድ የእቅድ አካል አድርጎ እየሰራ መሆኑን  ገልጸዋል።

የዓለም የኤች አይ ቪ / ኤድስ ቀንን አስመልከቶ ባለፈው ቅዳሜ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ከ120 በላይ የሪጅኑ ሰራተኞች በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ  የኤች አይ ቪ/ ኤድስ የምክርና የደም ምርመራ አድርገዋል።

Published in ማህበራዊ

የካቲት 5/2010 በመዲናዋ ከምግብና መጠጥ ጋር ባእድ ነገሮችን በመቀላቀልና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ሲሸጡ በተገኙ 2 ሺህ 316 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ የምግብ፣ መጠጥ፣ የጤና አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

ከበርበሬ ጋር ቀይ አፈር፣ ከእንጀራ ጋር የእንጨት ተረፈ ምርት (ሰጋቱራ)ና ጀሶ፣ ከፈሳሽ ዘይት ጋር ፋጉሎ ቀላቅሎ መሸጥ ዋና ዋናዎቹ ህገ ወጥ ድርጊቶች መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

ባለስልጣኑ ለኢዜአ እንደገለፀው በበጀት ዓመቱ ታህሳስ እና ጥር ወራት ብቻ በመዲናዋ በሚገኙ 7 ሺህ 943 የምግብና የመጠጥ አገልግሎት ተቋማት ላይ የተቀናጀ ቁጥጥር አካሂዶ 1 ሺህ 772ቱ  ላይ እርምጃ ወስዷል፡፡

በባለስልጣኑ የቁጥጥር ንዑስ የስራ ሂደት ተወካይ አቶ አባዲ አብረሃ እንዳሉት እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት መካከል 212ቱ ሲታሸጉ 534ቱ የፅሁፍ፣ 1 ሺህ 26ቱ  ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

የተቀናጀ ቁጥጥር ከተደረገባቸው 402 የምግብና መጠጥ አምራች ተቋማት ውስጥም 34ቱ የቃል፣ 37ቱ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ሲሆን 10ሩ መታሸጋቸውንም ነው አቶ አባዲ ያብራሩት፡፡

በ2 ሺህ 213 ጤና ነክ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ቁጥጥር ተደርጎ 463ቱ ላይ ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ማሸግ የደረሰ እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡

ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ እንሚያመለክተው በሁለት ወራት ውስጥ ከ14 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የተበላሸ ምግብ እና ከ 11 ሺህ ሊትር በላይ የተበላሸ ምግብና መጠጥ ተወግዷል፡፡

ከ580 ሊትር በላይ ጤና ነክ ምርቶች እና ከ3 ሺህ 200 በላይ የተበላሹ ቁሳቁሶችም እንዲወገዱ ተደርጓል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ የካቲት 5/2010 ዘንድሮ የሚካሄደውን 6ኛ ዙር የአካባቢ ምርጫና የድሬደዋና አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድሮች የምክር ቤት ምርጫን በብቃት ለማስፈጸም ዝግጀት እያጠናቀቀ መሆኑን  ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ለምርጫ አስፈጻሚዎች የተዘጋጀ የሁለት ቀናት ስልጠና ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ራሔል ታደሰ የስልጠና መድረኩን ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር እንደገለጹት ምርጫው ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ መልኩ ዴሞክራሲያዊ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ዝግጅቶች ተደርገዋል።

ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ዝግጅት በአሁኑ ወቅት በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመላው ሀገሩቱ ከሚገኙ ወረዳዎች ለህገ መንግስቱ ታማኝ የሆኑና ገለልተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተመልምለው የማሰልጠን ሥራ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠናም በምርጫ ህግ ማዕቀፍ፣ በመራጮችና በዕጩዎች ምዝገባ፣ በቅሬታ አቀራረብና አፈታት፣ በሰነዶችና ቁሳቁሶች አጠቃቀም ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዳማ ላይ ዛሬ በተጀመረው ስልጠና ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም ከሐረሪና ከጋምቤላ ክልሎች የተወጣጡ 300 የምርጫ አስፈፃሚዎች ተሳታፊ መሆናቸውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

Published in ፖለቲካ

ጅማ የካቲት 5/2010 የኢትዮጵያ ክፍተኛ ሊግ ጅማ አባቡናና ቡታጅራ ከተማ በጅማ ከተማ  ያካሄዱት ጨዋታ ባዶ ለባዶ በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ ።

አሰልጣኙን ባለፈው ሳምንት ያሰናበተው ጅማ አባቡና ወደ ሜዳ የገባው በአሰልጣኝ ይልማ ሃብቴ   እየተመራ ሲሆን  በሙሉ የጨዋታ ጊዜም  ጠንካራ የጎል ሙከራ ሳያደረግ ጨዋታውን አጠናቋል፡፡

አባቡናዎች የሚታወቁበትን አጥቅቶና ኳስ አደረጅቶ ወደ ጎል በመድረሱ በኩል በትናንቱ ጨዋታ ማሳየት ሳይችሉ ቀርተዋል ።

በቡታጅራ ከተማ በኩል በመጀመሪያው ግማሽ የጨዋታ ጊዜ በመከላከልና በመልሶ ማጥቃት  በሁለተኛው ግማሽ ደግሞ በመሀል ሜዳ ላይ ያተኮረ አጨዋወት ቢመርጡም ውጤታማ አላደረጋቸውም ።

ጅማ አባቡና አቻ ከመውጣቱ ጋር ተያይዞ ደረጃውን ከ8ኛነት ወደ 7ኛ ከፍ ያደረገ ሲሆን ተጋጣሚው ቡታጅራም ከ5ኛ ወደ 4ኛ ክፍ ማለት ችሏል፡፡

በጅማ ስታዲዮም የተገኙት  ድጋፊዎች  ለሁለቱም ክለቦች  ሚዛናዊ ድጋፍ በመስጠት አበረታትተዋል፡፡

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ የካቲት 5/2010 የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ዓመታዊ ጉባኤ ከየካቲት 12-16 /2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ መንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት 16ኛውን የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ጉባኤ አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

ጉባኤው "የመንገድ ሃብታችንን በመንከባከብ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት እንረባረብ" በሚል መሪ ሃሳብ እንደሚካሄድ የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተርና የአፍሪካ መንገዶች ጥገና ፈንድ ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ረሺድ መሐመድ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው በዚህ ጉባኤ የ35 የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶችና ከ200 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚገኙበት ይጠበቃል።

ይህም በአገሪቷ የኮንፈረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት፣ ለአገር ገጽታ ግንባታና በመንገድ ዘርፍ ግንባታ አህጉራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ምርጥ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቅሰም ያስችላል ብለዋል።

ጉባዔው ባለፈው ዓመት በኮትዲቯር ዋና ከተማ አቢጃን የተካሄደው 15ኛው ጉባዔ ውሳኔዎች አፈጻጸምን የሚገመግም ሲሆን የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ይካሄድባቸዋል።

ኢትዮጵያ ማኅበሩን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ እየመራች መሆኑን የጠቀሱት አቶ ረሺድ በጉባዔው ማኅበሩን ለቀጣይ ሁለት ዓመት የሚመራ ፕሬዝዳንት ምርጫ እንደሚያካሄድ ተናግረዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ከአዲስ አበባ አዳማ የባቡር ጉዞ የሚያደርጉ ሲሆን ስለ አገሪቱ የባቡር ኢንዱስትሪ ገለጻ ይደረግላቸዋል፤ የአዲስ-አዳማን የፍጥነት መንገድም ይጎበኛሉ።

የአፍሪካ የመንገዶች ጥገና ፈንድ ማህበር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2003 የተቋቋመ ሲሆን በአባል አገራት የሚገኙ መንገዶችን ለመጠገን፣ ለመጠበቅና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚሰራ ተቋም ነው። 

ማህበሩ በአሁኑ ወቅት 35 የአፍሪካ አገራትን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት5/2010 አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሰባት ተጠርጣሪዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መወሰኑን ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታወቀ።

ክሳቸው እንዲቋረጥ የተወሰነላቸው በአገሪቱ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ጉርሜሳ አያና፣ አቶ አዲሱ ቡላላ፣ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ አቶ ጌቱ ጋሩማ፣ አቶ ተስፋዬ ሊበን እና አቶ በየነ ሩዳ ናቸው።

በጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ 943/2008 አንቀጽ 6/3/ሠ መሰረት የተጠርጣሪዎቹ ክስ እንዲቋረጥ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ማመልከቱ ተገልጿል።

ችሎት በመድፈር በፍርድ ቤት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተጠርጣሪዎቹ የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የይቅርታ ቦርድ ለአገሪቷ ፕሬዚዳንት በሚያቀርበው የይቅርታ ሃሳብ መሰረት ጉዳያቸው የሚታይ መሆኑም ተነግሯል።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ቀደም ሲል ያሳለፋቸውን ውሳኔዎቸ ተከትሎ መንግስት በተለያየ የወንጀል ድርጊት በመሳተፍ ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውን ክሳቸውን የማቋረጥና ውሳኔ የተላለፈባቸውም በምህረት እንዲለቀቁ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  የካቲት 4/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ እስኪደርስ ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የፀጥታ አካላት ገለጹ።

የአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች አባላትን ያካተተ "የፀጥታ አካላት የሠላም ጉዞ" በሚል መሪ ሃሳብ የእግር ጉዞ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሠራዊት አባላትም ግድቡ የአገር አንድነትና ከፍታ ማሳያ ፕሮጀክት በመሆኑ የተለየ ቦታ እንደሚሰጡት ገልጸዋል።

ሻምበል ጋረደው ጋልዳ እንዳሉት''የሕዳሴ ግድብ የሕበረ ብሔራዊነት፣ የአገር አንድነት መገለጫ ነው፤ለእኔ የሕዳሴ ግድቡ የአንድ ኢትዮጵያዊነት መገለጫ ነው '' ብለዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ደህንነቱን ለማስከበር የተሰጣቸውን ተልዕኮ ከመወጣት ባለፈ ለ7ኛ ዙር የቦንድ ግዥ መፈፀማቸውንም ተናግረዋል።

ኮንስታብል ቢኒያም ታደለ እንደተናገረው''ድጋፍ እያደረግን ቆይተናል አሁን ከዚህም በኋላ እናደርጋለን፤ ይህን ስልህ ከወር ደመወዝም ቦንድም በመግዛት ያለውን ነገር እያደረግን እስካሁን ቆይተናል፤ በገንዘብ ብቻ አይደለም እስከ ሕይወት ፍፃሜ ድረስ እንገነባዋለን

''እኛ ፖሊሶች ነን፣ ወታደሮች ነን፣ አገራችንን ለመጠበቅ የሕይወት መስዋዕትነት እንከፍላለን፤ የህዳሴ ግድቡንም እንጠብቃለን፤ የሚዋጣውንም ሁሉንም እናደርጋለን፤ አሁንም እስካሁን ድረስ እያዋጣን ነው፤ በመስሪያ ቤታችንም እያዋጣን ነው ያለነው፤ መቼም አይቆምም ዓባይ አልቆ ግንባታው ሲያቆም የዛኔ ነው የምናቆመው'' በማለት አስተያየቷ የሰተቸው ደሞ ረዳት ኢንስፔክተር ማርታ ከተማ ነች፡፡

ግድቡ ተገንብቶ እስኪያልቅ ድረስ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሞራል ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን የጸጥታ አካላቱ አረጋግጠዋል።

ሻምበል አዝመራ በላይ በሰጠው አስተያየት ''የሕዳሴ ግድብ በሕዝቡ ተሳትፎና በሠራዊት አባላቱ ነው እየተሰራ ያለው፤ሕዳሴ ግድብን ደግሞ በራሳችን ነው የምንሰራው ሁሉ ነገር የእኛ ነው፤ እሱንም እንደጀመርነው ከሕዝቡ ጋር አንድ ላይ ሆነን እየገነባን አልቆ እንደምናየው ተስፋ እናደርጋለን'' ነው ያለው

Published in ፖለቲካ

አርባ ምንጭ  ጥር 30/2010 የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ህልውናን ለመታደግ የአመራር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ የጋሞ ጎፋ ዞን መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ ፓርኩ ለአደጋ የተጋለጠው በወሰን ማካለል ችግር በመሆኑ ዳግም የመከለል ሥራ እንደሚሰራ አመልክቷል፡፡

በጋሞ ጎፋ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ የቱሪስት መስህብ ጥናትና ልማት ግብይት ዋና ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሲሻወርቅ ስጦታው እንዳሉት ፓርኩ በኢኮ-ቱሪዝምና በአየር ንብረት ለውጥ አገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡

ይሁንና ፓርኩ በአሁኑ ወቅት በህገ-ወጥ ሰፈራ፣ ግብርና፣ የእንስሳት አደን፣ በደን ጭፍጨፋ እንዲሁም ከአርባ ምንጭ ከተማ በሚወጣው ቆሻሻ አደጋ እንደተጋረጠበት ገልጸዋል፡፡

በእዚህም በፓርኩ ውስጥ ከሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት መካከል ከሰንቀሌ የመጡት 130 የስዌይን ቆርኬዎች ሙሉ በሙሉ የጠፉ ሲሆን የሜዳ ፍየል፣ የሜዳ አህያና የቆላ አጋዘን እንዲሁም ሌሎች የዱር እንስሳት ቁጥራቸው እየተመናመነ መምጣቱን አቶ ሲሻወርቅ ገልጸዋል፡፡

የደን ጭፍጨፋ ችግርን ለመቅረፍ ከአካባቢና ደን ጥበቃ፣ ከፍትህና ፀጥታ አካላት እንዲሁም በየደረጃው ካሉ የቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት መዋቅሮች ጋር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት የችግሩ መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ በጋሞ ጎፋ ዞንና በኦሮሚያ ጉጂ ዞን የሚገኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፓርኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአደጋ ውስጥ ካሉ ፓርኮች ተርታ ሊመዘገብ የተቃረበ በመሆኑም ፓርኩን ለመታደግ የአመራር ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ስምኦን ሽብሩ በበኩላቸው፣ የፓርኩ መጥፋት በውስጡ ያሉ ብዝሃ ሕይወትና የአካባቢውን ማህበረሰብ እንደሚጎዳ ገልጸዋል።

በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም አስገንዝበዋል ፡፡

የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ሕልውናን አስመልክቶ በተከታታይ በተደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ከ10 ዓመታት ያላነሰ ውይይት ሲደረግ ቢቆይም እስካሁን ህልውናው ሊከበር ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት የአመራሩ ቁርጠኝነት ግድ እንደሚልም ጠቁመዋል ፡፡

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አብርሃም ማሪዬ በበኩላቸው ፓርኩ በ514 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት በ1967 ዓ.ም ዕውቅና ተሰጥቶት ቢወከልም ከዚያ በኋላ በአስተዳደሩ ትኩረት ባለመሰጠቱ ለጉዳት መዳረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በፓርኩ እየተፈጸመ ያለው ህገ-ወጥ ሠፈራ፣ ግብርና፣ ግጦሽ፣ አደንና ደን ጭፍጨፋ አገሪቱ ያወጣቻቸውን የዱር እንስሳት ጥበቃ ህጎችና የብሔራዊ ፓርክ አስተዳደር ህጎችን በተግባር ለማዋል አዳጋች መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ፣ በፓርኩ ክልል እስከ 880 አርብቶ አደሮች የሚኖሩ ሲሆን በእዚህም ከ20 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት በፓርኩ ውስጥ ይሰማራሉ።

ፓርኩ ከጊዜ ወደጊዜ ለግብርናና ለግጦሽ አገልግሎት መዋያ እየሆነ መምጣቱ አብዛኛው የዱር እንስሳት እንዲሰደዱ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ በፓርኩ ሕልውና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ትልቁ ማነቆ የወሰን ችግር በመሆኑ ዳግም ለመከለል ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል፡፡

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የደቡብ ምዕራብ ቀጠና አስተባባሪ አቶ ገብረ መስቀል ግዛው እንደገለጹት ፓርኩ በኦሮሚያ ጉጂ ዞን በኩል ወሰኑ አለመከበሩን ተከትሎ አደጋ ላይ ሊወድቅ መቻሉን አስረድተዋል ፡፡

ችግሩን ለመፍታት የደቡብና የኦሮሚያ ክልልን ያሳተፈ ውሳኔ ለማስተላለፍ በአሁኑ ጊዜ ቅድመ ዝግጅት የተጠናቀቀ በመሆኑ በሚደረገው ዳግም ክለላ የፓርኩ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ እንደሚችል አመለክተዋል።                                                

ፓርኩ በውስጡ ከ103 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት፣ 33 ተሳቢና ተራማጅ እንስሳት፣ 351 የአዕዋፍ ዝርያዎችና ከአንድ ሺህ በላይ የእፅዋት ዝሪያዎች መያዙን ፡፡

Published in አካባቢ

ሀዋሳ  የካቲት 4/2010 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን በሃዋሳ ከተማ ለ7ኛ ጊዜ ተካሄደ፡፡

ሩጫው በኢትዮጵያ ከተሞችን በማስተዋወቅ በኩል የራሱን አስተዋፅኦ እበረከተ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌትክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ ተናግሯል።

በሃዋሳ ከተማ ለ7ኛ ጊዜ ዛሬ በተካሄደው የግማሽ ማራቶን ታለቁ ሩጫ በ21 ኪሎ ሜትር ከተሳተፉ ተወዳዳሪዎች መካከል 70 ከመቶ የሚሆኑት የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው፡፡

በሃዋሳ ለሚካሄፈደው ሩጫ የውጭ ዜጎች ሲጋበዙ ከተማዋ ለሩጫ ምቹ ከመሆኗ በተጨማሪ የራሷ የሆነ መስህብ ያላት፣ ንጹህ፣ ለምለምና ሰላማዊ  በመሆኗን አጉልቶ ለማሳየት ጭምር መሆኑንም ተናግሯል።፡

ሰባተኛው የግማሽ ማራቶን ሩጫ ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንደነበረ የገለጸው ሻለቃ ኃይሌገብረስላሴ በሩጫው አምባሳሮች፣ ታዋቂ አትሌቶችና የውጭ ዜጎች በብዛት መሳተፋቸውን ገልጿል፡፡

"በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሚካሄደው ታላቁ ሩጫ የውጭ ሀገር ዜጎችና አምባሳደሮች ጭምር የሚሳተፉበት በመሆኑ የኢትዮጵያን ከተሞች እያስተዋወቀ ነው" ብለዋል፡፡

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገልገሎ ገዛኻኝ እንዳሉት፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክልሉ ስፖርት እንዲያድግ ተነሻሽነትን ከመፍጠር ባለፈ ሀገራዊ፣ አህጉራና ዓለም አቀፋዊ አንድነታትን ያጠናክራል፡፡

የዛሬው ውድድር ካለፉት ዓመታት መሻሻልና በተሳታፊዎች ቁጥርM መጨመር የታየበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በውደድሩ እስከ 3 ሺህ ሯጮች መሳተፋቸውንና በደማቅ ሁኔታ መጠናቀቁን የገለጹት ደግሞ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የኦፕሬሽን |ራ አስኪያጅ አቶ ዳግም ተሾመ ናቸው፡፡

የሃዋሳ ከተማ መሰረተ ልማት ማደግ ለሩጫው ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረው፣ ለውደድሩ በሰላም መጠናቀቅ የከተማው ፖሊስ ላደረገላቸው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡  

ውድደሩ የኤትሌቶች፣ የህዝብ፣ የወንዶች፣ የሴቶችና የህጻናት ተብሎ በአምስት ዙር የተካሄደ ሲሆን ሩጫውም በ21 እና በ7 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ለህጻናት በ800 ሜትር ተከፍሎ የተካሄደ ነው።

ለአሸናፊዎች በጥቅሉ100 ሺህ ብር ሽልማት የተበረከተ ሲሆን 1ኛ ሆነው የጨረሱ ተወዳዳሪዎች የ20 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው። 

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን