አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 11 February 2018

ጭሮ የካቲት 4/2010 ለሕብረተሰቡ ፈጣን፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት በመስጠት ለህግ የበላይነት መከበር እንሰራለን ሲሉ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን የፖሊስ አካላት ተናገሩ፡፡

ሕብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ላገለገሉ 412 የፖሊስ አባላት የረጅምና የአጭር ጊዜ አገልግሎት ሜዳሊያ ሽልማት ትናንት ተሰጥቷል፡፡

ከተሸላሚዎች መካከል ምክትል ኮማንደር የደራወርቅ አብነት በመሸለማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው "ሽልማቱ ህብረተሰቡን ይበልጥ በቅንነት ለማገልገል ቃል የምገባበት ነው" ብለዋል ፡፡

ህብረተሰቡ በፀጥታ አካላት ላይ እምነት ኖሮት "ፖሊስ የኛ ነው፤ እኛን ለማገልገል ነው የቆመው" ብሎ ለህግ የበላይነት መከበር ድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

"ሽልማቱ ለወደፊት የተሻለ ለመስራት የሚያበረታታና የበለጠ ኃላፊነት የተቀበልኩበት ነው" ያሉት ደግሞ ምክትል ኢንስፔክተር የሺጥላ ፀጋዬ ናቸው።

በቀጣይ ከሕብረተሰቡ ጎን በመሆን ኃላፊነታቸውን ለሕዝባዊ አገልግሎት ብቻ ከማዋል ባለፈ ለሕዝቡ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌ የሆኑት አቶ ዳዊድ ኢብራሂም በበኩላቸው "ፖሊሶች ቀንና ሌሊት የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ ስለሚደክሙ ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል፡፡

"ህብረተሰቡም ሰላምን ለማስጠበቅና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከፀጥታ አካላት ጎን መቆም ይኖርበታል" ብለዋል።

ለሀገር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በሰላም ወጥቶ ለመግባት የፀጥታ አካላት ድርሻ የማይተካ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ የገመቺስ ወረዳ ነዋሪ አቶ ኡመሬ መሀመድ ናቸው፡፡

ከማንኛውም ጊዜ በላይ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ ዴሬሳ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲን ለማስፈንና ልማትን ለማረጋገጥ የሕብረተሰቡና የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

"የፀጥታ አካላቱ ለሕብረተሰቡና ለሙያቸው ፍቅርና ታማኝነት ኑሯቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ ሕብረተሰቡን ለማገልገል ተግተው መስራት አለባቸው" ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ደቻሳ ቢቲማ በበኩላቸው የሽልማት ስነስርዓቱ የፀጥታ አካላት ሕብረተሰቡን የበለጠ ለማገልግል ዝግጁ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

በየደረጃው ያሉ የፍትህ አካላትም በቀጣይ ለህግ የበላይነት መከበር ከምንም በላይ ትኩረት ሰጥተው የህዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ አካላትን ለመከላከል በቁርጠኝነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ የካቲት 4/2010  የፀጥታ አካላት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ የሚያድርጉትን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ድጋፍ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ተጠቆመ።

የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 7ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ዛሬ የ4 ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞና የሰልፍ ትርኢት አድርገዋል።

የኦሮሚያ ክልል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አማን አሊ በእዚህ ወቅት እንዳሉት የፀጥታ አካላት የክልሉን ሰላም የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የክልሉ የፀጥታ አካላትን ጨምሮ የመንግስት ሠራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ህብረተሰቡ ከ1 ቢሊዮን 850 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የጸጥታ አካለት ሰላምን ከማስከበር ጎን ለጎን የግድቡ ግንባታ ከዳር እንዲደርስ እያደረጉ ያሉትን ሁሉን አቀፍ ተሳትፎና ድጋፍ አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የክልሉ ሕዝብና የፖሊስ አባላት በወቅታዊ የፀጥታ ችግር ሳይደናቀፉ ለግድቡ ግንባታ ከዳር መድረስ በጉልበት፣ በገንዘብና ባላቸው እውቀት የሚያደርጉት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በአሁኑ ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቁመዋል።

ከውስጥና ከውጪ በግድቡ ዙሪያ በአፍራሽ ኃይሎች  የሚናፈሱ አሉባልታዎችን ለማምከን ሕብረተሰቡ በአፈርና ውሃ እቀባ፣ በደን ልማትና በጥሬ ገንዘብ እያደረገ ያለውን ድጋፍ ከመቼው ጊዜ በላይ ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥና ልማቱን ለማስቀጠል የፀጥታ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ሥራ ሂደት ኃላፊ ኮማንደር ጉዲሳ ጉተማ ናቸው።

የክልሉ ፖሊስ አባላት የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ አንስቶ ሁለት ጊዜ ቦንድ መግዛታቸውን ጠቅሰው፣ "ለግንባታው ከዳር መድረስ ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ሰላምና ፀጥታን በማስከባር የላቀ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛሉ" ብለዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የፖሊስ አባላት መካከል ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል።

በመሆኑም የክልሉንም ሆነ የአካባቢውን ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ በማምጣት ለግንባታው ከዳር መድረስ በሙሉ አቅማቸው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ከዚህን ቀደም ለግድቡ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሱት ኮማንደር አስቻለው፣ በቀጣይም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሙያም ሆነ በገንዘብ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ገልጸዋል።

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ሰመራ የካቲት 4/2010 የአፋር ክልል ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት የስራ ዘመን ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ ከ140 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ በጀትና የአንድ ዳኛ ሹመት በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎው በክልሉ የፋይናንስ ቢሮ በቀረበው ከ140ሚሊዮን 104 ሺህ የሚበልጥ የተጨማሪ በጀት ረቂቅ ላይ ከተወያየ በኋላ አጽድቆታል።

የረቂቅ በጀቱ ምንጭም በክልሉ ከተለያዩ ዘርፎች ከተሰበሰቡ ገቢዎች እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን የህዝብና የመንግስት ሃብት የሆነው በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውልም ማሳሰቢያ ሰጥቷል።

ምክር ቤቱ የስነ-ምግባር ችግር ታይቶባቸዋል የተባሉ ዳኞች እንዲሰናበቱ የቀረበው ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ እንዲጸድቅ አድርጓል።

ከዚህ በተጨማሪም አንድ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛን ሹመት ካጸደቀ በኋላ መደበኛ ጉባኤውን አጠናቋል።

 

Published in ፖለቲካ

መቀሌ  የካቲት 3/2010 ወደ ትግራይ ክልል የገባውን የሕዳሴ ችቦ ተከትሎ ለግድቡ ግንባታ የበኩላቸውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን በመቀሌ ከተማ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የገለጹት ነዋሪዎቹ  የግድቡ መጠናቀቅ በሀገሪቱ እየተደረገ ያለውን የጸረ ድህነት ትግል ስለሚያፋጥን ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ። 

በከተማዋ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ወይዘሮ ዙፋን ፍትዊ ለግድቡ ግንባታ እስከ አሁን  ከ15 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በተለያዩ ጊዜያት በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ወደክልሉ ለገባው የህዳሴ ችቦ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውንና ችቦው መቀሌ ከተማ ሲደርስ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም ቦንድ በመግዛት ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።

"የግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ የኤሌክተሪክ ኃይል በተሻለ ሁኔታ እንድናገኝ ከማድረግ ባለፈ የሀገሪቱን እድገት ለማፋጠን ጠቀሜታ ስላለው የጀመርኩትን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክራለሁ" ብለዋል።

በእንስሳትና እንስሳት ተዋፀኦ ልማት ላይ የተሰማሩ አቶ ተክላይ ነጋ በበኩላቸው፣ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ በየዓመቱ የ5 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆታቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ የሚያደርገው የገንዘብ እገዛ የግድቡን ግንባታ ከማፋጠን በተጨማሪ ዜጎች የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ወደፊትም ለግድቡ ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

“በአሁኑ ወቅት ዋንጫው ወደክልሉ መግባትን ተከትሎ መንግስት ከእኛ የሚፈልገውን የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ህብረተሰቡ ከወዲሁ ራሱን ሊያዘጋጅ ይገባል” ብለዋል።

ቀደም ሲል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 1 ሺህ 500 ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ በመቀሌ ከተማ የሚኖሩት የሃይማኖት አባት መጋቢአላፍ ኢሳያስ ገብረመድህን ናቸው።

ካደረጉት የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ሕብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በማስተማርና በመቀስቀስ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የሕዳሴው ግድብ ችቦ ወደክልሉ መምጣትን ተከትሎም ህዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር የቅስቀሳና የማስተማር ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባባሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይለኪሮስ ጠአመ በበኩላቸው፣” በዘንድሮው ዓመት ከትግራይ ክልል 83 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ የተያዘውን ዕቅድ ለማሰካት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም ከክልሉ ህዝብ 469 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ገቢ መደረጉን አስታውሰዋል።

ችቦው በትግራይ ክልል በሚያደርገው ቆይታ አርሶ አደሮች ፣ ባለሀብቶችና የመንግስት ሠራተኞች ተሳትፎቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ ከ50 ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ቦንድ መዘጋጀቱንም አቶ ኃይሌኪሮስ ጠአመ ገልጸዋል።

የልማትና የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች እንዲሁም ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ የቦንድ ሽያጭ የሚካሄድባቸው ተቋማት ሲሆኑ በዚህም 83 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ነው።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ  የካቲት 4/2010 በመላው ትግራይ ጨዋታዎች ሰባት ወረዳዎች ተካፋይ በሆኑበትና ሰባተኛ ቀኑን በያዘው የሴቶች ክብደት ማንሳት ውድድር ሁለት አዲስ ክብረ ወሰን ተመዘገበ።

ትናንት በተደረገው " የክሊን ጃርክ እና ስናች " የክብደት ማንሳት ውድድር ፍፃሜ በክልል ደረጃ ሁለት ክብረወሰኖች ተሻሽለዋል።

በ48 ኪሎ ግራም የሴቶች የክብደት ማንሳት ውድድር ቀደም ሲል ተይዘው የነበሩት ሪከርዶች የተሻሻሉት በሰቲት ሑመራ ተወዳዳሪዋ ወጣት ሕይወት ተስፋይ ነው።

በክሊን ጃርክ ተይዞ የነበረው 43 ኪሎ ግራም ክብደት የማንሳት ክብረወሰን ወደ 47 ኪሎ ግራም ከፍ ያደረገችው ሲሆን፣ በስናች ተይዞ የነበረው 30 ኪሎ ግራም ደግሞ ወደ 34 ኪሎ ግራም ከፍ በማድረግ አዲስ ክብረወሰን ልታስመዘግብ ችላለች።

ሁለቱም ክብረወሰኖች የተሻሻሉት ቀደም ሲል በአላማጣ ተወዳዳሪዋ ወጣት ለምለም ውድነህ በክልል ደረጃ ተይዘው የቆዩትን 43 ኪሎ ግራም የክሊን ጃርክ እና 30 ኪሎ ግራም የስናች ክብደት ማንሳት ውድድሮች ናቸው።

በውደድሩ ላይ እንደተመለከተው የሰቲት ሑመራዋ ሕይወት ሁለቱን የውድድር አይነቶችን በእያንዳንዳቸው በአራት ኪሎ ግራም  አሻሽላለች። 

በስናች በተደረገው የፍፃሜ ውድድር ሕይወት ተስፋይ ከሰቲት ሑመራ ወረዳ 34 ኪሎ ግራም በማንሳት የወርቅ፤ ማህደር መለስ ከሸራሮ ወረዳ 26 ኪሎ ግራም በማንሳት የብርና ትርሀሰ አብርሃ ከላዕላይ አድያቦ ደግሞ 25 ኪሎ ግራም በማንሳት የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነዋል።

በክሊን ጃርክ ተመሳሳይ ውድድር ሕይወት ተስፋይ 47 ኪሎ ግራም በማንሳት ወርቅ፤ ማህደር መለስ ከሸራሮ 38 ኪሎ ግራም በማንሳት ብርና መርሃዊት ኪሮስ ከሀውዜን 33 ኪሎ ግራም በማንሳት የነሀስ ሜዳሊያ ለመሸለም በቅተዋል።

በሌላ በኩል አምስት ወረዳዎች በተሳተፉበት የሴቶች ዋና ጨዋታ የፍፃሜ ውድድር የተደረገ ሲሆን፣ በ200 የሴቶች ቢራቢሮ የፍፃሜ ውድድር ወጣት ሰሚራ አማረ ከሸራሮ አንደኛ በመውጣት አሸንፋለች።

ወጣት ሚሊዮን አዘናው ከሰቲት ሑመራ ሁለተኛ የወጣች ሲሆን፣ የሰቲት ሑመራዋ ወጣት አብርሀት አጠይብ የሦስተኛነት ደረጃ በመያዝ እንደቅደም ተከተላቸው የወርቅ፣ የብርና ነሀስ ሜዳሊያ ተሸልመዋል።

በሴትና ወንድ ጥንዶች በተደረገው 4 በ 100 ሜትር ቅብብል የዋና ውድደር ሰቲት ሑመራ ወርቅ፤ ሸራሮ ብር፤ ፀገዴ ነሀሰ ሜዳሊያ አግኝተዋል።

14 ወረዳዎች በተካፈሉበት የወንዶች የአንድ ሺህ 500 ሜትር ነፃ የዋና ቀዘፋ ውድድር ደግሞ ወጣት ዮናስ ርጥበይ ከአክሱም አንደኛ በመውጣት ውድድሩን በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳሊያ ተሽልሟል።

እንዲሁም ወጣት አስመሮም አብርሃ ከሰቲት ሑመራ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ፤ ወጣት ፋንታሁን አስናቀ ከፀገዴ ሦስተኛ በመውጣት የነሀስ ሜዳሊያ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ የካቲት 4/2010 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ የንቅናቄ ፕሮግራም የሠላም ጉዞ አዲስ አበባ ላይ በጸጥታ ኃይሎች የእግር ጉዞ ተጀምሯል።

"ሠላምና ህዳሴ ግድብ" በሚል መሪ ሐሳብ የሚከናወነው መርሃ ግብር መጀመሪያ የሆነው የእግር ጉዞ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ መስቀል አደባባይ እየተካሄደ ነው።

የእግር ጉዞው ተሳታፊዎች የሠራዊት አባላት በሚያሰሟቸው ታላቁ ህዳሴ ግድብ የሠላም ምንጭ ነው፣ ለወራሪ ጠላት እንዳልተበገርነው ለድህነትም አንበገርም፣ በህዳሴ ግድብና በሠላማችን አንደራደርም በሚሉ መፈክሮችና በተለያዩ ትርዒቶች ታጅቦ እየተካሄደ ነው።

የንቅናቄ ፕሮግራሙ የተዘጋጀው ሠራዊቱ ለህዳሴው ግድብ ያለውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑ ተገልጿል።

በእግር ጉዞው እየተሳተፉ የሚገኙት የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ናቸው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ከመከላከያ፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን ያዘጋጁት የንቅናቄ መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄዱ የተለያዩ ሁነቶች ይቀጥላል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ የካቲት 4/2010 በሀገሪቱ እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ዘርፉን በአዲስ አሰራር መምራት እንደሚያስፈልግ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የመንገድ ደህንነት እንቅስቃሴ የልምድ ልውውጥና የምክክር መድረክ በሃዋሳ ተጀምሯል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ወልደዮሐንስ እንደገለጹት በሀገሪቱ የትራፊክ አደጋ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

አደጋውን ለመቀነስ የትራንስፖርት ዘርፉ በባህሪው ውስብስብ መሆኑን ተረድቶ እስከዛሬ ያለውን አሰራር ቀይሮ በአዲስ መምራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ የሚሰሩ ሥራዎች አካባቢን መሰረት ያደረጉና ሳይንሳዊ ሊሆኑ እንደሚገባ የገለጹት ዳይሬክተሩ የምክክር መድረኩ በየክልሉ የተሻሉ ልምዶችን በመቀመር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስ በንቅናቄ መስራት ከተጀመረ ጀምሮ በየክልሎቹ ያለው አፈጻጸም ተቀራራቢ ቢሆንም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው መጠነኛ ዳሰሳ በደቡብ ክልል የተገኙ ተሞክሮዎች የተሻሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

"ከክልል እስከ ቀበሌ ያለው አመራርም ሆነ ዘርፉን የሚመራው አካል ተቀናጅቶ መስራት መቻሉንና በሞባይል ቴክኖሎጂ የተደገፈው የኤስ.ኤም.ኤስ የቁጥጥር ዘዴን መተግበሩ ከተሞክሮው ለአብነት የሚነሳ ነው" ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ስኳሬ ሹዳ እንደተናገሩት በክልሉ የተደራጀና ቀልጣፋ የአመራር ስርዓት በመፍጠር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው ፡፡

በክልሉ የትራፊክ አደጋ በአሽከርካሪ ስነ ምግባርና ክህሎት ማነስ፣ በሌሊት ጉዞና ህገ ወጥ ትራንስፖርት እንዲሁም በእግረኛችና አሽከርካሪዎች ግንዛቤ እጥረት የሚከሰት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ 77 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ለሁለት ወራት ታግደው ጉድለታቸውን እንዲያርሙ መደረጉን የገለጹት አቶ ስኳሬ፣ ህገ ወጥ ስምሪትንና የሌሊት ጉዞን ለማስቀረት የመውጫ ቅጹን ወደ መዝገብ በማዞር ችግሩን መቅረፍ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በክልል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአደጋ መንስኤና ከፍተኛ ስጋት እየሆነ የመጣው ባለሁለት እግር ተሸከርካሪ መበራከት ሲሆን አጠቃቀሙ ላይ በተሰራው ስራ ሞዴል ወረዳዎች ለመፍጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

የክልሉን ተሞክሮ ያቀረቡት በቢሮው የመንገድ ትራፊክ ደህንነትና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር አቶ መርከቡ ታደሰ በክልሉ የትራንስፖርት ዘርፉ ሥራ በቅንጅት እየተመራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመንገድ ደህንነት ችግር በአብዛኛው በህብረተሰቡ የግንዛቤ ማነስ የሚፈጠር በመሆኑ ከ3 ሺህ በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በእዚህም ግንዛቤ መፈጠሩንና በተማሪዎች ላይ በተሽከርካሪ አደጋ ይደርስ የነበረውን ሞት ወደ ዜሮ ማውረድ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ከቀበሌ ትራፊክ ደህንነት ኮሚቴ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሃይማኖት ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች የንቅናቄው አካል እንዲሆኑ መደረጉንም በተሞክሮነት አንስተዋል፡፡

በሞባይል ቴክኖሎጂ የተደገፈ የኤስ.ኤም.ኤስ የቁጥጥር ዘዴ መጀመሩ መረጃዎች ፈጥነው እንዲደርሱ ከማድረግ ባለፈ ቅሬታዎችንና በዘርፉ የሚታየውን ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪ በክልሉ ያለውን የትራፊክ አደጋ መጠን ለመቀነስ የተያዘው ግብ ላይ ባይደረስም የአደጋው መጠን በፍጥነት እንዳይጨምር እያደረገ መሆኑን አቶ መርከቡ አመልክተዋል።

በመድረኩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በመንገድ ደህንነትና በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊሲንግ የራሳቸውን ተሞክሮ አቅርበው ውይይት እየተደረገ ሲሆን የመስክ ምልከታና የ2010 ንቅናቄ ሰነድ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ታውቋል ።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 4/2010 ዛሬ በ10 ሠዓት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ያለበት የደቡብ ሱዳኑ ዋኡ ሳላም ክለብ እስካሁን አዲስ አበባ አልደረሰም።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምኒልክ ግርማ ለኢዜአ እንደገለጹት የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ዛሬ ከቀኑ 5፡00 ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ይደርሳል ቢባልም እስካሁን አልገባም።

ይመጡበታል የተባለው የኬንያ አየር መንገድ አውሮፕላን በተጠቀሰው ሠዓት አዲስ አበባ ቢገባም ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ የክለቡ ልኡካን

ቡድን የለበትም።

በመሆኑም ኬንያዊው የጨዋታ ኮሚሽነር የደቡብ ሱዳኑ ክለብ በተያዘለት ሠዓት አዲስ አበባ አለመድረሱን ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ አስታውቀዋል።

ከካፍ በተላለፈ መመሪያም በህጉ መሰረት ቡድኑ መጣም አልመጣም ጨዋታው በተያዘለት ሠዓት እንዲካሄድ ተወስኗል።

ዋኡ ሳላም ወደ አዲስ አበባ ስለመምጣት መቅረቱ ማረጋገጫ መስጠት እንደማይቻል የገለጹት አቶ ምኒልክ ቡድኑ በጨዋታው ሠዓት  ካልተገኘ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፎርፌ ተሰጥቶ ወደ ቀጣዩ ዙር እንደሚያልፍ ተናግረዋል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጨዋታውን ለመመልከት ወደ ስታዲየም የሚመጡ ደጋፊዎች በነጻ የሚገቡ መሆኑን አስታውቋል።

የደቡብ ሱዳኑ ክለብ ዋኡ ሳላም ክለብ ትናንት በቂ ዝግጅት ባለማድረጌ ጨዋታው በአንድ ቀን ይራዘምልኝ ሲል ያቀረበው ጥያቄ በካፍ ውድቅ መደረጉ ይታወቃል።

በተመሳሳይ ሌላው የደቡብ ሱዳን ክለብ አል ሂላል ጁባ ከቱኒዚያው ቤን ጉዌርዳን ክለብ ጋር ትናንት ሊያደርገው የነበረው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ለዛሬ እንዲሸጋገርለት ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ከሆነበት በኋላ ቱኒዚያ መድረስ ባለመቻሉ ፎርፌ ተሰጥቶበታል።

 

 

Published in ስፖርት

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን