አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 10 February 2018

ሀረር የካቲት 3/2010 ከመሪው የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ለማጠናከር እንደሚጥሩ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሐረማያና አወዳይ ከተሞች አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳሉት የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ያወጣው መግለጫ ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥና የጋራ ስራን የሚያጠናክር ነው፡፡

የአፍረን ቀሎ ሁምበና አባገዳ ሙሳ ሮባ በሰጡት አስተያየት የድርጅቱ ውሳኔ ተከትሎ በመገናኛ ብዙሃን  የተሰጠው መግለጫ  የሚደግፉትና ሲጠብቁት እንደነበር  ተናግረዋል፡፡

" እኛም አባገዳዎች መግለጫው ስኬታማ ለማድረግ የጀመርነውን የሰላምና ልማት ስራዎች ከድርጁቱ ጋር በመሆን አጠናክረን እንቀጥላለን"  ብለዋል። 

የአወዳይ ከተማ ነዋሪ አቶ ዋሬ መሀመድ በበኩላቸው የድርጅቱ መግለጫ  እድገትን የሚያፋጥንና  የኦሮሞ ህዝብ ጥቅምን የሚያስከብር በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

መግለጫው ለወጣቱ ተስፋ የሚሰጥ አቅጣጫዎችን ያመላከተና  ለተግባራዊነቱም ሁሉም ህብረተሰብ ከድርጅቱ ጎን ሆኖ ከሰራ ተጨባጭ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደሚያምን የተናገረው ደግሞ  የዚሁ  ከተማ  ነዋሪ ወጣት በዳሶ ኡመር ነው፡፡

የሐረማያ ከተማ ነዋሪ አቶ አህመድ ሙሳ በበኩላቸው  ድርጅቱ የደረሰበት ወሳኔ በአካባቢው ለነበረው  የጸጥታ ችግር ጉዳይ ዘለቄታዊ እልባት የሚሰጥ  መሆኑን ገልጸዋል፡፡

" ለስኬታማነቱም የድርሻችንን  በማበርከት ለድርጅቱ ያለንን አለኝታ  በተግባር እናስመሰክራለን" ብለዋል።

የክልሉን መንግስት ከሚመራው ኦህዴድ  ጋር በመሆን የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት  ለማጠናከር እንደሚጥሩ አስተያየት ሰጪዎቹ  ተናግረዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

መቐለ የካቲት 3/2010 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ግዳጅ በብቃት የመወጣቱ ሚስጥር በጠንካራ እሴቶች በመገንባቱ እንደሆነ የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ገብራት አየለ አስታወቁ፡፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት ቀን ለስድስተኛ ጊዜ ዛሬ በመቀሌ ከተማ  በድምቀት ተከብራል፡፡

የዕዙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ገብራት አየለ  ለበዓሉ ታዳሚዎች እንደገለጹት  ሰራዊቱ  የተሰጠውን ተልእኮ በቁርጠኝነት ለመፈጸም  ያለማመንታት ህይወቱን የሚሰጠው ከህዝባዊነቱ የመነጨ በመሆኑ ነው፡፡

ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ግዳጅ በብቃት የመወጣቱ ሚስጥር በጠንካራ እሴቶች በመገንባቱ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

"በዚህም በጎረቤት ሀገሮች ሰላም በማስከበር ስራ ላይ  ተአማኒና ተመራጭ ሰራዊት እንዲሆን አስችሎታል"ብለዋል፡፡

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠሙ የጸጥታ ችግር ስርዓት ለማስያዝ ሰራዊቱ ኃላፊነቱን  በብቃት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰራዊቱ ብሄራዊ ተዋዕጽውን የጠበቀና በሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች ተቀባይነት ያገኘ  ሆኖ እንዲዘልቅ በየጊዜው ከህዝቡ ጋር ምክክር እንደሚያደርግም  የዕዙ ዋና አዛዥ ገልጸዋል፡፡

" ከህዝብና ከሀገር ሉአላዊነት የምናስቀድመው ምንም ነገር የለም " ያሉት ደግሞ የሰራዊቱ አባል የሆኑት ሻለቃ ባምላክ ውብአለ ናቸው፡፡

ምክትል መቶ አለቃ ጸጋ አለም በበኩላቸው ሰራዊቱ ከራሱ  በፊት ለህዝብና ለሀገር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ ከተሳተፉት የመቀሌ  ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሀጂ መሓመድ ዓብደላ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት  ህዝቡ ላይ የሚደርሱ አደጋዎች በመከላከል ፈጥኖ የሚደረስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

" የተቸገሩ ህዝቦችን በመርዳትና በማገዝ በአለም አቀፍ ሰላም በማስከበር ስራው ልዩ ያደርገዋል፤ በዚህም ሰራዊቱ የህዝቡ ፍቅርና አመኔታ ያለው  በመሆኑ እናከብረዋለን" ብለዋል፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ  የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ረዳት ፕሮፌሰር   የማነ ዘርአይ  ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ደርግ ስርዓት የነበረው  ሰራዊት ጥንካሬውና ድክመቱን የሚዳስስ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ሰራዊቱ በዓሉን ያከበረው በፓናል ውይይት ሲሆን የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ሰመራ የካቲት 3/2010 በአፋር ክልል የአርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ በርካታ የልማት ስራዎች ቢኖሩም አሁንም ብዙ እንደሚቀሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ገለጹ።

የክልሉ ምክር ቤት ሶስተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ በሰመራ ከተማ ማካሔድ ጀምሯል።

ርዕሰ መተዳደሩ በጉባኤው ላይ እንደጠቆሙት በቀጣይ በክልሉ በሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች የአርብቶ አደሩን የተሟላ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የምክር ቤቱ አባላት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሰ-መስተዳደሩ አቶ ስዩም አወል ባቀረቡት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ እንዳመለከቱት በተለይም በእናቶችና ህጻናት ጤና፣በንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ዙሪያ የተከናወኑ ተግብራት በርካታ ቢሆኑም ከችግሩ አንጻር ብዙ የሚቀሩ ስውራዎች አሉ። 

በትምህርት ልማት መስክ በበጀት አመቱ የአርብቶ አደሩን ልጆች የትምህርት እድል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናው የንቅናቄ ስራ ከ229 ሺህ በላይ ልጆች በተለያየ እርከን በትምህርት ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

"ውሃን ማዕከል አድርጎ በተጀመረው የመንደር ማሰባሰብ ስራም ባለፉት ስድስት ወራት ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ አርብቶ አደሮችን በመንደር በማሰባሰብ የልማትና መልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ማድረግ ተችላል" ብለዋል።

በአርብቶ አደሩን ወደ ከፊል እርብቶ አደርነት ለማሸጋገር በተጀመሩ ስራዎች 34ሺ በላይ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች የተሸፈነ ሲሆን ከ990በላይ ሄክታር መሬትም በተለያዩ  የመኖ ዝርያዎች እየለማም እንደሚገኝ  አመላክተዋል።

በተጨማሪም ካሉት የእንስሳት ሃብት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኝ የእንስሳት ጤናና የገበያ መሰረተ ልማቶችን በአግባቡ ወደ ስራ በማስገባት ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዩን ለሚበልጡ የቤት እንስሳት ህክምናና ክትባቶች እንዲያገኙ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

በ12 የገበያ ማዕከላት አርበቶ አደሩ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስሮች አንዲፈጠርለት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከ79ሺህ በላይ እንስሳት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ ማድረግ መቻሉንም አስረድተዋል።

እስከ ሰኞ የካቲት 5/2010 ዓ.ም.ድረስ ቀጥሎ የሚካሂደው የምክር ቤቱ ገባኤ በሪፖርቱ ላይ ተወያይቶ ከማጽደቅ በተጨማሪ የተለያዩ አዋጆችንና ሹመቶችን ያጸድቃል ተብሎም ይጠበቃል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ የካቲት 3/2010 የአካባቢ ብክለት ያስከተሉ አምስት ፋብሪካዎች መዝጋቱን የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ገለጸ።

የባለስልጣኑ የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያዴሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአካባቢ፣ በአየር፣ በውሃ እና በወንዞች ላይ ብክለት ሲያስከትሉ የነበሩ 5 ፋብሪካዎች እንዲስተካክሉ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም ምላሽ ባለመስጠታቸው እንዲዘጉ ተደርጓል።

በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ፋብሪካዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር አድርገናል ያሉት አቶ ቦና ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ለ619 ፋብሪካዎች ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆነ የአመራረት ስርአት እንዲከተሉ የጽሁፍ ግብረ-መልስ ተሰጥቷል ብለዋል።

በሰበታ ከተማ የሚገኘው አፍዴ የቆዳ ፋብሪካ ወደ ወንዝ ቆሻሻ በመልቀቅ እንዲሁም በቢሾፍቱ የሚገኙት የወንደር ፒቪሲ ማምረቻ እና ኤልፎራ የዶሮ እርባታ ድርጅት በሰራተኞች ጤና ላይ ጉዳት በማድረሳቸውና የአካባቢ ብክለት በማስከተላቸው መዘጋታቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ኢደቡ አቦቴ ወረዳ የሚገኘው ኢስት ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያወጣው አቧራ እንዲሁም በጉጂ ዞን የሚገኘው የቀንጢቻ ታንታለም ማምረቻ ፋብሪካ በአካበቢና በሰው ላይ ጉዳት በማስከተላቸው በባለስልጣኑ የተዘጉ ተጨማሪ ፋብሪካዎች ናቸው።

ከተዘጉት 5 ፋብሪካዎች በተጨማሪ ለ126 ፋብሪካዎችና የልማት ድርጅቶች የመጀመሪያ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ለ40 ፋብሪካዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።

"ይህን ስናደርግ ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ነው"  የሚሉት አቶ ቦና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ፣ ከኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ጋር በመሆን የክትትልና የድጋፍ ስራዎች መስራታቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ፋብሪከዎች የሚወጡ የተለያዩ ቆሻሻዎች አካባቢውን በመበከል፣በሰውም ሆነ በእንስሳት ጤና ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ለረዥም ጊዜያት የመልካም አስተዳደደር ጥያቄዎችን ሲያስነሱ የቆዩ ናቸው።

ባለስልጣኑ ከኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን ከአካባቢ ጥበቃ ህግ አንጻር ፋብሪካዎች የሚሰሩትን ስራ ለማረጋገጥ በ20 ፋብሪካዎች ላይ የዳሰሳ ጥናት ማካሄዱን ገልጿል።

የጥናቱን ውጤትም የሚመለከታቸው አካላትና የፋብሪካዎቹ ባለቤቶች በተገኙበት ግብረ-መልስ የተሰጠ ሲሆን እያንዳንዱ ፋብሪካ የተሰጠውን ግብረ-መልስና ምከረ ሃሳብ በእቅድ እንዲያስተካክል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሆለታ ከተማ የሚገኘው የአፍሪ አበባ ልማት ድርጅት እና ኢትዮ-ጃፓን የቆዳ ፋብሪካ በአካባቢ ላይ ባስከተሉት ችግር የተነሳ በባለስልጣኑ ከተዘጉ በኋላ ችግሩን የሚቀንሱና የሚያስቀሩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀማቸው ወደ ማምረት እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ሌሎች በባለስልጣኑ የተዘጉ ፋብሪካዎች ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆነ የአመራረት ስልት ከተከተሉና ዘመናዊ የቆሻሻና አያያዝ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ከጀመሩ ወደ ስራ መመለስ እንደሚችሉም ኃላፊው ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢ ላይ ችግር እያስከተሉ በነበሩ 61 ፋብሪካዎች ላይ ከአካባቢ ህግ አንጻር በተደረገ የድጋፍና ክትትል ስራ እንዲሁም ከፋብሪካዎቹ ባለቤቶች ጋር በተካሄደ ውይይት 29ኙ ፋብሪካዎች መሻሻል አሳይተዋል ብለዋል።

የልማት ስራዎች ሲካሄዱ በአካባቢ፣ በማህበረሰብ እና በኢኮኖሚ ላይ የሚኖራቸውን ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በተግባር ማረጋገጥም የግድ መሆኑን አመላክተዋል።

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ የካቲት 3/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአዲስ አበባ መርካቶ በ195 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ባለ 11 ወለል ህንጻ አስመረቀ።  

ባንኩ ገዳ ህንጻ በሚል ስያሜ በመርካቶ መሃል ገባያ ያስመረቀው ህንጻ የደንበኞች የግንኙነት ማዕከልንም ይዟል።

ባንኩ 75ኛ የአልማዝ እዩ በልዩ የምስረታ በዓሉንም በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው።    

የባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ባንኩ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት በግንባታዎች ላይ በስፋት እየሰራ ነው።

ፕሬዝዳንቱ የገዳ ሥርዓት በኢትዮጵያ ታሪክ ያበረከተውን ድርሻ ለመዘከር በማሰብ ገዳ ህንጻ ብለው መሰየማቸውን አንስተዋል።  

809 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይሄው ህንጻ የባንክ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የሰራተኞች ካፍቴሪያ እንዲሁም ሁለገብ አዳራሽ እንዳለውም ገልጸዋል።     

ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎትና ልዩ ልዩ የደንበኞች አገልግሎት ማዕከላትንም በውስጡ ማካተቱን አብራርተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ባንኩ ከደንበኞች ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዘውና 951 የ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥ  የደንበኞች ግንኙነት ማዕከል ወደ ሥራ ማስገባቱንም ይፋ አድርገዋል።  

ማዕከሉ መረጃና ሙያዊ ምክር የሚመቻችበት፤ኀብረተሰቡ ከባንኩ የሚፈልገውን መረጃ የሚያቀርብበትና ባንኩ ለአገልግሎት መሻሻል ከተጠቃሚዎች ግብዓት የሚሰበስብበት ታላቅ የመረጃና የዕውቀት ማዕከል ይሆናል ብለዋል።   

ማዕከሉ ለአገልግሎት ጥራት መሻሻል ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑም ሁለት ሥራ አስኪያጆችና 160 ሰራተኞች መመደባቸውን ተናግረዋል።  

አቶ በቃሉ እንደሚገልጹት የማዕከሉ ወደ ሥራ መግባት ደንበኞች በመረጃ ፍለጋ የሚደርስባቸውን መጉላላት ከመቀነስ ባሻገር የደንበኞች ፍላጎት አመላካች የመረጃ ቋት የሚይዝም ይሆናል። 

የባንኩ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ተስፋዬ ጉተማ በበኩላቸው ባንኩ ለደንበኞች ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት ቅርንጫፍ ቢሮዎችን የመገንባት ተግባሩን እንደሚያጠናክር ገልጸዋል። 

በሚቀጥሉት ዓመታትም 48 ወለል ያለው የዋና መሥሪያ ቤት ግንባታ እና ከ10 ወለል በላይ ያላቸው የቦሌ፣ ሀዋሳ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ጅማና የአዳማ ዲስትሪክት ዘመናዊ ህንጻዎች እንደሚጠናቀቁም አክለዋል። 

ባንኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በሚል በ1934 ዓ.ም እንደተቋቋመ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በአሁኑ ወቅት ባንኩ ከ490 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ያለው ሲሆን ከ16 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችንም ማፍራት ችሏል።

የባንኩ ቅርንጫፎችም 1 ሺህ 235 መድረሳቸውን የባንኩ መረጃ ያመለክታል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ የካቲት 3/2010 ዶርካስ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅትና ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በዘጠኝ ሙያዎች ያሰለጠኗቸውን 297 ከስደት ተመላሽ እና ለስደት ተጋላጭ ወጣቶችን አስመረቁ።

ተመራቂዎቹ በእንጨት ሥራ፣ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ፣ በብረታ ብረት ማምረት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሆቴል ሙያ፣ በጨርቃ ጨርቅ ስፌት፣ በመኪና ጥገና፣ በከተማ ግብርና፣ በቢሮ አያያዝና በደንበኛ አስተዳደር ሙያ መስኮች ለስድስት ወራት በአዲስ አበባ የሰለጠኑ ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል 287 ያህሉ ከስደት ተመላሽ ወጣቶች ሲሆኑ፤ ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ 208ቱን፤ቀሪዎቹን ደግሞ ዶርካስ አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት አሰልጥኗል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ ብዙነህ አዱኛ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ስልጠና ወስደው ለሚሰማሩ ከስደት ተመላሽና ለስደት ተጋላጭ ወጣቶች በሥራ እራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ እገዛና ድጋፍ ማድረግ ይገባል።

ተመራቂዎቹ ስራ ፈላጊ  ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ ለስደትም የተጋለጡ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት በቂ ስልጠና አግኝተው የራሳቸውን ሥራ ለመፍጠርና ተቀጥረው ለመስራት ዝግጁ የሆኑ ናቸው ብለዋል።

ወጣቶቹ የራሳቸውን ሥራ ፈጥረው አገር የሚያኮሩ ዜጋ እንዲሆኑ የወላጆች ፍላጎት፣ ስልጠናና የድጋፍ ሰጪ አካላት እገዛ ብቻ በቂ አይደለም።

ስለሆነም ከወጣቶቹ ዝግጁነት፣ ቁርጠኝነትና ጥረት ባሻገር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግላቸው ጥሪ አቅረበዋል።

የሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ጫሊ እንዳሉት የዛሬዎቹ ተመራቂዎች በዘጠኝ ዓይነት ሙያዎች የቴክኒክ፣ የህይወት ክህሎት እና በስራ ፈጠራ የሰለጠኑ ሰልጣኞች ናቸው።

እስካሁን ስልጠናውን ከወሰዱ ሰልጣኞቹ መካከል 110 ያህሉ ሲቀጠሩ 87 ያህሉ ደግሞ በአነስተኛና ጥቃቅን እንዲደራጁ እንዲሁም 11 ሰልጣኞች የቅጥር ሁኔታ እየተመቻቸላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዶርካስ ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ ታረቀኝ በበኩላቸው ስልጠናው ተመራቂ ወጣቶቹን ለስደት በሚያጋልጡ ምክንያቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ስደትን እንደ አማራጭ እንዳይቆጥሩ ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ወጣቶቹ በሰለጠኑባቸው የሥራ መስኮች ውጤታማና ስኬታማ ሥራ እንዲሰሩ ተገቢውን ድጋፍና እገዛ ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ስልጠናው በቀጣይ በቦረና፣ በሀዋሳ፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታና በአዲስ አበባ በትኩረት የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ22 ሺህ በላይ ለስደት ተጋላጮችና ከስደት ተመላሽ ወጣቶችን በማሰልጠን ወደ ስራ የማሰማራት አቅድ መያዙንም አክለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ የካቲት 3/2010 የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ  ትራንስፎርሜሽንን ታሳቢ ያደረገ ፈጣን እንቅስቃሴ በማካሔድ ሀገራዊ ተልዕኮን በብቃት መወጣት እንደሚያስፈለግ ተገለጸ፡፡

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የእስካሁኑ  አፈፃፀም እንዲሁም የመጪው የመኸር አዝመራ እቅድ ላይ የሚመክር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግስቴ እንደተናገሩት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ  ከድህነት ወለል በታች የሚገኘውን 22 ሚሊዮን ህዝብ የመመገብ  ኃላፊነት አለበት ።

"እየጨመረ በመጣው የህዝብ ቁጥር እድገትና በምግብ ዋጋ መናር ምክንያት ከፍተኛ አሃዝ ያለው ሕዝብ በዘርፉ የምግብ ዋስትናው መረጋገጥ ይኖርበታል" ብለዋል።

በተቀናጀው የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ስራ የሚገቡ 400 ኩባንያዎች በጥሬ ዕቃነት የሚጠቀሙት የግብርና ምርት ፍላጎት የማሟላት ኃላፊነትም እንዲሁ።

በተያዘው ዓመት ከዚሁ ዘርፉ ብቻ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት ግብ እንደተቀመጠ ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው  የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ስራዎች ትራንስፎርሜሽንን ታሳቢ በማድረግ በፍጥነት ማከናወን እንደሚያስፈለግ ገልጸዋል።

ዘርፉ ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት ለመወጣት የክላስተር ልማት ስራውን ማጎልበት ፣ ከምርምር ተቋማት የሚወጡ ተክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም ፣ የአርሶ አደር  ማሰልጠኛ ማዕከላትን ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

"የኤክስቴንሽን ስርዓቱን ገበያ መር ማድረግ ፣ የመካናይዜሽን አጠቃቀምን ማጎልበት ፣ መጤ አረሞች ፣ በሽታዎችን  በአግባቡ መከላከልና  መቆጣጠር ያስፈልጋል" ብለዋል ።

መንግስት ዘርፉን ለማጠናከር አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ እያደረገ መሆኑንና በእጅ ያሉት መልካም አጋጣሚዎች ሁሉ አሟጦ መጠቀም ይገባል፡፡

ከመልካም አጋጣሚዎችም በተለያዩ ዘርፎች የሚከናወኑ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች እንዲሁም ዘርፉ ለማገዝ የሚንቀሳቀሱ ከ800 በላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ሚኒስትር ዴኤታው በማሳያነት ጠቅሰዋል ።

በሀገሪቱ  በኤክስቴንሽን ከሚሳተፉ 17 ሚሊዮን አርሶ አደሮች መካከል የተሟላ ፓኬጅ የሚጠቀሙት 27 በመቶ ብቻ እንደሆኑና ይህንን  ወደ 80 በመቶ ለማሳደግ ርብርብ መደረግ አለበት ብለዋል ።

በግብርናው ዘርፍ ሀብት ያፈሩ ሞዴል አርሶ አደሮች  በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተው መልሰው ግብርናውን እንዲያጠናክሩ የማድረግ ስራ በስፋት ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ዘንድሮ እየተሰበሰበ ካለው የመኸር አዝመራ 345 ሚሊዮን ኩንታል ይጠበቃል፤ በመጪው የመኸር ወቅት ደግሞ ሀገራዊ ምርትነ  ወደ 374 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱን በመድረኩ ተመልክቷል።

በኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ለማ ቦጋለ በበኩላቸው  በክልሉ በመኸሩ ወቅት ከለማው  6 ሚሊዮን ሐክታር መሬት ውስጥ አንድ ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር መሬት በሙሉ ፓኬጅ የተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

" 4 ሚሊዮን 400ሺህ ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን 133 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተካሄደ ነው"ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መልኬ ታደሰ ናቸው፡፡

ከትናንት ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው መድረክ  የክልል ግብርና ቢሮ ፣  የምርምር ማዕከላት የስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ሶዶ የካቲት 2/2010 የአየርላንድ መንግስት ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የአየርላንድ አምባሳደር ሶኒያ ሃይላንድ ገለጹ።

አምባሳደሯ የዱብሊን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የሚተገብረውን ፕሮጀክት አስመልክቶ ከሁለቱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና አመራሮች ጋር ትናንት መክረዋል።

አምባሳደር ሶኒያ ሃይላንድ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት " በትምህርት መሳሪያነት አቅምን መገንባት" በሚል የተቀረጸው ፕሮጀክት በግብርና፣ በጤና፣ በሥራ ፈጠራ ክህሎት፣ በኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም በትምህርት የሚደረገውን ድጋፍ አካቶ የያዘ ነው።

ፕሮጀክቱ የመማር ማስተማሩን ሂደት በጥናትና ምርምር ከማስደገፍ ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት፣ የአይ.ሲቲ እውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

በእዚህም በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፣ በእዚህ በኩል የአየርላንድ መንግስት ለወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሚያደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

" የአይርላንድና የኢትዮጵያ ሰላማዊ ግንኙነት ለበርካታ ሃገራት ሞዴል የሚሆን ነው" ያሉት አምባሳደሯ፣ ይህ ድጋፍ በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶ በበኩላቸው አንዳሉት ፕሮጀክቱን በጋራ ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውንና በምክክር መድረኩም በአተገባበሩ ላይ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ጥራት ያለው ትምህርት በማቅረብ ድህነትን ማሸነፍ ላይ ያተኮረ እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ሳሙኤል፣ በፕሮጀክቱ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮች ከልማት ጋር በማገናኘት በኩል ዩኒቨርሲቲው የነበረበትን የአቅም ውስንነት እንደሚፈታለት አስረድተዋል።

ከዱብሊን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ጋር የተጀመሩት ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ በማሸጋገር በሀገሪቱ ላሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሳሌ ለመሆን በትኩረት እደሚሰሩም ገልጸዋል።

የዱብሊን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተወካይ ፕሮፌሰር ፓት ግቨን በበኩላቸው የመማር ማስተማር ክህሎትን ጨምሮ በመሰረተ ልማቶት ከወላይታ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተደጋግፎ ለመስራት በጋራ  መስማማታቸውን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለውና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚከናወኑ ተግባራት በግብርና፣ በጤናና በሌሎችም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

"በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ያለውን አቅም በምርምር በማሳደግ እርስ በርስ የመማማር ዕሴቶችን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ፕሮጀክቱ ዕድል ይሰጣል" ብለዋል።

በተለይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የመምህራንን አቅም ለማሳደግ ከዱብሊን ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ የአጭርና ረጅም ጊዜ ስልጠናዎችን ለማግኘት መግባባት ላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

የዱብሊን ዩኒቨርሲቲ ከአየርላንድ መንግስት ጋር በመተባበር የተለያዩ ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን ለሚያቀርቡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ እኤአ በ2017 ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ባቀረበው ፕሮጀክት ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ማሸነፉ ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ የካቲት 3/2010 አደረጃጀቶችን በማሳተፍ ህገ ወጥ መድኃኒት፣ምግብና ምግብ ነክ ንግድን የመከላከል ስራውን እንደሚያጠናክር የምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ የ2010 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹን ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዷል፡፡

በዚሁ ወቅት  የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ የሁሉ ደነቀው እንደገለፁት መስሪያ ቤታቸው በሚያደረገው ምልከታ፣ቁጥጥርና ፍተሻ ብቻ በዘርፉ የሚስተዋለውን ህግ ወጥነት መግታት አይቻልም።

በመድኃኒት፣ምግብና ምግብ ነክ ንግድ ዙሪያ በስፋት  የሚታየውን ህገ ወጥ እንቅስቃሴን ለመግታት የተቀናጀ የጤና ልማት ሠራዊትና የህዝብ ክንፍ አደረጃጀቶች ተሳትፎ ማጎልበት አስፈላጊ ነው፡፡ 

ለዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፌዴራል  እስከ ክልልና ቀበሌ ድረስ የሚገኙ እነዚህን አደረጃጀቶችን  በመጠቀም  ህገ ወጥ መድኃኒት፣ ምግብና ምግብ ነክ ንግድን የመከላከል ስራውን እንደሚያጠናክር አቶ የሁሉ ገልጸዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ አገልግሎት ቁጥጥር ዳይሬክተር  አቶ በድሉ ኃብተማሪያም በበኩላቸው በመድኃኒት፣ምግብና ምግብ ነክ ንግድ ዙሪያ የሚታየው ህገ ወጥ ንግድ የመልካም አስተዳደር ማነቆ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ቁጥጥር ከተደረገባቸው 1ሺህ የጤና ተቋማት፣መድኃኒት አስመጪዎችና አከፋፋዮች፣ምግብና የምግብ ነክ አምራች ድርጅቶች ውስጥ ክፍተት የተገኘባቸው ከ500 በላይ በሚሆኑት እርምጃ መውሰዱን ጠቅሰዋል፡፡

በተወሰደው እርምጃ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ጥራትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የምግብ ምርቶችና ጥሬ እቃዎች ፣ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶች መወገዳቸውን አመልክተዋል።

በአማራ ክልል ዞኖችና ከተማ መስተዳደሮች የፍተሻ፣ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የገለፁት በክልሉ ጤና ቢሮ የጤናና ጤና ነክ ተተኪ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ካልዩፍ ናቸው።

በዚህም ከ260 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የለስላሳ መጠጦች፣ የታሸጉ ምግቦችና ሌሎችም ሸቀጣ ሸቀጦች መወገዳቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ጤና ቢሮ  የጤናና ጤና ነክ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ሃጎስ እንዳሉም ህግ ወጥ የመድኃኒት፣ምግብና ምግብ ነክ ንግድ የሚታይባቸውን አካባቢዎች ተለይተዋል፡፡

ከተለዩትም በተለይም  ሴቲቱ ሁመራ፣አንሻ፣አላማጣና ራያ አዜቦ ወረዳዎችን እንደሚገኙበት ጠቅሰው ከህዝብ ክንፉ ጋር በመሆን በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት እየመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአዳማ ከተማ ከትናንት ጀምሮ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የምክክር መድረኩ  ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ፣የህዝብ ክንፍ አደረጃጀቶችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ የካቲት 3 /2010 15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬና ነገ በክልል ከተሞች  ይካሄዳሉ።

ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት መቀሌ ላይ መቀለ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ።

በተመሳሳይ ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ፋሲል ከተማ አርባምንጭ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ አዳማ ከተማ ጅማ አባጅፋርን በሜዳቸው የሚያስተናግዱ ይሆናል ።

ድሬዳዋ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እንደሚጫወቱም መርሃ ግብሩ ያሳያል።

በአዲስ አበባ ስታዲዩም ሰኞ ደደቢት ከመከላከያ  ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት  ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልዲያ ከተማ በተጫዋቾች መበተን ምክንያት ቡድኑ እንዳይዳከም  ከወላይታ ዲቻ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት በ15ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከሃዋሳ ከተማ ጋር ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ ምክንያት ሌላው የተላለፈ ጨዋታ ሆኖል ።

ፕሪሚየር ሊጉን ደደቢት በ25 ነጥብ ሲመራ መቀሌ ከተማ በ24 ነጥብ ሁለተኛ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ጅማ አባጅፋርና አዳማ ከተማ በተመሳሳይ 21 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከ3 እስከ 6 ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በዘጠኝ ጎል ሲመራ፤ኦኪኪ አፎላቢ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክና አልሀሰን ካሉሻ ከጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ ሰባት ጎሎች ይከተሉታል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን