አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 01 February 2018

አዲስ አበባ ጥር 24/2010 በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል መቀራረብ ለመፍጠር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ሊጠናከር እንደሚገባ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር አቡበከር ሃፍኒ ማህሙድ ገለጹ።

አምባሳደር አቡበከር ሃፍኒ  ማህሙድ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤የሁለቱን አገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ይበልጥ ሊጠናከር ይገባል።

ለዚህ ደግሞ አገሮቹ የባህል እሴታቸውን ማሳደግ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ነው አምባሳደር ማህሙድ ያነሱት።

ጎን ለጎንም የሁለቱ አገሮች ጋዜጠኞችም በአገሮቹ ወስጥ እየተካሄደ ያለውን ትክክለኛ ነገር በመረጃ ላይ ተመስርተው መዘገብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ይህም በሁለቱ አገሮች መካከል መተማመንንና መቀራረብን ለመፍጠር አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የግብጽ የጤና ባለሙያዎች በኢትዮጵያ በጤናውም ዘርፍ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

“ባለሙያዎቹ በዓመት አራት ጊዜ ኢትዮጵያ በመምጣት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሙያ አጋሮቻቸውን ሲያግዙ ቆይተዋል፤ በቀጣይም ይህ ተጠናክሮ ይቀጥላል”  ብለዋል። 

ባለሙያዎቹ ለኢትዮጵያውያን የሙያ አጋሮቻቸው ልምዳቸውን ከማካፈልም ባለፈ፤ በቀጣይ በፋርማሲዩቲካል ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሯን አጠናክራ ለመቀጠል ፍላጎት እንዳላትም አምባሳደር ሃፍኒ ገልጸዋል። 

ግብጻዊያን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ይህም በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግብጽ ባደረጉት የሥራ ጉብኝት ከአገሪቷ ቢዝነስ ካውንስል ጋር ባደረጉት ውይይት ማረጋገጣቸውን አውስተዋል። 

ባለኃብቶቹ በኢትዮጵያ በንግዱና በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በመሰማራት በአገሮች መካከል ያለውን አጋርነት ለማጠናከር "አበርክቶው ከፍተኛ ነው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የግብጽ ኢንቨስትመንት 750 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ሲሆን፤ የአገራቱ የንግድ ልውውጥ ደግሞ 135 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን  መረጃዎች ያሳያሉ።

 

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር24/2010 የአሜሪካዎቹ ግሪንኮም እና አይሲሲቲ ኩባንያዎች የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ነዳጅ የሚቀይር ፕሮጀክት ለመገንባት ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ተፈጥሮ ጋዝና ባዮ ፊዩል ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ ከከርሰ ምድር የሚገኝን የተፈጥሮ ጋዝ ወደተለያዩ የነዳጅ ምርቶች መቀየር ያስችላል።

ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን ፕሮጀክት መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሰጥ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ የመጨረሻ ውሳኔም እየተጠበቀ ነው።

የኮሚቴው አባላት ቴክኖሎጂው ምን ያህል ይሰራበታል፣ የፋይናንስ ትርፋማነቱ፣ የተቋሞቹ ህጋዊ  ማንነትና የኢትዮጵያ መንግስት ኃላፊነት ምን ይሆናል የሚሉት አራት ጉዳዮች ለሶስት ወራት መገምገማቸውንና ውጤቱ ለኮሚቴው ቀርቦ በቅርቡ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጥበታል።

ግሪንኮም እና አይሲሲቲ የተባሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ነዳጅ የሚቀይር ፕሮጀክት ለመገንባት ሂደት ላይ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ማዕድን፣ ተፈጥሮ ጋዝና ባዮ ፊዩል ኮርፖሬሽን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ነዳጅ መጀመሪያ የተገኘው በ1970ዎቹ ቴኔኮ በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝ መሆኑን በኮርፖሬሽኑ የነዳጅ ፍለጋና ልማት ዳይሬክተር አቶ አንዳርጌ በቀለ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ አስተማማኝ ባለመሆኑና ጋዝን ወደ ነዳጅ የሚቀይረው ቴክኖሎጂ ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚጠይቅ እስካሁን ወደ ስራ እንዳልተገባበት ነው የገለፁት።

የነዳጅ ዋጋ እየጨመረ ሲመጣ የተፈጥሮ ጋዝ ዋጋ ባለበት በመቆየቱና የተፈጥሮ ጋዝን ወደ ነዳጅ መቀየር የሚያስችለው ቴክኖሎጂ በመሻሻሉ በርካታ የአለም አገሮች ጋዝን ወደ ነዳጅ በመቀየር እየተጠቀሙበት በመሆኑ ቴክኖሎጂው ኢትዮጵያ ቢመጣ የተፈጥሮ ጋዝ ክምችትን በሰፊው ስራ ላይ ለማዋል ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

በቴክኖሎጂው አማካኝነትም በኢትዮጵያ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ በተለያዩ ኬሚካላዊ ሂደቶች በማሳለፍ የአውሮፕላን ነዳጅን ጨምሮ ከድፍድፍ ዘይት የሚገኙ የነዳጅ አይነቶችን ማምረት እንደሚቻል ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን ለመገንባት ጥያቄ ያቀረቡት ግሪንኮምና አይሲሲቲ የተሰኙ የአሜሪካ ኩባንያዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ፕሮጀክቱን ለመክፈት ከአንድ አመት በፊት ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የማዕድን፣ ፔትሮሊየምና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር እና ሌሎችን ጨምሮ ስምንት ተቋማት የተካተቱበት የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳያቸው እየታየ ነው ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት በሚኒስትሮቹ ኮሚቴ የሚፀድቅ ከሆነ ኩባንያዎቹ በፍጥነት ወደ ስራ የመግባት ፍላጎት እንዳላቸው ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።

የተፈጥሮ ጋዝ በሚገኝበት የኦጋዴን አካባቢ በአራት ካሬ ኪሎሜትር የሚገነባውም ፕሮጀክቱ ከሁለት እስከ ሶስት አመት ሊወስድ እንደሚችል ኩባንያዎቹ ባቀረቡት ንድፈ ሃሳብ መካተቱን ገልፀዋል።

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ገንዘብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ገንዘቡን ኩባንያዎቹ ከአሜሪካ ባንኮች በብድር የሚያገኙት ይሆናል ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባ  ወደ ውጭ ሊላክ ከታሰበው የተፈጥሮ ጋዝ በተጨማሪ የአገሪቱን የቀን ፍጆታ 50 በመቶ ያህሉን ማለትም በቀን 35 ሺህ በርሜል ነዳጅ የማምረት አቅም ይኖረዋል ብለዋል።

ከዚህም ወስጥ 10 ሺህ በርሜሉ የአውሮፕላን ነዳጅ ሲሆን ቀሪው ቤንዚንና ናፍጣ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ይህም ሀገሪቱ ለነዳጅ የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ከፍተኛ የፋይናንስ ጥቅም ከማስገኘቱ በተጨማሪ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

ሀገሪቱ በሀይል ዘርፍ ከውጭ ጥገኝነት በማላቀቅ  ራሷን ለመቻል መነሻ እንደሚሆናት ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ የሚፀድቀው የሚኒስትሮቹ ኮሚቴ በሚያሳልፈው ውሳኔ ቢሆንም በሶስት ወር በተደረገው ግምገማ ፕሮጀክቱ በርካታ አወንታዊ ነገሮች እንዳሉት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 24/2010 የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የበረራ ደህንነት የመቆጣጠር አቅሙን ማሳደጉን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው ዛሬ እንዳስታወቁት የበረራ ደህንነት የመቆጣጠር አቅሙን በ 2008 ዓ.ም ከነበረው 64 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 69 ነጥብ 5 በመቶ አሳድጓል።

ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በቅርቡ የባለሥልጣኑን የበረራ ደህንነት የመቆጣጠር ብቃት ኦዲት በማድረግ ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ በዓለም አቀፉ ድርጅት ሕግና መመሪያ መሰረት የቁጥጥር ሥራዎችን በሚገባ በማከናወን አገራዊ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪውን በአስተማማኝ የደህንነት ደረጃ እንዲጓዝ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መጨረሻ ባለሥልጣኑ የደህንነት በረራ አቅሙን ወደ 90 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ በሲቪል አቪዬሽንና በአየር ትራንስፖርት የሚነሱ ችግሮችና ጥያቄዎችን ለመመለስ የዘርፉ ፖሊሲና አደረጃጀት እንደሚከለስም ጠቁመዋል።

ይህም በአገር ውስጥ ለመብረር ከግል ኦፕሬተሮች የሚነሳውን ጥያቄና የኤርፖርቶች የባለቤትነት ጉዳይን ጨምሮ በርካታ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

"በአሁኑ ወቅት 'ድሮን' ለበረራ ደህንነት ስጋት እየሆነ አይደለም ወይ?" የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ኮሎኔል ወሰንየለህ 'ድሮን' ከአውሮፕላን ጋር በመጋጨት የደህንነት ችግር የሚፈጥርና ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት 'ድሮን'ን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሰነድ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፈው ሣምንት በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ የፀደቀው የአፍሪካን አየር ክልል ለአሕጉሪቱ አየር መንገዶች ክፍት የማድረግ ስምምነትም ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የአገሪቱን የአየር ክልል አስተማማኝ በሆነ መልኩ በመምራትና ኢንዱስትሪው የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዲውል የማድረግ ሥራ እየሰራ ይገኛል።

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ጥር 24/2010 በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን በመተግበር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስፈፃሚ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው  የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ አሳሰቡ።

 የክልሉ ምክር ቤት  ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

 ምክትል አፈ-ጉባኤ ጁል ኛንጋል በጉባኤው መክፈቻ  እንዳሉት ኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራር ለልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እንቅፋቶች ናቸው፡፡

 እንቅፋቶቹን  በማስወገድ ለእቅዶች ስኬታማነት የምክር ቤቱ አባላትና አስፈፃሚ አካላት በቅንጀት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡

 በክልሉ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የጥልቅ ተሀደሶ ግምገማ  የተለዩትን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታትና የልማት ጥያቄዎችን ምላሽ የመስጠቱ ሄደትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ  አሳስበዋል፡፡

 የክልሉ ምክር ቤቱ በተለይ በግማሽ የበጀት ዓመቱ የታቀዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶችን በመከታተልና በመገምገም ወደ ተግባር እንዲለወጡ የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል።

 በቀጣይም የክትትልና ቁጥጥር ስራዎቹን ይበልጥ  በማጠናከር በክልሉ በልዩ ልዩ ዘርፎች ለተጀመሩ ግንባታዎች መፋጠን በትኩረት እንደሚሰራ አስታወቀዋል።

 ጉባኤው በሁለት ቀናት ቆይታው የክልሉን የ2010 ግማሽ በጀት ዓመት የልማትና መልካም አስተዳደር፣ የኦዲትና የጠቅላይ ፍርድ ቤት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶች ላይ ተወያይቶ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 እንዲሁም የክልሉን የቀጣይ ግማሽ በጀት ዓመት የተከለሰ የመልካም አስተዳደርና የልማት እቅድ፣ የተለየዩ አዋጆችንና ሹመቶችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ ከወጣው የድርጊት መረሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

 በጉባኤው የምክር ቤቱን አባላት ጨምሮ ከ300 በላይ የክልል ፣ የዞንና የወረዳ አመራር አካላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የወጣትና ሴት አደረጃጀት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 24/2010 በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ክለቦች የአጭር፣ የመካከለኛና የእርምጃ እንዲሁም የሜዳ ላይ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

በሻምፒዮናው የሁለተኛ ቀን ውሎ 13 የፍፃሜ ውድድሮች ይኖራሉ የተባለ ቢሆንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባደረገው የመርሃ ግብር ማስተካከያ መሰረት ስድስት የፍፃሜ ውድድሮች ተካሂደዋል።

በሴቶች የ800 ሜትር ለሲዳማ ቡና የተወዳደረችው አትሌት ሂሩት መሻሻ ሁለት ደቂቃ ከአምስት ሴኮንድ ከ 20 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሌ ከመስፍን ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ የመከላከያዋ አልማዝ ግርማ ደግሞ ሦስተኛ በመሆን ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

በ 100 ሜትር ሴቶች የመከላከያዋ ፋዬ ፍሬይሁን 12 ሴኮንድ ከ 25 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ ስትወጣ አትሌት ማርታ ዶቶሬ ከሲዳማ ቡና ሁለተኛ የደቡብ ፖሊስ አትሌት የሆነችው አማረች ዛጎ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በ400 ሜትር ሴቶች የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ፍሬህይወት ወንዴ 54 ሴኮንድ ከ74 ማይክሮ ሴኮንድ ስታሸንፍ ሌላኛዋ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተወዳዳሪ ማሕሌት ፍቅሬ እንዲሁም አትሌት ወርቅነሽ መለሰ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነዋል።

በወንዶች የ110 ሜትር መሰናክል ውድድር በኃይሉ አለምሸት ከመከላከያ 14 ሴኮንድ ከ42 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሲሆን ሌላው የመከላከያ አትሌት ሳሙኤል እሱባለው ሁለተኛ እንዲሁም የሲዳማ ቡናው ቢዋ ዲላ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በ100 ሜትር ወንዶች አትሌት በድሩ መሐመድ 10 ሴኮንድ ከ26 ማይክሮ ሴኮንድ አሸናፊ ሲሆን የኢትዮ-ኤሌትሪኩ ናታን አበበ ሁለተኛ አብዮት ሌንጮ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሦስተኛ ሆነዋል።

በወንዶች የጦር ውርወራ የሲዳማ ቡናው ሽፈራው ሽኑካ 63 ነጥብ 07 ሜትር በመወርወር አንደኛ ሲሆን ኡባንግ ኡባንግ ከመከላከያ እንዲሁም አዶላ ጅቦ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ተከታዩ ደረጃ ይዘዋል።

በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት ለወጡ አትሌቶች የሜዳሊያ ሽልማት የተሰጠ ሲሆን፤ እንደገቡበት የደረጃ ቅደም ተከተል የ2 ሺህ፣ የ1 ሺህ 500 እና የአንድ ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል።

ከፍፃሜ ውድድሮቹ በተጨማሪ በ 100 ሜትርና በ 800 ሜትር ወንዶች የግማሽ ፍፃሜ የማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል።

ነገ አራት የፍፃሜና ሰባት የግማሽ ፍፃሜ ውድድሮች እንደሚካሄዱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

ለአትሌቶች የውድድር አማራጭ ማስፋት ያደረገው የኢትዮጵያ ክለቦች የአጭር፣ መካከለኛና የእርምጃ የሜዳ ላይ ተግባራት አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ጥር 27 ቀን 2010  ይቆያል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ጥር 24/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፉት ስደስት ወራት ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት በብድር መልክ ለማቅረብ ከታቀደው የማቀነባበሪያ መሣሪያዎች ድጋፍ 33 በመቶው ብቻ መሳካቱ ተገለጸ።

 

የፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ የስድስት ወራት እቅድ አፈጻጸሙን እየገመገመ ነው።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ለኢዜአ እንደተገሩት ባለፉት ስድስት ወራት ለ3 ሺህ 500 ተጠቃሚዎች በብድር የመሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ ታቅዶ ነበር።

ይሁንና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ከተቋሙ በብድር የመሳሪያ ድጋፍ ያገኙት ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 ሺህ 161 ሲሆኑ ይህም ከእቅዱ 33 በመቶውን ይይዛል ብለዋል።

ተጠቀሚዎቹም በማምረቻ፣ በምግብ ማቀነባበርና በሌሎች የኢንደስትሪ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአገር ውስጥ የመሳሪያ አምራች ተቋማት የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፉ በብዛት የሚፈልጋቸውን መሣሪያዎች በወቅቱ አምርተው ለገበያ ማቅረብ አለመቻላቸው ደግሞ ለእቅዱ አለመሳካት በምክንያትነት ተጠቅሷል። 

የውጭ አገራት አምራቾች በጊዜ አስፈላጊ ምርቶችን አለማቅረባቸውም ለችግሩ ተጨማሪ ምክንያት ነው ተብሏል።

ጎን ለጎንም መሣሪያዎቹ ተገዝተው ወደ አገር እስኪገቡ ድረስ የሚያጋጥሙ የሎጂስትክ ክፍተቶችም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንዲሆን አበርክቶ አንዳላቸው ገልጸዋል። 

ዋና ዳይሬክተሩ "ኤጀንሲው በረጅም የብድር አቅርቦት መሣሪያ ማቅረብ ከጀመረ ገና ሦስት ዓመቱ ነው፤ አፈጻጸሙም ቢሆን ያን ያክል ዝቅትኛ ሊባል አይችልም" በማለት አስተባብለዋል።

ነገር ግን እነዚህን የተነሱትን ችግሮች ለማስተካከል በተለይም ከአገር ውስጥ መሳሪያ አምራች ተቋማት ጋር ወይይት በማድረግ ለመፍትሄው እንረባረባለን ብለዋል።

ኤጀንሲው በሁለተኛው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዓመታት 41 ቢሊዮን ብር መሣሪያ በብድር ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 24/2010 የላሊበላ ቤተ-ጎሎጎታ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጥገና የፊታችን ቅዳሜ አንደሚጀመር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

የላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት ከስምንት ምእተ ዓመት በላይ አድሜ ያስቆጠሩ በመሆናቸው ለተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች እንደተጋለጡ ሲጠቀስ  ቆይቷል።

ከዓለም እጅግ ድንቅ ጥበቦች መካከል የሰፈሩትን አነዚህን ቅርሶች ለመታደግ  ከአስራ አንዱ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል አምስቱ በጊዜያዊ የጣራ ከለላ ተሸፍነው ይገኛሉ።

ጊዜያዊ የጣራ ከለላዎቹ ዘላቂ መፍትሄ ካለመሆናቸውም በላይ ጣራዎቹን ደግፈው የያዙት ምሰሶዎች በቅርሶቹ ላይ ተጨማሪ ጫና እየፈጠሩ መሆኑም ተገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር  አቶ ዮናስ ደስታ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ  ቅርሶቹን በዘላቂነት የመጠገን ስራ በቤተ-ገብርኤል-ሩፋኤል ላይ በሙከራ ደረጃ ተከናውኖ በስኬት ተጠናቋል።

የጥገና ስራው ከኖርዌይ መንግስት እንዲሁም ከ'ዌልሰን ቻሌንጅስ' እና ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደተከናወነም ገልጸዋል።

በቤተ-ገብርኤል-ሩፋኤል ጥገና ፕሮጀክት የተገኘውን ልምድ በማዳበር  ጥር 26 ቀን 2010 በቤተ-ጎሎጎታ ሚካኤል ቤተክርስቲያን የጥገና ስራ በይፋ እንደሚጀመር ነው ዋና ዳይክተሩ የገለጹት።

ለጥገና ስራው ከአሜሪካ አምባሳደር ፈንድ የ580 ሺህ እንዲሁም ከ'ዓለም ሞኑመንት ፈንድ' 150 ሺህ ዶላር መገኘቱን ጠቁመው፤ "አሁን ላይ የጥገና ስራውን ማስጀመር የሚያስችል ዝግጅት ተጠናቋል" ብለዋል አቶ ዮናስ።

የጥገና ስራውም የቤተ-ገብርኤል-ሩፋኤል ጥገናን በመሩት ቶኒ ስትል በተባሉ ማሃዲስ እና በጣሊያኑ 'ስቱዲዮ ክሮቺ' ኩባንያ አማካኝነት እንደሚከናወንም አክለዋል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ሃይሉ ዘለቀ በበኩላቸው በአካባቢው ለሚኖሩ ወጣቶች አጭር ስልጠና በመስጠትም በጥገና ስራው ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል ብለዋል።

የጉዳት ዳሰሳ ጥናት ስራው 'ሌዘር ስካነር' እና 'ፎቶ ሜትሪ' በተባለ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ አንደተከናወነ ገልጸው፤ "አጠቃላይ የጥገና ስራው በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል" ብለዋል።

በቀጣይም ሌሎች የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትም እንደየጉዳታቸው ደረጃ በቅደም ተከተል ጥገና እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

የቤተ ጎለጎታ ሚካኤል ቤተ-ክርስቲያን በላሊበላ ካሉት አስራ አንድ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዱ ሲሆን፤ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተሰሜን በሚገኘው የመጀመሪያ ምድብ ውስጥ ይገኛል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ጥር 24/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት በሀገር አቀፍ ደረጃ ዘንድሮ ለሚካሄደው 6ኛ ዙር የአካባቢ ምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት አጠናክሮ መቀጠሉን ገለጸ።

ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልልና ከምዕራብ አማራ የተውጣጡ የ244 የመጀመሪያ ዙር የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ትላንት በእንጅባራ ከተማ ተጀምሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ቦርዱ ምርጫን የማስፈፀም ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት እየሰራ ይገኛል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በያዝነው ዓመት የሚካሄደው 6ኛ ዙር የአካባቢ ምርጫ በተሻለ መልኩ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ለእዚህም በምርጫ የህግ ማዕቀፍ፣ በመራጮችና በዕጩዎች አመዘጋገብ፣ በቅሬታ አቀራረብና አፈታት፣ በሰነዶችና ቁሳቁሶች አጠቃቀም ላይ አተኩሮም በአሁኑ ወቅት ስልጠናው እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ምክር ቤቶች ምርጫን ጨምሮ በዚህ ዓመት ለሚካሄደው 6ኛው ዙር የአካባቢ ምርጫ ለመራጮች የሚያስፈልጉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች የህትመት ዝግጅት መጠናቀቁንም አስረድተዋል።

የምርጫ አስፈጻሚዎቹም ምርጫው ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ እንዲከናወንና የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ስልጠናውን በአግባቡ እንዲከታተሉም አሳስበዋል።

ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ መሰረቱ ህገመንግስት እንደሆነ የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምባው አስረስ ናቸው።

በክልሉ ከ183 ወረዳዎች ከተመለመሉ 366 ምርጫ አስፈጻሚዎች መካከል 202ቱ በመጀመሪያው ዙር ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ከመጡት ጋር ስልጠናውን በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለቀሪዎቹ የምስራቅ አማራ ምርጫ አስፈፃሚዎች ከጥር 29 ጀምሮ በደሴ ከተማ ስልጠና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

ከምስራቅ ጎጃም ዞን መርጡለ ማርያም ምርጫ ክልል የመጡት አቶ አበባው አድጎ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ስልጠናው ፋይዳው የጎላ በመሆኑ በአግባቡ እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለምርጫ አስፈፃሚነት ተመልምላ ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምስራቅ በለሳ ምርጫ ክልል የመጣችው ወይዘሪት ማርዬ አስማረ ከስልጠናው በቂ ዕውቀት በመጨበጥና አጋዥ የምርጫ ሰነዶችን በማንበብ የተጣለባትን ምርጫን የማስፈፀም ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ከወዲሁ ራሷን ማዘጋጀቷን ተናግራለች።

በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ አንድ ሺህ 37 ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ለህገ መንግስቱ ታማኝና ገለልተኛ የሆኑ 2 ሺህ 74 ምርጫ አስፈጻሚዎች መመልመላቸው ታውቋል፡፡  

Published in ፖለቲካ
Thursday, 01 February 2018 20:02

የትራንስፖርት ፈተና

Published in ቪዲዮ

ጎባ ጥር 24/2010 በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በባሌ ዞን  ሰዌናና መዳ ወላቡ  ወረዳዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች በህከምና አገልግሎት  እጥረት መቸገራቸውን ገለጹ፡፡

የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ተፈናቃዮቹ  የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን አሰራር እየዘረጋ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በሰዌና ወረዳ “ቁኒ”ቀበሌ  ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ከሚገኙት ተፈናቃዮች  መካከል አቶ ተማም አብዱላሂ በመጠለያው  አካባቢ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ባለመኖራቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል ፡፡

ከዚህ በፊት ከሌላ ቦታ የሚመጡ በጎ ፍቃደኛ ሃኪሞች በራሳቸው ተነሳሽነት አልፎ አልፎ ከሚሰጧቸው የህክምና አገልግሎት በስተቀር በመደበኛነት የሚታከሙበት የጤና ተቋም እንደሌለ ነው አቶ ተማም  ያመለከቱት፡፡

በዚሁ መጠለያ የሚገኙት አቶ ካሚል ኢድሪስ በበኩላቸው በመጠለያው ያጋጠማቸውን የጤና አገልግሎት ችግር  መንግስት በአፋጣኝ  እንዲፈታላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመዳ ወላቡ ወረዳ “መዳ” ቀበሌ ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ካሉት ተፈናቃዮች መካከል ወይዘሮ ሙንታሃ ሁሴን አንዷ ናቸው፡፡

እሳቸው እንዳሉት ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ የነበረባቸው ችግር የተቃለለ  ቢሆንም የህክምና አገልግሎት  አለመኖሩ ችግር ሆኖባቸዋል።

መንግስት በጊዜአዊ መጠለያው  አካባቢ ውኃን ጨምሮ መሟላት የሚገባቸውን ሌሎች መሰረታዊ  አገልግሎቶች በመለየት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው የጠየቁት ደግሞ   በዚሁ መጠለያ  የሰፈሩት አቶ ሁሴን ሀጂ አህመድ ናቸው፡፡

የዞኑ ጤና ጥበቃ  ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እሸቱ ቶሎሳ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ተፈናቃዮች ያነሱትን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ለህክምና ተቋማት ቅርብ በሆኑ ጊዜአዊ መጠለያዎች አካባቢ የሰፈሩ ተፈናቃዮች በአቅራቢያቸው በነፃ እንዲታከሙ ፣ሩቅ ቦታ ላይ የሚገኙት ደግሞ ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኙ ድረስ ተንቀሳቃሽ ክሊኒኮች እየተቋቋሙላቸው ነው፡፡

በጊዜያዊ መጠለያ  አካባቢ የሚስተዋሉ የህክምና  አገልግሎትና  የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግሮችን በመለየት ከሚመለከታቸው  የዞንና የክልል አደጋ ስጋት ኮሚቴዎች ጋር  መፍትሔ ለመስጠት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የዞኑ የአደጋ ስጋትና የስራ አመራር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም ኃይሌ ናቸው፡፡

የፌደራል መንግስት ለተፈናቃዮች የሚያደርገው የምግብ እህል አቅርቦት ድጋፍ ጥሩ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን