አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 09 January 2018

አዲስ አበባ ጥር 1/2010  የሕንዱ 'የሞኔት ኢስፓት ኤንድ ኢነርጂ' ኩባንያ በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የኩባንያውን የስራ ኃላፊዎች በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

 የሞኔት ኢስፓት ኤንድ ኢነርጂ ኩባንያ ማኔጅንግ ዳይሬክተርና የሕንድ ቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ፕሬዝዳንት ሰንዴፕ ጃጆዲያ ከሚኒስትር ዴኤታው ጋር ባደረጉት ቆይታ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በብረታ ብረት ዘርፍ ለመስራት በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

 ኩባንያው ኢትዮጵያ ከውጭ ለግንባታ የምታስገባውን ከፍ ያለ መጠን ያለው ብረትና የብረታ ብረት ጥሬ ግብዓቶችን ለአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ለማቅረብ ማቀዱንም ጠቁመዋል።

 ኩባንያው ከመንግስት አካላት ጋር በመነጋገርና የቢዝነስና ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በመቅረጽ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ስራ ለመጀመር ማቀዱን አመልክተዋል።

 አገሪቷ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች መሆኗን ጠቁመው፤ በኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ያላትን አቅም ለመረዳት እንደቻሉም ነው ሚስተር ጃጆዲያ ያስረዱት።

 ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቢዝነስና ዳያስፖራ ሚኒስትር ዴኤታ ልዩ አማካሪ አቶ ዮሐንስ ፋንታ እንዳሉት፤ ኩባንያው በብረታ ብረት ዘርፍ ከፍተኛ ልምድ ያለው በመሆኑ በኢትዮጵያ በዘርፉ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ።

 ኩባንያው ጥናቱን በማጠናቀቅ "በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል" ብለዋል።

 ኩባንያው የ25 ዓመታት የስራ ልምድ ያለው ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በህንድ በዓመት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ብረት ያመርታል። በተጨማሪ በድንጋይ ከሰል ማውጣትና በኃይል ልማት ስራዎች ላይ መሰማራቱም ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ሽሬ እንዳስላሴ/ማይጨው ጥር 1/2010  በትግራይ ምዕራባዊ  ዞን ባለፈው የመኸር ወቅት የለማ ከ1ሚሊዮን 400ሺህ ኩንታል  በላይ የሰሊጥ ምርት ተሰበሰበ፡፡

 በተመሳሳይ ወቅት  በደቡባዊ ዞን የለማው ልዩ ልዩ የሰብል ምርትም በአብዛኛው ተነስቷል፡፡

 በምዕራባዊ ዞን ግብርና ገጠር ልማት መምሪያ የስነ አዝርእት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ተክለማርያም ነጋ እንደገለጹት የሰሊጥ ምርቱ የተሰበሰበው በምርት ዘመኑ ከለማው 296 ሺህ ሄክታር  ማሳ ነው፡፡

 በምርት ዘመኑ የተሰበሰበው የሰሊጥ ምርት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ112 ሺህ ኩንታል ብልጫ አለው።

 በመኽሩ ወቅት በባለሙያዎች የቅርብ እገዛ የምርት ማሳደጊያ ግብአት በጊዜው ጥቅም ላይ መዋሉና የዝናቡ ስርጭት ተስተካክሎ ለሰሊጥ ሰብል ተስማሚ መሆኑ ለምርቱ መጨመር በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

 ከዞኑ ከተሰበሰበው የሰሊጥ ምርት ውስጥ ከ462 ሺህ ኩንታል በላይ የባለሀብቶች ሲሆን ቀሪው የአርሶ አደሮች ነው።

 በሰሊጥ ልማቱ የተሳተፉት  ባለሀብት አቶ መስፍን ገብረፃዲቅ በሰጡት አስተያየት፣ በምርት ዘመኑ በሰሊጥ ሰብል ከሸፈኑት 15 ሄክታር ማሳቸው  96ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

 ዘንድሮ የሰበሰቡት የምርት መጠን ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ14 ኩንታል ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።

 አርሶ አደር በላይ አርአያ በበኩላቸው፣ ባላቸው አራት ሄክታር ማሳቸው ላይ ካለሙት ሰሊጥ 28 ኩንታል መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

 በሌላ በኩል ደግሞ በደቡባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ሃይላ ካሳ እንደገለጹት በአካባቢው በመኽሩ ወቅት ከ143 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶ በተለያየ የሰብል ዓይነት ከተሸፈነው ውስጥ እስካሁን 74 በመቶው ያህል ተሰብስቧል፡፡

 የአካባቢው ገበሬዎች ዘመናዊ የመውቂያ መሳሪያዎች በመጠቀም የምርት ብክነትን መካለከል እንዲችሉም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

 የክረምቱ ዝናብ የተወሰነ ዘግይቶ በመጀመሩ በሰብል ቡቃያው ላይ ተፅእኖ ቢያሳድርም በመሃል ላይ ስርጭቱ በመስተካከሉ ካለፈው የተሻለ ምርት ማምረት እንደቻሉ የተናገሩት ደግሞ  የእንዳመሆኒ ወረዳ አርሶአደር አሰፋ ረዳኢ ናቸው።

 አርሶ አደሩ እንዳሉት በአጭር ጊዜ የሚደርስ የስንዴ ምርጥ ዘር በሁለት ጥማድ መሬት በማልማት 31 ኩንታል ምርት አግኝተዋል፡፡

 የዚሁ ወረዳ አርሶአደር መረሳ ወልደሳሙኤል በበኩላቸው "መሬታችን በሚገባ አዘጋጅተን ብናለማም መስከረም ላይ የጣለው ኃይለኛ ዝናብ በሰብል እድገት ላይ ተፅእኖ ቢያሳድርም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር አዝመራው ጥሩ ነበር"  ብለዋል፡፡

 በምርት ዘመኑ በሁለት ጥማድ መሬት ካለሙት የስንዴ ምርጥ ዘር 25 ኩንታል መሰብሳባቸውንም አመልክተዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ጭሮ ጥር 1/2010 መምህራን በተረጋጋ ሁኔታ ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ብቁ ዜጋ እንዲቀርፁ ለማበረታታት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ መደረጉን የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሸምሰዲን አብራሂም ለኢዜአ እንደገለፁት የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የተሰጣቸው በ20 ማህበራት ለተደራጁ 214 መምህራን ነው።

በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናትም ለተጨማሪ 876 መምህራን በነፍስ ወከፍ 160 ካሬ ሜትር ቦታ በተመሳሳይ ይሰጣቸዋል ።

በዞኑ ካሉት 7ሺህ 451 መምህራን መካከል 50 በመቶ የሚሆኑትን ዘንድሮ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የሚያገኙበት እድል እየተመቻቸ መሆኑን ከአቶ ሸምሰዲን ገለፃ ለመረዳት ተችሏል።

የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ከተሰጣቸው መምህራን መካከል የጨርጨር ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ታሪኩ ወሰና  የመኖሪያ ቤት ችግራቸውን ለመፍታት መንግስት እያደረገ ባለው ጥረት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቤታቸውን በፍጥነት መገንባት እንዲችሉ ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የተሰጣቸው የቤት መስሪያ ቦታ በተሰማሩበት የመምህርነት ሙያም በትጋት በመስራት የትምህርት ጥራት ለማምጣትና የተማሪ ውጤት እንዲሻሻል የበኩላቸውን ለመወጣት ይበልጥ እንዳነሳሳቸው ጠቁመዋል፡፡

የጭሮ መምህራን ኮሌጅ መምህር ወንዱ ሀብተጊዮርጊስ በበኩላቸው"የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት የገቡትን ቃል ተግባራዊ ማድረጋቸው ከዚህ በፊት የነበረውን የመምህራኑን ቅሬታ የፈታ ነው"ብለዋል፡፡

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን የከተማ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አድማሱ ቀነዓ እንደገለጹት መምህራኑ ነፍስ ወከፍ 160 ካሬ ሜትር ቦታ እየተሰጠ ያለው ቤትና ንብረት እያላቸው በህገ ወጥ መልኩ የቀበሌ ቤትና ሰፊ የኢንቨስተመንት መሬት ወስደው ሳይሰሩ ብዙ ዓመት አጥረው ካስቀመጡ ግለሰቦች  በማስመለስ ነው።

የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተክሌ ዴሬሳ በበኩላቸው የትምህርት ስራውን ውጤታማነት ለማሳደግ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ውጤታማነቱት ለማሳደግ  ደግሞ የመምህራንን ጥያቄ መመለስ ወሳኝ መሆኑን  ገልፀው በዞኑ በየደረጃው ለሚገኙ መምህራን እንደ የአካባቢው ተጨባጭ ሁኔታ እየታየ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 1/2010 12 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ 650  የመስሪያ ቦታ ሼዶች ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በበጀት አመቱ በመዲናዋ ከ160 ሺ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ እንደሆነም ተጠቁሞል::

ከንቲባ ድሪባ ኩማ ከከተማዋ ከፍተኛ አመራር አባላትና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ጉለሌ፣ አቃቂ ቃሊቲና ቦሌ ክፍለ ከተሞች ግንባታቸው የተጠናቀቁ የመስሪያ ቦታ ሼዶችን ዛሬ ጎብኝተዋል። 

ከንቲባ ድሪባ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የከተማዋ ወጣቶች ስራ ፈጠራን በተመለከተ የሚያነሱትን ጥያቄ ለመፍታት ከ350 በላይ አዳዲስ ሼዶች ግንባታቸው ተጠናቋል።

በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ ከ300 በላይ ሼዶች እንዲለቀቁ መደረጋቸውን ተናግረዋል:: 

የተጠቀሱትን 650 ሼዶች ካለፈው ዓመት ጀምሮ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ ወጣቶች ተረክበው ስራ ሲጀምሩባቸው በመዲናዋ የሚታየውን የስራ እድል ፈጠራ ትርጉም ባለው ደረጃ ያሻሽለዋል ብለዋል።

ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሼዶች ለወጣቶች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በዕጣ እንደሚተላለፉ ጠቁመው፤ "በሽግግሩ ወቅት ተገቢ ያልሆነ አሰራር እንዳይኖር ገልጽነት፣ ተጠያቂነትና ህብረተሰቡን ባማከለ መልኩ ተግባራዊ ይደረጋል" ሲሉ አክለዋል::

ከዚህ ቀደም የመስሪያ ቦታ ሼዶች በየአካባቢው ይገነቡ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው፤ በአሁኑ ወቅት ግን ይህን በማስቀረት በኢንዱስትሪ ክላስተር እንዲገነቡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም "በቴክኖሎጂ፣ በስልጠና፣ በምርት ውጤት ትስስርና በመሳሰሉት ውጤታማ ስራ ለመስራት ያስችላል" ነው ያሉት ከንቲባው ።

የገበያ ትስስርና የፋይናንስ አቅርቦት ችግርን ለማቃለል ከባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀና የተደራጀ አሰራር እንደሚኖርም ከንቲባ ድሪባ ኩማ አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ልዑልሰገድ ይፍሩ በበኩላቸው ፤ መንግስት በበጀት አመቱ በመዲናዋ ከ160 ሺ በላይ የስራ ዕድል ለመፍጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።

በዚህም በዋናነት ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ስራው ቀዳሚ ሲሆን፤ የስራ እድሎቹን በማምረቻ፣ በግንባታ፣ በከተማ ግብርናና በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለመተግበር ዝግጁ መደረጉን ገልጸዋል::

ስራው የሁሉንም ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ፣ የአመለካከት ለውጥ እንዲሁም ቁርጠኛ የሆነ አመራርና ፈጻሚ የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 1/2010 በግማሽ ዓመቱ ከቱሪስት ፍሰቱ አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የሕዝብና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የቱሪስት ፍሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ባለፉት ስድስት ወራት 485 ሺ 806 የውጭ አገር ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል። ከዚህም ከአንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ነው የገለጹት።

ይህም ከለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር "የ10 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ አለው" ብለዋል።

ገቢው ከጉብኝት፣ ከኮንፈረንስና ሆቴል አገልግሎት እንዲሁም ከመሰል የቱሪዝም መስኮች መሰብሰቡን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት አንድ ቱሪስት በአማካይ የ16 ቀናት ቆይታ እንዳለውም ጠቁመዋል።

ለቱሪስት ፍሰቱ መሻሻል በየአካባቢው ሰላምና መረጋጋት እየሰፈነ በመምጣቱ መሆኑን ጠቁመው፤ አገሪቷ "በዲፕሎማሲና ውጭ ግንኙነት በኩልም በመልካም ሁኔታ ላይ መገኘቷ እንደምክንያትነት ይጠቀሳል" ብለዋል።

በአገር ውስጥ የቱሪስት ፍሰቱ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማስወገድም ከባለድርሻ አካላትና ከክልሎች ጋር በቅንጅት በመሰራት ላይ መሆኑን ገለጸዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የውጭ አገር ጎብኝዎች፣ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 1/2010 በኢትዮጵያ በአፍላ ወጣትነት እድሜ የሚያረግዙ ሴቶች 13 በመቶ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የጤናማ እናትነት ቀንን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ  ቀኑ "ለጤናማ እናትነት ይብቃ ማርገዝ በአፍላ ወጣትነት" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።

የሚኒስትር ዴኤታው አማካሪ አቶ ግርማ አሸናፊ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ዘንድሮ የሚከበረው የጤናማ እናትነት ቀን  በአፍላ ወጣትነት  እድሜ የሚከሰት እርግዝናን በመከላከል ላይ ትኩረት ያደርጋል።

በኢትዮጵያ  በዓመት ከሚረገዙት ሕፃናት መካከል 13 በመቶው አፍላ በሚባለው የወጣትነት ጊዜ የሚፀነሱ ናቸው ብለዋል ።

አፍላ የወጣትነት ጊዜ ከ15 እስከ 17 ዓመት እድሜ ውስጥ ያሉትን ወጣቶች የሚያጠቃልል መሆኑንም ተናግረዋል።

እነዚህ አፍላ ወጣቶች ሰውነታቸው ለአካል መጠን ባለመድረሱ በማርገዛቸው ለበርካታ የጤና፣ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች ተጋላጭ እንደሚሆኑ አመልክተዋል።

በዚህ ወቅት ከሚከሰትባቸው የጤና ችግሮቹ መካከልም የደም ግፊትና ማነስ፣ ጊዜውን ሳይጠብቅ በምጥ መያዝን ጨምሮ ለረዥም ጊዜ በማማጥ ለፊስቱላ ሕመም ተጋላጭ እንደሚሆኑም ነው የተጠቀሰው።

በተጨማሪም ከአፍላ ወጣቶች የሚወለዱ ህጻናትም እንዲሁ ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚጋለጡ አቶ አሸናፊ ያስረዳሉ

የዘንድሮው የእናቶች ቀን አከባበር አፍላ ወጣቶች ከእርግዝና እንዲርቁ  ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ የግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ በመፍጠር እንደሚካሔድም ነው የሚኒስተር ዴኤታው አማካሪ የተጠቆመው ።

ከዚህ ቀደም  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው በጤና ተቋማት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ እንደነበር የገለጹት አቶ ግርማ፤  በዚህም  "የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልተቻለም" ነው ያሉት።

በመሆኑም  በዚህ ዓመት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው በትምህርት ቤቶችና በወጣት ማዕከላት በአካል በመገኘት በችግሩ አስከፊነት ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ እንደሚከናወንም አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ ካለፉት 12 ዓመታት ጀምሮ የጤናማ እናትነት ቀን በየዓመቱ ለአንድ ወር በተከታታይ እየተከበረ ይገኛል።

በዚህም ሳቢያ በሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫዎች በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር 72 በመቶ መቀነስ መቻሉን ገልጸዋል።

የዘንድሮም ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 30 ቀናት የሚከበር መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኝው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ጥር 1/2010 ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ የሆቴልና ቱሪዝም  ምሩቃን የተማሩትን ተግባር ላይ ለማዋል የብቃት ውስንነት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን የሰጡ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ገለጹ፡፡

ከተቋማቱ መካከል በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የሃይሌ ሪዞሪት ስራ አስኪያጅ አቶ እምሻው ተሾመ እንዳሉት ወደ ተቋማቸው የሚመጡ  የሆቴልና ቱሪዝም  ምሩቃን ከዩኒቨርሲቲ ይዘው የሚወጡት እውቀት በተግባር ማሳየት ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡

የዘርፉ ተማራቂዎችን  ለመቅጠር በሚፈልጉበት ወቅት የአመለካከትና የተነሳሽነት ችግር እንደሚታይባቸው ጠቅሰው የሙያውን ስርዓት ካለማወቅም ባለፈ ራሳቸውንም የመግለፅ ውስንነቶች እንዳሉባቸው ጠቁመዋል፡፡

አቶ እምሻው " በንድፈ ሀሳብ ብቻ ተምረው መውጣታቸው በቂ የተግባር እውቀት እንዳይላበሱ አድርጓቸዋል" ብለዋል፡፡

በሀዋሳ የሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዮሴፍ ሃያለየሱስ በበኩላቸው ሰራተኞችን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በዋናነት ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲና ከሃዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሚመረቁ ባለሙያተኞችን አወዳድረው እንደሚቀጥሩ ገልጸዋል፡፡ 

ሆኖም አዲስ ከትምህርት ተቋማት የሚቀጥሯቸው ምሩቃን የስነ ምግባር ጉድለትና የተግባራዊ እውቀት እንደሚያንሳቸው ነው ያመለከቱት፡፡

ተቋማቸው አለም አቀፍ አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ በስራ ላይ በሚሰማሩበት ወቅት የቋንቋ ችግር እንደሚታይባቸውም አቶ ዮሴፍ ተናግረዋል፡፡

ይህም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ክፍተት በመፍጠር ጫና እንደሚሳድር አመልክተዋል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተግባር ትምህርት ለመውሰድ ለሚፈልጉ ተቋማትና ተማሪዎች ተቋማቶቻቸው  ክፍት መሆናቸውንም ስራ አስኪያጆቹ ገልጸዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲው የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ዕጩ ተመራቂ ተማሪ ብሌን ታሪኩ ከንድፈ ሃሳብ ባለፈ በተግባር የተደገፈ ትምህርት እንዳልተሰጣቸው ተናግራለች፡፡

 በዚህም ምክንያት ከእነሱ ቀድመው የተመረቁት ጭምር  ለችግሩ መጋለጣቸውን የገለጸችው ተማሪ ብሌን በቂ ትምህርታዊ ጉዞና ጉብኝትም እንደማያድርጉ ጠቁማለች፡፡

በንድፈ ሃሳብ የተማሩትን ወደ ተለያዩ ተቋማት በመሄድ ለመስራት የተግባር ልምምድ እድል ማግኘት እንዳልቻሉ የገለጸው ደግሞ በዩኒቨርስቲው የሶስተኛ ዓመት ተማሪ አማረ ዋለ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት ቀጣሪ ድርጅቶች በምሩቃን ላይ አመኔታ እያጡ መምጣታቸውንም ቀደም ብለው ተመርቀው ከወጡ ጓደኞቹ ተሞክሮ ማወቅ እንደቻለ ተናግሯል፡፡

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አማረ ያዕቆብ በበኩላቸው  ችግሮቹ በትምህርት ተቋማትና በተማሪዎች ዘንድ የሚስተዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

"ጊዜውን ያገናዘበ የትምህርት ስርዓት ያለመቅረፅ፣ ንድፈ ሃሳባዊ ትምህርት ብቻ መስጠት፣ አጫጭር ስልጠናዎችን ያለማዘጋትና ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ያለመስራት ችግሮች ይታያሉ "ብለዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ችግሩን ለመፍታት ተግባር ተኮር የሆቴልና ቱሪዝም ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት አድርጓል፣ ከሚቀጥለው ዓመት  ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የስርዓተ ትምህርት ቀረፃ እያካሄደ ነው፡፡

ዘመኑ የደረሰበት የዘርፉን እድገት ከግምት በማስገባት አዳዲስ ኮርሶችም እንደሚጨመሩ ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ምሩቃን የተለያዩ መድረኮችን፣ ሁነቶችና ፌስቲቫሎችን የማዘጋጀት ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ ለማገዝ በቅርቡ  የቱሪዝምና የሆቴል ሳምንት አዘጋጅቶ ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሳተፉ አድርጓል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 1/2010 ሕፃናት በአገራቸው ባህልና ወግ እንዲያድጉ ለማስቻል የውጪ አገር ጉዲፈቻን የሚከለክለው አዋጅ ጸደቀ።

አዋጁ የጸደቀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ማሻሻሉን ተከትሎ ነው።

በአዲስ መልክ የተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 1070/2010 ህፃናት በኢትዮጵያዊ ባህል፣በተወለዱበት አካባቢ ወግ፣ልማድና ማህበረሰባዊ እሴት እንዲያድጉ ያስችላልም ተብሏል።

የቀድሞው አዋጅ ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ህፃናት በአማራጭነት በውጪ ጉዲፈቻ እንዲያድጉ የሚፈቅድ መሆኑ ይታወሳል።ይህ ግን ሕፃናቱን ባደጉበት አገር ለተለያዩ ወንጀሎችና ማህበረሰባዊ ቀውሶች ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ለውጪ ጉዲፈቻ በሚሰጡት ሕፃናት ላይ የማንነትና የስነ ልቦና ቀውስ ይፈጠርባቸው እንደነበርም ተብራርቷል።

በውጪ ጉዲፈቻ ስም በሕጻናቱ ላይ ህገ ወጥ ዝውውርን ጨምሮ የመብት ጥሰት ይደርስባቸው እንደነበርም ነው የተገለጸው።

ይህንን ችግር ለማቃለልም አዋጁ እንዲሻሻል ተደርጓል።

አዲሱ አዋጅ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻን፣ የአደራ ቤተሰብንና መልሶ ማቀላቀልን በማበረታታት ሕፃናት ከወገናቸው ጋር በአገራቸው ባህል እንዲያድጉ እንደሚያስችል ተብራርቷል።

በዘርፉም በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መኖራቸውና ኢትዮጵያውያን ዜጎችም ለአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ተነሳሽነት ማሳየታቸው አዋጁን ለማሻሻል በመልካም አጋጣሚነት ተወስዷል።

በተመሳሳይም ምክር ቤቱ የፌዴራል የፍትህ አካላት ባለሙያዎች ስልጠና ማዕከልን ከህግና ፍትህ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር የሚያዋህደውን ማቋቋሚያ አዋጅና የፌዴራል የኤሌክትሮኒክ ፊርማ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የወጣውን አዋጅንም ተቀብሎ አፅድቋል።

ሁለት ተቋማት የነበሩ የፌዴራል የፍትህ አካላት ባለሙያዎች ስልጠና ማዕከልና የህግና ፍትህ ስርዓት ምርምር ኢንስቲትዩት ካላቸው አላማና ከሚያከናውኗቸው ተግባራት ተመሳሳይነት አኳያ አንድ ተቋም ሆነው "የፌዴራል የፍትህና የህግ ምርምር ተቋም" ተብለው በአዲስ መልክ በአዋጅ ቁጥር 1071/2010 ተቋቁመዋል።ተቋማቱ ወደ አንድ ተቋምነት መምጣታቸው የተሻለ ስራን ለማከናወን ያስችላል ተብሏል።

በሶስተኛነት ምክር ቤቱ ያፀደቀው የፌደራል ኤሌክትሮኒክ ፊርማ አዋጅ ቁጥር 1072/2010 ሲሆን፤በኤሌክትሮኒክ ንግድና በኤሌክትሮኒክ የተደገፉ መንግስታዊ አገልግሎቶችን ለማበረታታት እንደሚረዳም ታውቋል።

የኤሌክትሮኒክ ፊርማው የመልዕክት ልውውጥን ደህንነትን የሚያረጋግጥና በተለያየ መልኩ የሚገኙ የሃሰተኛ  ማስረጃዎችን ለይቶ ለማውጣት የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 09 January 2018 21:10

ብርሃን ፈንጣቂው ጅምር

            መሀመድ ዓሊ (ኢዜአ)

 ከሰው ልጅ የስሜት ህዋሳት አንዱ የሆነውን የአይን ክፍልን ለአይነ ስውርነት ከሚዳርጉት መንስዔዎች መካከል የአይን ሞራ ግርዶሽ (Cataract) ፣ የአይን ማዝ (ትራኮማ) እና ግላኮማ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 የትራኮማ በሽታ ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል በሽታዎች (Neglected Tropical Disease) ተብለው በተቀመጡ በሽታዎች ተርታ የሚመደብ ነው። ይህ በሽታ በአብዛኛው በግል እና አካባቢ ንፅህና ጉድለት የሚከሰት ሲሆን፣ በከፍተኛ ደረጃ የተፈጥሮ የአይን ብርሃንን የማሳጣት ጉዳት ያደርሳል።

ሆኖም ግን በአግባቡ ህክምና ከተደረገ 80 በመቶ ያህል የአይነ ስውርነት  በማከም ማስወገድ ይቻላል ይላሉ የጤና ባለሞያዎች። 

በሀገራችን ያለውን የአይን ሞራ ግርዶሽ ስርጭት ስንመለከት ሶማሊ ክልል 5 ነጥብ 8 በመቶ መሆኑን  ያመላክታል፡፡

ከዚሁ ቁጥር ውስጥ በቀላሉ አስቀድሞ መከላከል በሚቻል በሽታዎች  ለአይነ ስውርነት የተጋለጡ 400 ሺህ አዛውንቶች መኖራቸውን ይነገራል ፡፡ 

 ቁጥሮች እንደሚያመላክቱት በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች ከፍተኛው ስርጭት የሚስተዋለው በዚሁ በምስራቅ ኢትዮጰያ በሚገኘው ሶማሊ ክልል ነው።

በክልሉ ያለውን  የአይን  ሞራ  ግርዶሽ  ስፋት መነሻ በማድረግ እና ሌሎችም የአይን ህመም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳድግ የጤና አገልግሎት ባልተስፋፋበቸው  የገጠር አርብቶ አደር አካባቢዎች ርብርብ እየተደረገ ነው ።

 የአይን ህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ በሰኔ 2007 ዓ.ም የተቋቋመው ተንቀሳቃሽ የአይን ህክምና ቡድን ዛሬ በአይን ግርዶሽ ሲሰቃዩ የነበሩ በሺዎች ለሚቆጠሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከነበረባቸው  ህመም እንዲላቀቁ መልካም አጋጣሚ ሆኗል፡፡

በክልሉ አፍዴር ዞን ሀርጌሌ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ኢባዱ መዓልን አብዲላሂ ሁለቱም አይናቸው ማየት ተስኖአቸው የወለዷዋቸውን ስድስት ልጆች በአይናቸው ለማየትና ለመንከባከብ የታደሉ አልነበሩም  ይህ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ የአይን ህመም ሲሰቃዩ ቆይተዋል፡፡

ወይዘሮ ኢባዱ በተንቀሳቃሽ የአይን ህክምና ቡድኑ በተደረገላቸው ነጻ  የአይን ቀዶ ህክምና የአይን ብርሃናቸው በበራላቸው ቅጽበት የደስታ ሲቃ እየተናነቃቸው ‘’ዛሬ ሀርገሌ ነው ያለሁት ማየት ቻልኩኝ ’’ ሲሉ ተነፈሱ ።

በሲቲ ዞን ኤረር ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሀመድ ሀሰንም ለሀያ ዓመታት በአንደኛው አይናቸው ማየት እንደማይችሉና ከሶስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሁለተኛው አይናቸው ማየት በማቆሙ ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ያስታውሳሉ ።

 የህክምና ቡድኑ አባላት ወደ አካባቢያቸው መጥተው ባደረጉላቸው ቀዶ ጥገና ከነበረባቸው የአይን ህመም ተላቅቀው የአይን ብርሃናቸው በመመለሱ የተሰማቸውን ደስታ የገለጹት በሚከተለው መልኩ ነበር ። ‘’ትናንት በሰዎች እየተደገፍኩና እየተመራሁ ነበር ህይወቴን የምመራው  ዛሬ ግን  እይታዬን መልሼ አግኝቼዋለሁ ፡፡ በጣም ተደስቻለሁ ። ፈጣሪ ይመስገን’’፡፡

 ለረጅም አመታት ሲሰቃዩበት የነበረውን ከአይን ህመም ነጻ ሆነው ወደ ብርሃን አለም መሸጋገራቸውን  የተናገሩት ሌላዋ የሲቲ ዞን አይሻ ወረዳ ነዋሪ  ወይዘሮ ሐሊማ ኢብራሂም አላሌ ናቸው ፡፡

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ  በዓይናቸው ላይ ችግር እንደተፈጠረባቸው የገለፁት ወይዘሮ ሐሊማ ‘’ማየት አልችልም ነበር ። አጠገቤ ያለውን ውሀና ምግብ ሰው ካልሰጠኝ በስተቀር ወስጄ መጠቀምም ሆነ ልጆቼ ሲያለቅሱ መያዝና መንከባከብ አልችልም ነበር ፡፡ የትናንት ህይወቴ ጨለማ ነበር ። ዛሬ ግን የአይኔ ብርሃን ተመልሶልኛል፡፡ ለዚህ ላበቁኝ ለአላህና ለክልሉ መንግስት ምስጋና አቀርባለሁ ’’ ብለዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ለበሽታው በስፋት መከሰት ምክንያት  የበሽታውን ምንነት አለመረዳት እንደሆነ ግንዛቤ እንዳልነበራቸው ያስረዳሉ። አቶ መሀመድ ሀሰን የተባሉ የወረዳው ነዋሪ  “በፊት ህመሙን ቀለል አድርገን ነበር የምናየው። በምን እንደሚመጣብንም አናውቅም ነበር። ከእድሜ ጋር የሚመጣ አድርገን ስለምናሳብ ምንም ማድረግ አልቻልንም ነበር’’ በማለት ይገልጹታል።

እንደ ወይዘሮ ሐሊማ እና አቶ መሀመድ ሀሰን ሁሉ ሌሎችም እስካ አሁን በተንቀሳቃሽ ህክምና በተሰጠባቸው በክልሉ በ31 ወረዳዎች የሚገኙና በአይን ህክምና እጥረት ለረጅም አመታት ሲሰቃዩ የነበሩት አርብቶ አደር አዛውንቶች የአይን ቆብ ቀዶ ህክምና ተሰርቶላቸው  ብርሃናቸው ወደነበረበት መመለሱን የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀሰን ኢስማኤል ተናግረዋል፡፡

አስፈላጊው የህክምና ቁሳቁስ ያላቸው አስራ ስምንት የህክምና ባለሙያዎችን ያቀፈው የአይን ህክምና ቡድን በክልሉ የተለያየ አከባቢዎችን በመንቀሳቀስ የአይን ቆብ ቀዶ ህክምና በማድረግ እንዲሁም ለአይነ ስውርነት መነሻ የሆነውን የአፍላ ትራኮማ በማከም ፣ መድሃኒትና መነፅር ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች በነፃ በመስጠት በጠቅላላው ከ49 ሺህ ሰዎች በላይ ነፃ የአይን ህክምና ተጠቃሚ ማድረጋቸውንም   ገልጸዋል፡፡

የተንቀሳቃሽ የአይን ህክምና ቡድኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት ያከናወናቸውን ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል በክልሉ የአይን በሽታው ካለው ስፋትና ስርጭት አንጸር ነጻ የህክምና አገልግሎት በማስፋፋት በ2010 በጀት ዓመት 20 ወረዳዎችን ተጠቃሚ በማድረግ የተጀመረው የአይን ብርሀን ጉዞ ተጠናክሮ ለማስቀጠል በቂ ዝግጀት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡

በአብዛኛው በንጹህ ውሃ ጉድለት የሚከሰተውን ትራኮማ የአይን ህመም በሽታውን በዘላቂነት ለመቅረፍ የህብረተሰቡ ግንዛቤ የሚያሳድጉ ስራዎችም እየተሰሩ ይገኛል ብለዋል፡፡

ዋነኛው የአይነ ስውርነት ከሚያመጡ በሽታዎች አንዱ ካትሪክት ወይም የአይን ሞራ ግርዶሽ 49 ነጥብ 9 በመቶ የሚሆነው ከትራኮማ የሚመጣ መሆኑን 2016 በማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተደረገው የዳሰሳ ጥናት አመላክቷል፡፡

በትራኮማ የሚመጣው የአይነ ሞራ ግርዶሽ ለመከላከል የአፍላ ትራኮማ መድኃኒት ተደራሽ በማድረግ ወደ አይነ ስውርነት ከመሸጋገሩ በፊት ለመቆጣጠር የክልሉ ጤና ቢሮ መድኃኒቶችን ለሁሉም ተቋማት ለማሰራጨት ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት በቢሮው የተላላፊ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር  የአይነ ስውርነት መከላከለያ ህክምና ቡድን መሪ አቶ አህመድ በዴ ዱኣሌ ናቸው፡፡

አቶ አህመድ የበሽታው ስፋት መጠን አስደንጋጭ መሆኑን ገልፀው የሚያስቆጨው ነገር በአምስት ሰዎች ላይ ከተከሰተው አይነስውርነት የ4ቱን ቀድሞ በመከላከል ወይም በማከም ማስቀረት የሚቻል መሆኑ ነው ይላሉ 

ከአመት ወደ አመት እየጨመረ የመጣው የአይን ሞራ ግርዶሽ ለማከም በሊባን፣ በአፍዴር፣ በሲቲ፣ በኖጎብ፣ በቆራሃይና ጀረር ዞኖች ከሚገኙ 31 ወረዳዎች ነዋሪ የሆኑና የማየት ችግር ለነበረባቸው  ወገኖች በተደረገላቸው የአይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ዳግም ብርሃናቸውን ማገኘት ችለዋል፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ነው።

በጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አማካይነት በተሰጠው ትምህርት መሰረት መፀዳጃ ቤት መስራታቸውን እና በዚያም እየተጠቀሙ መሆኑን የገለፁት ወይዘሮ ሐሊማ፤ ይህ አይነቱ የጤና ትምህርት የአይን ሞራ ግርዶሽና ትራኮማን አስቀድሞ ለመከላከል የሚደረግ ጥረት ማህበረሰቡን ለመታደግ ያስችላል ብለዋል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች ማህበረሰቡ የራሱንና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ፣ መፀዳጃ ቤቶችን በማዘጋጀትና በአግባቡ በመጠቀም ትራኮማን እንዲካላከል እያስተማሩ መሆናቸውም ለማየት ተችሏል። ለትራኮማ እና ተያያዥ ለሆኑ በሽታዎች ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት ሴቶችና አረጋውን ደግሞ ዋነኛዎቹ የስልጠናው ተሳታፊዎች ናቸው።

እነዚህን ሴቶች በጤና ልማት ቡድን፣ አንድ ለአምስት እና በመሳሰሉት በማደራጀት እርስ በእርሳቸው እንዲወያዩ እና ትምህርት እንዲወስዱ እየተደረገም ይገኛል። ጥረቱ የሚደነቅ ውጤቱ ደግሞ ብርሃን የሚያስፈነጥቅ ነውና በርቱ እንላለን !

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ ጥር 1/2010 በጸረ-ሽብር አዋጁ መሻሻል፣ መሰረዝና መጨመር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎች ድርድር አደረጉ፡፡

ተደራዳሪ ከሆኑት14ቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ባለፈው ታህሳስ 'በጸረ-ሽብር አዋጁ መሻሻል፣ መሰረዝና መጨመር አለባቸው' ያሏቸውን አንቀጾች በጽሑፍ ለኢህአዴግ ማቅረባቸው ይታወሳል።

በዛሬው የድርድር ሂደት ሶስቱ በተናጠልና 11ዱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች በጋራ ዋና ዋና ያሏቸውን የማሻሻያ ሃሳባቸውን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ "የፖለቲካ ስነ-ምህዳር ያጠባሉ፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ  እንቅፋት ይፈጥራሉ" ያሏቸውን የመደራደሪያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። 

ሁሉም ተደራዳሪ ፓርቲዎች "የአገሪቷ ጸረ-ሽብር ህግ አስፈላጊ ነው" ብለው እንደሚያምኑም ነው ያመለከቱት።

ተደራዳሪ ከሆኑት 11ዱ አገር አቀፍ ፓርቲዎቹ በጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ "አሉን" ያሏቸውን አራት የማሻሻያ፣ ስድስት የሚሰረዙና አምስት የሚጨመሩ የአዋጁ የድርድር ሃሳቦች ላይ ማብራርያ አቅርበዋል።

በዚህም ኢህአዴግ የሽብር ድርጊት በባህሪው ካለው ውስብስብነት፣ የወንጀሉ አደገኛነትና ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ አኳያ ጸረ-ሽብር ህጉ ዓለማቀፋዊ ደረጃ ያሟላ፣ ሊሰርዝና ሊሻሻል የሚያስችል ህጋዊ መሰረት ያለው ምክንያት እንዳላገኘበት ምላሽ ሰጥቷል።

በዚህም ኢህአዴግ መሰረዝ አለባቸው የተባሉትን አራቱንና መሻሻል አለባቸው ተብለው የቀረቡትን ስድስት የአዋጁን አንቀጾች በተመለከተ ያልተቀበለበትን ምክንያት አብራርቷል።

በአዋጁ ላይ መጨመር አለባቸው በተባሉት አምስት የአዋጁ አንቀጾች ላይ ግንባሩ  እንደሚስማማና  በአብዛኛው ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ መሆናቸውንም አብራርቷል።

መኢብን ፈንድ የማቋቋሚያና ተከሳሾች በማወቅና ባለማወቅ የፈጸሙትን ጥፋት የማጣራት ሂደትን በተመለከተ ጥያቄ አቅርቧል።

ኢህአዴግ ከፈንድ ጋር በተያያዘ የሚታይ ጉዳይ ካለ እናየዋለን፤ "በማወቅና ባለማወቅ ጸረ-ሽብር ህጉን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎችን በተመለከተ አዋጁ የሚሻሻልበት አሳማኝ ምክንያት የለም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ጸረ-ሽብር አዋጁ "ከአገሪቷ ህገ-መንግስት ጋር ይጣረሳል፣ ህገ-መንግስታዊ መሰረትም የለውም እንዲሁም ራሳቸውን ነፃ ታጋዮች ብለው የሰየሙ ለምን አሸባሪዎች ይባላሉ" የሚል ጥያቄ በኢራፓ በኩልም ቀርቧል።

"አዋጁ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የለውም ማለት በፍፁም የተሳሳተና በምክንያታዊነት ያልተደገፈ ነው" ሲል ኢህአዴግ ማብራሪያ ሰጥቶበታል።

ማንኛውም ግለሰብ ይሁን ድርጅት የውጭና የአገር ውስጥ ዜግነት ይኑረው በሽብርተኝነት ድርጊት ተሳትፎ ከተገኘ በጸረ-ሽብር አዋጁ ጉዳዩ እንደሚታይና ስያሜም እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ኦጋዴን ነፃ አውጪ ይሁን ሌሎች አሸባሪ የሚለውን ስያሜ በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ስያሜው የተሰጣቸው ድርጅቶች መሆናቸውን ግንባሩ  አስታውቋል።

ኢህአዴግ በገዳ ስርዓት አራማጅ በኩል የቀረበውን የማሻሻያና የመቀነስ የድርድር ሃሳብም እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል።

ፓርቲዎቹ በአዋጁ ላይ ተጨማሪ ድርድር ለማድረግ ጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን