አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 08 January 2018

በወልደሚካኤል ገ/መድህን  (አክሱም ኢዜአ )

ባለ3 ሺህ አመት የእድሜ ባለጸጋ፣የታሪክና ስልጣኔ መሰረት፣የነገስታትና የነጻነት አብነት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የ90 ሚሊዮን ህዝብ እናትና የብዝሃነት ማማ፣ የፊደልና የዘመን አቆጣጠር ባለቤት ኢትዮጵያ ስትባል ውስጡ ደስ የማይለው ፍጡር የለም ። እንኳንም የኛ ሆነች እኛም የእሷ ሆንን ያስብላል ።

ካለ ህብር አበባ ውበት እንደሌለው ሁሉ ካለ ብሄር ብሄረ ሰቦችና ህዝቦቿ ኢትዮጵያም  ውበት አይኖራትም ። ከ85 በላይ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አቅፋ የያዘች ሀገር የህልውናዋ መሰረቶች ህዝቦቿ ናቸው ። የህዝቦቿ የአንድነት መሰባሰቢያ አውድማ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት ።

የኢትዮጵያና ህዝቦቿ ሰላም ፣ ልማት ፣ እድገትና ብልፅግና ተጠብቆ የሚኖረው ደግሞ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ልዩነታቸውን ውበታቸው አድርገው ተባብረው ፣ ተከባብረውና ተቻችለው በእኩልነት ላይ የተመሰረተውን አንድነታቸው አጠናክረው ሲቀጥሉ ነው ።

ለፅሁፌ መነሻ የሆነው በአክሱም ዩኒቨርሲቲ “ ቱሪዝም ለሰላምና አብሮነት “ በሚል መሪ ቃል ለ8ኛ ጊዜ  የቱሪዝም ሳምንት ተከብሮ ነበር ። በበዓሉ ላይ ከተሳተፉ ሙሁራን መካከል የታሪክ፣ቋንቋና ፍልስፍና ተማራማሪና በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሃቅ  አንዱ ነበሩ ። ስለ ሰላምና አብሮ መኖር አስፈላጊነትም ንግግር አድርገው ነበር ።

“በአንድ ወቅት በአሜሪካን ሀገር ሳስተምር ኢትዮጵያ የምትባለው ሃገር ታሪክና ስልጣኔ አላት ወይ ? ብለው ተሳታፊዎች ጠየቁኝ “ ብለው ንግግራቸውን ጀመሩ ። “ እንዴ ! ኢትዮጵያ እኮ በመፅሀፍ ቅዱስና በላቲንና በግሪክ ቋንቋዎች ጭምር ተደጋግማ የተጠቀሰች አገር ናት ። የእናንተ አገር ግን አንድ ጊዜም እንኳን አልተጠቀሰም “ በማለት ከጥንት ጀምሮ የምትታወቅ አገር መሆንዋን ነገርኳቸው ይላሉ ።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት  በ6ተኛው ክፍለ ዘመን በሮማዊያን ፕሮኮፒስ በሚል በላቲን ቋንቋ የተጻፈው መጽሓፍ  በአለም ላይ ሶስት ትልቅ መንግስታትና ህዝብ አሉ ።እነሱም ሮም ፣ኢራንና ኢትዮጵያን/አክሱማውያን/ ናቸው ተብሎ ተጽፎ ነበር።ስለዚህ  ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በአለም የታወቀች፣ ትልቅ ስፍራና ታሪክ ያላት አገር ናት ።

ሄግል የተባለው የጀርመን ፈላስፋ  “የራሱ ፊደል የሌለው ህዝብና ሃገር ታሪክ የለውም” ብሎ እንደነበር ፕሮፌሰሩ ይጠቅሳሉ ። ኢትዮጵያ ግን የራሷ ፊደል አላት ። ታሪካችንና ባህላችን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲነገር የነበረና ያለ በመሆኑ  ባለ ደማቅ ታሪኮች ነን በማለት አስረድተዋል።

የሳባውያንና የግእዝ ፊደል ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ባህልዋና ታሪክዋን አስቀምጣ ኖራለች የሚሉት ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሄ ፊደል በመኖሩ በአለም ላይ ከፍተኛ ስፍራ እንድትይዝ እና  ኢትዮጵያ ከመጀመሪያ ጀምሮ የራሷ ጽሑፍና ታሪክ እንዲኖራት ማስቻሉን ገልፀዋል ።

በአለም ላይ የኢትዮጵያ ስም እንደ ባንዴራ እየተውለበለበ ነው ። የዓለም ጥቁር ህዝቦች ለነጻነታቸው ሲታገሉ ኢትዮጵያን ምሳሌ በማድረግ ነው ።

ፕሮፌሰር ኤፍሬም እንደሚሉት አገራችን በብዙ ነገር ለአለም ተምሳሌ ናት ። የኢትዮጵያን እሴቶችና የባህል መገለጫ  የሆኑት መቻቻል፣መከባበር፣አብሮ መኖርና መደጋገፍ  በአለም ማህበረሰብ ዘንድ በተምሳሌትነት እንድትቀመጥ እንዳደረጋት አብራርተዋል ።

የሚያሳዝነው ግን ይህ ለአለም ማህበረሰብ ምሳሌ የሆነውን ባህላችንን፣ታሪካችንና ነጻነታችንን እኛ ኢትዮጵያውያን ራሳችን ትኩረት እንሰጠውም ።ታሪካችንንም አናውቀም ። ስለሆነም ባህላችንን እናጠናክር ! የተማራማሪው ምክር ነው።

በሰዎች መካከል በተለያዩ አጋጣሚዎች እየተፈጠሩ የሚገኙት ግጭቶችና በብሄር ማንነት ላይ የተመሰረተ ገጽታ የሚያላበሱበት ሁኔታ አሳፋሪ እንደሆነ፣የቆየውን አብሮ መኖር፣የመተሳሰብና የመደጋገፍ ባህል ማጠናከር እንደሚገባና ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ወስዶ መንቀሳቀስ እንዳለበት  ሙሁሩ ያሳስባሉ ።

ህዝቡ አብሮ መኖር ይፈልጋል ። ሰላም ይሻል ። የሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤው ህዝብ ነው የሚል እምነት የላቸውም ። ተማርን የሚሉ አንዳንድ ሃይሎች የሚፈጥሩት ነውና ቆም ብለው ሊያስቡበት ይገባል የሚል አስተያየትም  ሰንዝረዋል ።

ልዩነታችን እንደ አበባ ማየት አስፈላጊ ነው ። አበባ ቀይ፣ብጫ፣ነጭ፣ሰማያዊና ሌሎች ህብር እንዳለውና እንደሚያምር  ብዝሃነታችንም  እንደ አበባ ያማረ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ልዩነታችንንና ታሪካችችን አውቀን በማመዛዘን እየኮራንና እየተባብርን ብናድግ  ለመልካም ነገር የሚውል ሀብት ነው ይላሉ ።

ፊት ለፊታችን ያለው ሁለት መንገድ ነው አንዱ የጥፋት ሲሆን ሁለተኛው የሰላም፣ የልማት፣የእድገትና የመተባበር  መንገዱን ይዘን ወደፊት መራመድ አለብን ሲሉም ይመክራሉ ።

ሰላም የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሰረት ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ ለሰላም ዘብ በመቆም ልማታችንን በማፋጠን በእድገት ጎዳና ወደ ፊት በመራመድ ተምሳሌነታችንን ማደስ ይጠበቅብናል ሲሉ ይመክራሉ ።

በመጨረሻ ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ፕሮፌሰር አዱኛው ወርቁ ሰው እንዴት አቃተው በሚል ርዕስ በቅርቡ የለገሱንን  አጭር ግጥም ላካፍላችሁ እና ተወያዩበት።

          ሰው እንዴት አቃተው?

ጦጣን ጦጣ አይገድለው ዝንጀሮን ዝንጀሮ

ጅብን ጅብ አይገድለው ቀበሮን ቀበሮ

ሲደላው ተጫውቶ ሲርበው አድኖ ወይንም ስር ጭሮ

እንስሳን እንኳን ሲኖር እንደዚህ ተባብሮ

ስንት የሚያስብበት እያለው አእምሮ

ከተፈጥሮ ልቆ ብዙ ተመራምሮ

ሰው እንዴት አቃተው መኖር ተከባብሮ?

ሰው እንዴት አቃተው መኖር ተፈቃቅሮ?

 

 

Published in ዜና-ትንታኔ

መቀሌ ታህሳስ 30/2010 በትግራይ ክልል በርካታ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ለቱሪስት መስህብነት አገልግሎት እየዋሉ እንዳልሆነ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በክልሉ መስራቃዊ ዞን አጽቢ ወንበርታ ወረዳ ይበልጥ የሚዘወተረውና "ሁራ ሰለስተ" በሚል የሚጠራውን ባህላዊ ጭፈራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የባህል ፌስቲቫል ትላንት በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ተካሂዷል፡፡

በዝግጅቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም መምህር ኃይላይ በየነ እንዳሉት  በክልሉ  ለቱሪስት እይታ ያልበቁ የመስህብ ስፍራዎች  በርካታ ናቸው፡፡

" እስካሁን በጎብኚዎች ከሚታወቁት የአክሱም ኃውልትና የገርዓልታ ተራራዎች በስተቀር ብዙም አዳዲስ የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች አልተዋወቁም" ብለዋል፡፡

መምህር ኃይላይ እንዳሉት በክልሉ ከ120 በላይ ጥንታዊ ውቅር አብያተክርስቲያናት ፣ ተፈጥሯዊ ጥብቅ የዴስአ ደን፣ በደኑ ብቻ የሚገኝ "ብላክ ዊንግ’’ የተባለ ወፍና የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡

በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ብቻ ከዘመነ አክሱምና ቅድመ አክሱም ጋር የተያያዙ 21 የአርኬዮሎጂ ቦታዎች እንዳሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ጭምር መረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

በስድስተኛው ክፍለ ዘመን የተገነቡ ጥንታዊ ውቅር አብያተክርስቲያናትም በዚሁ ወረዳ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

በመስህብ ሥፍራዎቹ አካባቢ በቂ መሰረተ ልማት አለመዘርጋቱ ጎብኚ ለማጣታቸው አንዱ ምክንያት መሆኑንም መምህር ኃይላይ ጠቅሰዋል፡፡

በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን አለመተዋወቃቸው፣ ከቱሪስት አስጎብኚ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በትብብት አለመሰራቱ የመስህብ ሥፍራዎቹ ለሕብረተሰቡ ጥቅም እንዳይውሉ ማድረጉንም አስረድተዋል፡፡

እንደ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢው ገለጻ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን ለማስተዋወቅ በቅድሚያ የጥናት ሥራዎች ሊካሄዱ ይገባል።

የክልሉ መንግስት መንገድ፣ መብራትና ሌሎች ለቱሪስት ምቾት የሚሰጡ የመሰረተ ልማት ሥራዎችን ማከናወን እንዳለበትም አመልክተዋል።

"ሃይማኖታዊ ቱሪዝም በማዘጋጀት የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ሥፍራዎቹን እንዲጎበኝ የማድረጉ ስራም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል፡፡

" ’ሁራ ሰለስተ’ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ሀገረሰባዊ ጭፍራ ለማድረግ በቅድሚያ ጥልቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ ሌላው ጥናት አቅራቢና በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ መምህር ሳሙኤል ረዲ ናቸው፡፡

ሁራ ሰለስተ በክልሉ በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ከገና በዓል ዋዜማና በበዓሉ ቀን በወንዶች የሚከወን ሳቢ ትእይንት ያለው ባህላዊ ጭፈራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ጭፈራው ከጥንት አመጣጡ ጋር ሳይበረዝ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በቀጣይ ቅንጅታዊ ስራዎች እንደሚያስፈልጉም አመልክተዋል።

ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎች የጠቆሟቸው የዘርፉ ተግዳሮቶች ትክክል መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የአጽቢ ወንበርታ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት ብርሀን ሀጎስ  ናቸው፡፡

በወረዳው የሚገኙ ባህላዊ፣ ጥንታዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን ለማስተዋወቅ የ "ሁራ ሰለስተ ባህላዊ ፌቲቫል"ን በማዘጋጀት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡

በወረዳው ከሚገኙ 24 ጥንታዊ ውቅር አብያተክርስቲያናት መካከል ለሰባቱ በአሁኑ ወቅት በሕብረተሰቡ ጉልበት መንገድ የመጥረግ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

የመስህብ ሥፍራዎቹን ለማስተዋወቅ የተጀመረው ጥረት የአካባቢውን ነዋሪዎች ማስደሰቱን የተናገሩት ደግሞ የአጽቢ ወረዳ ነዋሪ አቶ አታክልት እምባየ ናቸው፡፡

በተለይም የዴስአ ጥብቅ ደንና ጥንታዊ ውቅር አብያተክርስቲያናት እስካሁን በሕብረተሰቡ እንክብካቤ እየተደረገላቸው የቆዩ መሆናቸውን አቶ አታክልት ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ታህሳስ 30/2010 የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸው የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት በማሟላት ኑሯቸውን ማሻሻል እንዳስቻላቸው በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር አስተያየታቸውን የሰጡ አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በተያዘው የበጋ ወቅት በብሄረሰብ አስተዳደሩ እስካሁን ከ82 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ገበያ ተኮር በሆነ ሰብል ለምቷል፡፡

በባንጃ ወረዳ የአስኩና አቦ ቀበሌ አርሶ አደር ተፈራ አባዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ መሆን ከጀመሩ አራት ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡

መሬታቸውን በቡና፣ ሽንኩርት፣ ጥቅል ጎመን፣ ድንችና ስንዴ ሰብል በማልማት ከፍጆታ የተረፈውን ለገበያ በማቅረብ በአንድ የምርት ወቅት እስከ 25 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚሁ ወረዳ የሰንከሳ ሚካኤል ቀበሌ አርሶ አደር እንዳለው አያሌው እንዳሉት በመስኖ ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት በቋሚ አትክልትና የጓሮ አትክልቶች በዓመት ሁለት ጊዜ በማልማት እየተጠቀሙ ነው።

የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት ቀለባቸውን ለመሸፈን ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ ከመስኖ ልማት በዓመት ከ70 ሺህ ብር በላይ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በመስኖ የአፕል ልማትና ችግኝ ዝግጅት ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ስድስት ዓመት እንደሆናቸው የተናገሩት ደግሞ በፋግታ ለኩማ ወረዳ የእንደውሃ ቀበሌ አርሶ አደር መለሰ በሬ ናቸው።

ተክለው ከሚንከባከቧቸው ከ60 የአፕል ተክሎች ከሚያገኙት ምርትና ከአፕል ችግኝ ሽያጭ እስከ 50 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውም የነበረባቸውን የምግብ ክፍተት ከማሟላት አልፈው ኑሯቸውን እያሻሻሉ እንዲመጡ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ግብርና መምሪያ የመስኖ አጠቃቀም ባለሙያ አቶ አበበ ፈንታሁን በተያዘው የበጋ ወቅት የተለያዩ የመስኖ አውታሮችን በመጠቀም ከ110 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እስካሁንም 82 ሺህ 422 ሄክታር መሬት በቋሚ ተክሎችና ገበያ ተኮር በሆኑ ሰብሎች ማልማት ተችሏል፡፡

" በቀጣይም በዕቅድ የተያዘውን ቀሪ መሬት በአንደኛና ሁለተኛ ዙር በማልማት ከ13 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል" ብለዋል ባለሙያው።

በመስኖ ልማቱ ከ175 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሳው የቀረበላቸውን 123 ሺህ 382 ኩንታል ማዳበሪያ እንዲጠቀሙ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።  

ባለፈው ዓመት በዞኑ በመስኖ ልማት የተሳተፉ አርሶ አደሮች በሁለት ዙር ካለሙት መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ታህሳስ 30/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ በአርኪዎሎጂ ቁፋሮ የተገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጥቅም ላይ ሳይውሉ ለጉዳት መጋለጣቸውን የወረዳው ባህልና ተሪዝም ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አንጓች ካሳሁን ለኢዜአ እንደተናገሩት በአርኪዎሎጂ ቁፋሮ የተገኙት እነዚህ ታሪካዊ ቅርሶች  አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን እድሜ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡

ከቅርሶቹ መካከል የጥንታዊ ሰው የእጅ መገልገያ መሳሪያዎች፤ የእንስሳትና የተክሎች ቅሬት አካሎች ይገኙባቸዋል፡፡

"በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአርኪዎሎጂ ትምህርት ክፍል በቁፋሮ የተገኙትን ቅርሶች  በማስተዋወቅም ሆነ ቅርሶቹ በተገኙባቸው ቦታዎች የተደረገ ጥበቃና ክብካቤ ባለመኖሩ ለጉዳት ተጋልጠው "ይገኛሉ፡፡

በቁፋሮው የተገኙትን ቅርሶች ጨምሮ አለምጸሃይ ናውዳርዳና ሀዳር የተባሉት የአርኪሎጂ ስፍራዎቹን ተመራማሪዎች በዘርፉ የጠለቀ ምርምር እንዲያካሂዱ ቦታዎቹን ከልሎ ማስጠበቅ አልተቻለም።

ጽህፈት ቤቱ የአርኪዎሎጂ ስፍራዎቹን ከልሎ ለማስጠበቅም ሆነ በቁፋሮ የተገኙትን ቅርሶች በአግባቡ ለማስቀመጥ የተመደበለት በጀት ባለመኖሩ ያከናወነው ስራ  እንደሌለ ኃላፊዋ  ተናግረዋል፡፡

"በአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የተገኙ ቅሬተ አካላት በአካባቢው ቀጣይነት ያለው ጥልቅ ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ጠቋሚ ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ" ያሉት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ተወካይ አቶ ታድሎ ጥሩ ናቸው፡፡

ጓንግ የተባለውን ወንዝ ተከትሎ የተገኙት ከድንጋይ የተሰሩት የጥንታዊ ሰው የእጅ መገልገያ መሳሪያዎች በአካባቢው የሰው ዘር አመጣጥን ለማጥናት አማራጭ መንገዶች እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አስናቀው አዳነ በበኩላቸው በአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የተገኙትን ቅርሶችና ስፍራዎች ለመጠበቅም ሆነ ለማስተዋወቅ በቀጣይ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

በአርኪዮሎጂ ዘርፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቱሪዝም ትምህርት ክፍሎች የጥናትና ምርምር በማካሄድ ዘርፉን ሊደግፉ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

በጎንደር ዩንቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር አውግቸው አማረ ዩንቨርሲቲዎች በቅርስ ጥበቃና ልማት ዙሪያ በባለቤትነት እንዲሰሩ የህግ ማእቀፍ ሊዘጋጅላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉም የጠለቀ ምርምርና ጥናት እንዲያካሂዱም ለፕሮጀክቶች ቀረጻ ስራ በቂ በጀት ሊመደብላቸው እንደሚገባም እንዲሁ፡፡

ከሀገር ውስጥና ከውጪ ሀገር የተውጣጡ ከፍተኛ የአርኪዮሎጂ ፣የአንትሮፖሎጂና የአንቶሎጂ የተመራማሪዎች ቡድን ጭልጋን ጨምሮ በመተማና በቋራ አካባቢዎች ጥናትና ምርምር ለማካሄድ ሰሞኑን ወደ ስፍራዎቹ መንቀሳቀሳቸውን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታውቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/2010 ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በኩባ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ፕሬዚዳንቱ ለጉብኝት ወደ ኩባ ያቀኑት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ራውል ካስትሮ  ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት ነው።

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በተለይ ሁለቱ አገሮች  በትምህርት፣ በጤናና በቴክኖሎጂ ዘርፎች  ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ከኩባ ባለስልጣናት ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።

በተያያዘ ዜና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዛሬ ገብተዋል።

በነገው ዕለትም ከአገሪቱ አቻቸው ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን እንዲሁም ከሰራተኛና የሰው ኃብት ሚኒስትር ጋር  የሁለቱን አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚመክሩ በመግለጫው ተመልክቷል።

Published in ፖለቲካ

ጎባ ታህሳስ 30/2010 የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ከ90 በላይ ማህበረሰብ ተኮር የምርምር ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን ገለጸ ፡፡

ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተካሄዱ ያሉት እነዚህ የምርምር ፕሮጄክቶች ከመማር ማስተማር ስራው በተጓዳኝ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው የምርምር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የምርምር ፕሮጀክቶቹ  በግብርና፣ በጤና፣ በተፈጥሮ ሀብትና በሌሎች ስምንት የትኩረት መስኮች ላይ ናቸው፡፡

ለማስፈጸሚያም  10 ሚሊዮን ብር  በጀት  መመደቡን ያመለከቱት ዶክተር ስሜነህ " ከ200 በላይ መምህራንና ተማሪዎችም በምርምሩ ዘርፍ በመሳተፍ ላይ ናቸው" ብለዋል ።

ዩኒቨርሲቲው የአርሶና አርብቶ አደሩን የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማቀላጠፍ  በባሌ  ሮቤ፣ መዳ ወላቡና ጊኒር ወረዳዎች የምርምር ጣቢያ ከፍቶ እየሰራ ይገኛል ፡፡

በምርምርና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሴት መምህራን ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግም በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ዶክተር ስሜነህ እንዳመለከቱት ባለፉት ዓመታት በዩኒቨርስቲው ምሁራን ከተካሄዱት ምርምሮች መካካል የተሻሉትን በመምረጥ በዩኒቨርሲቲውና አለም  አቀፍ እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ  ለህትመት እንዲበቁ ይደረጋል ።

በጊኒር ወረዳ ሀረዋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሀሰን ሻፊ  በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በአካባቢያቸው  በከፈተው የምርምር ጣቢያ የግብርናና የእንስሳት መኖ ልማት ዘዴ የተሻለ እውቀት በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

" ከዩኒቨርሲቲው ምርምር ጣቢያ ባገኘሁት እውቀት ስንዴ በመስመር በመዝራቴና የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም  ከአንድ ሄክታር እስከ 75 ኩንታል ስንዴ ማምረት ችያለሁ" ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት በአካባቢቸው የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን የመጠቀም ባህላቸው አነስተኛ በመሆኑ የሚያገኙት የምርት ውጤትም ዝቅተኛ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ በመዳ ወላቡ ወረዳ  የመዳ ቀበሌ አርሶ አደር ሁሴን ከዲር ናቸው፡፡  

ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢያቸው በከፈተው የምርምር ጣቢያ ባገኙት ልምድ በመታገዝ በሄክታር እስከ 50 ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በ1999 ዓ.ም ከተቋቋመ ወዲህ ከ230 በላይ ማህበረሰብ ተኮር ምርምሮችን አካሄዷል፡፡

የምርምሩ ውጤቶቹንም ለአርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም ለሌላውም ማህበረሰብ ተደራሽ ሆኖ እንዲጠቀምበት በሲፖዚየም፣ በመስክ ቀን በዓል፣ የተጀመሩ የምርምር ጣቢያዎችን በማስፋፋት የማስተዋወቁ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉም ዩኒቨርስቲው አመልክቷል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ 30/2010 ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎቹ ነዳጅ ምርቶች ዋጋ በጥር ወርም በነበሩበት እንዲቀጥሉ የንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው እስከ ጥር 30 ቀን 2010 ዓ.ም ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎቹ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በነበረበት ይቀጥላል።

የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በአዲስ አበባ በታህሳስ ወር ሲሸጥበት ከነበረው 21 ብር ከስድስት ሳንቲም 40 ሳንቲም ጭማሪ በማድረግ 21 ብር ከ46 ሳንቲም እንዲሸጥ ተወስኗል።

መንግስት እያከናወነ ያለውን የገበያ መረጋጋት ስራ የበለጠ ውጤታማ ለማድረግና የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ በአገር ውስጥ ገበያ አለመረጋጋትን እንዳይፈጥር ከአውሮፕላን ነዳጅ በስተቀር የሌሎቹ የነዳጅ ምርቶች ዋጋ በነበሩበት እንዲቀጥል መደረጉ ተጠቁሟል።

በዓለም አቀፍ ገበያ የሚኖረውን የነዳጅ ዋጋ መነሻ በማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ሚኒስቴሩ በመግለጫው ጠቁሟል።

 

Published in ኢኮኖሚ

መቱ ታህሳስ 30/2010 በኢሉአባቦር ዞን ባለፉት አምስት ወራት ከ10 ሺህ 500 በላይ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች መሰማራታቸውን የዞኑ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አብዲሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ወጣቶቹ በ1ሺህ 700 ማህበራት የተደራጁና በግብርና፣ በግንባታ፣ በጥቃቅን ንግድ፣ በአገልግሎትና በመሳሰሉት የሥራ መስኮች የተሰማሩ ናቸው፡፡

ከወጣቶቹ መካከል 5 ሺህ ያህሉ በ790 ማህበራት ተደራጅተው በተዘዋዋሪ ልዩ ፈንድ ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን ቀሪዎቹ በመደበኛው ዘርፍ ወደ ሥራ የገቡ ናቸው፡፡

በተዘዋዋሪ ልዩ ፈንድ ወደ ሥራ ከገቡት መካከል 1ሺህ 36 የሚሆኑት ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ መስኮች በዲግሪና በዲፕሎማ የተመረቁ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ በመደበኛውና በልዩ ፈንድ ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶች ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር ገንዘብ ተሰጥቷል፡፡

ከእዚህ በተጨማሪም በገጠርና ከተሞች አካባቢ ከ952 ሄክታር በላይ የመስሪያና መሸጫ ቦታ እንዲሁም 74 ሼዶች ለወጣቶች እንደተሰጡም ተናግረዋል።

ለወጣቶቹ ብድርና የመስሪያ ቦታ ከመስጠት ጎን ለጎን ከተለያዩ መንግስታዊና የግል ተቋማት ጋር ከ44 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል፡፡

እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስም ከ52 ሺህ በላይ ወጣቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ታቅዶ  የተጠናከረ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

በመቱ ከተማ በኬክና ዳቦ አቅርቦት የሥራ መስክ የተሰማራው ወጣት ገመቺስ አለሙ በበኩሉ እንዳለው በዚህ ዓመት ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በብድር ባገኙት 30 ሺህ ብር ራሳቸውን ለመለወጥ እየሰሩ ነው፡፡

"ለሥራችን ስኬት በከተማው ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር ተፈጥሮልና"ያለው ወጣቱ፣ ከ90 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የመስሪያ ቁሳቁስ በሊዝ መልክ ማግኘታቸውንም አስረድቷል፡፡

መንግስት የብድር ገንዘብ አመቻችቶ ወደ ሥራ ለማስገባት እያደረገ ባለው ጥረት ሁሉም ወጣቶች ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውን መለወጥ እንዳለባቸው መክሯል፡፡

በከተማው በእንጨትና ብረታ ብረት የሥራ መስክ የተሰማራው ወጣት አብዱ መልካ በበኩሉ፣ በተመረቀበት የብረታ ብረት ሙያ ወደ ሥራ ገብቶ ውጤታማ መሆን እንደጀመረ ተናግሯል፡፡

" ከስራችን መስፋፋት ጋር በተያያዘ የቦታ መጣበብ ችግር እየሆነብን ነው" ያለው ወጣቱ መንግስት እንደ ገጠሩ ሁሉ በከተሞችም ወደ ሥራ ለሚገቡ ወጣቶች ሰፊ የመስሪያ ቦታ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡

ከዞኑ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በዞኑ ባለፈው አመት በ1 ሺህ 130 ማህበራት የተደራጁ ከ38 ሺህ በላይ ወጣቶች በገጠርና በከተሞች በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር ታህሳስ 30/2010 የእንጅባራ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ስድስት ወራት ከኮንፍረንስ ቱሪዝም ከስድስት ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ፡፡

የአስተዳደሩ ባህል፣ ቱሪዝም፣ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት እንዳለው ከተማዋ በፍጥነት ከማደጓ ጋር ተያይዞ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል እየሆነች መጥታለች።

ባለፉት ስድስት ወራት የተገኘው ገቢም ወደ ከተማዋ ለኮንፍረንስ ቱሪዝም ከመጡ 9 ሺህ 100 የሃገር ውስጥ ተሳታፊዎች መሆኑን በጽህፈት ቤቱ የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ አቶ አገኝ ገድፍ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ገቢውን ያገኙትም 130 በሆቴልና ቱሪዝም፣ በምግብ ቤትና ሌሎች አገልግሎት ሰጭ ተቋማት የተሰማሩ ናቸው።

ባህላዊ ገጽታን ተላብሰው በሚዘጋጁ የጀበና ቡና አቅራቢዎች፣ በጫማ ጠረጋና መሰል አግልግሎት ሰጭ ስራዎች የተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ጭምር ተጠቃሚ መሆናቸውን የቡድኑ መሪ ተናግረዋል።

"አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ደንበኞቻቸውን የሚያረካ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡና የሰለጠኑ ባለሙያዎችን እንዲቀጥሩ ጥረት እየተደረገ ነው "ብለዋል።

ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተሳታፊዎች ተመጣጣኝ የዋጋ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው "እስከ ዓመቱ መጨረሻም ከ30 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች እንደሚመጡ ይጠበቃል" ብለዋል፡፡

በከተማዋ የሆቴል ባለቤት አቶ ገነቱ መኮነን በበኩላቸው ከአራት ዓመት በፊት በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ሆቴላቸው 30 የመኝታ አልጋዎችና ሦስት የመሰብሰቢያ አዳራሾች እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም  የመሰብሰቢያ አዳራሾችም ሆነ የመኝታ አልጋዎች በተሰብሳቢዎች እንደሚያዙ አመልክተው፤ ይህም ሌሎች አዳዲስ ባለሃብቶችን እየሳበ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ከተማዋ ወደ ህዳሴው ግድብና ወደጃዊ ስኳር ፋብሪካ በሚወስደው አማካኝ ቦታ ላይ መገኘቷና የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ መገንባቱ ደግሞ ለዕድገቷ መፋጠን ተጨማሪ አቅም እንደሆኑም አቶ ገነቱ ጠቁመዋል። 

ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ተሳታፊዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት አስተናጋጆችና ስራ አስኪያጆች በሆቴልና በቱሪዝም ዘርፍ  የተመረቁ ባለሙያዎችን በመቅጠር ያገኙትን እድል ለመጠቀም እየሰሩ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሆቴል ባለቤት አቶ ጥላሁን ተሰራ ናቸው፡፡

በከተማው በጀበና ቡና ስራ የተሰማራችው ወጣት ውዴ ታከለ በበኩሏ ቀደም ሲል የከተማዋ እንቅስቃሴ ቀዝቃዛና ለስራ ምቹ ሁኔታ እንዳልነበረ ገልጻለች፡፡

ወጣቷ እንዳለች አሁን  ሳምንቱን ሙሉ ስብሰባ እንደማይጠፋና እርሷም ባሏት በርካታ ተጠቃሚ ደንበኞች የተሻለ ገቢ እያገኘች  ነው፡፡

የምታገኘውን ገቢ በአግባቡ በመቆጠብ በቀጣይ በምግብ ቤት ስራ ለመሰማራት ማቀዷንም ወጣት ውዴ ጠቅሳለች፡፡

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና ከተማ እንጅባራ ባለፈው በጀት ዓመትም ከ24 ሺህ 500 በሚበልጡ ተሳታፊዎች መጎብኘቷም ተመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ታህሳስ 30/2010 በመኽር ወቅት በተለያዩ ሰብሎች ከለማው መሬት እስካሁን ድረስ 87 በመቶ የሚሆነው ታጭዶ መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እንየ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ሰብሉ የተሰበሰበው በ2009/2010 የመኽር ወቅት ከለማው ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው።

በብርዕ፣ በአገዳ፣ በቅባት፣ በጥራጥሬና በሌሎች ሰብሎች ከለማው መሬት ዘግይተው ከተዘሩትና ከደጋማ አካባቢዎች በስተቀር እስካሁን አብዛኛው ሰብል ታጭዶ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

ያልተሰበሰበውን ቀሪ ሰብል እስከ ጥር ወር አጋማሽ ድረስ ሙሉ በሙሉ አጭዶ ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

"በመኽሩ የዝናቡ አጀማመርና ስርጭት የተሻለ ከመሆኑ በተጨማሪ የከፋ የተፈጥሮ አደጋ አለመከሰቱ ይገኛል ተብሎ በዕቅድ የተያዘውን 133 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንዲጠበቅ አድርጎታል" ብለዋል።  

ከእዚህ በተጨማሪ 4 ሚሊዮን 152 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና 143 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ከማዋል ባለፈ ሰብልን በኩታ ገጠም ማልማት መቻሉ ምርቱን እንዲጠበቅ ያደረገ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ወይዘሮ እንየ አስረድተዋል።

በተለይ በበቆሎ ሰብል ላይ ተከስቶ የነበረውን አሜሪካን መጤ ተምች በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ ኬሚካል በመርጨትና በባህላዊ መንገድ ለመከላከል በተደረገ ርብርብ ውጤት በመገኘቱ የራሱ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግረዋል።

ባላቸው ሁለት ሄክታር ተኩል መሬት ላይ ያለሙትን የበቆሎ፣ ጤፍና ዳጉሳ ሰብል ሙሉ በሙሉ አጭደው መሰብሰባቸውን የገለጹት ደግሞ በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ የጎምባት ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ሹመት በለጠ ናቸው።

ስድስት ኩንታል ማዳበሪያ ተጠቅመው በማልማታቸውም ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ወረዳ እግዚአብሔርአብ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር አለሙ ጫኔ በበኩላቸው በመኽር ያለሙትን ሰብል አጭደው በመሰብሰብ ወደጎተራ ለማስገባት በመውቃት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት በክልሉ በመኽር እርሻ ከለማው መሬት ከ95 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን