አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 07 January 2018

ነቀምቴ ታህሳስ 29/2010 አንድም ሰው በኤች.አይ.ቪ /ኤድስ እንዳይያዝ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኞች ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጅማ ፣ ነቀምቴና አካባቢው የሚገኙ ሠራተኞች " አሁንም ትኩረት ለኤች.አይ.ቪ መከላከል" በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀንን ትናንት በነቀምቴ ከተማ አክብረዋል ።

የበዓሉ ተሳታፊዎች በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የሕብረተሰቡን መዘናጋት ተከትሎ የበሽታው ሥርጭት እየጨመረ መጥቷል።

የበሽታውን ስርጭት በመከላከል "አንድም ሰው በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እንዳይያዝ " የበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ከታሳታፊዎቹ መካከል ወይዘሪት ዛራ አሊ በሰጡት አስተያየት፣ በበሽታው ሴቶች ይበልጥ ተጠቂ በመሆናቸው ራሳቸውን ከመጠበቅ ባለፈ ሌሎችን በመምከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

"ሚዲያው ስለ በሽታው ስርጭትና አሁን ያለበትን ደረጃ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መስራት ይኖርበታል" ብለዋል ።

ሌላው ተሳታፊ አቶ ብርሃኑ ዘለቀ በበኩላቸው የበሽታውን ስርጭት መግታት የሚቻለው  ሁልጊዜ  ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ሲቻል  ነው ብለዋል።

የኤች.አይ.ቪ/ኤድሰ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አሻግሬ ጥላሁን የተባሉ ሠራተኛ በበኩላቸው በሽታው ከጥንቃቄ ጉድለት የሚመጣ በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ ጥንቃቄ በማድረግ ሕይወቱን እንዲጠብቅ መክረዋል።

ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖችም የጸረ ኤች አይ ቪ መድኃኒቱን በአግባቡ በመውሰድ እንደማንኛውም ሰው ሰርቶ መኖር እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሠራተኞች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ ምርከና ዳንዴሣ በበኩላቸው "ኤች.አይ.ቪ. ከድህነት ቀጥሎ በዋነኛነት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን እየጎዳ ያለ በመሆኑ ልንታገለው ይገባል" ብለዋል፡፡

በዓሉ የቫይረሱን ስርጭት በጋራ ለመከላከል የሚያስችል መረጃ ለመለዋዋጥ፣ ራስን ለማዳን ቃል ለመግባት፣ ሌሎችን ከበሽታው ለመታደግ  ቁርጠኛ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ታቅዶ መዘጋጀቱንም አስረድተዋል ።

"ቀኑንና ዓመት ጠብቆ  ማክበር ብቻ ሳይሆን በየቀኑ ሰዎች በኤች.አይ.ቪ እንዳይያዙ መስራት አለብን" ያሉት አቶ ምርከና፣ ሁሉም የድርሻውን አስተዋጽኦ ማድረግ ከቻለ ስርጭቱን በአገር ደረጃ መግታት እንደሚቻል አስረድተዋል ።

በበዓሉ ላይ ሠራተኞቹ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነጻ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የደም ምርመራ አድርገዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ታህሳስ 29/2010 በፍጆታ ዕቃዎች ላይ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር አምራቹና ሸማቹ ማህበረሰብ ገበያን በማረጋጋት በኩል ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለባቸው የአዳማ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

የገናና ጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ሀገር አቅፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ትናንት በአዳማ ከተማ ተከፍቷል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የከንቲባዋ ተወካይ አቶ ቱራ ግዛው በእዚህ ወቅት እንዳሉት በፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚኖራውን የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር አምራቹና ሸማቹ ገበያ በማረጋጋት ተግባር የተቀናጀ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል።

በሸቀጦችና የግብርና ምርቶች ላይ የሚኖረው የዋጋ ጭማሪ የከተማዋንና አካባቢውን ሕብረተሰብ እንዳይጎዳ ከማድረግ ባሻገር የገበያ ግሽበት እንዳይከሰት መቆጣጠር ተገቢ እንደሆነም አመልክተዋል። 

"የንግድ ትርዒትና ባዛሩ ዓለማ ሕዝባዊ በዓላትን ምክንያት በማድረግ በሸቀጦችና የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ አምራችና ሸማቹ በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነው" ብለዋል ።

ሕብረተሰቡ የግብርና ምርቶችን ጨምሮ ሁሉንም ሸቀጦችና የፍጆታ እቃዎች በአንድ ቦታ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ በማድረግ በኩልም ባዛሩ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

የአዳማ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፈይሳ አራርሳ በበኩላቸው ባዛሩ በበዓላት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረት በማረጋጋት ሕብረተሰቡ እንዳይጎዳ ለማድረግ ሲባል መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የገናና ጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀው ሀገር አቅፍ የንድግ ትርዒትና ባዛር አምራቹንና ሸማቹን ሕብረተሰብ የሚያቀራርብ መሆኑም ገልጸዋል።

በባዛሩ ላይ ከ300 በላይ የንግድ ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የከተማዋን የንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰት ለማሳለጥም ሆነ ገቢዋን ለማጠናከር ባዛሩ የጎላ ፋይዳ እንዳለው የገለጹት ደግሞ የአዳማ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፍት ቤት ኃላፊ አቶ ሻምበል ወርቅነህ ናቸው።

ባዛሩ በከተማዋ በበዓላት ወቅት የሚኖረውን ህግ ወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጭምር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

በንግድ ትርኢትና ባዛሩ ላይ የግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ የኢንዱስትሪ ውጤቶችና ሌሎች ተዛማጅ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ ላይ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አቶ ሻምበል አመልክተዋል።

በንግድ ትርዒትና ባዛሩ ላይ ሲሸምቱ የተገኙት አቶ ዳምጠው አለሙ ሁሉም የፍጆታ እቃዎችና ሸቀጦች በተመጣጣኝ ዋጋ በባዛሩ ላይ መቅረባቸውን ተናግረዋል።

በባዛሩ ላይ  ምርቶች ይዘው ከቀረቡት መካከል አቶ ተስፋዬ ባለሚ በበኩላቸው በከተማዋ በሚካሄደው የንግድ ትርዒትና ባዛር ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ስምንት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ታህሳስ 29/2010 የላል ይበላ የገና በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ በድምቀት መከበሩን የላል ይበላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የከተማው ምክትል ከንቲባና የባህል፣ ቱሪዝም፣ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሌ ንጋቴ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ ከ200 ሺህ በላይ ምዕምናን በተገኙበት ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠበቆ በሰላምና በድምቀት ተከብሯል።

በዓሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር ቀደም ሲል የተደራጁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ምዕምናኑን በትህትናና በአክብሮት በማስተናገድ የጎላ ሚና መጫወታቸውን ገልፀዋል።

የአካባቢው ህዝብ ገንዘብ በማዋጣት ለበዓሉ የመጡት ምዕመናንን ጾማቸውን እንዲገድፉ ከማድረግ ባለፈ መንገድ በመምራትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን መወጣቱን አመልክተዋል።

የፀጥታ አካላትም ከህዝቡና ከበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ጋር በመተባበር በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ያደረጉት ዝግጅት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ማስቻሉን ተናግረዋል።

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተጠፋፉ ቤተሰቦችን በማገናኘትና የተሰረቁ ንብረቶችን ለባለቤቶቹ በማስመለስ በኩል የጎላ ሚና ነበራቸው።

ከወጣቶቹ ጋር በቅንጅት በተሰራው ሥራም 12 ሞባይሎችንና ሌሎች ንብረቶችን የሰረቁ ሌቦች መያዛቸውን አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ የሃሰት የምንኩስና ልብስ ለብሰው ለማጭበርበር ሲሞክሩ የተገኙ ሦስት ሰዎችም መያዛቸውን ነው የገለጹት።

በበዓሉ ላይ ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የመጡ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ሁለት ሺህ 500 የውጭ ሃገር ዜጎችም ተገኝተዋል።

"የበዓሉ በሰላምና በድምቀት መከበር የሀገሪቱን ገጽታ ለመላው ዓለም ለማሳየት የሚያስችል ከመሆኑ ባለፈ የተሻለ የቱሪስት ፍሰት እንዲኖር የሚያግዝ ነው" ብለዋል

በዚህ ዓመት የበዓሉ ተሳታፊዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጭማሪ እንዳለው የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ በበዓሉ ላይም የሃይማኖት አባቶች፣ የፌደራልና  የክልል የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2010 ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ምስራቃዊውን ድንበሯን እንደዘጋች በይፋ አስታውቃለች።

አገሪቷ ይህን ያስታወቀችው በከሰላ ግዛት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን  ማስፈር ተከትሎ ነው። በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገሮች መካከል ውጥረት አይሏል።

እንደ ሱዳን ዜና አገልግሎት /ሱና/ ዘገባ ግን በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ድንበር መዘጋቱን ነው ያመለከተው።

የሱዳን መንግስት ወታደሮቹን ወደ ስፍራው የላከው በከሰላ ግዛት ታውጆ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ህግ ወጥ መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር፣ ህጋዊ ያልሆኑ ተሽካርካሪዎችን ለመሰብሰብ እንዲሁም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል መሆኑን ማስታወቁ ተዘግቧል።

የከሰላ ግዛት ገዢ ሚስተር አዳም ጃማ በአካባቢው የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ ከታህሳስ 27 ምሽት ጀምሮ ከኤርትራ ጋር የሚያዋስነው ድንበር እንዲዘጋ ትዕዛዝ ተላልፏል።

ኤል ላፋ የተሰኘች መሳለጫ በኩል የሚደረገው የህዝቡ እንቅስቃሴም በአካባቢ የታወጀውን አዋጅ የተከተለና ህግና ደንብን ያከበረ መሆን አለበት።

ባለፈው ወር በምዕራብ ሱዳን በምትገኘው ሰሜን  ኮርዶፋን ግዛት እንዲሁም በምስራቅ ሱዳን በምትገኘው ከሰላ ግዛት የሱዳን መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ

ጋምቤላ ታህሳስ 29/2010 የሕብረት ሥራ ማህበራትን በማጠናከርና በማስፋፋት ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ማስቀጠል እንደሚገባ የፌደራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው በጋምቤላ ክልል በየደረጃው ከሚገኙ የአመራር አካላት ጋር በሕብረት ሥራ ማህበራት አደረጃጀት ላይ ውይይት አካሂዷል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር በመድረኩ ላይ እንዳሉት ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጎዳና ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት ስኬታማ እዲሆን በየአካባቢው የሚገኙ የሕብረት ሥራ ማህበራት ሊጠናከሩ ይገባል፡፡

ኤጀንሲው የሕብረት ሥራ ማህበራትን በማስፋፋትና ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ዘርፉ ለማስገባት ትኩረት አድጎ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑንም ጠቁመው ይህን እውን ማድረግ እንዲቻል በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በዘርፉ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች ከ82 ሺህ በላይ መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት፣ ከ380 በላይ የሕብረት ሥራ ዩኒዮኖችና 3 የሕብረት ሥራ ፌዴሬሽኖችን በማደራጀት ከ17 ሚሊዮን በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ዘርፉን በማስፋፋትና በማጠናከር ሀገሪቱ ድህነትን ለመቀነስ እያደረገች ያለውን ጥረት እውን ለማድረግ አመራር አካላት በየአካባቢው ለሚገኙ ማህበራት የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ አስገንዝበዋል።፡

በተለይም ለማህበራቱ እድገትና መጠናከር እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመቅረፍ በኩል ሚናቸው የጎላ መሆን አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ኤጀንሲው ያሉትን ችግሮች በጋራ ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የርዕሰ መስተዳደሩ ተወካይ አቶ ማይበር ኮር በበኩላቸው፣ በክልሉ ያለው የሕብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴ ውስን መሆኑን ገልጸዋል።

"በቀጣይ የክልሉ መንግስት በዘርፉ የሚታየውን ችግር በመፍታት የክልሉን ስር አጥ ወጣት ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በኩላቸው በሰጡት አስተያየት በክልሉ ያለው የሕብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴ ደካማ ከመሆኑም ባለፈ በተደራሽነትም ውስንነት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ኡጁሉ ጊሎ  ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ የሕብረት ስራ ማህበራት እንቅስቃሴ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የተገደበ በመሆኑ በዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ውሱን ነው።

እንደ አቶ ኡጁሉ ገለጻ፣ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታትና የሕብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በኩል የክልሉ ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡

"የሕብረት ሥራ ማህበራትን በባለቤትነት ስሜት በመያዝና ለማህበራቱ አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረግ በኩል አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት" ያሉት ደግሞ ሊላው አስተያየት ሰጪ አቶ ደፋር ተሬሳ ናቸው፡፡

ከክልሉ ሕብረት ሥራ ማህበራት ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በጋምቤላ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው 902 የተደራጁ መሰረታዊና  ሦስት ዩኒየን ማህበራት ይገኛሉ።

ማህበራቱ በተለያዩ ዘርፎች በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ እስካሁንም በክልሉ ለሚገኙ ከ18 ሺህ 300 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 29/2010 ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲናና የአለም ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም በ"ስብሰባ ቱሪዝም" ዘርፍ የምታደርገው እንቅስቃሴና የምታገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑ ተገለፀ።

ዘርፉ እንዲያድግ ዘርፉን የሚመራ ተቋም መፈጠርና የባለድርሻ አካላት አሰራር ቀልጣፋ መሆን ያስፈልጋል ተብሏል።

ኢትዮጵያ አለም አቀፍ  ስብሰባዎችንና ባዛሮችን በማስተናገድ ረገድ ገና ጅምር ላይ መሆኗ ነው የሚገለፀው።

በአገሪቷ እያደገ ያለው የሆቴሎችና የቱሪስት መዳረሻዎች  ብዛት ከሚፈጥረው መልካም አጋጣሚ አኳያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በማስተናገድ ረገድ  መሰራት ካለበት በታች እየተከናወነ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።

ጆርካ ኤቨንትስ ሁነቶችን ከማዘጋጀት ባለፈ ዓለም አቀፍ የሆኑ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው።

የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ወጣት  ነብዩ ሰለሞን፤ በዘርፉ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታዎች ቢኖሩም የስብሰባ ቱሪዝም ገና ያልተነካና በሚፈለገው ደረጃ ያልተሰራበት ኢንቨስትመንት መሆኑን ይናገራል።

ሆኖም ከሶስት ዓመት በፊት ወደ ስራ ለመግባት ቢያስብም ፈቃድ የሚሰጡ አካላት በር ክፍት አለመሆኑን ጠቁሟል።

የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ስራውን ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ክፍተቱን ለመድፈንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችንና ኤግዚቢሽኖችን ለማዘጋጀት በእንስቃሴ ላይ ያለው የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል አክስዮን ማህበር የማዕከላት ግንባታ ጀምሯል።

የአዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን አክስዮን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አያሌው አባይ እንደሚሉት፤ አገሪቷ የአፍሪካና የአለም ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም ከዘርፉ የሚፈለገውን ጥቅም እያገኘች አይደለም።

ከተሰራበት ውጤት ሊያስገኝ የሚችልና ተጠቃሚ የሚያደረጉ መልካም አጋጣሚዎች መኖራቸውን ይገልፃሉ።

የዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግም "ከቪዛና ከገቢዎች ጋር ተያይዞ ያለው ሂደት ቀላልና ፈጣን ሊሆን ይገባዋል" ብለዋል።  

ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ለማዘጋጀት ጠንካራ አካል ባለመኖሩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን ዘርፉን መቀላቀል ትርፋማ እንደሚያደርግ በማሰብ ወደ ግንባታ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በዘርፉ ትልቅ አሻራን እያሳረፉ ከሚገኙ ድርጅቶች መካከል ኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ግሩፕ አንዱ ሲሆን፤ ከስብሰባ ቱሪዝም ያን ያህል ተጠቃሚ እንዳልተሆነ ነው ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አቶ ቁምነገር ተከተል የሚናገሩት።

በመንግስት በኩል  የሚመጡ ስብሰባዎች ቢኖሩም ከየተቋማቱ ስራ ጋር ያላቸው ግንኙነት  ቅንጅት ስለሌላቸው በስብሰባ ቱሪዝም ላይ ሰርተዋል ሊባል እንደማይችል ይጠቅሳሉ።

ከዚህ ሌላ ዘርፉን የሚያስተባብርና የሚቆጣጠር ህጋዊ አካል በሌለበት ሁኔታ "ዘርፉ ራሱ እግር አውጥቶ ይራመድ" ማለት ቅዠት እንደሆነም ነው የሚያክሉት።

ዘርፉ እንዲያድግና አገሪቷም ሆነች በዘርፉ የሚሰማሩት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከፖለቲካዊ ስብሰባ ባሻገር የቢዝነስ ስብሰባዎች ላይ መሰራት እንዳለበት ይጠቁማሉ።

የቢዝነስ ስብሰባን በስፋት ማዘጋጀት የአገሪቷን የውጪ ምንዛሪ ችግር እንደሚያቃልልና ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም ከፍ ሊል እንደሚችል ይገልፃሉ።

በዓለም ላይ  ከ10 ሺዎች በላይ አባላት ያላቸው ከ24 ሺ በላይ የተለያዩ ማህበራት አቅደው በየጊዜውና በየዓመቱ ስብሰባ ስለሚያደርጉ በእነርሱ ላይ ብቻ እንኳን መስራት ከፍተኛ ገቢ እንደሚያስገኝ ያስረዳሉ።

የባህልና ቱሪዝም የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ እንደሚሉት፤ ከአመት አመት ዘርፉ እድገት እያሳየ ቢሆንም በስፋት እየተሰራበት አይደለም።

አሁን ኢትዮጵያ ካላት ሰላምና የዲፕሎማሲ ስራ ጋር በማያያዝ በዘርፉ ላይ መሰማራት መልካም አጋጣሚ ነውም ብለዋል።

መንግስት ከሚያሰናዳው ስብሰባ ባለፈ በዘርፉ ለመንቀሳቀስ ፍላጎት ያላቸው ተቋማት "በስፋት ሊሰሩበት ይገባልም" ብለዋል።

ባህልና ቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በዋናነት በሆቴሎች ማስፋፋትና አቅም መገንባት ላይ ድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልፀው፤ በሚፈለገው ልክ አገሪቱ ከስብሰባ ቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ዘርፉ ሊመራ የሚችል አንድ አካል ማቋቋም እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከዋሽንግተንና ብራስልን ቀጥላ ሶስተኛዋ የአለም ተቋማት መቀመጫ ብትሆንም፤ ከቱሪዝም ጉባኤ የምታገኘው ገቢ ግን ይህን መሰል እድልና አጋጣሚ ከሌላቸው ደቡብ አፍሪካና ኬንያ በታች መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በኮንፈረንስ ምክንያት ወደ አገሪቱ የሚገቡ ተሳታፊዎች ቁጥር ባለፉት ሁለት አመታት ከነበረው 59 ሺህ ወደ 79ሺ ማደጉን የባህልና ቱሪዝም መረጃ ያሳያል።

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ታህሳስ 29/2010 በደቡብ ወሎ ዞን የተገነባው የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ዘመኑ አዲስ የተመደቡለትን 1 ሺህ 135 ተማሪዎችን መቀበሉን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ታምሬ ዘውዴ ተቋሙ ባለፈው ታህሳስ 25 እና 26 ቀን 2010 ዓ.ም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተመደቡለትን ተማሪዎች በቱሉ አውሊያና በመካነሰላም ካምፓሶቹ ተቀብሏል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአራት ኮሌጆች በ17 የትምህርት ክፍሎች በቅርብ ቀናት ውስጥ ትምህርት መስጠት እንደሚጀምር ገልፀው፣ የመማር ማስተማር ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ለመማር ማስተማር ሥራው የሚያግዙ 62 መምህራንና 200 የሚጠጉ የአስተዳደርና የቴክኒክ ሠራተኞች ተቀጥረው ሥራ ጀምረዋል።

ለዩኒቨርሲቲው የህንጻ ግንባታና የውስጥ ለውስጥ መሰረተ ልማት ማሟያ ከመንግስት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ጥቅም ላይ መዋሉንም አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሠራተኞች ቢሮ፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቤተ መጻህፍት፣ የተማሪዎች ማደሪያ፣ የመመገቢያና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን ጨምሮ 38 ሕንጻዎች እንዳሉትም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢንተርኔት አገልግሎት ለማስጀመርም አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ነው ዶክተር ታምሬ የለጹት፡፡                  

በዩኒቨርሲቲው በግብርና ሳይንስ ትምህርት ክፍል የተመደበችውና ከምስራቅ ጎጃም "ሜጫ" አካባቢ የመጣችው ተማሪ ሙሉ ልቦና ዩኒቨርሲቲው አዲስ ቢሆንም የውስጥ አደረጃጀቱ የተሟላና ለመማር ማስተማሩ ምቹ መሆኑን ተናግራለች፡፡

ወደተቋሙ ስትመጣ የተደረገላት ጥሩ መስተንግዶ "ቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማኝ አድርገጎኛል" ብላለች፡፡

ከአዲስ አበባ የመጣውና በቱሉ አውሊያ ካምፓስ በተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የተመደበው ተማሪ ህዝቅያስ አዋሽ በበኩሉ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ ማቀዱን ናግሯል። 

መቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ ዘንዶሮ ወደሥራ ከሚገቡ አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ሲሆን በመጭው ጥር 5 ቀን 2010 ዓ.ም በይፋ ይመረቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሚዛን ታህሳስ 29/2010 የቦንጋ ዩኒቨርሲቲና የአካባቢው ማህበረሰብ ያደረጉላቸው አቀባበል እንዳስደሰታቸው አዲስ ገቢ ተማሪዎች ተናገሩ።

ተቋሙ በበኩሉ የተመደቡለትን አዲስ ተማሪዎች ከታሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እየተቀበለ መሆኑን አስታውቋል።

ከቢሾፍቱ ከተማ የመጣውና በተቋሙ በግብርና ትምህርት ዘርፍ የተመደበው ተማሪ ነብዩ ደምሴ እንዳለው ሕብረተሰቡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ያደረገለት አቀባበል ያልጠበቀውና የተለየ እንደነበር ተናግሯል ፡፡

ተቋሙ መኪና በመመደብ ከጅማ ከተማ ጀምሮ እንደተቀበላቸውና ግቢ ከደረሱ በኋላም የማደሪያ ክፍላቸውንና አስፈላጊ ነገሮችን በአስተባባሪዎች አማካኝነት በቀላሉ ማግኘት አንደቻሉ አመልክቷል።፡

በአካባቢው ማህበረሰብ የተደረገለት አቀባበል ልዩ ስሜት እደፈጠረበት የገለጸው ደግሞ ከአማራ ክልል ድጎ ከተማ የመጣው ተማሪ ልመንህ እንዱዓለም ነው።

"በተመደብኩበት የግብርና ትምህርት ውጤታማ ለመሆን ከወዲሁ የስነልቦና ዝግጅት አድርጊያለሁ" ብሏል

ከባሌ ሮቤ የመጣችው ተማሪ ሀና አሸብር በበኩሏ ከጅማ ጀምሮ የዩኒቨርሲቲው አውቶቡስ ተቀብሎ እስከ ዩኒቨርሲቲው እንዳደረሳቸውና ይህም ተማሪዎችን ከተጨማሪ ወጪ እንደታደጋቸው ተናግራለች፡፡

የአካባቢው ሕብረተሰብ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር ለተማሪዎች እያደረገ ያለው አቀባበልም ከመምጣቷ በፊት የነበረባትን ስጋት እንዳጠፋላት ተማሪ ሀና ገልጻለች፡፡

በቦንጋ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ዓለሙ ገብሬ በበኩላቸው አዲስ ተመድበው እየገቡ ለሚገኙ ተማሪዎችን የአካባቢው ሕብረተብ በተለያዩ ዝግጅቶች አቀባበል እያደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"የምኖርበት ቀበሌ ነዋሪዎች 13 ሺህ ብር አዋጥተው አንድ ሰንጋ በሬና ውሃ በመግዛት ለተማሪዎቹ አቀባበል እንዲውል አበርክተዋል" ብለዋል።

ሁሉም የቦንጋ ከተማ ነዋሪ ያቅሙን ገንዘብ ከማዋጣት ባለፈ በአካል ተገኝቶ አቀባበል በማድረግ አዲስ ገቢ ተማሪዎች እንግዳነት እንዳይሰማቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊ ዝግጅቶችን አድርጎ ተማሪዎቹን በመቀበል ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተማሪዎች ማደሪያ ፣ የመማሪያ ፣ መመገቢያ፣ የቤተ መጻሕፍትና የግብይት ማዕከላትን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለዘንድሮ ዓመት በአራት ኮሌጆችና 14 የትምህርት ክፍሎች 1 ሺህ 500 ተማዎች የተመደቡለት ሲሆን የመማር ማስተማር ሥራውን በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።

ዩኒቨርሲቲው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ዘንድሮ ወደሥራ ከሚገቡ11አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑን ይታወቃል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጭሮ ታህሳስ 29/2010 የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሀገሪቱ ለተከሰቱ ችግሮች ራሱን ተጠያቂ ማድረጉ በቀጣይ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ዝግጁ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

በሆቴል ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት  አቶ መልካሙ ጥላሁን በሰጡት አስተያየት ሰላምና መረጋጋት ከሌለ  ነግዶ ማትረፍ ይቅርና በሰላም ወጥቶ መግባትም አይቻልም ብለዋል።

"ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት ነው" ያሉት አቶ መልካሙ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የደረሱበት አንድነትና ስምምነት ለሀገራችን ልማትና እድገት ቀጣይነት ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በ17 ቀናት ግምገማው እራሱን ያየበት መንገድ ለተከሰቱ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣትና የሕብረተሰቡን ጥያቄዎች በሂደት ለመመለስ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።

በከተማው የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት አቶ ስለሺ ታዬ በበኩላቸው "ከዚህ በፊት በአንድነት ሲኖሩ የነበሩ ብሔር ብሔረሰቦች ባልተለመደ ሁኔታ ወደአለመተማመን ደረጃ የደረሱት መንግስት ሕብረተሰቡ ለሚያቀርበው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ባለመስጠቱ ነው" ብለዋል፡፡

አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ መግባባት ላይ መድረሳቸው የሀገሪቱን እድገት በጋራ ለማስቀጠልና ከግብ ለማድረስ ጉልህ አስተዋጾ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል ።

በድርጅቶቹ በኩል የተፈጠረው የሀሳብ አንድነት በተግባር እንዲቀየር ሕብረተሰቡ ጭምር ከመንግስትና ከኢህአዴግ ጎን በመቆም የድርሻውን ማበርከት እንዳለበት አመልክተዋል።

"ትናንት በሌሎች ሀገሮች ስንሰማው የነበረው በዘርና በጎሳ ተከፋፍሎ ግጭት ውስጥ መግባት የኛም እጣፋንታ እንዳይሆን ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን" ያለው ደግሞ ወጣት ጋዲሳ ለገሰ የተባለ የከተማዋ ነዋሪ ነው።

አሁን አራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች አለመተማመንና መጠራጠርን በማስቀረት የጋራ መግባባት ላይ መድሳቸው ለሕብረተሰቡ አንድነት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳለው ተናግሯል።

ወጣት ጋዲሳ እንዳለው መንግስት የሕብረተሰቡን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥና ለወጣቶች ሥራ በመፍጠር ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን ሥራ  አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።

ነዋሪዎቹ ሀገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ ላሳለፋቸው ውሳኔዎች ተግባራዊነትና ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

ጂግጀጋ ታህሳስ 29/2010 ሰላም በዘላቂነት ለማስፈን የሚያስችል ጠንካራ ተግባራዊ እርምጃ  ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደሚጠብቁ በጅግጅጋ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

ነዋሪዎቹ እንዳመለከቱት የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ግምገማ  መጠናቀቁን ተከትሎ በአራቱ አባል ድርጅቶች ሊቀመናብርት በመገናኛ ብዙሃን የሰጡትን መግለጫ ተከታትለዋል፡፡

የጋራ መግለጫው በአሁኑ ወቅት የሚታየውን ያለመረጋጋት ለማስተካከል የሚረዳ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

በከተማው የዜሮ አንድ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሐሊማ ዓብዲ በአካባቢያቸው ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር  ዳግም እንዳይኖር ኢህአዴግ ባደረገው ሰብሰባ ቁርጥ ያለ መፍትሔ ይዞ ይመጣል ብለው ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በሰብሰባው የተላለፉት ውሳኔዎች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡

በኦሮሚያና በሶማሊ አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ግድያዎች የተጠረጠሩ ጥፋተኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ውሳኔ መስጠቱ እንደሚደግፉ ወይዘሮ ሐሊማ ገልጸዋል፡፡

"ለዓመታት በፌዴራሊዝም ስርዓት ተሳስርን በመቻቻል ጠንካራ ኢኮኖሚ እየፈጠርን ብንቆይም በአሁኑ ወቅት ሀገራችንን ለአደጋ የሚያጋልጥ ሁኔታ ብቅ ብሏል" ያሉት ደግሞ በከተማው የቀበሌ ዜሮ አምስት ነዋሪ  አቶ አቡበከር መሀመድ ናቸው፡፡

ይህንን ችግር ለማስቆም እና ሰላም ለማስፈን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በውሳኔያቸው መሰረት ሊተገብሩት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የህብረሰቡ የልማት፣የፍትህና የስራ አጥነት ችግሮች ለመፍታት ብሔራዊ ድርጅቶቹ በአንድ አቋም ተስማምተው መግባባት ላይ መድረሳቸው  እንደሚደግፉ የገለጹት   አቶ አቡበከር ወደ ተግባር በመግባት ሰላም ለማስፈን ጠንካራ እርምጃ ከድርጅቶች እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

የብሔራዊ ድርጅቶቹ ግምገማ  ውጤት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ የበሰለ ውሳኔ የተላለፈበት ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የተናገሩት ደግሞ በከተማዋ የቀበሌ ዜሮ ስድስት  ነዋሪ አቶ መሐመድ አቢብ ናቸው፡፡

እንደሳቸው ገለጻ  ወጣቱ በሁሉም ዘርፍ ተሳታፊ ማድረግ ግዴታ በመሆኑ ድርጅቶቹ በዚህ ጉዳይ ተስማምተው ለውጥ ለማምጣት ቁርጠኛ መሆናቸው አስደስቷቸዋል፡፡

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን