አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 06 January 2018

ነቀምቴ/መቱ/ ፍቼ ታህሳስ 28/2010 አራቱ የኢሕአዴግ እህት ድርጅቶች ለማስተካከል የደረሱበትን ውሳኔ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ በነቀምቴ፣ በኢሉአባቦርና በፍቼ አካባቢዎች አስተየየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ገለጸ፡፡

ከነቀምቴ  ነዋሪዎች መካከል አቶ ሙሉጌታ ቢራቱ  እንዳሉት  አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች  በጋራ በመሆን የሰጡት መግለጫ  በመገናኛ ብዙሀን አመካኝነት ተከታትለዋል፡፡

ይህም በሀገሪቱ  አንድ የጋራ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመገንባትና  በመካከላቸው  ያለውን መጠራጠር  አስቀርቶ ለአንድ ዓላማ ጸንተው እንደሚሰሩ የሚያደርጋቸው  ነው ።

"ስልጣን የህዝብ መሆኑን ያወሳው  መግለጫው  ከሁሉም ነገር ሀገርንና ህዝብን ያስቀደመ በመሆኑ ሙሉ ድጋፋችንን እንሰጣለን "ብለዋል ።

በመግለጫው በተለያዩ ወንጀሎች የተከሰሱና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያለ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይቅርታ  እንደሚደረግ መገለፁ  የፖለቲካ ምህዳሩ በማስፋት የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት በተግባር መተርጎሙን  በተግባር የሚያመላክት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ ኤቢሣ ጉያሣ በበኩላቸው  አራቱም ድርጅቶች እንደ አንድ ሆነው በመካከላቸው የነበረውን መጠራጠር በማስወገድ ተግባብተው ለአንድ ዓላማ መቆማቸው እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪው እንዳመለከቱት በየክልሉ ሠላም ሰፍኖ  ልማትን በማፋጠንና የሀገሪቱን ሉአላዊነት ተጠብቆ እንዲቆይና በብሔር ብሔረሰቦች መካከል  መተማመን እንዲኖር የሚረዳ ነው፡፡

መግለጫው  በሕዝቦች መካከል  መፈቃቀርና መከባበር እንዲኖር  ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን የገለፁት ደግሞ  ሌላው  ነዋሪ አቶ ገበየሁ ዱጋሣ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንድ የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች በበኩላቸው የኢህአዴግ  ስራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ ያስተላፋቸው ውሳኔዎች አስተማኝ ሰላም እንዲሰፍን  ልማቱን ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖው ገልጸዋል፡፡

ከነዋሪዎቹ መካከል የዞኑ  ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ለማ እንዳሉት ስራ አስፈጻሚው ያስተላለፋቸው  ውሳኔዎች የታላቁ የህዳሴ ግድብ ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎችን ለማደናቀፍ የሚጥሩ የአፍራሽ ኃይሎች ሴራ የሚያከሽፍ ነው፡፡

ውሳኔው በሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ ችግሮችን በመፍታት በወሰንና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሲከሰቱ የነበሩ ያለመግባባቶችን እልባት ለመስጠት እንደሚያስችልም ጠቅሰዋል፡፡

ሀገሪቱን የሚመሩ ብሄራዊ ድርጅቶች ችግሮችን ለመፍታት የጀመሩትን ጥረቶች መላው ህብረተሰብ በመደገፍ ለዲሞክራሲው መጎልበት፣ አስተማማኝ ሰላምና ልማት እንዲቀጥል የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

"ስራ አስፈጻሚው ችግሮችን በጥልቀት በመገምገምና  በመፈተሽ ያስተላለፈው ውሳኔ አስደሳችና  ታሪካዊ ውሳኔ ነው"ያሉት ደግሞ የዞኑ አስተዳደር የመንግስት ሰራተኛ አቶ ከበደ ረጋሳ ናቸው፡፡

ሀገሪቱን በሚመሩ ብሄራዊ ድርጅቶቹ መካከል የተፈጠረው መግባባት በአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝቦች ውስጥ የመተማመን እና በአንድነት በልማቱ የመሳተፍ ባህል ያጠናክራል፡፡

" ውሳኔው የህግ የበላይነት እንዲጠናከር የዲሞክራሲ ስርአቱ እንዲጎለብት፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚያደርግና   የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴውን ለመከላከል የሚያስችል  ነው"ብለዋል አቶ ከበደ ፡፡

በወሰን ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን በአፋጣኝ መልሶ በማቋቋምና በህዝቦች መካከል የነበረውን የመቻቻልና መከባበር ባህል ወደ ነበረበት በመመለስ ረገድ  በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡

የመቱ ከተማ  ነዋሪ አቶ አለሙ ኦላና  ስራ አስፈጻሚው በተለያዩ ምክያቶች የተያዙ የፖለተካ  ፓርቲ አመራሮችን ለመፍታት ያስተላለፈው ውሳኔ የፖለቲካ ስነምህዳሩን ሊያሰፋ የሚያችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ውሳኔው በፍጥነት ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለበትም አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ከፍቼ ከተማ ነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ሁንዴ ከበደ በሰጠው አስተያየት ችግሮችን ለመፍታት የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያስቀመጠውን የመፍትሄ ሃሳብ ከልብ እንደሚደግፈው ተናግሯል፡፡

ለተፈፃሚነቱም የበኩሉን እንደሚወጣ በጠቆም፡፡

ወጣቱ እንዳለው በተለይ ሕገ መንግስታዊ  መብቶች ተከብረው የሰላም ፣የልማትና የመልካም አስተዳደር ቱሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን የበኩሉን ለማበርከት ዝግጁ ነው ።

የፍቼ ከተማ  የሀገር ሽግሌ አቶ ማሞ በላቸው በበኩላቸው ሀገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ  ችግሮችን ለማረም ቁርጠኛ አቋም መያዙ ለሕብረተሰቡ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መፍትሄ ለመስጠት ያለውን ዝግጁነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡም አመልክተዋል፡፡

የከተማው  ሴቶች ማህበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ብርቄ ዘውዴ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሃገሪቱን ሁኔታን ገምግሞ የደረሰበት ውሳኔና ያስቀመጠው የመፍትሄ አቅጣጫ ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

የኦህዴድ አባል እንደሆነ የገለፀው ወጣት እስማኤል ቃሲም ከውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲ አኳያ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የወሰደው የእርምት እርምጃ የሚደነቅና ለበለጠ ትግል አባላቱን የሚያነሳሳ በመሆኑ እንደሚደግፈው ተናግሯል ።

ለሕዝብ ጥያቄ  ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻልም ማስተካከያው የሚያግዝ መሆኑንጠቅሶ በተለይ አባሉ ለበለጠ አገልጋይነት የሚያዘጋጀው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

Published in ፖለቲካ
Saturday, 06 January 2018 23:42

"ስሚኝማ ኤልዳዬ!"

አየለ ያረጋል (ኢዜአ)

ስሚኝማ ኤልዳዬ! ህጻን ሲወለድ አስታወስሽ? በንጋትም ሆነ በመዓልት፤ ምጥ የያዛት እናት ስትንጎራደድ፣ ስትንቧች ስቃይዋ ያስጨነቃቸው ጎረቤቶች ሲንቆራጠጡ፤ አንደኛዋ ሰኞ መደብ ሌላኛዋ ማክሰኞ፣ በጭቃ ደረጃዎች፣ በከብቶች ግርግም በራፍ፣ በጉበኑ ስርቻ ተወሽቀው 'ማርያም ማርያም' ሲሉ፤ ወንዶችም ከጎጆ ቤቱ ደጃፍ ተኮልኩለው ትርታቸው ሲደልቅ፤ አንደበታቸው በአይዞነት መንፈስ ቃላት ሲለዋወጥ፤ ምናልባትም እንግዳ ሰላላ ድምጽ ማቃጨሉን ተከትሎ የ'እልል'ሆታ ሲከተል ታወሰሽ? ቤት ካፈራው ገንፎ ተገንፍቶ ሲቀመስ ልብ አልሽልኝ?

ኦ! ይቅርታ! ለካስ አንቺ እንዲህ አይነት ዝባዝንኬ ነገር አይገለጽልሽም። 'ኩሉ ነገር ዘይኃልቅ ውስተ ቤተ ድውያን' እንዲሉ! ነገረ ውልደት በቤተ ድውያን/ሆስፒታል/ በዘመን አፈራሽ ህክምና መከናወኑ ነው የሚገባሽ። ሚጢጢዬ እህትሽ ከእናትሽ ማህጸን ወደ እቅፍ መሸጋገሯን እንጂ ቅድመ አያትሽ በዚህ ባልኩሽ ዑደት ወደ ዓለም በራፍ መምጣቷ አይታወስሽም!

እሺ ይሄን ስሚኝ! ስለ አያቴ ልንገርሽ! ያው ወርኃ ታኅሣሥ ማለቁ አይደል። በነገርሽ ላይ ‘ታኅሣሥ’ የሚለው ቃል ‘ኀሠሠ’ ከሚለው የግዕዝ ቃል የመጣ ሲሆን፤ ምርመራ ፍለጋ የሚል አንድምታ እንዳለው የቋንቋ ሊቃውንት ያትታሉ። ወቅቱ መኸር ነውና ከምርት ፍለጋ (ስብሰባ ጋር አያይዘውም ይፈትቱታል። ስለ ገና ማዕበል ሳትሰሚ አትቀሪም፤ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀሉ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪዎች የቀለም ምርታቸው የሚሰበሰቡበት፤ የካፌ ቆይታቸውን የሚያረጋግጡበት ወቅት ነውና ምርቱ ካማረ አማረ፤ ካላማረ ማዕበል መታቸው ይባላል። ከማዕበል ይጠብቅሽ-ኤልዳዬ። ታኅሣሥ ሲገባደድ ጥር ይከተላል አይደል! በውርኃ ጥር ደግሞ ከጥምቀት ጀምሮ የበርካታ ታቦታት የንግስ በዓላት የሚከበርበት ነው (በኔ ትውልድ ቀዬ)። እና ታኅሣሥ ሲገባደድ፤ ጥር ሲብት የትምህርት ውጤት ማዕበል ብቻ ሳይሆን የፍቅር ማዕበልም ይከሰታል። (አንቺን ይግጠምሽ አይግጠምሽ ባላውቅም)። ለምሳሌ በዚህ ሰሞን እንዲህ ይዜማል፡-

ማዕበሉ የመታት እሷ

                                 "ታኅሣሥ ገሠገሠ ከተፍ አለ ገና፣

                                  እጠብቅሀለሁ አንተ ልጅ ቶሎና..."

 

ማዕበሉ የገረፈው እሱም

                              "በማለዳ ጀንበር በገና ጨረቃ፣

                              እኔን እኔን ብላ መጣች ተደብቃ…." ይላል።

 

እናም "ምግብ አያስበላ አያስለብስ ልብስ፣

ሞገደኛው ፍቅሩ ይዞኝ በታኅሣሥ…" እየተባለ በጥንዶች ዘንድ ይዜማል እንግዲህ።

መቸም አንዱን ጥሎ አንዱን ነው ወደ አያቴ ልምጣልሽ! አያቴ ታኅሣሥ ከመገባደዱ ቀደም ብሎ እንጎቻ ታስነጉታለች፤ አሻሮ ታስቆላለች፤ የውኃ ቅሏን ታዘጋጃለች፤ ልብሰ መንኩስናዋንም ታመቻቻለች፤ ከመንደሩ መሰሎቿ ጋርም ጉዞ ትጀምራለች - ወደ ላልይበላ። የገናን በዓልን ለማክበር- አብያተ ክርስቲያናትን ለመሳለም።

'ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ' ነውና ምሳሌው 'ለምን አያትህ ወደ ላልይበላ ትሄዳለች' ማለትሽ አይቀርም። ቀደም ሲል 'ህጻን ሲወለድ አስታወስሽ' ማለቴ ካለነገር አይምሰልሽ። መቸም ህጻን ሲወለድ የቤተሰብ፣ ጎረቤትና አድባሩ ደስታው የት የሌለ ነው። እና ከዛሬ 2 ሺ 10 ዓመታት በፊት ቀደም ሲል እንዳልኩሽ አይነት ደሳሳ ቤት አንዲት ነፍሰጡር እናት ቤተልሔም በተባለች ከተማ ውስጥ ግርግም (ከብቶች በረት) ውስጥ ምጥ ተይዛ እየተንቆራጠጠች ነበር፤ ተገላገለችም። ታኅሣሥ 29! የዳዊት ከተማ ነዋሪዎችም ተደነቁ፤ እልልታ ሆነ።

"እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል" ተባለ።  ሰማያዊያንና ምድራዊያን ነገዶች፣ ነብያትና መላዕክት ያወደሱት፤ እረኞች ያወሩለት፤ ሐዋርያት ያከበሩት፣ ኃአጣን  የዳኑበት፤ ግዞተኞች የተፈቱበት፤ ክርስቲያኖች የወረሱት ኢየሱስ ክርስቶስ ከድንግል ማርያም ተወለደ። ሰብዓ ሰገልም በአብሪ ኮከብ እየተመሩ ለህጻኑ ስጦታዎች ይዘው ወደ እየሩሳሌም ገሰገሱ። ከነዚህ ሰብዓ ሰገሎች መካከል "ኢትዮጵያዊያንም ነበሩበት" ይላል ታሪከ ቤተ ክርስቲያን። ከዚያም ከየዓለማቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚነጉዱ ክርስቲያኖች ሁሉ የእምነቱ ተከታይ ኢትዮጵያውያንም የክርስቶስን ልደት ለመዘከር በየዓመቱ መሄድ ጀመሩ።

 

ከዛሬ ዘጠኝ መቶ ዓመታት በፊት ግን የወቅቱ የዛግዌ ንጉስ (ቅዱስ ላልይበላ) የኢትዮጵያውያን ድካም አሳሰበው። እናም ክርስቲያኖች ክርስቶስን ልደት በአገራቸው እንዲያከብሩ ዳግማዊ እየሩሳሌም ማነጽ ፈለገ። እስካሁንም አምሳላቸው ያልተገኘላቸው ወደፊትም ይታነጻሉ ተብለው የማይታሰቡ ውቅር አብያተ ክረስቲያናትንም አሳነጸ። ምዕመናኑም የመካከለኛው ምስራቅ ድካም ቀርቶላቸው "ዮም ተወልደ ቤዛ ኵሉ ዓለም" (ዛሬ የዓለም ቤዛ ተወለደ) እያሉ በየዓመቱ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በዓሉን ያከብራሉ፤ በላልይበላ፡፡ አያቴም ስንቋን ይዛ የመሄዷ ምስጢር ይህ ነው።

መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳዋልና! እነዚህ ወደር አልባ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አደጋ ላይ መሆናቸውን ሳትሰሚ አልቀረሽም። አፋጣኝ መፍትሔ ካልተሰጣቸው ለማንነታችንና ታሪካችን አሻራ ቅርሶች ለምን ጊዜም ላናጋኛቸው የመፈራረስ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ነው የሚነገረው። የሚመለከተው ተቋም ፈንድ ማሰባሰብ፣ ተቆጣጣሪ ጽህፈት ቤት ማቋቋምና ጥናት ማድረግ ሥራዎች እንደሚያደርግ ሲናገር ተደምጧል። ዞሮ ዞሮ መገንባት ቢያቅተን 'ተመን አልባ' ሀብቶችን መንከባከብና መጠበቅ ለነገ የማይባል ለሁላችን ኃላፊነት ነውና እንረባረብ ማለቴ ነው።

ወደ በዓል አከባበር ስመለስ። መስቀልና ጥምቀት በተለየ ድምቀት የሚከበርባቸው ከተሞች እንዳሉ ሁሉ የገና በዓልም በላልይበላ በልዩ ሁኔታ ይከበራል። በቤተ ክርስቲያን ከታህሳስ 23 ቀን ጀምሮ በአገልግሎት ይታደራል። በታኅሣሥ 28 ማታም ጥንግ ድርብና ጥቁር ካባ በለበሱ ካህናት የራሱ ቀለምና ዜማ ያለው ሥርዓተ ማህሌት ሌሊቱ በወረብና ዝማሬ እየቀረበ ይታደራል። በዕለቱም በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምዕመናን መንፈሳዊ በዓሉን ለማክበርና ከ'በረከቱ ለመሳተፍ'፤ ሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናቱንና መንፈሳዊ የበዓል ሥርዐቱን ለመጎብኘት ይጎርፋሉ።

በዓሉ ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አገራዊ ፋይዳ የጎላ ነው። የልደት በዓል በመላው ዓለም የሚከበርም ሆነ በሁሉም የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ቢከበርም በላልይበላ ግን (የቅዱስ ላልይበላ ልደት በመሆኑም) በልዩ ድምቀት ነው የሚከበረው።

"በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ" እንዲሉ አበው በገና በዓል ሲከበር በርካታ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች አሉ። አሁን እኔ ሳድግ የዋንዛ ገና ቆርጨ፣ አለስልሸ፣ ከሰፈሩ ጉብላሊት ጋር ከሰፊው መስክ እንቁራ(ሩር) ስላጋ የነበሩኝ ትዝታዎች ውል ውል ይለኝ አይደል? ሌላውም እንደየአካባቢውና አስተዳደጉ ሁሉም የራሱ እልፍ ገጠመኞች ይኖሩታል። የበዓል ሰሞን ገበያ መቼም ባለአመል ነው። እናም ዶሮም ሆነ በግ ለመገብየት ወደ ገበያ ጎራ ያለ አባወራ፤ አስቤዛ ለመሸመት ወደ ጉልት ከተፍ ያለች እናት፣ የስጦታ ዕቃዎችን ለመገብየት ወደ ገበያ ማዕከላት ያቀና ገብያተኛ የመስረቅ፤ የመጭበርበር አጋጣሚዎች ይኖሩታል። የግርግር ገበያ መዘዙ እልቁ ቢስ ነው እቴ! ሐሰተኛ የፍጆታ ምርቶችም ሆነ ጤናማ ያልሆነ እንስሳት ይገበያል። በበዓል ሰሞን በቅርጫም ሆነ በግብዣ ወቅት የሚፈጠረው በጎም፤ ክፉም ገጠመኞች ስለሚኖሩም በዓሉን ብዙዎቹ ይናፍቁታል። ቤት ብቻም አይደል! በምግብና መጠጥ አገልግሎት ሰጭ የንግድ ድርጅቶች ደስታና ፈንጠዚያ ይከወናል። ይህን ተከትሎ በዚህ ቅጽበት ሞራላዊ ደስታ ልክ ኢኮኖሚያዊና አካላዊ ኪሳራዎች ይከሰታሉ። ፍቅረኞች ተናፋቂ ጊዜ የሚያሳልፉበት፣ ለጋብቻ ደወል የሚደዋወሉበት ዕለትም ይሆናል። ልጅ የሚያገኝ፣ ሎተሪ የሚደርሰው፣ ሌላም ሌላም አጋጣሚዎች። እናም በየፊናው 'የገና ስጦታዎች' አሉ። 'ስጦታ' ዋጋው ብቻ ሳይሆን "ባህሉም አይሏል" እያሉ አይደል ታዛቢዎች።

ኤልዳዬ ስጦታ እንደምትወጅ አውቃለሁ! አንቺ ደግሞ ያው በቅርብ ወራት ምንዛሬው በሶስት ብር መጨመሩን ተከትሎ ይሁን አይሁን ባላውቅም እንደው ይገርምሻል ሁሉ ነገር እሳት ሆኗል። የሶሲ ቡና በሁለት ብር፣ የሸምሱ እንጀራ በአንድ ብር፣ የምጥን ሽሮ በአምሰት ብር፣. . . ጨምረዋል። የአልባሳት፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋን ለዛውም በበዓል ወቅት ልብ በይ እንግዲህ። የእንቁላል፤ የቅርጫ ስጋ፣ የዶሮ፣ የበግ. . . እረ ስንቱ ተወርቶ አያ!

እና ምን ማለቴ መሰለሽ ያው ደመወዙ እዚያው፤ የቁስና አገልግሎቱ ዋጋ እየናረ አካሄዳቸው አልጣጣም ብለዋል። ለዚህ ነው አንጀት አራሽ ስጦታዎችን ያቀርባል ብለሽ እንደማጠብቂ ተስፋ እማደርገው። (በርግጥ የገና ዛፍና መሰል ስጦታዎች ከባህልም ትፈልጊ አይመስለኝም) ያም ሆኖ ግን አንድ ስጦታ አለኝ። ከእናንተ ቤት ፊት ለፊት ካለው ሱቅ አስቀምጨልሻለሁ። የላኪና ተቀባይ አድራሻ የለውም።

ለመለየት እንዲያመችሽ ግን “ላልይበላን እንታደግ” የሚል ምልክት ከጀርባው ተጽፎበታል።

መልካም፤ ደግ ደጉን እምንሰማበት ቸር አውዳ ዓመት ይሁንልሽማ ኤልዳዬ!!

 

Published in መጣጥፍ

ሚዛን ታህሳስ 28/2010 በደቡብ ክልል ቤንች ማጂ ዞን ዛሬ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ።

በዞኑ ጉራ ፈርዳ ወረዳ ትራፊክ አደጋ መከላከል ቁጥጥር ዋና የስራ ሒደት መሪ ዋና ሳጅን ወሰን ደንቢ እንደገለጹት አደጋው የተከሰተው በጉራፋርዳ ወረዳ ቡርጂ ቀበሌ ልዩ ቦታውም ቃለ-ህይወት ቤተክርስቲያን አካባቢ ከጠዋቱ 4፡30 ላይ ነው፡፡

ከዲማ ወደ ሚዛን እየተጓዘ የነበረ ኮድ 3-12047 ደሕ ቅጥቅጥ የሕዝብ አይሱዙ እና ከቢፍቱ ከተማ ወደ ኩጃ እየሄደ ባለ ታርጋ ቁጥር በሌለው ሞተር ሳይክል መካከል በተከሰተ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ሊያልፍ ችሏል።

"ሞተረኛው ሲያሽከረክር የመንገዱ ላይ ያጋጠመውን እንስሳ ሸሽቶ በከፍተኛ ፍጥነት ላይ በነበረው ቅጥቅጥ አይሱዙ መስመር በመግባቱ የሞተሩ አሽከርካሪና ተሳፋሪው በደረሰባቸው ጉዳት ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል"  ብለዋል፡፡

የአደጋው ምክንያት የቅጥቅጥ አይሱዙው ከልክ በላይ መፍጠንና የሞተረኛው ብቃት ማነስ እንደነበር በምርመራ ማረጋገጥ እንደተቻለ ዋና ሳጅን ወሰን ገልጸዋል።

ከተፈቀደ የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ገልጸው አሽከርካሪዎች ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ28/2010 የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባካሄደው ግምገማ ለወቅታዊና አገራዊ ችግሮች ራሱን ተጠያቂ ማድረጉ ቁርጠኝነቱን ያንጸባረቀበት ውሳኔ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የማህበራትና የፌዴሬሽን አመራር አባላት ገለፁ።

ሥራ አስፈፃሚው ያሳለፋቸውን የመፍትሔ ውሳኔዎች በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲቀይርም አስተያየት ሰጭዎቹ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ዮሃንስ ገብረሥላሴ እንደገለጹት፤ ሥራ አስፈፃሚው ባካሄደው ግምገማ ለወቅታዊ አገራዊ ችግሮች ራሱን ተጠያቂ ማድረጉ ትክክል ነው።

"የአገር ጉዳይ ከግለሰብም ከድርጅትም በላይ  ነው" ያሉት ምክትል ሰበሳቢው፤ የሥራ አስፈፃሚው ውሳኔ ተግባራዊ ሲሆን አሁን የሚታዩ ችግሮችን እንደሚቃለሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። 

ሥራ አስፈፃሚው በቀጣይ የአገሪቷን  ሰላምና አንድነት ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የውጭና የውስጥ ኃይሎች የሚያደርጉትን ሴራ በስፋትና በጥልቀት እንዲመለከትም መክረዋል።

"ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጊዜ ወስዶ በስፋትና በጥልቀት የችግሮቹን ምንጭ ለይቶ ራሱን ተጠያቂ ማድረጉ ለህዝቡ በተለይም ለወጣቶች ተስፋ ሰጪ ነው" ያለው ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወጣት ወንድወሰን ሽፋ ነው። 

ገዢው ፓርቲ በግምገማው የለያቸው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ የፀረ-ዴሞክራሲ ተግባር፣ የእህት ድርጅቶች እርስ በርስ መጠራጠሮችና መርህ አልባ ጉድኝቶችን ለመፍታት ያስቀመጣቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎች በፍጥነት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለበትም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ወርቅነሽ ወልደየሱስ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ሥራ አስፈፃሚው ለችግሮቹ ሌላ አካልን ተጠያቂ ሳያደርግ እራሱ ኃላፊነት መውሰዱ ትክክለኛና ቁርጠኛ ግምገማ ማካሄዱን ማሳያ ነው።

እያንዳንዱ አመራር አባል ለተፈጠረው ችግር ኃላፊነት መውሰድ እንደሚገባው የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ሥራ አስፈፃሚው ለሚፈጠሩ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት እንዳለበትም ተናግረዋል።

ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ ሁሉም የመንግስት መዋቅሮችና  አደረጃጀቶች ለውሳኔው ተግባራዊነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስተያየት ሰጪዎቹ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ለ17 ቀናት ያካሄደውን  ግምገማ ካጠናቀቀ በኋላ የሀሳብ አንድነት ላይ መድረሱና በተግባርም ሕዝቡን ለመካስ ተግቶ እንደሚሰራ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት መግለፃቸው ይታወሳል።

Published in ፖለቲካ

ባህርዳር ታህሳስ 28/2010 ባለፉት 17 ዓመታት ለኢንቨስትመንት የወሰዱትን ቦታ አጥረው ባላለሙ 171 ባለሃብቶች ላይ ከማስንቀቂያ ጀምሮ ቦታውን እስከመንጠቅ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን የባህርዳር ከተማ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የአንቨስትመንት ማስፋፊያ ዋና የስራ ሂደት  ቡድን መሪ አቶ ወንድወሰን ለገሰ ለኢዜአ እንዳስታቁት እርምጃው የተወሰደው ባለሃብቶቹ በውላቸው መሰረት ወደ ስራ መግባት ባለመቻላቸው ነው።

በዚህም መሰረት 118 ባለሃብቶች ለኢንቨስትመንት ተረክበውት የነበረውን ቦታ የተነጠቁ ሲሆን ለ53 ባለሃብቶች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልፀዋል።

በተነጠቁት ባለሃብቶች እጅ የነበረ 659 ሺህ 900 ካሬ ሜትር የኢንቨስትመንት ቦታም ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን አስታውቀዋል።

ማስጠንቀቂያ የወሰዱ ባለሃብቶች በእጃቸው ላይ የሚገኘውን 333 ሸህ 400 ካሬ ሜተር ቦታ በቀጣይ በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ማልማት ካልቻሉ ተመላሽ እንደሚወሆን ተናግረዋል።

በባለሃብቶቹ ላይ እርምጃው የተወሰደውም ከ1993 እስከ 2008 ዓ.ም ድረስ የተረከቡትን ቦታ በውላቸው መሰረት ማልማት ባለመቻላቸው እንደሆነም አስረድተዋል።

ከነዚህ ውስጥም መሬትን አጥረው ያስቀመጡ፣ ለሦስተኛ ወገን ያስተላለፉ፣ አቅም ሳይኖራቸው በባለሃብት ስም ቦታ ተረክበው ጊዜ ጠብቀው መሬትን ለመሸጥ ዓላማ ያላቸውና ከውል ውጭ እያከራዩ የሚጠቀሙ ባለሃብቶች እንዳሉበት ገልጸዋል።

እርምጃው ከመሰዱም በፊት በተደጋጋሚ ወደ ስራ እንዲገቡ ክትትልና ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በተሰጣቸው ጊዜ ኢንቨስትመንቱን እንዳላከናወኑም ጠቁመዋል።

አቶ ወንድሰን  በቀጣይም በሌሎችም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እየተጠና መሆኑን አስገንዝበዋል።

በባህርዳር ከተማ ከሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከፍተኛና መካከለኛ ፕሮጀክቶች ወደ ማምረት ተሸጋግረው ከሦስት ሺህ 700 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩም ታውቋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ28/2010 በአዲስ አበባ ለገና በዓል የዶሮ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው ገበያተኞች ተናገሩ።

በዓላት ሲቃረቡ ለበዓል የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ቀደም ብሎ መግዛት ለአላስፈላጊ ወጪ፣ ከእንግልት እንዲሁም ከስርቆት መዳን ይቻላል።

ይሁን እንጅ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይገዙ ቆይቶ የበዓል ዋዜማ ወደ ገበያ መውጣት ለከፍተኛ ዋጋ ጭማሪና እንግልት ይዳርጋል።

ኢዜአ ከሳምንት በፊት ያነጋገራቸው የዶሮ ነጋዴዎች ከ150 ብር ጀምሮ ቢያቀርቡም ብዙም ገዢ እንደሌለ፤ሰው የበዓል ዋዜማ እንደሚገዛና በዚያም ወቅት ግርግር እና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እንደሚታይ ነበር የነገሩን።

የኢዜአ ሪፖርተር በመገናኛ፣በላምበረት፣በቀበና፣በአዲሱ ገበያ አከባቢ የሚገኘው ሾላ ዶሮ ተራ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የዶሮ ገዢዎች ቀድመው ዶሮን ላለመግዛት የማቆያ ቦታና የዶሮዎቹ ጤንነት ሁኔታ ምክንያት እንደሆናቸው ገልፀዋል።

ይሁን እንጅ ዛሬ ገበያ በወጡበት ወቅት ካለፈው አመት በዓል ጋር ሲነፃፀር የዶሮ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ እንዳሳየ ነው የገለፁት።

ወይዘሮ በሻቱ ካሳ "የዶሮ ዋጋ በጣም ከፍ ብሏል፤ እኔ የዛሬ ዓመት 100ብር፣180 ብር ገዝቻለው።  ዛሬ 400ብር፣450 ብር፣480 ብር ነው የሚባለው ። በአዲስ ዓመት 200 ም፣250ም ተገዝቷል።” ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ አመለወርቅ ሙሉጌታ በበኩላቸው  “አነስተኛዋን ዶሮ 390 ነው ያሉኝ ለእንቁጣጣሽ 150፣160 ተገዝቷል፣ አሁን ግን በጣም ተወዷል።”

ዶሮ ነጋዴዎች በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው ዶሮ ከሚገዙባቸው ገበያዎች ላይ ጭማሪ በመታየቱ መሆኑንና ላለመክሰር ሲሉ ካለፈው የበዓል ገበያ ጭማሪ እንዳሳዩ ተናግረዋል።

የዶሮ ነጋዴው አቶ ሰቦቃ ቱሉ አንድ የሃበሻ ዶሮ በ340 ብር እንደሚገዙና አስርብር ብቻ አትርፈው እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡

የበግና የበሬ ዋጋም የዶሮውን ያህል አይሁን እንጅ ካለፈው በዓል አንጻር ጭማሪ ማሳየቱንም ነው የበግና በሬ ነጋዴዎች የሚናገሩት።

የበግ ነጋዴው አቶ ዘውዱ ተሰማ በላተኛው አቅሙ የፈቀደውን እንደሚገዛ ገልፀው ካለፈው ገበያ አንፃር “ዝቅተኛው  1 ሺህ፣መካከለኛው 3 ሺህ 500፣ከፍተኛው እስከ 6 ሺህ ይሸጣል፤ካለፈው ገበያ አንፃር የ800 ብር አካባቢ ጭማሪ አሳይቷል።”ብለዋል፡፡

የበሬ ነጋዴው አቶ ከተማ ካሳው በበኩላቸው የበሬ ገበያው ብዙም ውድ እንደማይባል ገልፀው ከፍተኛ ዋጋ አንድ በሬ 21 ሺህ ተሸጧል፤መካከለኛ የ15 እና 14ሺህ ፣ ዝቅተኛው ዋጋ ደግሞ እስከ 8 ሺህ ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

Published in ኢኮኖሚ

አዳማ ታህሳስ 28/2010 በህግ ቁጥጥር ሥር የነበረውን ተጠርጣሪ በጥይት የገደለ የፖሊስ አባል በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን የአዳማ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ።

የፍርድ ቤቱ መረጃ እንደሚያመለክተው የፖሊስ ባልደረባ የነበረው ደበል ፍቃዱ ወንጀሉን የፈጸመው ህዳር 1/2010 ዓ.ም በህግ ቁጥጥር ሥር የነበረውን አብዲ መሀመድን ወደ ማረሚያ ቤት እንዲያደርስ በታዘዘበት ወቅት ነው።

ተከሳሹ ሟቹን በመውሰድ ላይ እያለ በአዳማ ከተማ ወረዳ ሁለት ዳቤ ሶሎቄ ቀበሌ ኩሩፋ የተባለ ቦታ ሲደርሱ ቢያመልጠውም በህብረተሰቡ ጥቆማ ከተደበቀበት ተይዞ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲሔድ የፖሊስ ባልደረባው መንገድ ላይ በጥይት መቶ መግደሉ ተረጋግጧል።

ወንጀል ፈጻሚው በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ የክስ መዝገቡ ከተመረመረ በኋላም ፍርድ ቤቱ ታህሳስ 26 ቀን 2010  በዋለው ችሎት በ20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የበየነበት መሆኑን የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ናኦል አሰፋ ገልፀዋል ።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያስተላለፈው ዓቃቤ ህግ ያቀረበውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ  ተከሳሹ መከላከል ባለመቻሉና ጥፋተኛ መሆኑን በመረጋገጡ መሆኑንም አብራርተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ታህሳስ 28/2010 ሀገሪቱን ከአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት ለመታደግ ጥራቱን የጠበቀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በየደረጃው ማከናወን እንደሚገባ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዶክተር ኢያሱ አብርሃ አሳሰበ።

በተያዘው ዓመት የተፋሰስ ልማት ስራ የዝግጅት ምዕራፍ የአፈጻጸም ግምገማ መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

ሚኒስትሩ በመድረኩ ላይ እንዳስታወቁት በሀገሪቱ ለረጅም ዓመታት የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ የተለያዩ ችግሮችን አስከትሏል።

በተለይ ለግብርና ልማት ወሳኝ የሆኑ የአፈር ለምነት፣የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ፣እፀዋትና ደኖች መመናመንና ድርቅ መከሰቱን  ጠቅሰዋል።

"ችግሩ የደረሰባቸውን አካባቢዎች ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ በተፈጥሮ ሂደት እንዲያገግም እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በማከናወን  መልሶ የማዳን ስራ መከናወን አለበት "ብለዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት የሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ለማሳካትና የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃን አጠናክሮ ለመቀጠል የተለያዩ ተግባራትን ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ዶክተር ኢያሱ እንዳሉት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል፣ ከፍተኛ የኃይል ማመንጪያ ግድቦችና የመስኖ አውታሮች የታለመላቸውን ዘለቄታዊ ጠቀሜታ እንዲሰጡ ለማድረግ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ ወሳኝ ነው።

በተቀናጀና በተናበበ መልኩ ጉልበት ሳይባክን ጥራቱን የጠበቀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በየደረጃው ሊከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል።

በዚህም " አካባቢያዊ ጠቀሜታዎችን ከማረጋገጥ ባሻገር ሀገሪቱን ብሎም ዓለምን እያሰጋ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ችግር መቋቋምና መላመድ ይቻላል "ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ በበኩላቸው በተያዘው ዓመት የተፈጥሮ ሀብት ልማት፤ ጥበቃ እና አጠቃቀም ስራዎች ለማከናውን መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

እቅዱን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጥ በሚችል መልኩ ለመተግበር በየደረጃው የሚገኙ ፈጻሚ አካላትን በአመለካከት ፣በክህሎትና በእውቀት ለማብቃት ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

ከጥር 1/2010  ጀምሮ ለ20 የስራ ቀናት በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዘመቻ ላይ ከ22 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮች፣ሴቶችና ወጣቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

ለስራውም ከ13 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ  የእጅና  የቅየሳ መሳሪያዎች መዘጋጀቱን አቶ ተፈራ ጠቅሰዋል።

በዚሁ እንቅስቃሴ ሥነ-አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ተገቢውና ወቅታዊ  ጥገናና ዕድሳት ይደረግላቸዋል፡፡

የማህበረሰብ ተፋሰሶች  ልማት፣ አዳዲስ የጠረጴዛማ እርከን፣ ውሃ ማሰባበሰብ፣ የክትር ሥራና የተጎዳ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ መከላከል ሌላው ተግባር ነው።

ባለፉት  ዓመታት የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር እና በማስፋት እጥረቶች ዘንድሮ ደግመው እንዳይከሰቱ  የሚያስችል ግብ መቀመጡንም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና  ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡

Published in አካባቢ

አርባምንጭ ታህሳስ 28/2010 የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በአርባ ምንጭ ከተማ ለሚገኙ ለ80 አረጋዊያን የምግብ ዘይትና የዳቦ ዱቄት ድጋፍ ተደረገ፡፡

ድጋፉን ያደረገው በአርባ ምንጭ  የሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር ተወካይ አቶ ደስታ ደጀኔ እንደገለጹት ዛሬ ያደረጉት ይሄው ድጋፍ 25 ሺህ ብር ግምት ያለው ነው፡፡                          

በአርባ ምንጭ ሲቀላ ክፍለ ከተማ ድልፋና ቀበለ ነዋሪ አረጋዊት  ላቀች አንግቶ  ሐበሻ ቢራ የመስራት አቅም የሌላቸውን አረጋዊያንን  በማሰብ ባደረገው  ድጋፍ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም  ሁለት ሊትር የምግብ ዘይት እና የዳቦ ዱቄትም የድርሻቸውን ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

በድጋፍ አሰጣጡ ስነስርዓት ወቅት የተገኙት የጋሞ ጎፋ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ዘካሪያስ ካሣ ሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማህበር  ከዚህ ቀደም ለ2ሺህ 700  አረጋዊያንና ችግረኛ ተማሪዎች 600 ሺህ ብር የሚገመት የተለያየ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡

አርባምንጭን ጨምሮ በዞኑ የሚገኙ አረጋዊያን ዘላቂ ድጋፍ እንዲያገኙ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን ለመፍጠር  ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል ፡፡

Published in ማህበራዊ

ድሬደዋ ታህሳስ 28/2010 ኢህአዴግ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች ወደ ተግባር በማሸጋገር የተሻለች ሀገር ለመገንባት ተግቶ መስራት እንደሚጠበቅበት በድሬደዋ አስተዳደር አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች  ተናገሩ፡፡

አስተያየት ሰጪዎቹ እንዳሉት የሀገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋትና መድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ለማጠናከር ከሁሉም ጋር ውይይት  ማድረግ ይገባል፡፡

ሀገር እንደሚመሩ ድርጅቶች  ተዋህደው  ልዩነትን በማጥበብ ስኬት ለማስመዝገብ መወሰናቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

የመንግስት ሠራተኛ የሆኑት አቶ ከበደ ካሣ በ26 ዓመታት  የኢህአዴግ ሥርዓት ዘመን ይህን መሰል ነጻና ግልፅ የሆነ መግለጫ ስምተው እንደማያውቁ ጠቅሰው "ውሳኔው መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል "ብለዋል፡፡

" እኔም ሆንኩ ሌላው የምንጠብቀው ውሳኔውን ወደ ተግባር በማሸጋገር ተጨባጭ ውጤት ማየት ነው፤ የተሻለ ሰላምና ዕድገት ማየት ነው" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ አብዱረህማን አሊይ የተባሉ የገንደቆሬ ነዋሪ በበኩላቸው በሀገር ጉዳይ ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በጠረጴዛ ዙሪያ የመወያየት ባህሉን ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በአስተዳደሩ የዜሮ አምስት ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ወሰን ወንድሙ "ለሀገሪቱ ሰላም መናጋት አንዱ መንስኤ ወጣቱ ተምሮ ሥራ ማጣቱ ነው ፤ኢህአዴግ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ከፈታው ጥሩ ውጤት ይገኛል እላለሁ" ብሏል፡፡

በአስተዳደሩ የዜሮ ሁለት ቀበሌ ነዋሪው አቶ ስንታየሁ እንግዳ በበኩላቸው  " አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች ብቻ የወሰኑት ውሳኔ ሀገርን ወደ ተሻለ ልማት ፣ እድገትና ሰላም አያሻግርም ፤ ተመሣሣይ ፍጭትና ግምገማ በአጋር ድርጅቶች ላይ ፣በክልሎችና ከተሞች ላይ በመድገም ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ይገባል" ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ የተሻለ ሰላም ፣ልማትና እድገት ለማስመዝገብ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን