አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 05 January 2018

ሀረር ታህስ 27/2010 አራቱ የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ያሳለፉት ውሳኔ የሃገሪቱን የዴሞክራሲ ስርዓት ያጠናክራል ሲል ሃብሊ /የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ/ አስታወቀ።

የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ አባልና የሊጉ ምክትል አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አሚራ አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት ሐብሊ በአገሪቱ  የሚከሰቱ  ግጭቶች ወደ ሰላም እንዲያመሩ ከክልሉ መንግስትና ህዝብ ጋር እየሰራ ይገኛል።

"ለአለመግባባትና ግጭቶች መነሻ የሆኑትን የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮችን  ድርጅቱ  የወቅቱ ይገመግማል በጥልቅ ተሃድሶም ይፈትሻል፤ ለልማት ጸር የሆኑና ለህዝብ ሰላም ማጣት ምክንያት ለሆኑትም መፍትሄ እየሰጠ ይገኛል"ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ሃገሪቱን የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ለመፍታት እያከናወነ የሚገኘው የውይይት መድረክ የዴሞክራሲ ስርዓቱን በማጠናከርና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ለውጥ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

"በተለይ በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላምን ለማረጋገጥ፣የተጀመረውን የልማት ጉዞ ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ውይይቱ ከፍተኛ ፋይዳ አለው" ብለዋል።

ሐብሊ በተለይ የኪራይ ሰብሳቢነትና የጸረ-ዴሞክራሲ አካሄድ የስርዓቱ አደጋዎች በመሆናቸው ከድርጅቶቹ ጋር ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ክልሉ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩበት እንደመሆኑ ሰላምን በማስፈንና የዜጎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ከማጠናከር አኳያ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2010 በአዲስ አበባ በሚገኙ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት የስኳርና ዘይት አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

ቀደም ሲል በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የአቅርቦት ችግሩ እንደነበር ኢዜአ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አቅርቦቱን በተሻለ ሁኔታ ማግኘት እየቻሉ መሆኑን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

የአራዳና የኮልፌና ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎቹ ቀደም ሲል የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ስኳርና ዘይት በቀላሉ ለማግኘት ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን  ያለው አቅርቦት እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ  ነዋሪዋ ወይዘሮ አብነት ከበደ እንዳሉት፤ የሸቀጦቹ አቅርቦት ላይ ይታይ የነበረው ችግር እየተቃለለ ነው።

በአሁኑ ወቅት አቅርቦት ቢኖረም የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ላይ ችግር እንደሚስተዋልባቸው ወይዘሮ አብነት ተናግረዋል።

የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ ሙራድ ፈረጃ፤ የቤተሰባቸው መሰረታዊ ፍጆታ የሆኑት ስኳርና ዘይት በበቂ ሁኔታ እያገኙ መሆኑን ነው የገለጹት።

በየወቅቱ የወር ፍጆታቸውን እያገኙ በመሆኑ ደስተኛ እንደሆኑ የነገሩን ወይዘሮ ሳራ ጸጋዬ የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 ነዋሪ ናቸው ።

የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ ከበዓላት መምጣት ጋር ተያይዞም ሆነ ከበዓል ውጭ ህብረተሰቡ በየአካባቢው ስኳርና ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦችን እንዲያገኙ እየሰሩ መሆኖቸውን ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የፋና ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ አሻግሬ አካሉ እንዳሉት፤ ቀደም ሲል በአገር ዓቀፍ ደረጃ አጋጥሞ የነበረውን የስኳር እጥረት ተከትሎ ሸማቾች እንዳይጉላሉ በቤተሰብ ሁለት ኪሎ ግራም ስኳር ይከፋፈል ነበር።

አሁን ላይ አቅርቦቱ በቂ በመሆኑ "ነዋሪው በቤተሰቡ መጠን ሸቀጦቹን እንዲያገኝ እየተደረገ ነው" ብለዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ  ክፍለ ከተማ  ወረዳ 1 የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት የኦዲት ቡድን መሪ አቶ ግርማ ቱካ  እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት  ህብረተሰቡ  የስኳርና የዘይት እንዲሁም ከ15 ያላነሱ  የተለያዩ  ሸቀጦች በተመጣጣኝ  ዋጋ እንዲያገኝ  እየተደረገ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ነጌሌ/ጎባ ታህሳስ 27/4/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ የሰጠው መግለጫ ወቅታዊና ሃገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን በኦሮሚያ ባሌ ሮቤና ነጌሌ ቦረና ከተሞች አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

ድርጅቱ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎችም በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ እንደሚሹ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

የሮቤ ከተማ ጨፌ ኦዳ ነዋሪው አቶ አብዱልቃድር አሚን እንደተናገሩት የተላለፈው ውሳኔ በሀገሪቷ አስተማማኝ ሰላም እንዲኖርና የተጀመሩ የልማት ውጥኖችም ከግብ እንዲደርሱ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።

በመግለጫው ላይ የተመለከቱት ውሳኔዎች ህዝብ የሚፈልጋቸው በመሆናቸው በፍጥነት ተግባራዊ መረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የጨፌ ዶንሳ ነዋሪው አቶ አህመድ በከር በበኩላቸው በውሳኔው ላይ ኢሰብዓዊ ተግባር ይፈጸምበት የነበረው የማዕከላዊ እስር ቤት እንደሚዘጋ መገለጹ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ።

የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በማስጠበቅም ሰላማዊና የተረጋጋ እድገትን ለማስቀጠል እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

ሌላዋ የከተማው ነዋሪ መምህርት ሮማና አብደላ እንደተናገሩት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ውሳኔ በሃገራችን የተጀመረውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዲጎለብት በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ አለው።

በፈጸሙት ወንጅል ምክንያት በአቃቤ ህግ ጉዳያቸው የተያዘም ሆነ የተፈረደባቸውና በእስር የሚገኙ  የፖለቲካ አመራሮች ለተሻለ ሃገራዊ መግባባትና የዲሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት ሲባል እንዲፈቱ መወሰኑ ተገቢ መሆኑን ገልጽዋል።

በተመሳሳይም ስራ አስፈጻሚው ያስተላለፈው ያልተጠበቀ መግለጫ ከብሄር ልዩነት ይልቅ ሀገራዊ አንድነትን የሚያመጣ ትክለኛና ወቅታዊ በመሆኑ እንደሚደግፉት የነገሌ ቦረና ከተማ ወጣቶች ገልጸዋል።

በከተማው የ03 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት በዳዳ ሰመሎ አፈቱ መግለጫው በመንግስት እስከ አሁን ካስተላለፋቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ሁሉ የተለየ ሥፍራ እንደሚሰጠው ገልጾ ይሔም ወቅታዊና ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን አስረድቷል።

በሰበባ አስባቡ  ብሄርን እየለዩ ድንጋይ የሚወረውሩና በዩኒቨርሲቲዎች ሁከትና ብጥብጥ የሚያነሱ ተማሪዎችም ከዚህ ተምረው ለሀገራቸው ሰላምና ለልማት ቅድሚያ በመስጠት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁሟል።

ሌላዋ  የከተማው ወጣት ሳራ ኮቶላ በበኩሏ መግለጫው ልዩ የስልጣን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ብሄርን ከብሔርና ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨት ለፖለቲካ ትርፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ፀረ-ሰላምን ሃይሎች አንገት ያስደፋ መሆኑን ተናግራለች።

መግለጫው በህዝቦች ዘንድ የሰላምና የአንድነት ተስፋ ያጫረ መሆኑን የገለጸችው ወጣቷ የሃገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የመሪው የኢህአዴግ  አባል ድርጅቶ ተወያይተው አቅጣጫ ማስቀመጣቸው መጪውን ጊዜ የተሻለ እንደሚያደርገው አስረድታለች።

በዚሁ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪው ወጣት አበራ ሞገስ በበኩሉ ኢህአዴግ በሀገር ውስጥ የተፈጠሩ ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት የሄደበት መንገድ መልካም የሚባልና ከዚህ በፊት ያልታየ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ድርጅቱ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚወቀሰው ችግሮችን በመለየት ሳይንሆን በአፈጻጸም ላይ በመሆኑ ሊያስብበትና ላስቀመጠው አቅጣጫ ተፈፃሚነት በፍጥነት ወደ ስራ ሊገባ እንደሚገባም ጠቁሟል። 

ኢህአዴግ የሚመራው የሀገሪቱ መንግስት ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ በየጊዜው መመሪያ ቢያወጣም ከብድር አገልግሎት፣ከገበያ ትስስርና ከማምረቻና መሸጫ ቦታ ዙሪያ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸው እንደሚፈልግም ተናግሯል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2010 በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጉጉት ከሚጠበቁ በዓላት አንዱ ገና ነው።                 

ገናን ከሌሎች በዓላት ለየት የሚያደርገው ደግሞ ለቤተሰብ፣ለወዳጅ ዘመድ፣ ለጓደኛና ለፍቅረኛ ''የእንኳን አደረሳችሁ'' ስጦታ የሚበረከትበት መሆኑ ነው።

በዓሉን አስመልክቶ በአዲስ አበባ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች ከፕላስቲክ የገና ዛፍ ጀምሮ ማራኪ የስጦታ ዕቃዎችን ለሸማቾች ማቅረብ ከጀመሩ ቀናት ተቆጥረዋል።

ሸማቹም እንደ ፍላጎቱና ኢኮኖሚ አቅሙ ልቡ ያረፈበትን ስጦታ አልያም የቤቱን ማስዋቢያ በመግዛት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጀቱን ጀምሯል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከተማዋ የገና በዓል አከባበር ከኢትዮጵያዊ ባህል ይልቅ ወደ ምዕራባውያኑ ያደላ ከመሆኑ ባለፈ ለስጦታና ለቤት ማስዋቢያ የሚወጡ ወጪዎች ነዋሪውን የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ እየከተቱት መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓል ገበያ ሸማቾች በዓሉን አስመልክቶ ስጦታ መለዋወጡ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

ይሁንና ለስጦታና ለቤት ውስጥ ማስዋቢያ ሲባል የሚወጣው አላስፈላጊ ወጪ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚያሳድር መሆኑን ነው ወጣት እንዳለ ኢዳኤ የተናገረው፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ይሁኔ ዮሃንስ በበኩላቸው ''አሁን እየተለመደ የመጣው የገና በዓል አከባበር ወደ ውጪዎቹ ያዘነበለ ነው ኢትዮጵያዊ አከባበር እየጠፋ ነው'' ሲሉ ይሞግታሉ።     

እርሳቸው የገና ዛፍን ጨምሮ ለሌሎች አላስፈላጊ ቁሳቁሶች ትኩረት እንደማይሰጡና ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ብቻ እንደሚያዘጋጁ ገልጸዋል።

''በዓሉ በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበር ሲሆን የሚገዛውም የገና ዛፍ ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል በመሆኑ እዚህ ግባ የሚባል የኢኮኖሚ ጉዳት አያመጣም'' በማለት የሚሞግቱም አልጠፉም።    

ወጣት ሪታ ርዕሶም በዓሉን የበለጠ ለማሳመር የገና ዛፍን አንድ ጊዜ በመግዛት ለረጅም ጊዜ መጠቀም በኢኮኖሚ ላይ የጎላ ተጽዕኖ አላሳደረብኝም ትላለች።   

ወይዘሮ ሚሚ ለገሰም የተፈጥሮ ዛፎችን ከመቁረጥ ሰው ሰራሽ የገና ዛፎችን መጠቀም የተሻለ አማራጭ ነው ትላለች።  

ላለፉት 10 ዓመታት የስጦታ እቃዎችን በማቅረብ ንግድ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ሙሉወርቅ አልታዬ እንደሚሉት በሸማቾች ዘንድ ገናን ጨምሮ ለተለያዩ በዓላት የስጠታ እቃዎችን የመግዛት ልምድ እየጨመረ ነው።

በዚህም በዓላትን ተከትሎ በሚደራው ገበያ የእርሳቸውም ገቢ እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።     

ሌላዋ ነጋዴ ወጣት ቅድስት ፍቃዱ በዘንደሮው የገና በዓል የእቃዎች ዋጋ ከመጨመሩ ውጪ ጥሩ ገበያ መኖሩን ገለጻለች።

የገናን በዓል አስመልክቶ የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ የገባያውን ሁኔታ የቃኘ ሲሆን የገና ዛፍ እስከ 1 ሺህ ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ታዝቧል።      

 

Published in ማህበራዊ

ሶዶ ታህሳስ27/2010 የገና በዓልን አንድነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገልጹ፡፡

ተማሪዎቹ እንዳሉት ቤተሰቦቻቸው ከላኩላቸው የኪስ ገንዘብ በማዋጣት በዓሉን በጋራ ያከብራሉ፡፡

በዩኒቨርስቲው ኦቶና ካምፓስ የጤና ሳይንስ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ኤልሳ ክፍሌ በሰጠችው አስተያየት "የኢትዮጵያውያን እሴት የሆነውን አብሮነት ፣መቻቻልና ፍቅርን በሚገልጽ መልኩ ስጦታ በመለዋወጥ ገናን እናከብረዋለን "ብላለች፡፡

ከቤተሰቦቻቸው ርቀው ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ቢሆኑም በዓሉን በጋራ ሆነው በደስታ እንደሚያሳልፉት ተናግራለች፡፡

ለዚህም ገንዘብ በማዋጣት አንዱ ለአንዱ ስጦታ በማበርከት  በቤተሰባዊነት ስሜት ለማክበር በማደሪያ ክፍላቸው ኮሚቴ በማቋቋም እየተዘጋጁ ነው፡፡

የፈተና ወቅት በመሆኑ ጊዜያቸውን በማይሻማ መልኩ እንደሚያከብሩት ጠቅሳለች፡፡

በዋናው ግቢ የኮንስትራክሽን ማኔጅሜንት የአራተኛ ዓመት ተማሪ ስጦታ ሙሉ በበኩሏ የቤተሰብ ናፍቆት ቢኖርባትም ይህንን የማይረሳ የመተሳሰብና የፍቅር ስሜት ባለው መልኩ በዓሉን ከጓደኞቿ ጋር በአንድነት እንደሚያከብሩት ተናግራለች፡፡

" ሁላችንም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጣን ነን፤ በብሔር ስብጥራችን በግቢው ውስጥ ትንሿን ኢትዮጵያ በቀላሉ ትመለከታለህ "በምንም ዓይነት መስፈርት መለያየት የለም፤ አንዱ የሌላውን በማክበርና ልምድ በመቅሰም በኢትዮጽያዊነት ስሜት እንደ እህትና ወንድም ሆነን ነው የምናከብረው ብላለች ተማሪ ስጦታ፡፡

በተለይ የገና በዓል ከፈተና ወቅት ጋር የቀረበ በመሆኑ የሙጠበትን ዓላማ ሳይዘነጉ  በኃላፊነት መንፈስ በዓሉን በልክ ለማክበር  መነጋገራቸውን ጠቅሳለች፡፡

የእንግሊዝኛ ትምህርት ክፍል የሶስተኛው ዓመት ተማሪ የሆነው አብዲሳ ጎበና  በዓሉን ከትምህርታቸው በተጓዳኝ በደስታ እንደሚያከብሩት ተናግሯል፡፡

" እኛ ኢትዮጵያዊን የተለያዩ ባህልና የማንነት መገለጫ ያለን እንደመሆናችን አንዱ በሌላው ላይ ጫና ሳያሳድር የመቻቻል ባህላችንን ይበልጥ አጉልተን ከወትሮው በበለጠ መልኩ በአንድነት እናከብራልን" ብሏል፡፡

Published in ማህበራዊ

ታህሳስ 27/2010 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቷ ሠላምና መረጋጋትን ለማስፈን ኃላፊነቷን እንደምትወጣ ገለጸች።

መላው የአገሪቷ ሕዝብም ለሠላም ዘብ እንዲቆም ቤተ ክርስቲያኗ ጥሪዋን አስተላልፋለች።

ቀጣዩ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ሲከበር ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉም በጋራ ማክበር እንደሚገባ ጥሪ ቀርቧል።

በዓሉን በማስመልከት በሚካሔደው ጾም መላ ሕዋሳቶች ሰዎችን ከሚጎዱ፤ ሠላምን ከሚነሱና ወደ አላስፈላጊ ነገሮች ከሚመሩ ነገሮች መቆጠብ ስለሚገባ ቤተ ክርስቲያንም ለምዕመናኗ ከሠላም ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች የምትሰጠውን ትምህርት አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጻለች።

ኢዜአ የቤተክርስቲያኗን  የሥራ አመራሮችና የእምነቱን ተከታዮች  የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ከሠላም ጋር ያለው ቁርኝት እንዲሁም በወቅታዊ የአገሪቷ ጉዳይ ዙሪያ አነጋግሯል።     

በቤተ ክርስቲያኗ የትምህርትና ሥልጠና መምሪያ ኃላፊ አባ ሰረቀብርሃን ወልደሣሙኤል “የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ መሠረቱ ሠላምን ማወጅ ነው” ይላሉ።

ሠላም የሁሉም መሠረት በመሆኑና ያለ ሠላም አንዳች ነገር መከወን የማይቻል በመሆኑ ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ አባታዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል። 

“በአገሪቷ ዘላቂ ሠላምን የማስፈን ጉዳይ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁላችንም ሠላማችንን ልንጠብቅ ይገባል” ያሉት አባ ሰረቀብርሃን፤ "ማንም አካል በውስጡ ያለውን ጥያቄ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይኖርበታል።"  

ሁሉም ኢትዮጵያውያን የአገሪቷን ሠላም ሊጠብቁ እንደሚገባና አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩ እንኳን ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ሠላማዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ እንደሚገባ አባ ሰረቀብርሃን ገልጸዋል።  

በዓሉም እንደ ጥንቱ አብሮ በመብላትና መጠጣቱ ሊከበር ይገባል ያሉት አባ ሰረቀብርሃን፤ "አሁን ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው ጥረት ሁላችን ተባብረን ሠላማችንን፣ ልማታችንን፣ ወገኖቻችንን በማክበርም ጭምር ልደቱን እንድናከብር አደራ እላለሁ።”

“ክርስቶስ የመጣው ለሠላም ነውና በዓለ ልደቱን ስናከብር ሁሉም በአንድነት ልናከብር ይገባል” ያሉት ደግሞ በቤተክርስቲያኗ የሊቃውንት ጉባዔ አባል የሆኑት ሊቀ መምህራን ኃይለመስቀል አጠና ናቸው።

 “ሠላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ በዕለት ተዕለት አገልግሎቷ ስለ አገር ሠላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አንድነትና ስለ መላ ፍጥረት ሳትጸልይ የዋለችበት ጊዜ የለም፤ በቀጣይም ምዕመኗ ስለ ሠላም ተቆርቋሪ እንዲሆኑ አስተምህሮዋን አጠናክራ ትቀጥላለች“ ብለዋል ሊቀ መምህራን ኃይለመስቀል።   

በቤተ ክርስቲያኗ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ርዕሰ ደብር መሐሪ ኃይሉ በበኩለቸው፤ በአገሪቷ በነበረው የፀጥታ ችግር በሰው ላይ የደረሰው የሕይወት መጥፋት እንዳሳዘናቸው ገልጸው፤ በቀጣይ ይህ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም ሁሉም መስራት ይገባዋል።

“በአፍ ብቻ ሠላም ሊገኝ አይችልም፤ የጌታን ልደት ስናከብርም መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ፤ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆነን በአገሪቷ ሠላም እንዲሰፍን ማድረግ ከሁሉም የሚጠበቅ ነው” ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሲከበርም እንደ ጥንቱ በጋራ የመብላትና የመጠጣት ባህሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ ሁሉም በፍቅር አብሮ እንዲያከብርና ያለው ለሌላቸው በማብላት መከበር እንደሚገባ ርዕሰ ደብር መሐሪ ጥሪ አቅርበዋል።

የእምነቱ ተከታይ የሆኑት አቶ ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ ጾም ሲጾም ስለ አገር ሠላም፣ አንድነትና ሕብረት እያሰቡ መሆን እንዳለበት ይገልጻሉ።

"ቤተ ክርስቲያኗ፣ በቅዳሴዋ፣ በኪዳኗ፣ በጸሎትና በአጠቃላይ አገልግሎቷ ከወንጌል በማጣቀስ ስለ ሠላም ያላስተማረችበት ያልዘመረችበት ጊዜ የለም፤ አሁንም ለምዕመናን አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል" ብለዋል።

አቶ ካህሳይ እንደገለጹት፤ በድሮ ጊዜ በኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ በዓላት የዕርቅ መድረክ ስለነበራቸው የተጣሉት ሳይታረቁ በዓላት አያከብሩም ነበር።

“በተለይ የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ከጥንት ጀምሮ የዕርቅ በዓል ስለሆነ የተጣሉትን ሰብስቦ በማስታረቅ ነበር የሚከበረው” ይላሉ።

"በዓሉ ዝምብሎ ደግሶ መብላት መጠጣት ብቻ ሳይሆን፤ ድሮ ወላጆቻችንና ቤተ ክርስቲያንም ያቆዩልንን ሥርዓት ምንም ከሌላቸው ጎረቤት ጋራ አብሮ መብላት፣ መጠጣት የሌለውን እያሰቡ በዓሉን ማክበር ይኖርብናል” ብለዋል።       

አባቶቹ “እንኳን ለ2010ኛ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሠላም አደረሳችሁ” የሚል መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2010 ደኖች በሚገኙበት አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች የተፈጥሮ ደኖች በበጋ ወቅት በሚከሰት እሳት አደጋ እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አሳሰበ።

በሚኒስቴሩ የተፈጥሮ ደን ጥበቃና እንክብካቤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካብታሙ ግርማ ለኢዜአ  እንዳሉት ከዚህ በፊት በተለያዩ ዓመታት ሰፊ ሽፋን ያላቸው ደኖች ለእሳት አደጋ ተጋልጠዋል።

ባለፈው ዓመት በደቡብ ክልል ጂንካና ከፋ፣ በኦሮሚያ ዝቋላ እንዲሁም በአማራ አዊ ዞን በደኖች ላይ የእሳት አደጋ መከሰቱን የገለጹት አቶ ካብታሙ ለቃጠሎው ዋነኛ መንስኤዎች በጫካ ማር ቆረጣ፣ በከሰል ማክሰል፣ በእርሻ ማሳ ጽዳትና መሰል ተግባራት የሚሳተፉ አካላት በስፍራው እሳት በወቅቱና በተገቢው መንገድ ባለማጥፋታቸው ነው ብለዋል።

ከደን ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተፈጥራዊ ደኖች በበጋ ወቅት በተለያዩ መንስኤዎች በእሳት አደጋ እንዳይጎዱ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በቃጠሎው ተሳታፊ የነበሩ ግለሰቦችም ለፍርድ ቀርበው ተጠያቂ መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ይሁንና አደጋውን ለመቀነስ ለተፈጥሯዊ ደኖች ጥበቃና እንክብካቤ በአሳታፊ የደን አስተዳደር ስርዓት ከተደራጁ ማህበራት፣ ከአምልኮና እምነት በደን አካባቢ የሚኖሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በአሳታፊ የደን አስተዳድር ስርዓት ተደራጅተው ኑሯቸውን እንዲመሩ የተደረገው ደኑን እየጠበቁና እየተንከባከቡ ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ ታልሞ ነው ብለዋል።

የንብ አናቢያንም ማር በሚቆርጡበት ወቅት የሚጠቀሙበት እሳት በደኖች ውስጥ የእሳት አደጋ እንዳያስከትል አናቢያን በሂደት ከባሕላዊ ወደ ዘመናዊ የማነብ ስራ እንዲቀየሩ ለመደገፍ ታሳቢ ያደረገ ነው።

"የአምልኮና የእምነት ተቋማት አካባቢ ያሉ የተፈጥሮ ደኖች በብዛት የዘር ምንጭ ናቸው" ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ደኖቹ እንዲጠበቁ ከአምልኮና ከኃይማኖት አባቶች ጋር በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

በተያዘው ዓመት በጉዳዩ ላይ ከሁለት ወር በፊት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ለመፍጠርና ችግሩን ለመከላከል ስልጠና በመስጠትና በራሪ ወረቀረቶችን በመበተን የተፈጥሮ ደኖች ከእሳት አደጋ ለመከላከያ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል።

Published in አካባቢ

አርባምንጭ ታህሳስ 27/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በሀገሪቱ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መሆናቸውን አስተያየታቸውን የሰጡ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

 ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ሀገሪቱን የሚመራው ኢህአዴግ ለውሳኔው ተግባራዊነትና ውጤታማነት ህብረተሰቡን ማሳተፍ ይገባዋል፡፡

 በሲቀላ ክፍለ ከተማ የመናኸሪያ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ታገል ተገኑ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎችን ተከትሎ አራቱ እህት ድርጅቶች የሰጡትን መግለጫ በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት መከታተላቸውን ተናግረዋል፡፡

 መንግስትን  የሚመራው ኢህአዴግ ችግሮቹን  በመፈተሽ የማስተካከያ አርምጃ ለመውሰድ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል ብለው እንደሚያምኑም  ገልጸዋል፡፡

 ሆኖም ውሳኔው ስርነቀል ለውጥ እንዲያመጣ ሴቶችን፣ ወጣቶችን፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ሊያሳትፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 በከተማው የምንጭ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት መስፍን ካንኮ በበኩሉ የአራቱ ብሔራዊ ድርጅት ሊቃነመናብርት ከትናንት ወዲያ በጋራ መግለጫ ከመስጠታቸው በፊት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ያሳለፈውን ውሳኔ ለመረዳት ተቸግሮ እንደነበር አመልክቷል፡፡

 ብሔራዊ ድርጅቶቹ በጋራ መግለጫ ከሰጡ በኋላ ግን ግልጽ እንደሆነለት የጠቀሰው ወጣቱ፣ በመግለጫው ይፋ የተደረጉ ጉዳዮችን በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ በህዝብ ዘንድ አመኔታ ለማትረፍ መስራት ተገቢ መሆኑን ገልጿል፡፡

 በተለይ በስራ አስፈጻሚው መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመተማመን ችግር ለማስወገድና ልዩነቶችን ለማቻቻል የጋራ መግባባት ላይ መደረሱ ተገቢ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

 ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በችግሮቹ ዙሪያ ረጅም ጊዜ ወስዶ መወያየቱና ግልጸኝነት መፍጠሩ ለመፍትሄ ምቹ ሁኔታ መኖሩን እንደሚያሳይ የተናገሩት ደግሞ በሴቻ ክፍለ ከተማ የዶይሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ግርማ ሟሴ ናቸው፡፡ 

 " ችግሩ የቱ ጋር እንዳለ ከማንም በላይ ህዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል " ያሉት አቶ ግርማ፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የለየውንም ሆነ በህዝብ መካከል የሚታዩ ችግሮችን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ሕብረተሰቡን በስፋት ማሳተፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

 በሼቻ ክፍለ ከተማ የጫሞ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እማምንሽ ማሞ በበኩላቸው፣ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በመካከላቸው የነበረውን አለመተማመንና ጥርጣሬ በግልጽ ውይይት መፍታቱ በቀጣይ ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ ለመምራት ይበጀል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

 የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በሀገሪቱ ስርነቀል ለውጥ ማምጣት እንደሚያስችል ያመለከቱት አስተያየት ሰጪዎቹ ለውሳኔው ተግባራዊነት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2010 ከእርድ ጀምሮ ለቆዳና ሌጦ የሚደረገው ጥንቃቄ አሁንም አለመሻሻሉ ተገለጸ።

ከወትሮው በበለጠ በበዓላት ወቅት የእንስሳት እርድ በስፋት ይከናወናል። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለገና በዓል በሚያከናውነው እርድ ለቆዳና ሌጦ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ ለገበያ እንዲያቀርብ የቆዳ ነጋዴዎችና ፋብሪካ ባለቤቶች ጠይቀዋል።

ቆዳና ሌጦ ላይ የሚደርሰው ችግር ከእንስሳት ጤና አጠባበቅ የሚጀምር ቢሆንም፤ በእርድ ወቅት በህብረተሰቡና በቄራዎች፣ በአሰባሰቡ ደግሞ በገዥዎችና በቆዳ ነጋዴዎች ዘንድ አሁንም የጥንቃቄ ጉድለቱ በስፋት እንዳለ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ጥሬ ቆዳና ሌጦ አቅራቢዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አባተ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በበአላት ወቅት ለሚከናወን እርድ ህብረተሰቡ ለቆዳና ሌጦ የሚያደርገው ጥንቃቄ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው።

ይህ የጥንቃቄ ጉድለትም በህብረተሰቡ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በቄራ ድርጅቶች ዘንድም እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

ከየቦታው የሚሰበሰበው ቆዳና ሌጦ ለጊዜው አነስተኛ ገንዘብ ቢመስልም ለአገር ግን ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግለት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ቆዳ ከ4 ሰአት በላይ ጨው ሳይቀባ ከቆየ ሊበላሽ እንደሚችል የገለጹት አቶ ብርሃኑ ወደ ፋብሪካዎች እስኪሄድ ድረስ ሊደረጉ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአዳቶር ቆዳ ፋብሪካ ባለቤት አቶ አየለ ደጀኔ በበኩላቸው ቆዳ ነጋዴዎች የሰበሰቡትን ቆዳ በወቅቱ ለፋብሪካዎች ባለማቅረባቸው ለብልሽት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ጸሃፊ አቶ አብዲሳ አዱኛ እንደሚሉት በጓንት፡ በቆዳ አልባሳት፡ በጫማና በሌሎች ምርቶችም አገሪቱን በአለም ገበያ ለሚያስተዋውቀው ቆዳ ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባል።

ከቆዳ ጥራት ጋር በተገናኘ የእንስሳቱን ጤና በመጠበቅም ሆነ በእርድ ወቅት ብዙ ስራ እንደሚቀር የተናገሩት ደግሞ የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለባቸው ንጉሴ ናቸው።

ለበአሉ በሚከናወነው እርድ ወቅት በቆዳና ሌጦ አያያዝ፡ ማጓጓዝና አዘገጃጀት ላይ ከክልል ጋር ምክክር አድርገናል ብለዋል።

በቆዳ ገፈፋ፣ አሰባሰብና ለገበያ በማቅረብ በኩል በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ችግሩ በአንድ ጊዜና በአንድ አካል የማይፈታ በመሆኑ ተከታታይነት ያለው የማስተማር ስራ በዘርፉ ለሚንቀሳቀሱ ባለደርሻ አካላት እየተሰጠ ነው።

የግብይት ሰንሰለትን በተመለከተ  ቆዳው ሳይበላሽ በወቅቱ ከህብረተሰቡ ገዝቶ ለፋብሪካዎች ማቅረብ የሚያስችል የአዋጅ ማሻሻያ መደረጉንም ይናገራሉ።

ህብረተሰቡ ለስጋው የሚያደርገውን ጥንቃቄ ያህል ለቆዳም በማድረግ የበኩሉን ሀላፊነት እንዲወጣ ሚኒስቴሩ ጠይቋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎባ ታህሳስ 27/2010 የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ኑሯቸውን በእቅድ በመምራት አቅምና ገቢን ያገናዘበ  የቤተሰብ ቁጥር  እንዲኖራቸው   ማገዙን በባሌ ዞን ሲናና  ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡ  ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

 ባለፉት አምስት ወራት 73 ሺህ 390 እናቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡

 በወረዳው የሮቤ አካባቢ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አልፍያ በድሪ እንዳሉት  ቀደም ሲል  ልጅ በእድሉ ያድጋል በሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ልጆችን አከታትለው  በመውለድ ለችግር ተጋልጠው ነበር ፡፡

 "አሁን በአካባቢያችን የተመደቡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሰጡን ግንዛቤና ሙያዊ ድጋፍ በአካባቢያችን  በሚገኙ የጤና ጣቢያ ተቋማት  ፍላጎትን መሰረት ያደረገ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኛለሁ" ብለዋል፡፡

 በዚህም አቅምና ገቢን ያገናዘበ ቤተሰብ እንዲኖራቸው የረዳቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

 ወይዘሮ ካፊያ ሁሴን የተባሉት የቀበሌው ነዋሪ በበኩላቸው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አራርቆ በመውለድ የእናትና የህጻናትን ጤንነት ለመጠበቅ ብሎም  የኑሮ ጫናን ለመቀነስ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

 ወይዘሮዋ እንዳሉት  የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ልጆቻችንን አራርቆ በመውለድና በተገቢው እንክብካቤ ለማሳደግ አስችሏቸዋል፡፡

 ከአራት ዓመታት በፊት ስለ ቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እውቀት ስላልነበራቸው አከታትለው በመውለድ ጤናማ ህይወት ለመምራት ተቸግረው መቆይታቸውን የተናገሩት ደግሞ  የበሳሶ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ  ከበቡሽ ሰለሞን ናቸው ፡፡

 በአካባቢያቸው የጤና ተቋማት በመስፋፋታቸውና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን የቅርብ እገዛ በማግኘታቸው የረጅም ጊዜ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

 የወይዘሮ ከበቡሽ ባለቤት አቶ አለሙ ኢጃራ  በበኩላቸው በአካባቢያቸው የስነ ተዋልዶ  ጤናና ተያያዥ ጉዳዮች ቀደም ሲል የእናቶች ብቻ ተደርገው ይታዩ እንደነበር አስታውሰዋል።

 አቶ አለሙ እንዳሉት በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ባገኙት ግንዛቤ ከባለቤታቸው ጋር ተመካክረው አቅማቸውን ያገናዘበ ቤተሰብ እንዲኖራቸው አድረገዋል።

 በዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት የቤተሰብ ጤና አገልግሎት ባለሙያ አቶ አብዱረህማን አደም እንደገለጹት በባሌ 18 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳድሮች ባለፉት አምስት ወራት 73 ሺህ 390  እናቶች የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል ።

 የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እናቶች ቁጥር ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም 10 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው የሕብረተሰቡ ግንዛቤና  የወንዶችም ተሳትፎ እያደገ መምጣት ክንውኑን ከፍ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

 እናቶች በዞኑ በሚገኙ አራት ሆስፒታሎችን ጨምሮ ከ180 በላይ የጤና ተቋማት አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡

 ባለሙያው " የቤተሰብ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑ እናቶች መካከል 2 ሺህ የሚሆኑት የረዥም ጊዜ የተቀሩት ደግሞ የአጭር ጊዜ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው" ብለዋል ፡፡

 በባሌ ዞን ከ342 ሺህ 200 በላይ በመውለድ የእድሜ ክልል የሚገኙ እናቶች እንደሚኖሩ የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን