አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 04 January 2018

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010 የእስራኤል ባለኃብቶች በኢትዮጵያ በኃይል ማመንጫና በሰው ኃይል ልማት ዘርፎች የግማሽ ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ሊጀምሩ ነው።

ከ10 ኩባንያዎች የተወጣጡ የእስራኤል ባለሃብቶች ዛሬ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል።

የሃይል ማመንጫ፣ የሰው ሃይል ልማት፣ ትምህርት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ግብርና ባለሃብቶቹ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካሳዩባቸው ዘርፎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ከነዚህም መካከል ጊጋ ዋት የተሰኘው ኩባንያ በሃይል ማመንጫና በሰው ሃይል ልማት ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ ገልጿል።

የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ሚስተር ጆሴፍ አብራሃሞቪች 500 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ፕሮጀክት በሃይል ማመንጫ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እንዳሰቡ ነው የተናገሩት።

ኩባንያቸው የንፋስና የፀሐይ ሃይል ማመንጨት ላይ እንደሚሰራ የተናገሩት ስራ አስፈጻሚው ለአምስት አመት ለሚቆየው የሙከራ ፕሮጀክታቸው ከአስር የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ለመስራት እንቅስቃሴ እንደጀመሩ ነው የገለጹት።

አላማውም የአገሪቱን የሃይል ፍላጎት አማራጭን ከማስፋት ባለፈ በ100 ሺ የሚቆጠሩ መሃንዲሶችን ማሰልጠን መሆኑን ነው የተናገሩት።

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ በበኩላቸው የባለሃብቶቹ እንቅስቃሴና ያሳዩት ፍላጎት የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ገልጸዋል።

ሁለቱ አገራት የነበራቸውን የጠነከረ ፖሊቲካዊ ግንኙነት የጋራ ጥቅም ላይ ወደ ተመሰረተ ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲኖረው የሚያደርግም ነው ብለዋል።

አገሪቱ ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታዎችን እንደምትፈጥር የገለጹት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ናቸው።

የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ከባለሃብቶቹ ጋር በቅርበት በመስራት ሃሳቡ ወደ ተግባር እንዲለወጥ የበኩላቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያና ህዝን ግንኙነት ዴሊቨሮሎጂ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና እስራኤል በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ከጀመሩ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠሩ ሲሆን የአገራቱን ሁለንተናዊ ትብብር የሚያጠናክሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ቱሪዝምና ግብርና ዘርፎች ከአንድ ዓመት በፊት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳሰ 26/2010 በኦሮሚያና ሶማሊ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙ ተጠርጣሪዎችን በፍጥነት ለሕግ በማቅረብና ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ከሁለቱም ክልሎች የተፈናቀሉ ዜጎችንም ወደ ቄዬአቸው ተመልሰው ከነበሩበት አካባቢ ሕብረተሰብ ጋር እንደቀድሞው በሠላም መኖር እንዲጀምሩ የተጠናከሩና ቀጣይነት ያላቸውን የሠላም ጉባዔዎች ማካሄድ ያስፈልጋልም ተብሏል።   

ይህንኑ በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሱፐርቪዥን ቡድን በማቋቋም  ሲያካሄድ የቆየውን  የመስክ  ምልከታውን ሪፖርት ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ በማቅረብ ውይይት ተካሂዶበታል።  

 ሪፖርቱን ያቀረቡት የሱፐርቪዥን ቡድኑ አስተባባሪ  አቶ ጫኔ ሽመካ የመስክ ምልከታው የተደረገው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች  በሦስት አቅጣጫ ነው ብለዋል።

 የመስክ ምልከታው የተካሄደው ወካይ በሆኑ ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 16 ወረዳዎች፣ ተፈናቃዮች የተጠለሉባቸው 21 የከተማና የገጠር ቀበሌዎች ላይ መሆኑም ተነግሯል፡፡

 በተፈናቃዮች ላይ የደረሰው ፀረ-ሕገመንግሥታዊ ተግባር በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች ሳይሆን በልዩ የፀጥታ ኃይሎች፣ የየአካባቢው ፖሊሶችና ሚሊሻዎች፣ የአስተዳደር አካላት የተፈጸመ መሆኑን በመስክ ምልከታው ወቅት ተረድተናል ነው ያሉት።

 አቶ ጫኔ ቡድኑ በመስክ ምልከታ ወቅት ያገኙትን  መረጃ ዋቢ በማድረግ ለምክር ቤቱ አባላት ባቀረቡት ሪፖርት ኢ-ሰብአዊ በሆነ መልኩ ህጻናት ወላጆቻቸውን ማጣታቸውን፣ በሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት መድረሱን፣ ሕፃናትና እናቶች ላይ ዘግናኝ በደል መፈጸሙን ገልጸዋል።

 በሪፖርቱ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከልም፤ ’በሠላም አብረን ለዘመናት በምንኖር ሕዝቦች መካከል ታይቶ የማይታወቅ ግፍ ሲፈጸም መንግሥት ፈጥኖ እርምጃ መውሰድ ሲገባው ዝም ብሎ ተመልክቶናል፤ ዘግይቶም ቢሆን ያለንበትን ሁኔታ የተመለከቱ አመራሮችም መፍትሔ አልሰጡንም’ የሚል ከተፈናቃዮች በቅሬታ መልክ መነሳቱ ተገልጿል።

 የሱፐርቪዥን ቡድኑ አባላትም ግጭቱ  አፋጣኝ መፍትሔ ሳያገኝ መቆየቱ ይህ ሁሉ አደጋ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

 በመሆኑም በቀጣይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙ አጥፊዎች በአፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አሳስበዋል።

 ተፈናቃዮችን ወደ ሠላማዊ ኑሯቸው መመለስ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ ባለመሆኑ የማቋቋም ሥራው ሊፋጠን እንደሚገባም አሳስበዋል።

 በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነትና ትስስር ወደነበረበት ለመመለስ የሠላም ጉባዔዎች ተጠናክረው ሊካሄዱ እንደሚገባ የሱፐርቪዥን ቡድኑ አጽንኦት ሰጥቶበታል።

 'የተፈናቃዮቹ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?'፣ 'መንግሥት በአሁኑ ወቅት በዚህ ጉዳይ ምን እየሰራ ነው?' እና መሰል ጥያቄዎች  የምክር ቤቱ አባላት ያነሱ ሲሆን የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ሰጥተዋል።

 ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው የመመለስ ሥራው በመንግሥት በኩል በምን ደረጃ ላይ ይገኛል ለሚለው የፌዴራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔ ምላሽ ሰጥተዋል።

 "ተፈናቃዮችን ወደ አካባቢያቸው ለመመለስ ቅድሚያ ሕዝባዊ ኮንፍራንስ ለማካሄድ ቢታቀድም በነበሩ ችግሮች ዘግይቷል፤ ሁለቱ ክልሎችም በዚህ ጉዳይ ተቀናጅተው በጋራ መሥራቱ ላይም ክፍተቶች ነበሩ" ብለዋል።

 በአሁኑ ወቅት ግን ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ቄዬቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

 የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ የተፈናቃዮች መረጃ በወቅቱ ባለመድረሱ እርዳታ በማድረስ በኩል ክፍተቶች አልፎ አልፎ መስተዋሉን ተናግረዋል፡፡

 መንገድ ላይ ለዚሁ ተግባር የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን የማገት ሁኔታዎች ማጋጠማቸውን ለምክር ቤቱ አንስተዋል። 

 በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከክልሎቹ አመራሮችና የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ለተፈናቃዮቹ የሚደረገው እርዳታ ያለመስተጓጎል እንዲቀርብ ይደረጋል ነው ያሉት።

 የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ አብዩ ኮሚሽኑ ከክልሎቹ መስተዳድሮች ጋር በመተባበር ወንጀለኞችን በአፋጣኝ ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

 "በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ክልሎች በርካታ ዜጎች ለሕልፈት  ተዳርገዋል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ኃብት ንብረታቸው ወድሟል፤ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትም ተፈጽሞባቸዋል" ብለዋል ኮሚሽነሩ።

 ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እስካሁን በተሰራው የምርመራ ሥራ ከኦሮሚያ 98፣ ከሱማሌ ክልል ደግሞ ዘጠኝ ግለሰቦች ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ 'እጃቸው አለበት' ተብለው በመጠርጠራቸው በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

 በክሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ለተፈጠረው ግጭት መንግሥት አፋጣኝ እርምጃ ባለመውሰዱ፣ የፀጥታ አካላትም በፍጥነት ባለመድረሳቸው ለበርካታ ዜጎች መፈናቀል፣ መሞት፣ ኃብት ንብረታቸውን ማጣትና ለከፋ እንግልት መዳረግ በር መክፈቱንም ሪፖርቱ አመላክቷል።

 በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች በተከሰተው ግጭትም በርካታ ሕፃናት ትምህርታቸውን አቋርጠዋል ተብሏል።

ምክር ቤቱ በኦሮሚያና ሱማሌ ክልላዊ መንግሥታት በወሰን አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በምክር ቤቱ የተቋቋመው የሱፐርቪዥን ቡድን ባቀረበው ሪፖርት ላይ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለሟቋቋም ከተዋቀረው ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በመወያየት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ አጽድቋል።  

Published in ፖለቲካ

አዳማ ታህሳስ 26/2010 በኢትዮጵያ የሚገኘው የዓሣ ሀብት ክምችት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ መሆኑን የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስቴር ገለጸ።

ሀገሪቱ ባሉት የውሃ አካላት ውስጥ ከ100 ሺህ ቶን በላይ የዓሣ ሀብት ክምችት ይገኛል።

የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገብረኢግዝያብሔር ገብረዮሓንስ ለኢዜአ እንዳሉት ሀብቱን ለማልማትና በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል በሀገሪቱ የውሃ አካላት ውስጥ የሚገኙ የዓሣ ዝሪያዎች በአይነት፣በመጠንና በባህሪያት ተለይቶ መታወቅ አለበት፡፡

የውሃ አካላቱ በዓመት በዘላቂነት ሊሰጥ የሚችለው የዓሣ ምርት  አቅርቦትና ፍላጎትን መሰረት ያደረገ መሆን ይገባዋል።

የዘርፉን ልማት ለማከናወን በፖሊሲ ማዕቀፍ የተደገፈ ስትራቴጂክ እቅድ መዘጋጀቱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

"የስትራቴጂክ እቅዱ ዓላማ በእያንዳንዱ የውሃ አካላት ውስጥ የሚገኙ የዓሣ ዝሪያ ዓይነት፣መጠን ፣ባህሪያት፣የሥርጭትና ከምችት ደረጃ በጥናት ለመለየትና በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል ነው "ብለዋል።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ ብቸኛ የሆኑና ያልሆኑ የዓሣ ዝሪያዎች በሰው ሠራሽ ችግር ምክንያቶች እንዳይጠፉ ክትትልና ቁጥጥር ለማድረግ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዓሣ ክምችት በተመናመነባቸው የውሃ አካላት ውስጥ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የዓሣ ጫጩቶችን በመጨመርና በማባዛት የአርቢውን ህብረተሰብ ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ የትኩረት አቅጣጫም ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በወካይ የግብርና ሥነ ምህዳር ቀጠናዎች ላይ ተፈላጊ የሆኑ የዓሣ ዝሪያዎች ማራቢያና ማባዣ ማዕከላትን በባለሃብቶች፣በማህበራትና በመንግስት ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተቀረፀው የፖሊሲ ማዕቀፍና ስትራቴጂ በምርምር ስራዎች ውስጥ ዘርፉ የሚፈልገውን ቴክኖሎጂ ለማቅረብና በዘርፉ የተሻለ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፈቀደ ፈይሳ ናቸው።

በሀገሪቱ ባሉት የውሃ አካላት ከ100ሺህ ቶን በላይ የዓሣ ሀብት ክምችት እንደሚገኝ የጠቀሱት ዶክተር ፈቀደ "ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እያመረትን ያለነው 40 በመቶ ብቻ ነው" ብለዋል።

አሁን ያለውን 40 ሺህ ቶን ዓመታዊ የዓሣ ምርቱን ለማሳደግና የዘርፉን ልማት ለማዘመን የተቀረፀው ፖሊሲና ስትራቴጂ ወሳኝ መሳሪያ መሆኑን አመልክተዋል።

ለዚህም ውጤታማነት የዓሣ ዝሪያዎች ማራቢያና ማባዣ ማዕከላትን ማስፋፋትና ማጠናከር  ተገቢ መሆኑን ጠቁመው "ባለሃብቶች፣ማህበራትና የመንግስት ፈፃሚ ተቋማት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል" ብለዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን የዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የዓሳ ሀብት ልማት የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ሲሳይ አበበ በበኩላቸው በአካባቢው በሚገኙ የውሃ አካላት ውስጥ ከ6ሺህ ቶን በላይ ዓመታዊ የዓሣ ምርት እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የዓሳ ጫጩቶችን በማምጣትና  የጫጩት ዝሪያዎች በሌሉበት የውሃ አካላት ውስጥ በመጨመር የዘርፉን ልማት ለማስፋፋት እየተሰራ ነው፡፡

አቶ  ሲሳይ እንዳሉት በተያዘው የበጀት ዓመት በዞኑ በሚገኙ የውሃ አካል ውስጥ የዓሣ ልማት ለማከናወን አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ የጫጩት ዝርያዎችን  ለአልሚዎች ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010 በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ግጭት አፋጣኝ መፍትሄ ያላገኘው በመንግስት ድክመት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግጭቱን አስመልክቶ መንግሰት እያደረገ ባለው ጥረት ዙሪያ ማብራርያ ሰጥተዋል።

 በዚሁ ጊዜ በሁለቱ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ግጭት እንደተፈጠረ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ጥረቶችን ቢያደርግም ግጭቱን ፈጥኖ በማስቆም የሰው ህይወት አንዳይጠፋ፣ንብረት እንዳይወድምና ዜጎች ከአካባቢያቸው እንዳይፈናቀሉ ማድረግ አለመቻሉን ገልጸዋል።

 በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር ለማስቆም የአካባቢው፣የክልሎቹና የፌዴራል አመራር አካላት ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ ቢሆንም ከደረሰው ጉዳት አኳያ ውጤታማ አለመሆኑንም አቶ ደመቀ ገልጸዋል።

 ችግሩ ከኢኮኖሚ ፍላጎቶች እንዲሁም ከወሰን ማካለል ጋር ተያይዞ በወቅቱ ምላሽ እየተሰጠ ችግሩ እንዲፈታ አለመደረጉ ችግሩን እንዳባባሰውም ተናግረዋል።

 ለዚህ ደግሞ መንግስት ከፍተኛውን ኃላፊነት ይወስዳል ብለዋል።

 ''በየደረጃው ያሉ ከፍተኛ አመራር አካላት ይሄ ግጭተ ካጋጠመ ጀምሮ በተለይ በዚህ ዓመት በስፋትና በዚህ ደረጃ ካጋጠመ ጀምሮ ጉዳዩን ለመቆጣጠር አዳዲሰ ሁኔታ እንዳይኖር ለመከላከል ብዙ ግምገማዎች ወይይቶችና ሰምሪቶች አድርገዋል'' ነው ያሉት

 በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ደረጃ ባደረገው ግምገማ በግጭቱ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ የቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡንም አስታውሰዋል።

በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት መልሶ ማቋቋም ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የመጀመሪያ ተልዕኮ አድረጎ እንደሚሰራም አቶ ደመቀ ተናግረዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010 ዳንጎቴ ቢዝነስ ግሩፕ በኢትዮጵያ ያለውን ኢንቨስትመንት በእጥፍ ለማሳደግ ማቀዱን ገለጸ።

ናይጄሪያዊው የዳንጎቴ ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያዎች ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር መክረዋል።

ባለኃብቱ በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ ያላችው ኢንቨስትመንት ከየትኛውም የአፍሪካ አገራት የበለጠ መሆኑን ገልጸው በቀጣይም በኢትዮጵያ ያላቸውን የሲሚንቶ ኢንቨስትመንት በእጥፍ ለማሳደግ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።

ከዚህም ሌላ የሲሚንቶ ማሸጊያ ከረጢት ፋብሪካ የመገንባት እቅድ እንዳላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ገልጸዋል።

''እኛ ለአንድ ጊዜ ተጠቅመን መሄድ የምንፈልግ ኢንቨስተር አይደለንም'' ያሉት ባለሃብቱ አገሪቱ የሚያጋጥማትን ችግርም አብረን ተጋፈጥን የጋራ ተጠቃሚነት እናረጋግጣለን ሲሉም ተደምጠዋል።

ለዚህ ደግሞ የአገሪቱ ህዝብና መንግስት የሚያደርገው ትብብርም ለዚህ ስንቅ የሚሆነን ተስፋ ሰጥቶናል በማለት በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ለሚፈጠረው ችግርም መፍትሄ ለማፈላለግ የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንግስት ለኢንቨስትመንታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚዲያና ህዝብ ግንኙነት ዴሊቨሮሎጂ ሚኒስትር አቶ ዛዲግ አብርሃ ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ባጋጠሙት አለመረጋጋቶች ምክንያት ካምፓኒው ከኢትዮጵያ ለመውጣት እንደሚፈልግ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲራገብ እንደቆየ ያስታወሱት አቶ ዛዲግ አሁን እያደረጉት ያሉት የማስፋፋት እንቅስቃሴ ሀሰት መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ከ600 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያለው ሲሆን በተጠናቀቀው የፈረንጆች 2017 ዓመት በ14 የአፍሪካ አገራት ካሉ የድርጅቱ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ከፍተኛውን ትርፍ ማግኘቱ ይታወሳል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010 በኢትዮጵያ የማሳ ዳርቻዎችና ተራራማ ስፍራዎች በደን ልማት ቢሸፈኑ ትርፉ ምን ድረስ ነው?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ትምህርት ማዕከል አስተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር መኩሪያ አርጋው ኢትዮጵያ ለደን ልማት ምቹ የአየር ንብረት ያላት ግን ያልተጠቀመችበት ዘርፍ ነው ይላሉ።

የደን ዘርፍ በማር ምርት፣ በጫካ  ቡና፣ ጣውላ እና በሌሎች ምርቶች ለሀገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የምርት እድገት ካለው ፋይዳ በተጨማሪ በአፈርና ውሃ እንዲሁም በብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ ካርቦን በመቀነስ፣ የከባቢ አየር ንጹና ለጤንነት ተስማሚ በማድረግ፣ የአፈር ለምነትንና የመሬትን ምርታማነት በመጨመርም ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ያብራራሉ።

የደን ሽፋኑን ለማሳደግ በአገሪቱ ለደን ልማት የሚሆን መሬት የለም የሚሉ ባለሙያዎች እንዳጋጠማቸው የሚናገሩት ምሁሩ፤ እምቅ የደን ልማት የሚሆኑ የእርሻ ማሳ ዳርቻዎችና ተራራማ ስፍራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

እናም በአርሶ አደሮች ማሳና በመንገድ ዳርቻዎች ደንን በማልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ማግኘት ይቻላል ይላሉ።

በሌላ በኩል በአገሪቱ እጅግ በርካታ በደን ሊሸፈኑ የሚችሉ የተራቆቱ ተራራማ ስፍራዎች እንዳሉ ገልጸው፤ በተራሮች ደን ልማት እጅግ በርካታ ወጣቶችን ማሰማራት እንደሚቻል ያመለክታሉ።

ተራሮችን በምግብ ነክ፤ ደኖችም ሆነ በእንጨት ምርት የሚሆኑ ተክሎች መሸፈን ከአካባቢ ስነ ምህዳር ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባሻገር ለአገር የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

ቻይና የሀገረ ፈረንሳይን አራት እጥፍ የሚሆን ምድረ በዳ መሬት በ10 ዓመታት ውስጥ ለባለሀብቶች በማከራየት የፍራፍሬ ማዕከል ማድረግ እንደቻለች የሚናገሩት ዶክተር መኩሪያ፤ የኢትዮጵያ ተራሮች በመንግስት ብቻ ሳይሆን ለግለሰቦች ቢከራዩ ትርፉ ከፍተኛ ነው ባይ ናቸው።

ስለሆነም በጣም አዋጭ ግን ትኩረት ያልተሰጠውን የደን ዘርፍ መንግስት ወጣቶችንና ባለሀብቶችን በደን ልማት ዘርፍ እንዲገቡ ማበረታታት እንዳለበት ተናገረዋል።

በአካባቢ፤ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የተፈጥሮ ደን ጥበቃና እንክብካቤ ዋና ዳይሬክተር አቶ ካብታሙ ግርማ ከህዝብ ቁጥር እድገት ጋር ተያይዞ እየተመናመነ የመጣውን የደን ሽፋን ለመጠበቅና ለማልማት ትኩረት ተሰጥቷል ይላሉ።

ዘላቂነት ያለው የደን ልማት በሀገሪቱ ውስጥ  እንዲስፋፋ ኃይል ቆጣቢና ዘመናዊ ምድጃዎችን በማቅረብና በማሰራጨት፤የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በደን መሸፈን፤ የደን ልማትና ቁጥጥር ማጠናከር፤ የተራቆቱ የግብርናና የግጦሽ ቦታዎችን በመከለል የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ማከናወን ተጠቃሽ ናቸው።

በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች አድገው ቶሎ እንዳይቆረጡ ለጣውላ ምርት የማያገለገሉ አገር በቀል ዛፎች እንዲለሙም ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

በግጦሽና እርሻ ማሳዎች ዙሪያ ደን ልማት ለማከናወን አገሪቱ ወጥ የሆነ የመሬት አጠቃቅም ፖሊሲ እንደሌላት ይናገራሉ።

ያም ሆኖ ዘርፉን በተቀናጀ መልኩ ለመደገፍ ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች የተሻለ ልምድ ካላቸው አገሮች ልምድ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

በቅርብ ዓመታት በዓለም ምግብ ድርጅትና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በተጠና ጥናት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 15 በመቶ ደርሷል።

በግብርና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲ በ2022 ዓ.ም 20 ሚሊዮን አባራዎች ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎችን ወደ መጠቀም ማሸጋገር፤ የደን ሽፋኑ በ2 ሚሊዮን ሔክታር ማሳደግ፤1 ሚሊዮን ሔክታር የተራቆተዉን መሬት መልሶ በደን ለመሸፈንና ለመንከባከብ ዕቅድ ተይዟል፡፡ 

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010  የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ)  ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየወሰደ ያለው እርምጃ ለኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።

ሚንስቴሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫው በዋናነት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ውክልናዎችን ለማስፋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችና የደቡብ ሱዳን  የሰላም ስምምነት ተግባራዊነት  ላይ ያተኮረ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደተናገሩት፤ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየወሰደ ያለው እርምጃ ለአገሪቱ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ትልቅ ፋይዳ አለው።

"በአገር ውስጥ ሰላም እንዲመጣ፤ ዲሞክራሲው ስር እንዲሰድ፤መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት፤ ዲሞክራሲው እንዲጠናከር የሚወሰድ እርምጃ ሁሉ ለውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ስኬት አስፈላጊ ነው። ሰላም በሌለበት ኢንቨስትመንት ማሰብ አይቻልም፣ሰላም በሌለበት ልማትን በአጠቃላይ ማሰብ አይቻልም። ሰላም በሌለበት ዲሞክራሲው ስር እንዲሰድ ማድረግ አይቻልም። ስለዚህ በመንግስት እየተወሰደ ያለው እርምጃ ለውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ትግበራና ስኬት አስተዋጽኦ ያደርጋል።ይሄ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ውጤታማ እንዲሆን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ከውጭ ግንኙነት አንጻር አስፈላጊውን ርብርብ የሚያደርግ ይሆናል።"

እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ከውጭ አገራት ተቋማትና መንግስታት ተጽዕኖ ነጻ በሆነ መልኩ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለሙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ባለው የውጭ ግንኙነትና አገራዊ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ  የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ከውስጥ ወደ ውጭ የሚመለከት መሆኑ በግልጽ መቀመጡንም አንሰተዋል።

"በመሆኑም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰላም፣ዲሞክራሲና ልማት ለውጭ ግንኙነት ፖሊሲው አፈጻጻምና ስኬታማነት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ ነው" ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ አለም አቀፋዊ ውክልናዋን ለማስፋትና ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ለመክፈት ካቀደቻቸው ሚሲዮኖች መካከል በሞሮኮ፣በአልጄሪያና በሩዋንዳ ኤምባሲዎች መከፈታቸውን ገልጸዋል።

ቃል አቀባዩ በቱርክ ኢስታምቡል ቆንስላ ጄኔራል መከፈቱን ጠቅሰው፤  በቀጣይም  በአፍሪካ፣በአውሮፓ፣በሰሜን አሜሪካ፣እስያና በመካከለኛው ምስራቅና ኦሺኒያ 40 የክብር ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን ለመክፈት እቅድ ተይዟል ነው ያሉት። 

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ አካላት በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ ያደረጉት የሰላም ስምምነት እንዲተገበር ኢጋድና አለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አክለዋል።

ተቀናቃኝ አካላቱም ለሰላም ስምምነቱ መተግበር ቁርጠኝነት በማሳየት ወደ ስራ ገብተዋል ነው ያሉት።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010 የተፈጠረላቸው የገበያ አማራጭ የተሻለ ልምድ ለማዳበርና ደንበኛ ማፍራት እንዳስቻላቸው ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመጡ በአዲስ አበባው የገና ኤግዚብሽንና ባዛር ተሳታፊ ነጋዴዎች ገለጹ።

ዛሬ በሚጠናቀቀው ኤግዚብሽንና ባዛር ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 185 ጥቃቅን፣ ሰባት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ተሳታፊ ሆነዋል።

ምርቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ በማምጣት እያስተዋወቁና ለሸማቾች እያቀረቡ የሚገኙ አምራች ነጋዴዎች በተፈጠረላቸው የገበያ አማራጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ አምራቾች ተናግረዋል።

ከትግራይ ክልል አላማጣ ወረዳ የመጡት አቶ ዳውድ አብደላ እንዳሉት የባህል አልባሳት ለገበያ ያቀረቡ ሲሆን ከሸማቹ ጋር በተፈጠረው የገበያ ትስስር ተጠቃሚ ናቸው።

ከሌሎች አቅራቢዎች ጋርም የልምድ ልውውጥ ለማድረግም እንዳገዛቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ከደቡብ ክልል ሸካ ዞን ማሻ ከተማ የመጡት የመክሊት ማር አምራች አቶ አባተ ገቢቶ በበኩላቸው የማር ምርታቸውን ከክልላቸው ውጭ ተዘዋውረው ለገበያ ማቅረብ መቻላቸው ደንበኞችን ለማፍራት ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ።

ሌላዋ ከአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመጡት ወይዘሮ ብርሃን ካህሳይ እንዲሁ በተፈጠረው የገበያ ትስስር ደምበኞችን ከማፍራት ባሻገር ተጨማሪ ምርት ማምረት የሚያስችል ትእዛዞችን ከሸማቾች እያገኙ በመሆናቸው ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

የሞሪንጋ ቅጠልን በተለያየ መልክ በማዘጋጀት ለገበያ እየቀረቡ በመሆኑ ምርቱን ለማስተዋወቅ እንዳገዛቸው የተናገሩት ደግሞ ከደቡብ ክልል ደራሼ ዞን የመጡት አቶ ዲያቆን ሙላቱ ናቸው።

ከደቡብ ክልል የባህል አልባሳት አምራች የሆነው ወጣት እዮብ ፍሰሃ ከሃዋሳ በመምጣት ምርቱን ለሸማቾች ማቅረብ የሚችልበት እድል መመቻቸቱ ለገበያ ትስስሩ ያለው ሚና የጎላ እንደሆነ ገልጾ በንግድ ሱቁ ከሚያገኘው ገቢ በላይ ጥቅም እያገኘ እንደሆነ ነው የሚናገረው።    

በኤግዚቢሽኑ 15 ሺህ 200 በሚደርሱ ሰዎች የሚጎበኝና የአራት ሚሊዮን ብር ሽያጭና የገበያ ትስስር ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2010 አዲስ አበባን ውብ፣ ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ ባለፈው ህዳር 30 በይፋ የተጀመረው የፅዳት ዘመቻ በመጪው ቅዳሜ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚቀጥል የከተማዋ ጽዳት አስተዳድር ኤጀንሲ ገለጸ።

 በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ቡልጋሪያ ኤምባሲ አካባቢ በ500 ካሬ ሜትር ላይ ለሚገነባ የደረቅ ቆሻሻ ማስቀመጫ የመሰረት ድንጋይ ያስቀምጣሉ ተብሏል።

 የኤጀንሲው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ማስረሻው አስናቀ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ ቤት ለቤት ቆሻሻ የሚሰበስቡ 578 ማህበራትን ወደ 72 የጽዳት የሽርክና ማኅበራት ይደራጃሉ።

 ማኅበራቱ ወደ ሽርክና የሚቀየሩት የተደራጀ አቅም በመፍጠር በየቤቱ የተመረተውን ቆሻሻ ወደ ሃብትነት ለመቀየር እንዲያስችል ነው ብለዋል።

 በመዲናዋ ወደ ሽርክና ማኅበር የማደራጀት ሥራው ከኮልፌ ቀራንዩና ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ ውስን ማኅበራት በስተቀር በሌሎች የመዲናዋ ማኅበራት በኩል ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን አቶ ማስረሻው ተናግረዋል።

 ለእያንዳንዱ የሽርክና ማኅበርም 5 መቶ ካሬ ሜትር ቦታ የሚሰጥ ሲሆን እስካሁን በአሁን ጊዜ ለ39 ማኅበራት የሚሆን ቦታ ተዘጋጅቷል።

 ለቀሪዎቹ ደግሞ ቦታ ለመረከብ አስተዳድሩ ከመሬት ልማት ማኔጅመንት ጋር እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

 በሽርክና መደራጀታቸው ቀደም ሲል ያልነበራቸውን በቂ የቆሻሻ ማሰቀመጫና ማረፊያ ችግር በመቅረፍ በቂ ቦታና ምቹ ማረፊያ እንዲያገኙ ያግዛቸዋል ብለዋል።

 በየቦታው የሚታዩ የቆሻሻ ክምሮችን በፍጥነት ለማንሳትም ማህበራቱ አሁን የሚጠቀሙበት ጋሪ ወደ ተሽከርካሪ እንደሚቀየር አስታውቀዋል።

 እስካሁን በንፋስ ስልክ ላፍቶ 90፣ በቦሌ 13፣ በጉለሌ 5፣ በየካ 10፣ በአዲስ ከተማ 4 እንዲሁም በቂርቆስና አራዳ ክፍለ ከተሞች ሶስት ሶስት የጽዳት ማህበራት በሽርክና ማኅበራትነት ተደራጅተዋል።

 ''እኔ ከተማዬን አደጻለሁ! እናንተስ ?˝ በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የድጻት ዘመቻ በመጪው ታኅሳስ 28 ቀን 2010 ቅዳሜ እንደሚቀጥል ኤጀንሲው አስታውቋል።

Published in አካባቢ

ጎባ ታህሳስ 26/2010 የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰው ህይወት አጥፍተዋል ባላቸው ሁለት ግለሰቦች ላይ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወሰነ ፡፡

ፍርድ ቤቱ  አስፋው ታደሰና ነስሩዲን ጀማል በተባሉ ተከሳሾች ላይ የቅጣት ውሳኔውን ያስተላለፈው ዛሬ በዋለው ችሎት ነው ፡፡

ተከሳሾቹ በዞኑ ጊኒር ከተማ ዜሮ አንድ ቀበሌ ግንቦት 19/2009 ዓ.ም ወይዘሮ እጅጋየሁ ወልደየስ የተባሉ የግል ተበዳይን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸው በማስረጃ እንደተረጋገጠባቸው  የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ ገዛኽኝ ተረፈ ገልጸዋል፡፡

ዳኛው እንዳመለከቱት ግለሰቦቹ  ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ብለው ሟቿን  በገዛ ግቢያቸው  ህይወታቸውን ካጠፉ በኋላ አስክሬናቸውን በግቢው  ውስጥ እንዲደበቅ አድርገዋል፡፡

ድርጊቱን በተፈጸመበት ማግስት የሰፈሩ ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ አንደኛው ተከሳሽ ወዲያውኑ ሊያዝ ችሏል፡፡

ወንጀሉን ከፈጸመ በኋላ ወደ አርሲ አሰላ በመሸሽ ለማምለጥ የሞከረውን ሁለተኛ ተከሳሽ ነስሩዲን ጀማል ደግሞ የዞኑ ፖሊስ ከአርሲ ዞን ፖሊስ ጋር በመተባበር መያዙን የፍርድ ቤቱ ዳኛ አስታውቀዋል፡፡

ተከሳሾቹ ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው ቢከራከሩም ድርጊታቸው  በሰውና በሰነድ ማስረጃ በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡

አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ ወንጀሉን ሆነ ብለውና  ተደራጅተው ኢሰብኣዊ በሆነ መልኩ በመፈጸማቸው ቅጣቱ እንዲከብድባቸው ጠይቋል ፡፡

ፍርድ ቤቱ ከግራ ቀኙ የቀረበለትን ክርክር ካዳመጠ በኋላ ግለሰቦቹ ከዚህ በፊት ምንም ዓይነት የክስ ቻርጅ እንደሌለባቸውና የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን እንደ ፍርድ ማቅለያ ይዞ እያንዳንዳቸው በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል ፡፡

በፍርድ ሂደቱ ላይ የተገኙት የሟች ልጅ ወይዘሮ ዮዲት አበጀ  የቅጣት ውሳኔው በቂና አስተማሪ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

የባሌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለፉት ስድስት ወራት ከ11 ሺህ የሚበልጡ የፍትሃብሔርና የወንጀል መዝገቦች ውሳኔ እንዲያገኙ ማድረጉን ከፍርድ ቤቱ የተገኘው   መረጃ ያመለክታል ፡፡ 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን