አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 03 January 2018

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 ተጠቃሚዎች የሜትር ታክሲዎችን አፕሊኬሽን በመጠቀም በካርድ የሚፈጸም ክፍያ አገልግሎት የሚያገኙበት አሰራር ተጀመረ።

ኢታ ሶሉሽንስ እና ዳሸን ባንክ አገልግሎቱን በጋራ የሚሰጡበትን የካርድ ክፍያ አሰራር ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

የክፍያ ሥርዓቱ ከእጅ በእጅ የክፍያ ሥርዓት ውጭ የሆነና ተጠቃሚዎች ከዳሽን ባንክ በሚገዙት የሁለቱን ኩባንያዎች ዓርማ በያዘ ካርድ  አገልግሎት የሚያገኙበት ነው።

የኢታ ሶሉሽንስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ገብረህይወት እንደገለጹት ካርዱን የያዘ ደንበኛ በ"8707" ነጻ የስልክ መስመር ሲደውል ሜትር ታክሲው ያለበት ስፍራ ይደርስለታል።

አዲሱ የአሰራር ሥርዓት ህብረተሰቡ በታክሲ ጥበቃ የሚያባክነውን ጊዜ የሚቀርፍ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ በኪሎ ሜትር 13 ብር እንደሚያስከፍል የገለጹት አቶ ተመስገን ታክሲዎቹ በመዲናዋ ለታክሲ መዳረሻነት በሚመቹ ቦታዎች በየሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ዝግጁ ሆነው እንደሚጠብቁ ነው ያስረዱት።

"8707" ነጻ የስልክ ጥሪ መስመርን መጠቀም ያስፈለገው አገልግሎቱን የሚሹ ደንበኞች 24 ሠዓት ያለምንም የኔትወርክ ችግር መደወል እንዲችሉ ታስቦ መሆኑን አክለዋል።

ታክሲ ፈላጊ ደንበኞች ታክሲዎች ተገልጋዮች ያሉበት ድረስ ለሚመጡበት ክፍያ መፈጸም አይጠበቅባቸውም ነው ያሉት።

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ኢህአዴግ አሁን የደረሰበትን የሀሳብ አንድነት በተግባር በመግለጽ ሕዝቡን ለመካስ ተግቶ እንደሚሰራ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት አስታወቁ።

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለ17 ቀናት ያካሄደውን ግምገማና የደረሰበትን ውጤት አስመልክቶ የአራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሀፈት ቤት ማበራሪያ ሰጥተዋል።

የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው “ከሰማይ በታች ምንም ዓይነት ነገር እንዲቀር አልተደረገም” በሚል በገለጸው የ17 ቀናቱ ግምገማ   ከመቼውም ጊዜ በላይ የሀሳብ አንድነት በመፍጠር ባለ ስምንት ነጥብ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጦ ለተግባር መሰረት መጣሉ ነው የተገለጸው።

ግምገማውን ገና ከጅምሩ “ታሪካዊ ለማድረግ ታስቦ” የተገባበት በመሆኑ ሁሉም ድርጅቶች በአሸናፊነት የወጡበት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ደረጃ ለተፈጠረው ችግር የአካል ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ግምገማ ማድረጋቸውን ነው ሊቃነ መናብርቱ ይፋ ያደረጉት።

በአገሪቷ ለተፈጠረውና በግልጽ እየታየ ላለው ችግር ሥራ አስፈጻሚው ራሱን ተጠያቂ በማድረግ ለችግሩ የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ የሚያስችለው ቁመና ላይ መገኘቱንም ነው ያረጋገጡት።

በአሁኑ ግምገማ የተፈጠረው አመለካከት ለተግባር አንድነት መነሻ እንደሚሆን ያረጋገጡት ሊቃነ መናብርቱ፤ ሥራ አስፈጻሚው በፍጥነት ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን በመለየት ወደ ተግባር መግባቱን  አረጋግጠዋል።

በግንባሩ ውስጥ እርስ በእርስ መጠራጠርና አለመተማመን እየሰፈነ የመጣበት ሁኔታ እንደነበረ   አስታውሰው  ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ጠለቅ ያለ ግምገማ መደረጉንና የሃሳብ አንድነት መፈጠሩን  ገልፀዋል ።

የኢህአዴግና የደኢሕዴን ሊቀመንበር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት ሥራ አስፈጻሚው በነጻነትና ግልጽነት ወስኖ በገባው መሰረት የሀሳብ አንድነት ለመፍጠር ያስቻለውን ጥልቅ ውይይት አድርጓል።

የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና የብአዴን ሊቀመንበር ደመቀ መኮንን እንደገለጹት ደግሞ፤ ችግሮቹ ያሉት በአንድ ድርጅት ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘንድ መሆኑ ታይቷል።

በግምገማው የተፈጠረውን የሀሳብ አንድነት ወደ ተግባር ለመቀየር መወሰኑንም ነው የገለጹት፡፡

የኦህዴድ ሊቀመንበር ለማ መገርሳ በበኩላቸው ግንባሩ ጤናማ የፖለቲካ ሂደቱን ጠብቆ ለመሄድ ችግሮቹን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጡ ወሳኝ  መሆኑን ተናግረዋል።

በግምገማው ሁሉም ነገሮች በቡድንም ሆነ በግል በግልጽ መታየታቸውን አመልክተው፤ አገሪቱን  ጥያቄ ውስጥ የከተተው ሁኔታ በጥልቀት መታየቱንና በግልጽ ውይይት መደረጉን አረጋግጠዋል።

የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እንደተናገሩት በአሁኑ ግምገማ ቀደም ብሎ በተካሄዱ ተሃድሶዎች ያልታዩ ጉዳዮችንም መፈተሽ ተችሏል።

በውስጥ የነበሩ ክፍተቶችን፣ መጠራጠሮችንና አለመተማመንን ለመፍታት ያስቻለ  ውይይት  መደረጉንም ነው የጠቆሙት።

በሌላ በኩል ብሄራዊ ድርጅቶቹ ውስጠ ዴሞክራሲ እየጠፋ መምጣቱ ለድርጅቱም ሆነ ለአገሪቷ አደገኛ መሆኑን በመገንዘብ የማስተካከያ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

ይህም  ለቡድንተኝነትና መጠቃቀም በር መክፈቱን ጠቁመው  መርህ አልባ ግንኙነት እንዲሰፍን አድርጎ መቆየቱንም አብራርተዋል ።

በግንባሩ ውስጥ የታየው የውስጠ ዴሞክራሲ እጦት ወደ ሌላ እየተላለፈ የሀሳብ መንሸራሸርን የገታ ሲሆን፤ ጉዳዮች በመርህ ደረጃ አለመታየታቸው  ለችግሮቹ መስፈንና ለመርህ አልባ ግንኙነቱ መፈጠር መንስኤ መሆናቸው ተመልክቷል።

በግንባሩ ውሰጥ “እኔ ትክክል ነኝ“ የሚል አስተሳሰብ እየነገሰ መምጣቱንም ነው ሊቃነ መናብርቱ ያመለከቱት።

በዚህም በግለሰባዊና ቡድናዊ ስሜት ተገፋፍተው  ስህተቶች መፈጠራቸው ተጠቁሟል።

በግንባሩ ዴሞክራሲ እንዲሰፍንና የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ከማድረግ አኳያ የነበሩ ጉድለቶች መታየታቸውንም ጠቁመዋል።

የኢህአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ የተቃዋሚ  ፓርቲዎች ተሳትፎ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋትና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲያብብ ከማድረግ አኳያ የነበሩ ተጽዕኖዎች በዝርዝር መፈተሻቸውን ሊቀመንበሩ አብራርተዋል፡፡

የህግ የበላይነትን ባረጋገጠ መንገድ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት የሚያስችሉ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

Published in ፖለቲካ

አዳማ ታህሳስ 25/2010 የሃገራችን የግብርና ስነ-ምህዳር ለሃር ልማት ምቹ ቢሆንም ከዘርፉ የሚገኘው ምርት የሚፈለገውን ያክል እንዳላደገ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር ገለጸ።

የሀር ልማትን ይበልጥ ለማዘመንና ለማሳደግ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢፌዴሪ እንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ገብረኢግዝአብሔር ገብረዮሓንስ ለኢዜአ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቷ እየተከናወነ ያለው የሐር ልማት እጅግ አነስተኛ ነው ።

ልማቱ በግለሰቦች በገቡት የጉሎና የእንጆሪ ሐር ትል ዘሮች አማካይነት የሚካሔድ መሆኑን ገልፀው በዘርፉ በተደረገው ጥናት ከነዚህ የሚገኘው ኩብኩባና የሐር ድር  ምርት መጠን በጣም አነስተኛና ጥራቱም ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ከውጭ ሀገር የሚገቡ የሐር ትሎች ዲቃላ በመሆናቸው ከአንድ ትውልድ በኋላ የሐር ምርታቸውና የኩብኩባ መጠናቸው እየቀነሰ እንደሚሔድ ገልጸው ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ራሱን የቻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

መንግስት የዘርፉን ልማት ለማስፋፋትና ለማሳደግ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል አሰራር፣አደረጃጀትና የህግ ማዕቀፎችን እየዘረጋ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከውጭ ሀገር በሚገቡ ድቅል የሐር ትል ዘሮች የዘርፉን ልማት በተገቢው መንገድ ለማከናወን አዋጭ ባለመሆኑ የሀገር ውስጥ የሐር ትል ወላጅ ዘር ጣቢያ ተቋቁሞ በማራባትና በማባዛት ለተጠቃሚዎች የሚሰራጩበትን ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።

"በዋናነት ለግብርና ስነ-ምህዳራችን ተስማሚ የሆኑ ድቅል የሐር ትል ዘሮችን የመለየት፣ምርታማ የሆኑትን በመምረጥ በመንግስትና በባለሃብቶች ማዳቀያ ጣቢያዎች እንዲራቡና እንዲባዙ በማድረግ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ይገባል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ፈቀደ ፈይሳ በበኩላቸው "ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የሐር ልማት ለማከናወን መልካሳ ግብርና ምርምር ማእከል ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው"  ብለዋል።

በማዕከሉ የሐር ትል ዝርያዎችን መሰረት በማድረግ የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ የጉሎና የእንጆሪ መኖ ልማት በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

"ለሐር ትል ልማት የሀገራችን የግብርና ስነ ምህዳር ተስማሚ ነው" ያሉት ዳይሬክተሩ ድቅል የሐር ትሎችን ከውጭ ሀገር በማስገባት የማላመድ፣ምርታማ የሆኑትን በምርምር የመለየትና ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቐለ ታህሳስ 25/2010 በዓመት 40 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኘውና በኢዛና የማዕድን ኩባንያ የተገነባው የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ የሙከራ ምርት ጀመረ።

በሰሜን ምዕራብ ትግራይ አስገደ ፅምብላ ወረዳ ልዩ ስሙ ሚሊ በተባለ ቦታ የተገነባው የወርቅ ፋብሪካ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት መሆኑን የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ፀጋይ አሰፋ ገልጸዋል።

ፋብሪካው በ20 ሄክታር መሬት ላይ የተተከለና ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ያሟላ ሲሆን በቀን 840ቶን አፈር በመፍጨት ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ግራም ወርቅ እንደሚያመርት ገልጸዋል።

በዓመት 1ሺህ 300 ኪሎ ግራም በማምረት ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ለሃገሪቱ እንደሚያስገኝ የሚጠበቀው ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት በቀን ሶስት ኪሎ ግራም በማምረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

"ዕውቀትና ልምድ ያላቸው ተጨማሪ ባለሙያዎችን ከውጭ በመቅጠርና ልምድ በመውሰድ ሙሉ በሙሉ ማምረት ሲጀምር በቀን ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ግራም ያመርታል"ብለዋል።

ፋብሪካው የአካባቢ ብክለት እንዳያስከትል በ10 ሚሊዮን ብር የፍሳሽ ማስወገጃ እንደተዘጋጀለትም ተናግረዋል።

የፋብሪካው ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ወንድወሰን አወጣሀኝ " ፋብሪካው የተተከለበት ቦታ ከአምስት ዓመት በላይ በውጭና የሃገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች አዋጭነቱ ተረጋግጧል" ብለዋል።

በአካባቢው በተደረገው የአፈር ምርመራ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሜትር ጥልቀት የወርቅ ክምችት እንደሚገኝ በጂኦሎጂ ጥናትና የላብራቶሪ ምርመራ መረጋገጡንም አስታውቀዋል።

ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ለ200 ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ሲጀምር የመቀበል አቅሙን ከ300 በላይ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

በባህላዊ የወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩትን በማደራጀትም የሰበሰቡትን ወርቅ ባለው ገበያ ለፋብሪካው እንዲያቀርቡ የቴክኖሎጂ ስልጠናዎችን ጨምሮ ቀለል ያሉ የወርቅ መፈተሻ መሳሪያዎችንና የኬሚካል ድጋፍ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

የኢዛና ማዕድን ቁፋሮ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ አቶ አታኽልቲ አርአያ በበኩላቸው ወርቅ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም የማዕድን ቁፋሮዎችን ለማካሄድ ከውጭ ሃገር የተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በመሆን እያጠና እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በሚሊ የተተከለው የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ በሃገራችን ከ33 ዓመት በፊት ከተተከለው የአዶላ የወርቅ ፋብሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።

Published in ኢኮኖሚ

ጭሮ ታህሳስ 25/2010 በየዓመቱ የሚካሄደው የምዕራብ ሐረርጌ ስፖርታዊ ውድድር የፊታችን ዓርብ ይጀመራል።

የዞኑ የወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን መሀመድ እንደገለፁት "ስፖርት ለሰላምና ለአንድነት" በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ውድድር ዘንደሮ የሚካሄደው ለ24ኛ ጊዜ ነው፡፡

ውድድሩ በመጪው ጥር ወር አጋማሽ በሚካሔደው የመላው ኦሮሚያ ጨዋታዎች ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞች ለመምረጥ ይረዳል ።

"በውድድሩ ላይ ከ15 ወረዳዎችና  ከሁለት  የከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች ይካፈላሉ"ብለዋል ።

ጨዋታው በዞኑ እስከ ጥር 6 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በ12 የስፖርት ዓይነቶች የሚካሔድ ሲሆን ከተሳታፊዎቹ መካከል 550 ሴት ስፖርተኞች ይገኙበታል፡፡

ውድድሩ ስፖርታዊ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ የልምድ ልውውጥ የሚካሄድበት፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶች የሚጠናከርበት መድረክ እንደሚሆን ከአቶ ሁሴን ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

Published in ስፖርት

ፍቼ ታህሳስ 25/2010 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባለፉት አራት ወራት በማህበር የተደራጁ 14 ሺህ 8ዐዐ  ሴቶችና  ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ተደረገ፡፡

የዞኑ የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ ተፈሪ ቦጋለ እንደገለጹት ስራ አጥ የነበሩት ወጣቶችና ሴቶች ተደራጅተው  ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገው ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ ፣ የስልጠናና የመስሪያ ቦታ አቅርቦት ተመቻችቶላቸው ነው፡፡

እነዚህ ሴቶችና ወጣቶች የመንቀሳቀሻ ገንዘብ በማጣት ሲቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው በ123 ማህበራት ተደራጅተው በመንግስትና በሕዝብ በተደረገላቸው ድጋፍ በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሰማራታቸውን ተናግረዋል፡፡

የተሰማሩባቸው የስራ መስኮችም የከተማ ግብርና ፣ ማዕድን ማውጣት አነስተኛ ኢንዱስትሪ፣ ግንባታ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድና አገልግሎት ዘርፎች ናቸው ።

የስራ እቅዳቸውን መነሻ በማድረግ እስከ 650 ሺህ ብር የሚደርስ ብድር እንደተሰጣቸው ያመለከቱት ኃላፊው  ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ብቻ 10  ሚሊዮን ብር መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

በማህበር የተደራጁት ሴቶችና ወጣቶች በተሰማሩበት የስራ መስክ ውጤትና እርካታ እንዲያገኙ በማሰብ ከ12 ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል ።

በወረጃርሶ ወረዳ የኑኑ ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ጌታቸው ሰማ ከጥቂት ወራት በፊት ሥራ አጥ እንደነበር ጠቅሶ መንግስት የወጣቶችን ችግር በመገንዘብ ያመቻቸው የብድር ገንዘብና ሥልጠና ከሥራ አጥነት አላቆ የራሱን ገቢ እንዲያገኝ እድል እንደፈጠረለት ተናግሯል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በስሙ  በተሰየመው የጠጠርና አሸዋ ማምረት ሥራ ከሌሎች 11 ጓደኞቹ ጋር ተሰማርቶ በወር እስከ 2 ሺህ 5ዐዐ ብር ገቢ እንደሚያገኝና የካፒታል አቅሙን  እያሳደገ መሆኑን ገልጿል፡፡

ሌሎች ወጣቶችም የአካባቢያቸውን ሁኔታ በማጥናት ያገኙትን ስራ ቢሰሩ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውን ችግር በመፍታት ጭምር ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁሟል ።

በግሉ ማመልከቻ ባስገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተደራጅቶ የብድርና የስልጠና ድጋፍ ከማግኘት በተጨማሪ ፍቃድ አውጥቶ ከሶስት ወራት በፊት በብረታ ብረት ሥራ መሰማራቱን የተናገረው ደግሞ በፍቼ ከተማ ቀበሌ ዜሮ ሶስት ነዋሪው ወጣት ስለሺ ጐንፋ ነው፡፡

በግራር ጃርሶ ወረዳ የወርጡ ቀበሌ ነዋሪዋ ወጣት ትግስት አለኸኝ በበኩሏ በቅርቡ  ከአምስት አጋሮቿ ጋር በማኑፋክቸሪንግ ሥራ መሰማራቷን ገልጻለች፡፡

መንግስት የሴቶችን የስራ አጥነት ችግር ለማቃለል የጀመረው ጥረት መንግስታዊ  ባልሆኑ አካላት ጭምር  ሊታገዝ እንደሚገባም ጠቁማለች፡፡

"በተለይ የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ ያሉትን  ችግሮች ለመፍታት  ከድርጅቶችና ከሕብረተሰቡ ብዙ ይጠበቃል "ብላለች ።

ባለፉት አራት ወራት በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡት ወጣቶች መካከል 5 ሺህ 100   የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ የዞኑ የስራ እድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ታህሳስ 25/2010 በማእከላዊ ጎንደር ዞን የደረሱ ሰብሎችን ከዝናብና ከውርጭ ጉዳት ለመታደግ አርሶ አደሩ ባደረገው ጥረት በ434ሺ ሄክታር መሬት የደረሱ ሰብሎች መሰብሰባቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ለኢዜአ እንደተናገሩት በዞኑ በ2009/10 ምርት ዘመን ከለማው በ484ሺ ሄክታር 89 ነጥብ ስድስት በመቶ የሚሆነውን መሰብሰብ ተችሏል።

ከተሰበሰቡ የደረሱ ሰብሎች መካከል ሰሊጥ፣ በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ዳጉሳ፣ የቢራ ገብስና የቅባት ሰብሎች እንደሚገኙበት የገለጹት ኃላፊው የአርሶ አደሮቹ የልማት ቡድኖች ስራውን በተቀናጀ መልኩ ለማቀላጠፍ እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል።

"በጠገዴና በታች አርማጭሆ ወረዳዎች በምርት ዘመኑ በሰሊጥ ከተሸፈነው ከ100ሺ ሄክታር በላይ መሬት ከግማሽ ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጠው የሰሊጥ ምርት ተሰብስቦ ለገበያ በመቅረብ ላይ ይገኛል" ብለዋል።

በኩታ ገጠም እርሻ የተዘራውን ሰብል አርሶ አደሩ ያዳበረውን በጋራ የማረስ፣የመዝራትና የማረም ልምድ በመጠቀም የደረሱ ሰብሎችን ለመሰብሰብ እንዳገዘ ተናግረዋል።

በምርት አሰባሰብና አቀማመጥ ወቅት የሚስተዋለውን የድህረ ምርት ብክነት ለመቀነስም ለአርሶ አደሩ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በልማት ጣቢያ ባለሙያዎች አማካኝነት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በተለይ በአውድማ፣ በንፋስና በእንስሳት እንዲሁም በጎተራ በማስቀመጥ በአይጦችና በተባይ የሚደርሰውን የምርት ብክነትና ጉዳት ለመከላከል የሚረዳ ትምህርት ተሰጥቷል።

በጭልጋ ወረዳ የጮንጮቅ ቀበሌው አርሶ አደር ደሴ አስማረ "በአካባቢው ማለዳ ላይ የሚስተዋለው ውርጭ በደረሱ ሰብሎች ላይ የምርት ጥራት መጓደል የሚያስከትል በመሆኑ አዝመራዬን ሰብስቤ ወደ ጎተራ ማስገባት ጀምሬአለሁ" ብለዋል።

"በህዳርና በታህሳስ ወር የሚከሰተው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ውርጭ ቀድሞም ምርት የሚያበላሽ በመሆኑ ጥንቃቄ አደርጋለሁ" ያሉት ደግሞ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የዳስ ድንዛዝ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይደግ መላኩ ናቸው።

"የደረሱ ሰብሎችን በደቦና ቤተሰብን ጭምር በማሳተፍ በአግባቡ አጭዶ በመከመርና በመውቃት የምርት ብክነትና ጥራት መጓደል ሳይደርስ ሰብሌን መሰብሰብ ችያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

በዞኑ በምርት ዘመኑ በተለያዩ ሰብሎች ከተሸፈነው 484ሺህ ሄክታር መሬት ከ11 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ታህሳስ 25/2010 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የገቢ አቅማቸው ዝቀተኛ ለሆነ ለ2 ሺህ 200 የሕብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህግ አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ።

 የህግ ትምህርት ቤቱ በማዕከላቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ትናንት በጎንደር ከተማ ተካሂዷል፡፡

 በእዚህ ወቅት እንደተገለጸው ዩኒቨርሲቲው አገልገሎቱን የሰጠው በሰሜንና ደቡብ ጎንደር ዞኖች ባቋቋማቸው ነጻ የህግ ድጋፍ ማዕከላት በኩል ነው።

 የዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ቤት ዲን አቶ አበበ አሰፋ እንዳስታወቁት በዞኖቹ 15 ነጻ የህግ ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ተቋቁመው ሕብረተሰቡን እያገለገሉ ነው።

 አቅመ ደካሞች፣ ሴቶችና ህጻናት፣ አካል ጉዳተኞችና የኤች.አይ.ቪ ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው ወገኖች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 "ለእነዚህን የሕብረተሰብ ክፍሎች ጉዳያቸውን እስከ ሰበር ችሎት በመውሰድ ትክክለኛ ፍትህ እንዲያገኙ ተደርጓል " ብለዋል ።

 እንደ አቶ አበበ ገለጻ ለሕብረተሰብ ክፍሎቹ የተሰጠው አገልግሎት በገንዘብ ሲሰላ ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ነው ።

 የነፃ  ህግ  ድጋፉ መስጫ ማእከላቱ ህብረተሰቡን ከማገዛቸው ባሻገር የህግ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተግባር ልምድ እንዲቀስሙ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውንም ገልጸዋል፡፡

 የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ  በበኩላቸው  "ዩኒቨርሲቲው ማዕከላቱን በገንዘብና በቁሳቁስ ከመደገፍ ጀምሮ የህግ ባለሙያዎች በመመደብ ጭምር ለሕብረተሰቡ ነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ እያደረገ ነው " ብለዋል ።

 ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት እየተሰጠ ያለው የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት በተደራጀ አግባብ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ።

 በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኮሚሽነር አቶ አበረ ሙጨ እንደገለፁት፣ የሕብረተሰቡን የህግ ግንዛቤ ለማሳደግ ተቋማቱ የንቃተ- ህግ ትምህርት በስፋት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

 የምዕራብ በለሳ ወረዳ ነዋሪ ቄስ አሰፋ ተገኘ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት "ለጠበቃ የምከፍለው 15ሺህ ብር በማጣቴ አቁሜ የነበረውን የህግ ጉዳይ ማእከሉ ባደረገልኝ ነጻ ድጋፍ ቀጥዬ በፍርድ ቤት ፍትህ አግኝቻለሁ " ብለዋል ።

 "በደረሰብኝ የመኪና አደጋ በገንዘብ እጦት ምክንያት ጠበቃ አቁሜ ለመከራከር ባለቻሌ ማዕከሉ የህግ ባለሙያ በመመደብ ድጋፍ አድርጎልኛል" ያሉት ደግሞ አቶ ዘመነ አሳየኸኝ የተባሉ የመንግስት ሰራተኛ ናቸው፡፡

 በዞኖቹ በተቋቋሙት ማዕከላት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከ26ሺህ በላይ ለሚሆኑ የመክፈል አቅም የሌላቸው የተለያዩ የሕብረሰብ ክፍሎች ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ማግኘታቸው ታውቋል።

 ለአንድ ቀን በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ የፍትህ አካላት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ተወካዮች እንዲሁም የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ኃላፊዎች፣ የህግ ተማሪዎችና የማህበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ታህሳስ 25/2010 በአዲስ አበባ የአገር ባህል አልባሳት ዋጋ ተመጣጣኝና አቅምን ያገናዘበ መሆኑን ሸማቾች ተናገሩ።

የአገር ባህል አልባሳት አምራችና ነጋዴዎች በበኩላቸው አልባሳቱን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም እንስቶች በተለይም በበዓላት ብቻ ይደምቁበት የነበረው የአገር ባህል ልብስ አሁን ላይ በወንዶችም እየተዘወተረ ይገኛል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአገር ውሰጥም ሆነ በውጭ አገር በሚካሄዱ የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ በአገር ባህል ልብስ ደምቆ መታደም በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየተለመደ የመጣ ተግባር ሆኗል።

የኢዜአ ሪፖርተር በአዲስ አበባ ባህል አልባሳት ዙሪያ ያለውን የገበያ ሁኔታ በሽሮሜዳ አካባቢ ተዘዋውሮ ተመልክቷል።

በሽሮ ሜዳ አካባቢ የአገር ባህል አልባሳትን ሲገበያዩ ካገኘናቸው ሰዎች መካከል አቶ ግርማ መኩሪያ፤ የበዓል አልባሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚናገሩት።

አልባሳቱ በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው ደግሞ ለተፈላጊነታቸው ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት እሱባለው ኃይለማርያም የባህል አልባሳት ዋጋ እንደ የንግድ አካባቢዎች እንደሚለያይ ይናገራል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የራስ ጥቅምን ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለማሳደግ በኣልባሳቱ የተጋነነ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች እንዳሉም ወጣት እሱባለው ተናግሯል።

"የአገር ባህል አልባሳት በብዛትና በአይነት መቅረብ የተጠቃሚዎች ፍላጎት እንዲጨምር አስተዋፆ አበርክቷል" ያሉት ደግሞ አቶ ዓለምዓየሁ ለማ ናቸው።

የአልባሳቱ ዋጋ የተጋነነ እንዳልሆነም አክለዋል።

የባህል አልባሳት አምራችና ነጋዴዎች በበኩላቸው አልባሳቱን በተለያዩ ዲዛይኖች ማቅረባቸውንና የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።

በሽሮ ሜዳ አካባቢ የባህል አልባሳት ሱቅ ባለቤት የሆነው ወጣት ተመስገን አሰፋ በበኩሉ የአገር ባህል አልባሳት  በይበልጥ ዘመናዊ እየሆኑ መምጣታቸው የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ሌላው የባህል አልባሳት ሱቅ ባለቤት ወጣት ተክቶ ሲሳይ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ የባህል አልባሳትን  በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረቡን ይናገራል ።

Published in ኢኮኖሚ

ዲላ ታህሳስ 25/2010 በደቡብ ክልል የሀገረሰብ ነባር የሰብል ዝርያዎችን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የአካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን ገለፀ፡፡

በጌዴኦ ዞን የቡሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ሀገር በቀል ዝርያዎችን ጠብቆ ለማቆየት በማህበር ተደራጅተው እያከናወኗቸው ያሉ ተግባራት በክልሉ የሥራ ኃላፊዎችና ከተለያዩ ዞኖች በመጡ አርሶ አደሮች ተጎብኝቷል ፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ላይ የተገኙት በደቡብ ክልል አካባቢ ጥበቃና ደን ባለስልጣን የብዝሀ-ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ባፋ እንደገለፁት፣ በሀገሪቱ ከዚህ በፊት በየአካባቢው ይመረቱ የነበሩና አሁን ላይ ለመጥፋት የተቃረቡ በርካታ ሀገር በቀል ሰብሎችና የእፅዋት ዝርያዎች አሉ፡፡

"ዝርያዎቹ ከምግብነት ባለፈ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ሲሆን በሽታና የአየር ፀባይ መዛባትን የመቋቋም እንዲሁም አካባቢን የመላመድ አቅም አላቸው" ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዝርያዎቹ ሳይጠፉ ለመንከባከብና ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል የክልሉ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል ፡፡

አቶ መላኩ እንዳሉት፣ እስካሁን በክልሉ ሰባት የአርሶ አደሮች የሀገረሰብ ነባር ሰብል ጥበቃና የዘር ባንክ ማህበራት ተቋቁመው አርሶ አደሩ በራሱና በማህበሩ ማሳ ላይ ዝርያዎቹን እንዲያመርትና ለሌሎች እንዲያስተላልፍ ጥረት እየተደረገ ነው ፡፡

ጉብኝቱ በጋሞጎፋ፣ ስልጤ እና ጉራጌ ዞኖች እየተቋቋሙ ላሉ ተጨማሪ የአርሶአደሮች የሀገረሰብ ነባር ሰብል ጥበቃና የዘር ባንክ ማህበራት ግብአት እንዲሆንና አርሶ አደሮቹ ልምድ እንዲቀስሙ ታስቦ መካሄዱን አቶ መላኩ አስረድተዋል፡፡

በጌዴኦ ዞን የአካባቢ ጥበቃና ደን ልማት ጽሕፈት ቤት የብዝሀ-ሕይወት ዳይሬክቶሬት ቡድን መሪ አቶ ሞገስ ተሰማ የማህበሩ አባል የሆኑ አርሶ አደሮች ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጽህፈት ቤቱ በመስመር የአስተራረስ ዘዴና በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ላይ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል፡፡

በቡሌ ወረዳ የሆርሲንሶ የነባር ሰብል ጥበቃና አምራች መሰረታዊ ሕብረት ሥራ ማህበር ሰብሳቢ አርሶ አደር ከበደ አዱላ፣ ማህበሩ በ2005 ዓ.ም 50 አባል አርሶ አደሮች መመስረቱንና በአሁኑ ወቅት የአባላቱ ቁጥር 139 መድረሱን ተናግረዋል ፡፡

"ማህበሩ በአሁን ወቅት 42 ነባር የሀገረሰብ ሰብል ዝርያዎችን በማሰባሰብ በአርሶ አደሩና በማህበሩ ማሳ ለይ እያመረተ ይገኛል" ብለዋል።

አባላቱ ለዘር የሚወስዱትን ሰብል 20 በመቶ ወለዱን ጨምረው በምርት ማሰባሰብ ወቅት ለማህበሩ እንደሚመልሱም አመልክተዋል።

ማህበሩ በዘር ወቅት ለአባላቱ አሰራጭቶ የሚሰበስበውን ጨምሮ በዓመት ከ43 ኩንታል በላይ የሰብል ዘሮችን ወደ ዘር ባንኩ እንደሚያስገባም አስረድተዋል ፡፡

ከስልጤ ዞን ዳሎቻ ወረዳ የመጡት አርሶ አደር ሸረፋ ላሉቴ በበኩላቸው በወረዳቸው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመሆን አዲስ የነባረ ሀገር በቀል ሰብል ጥበቃ ማህበር እያቋቋሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

"በጉብኝቱ የቀሰምኩትን ልምድ በአካባቢዬ ለመተግበር ተዘጋጅቻለሁ" ብለዋል ፡፡ 

Published in አካባቢ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን