አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 02 January 2018

ጋምቤላ ታህሳስ 24/2010 መገናኛ ብዙሃንና የኮሚውኑኬሽን ዘርፉ የሀገሪቱን ብዝሃ ሕይወት በማስተዋወቅ በኩል በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አስታወቁ።

የማጃንግ ደን በአለም የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራነት /ባዮስፊር ሪዘርቭ/መመዝገቡን አስመልክቶ በማጃንግ ዞን ሜጢ ከተማ በተካሔደ አውደ ጥናት ላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ሃገሪቱ በርካታ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም በዘርፉ ብዙም አልተሰራበትም።

የሚታየውን የመረጃ ተደራሽነት ክፍተት በማሳደግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነቷን እንድታሳድግ በማስተዋወቅ በኩል የመገናኛ ብዙሃንና ኮሚኒኬሽን ዘርፉ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

በሀገሪቱ የሚገኙ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ ሀብቶችን በመንከባከብ በኩል ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው የማጃንግ ደን በሀገራችን አምስተኛው የአለም የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራ ሆኖ መመዝገቡ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ደኑ በተለይም ከቱሪዝም መስህብነት ባለፈ ለሀገሪቱ ብሎም ለአለም የከባቢ አየር ለውጥ የሚያበረክተው አስተዋፆኦ ከፍተኛ እንደመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላትና የአካባቢው ማህብረሰብ ሊንከባከበው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በበኩላቸው "ሀገሪቱ የጀመረችውን ልማት ለማሳካት በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር የታገዙ ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

ለስኬታማነቱም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለይም የአካባቢያቸውን የብዝሃ ህይወትና ስነ-ምህዳር መሰረት ያደረጉ ሥራዎችን በጥናትና ምርምር ውስጥ በማካተት ማህብረሰቡን ተጠቃሚ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ሚኒስትር መሰሪያ ቤቱ በተለይም በሀገሪቱ ችግር ፈቺ ምርምሮችን ለሚያከናውኑ ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይስና የባህል ድርጅት/ዩኔሴኮ/የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራነት የተመዘገበው የደኑ ብዝሃ ህይወት ተጠብቆ እንዲቆይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት፣የአካባቢው ማህብረሰብና አመራሮች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጋትለዋክ ቱት በበኩላቸው  የክልሉ መንግስት የአካባቢውን ብዝሃ ህይወት በማስጠበቅ የማህብረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ይገኛል።

የማጃንግ ደን የከባቢ ህይወት ጥብቅ ስፍራ ሆኖ የተመዘገበው ከያዮ፡ከሸካ፡ከከፋ ደኖችና ከጣና ሐይቅ ቀጥሎ በኢትዮጵያ አምስተኛ በአለም ደግሞ 669ኛ በመሆን ነው።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2010 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መድረክ በአገሪቷ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጋር በመሆን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።

 የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት መድረክ ከተለያዩ በጎ አድራጎት ተቋማት፣ ከፌደራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።

 የመድረኩ ኤክስኪዩቲቭ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ነጋሽ ተክሉ፤ “ያለ ሠላም ማንኛውንም ተግባራት ማከናወን ስለማይቻልና ሠላም የሁላችንም ጉዳይ በመሆኑ ተባብረን መሥራት ይኖርብናል” ብለዋል።

 በመሆኑም መድረኩ በተለይ በአገራዊ የጋራ ጉዳዮች የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

 የኢትዮጵያ ሴቶች ኔትወርክ ማኅበር ወይዘሮ ሳባ ገብረመድኅን በበኩላቸው፤ በዓለም፣ በአህጉር እና በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ግጭቶች ሴቶች ተጠቂ ሲሆኑ እንጂ የመፍትሔ አካል ተደርገው ሲታዩ እምብዛም አይስተዋልም ብለዋል።

 የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ሕሉፍ ወልደሥላሴ ጉባዔው የተቋቋመለትን ዓላማ አንግቦ በተለይ በኃይማኖት ሽፋን የሚመጡትን ፀረ-ሠላም ኃይሎችን ለመመከት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 በቀጣይም ጉባዔው በተለይ እንደ መልካም አስተዳደር፣ በሠላም ጉዳዮችና መሰል አገራዊ የጋራ አጀንዳዎች ላይ ገለልተኛ በሆነ መልኩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የጀመረውን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግረዋል።

 ከፌደራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዘላቂ መፍትሔ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ መለሰ እንዳሉት፤ በክልሎች መካከል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ ዘዴዎችን በማስቀመጥ በመሠራቱ ውጤት ማምጣት ችሏል።

 “እንደ አገር የሚከሰቱ ግጭቶችን የመከላከልና የመፍታት ስትራቴጂው ትኩረት ሲያደርግ የነበረው በክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ነበር” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ስትራቴጂው አሁን በከተሞችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተከሰቱት ችግሮች ያላካተተ ነበር።

 ግጭቶች ቢኖሩም ባይኖሩም የሠላም ባህልን እያጠናከሩ መሄድ እንደ አገር ወሳኝ በመሆኑ በቀጣይ ሁሉም ዜጋ ለአገሩ ሰላም ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል።   

 

Published in ፖለቲካ

መቀሌ ታህሳስ 24/2010 የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የድርሻቸውን እንደሚወጡ በትግራይ ክልል የሚገኙ የብዙሀን መገናኛና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ተናገሩ።

የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን " የሙስና ወንጀልን በመከላከል በኩል የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሚና " በሚል ርዕስ  በውቅሮ ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

በስልጠናው የተሳተፉ ከ150 በላይ የተለያዩ ተቋማት ጋዜጠኞችና የክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የህዝብ ግኑኝነት ባለሙያዎች እንዳሉት፣ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣውን የሙስና ወንጀል ለመከላከል የድርሻቸውን ይወጣሉ።

በትግራይ ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተሾመ ጣማለው እንዳለው፣ በአሁኑ ወቅት የልማት ፀር ከመሆን ባለፈ የስርዓቱ አደጋ እየሆነ የመጣውን ሙስናን ለመታገል የብዙሀን መገናኛዎች ተገቢ ሽፋን እየሰጡ አይደለም።

ህዝቡ በጸረ ሙስና ላይ የጀመረውን ትግል ለማጠናከር የብዙሀን መገናኛ ተቋማት ሚና ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ገልጾ፣ "የሚዲያ ባለሙያዎችም የህዝቡን ትግል ለማነቃቃት የሚያስችሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን በመስራት የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል" ብሏል።

የትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ፕሮግራም ኃላፊ ኢንስፔክተር ገብረሚካኤል ኪዳነ በበኩላቸው፣ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዳይረጋገጥ ከሚያደናቅፉ ዋናዋና ችግሮች መካከል የሙስና ወንጀል ቀዳሚው መሆኑን ተናግረዋል።

"ሙስኞችና ከሙሰኞች ጋር የሚያብሩ አካላትን በመከታተል ተጠያቂ አንዲሆኑ ለማድረግ የብዙሀን መገናኛ ተቋማትና በየደረጃው የምንገኝ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ድርሻ የላቀ በመሆኑ በትኩረት ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።

በትግራይ የሚገኙ የሴቶች የልማት ቡድኖች ሙስናን ለመታገል የጀመሯቸውን ትግሎች በማነቃቃት የተጠናከረ ሥራ አንደሚሰሩ የገለጸው ደግሞ የትግራይ ክልል ሴቶች ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ወጣት ኃለፎም ኃይለ ነው።

ሴቶች በሙስና ቀዳሚ ተጎጂዎች መሆናቸውን አውቀው በተናጠልና በማህበር ተደራጅተው ትግላቸውን እንዲያጠናክሩ የሚድያ ድጋፎችን ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በውቅሮ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደ ግምገማዊ ስልጠና የተገኙት የክልሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ታደሰ ገብረዋሀድ በበኩላቸው የፀረ ሙስና ትግሉ ሳይጠናከር የትም መድረስ እንደማይቻል ተናግረዋል።

በመሆኑም ለሀገሪቱ የሕዳሴ ጉዞ እንቅፋት እየሆነ ያለውን የሙስና ወንጀል በመታገል በኩል የሚዲያ ተቋማትና የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ተገንዝበው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"ሙሰኞችን የሚያጋልጡ የምርመራ ዘገባዎችን በማቅረብ ግዴታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ካለፈው ዓመት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከ50 ሺህ ለሚበልጡ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠቱ ተገልጿል፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2010 የታላቁ ህዳሴ ግድብ የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት 9 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲፈጸም፤ የሁለተኛው ፕሮጀክት የ'ሳድል ዳም' ደግሞ 11 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የድንጋይ ሙሌት መከናወኑ ተገለጸ።

የግድቡን ግንባታ ሂደትና የደረሰበትን ደረጃ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ገለፃ አድርገውላቸዋል።

በስፍራው የተገኙት ባለሞያዎችም የግድቡ ተቋራጭ ኩባንያዎች የሲቪልና የኤሌክትሮ ሃይድሮ መካኒካል ስራዎችን በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተመልክተዋል።

የዋናው ግድብ ቁመት ከባህር ወለል በላይ 145 ሜትር ከፍታ ሲኖረው፤ ወደ ጎን ደግሞ 1 ሺህ 780 ሜትር ርዝመት አለው።

በዚህ የግድቡ ከፍታ ላይ ለመድረስ 10 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የአርማታ ሙሌት እንደሚያስፈልግ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ኃላፊ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ግንባታ እየተሳተፈ ያለው የሰው ኃይል ቁጥር ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታ ይታይበታል ያሉት ኢንጂነር ስመኘው ቀደም ሲል የሰራተኞቹ ቁጥር 13 ሺህ ደርሶ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ዘጠኝ ሺህ ሰራተኞች በግንባታው ላይ እየተሳተፉ ነው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ከፍታ በጨመረ ቁጥር የግንባታው ስፋት እየጠበበ መሄዱ ለሰው ኃይልና ለማሽነሪዎች መቀነስ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዋናው ግድብ ግርጌ የሚገኙት ሁለቱ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የኤሌክትሮ ሃይድሮ መካኒካልና የሲቪል ስራ እንዲሁም የድንገተኛና ከፍተኛ የውሃ ሙሌት ማስተንፈሻ በሮች ስራዎች በቅንጅትና በተፋጠነ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የ'ሳድል ዳም' ግድብ 5 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 50 ሜትር ቁመት ያለው ሲሆን፤ ይህን 50 ሜትር ቁመት ከፍታ ለመሙላት 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የድንጋይ ሙሌት ያስፈልገዋል ብለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈፃፀም 63 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሃን ታህሳስ 24/2010 በአማራ ክልል በአሰሪዎችና ሠራተኞች መካከል ሰላማዊ የሥራ ግንኙነት በመፍጠር የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነትና ውጤታማነት ማሳደግ እንደሚገባ የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለፀ። 

በሰሜን ሸዋ ዞን አገረማሪያም ወረዳ ቱለፋ ቀበሌ በሚገኘው " ኤቨርብራይት" የፕላስቲክ ማምረቻና በአጎለላና ጠራ ወረዳ ጫጫ ከተማ በተገነባው "ሱፐር ኤግል አረቄ ፋብሪካ" የሠራተኞች መሰረታዊ ማህበር ተመስርቷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን መኳንንት በማህበር ምስረታው ወቅት እንደገለፁት ሠራተኞች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን በተደራጀ መንገድ ለመጠበቅና ጥቅሞቻቸውን ለማረጋገጥ መደራጀታቸው ጠቃሚ ነው።

በሠራተኞችና በአሰሪዎች መካከል የሚኖረውን የሥራ ግንኙነት በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ በማድረግ ምርታማነትን ማሻሻልና የእኩል ተጠቃሚነት መንፈስን ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ግንኙነታቸው እየተጠናከረ መምጣት አንዳንዴ በሥራ ሂደት አለመግባባት ሲከሰት በመወያየት እንዲፈታና ሁለቱም ወገኖች በህገ መንግስቱ የተረጋገጡላቸውን መብቶች በአግባቡ እንዲጠቀሙ ያግዛል።

በሀገረ ማሪያም ከሰም ወረዳ ቱለፋ ቀበሌ በቻይና ባለሀብቶች የተገነባው “ኤቨርብራይት” የፕላስቲክ ማምረቻ የግል ኢንተርፕራይዝ አስተዳደር ኃላፊ አቶ ኤርምያስ በኩየት እንዳሉት ድርጅቱ በ16 ሄክታር መሬት ላይ የተገነባ ነው።

ፋብሪካው በዓመት 80 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም እንዳለውና ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከልም የማዳበሪያ ከረጢት፣ የፕላስቲክ ሸራና ገመድ እንዲሁም የተለያዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

የሰራተኞች መሰረታዊ ማህበር መመስረቱ ድርጅቱ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ ጥራትን ለማሻሻል እንዲሁም ሠራተኞች በሚገጥሟቸው ጉዳዮች ላይ በተወካዮቻቸው አማካኝነት ለመወያየት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የድርጅቱ ሠራተኛ ወይዘሮ መኪያ ተማም በበኩላቸው " እስካሁን ድረስ የዓመት እረፍት አሰጣጥ በሠራተኞች ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ ተቸግረን ነበር " ብለዋል።

መደራጀታቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በሰከነ መንገድ በውይይት ለመፍታት እንደሚያግዛቸው አመልክተዋል።

የሱፐር ኤግል አረቄ ፋብሪካ ሠራተኛ ወጣት አየለች ተሾመ  "ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ አይከፈልም፤ የጾታ ልዩነትን መሰረት በማድረግም የክፍያ ልዩነት አለ" ብላለች።

ከዚህም በተጨማሪ የሥራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ አልባሳትና ሌሎች ቁሳቁሶች በተገቢው መንገድ በፋብሪካው እንደማይሰጡ ገልጻ፣ መደራጀታቸው ያሉባቸውን ችግሮች በተገቢው መንገድ ለመፍታት ይጠቅማል የሚል እምነት እንዳሳደረባት ተናግራለች።

አቶ ከበደ ተሰማ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው በአካባቢው እያደገ ለመጣው የኢንዱስትሪ ፍሰት መሰረታዊ ማህበር መደራጀቱ የሰራተኛውን መብት ለማስጠበቅ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

በሰሜን ሽዋ ዞን እስካሁን 41 መሰረታዊ የሠራተኞች ማህበራትና አራት የአሰሪ ማህበራት በማቋቋም የኢንዱስትሪ ሰላምን ለማስፈን ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ታህሳስ 24/2010 ከዩኒቨርስቲ  በሲቪል ምህንድስና ሙያ የተመረቁ  ወጣቶችን በገጠር መንገድ ጥገና ስራ ላይ እንዲሳተፉ ዝግጅት መደረጉን  የትግራይ ክልል የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድና የከተሞች ምግብ ዋስትና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ገለጸ።

ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በዘርፉ ሙያ የተመረቁ 327 ወጣቶችን ማሳተፍ በሚቻልበት ላይ ያተኮረ  የሁለት ቀናት ስልጠና በውቅሮ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በኤጀንሲው የጥቃቅንና አነስተኛ የስራ እድል ፈጠራ ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ካሕሳይ ተስፋይ እንዳሉት የስልጠናው ዓላማ ወጣቶቹ በመንገድ ጥገና የኮንትራት አስተዳደር ላይ ማድረግ ስላለባቸው  ቅድመ ሁኔታና ጥንቃቄዎች ግንዛቤ አግኝተው  ወደ ስራ እንዲሰማሩ ለማስቻል ነው።

የመንገድ ጥገና ስራው ወጣቶቹ የስራ እድል ከመፍጠር ባለፈ ወጣቶች ስለ ቁጠባ አስፈላጊነት ተረድተው ከሚያገኙት ገቢ ቆጥበው ወደ ተሻለ ስራ እንዲሸጋገሩ ጭምር ስልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

" በቀጣይም በራስ የመተማመን ባህል እንዲያዳብሩና በሀገሪቱ የልማት ስራ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ያግዛቸዋል" ብለዋል አቶ ካሕሳይ።

ለዚህም ማስፈጸሚያ የክልሉ መንግስት ከ53 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ መድቧል።

"ተመራቂዎቹ በስራ ቆይታቸው በትግራይ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ 376 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የገጠር መንገድ በስድስት ወራት ጠግነው አገልግሎት ላይ እንዲያውሉ ይጠበቃል"ብለዋል።

ከመቐለ ዩኒቨርስቲ በ2008 ዓ.ም በሲቪል ምህንድስና የተመረቀው ወጣት ተስፋዬ ካህሳይ በሰጠው አስተያየት የስራ እድሉ ከራሱ አልፎ ሌሎች ወጣቶችን ለመጥቀም እንደሚያስችል ተናግሯል።

ከዚህ ስልጠና በኋላ በምንሰማራው ስራ ለራሳችን፣ ለቤተሰቦቻችንና ለሌሎች የስራ እድል ለሌላቸው ወገኖቻችን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የምንችልበት እድል የሚፈጥር ነው፡፡

በውሃ ሃብት ምህንድስና ሙያ  ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ የተመረቀችው ወጣት ህይወት ገብረ ህይወት በበኩሏ በትምህርት ያገኘችውን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር እራሷን ለመጥቀምና በአካባቢው ልማት የድርሻዋን  ለመወጣት መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡

“ከስራ እጥነት ወጥቼ የራሴ የስራ እድል ማግኘት ማለት ለኔ ትልቅ ደስታ ነው፤  ከዚህ ተነስቼ ራሴን ችዬ የምተዳደርበት ሁኔታ ለመፍጠር ወደምጀምርበት ደረጃ ለመድረስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርልኛል፡፡” ብላለች፡፡

የተመቻቸው የስራ እድል የራሱን ኑሮ በተሻለ መንገድ ከመምራት በተጨማሪም በሙያው ያስተማረውን ህዝብ ለማገልገል የሚያስችለው መሆኑን የተናገረው ደግሞ  ከወሎ ዩኒቨርስቲ በሲቪል ምህንድስና ሙያ የተመረቀው ወጣት ጥጋቡ እጅጉ ነው፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/2010 የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ነገ ታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ይጀምራል ካለው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ውስጥ የአዲስ አበባና የአዳማ ተጓዦች አገልግሎት ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ማራዘሙን ገለፀ።

ከድሬዳዋ ጅቡቲ ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት ግን በተጠቀሰው ቀንና ሰዓት የሚጀመር መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል።

ኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጌጅ የባቡር ትራንስፖርት የመንገደኞችና የጭነት አገልግሎት ከታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ስራ እንደሚጀምር ትናንት ማስታወቁ ይታወሳል።

ይሁንና የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ጥላሁን ሳርካ ለኢዜአ እንደገለጹት ከለቡ/አዲስ አበባ/ አዳማ ተጓዦች አገልግሎት ለአንድ ሳምንት ተላልፏል።

ደንበኞች ተገቢው የጉዞ ሰነድ እንዲያሟሉ የሚጠበቅ በመሆኑ ከጉዞው 48 ሰዓት ቀደም ብሎ አስፈላጊውን መረጃ ማሟላታቸው መረጋገጥ እንዳለበት የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤  ከአዲስ አበባና አዳማ ለሚነሱ ደንበኞች አገልግሎት ለመስጠት ከጉዞ ሰነድ ጋር የተያያዙ ሥራዎች በተፈለገው ፍጥነት ባለማለቃቸው የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሊራዘም ችሏል ብለዋል።

የጉዞ ትኬቱን ግን ከዛሬ ጀምሮ ተጓዦች እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ስለሆነም የአዳማ  እና የአዲስ አበባ  ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚዎች በመጪው ሳምንት ማክሰኞ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ከጥዋቱ 2 ሰዓት ጀምሮ አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ጠቁመዋል።

የአገልግሎትን ታሪፍ ዝርዝር መረጃ ኢዜአ ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀምር ተጓዦች ጉዞ ከሚጀመርበት ጊዜ 45 ደቂቃ ቀድመው መገኘት እንደሚጠበቅባቸው አስታውሰዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 24/4/2010 ህብረተሰቡ ለመልካም አስተዳደር መጓደልና ብልሹ አሰራር ምንጭ የሆነውን ሀሰተኛ ሰነድ የሚጠቀሙ አካላትን እንዲያጋልጥ የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ 14ኛውን አለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን ''ሀሰተኛ ሰነዶችን በማጋለጥ የጸረ-ሙስና ትግሉን ማጠናከር'' በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ  በአዲስ አበባ በውይይት አክብሯል።

ኮሚሽነሩ አቶ አየልኝ ሙሉዓለም በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሙስናን መከላከል ካልተቻለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን፣ ሰላምና መረጋጋትን፣ የተጠናከረ የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትንና ውጤታማ የፋይናንስ አጠቃቀም ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ አይቻልም።

ህብረተሰቡ ለብልሹ አሰራርና ሙስና ምንጭ የሚሆነውን ሀሰተኛ ማስረጃን በማጋለጥ አገራዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባልም ብለዋል።

ለሙስና ተጋላጭ በሆኑት በመሬት አስተዳደር፣ በግብር አስተዳደር፣ በትላልቅ የመንግስት ግዥዎችና በፍትህ ዘርፎች ላይ ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ የሚፈፀም ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኝነትን ማሳየት ይገባል ብለዋል።

የጸረ-ሙስና ትምህርትን ለማስፋፋትና ሙስናን ቀድሞ ለመከላከል በትምህርት ቤቶችና በየተቋማቱ በሚገኙ የስነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በኩል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በፀረ ሙስና ትግሉ ተሳታፊ እንዲሆን ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኮሚሽኑ ሀብትና ጥቅምን በማሳወቅና ማስመዝገብ እና ሌሎች ሙስናን መከላከል የሚያስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ትግሉን በሃላፊነት የማስተባበር ግዴታውን ይወጣል ብለዋል።

ሀሰተኛ ሰነድን በመጠቀም የማይገባ ጥቅም ማግኘት ሙስና በመሆኑ ዜጎች በአንድ በኩል ራሳቸውን ከሙስና በማራቅ፣ በሌላ በኩል ሙሰኞችን በማጋለጥ ለእውነት መቆም እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም የተፈፀሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ የሀብት ምርመራ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተረፈ ሆርዶፋ በበኩላቸው ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተወሳሰበና  እየጨመረ እንደመጣ ተናግረዋል።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን፣ መታወቂያዎችን፣ መንጃ ፈቃዶችን በመጠቀም ከፍተኛ የፋይናንስና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየደርሱ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

በቅርቡ በተደረገው ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የመጠቆምና የማጋለጥ ስራ በአማራ ክልል 4 ሺህ በጥቆማ፣ 532 ራስን በማጋለጥ ሀሰተኛ ማስረጃዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል 6 ሺህ 447 ራስን ማጋለጥ፣ ከ20 ሺህ በላይ ጥቆማዎች እንደደረሱ ተናግረዋል።

ድርጊቱ በአገር ንብረት እና መልካም አስተዳደር ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ችግሩን ለመከላከል የአመለካከት ለውጥ መፍጠር፣ ሀሰተኛ ማስረጃዎችን መቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን መዘርጋት ያስፈልጋልም ብለዋል።

ሀሰተኛ ሰነድ በቀላሉ እንዳይዘጋጅ በትክክለኛው ሰነድ ላይ ልዩ ምልክት ማዘጋጀት ተቋማት የግድ ሊተገብሩት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ አለም አቀፉን የፀረ ሙስና ስምምነት ተቀብላ የፀረ ሙስና ህግ የአገሪቱ አንድ የህግ ሰነድ እንዲሆን በማድረግ ሙስናን ለመከላከል እየሰራች ነው።

Published in ፖለቲካ

ታህሳስ 24/2010 በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት 2018 የኢትዮዽያ ኢኮኖሚ በፈጣን ሁኔታ ዕድገት እንደሚያሳይ ኒው ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡

በምጣኔ ሃብት ዙሪያ ዓመታዊ ሪፖርት የሚያወጣውን የፕራይስ ወተር ሃውስ ኩፐርስ (PwC’s) ትንበያን መሰረት በማድረግ ኒው ቴሌግራፍ እንደዘገበው በተጠቀሰው ዓመት ከ6-7 በመቶ እንደሚያድግ ከተተነበየው የቻይና ኢኮኖሚ በበለጠ የኢትዮዽያ ምጣኔ ሃብት በፈጣን ሁኔታ እንደሚያድግ ትንበያው አመላክቷል፡፡

ከኢትዮዽያ ባልተናነሰ የህንድ፣የጋና እና የፊሊፒንስ ኢኮኖሚም እንደሚያድግ ዘገባው አመልክቷል።

በተያያዘም በ2018 ይመዘገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ፈጣን አስር የምጣኔ ሃብት ዕድገቶች ስምንቱ በአፍሪካ እንደሚመዘገቡም የፒ ደብሊው ሲ ትንታኔ አሳይቷል።

የአለም አቀፉ ኢኮኖሚም በተያዘው ዓመት በ4 በመቶ ዕድገት እንደሚኖረው ያሳየው ሪፖርቱ ከዚህ ውስጥ ዩ ኤስ አሜሪካ፣እስያና ዩሮ ዞን 70 በመቶ የምጣኔ ሃብት አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል፤እኤአ በ2000 ከነበራቸው የ60 በመቶ አስተዋፅኦ የተሻለ እንደሆነም በዘገባው ተመልክቷል።

ዩሮ ዞን በተባለው አካባቢ የምጣኔ ሃብት ዕድገቱ ከ2 በመቶ በላይ እንደሚሆንና ኔዘርላንድ በ2 ነጥብ 5 በመቶ የምጣኔ ሃብት ዕድገት አካባቢውን እንደምትመራው ነው የተተነበየው፡፡

ከተቀሩት የአውሮፓ ሀገራት ህብረት የመነጠል ዘመቻ ላይ የምትገኘው ዩናይትድ ኪንግደም የኢኮኖሚ ዕድገቷ 1 ነጥብ 4 በመቶ ሊሆን እንደሚችል በትንበያው ተጠቁሟል።

የነዳጅ ዋጋም በተያዘው ዓመት ባለበት ሊቆይ እንደሚችል ያስቀመጠው መረጃው በቅርቡ የነዳጅ አምራች ሃገራት ስብስብ ኦፔክ ምርቱን በቀን ወደ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በርሜል ለማሳደግ መስማማቱን በዋቢነት አንስቷል።    

የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት 2018 ከፍተኛ የኢነርጂ ፍላጎት የሚታይበት ዓመት እንደሚሆንም ትንበያው አመላክቷል።   

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ጎንደር ታህሳስ 24/2010 የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ የተመደቡለትን አንድ ሺህ 500 ተማሪዎች ተቀብሎ የመማር ማስተማር ሥራውን ለመጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀጃው ደማሙ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ተቋሙ በትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን ተማሪዎች ጥር 2 እና 3 ቀን 2010 ለመቀበል ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ 

ለተቋሙ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው 64 መምህራን ከትምህርት ሚኒስቴር ከመመደባቸው በተጨማሪ በቅጥር ጭምር የማሟላት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚቀበላቸው አዲስ ተማሪዎች በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ፣ በግብርና፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ የትምህርት መስኮች ጨመሮ በ15 የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ ዲግሪ የሚሰለጥኑ ናቸው፡፡

"በምርምርና በማህበረሰብ ዘርፍም ዩኒቨርሲቲው በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ እንደመገኘቱ ፓርኩን ለመደገፍና የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን ስትራቴጅክ ዕቅድ አዘጋጅቶ ይሰራል" ብለዋል፡፡

ለተማሪዎች የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ የመማሪያ፣ የቤተ-ሙከራ፣ የቤተ-መጻህፍት፣ የመኝታና የመመገቢያ ሕንጻዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲው የግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እርዚቅ ወዳጆ ናቸው፡፡

የሰባት ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታና ስድስት የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመሮች ተከላ ሥራ መከናወኑና በእዚህም ተቋሙ በቂ የመብራት ኃይል እንዲያገኝ መደረጉን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የውስጥ ለውስጥ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑንና ሌሎች ለመማር ማስተማሩ የሚያግዙ የግንባታ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ እርዝቂ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችን በተሟላ መንገድ ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችለውን ዝግጅት ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ በ204 ሄክታር መሬት ላይ ለተገነባው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ የፌደራል መንግስት ከ450 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል።         

የደባርቅ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን ለተማሪዎች የተሟላ አቀባበልና መስተንግዶ ለማድረግ ከወዲሁ ዝግጅት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን