አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 12 January 2018

አዳማ ጥር 4/2010 ህብረተሰብ አቀፍ የተቀናጀ የስነ ምህዳር ጥበቃና የመሬት ልማት አስተዳደር ፕሮጀክት ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የአካባቢ ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ ዘላቂ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ ዶክተር ተስፋዬ ኃይሌ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ከዳር ለማድረስ ነው፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ የብዝሃ ህይወት ሃብቱ በሀገሪቱ የልማት ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረውና የተጀመረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ህብረተሰቡን በንቃት በማሳተፍ ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ነው።

የሀገሪቱን ምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥም  ያግዛል።

ፕሮጀክቱ በኦሮሚያ፣አማራ፣ደቡብ፣ትግራይ፣ሶማሌና አፋር ክልሎች በሚገኙና በምግብ እጥረት በተጎዱ 12 ወረዳዎች በሙከራ ደረጃ ከ2010 ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው።

ለፕሮጀክቱ ማካሄጃ  ከተባበሩት መንግስታት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም 11 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ መደረጉን ያመለከቱት ባለሙያው " ከህዝብና ከመንግስት 144 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የቁሳቁስ ፣የጉልበትና የዕውቀት ተሳትፎ ይደረጋል "ብለዋል።

እስከ 2014 የሚቆየው ፕሮጄክቱ ከ220 ሺህ በላይ ቤተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ከዶክተር ተስፋዬ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል ።

በዚህም የእንስሳት መኖ ልማት፣ንብ ማነብ፣በአፈርና ውሃ ዕቀባ፣በደን ልማት፣በአካባቢ ጥበቃና ተያያዥ መስኮች ከ140ሺህ በላይ ወጣቶች ጨምሮ ሌሎችም የህብረተሰብ  ክፍሎች ይሳተፋሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማሪዮ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የብዝሃ ህይወት ሃብቱ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማስቻል የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለብዝሃ ህይወት ሀብት ልማት ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በሁሉም ወረዳዎች ለማስፋፋትም  የደንና አካባቢ ሚኒስቴር፣  የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡

Published in አካባቢ

አዳማ ጥር 4/2010 ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ በተሻለ ውጤታማነት ለማስፈጸም ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የኦሮሚያ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች ገለጹ።

የኦሮሚያ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ የተፋሰስ ልማትና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንዳስታወቁት ዘንድሮ የሚካሄደውን የተፋሰስ ልማት በክልሉ በተሻለ ሁኔታ ለማከናወን ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

ለእዚህም ወደሥራ ከመገባቱ በፊት በየደረጃው ከሚገኙ የአመራር አካላትና ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉንና የክህሎት ስልጠና መሰጠቱን ጠቁመዋል።

ለልማት ሥራው አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ ፈጻሚ አካላትን ዝግጁ የማድረግ ሥራ ቀደም ብሎ መጠናቀቁንም አስታውቀዋል።

" ነባሩን የኦሮሞ ሕዝብ የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ፣ እሴትና ባህል ለዘላቂ ልማት ንቅናቄ በሚል መርህ" በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እንቅስቃሴው መጀመሩንም አመልክተዋል።

አቶ ስለሺ እንዳሉት፣ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራው 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል።

በዘመቻ መልክ ለአንድ ወር ከሚከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የተለያዩ የስነ አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች፣ 890 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን  ሥራ ይገኙበታል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የውሃ ማስወገጃ እስተራክቸር፣ የእርጥበት ማቆያ፣ 514 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና ከእንሰሳት ንኪኪ ውጭ ማድረግና ሌሎችም በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን መታቀዱንም አስረድተዋል።

የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ተወካይ አቶ ኬት ቾል በበኩላቸው እንዳሉት፣ በክልሉ የዘንድሮውን የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ደረጃ ማከናወን እንዲቻል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

በ2010 በጀት ዓመት 538 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ አዳዲስ የሥነ-አካላዊ፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ለማከሄድ ዕቅድ መያዙን ጠቁመው፣ በተያዘው ጥር ወር በአምስት ወረዳዎች የተለየዩ የህዝብ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የተፋሰስ ልማት ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል። 

ሥራውን ለማስፈጸም 198 ሺህ የተለዩ የቅየሳና የእጅ መሳሪያዎች መዘጋጀታቸውንም አቶ ኬት ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት ልማት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ቦጋለ ሌንጮ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማትን አስመልክቶ ለተሳታፊዎችና አመራር አካላት ቀደም ብሎ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በክልሉ በሚከናወነው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ በጉልበት የሚሳተፍ 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሰው ኃይል  መለየቱንም አመልክተዋል።

ከዓመት ዓመት የሚሰሩ ሥራዎች እየተሻሻሉ ቢመጡም የጥራት፣ ልቅ ግጦሽ እንዲሁም የተሰሩ ሥራዎች  መረጃ አያያዝ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ ገልጸው፣ ዘንድሮ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተከናወኑ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች ከጥቅም ውጪ ሆነው የነበሩ ተራሮች፣ የእርሻ፣ የደንና የግጦሽ መሬቶች አገግመው ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል።

የከርሰ ምድር ውሃ፣ የአፈር ለምነትና በመስኖ የሚለማው መሬት የጨመረ ሲሆን የአፈር መሸርሸር መጠን ዝቅ ማለቱም ተመልክቷል።

ከዚህ በተጨማሪ በመኖ አቅርቦት፣ በማር ምርት መጨመር፣ በሴቶች ተጠቃሚነት፣ በድህነት ቅነሳና በምግብ ዋስትና ላይ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው።

 

Published in አካባቢ

ነቀምቴ ጥር 4/2010 በምሥራቅና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ዓመታዊ የወረዳዎች የልዩ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን ውድድር ዛሬ በነቀምቴ ከተማ ሲጀመር የዞኑ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽፈህት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እመቤት በየነ እንገለጹት ውድድሩ ሶስት ዓላማዎችን ያነገበ ነው ።

ብቃት ያላቸውን ስፖርተኞችን በማፍራት ዞኑን በመወከል በመላ ኦሮሚያ ጨዋታዎች ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞች ለመምረጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለሳምንት በሚካሔደው ውድድር ላይ በሁለቱም ጾታ ከዞኑ 17 ወረዳዎች የተውጣጡ 731 ስፖርተኞች ተሳታፊ ይሆናሉ።

ውድድሩ የእግር ኳስ፣ የቦሊቦል፣ ፣ዳርት፣የፓራ ኦለምፒክ ፣አትሌቲክስ ፣የጠረጴዛ ቴኒስ ፣ባድሜንቴን ያካተተ መሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል ።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የየስፖርት ምክር ቤት ሰብሰቢ አቶ ሀብታሙ ቦረና እንዳሉት  የስፖርት ውድድር ለአካል ብቃትና ጥንካሬ ብቻ  ሳይሆን ፍቅርና አንድነትን ከመፍጠር አንፃር ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው ገልፀዋል ።

በመክፈቻው በተካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ጉቶ ጊዳ ወረዳ ተጋጣሚው  ሀሮ ሊሙ ወረዳን 4 ለ 0  በሆነ ውጤት አሸንፏል ።

በተመሳሳይ መልኩ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ጥር 1 ቀን 2010 የተጀመረው ዓመታዊ የወረዳዎች የስፖርት ውድድር በጥሩ ሁኔታ ቀጥሎ እንዳለ  የዞኑ የወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ታሪኩ ታከለ እንዳሉት ከሆሮጉድሩ ወለጋ 11 ወረዳዎችና ከአንድ የከተማ አስተዳደር የተውጣጡ 1ሺህ 200 ስፖርተኞች በ7 የስፖርት ዓይነቶች እየተወዳደሩ ይገኛሉ፡፡

Published in ስፖርት

ጅማ ጥር 4/2010 በጅማ ከተማ የአገልግሎት ጊዜው ያለፈበት "በክለር" የተባለ መጠጥ ከማከፋፈያ ቤቶች መሰብሰቡን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ፡፡  

የባለስልጣኑ ኃላፊ አቶ አድናን ሻሚል ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት 4 ሺህ ጠርሙስ መጠጥ ሊሰበሰብ  የቻለው  ፍተሻ ከተካሄደባቸው ሦስት የቢራ ማከፋፈያ ቤቶች በሁለቱ ላይ ተከማችቶ በመገኘቱ ነው፡፡

ከማከፋፈያ ቤቶቹ የተሰበሰበው መጠጥ  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ጥር 1 ቀን 2017 የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የመጠቀሚያው ጊዜ ያለፈበት ማንኛውም ምርት በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኃላፊው አሳስበዋል፡፡

"በጅማ ከተማ የተያዘው መጠጥ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ሊኖር ስለሚችል ሕብረተሰቡ ማንኛውም የታሸጉ ምግቦችና መጠጦችን ሲጠቀም የመጠቀሚያ ጊዜው ያላለፈ መሆኑንና ትክክለኛነቱን አረጋግጦ መግዛትና መጠቀም ይኖርበታል" ብለዋል።

ሕብረተሰቡ አጠራጣሪ ምርቶች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በፍጥነት እንዲያሳውቅም አቶ አድናን አስገንዝበዋል።

የኢዜአ ጋዜጠኛ በጅማ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ ሆቴሎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው የመጠቀሚያ ጊዜ አልፎበታል የተባለው መጠጥ አሁንም ለሽያጭ እየቀረበ መሆኑን ታዝቧል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ጥር 4/2010 ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ለማዘመን እስከ ቀበሌ ድረስ የኔት ወርክ ማስፋፊያ ዝርጋታ ቢያካሂድም አሁንም የጥራት መጓደል ችግር እያጋጠመ መሆኑን ደንበኞች ተናገሩ።

ድርጅቱ በአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችና  መፍትሄው ዙሪያ ትናንት በባህርዳር ከሚገኙ ደንበኞች ጋር ተወያይቷል፡፡

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቢስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ የመጡት አቶ የሽዋስ ጥላሁን እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም የገጠሩ ህብረተሰብ የሞባይልና የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆን ማስፋፊያ ቢያካሂድም የአልግሎት ጥራት መጓደል አሁንም ችግር ሆኖ ቀጥሏል።

በቅንጅት መጓደል ሳቢያም የተዘረጉ የመሰረተ ልማት ስራዎች በየጊዜው እየተጎዱ ለአገልግሎት ጥራት መጓደል ችግር እየሆኑ ነው ያሉት ደግሞ አቶ አስሜ ብርሌ የተባሉ ደንበኛ ናቸው።

እያጋጠመ ያለውን የኢንተርኔትና መሰል አገልግሎቶች ጥራት መጓደል ለማስተካከል  ድርጅቱ ከመንገድ፣ ከመብራት፣ ከውሃና መሰል ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ሊሰራ ይገባል።

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን ባልደረባ አቶ መላኩ ጥላሁን በበኩላቸው የመረጃና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ዘላቂነት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ማዕከላቱ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ለሚያስገባቸው ዕቃዎች በቀላሉ መለዋወጫ የሚገኝላቸውን ቴክኖሎጂዎች ለይቶ ስራ ላይ ማዋል አለበት" ብለዋል።

የደንበኞችን እርካታ ለመፍጠር ከመድረኩ የተነሱ ችግሮችን ተቀብሎ በቀጣይ ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በኢትዮ ቴሌኮም የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ብሩክ አድሃና ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳመለከቱት በቂ የመለዋወጫ አቅርቦት ያላቸውን ቴክኖሎጂዎች በማስመጣት ስራ ላይ ለማዋል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡

በተለይ በገጠር ቀበሌዎች የሶስተኛው ትውልድ የተባለው ኔት ወርክ አገልግሎት መስፋፋቱ ወጣቶች በቀላሉ ባሉበት አካባቢ ሆነው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።

የተዘረጉ የፋይበር መስመሮችም በልማት ምክንያት በአንድ በኩል ቢቆረጡ አገልግሎቱ ሳይሰናከል  በሌላ በኩል እንዲሰሩ የሚያስችሉ አሰራርን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ቀጥታ ያልሆነ ሽያጭ ክፍል ኃላፊ አቶ ይመር ተፈራ የሚስተዋለውን በኃይል ምክንያት  የኔት ወርክ መቆራረጥ ችግር ለመፍታት  133 አማራጭ ጄኔሬተር የመትከል ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ይህም ከመብራት መጥፋት ጋር ተያይዞም በመደበኛ ስልክ፣ በሞባይል፣ በኢንተርኔትና ሌሎች አገልግሎቶች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ያስችላል ነው ያሉት አቶ ይመር።    

ሪጅኑ ከክልሉ መንግስትም ሆነ ከአጋር አካላት ጋር የሚያጋጥሙ የኔት ወርክ መቆራረጥ ችግሮችን ለመፍታት ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል። 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ ጥር 4/2010 በአነስተኛ ዋጋ እየቀረበላቸው ያለው አማራጭ የሽግግር የንብ ቀፎ ይበልጥ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን በትግራይ ክልል ሀውዜን ወረዳ አስተያየታቸውን ለአዜአ የሰጡ ማር አምራች አርሶ አደሮች ተናገሩ።    

የመቀሌ ግብርና ምርምር ማዕከል በበኩሉ የማር ምርትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የንብ መኖና አማራጭ የሽግግር የንብ ቆፎ ለአርሶ አደሩ እያቀረበ መሆኑን ገልጿል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን ሀውዜን ወረዳ የሰላም ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ብርሃነ ጸጋይ ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት አማራጭ የሽግግር የንብ ቆፎ በዋጋ አነስተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ  ከቦታ ወደ ቦታ በቀላሉ ለማንቀሳቀስ ስለሚቻል በአርሶአደሮች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ መጥቷል ብለዋል።

ከሸንበቆ የተሰራው አዲሱ የሽግግር ቀፎ ምርታቸውን እንዳሳደገላቸውም ነው የተናገሩት፡፡

በወረዳው የደብረብርሃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጸጋይ መለስ በበኩላቸው፣ በምርምር ማዕከሉ በተሰራው የንብ ቀፎ አጠቃቀም ላይ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ከሸንበቆ የተሰራው ቀፎ ለንቦቹ ተስማሚ ሙቀት የሚሰጥ በመሆኑ የማር ምርታቸው እያደገ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ንቦቹ ምግባቸውን ለማግኘት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በአካባቢው ብርድ ምክንያት እንደማይገደብ በ14 የንብ ቀፏቸው ባሉ ንቦች ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል።

በመቀሌ እርሻ ምርምር ማዕከል የንብ ተመራማሪ አቶ ሃፍቶም ገብረመድህን እንዳሉት፣ በትግራይ ክልል ለንብ መኖ የሚውሉ የእጽዋት አይነቶችና የሚያብቡበትን ወቅት በጥናት የመለየት ሥራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እጽዋቱን የማባዛትና ወደ አርሶአደሮች የማስፋፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም በክልሉ ያለው ነጭ ማር ይበልጥ እየታወቀ እንዲመጣና በብዛት እንዲመረት የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ሃፍቶም ገለጻ፣ ከንብ ቀፎ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል በየጊዜው የዋጋ መናር በቀዳሚነት ይጠቀሳል።

“ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል አማራጭ የሽግግር የንብ ቆፎ ተሰርቶ በዝቅተኛ ዋጋ ወደ አርሶአደሩ እየቀረበ ነው” ብለዋል።

ሌላው በማዕከሉ የንብ ተመራማሪ የሆኑት አቶ ጉዑሽ ጉዲፋይ ፣ በክልሉ “ተበብ፣ ግርቢያና ስዋ ቀርኒ” የተባሉት የእጽዋት አይነቶች ንቦች በዋነኝነት ለምግብነት ከሚጠቀሙባቸው ተክሎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህን እጽዋት በተለያዩ ዘዴዎች በማባዛት  በክልሉ ያለውን የንብ መኖ እጥረት ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አምቦ ጥር 4/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ የሚገኙ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኞች ማቋቋሚያ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ ፡፡

የወረዳው የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሞአ ዳመሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ድጋፉ የተደረገው ህብረተሰቡ  በጉዳዩ ዙሪያ ከተወያየ በኋላ ነው።

በእዚህም በአንዳንድ የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብ 270 ሺህ ብር እንዲሁም  ከ80 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።

ድጋፍ ካደረጉ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካካል የጊንጪ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ቢየሺ ዲሪብሳ በሰጡት አስተያየት "በወሰን ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች አቅሜ የፈቀደውን ድጋፍ በማድረጌ ደስተኛ ነኝ " ብለዋል።

" ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ተፈናቃዮቹ እስኪቋቋሙ ድረስ የቻልኩትን ድጋፍ አደርጋለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ አበራ ሳሙኤል ናቸው ።

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ ጥር 4/2010 በነቀምቴ ከተማ የለጋ ማርጋ ብረታ ብረት መለዋወጫና ማምረቻ አክሲዮን ማህበር አባላት 2 ሚሊዮን ሰባት መቶ ሺህ ብር  ብድር  ወስደው ወደ ስራ ቢገቡም የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ ገለጹ፡፡

የማህበሩ ተወካይ ወጣት አዱኛ ጆቴ  ወደ ስራው ከገቡ ከአንድ ዓመት በላይ እንደሆናቸው ገልፆ 72 ዓይነት የተለያዩ ማሽኖች ገዝተው  በማምረት ስራ ቢሰማሩም የገበያ ትስስር ስላልተፈጠረላቸው ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ተናግሯል፡፡

ለገበያው መጥፋት ምክንያት ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበት አመቺ ቦታ አለማግኘታቸው ፣ አንዳንድ መንግስታዊ ተቋማት የራሳቸው የሆነ የብረታ ብረት ወርክሾፕ ማቋቋማቸውና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ቃል የገቡ ተቋማትም ሆነው አለመገኘታቸው ነው፡፡

የማህበሩ አባል ወጣት ተክሉ እሸቱ እንደገለጸው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ የማህበሩ አንድ ተስፋ የነበረ ቢሆንም የራሱ የሆነ የብረታብረት መለዋወጫና ማምረቻ ማዕከል በማቋቋሙ ገበያው እንዲጠብ አድርጎታል ።

ከፍንጫአና ከአርጆ ስኳር ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር ለመፍጠር የተደረገው ስምምነትም እስከ አሁን  የተፈጻሚ  እንዳልሆነ  ወጣት ተክሉ ተናግሯል ።

" መንግስት አደራጅቶና ተገቢውን የማንቀሳቀሻ የብድር አገልግሎት ሰጥቶ ወደ ስራ እንዳስገባን ሁሉ ምርታማነታችንን ጠብቀን ራሳችንን ፣ ቤተሰባችንንና ሀገራችንን እንድንጠቀም ገበያን በማመቻቸት ሒደት ሊያግዘን ይገባል"ብሏል።

የነቀምቴ ከተማ ምክትል ከንቲባ  አቶ አለማየሁ ደሬሳ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በከተማው በተለያዩ የስራ መስኮች ለመሰማራት የተደራጁ ወጣቶች በተደረገላቸው የገበያ ትስስር አብዛኛዎቹ ውጤታማ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በለጋ ማርጋ ብረታብረት መለዋወጫ እና ማምረቻ የተሰማሩ ወጣቶች የገበያ ትስስር ቢፈጠርላቸውም ስምምነቱ ተግባራዊ ባለመሆኑ ተጠቃሚዎች አልሆኑም ።

" ችግሩን ለመፍታት   በአካባቢው ከተሞች፣በስኳር ፋብሪካዎችና በአጎራባች ዞኖች ጭምር ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁና የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ  እየተሰራ ነው "ብለዋል ።

አቶ አለማየሁ  እንዳመለከቱት በተያዘው  በጀት ዓመት ከ6 ሺህ  ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን  ሁለት ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች የመስሪያ ቦታና ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 4/2010 ወጣቶች በተፋሰስ ልማት እያሳዩት ያለውን ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባዘጋጀው ሳምንታዊ የአቋም መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ ባደረገው ርብርብ የግብርና ምርታማነት እንዲጨምር እንዳስቻለ ያመለከተው ጽህፈት ቤቱ፤  ይህም የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ እንዲሻሻል እገዛ ማድረጉን ጠቁሟል።

የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ለመስኖ  ልማት መጎልበት አዎንታዊ ሚና ማበርከቱን በመግለጫው ተመላክቷል።

ከጥር 1 ቀን 2010 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ ከ10 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኙም ተገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ወጣቶች በአገር አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ስራ ላይ አፍላ ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ እያወጡ መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህን ቁርጠኝነት በሌሎች መስኮችም አጠናክረው  እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል።

ወጣቶችን ጨምሮ መላው የገጠሩ ማሀበረሰብ እያካሄደው ላለው የተፋሰስ ልማት ስራ ጽህፈት ቤቱ አድናቆቱን ገልጿል።

የመግለጫው ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል:-

 በኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም

መግለጫ- ጥር 4/2010 ዓ.ም.

ወጣቶቻችን በተፋሰስ ልማቱ ላይ እያሳዩት ያለው ተሳትፎ በሁሉም ዘርፎች ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!

አገራችን ድርቅን የመቋቋም ጠንካራ አቅም ማጎልበት የቻለችው፣ መንግሥት የነደፈውን ፖሊሲና ስትራቴጂ ተከትሎ መላው ህዝባችን ባደረገው ያላሰለሰ ርብርብ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ለማሳደግ በመቻላችን መሆኑ ይታወቃል። በግብርና ምርታችን ላይ በየዓመቱ እየተመዘገበ ያለው ዕድገት በምግብ ራሳችንን ከማስቻሉም በላይ የአርሶ አደሩን እና የአርብቶ አደሩን ህይወት በተጨባጭ መለወጥም ያስቻለ ነው።

የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ካሉት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መካከል፣ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ተጠቃሽ ነው። ባለፉት ዓመታት ባካሄድነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራዎች ክፉኛ ተራቁተው የነበሩ አካባቢዎች ተመልሰው እንዲያገግሙ ማድረግ ችለናል። ይልቁንም ዘርፈ ብዙ ጥቅም ባላቸው ተክሎች እንዲሸፈኑ በማድረግም የአርሶ አደሩን የምግብ ፍላጎት ከመሟላት ባሻገር ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኝ አስችሏል። አነስተኛ የአርሶ አደር መስኖዎች እንዲበራከቱ በማድረግም በመስኖ የሚለማውን መሬት በየዓመቱ በእጅጉ እንዲሰፋ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ  የድርቅ ተጋላጭነታችንን መቀነስ ተችሏል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ውጤቶች ሊመጡ የቻሉት በገጠር በሚኖረው ሕዝባችን የላቀ ተሳትፎ ነው።

በተመሳሳይ ካለፈው ጥር 1 ቀን 2010 ጀምሮ ለአንድ ወር ያህል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ባለው  የአፈርና የውሃ ጥበቃ ሥራ ከ10 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ከፊል አርብቶ አደሮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ።  በአንድ ጊዜ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ በጋራ ወጥቶ የአገራችንን የአየር ንብረት መጠበቅ፣ የግብርና ምርትና ምርታማነታችንን ማሳደግ እና ግብርናውን ማዘመን በሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሳተፉ ህዝባችን ከድህነት ለመላቀቅ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያረጋግጥ ነው። በልማቱ ላይ እየተሳተፈ ካለው ህዝባችን ብዙውን ቁጥር የሚይዘው በገጠር የሚገኘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል መሆኑ ደግሞ ሌላው ሊሰመርበት የሚገባ ሃቅ ነው።

ወጣቶቻችን በዚህ መሰሉ ግዙፍ የልማት ተግባር ላይ በንቃት መሳተፋቸው የአገራችንን ሁለንተናዊ ዕድገት ከማፋጠን አኳያ የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው ቀደም ሲል የተመዘገበው ውጤት ያረጋግጥልናል። በመሆኑም ያለፉ ዓመታትን ተሞክሮዎች በመቀመር፣ በቂ ዝግጅት ተደርጎበት ወደ ስራ የተገባበት የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት በጥራት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚካሄድ ሲሆን በዚህም ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል።

እንደሚታወቀው በአገራችን እየተካሄደ ያለው የተፋሰስ ልማት የገጠሩን ህዝብ፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ዘመናዊና የላቀ ዋጋ ባላቸው የግብርና ሥራዎች ላይ በማሠማራት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥን ታሳቢ ያደረገ ነው። ካለፍንበት ሂደት እንደምንረዳው በመቶ ሺህዎች ለሚቆጠሩ ወጣት ሞዴል አርሶና አርብቶ አደሮች መፈጠር፣ ለቀጣዩ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ ለሆነው ካፒታል መፈጠር በተፋሰስ ልማት  የተከናወኑ ሥራዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

በመሆኑም የገጠሩ ህዝባችን እያካሄደው ላለው የተፋሰስ ልማት መንግሥት አድናቆቱን ይገልጻል። በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል አፍላ ጉልበቱን እያፈሰሰበት ያለው ይህ የልማት ሥራ ነገ ተነገ ወዲያ የእሱን ህይወት በመለወጥ ረገድ ከሚኖረው ፋይዳ በተጨማሪ አገራችንን ከተፈጥሮ አየር መዛባት የሚታደግ እና ዘላቂ ልማቷን የሚያረጋግጥ የአርበኝነት ተግባር በመሆኑ ሊኮራበት ይገባል። በዚህ አጋጣሚ ለተፋሰስ ልማቱ ውጤታማነት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም መንግስት ጥሪውን ያቀርባል።

የአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊሳካ የሚችለው መላው ህዝባችን በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በተፋሰስ ልማቱ ላይ እያሳየው ያለው ቁርጠኝነት በሌሎች መስኮችም ተጠናክሮ ሲቀጥል መሆኑን መረዳት ይገባል። በመሆኑም፣ በከተማም ይሁን በገጠር፣ በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ፣ በትምህርትም ላይ ይሁን በሥራ ላይ የምትገኙ ወጣቶቻችን ሁሉ እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የተፋሰስ ልማት በመሳሰሉት ታላላቅ ፕሮጀክቶቻችን ላይ ወጣቶቻችን እያሳዩት ያለውን አርዓያነት በመከተል በሁሉም ዘርፍ የተሻለች አገር ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አገራዊ ሃላፊነታችሁን እንድትወጡ መንግስት ጥሪውን ያቀርባል። 

Published in ፖለቲካ

መቱ/ፍቼ ጥር 4/2010 በኢሉአባቦር ዞን የቡና ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደግ የሚችሉ ከ146 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በአርሶአደሩና በመንግስት ጣቢያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን የዞኑ ቡና፣ ሻይ እና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ17 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት በመሳተፍ የመጀመሪያ ምርት ማግኘት መጀመራቸውም ተመልክቷል።

የባለስልጣኑ  ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ አዲሱ ለኢዜአ እንደገለጹት የቡና ችግኞቹ እየተዘጋጁ ያሉት በዞኑ 13 ወረዳችዎች ባሉ 9 ሺህ 320 የአርሶአደርና 38  የመንግስት ችግኝ ጣቢያዎች ላይ ነው፡፡

አዳዲስ ዝርያዎቹ ከጅማ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙ ሲሆን በአግባቡ ከተያዙ በሄክታር ከ12 እስከ 20 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ናቸው፡፡

በቡና ችግኝ ዝግጅቱ ከ26 ሺህ 500 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንድ ሺህ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

እየተዘጋጁ ያሉት የቡና ችግኞች በመጪው ክረምት በ21 ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የሚተከሉ ናቸው።

የግብርና ባለሙያዎች ዘሩን ከመዝራት ጀምሮ በችግኝ አያያዝና እንክብካቤ ላይ ለአርሶአደሩ በቅርበት ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም አቶ ከተማ አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ  በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከ17 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት በመሳተፍ የመጀመሪያ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን አአስታውቋል።

የባለስልጣኑ የሰሜን ሸዋ ዞን ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ ጅማ እንዳሉት በዞኑ ሰባት ወረዳዎች በሚገኙ 113 ቀበሌዎች የሚኖሩት አርሶ አደሮች ምርቱን ያገኙት ባለፉት ሦስት ዓመታት በሙከራ ደረጃ ካለሙት የቡና ችግኝ ነው።

በየዓመቱ የሚቀርብላቸውን ሁለት መቶ ሺህ የቡና ችግኞች በመጠቀም የቡና ልማቱን በማስፋፋት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ዘንድሮም  በዞኑ ችግኝ ጣቢያዎች የተዘጋጁ 700 ሺህ የቡና ችግኞች ለአርሶ አደሮች እንደሚሰራጩ አመልክተዋል ።

በሰሜን ሸዋ ዞን የቡና እርሻን በስፋት ለማካሄድ በባለሙያዎች ጥናትና ምርምር እየተካሔደ ሲሆን እስካሁንም ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ቡና ተመርቶ ለቤት ውስጥና ለአካባቢ ፍጆታ መዋሉ ተመልክቷል ።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን