አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Thursday, 11 January 2018
Published in ቪዲዮ

ጊምቢ ጥር 3/2010 በምዕራብ ወለጋ ዞን ባለፉት ስድስት ወራት ከ27 ሺህ  ባላይ እናቶች በጤና ተቋም መውለዳቸውን የምዕራብ ወለጋ ዞን ጤና አጠባበቅ ፅህፈት ቤት አስታወቀ ።

 የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ከድር ሙዘይን ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ስድስት ወራት ከ32 ሺህ በላይ እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ ታቅዶ 27 ሺህ 600 እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል።

 ክንውኑ ከዕቅዱ ጋር ሲታይ 73 በመቶ፤ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ በ10 በመቶ ያነሰ መሆኑን አቶ ከድር አመልክተዋል።

 "አምቡላንሶች ጊዜ ጠብቆ ብቃታቸው እንዲፈተሽ አለመደረጉና ሲበላሹ ወዲያው ጥገና አለማድረግ እናቶችን በወሊድ ወቅት ወደ ጤና ተቋም የማጓጓዝ አገልግሎቱን በሚፈለገው መጠን እንዳይሆን አድርጓል" ብለዋል ።

 ችግሩ በበጀት እጥረት የተፈጠረ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው ለመፍትሄው ከሚመከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

 በጤና ተቋም ማቆያ ቦታ ለወላድ እናቶች ይደረግ የነበረው እንክብካቤ በአብዛኛው ጤና ጣቢያ ላይ መቋረጡ ሌላው በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ማነስ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

 ለእዚህም ጽህፈት ቤቱ ሕብረተሰቡን በማስተባበርና የነበረው አሰራር በመመለስ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር ለመጨመር አቅዶ እየሰራመሆኑን ጠቁመዋል።

 አቶ ከድር እንዳሉት፣ በሀገሪቱ በተያዘው ስትራቴጂክ ዕቅዱ ከ100 ሺህ ነፍሰጡር እናቶች መካከል በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶችን ቁጥር ከ421 በታች ለማድረስ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው።

 "ለእዚህም እናቶች  ማርገዛቸውን ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ ያለማቋረጥ የቅድመ ወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙና በጤና ተቋም እንዲወልዱ በትኩረት ይሰራል" ብለዋል ።

 በዞኑ የቂልጡ ካራ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ በሊና በወረዳው ባለፉት ስድስት ወራት 1 ሺህ 222 እናቶች በጤና ተቋም እንዲወልዱ መታቀዱንና 94 በመቶ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

 በቂልጡ ካራ ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ ልጃቸውን በሰላም የተገላገሉት ወይዘሮ አረጋሽ ተሾመ በበኩላቸው የቅድመ ወሊድ ክትትል ማድረጋቸውና የጤና ባለሙያን ምክርን ተግባራዊ በማድረጋቸው ጤናማ ልጅ ለመውለድ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

 ከዓመታት በፊት በአካባቢያቸው አገልግሎቱን በማጣት የተጎዱ እናቶችና ሕፃናት እንደነበሩ የገለጹት ደግሞ ሌላዋ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ወይዘሮ ዘውዴ ሂርጳ ናቸው።

 በዞኑ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ወረዳ ያሉ ጤና ጣቢያዎች፣ በአራት የመንግስትና ሁለት የግል ሆስፒታሎች የማዋለድ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ፅህፈት ቤት መረጃ  ያመላክታል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጅማ  ጥር 3/2010 ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር የምታከናውናቸው የልማት ስራዎች አጠናክራ እንደምትቀጥል የጃፓን አምባሳደር ሲንቺ ሳይዳ ገለጹ ፡፡

አምባሳደሩ ዛሬ በጃፓን አለም አቀፍ ትብብር (ጃይካ) ድጋፍ በጅማ ዞን የሚሰሩ የቡና እንዲሁም በመስኖ የሚለሙ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማቶችን  ጎብኝተዋል

በዞኑ በሰቃ ጨቆርሳ ወረዳ ኢትዮ ሸድ በመስኖ የሚያለማውን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሸቤ ሰንቦ የሚካሔደውን የጫካ ቡና ልማትን  አምባሳደሩ ከጎበኟቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

አምባሳደር ሺንቺ ሳይዳ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት የጅማ ዞን ለምለምና ለየትኛውም አይነት የግብርና ስራ ምቹ በመሆኑ የአካባቢው አርሶአደሮች የተፈጥሮ ስጦታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ኑሯቸው መለወጥ ይገባቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን የመካከለኛ ገቢ ባለቤት ለማድረግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የጃፓን መንግስት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል ።

"ለወደፊቱም የጅማ ዞን አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን "ብለዋል፡፡

የጅማ ዞን የሚመረተው የተፈጥሮ ቡና በጃፓን የሚወደድና ልዩ  ጣዕም ያለው በመሆኑ በሀገራቸው የገበያ አድማሱን ለማስፋት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ለአርሶአደሩ ሰፊ  የገበያ አማራጭ ከመሆን ባለፈ የቡና ጥራትን በማስጠበቅ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደሚደረግም አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል መስኖ ልማት ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ  አቶ ሰይፈዲን ማሃዲ  በበኩላቸው የጃፓን መንግስት የኢትዮጵያን  የመስኖ ልማት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ልማቱን ለማሳደግ በዕውቅትና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ ጃፓን የምትሰጠው ድጋፍ  ህብረተሰቡን  ከድህነት ለመውጣት የሚያደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ጠቅሰዋል፡፡

በሸቤ ወረዳ 12 ቀበሌዎች መካከል የቡና ጣዕም ውድድር የተካሄደ ሲሆን አሸናፊዎቹም በጃፓንና በኢትዮጵያ ባለሙያዎች ተመርጠዋል፡፡

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ የወጡት በከዱኬ ፣ ወንተሎና ሃሪሬ ቀበሌዎች በቀጥታ ምርታቸውን ወደ ጃፓን የሚልኩበት እድል እንደሚፈጠርላቸው በስነ ስርዓቱ ላይ  ተገልጻል፡፡

አንደኛ የወጣው የከዱኬ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ጀበል አባሲመል በሰጡት አስተያየት "ለቡና ጥራት የሰጠነው ትኩረት አሸናፊ አድርጎናል" ብለዋል፡፡

በውድድሩ ላይ ተሳትፈው  ያልተሳካላቸው የሰንቦ ቀበሌ ነዋሪው አቶ አባዋሪ አባጀበል በበኩላቸው ቀበሌያቸው  ባያሸንፍም ውድድሩ ከቡና ገበያ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወቅት እየደረሰ መምጣቱን እንደሚጠቁምና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን  ተናግረዋል ፡፡

" በአሁኑ ወቅት የተለያዩ  ቡና ገዥዎች  ከአሜሪካ፣ ከጣሊያንና ከጃፓን  ወደ አካባቢችን  እየመጡ ስለሆነ ከእኛ የሚጠበቀው ጥራት ያለው ቡና ማምረት ብቻ ነው "ብለዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ድሬደዋ ጥር 3/2010 በድሬዳዋ አስተዳደር ህዝቡ ያነሳቸውን  የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለመፍታት ጠንክረው እንደሚሰሩ በአስተዳደሩ አስተያየታቸውን የሰጡ  የመንግስት ሰራተኞች ተናገሩ፡፡

ባለፈው ታህሳስ ወር በገጠርና በከተማ ለሚገኙ 5ሺህ የሚጠጉ የመንግስት ሠራተኞች በመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ዙሪያ ሥር -ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

ይህንን ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሠራተኞች በስልጠናው ያገኙትን  ግንዛቤ በመተግበር ህብረተሰቡ  ያነሳቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች  ለመፍታት እንደሚተጉ ገልጸዋል፡፡

በአስተዳደሩ  የንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሠራተኛ አቶ አብዲ መሐመድአሚን  እንዳሉት ህዝብን ለብሶት የዳረገው ኃላፊነታችን በአግባቡ አለመወጣት አንዱ መንስኤ ነው፡፡

" ህዝቡ ሲደሰት የኛም ደስታ ይሆናል፤ ተገልጋይ በየመድረኩ ላቀረበው የአገልግሎት ጥያቄ ቅሬታ ለመፍታት ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል፡፡

ተገልጋዩ በተደጋጋሚ  የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት ሰሞኑን የተሰጣቸው  የለውጥ መሣሪያዎች ስልጠና የማስፈጸም አቅማቸውን እንደሚያጠናክረው ገልጸዋል፡፡

የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መንስኤዎች ከክህሎት፣ ከዕውቀትና ከአመለካከት የሚመነጩ በመሆናቸው ለነዚህ የማያዳግም መፍትሄ በማስቀመጥ ለተገልጋዩ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የተናገሩት ደግሞ በመሬት ልማትና ማነጅመንት ቢሮ የዘርፉ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መላኩ ናቸው፡፡

አቶ አሰፋ አፈታ የተባሉ ሠራተኛ በበኩላቸው በስልጠናው ያገኙትን እውቀት በተናጠልና በተቀናጀ መንገድ በመተግበር ፈጣን አገልግሎት ለተግልጋይ ለመስጠት የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን ዘንድሮ በተጠናና በተደራጀ መንገድ የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም ከአመራር እስከ ታችኛው ፈጻሚ ሠራተኛ በየተቋሙ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችላቸው ስልጠና በመስጠት ለውጥ ለማምጣት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የፌደራል የሰነዶች ማረጋገጫ ጽህፈት ቤት ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ተገልጋዩን ለማርካት እያሳዩ ያሉት  ቁርጠኝነት ሌሎችም በመልካም  ተሞክሮነት እንዲውስዱት ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

የተሻለ ሥራ እንዲፈጸም  ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ነው ከንቲባ ኢብራሂም የገለጹት፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ድሬዳዋ ጥር 3/2010 ሕብረተሰቡን ከጎን በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን ኢጋድ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢጋድ የሰላምና የፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ተናገሩ፡፡

ሶማሊያን ከአልሻባብ ሽብርና ውድመት ነጻ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሀገሪቱ የጎሳ መሪዎችና የሃይማኖት አባቶች ያላቸው ሚና ወሳኝ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አልሻባብ የሚያራምደውን ፕሮፓጋንዳ ለመመከትና የሶማሊያን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የሚያግዝ የሦስት ቀናት ስልጠና በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።

ከትናንት ጀምሮ እየተሰጠ ባለው ስልጠና ከሶማሊያ የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎችና ተቀባይነት ያላቸው ሴቶችና ግለሰቦች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢጋድ የሰላምና የፀጥታ ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው ስልጠና የአልሻባብን የተሳሳተ አካሄድና ፕሮፓጋንዳ የመመከት ዓላማ አለው።

በስልጠናው ሽብርተኞች ያነገቡትን የተሳሳተ አስተምህሮና ሃይማኖትን የተንተራሰ የእስልምና ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲረዱ ከማድረግ ባለፈ በቀጣይ ለሶማሊያ ሰላም የድርሻቸውን እንዲወጡ የማገዝ ግብ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ስለአልሻባብ ማንነት ተገቢው እውቀት እንዲያገኙ መደረጉ የአልሻባብን የሽብር ተግባርና የመስፋፋት እንቅስቃሴ ለመከላከል በሚደረገው ጥራት ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ሲባል ስልጠናው መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።

ኢጋድ ሕብረተሰቡን ከጎን በማድረግ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ፀጥታን ለማስፈን የሚያከናውናቸውን ተግባራት በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮማንደር አበበ  ገልጸዋል።

ሰልጣኞች የቀሰሙትን ትምህርት በቀጣይ ለማህበረሰቡ በማስተላለፍ የተሻለች ሶማሊያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ በአሁኑ ወቅት የኢጋድ አባል ሀገራት ሲሆኑ ኤርትራ ራሷን ከአባል ሀገርነት በቅርቡ ማግለሏ የሚታወስ ነው፡፡

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጥር 3/2010 አገር አቀፍ ተደራዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በጸረ ሽብር አዋጅ ባሉ አንቀፆች ላይ በዝርዝር ለመደራደር በቀጠሮ ተለያዩ።

ፓርቲዎቹ አዋጅ ቁጥር 652/2001ን በሚመለከት ከዚህ በፊት ባደረጉት ድርድር እንዲሻሻሉ፣ እንዲወጡና እንዲጨመሩ የሚፈልጓቸውን አንቀፆች ማቅረባቸው ይታወሳል።

ፓርቲዎቹ አዋጁን በሚመለከት ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ  የተደራደሩ ሲሆን፤ እንዲሻሻሉ፣ እንዲወጡና እንዲጨመሩ ያቀረቧቸው አንቀፆች ላይ  አንድ በአንድ ሳይደራደሩ ጥቅል ሃሳቦችን ሲያንፀባርቁ ውለዋል።

"አዋጁ ከአገሪቷ ህገ - መንግስት ጋር ይጣረሳል” የሚለው ሃሳብ በፓርቲዎቹ ከተነሱ ጥቅል ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በበኩሉ "የፀረ ሽብር አዋጁ በጥቅል ችግር አለበት ከማለት ይልቅ ችግር አለባቸው ተብለው በቀረቡ አንቀፆች ላይ በዝርዝር እንደራደር”  የሚል ሃሳብ በተደጋጋሚ  አንስቷል።

ይሁን እንጂ በዛሬ ውሎ ስለ አዋጁ የተነሱ ጥቅል ጉዳዮች ሰፊ ጊዜ ወስደዋል።

ኢህአዴግ በጊዜ እጥረት ምክንያት በቀረቡ ሃሳቦች ላይ መልስ ባለመስጠቱ፤ በቀጣይ የድርድር  ጊዜ ለጥያቄዎቹ ማብራሪያ ይዞ እንደሚቀርብ  አስታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተደራዳሪ ፓርቲዎች ስለወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ኢህአዴግ ጥያቄውን መቀበሉን ገልጿል።

ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም በታህሳስ 10 እና 13 ቀን 2010 ዓ.ም ያደረጓቸው ድርድሮችን ቃለ ጉባኤም አፅድቀዋል።

በአዋጁ ላይ ተጨማሪ ድርድር ለማካሄድ ለጥር 9 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

Published in ፖለቲካ

ማይጨው ጥር 3/2010 የትግራይ ደቡባዊ ዞን ማዕከል ለሆነው የማይጫው ከተማ ለአስር ዓመታት የሚያገለግል አዲስ የእድገት ማስተር ፕላን ዝግጅት ተጀመረ፡፡

 የከተማው አስተዳደር  ከንቲባ  ተስፋዬ ኪዳኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ባለፈው ወር የተጀመረው   የማስተር ፕላን  ዝግጅት የክልሉ  መንግስት በመደበው ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ የሚካሄድ ነው።

 ማዘጋጀት ያስፈለገው ላለፉት አስር ዓመታት  ያገለገለው ነባሩ ማስተር ፕላን የከተማውን ግማሽ አካል በአረንጓዴ ስፍራነት በመከለል ለልማት ስራ ማነቆ ሆኖ በመቆየቱ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በአረንጓዴ ክልል ውስጥ  የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በመሬት ይዞታቸው ላይ አንዳችም የግንባታ ስራ እንዲያከናውኑ የሚፈቅድ ባለመሆኑ ቅሬታ እያስነሳ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኗል።

 እንደ መንገድና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮችን ለመዘርጋት የሚከለክል ጭምር ስለነበር የከተማውን  ልማት ማፋጠን  አልተቻለም።

 ከንቲባው  እንደ  ገለጹት    አዲሱን   የእድገት  ማስተር ፕላን   የማህበራዊ  አገልግሎቶችን በማስፋፋት ነዋሪዎችን  ተጠቃሚ  ማድረግ  ያስችላል።

 እንዲሁም   ካሁን በፊት ያልነበሩትን  የማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ የሆቴልና ቱሪዝም ኢንቨስትመንት ማከናወኛ ቦታዎች፤የሊዝ መሬት ማስፋፊያ፣ የታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን በግልፅ ያስቀመጠም ነው።

 የግል ይዞታን የመገንባትና የማስፋፋት ጥያቄ ከመመለስ ባለፈ የመንግስት ሃብትን በአግባቡ በመምራት  ለከተማው እድገትና ልማት እንዲውል እድል የሚፈጥር ነው ተብለዋል።

 የማስተር ፕላኑ ዝግጅት ከስምንት ወራት በኋላ ተጠናቆ  ወደ ተግባር እንደሚሸጋገርም ከንቲባው  አመልክተዋል።

 በማይጨው ማዘጋጃ ቤት የመሬት ልማት ባለሙያ አቶ ንጉስ መሃሪ በበኩላቸው ካሁን በፊት የነበረው የከተማው ማስተር ፕላን  ከ43 በመቶ  በላይ የሚሆነው የመሬት ይዞታ በአረንጓዴ  ቦታነት በመከልል ከተማውን ለማልማት  እንቅፋት መሆኑን  ተናግረዋል።

 እየተዘጋጀ ያለው ማስተር ፕላን አዲስ መንገድ  ለመክፈትና ተጨማሪ የሊዝ መሬት እንዲኖር የሚፈቅድ በመሆኑ የማህበራዊ አገልግሎቶችን  በማስፋፋት ነዋሪውን  ተጠቃሚ  እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።

 ከከተማው  ነዋሪዎች መካከል አቶ ንጉሴ ግዴይ በሰጡት አስተያየት መኖሪያ ቤታቸውን አሻሽለው ለመስራትና መንደራቸው በመንገድ  ለማገናኘት አቅዶት የቆየው የአርንጓዴ ክልል አዲሱ ፕላን ሲጠናቀቅ መፍትሄ ያስገኛል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 3/2010 ኢትዮጵያ ለ2020 የቻን ውድድር እያደረገች ያለውን ዝግጅት ሊገመገም መሆኑን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) አስታወቀ

በ2020 የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) አስተናጋጇ ኢትዮጵያ ለውድድሩ እያደረገች ያለውን ዝግጅት የሚገመግም ተቆጣጣሪ ቡድን በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚልክ ካፍ ገልጿል

በካፍ ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ ሊቀመንበርነት የሚመራው የኮንፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት በሞሮኮ ካዛብላንካ ከተማ ባደረገው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች አስተላልፏል።

ኢትዮጵያ ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄድውን ውድድር እንድታዘጋጅ በካፍ ከተመረጠች ሁለት ዓመት ሆኗታል 

በዚህ የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አገሪቷ እያደረገች ያለችውን ቅድመ ዝግጅት የሚመለከት የካፍ ተቆጣጣሪ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ምልከታ እንዲያደርግ ተወስኗል

ቡድኑ ሃገሪቱ ውስጥ ያሉት ስታዲየሞች ጥራት እና ለውድድሩ በግዜው የመድረስ እድላቸውን የሚፈትሽበት የመጀመሪያው ስራ ይሆናል፡ 

ከስታዲየሞች በሻገር የትራንስፖርት፣ የሆቴል አቅርቦትም ከሚፈተሹ ሌሎችን አንኳር ጉዳዮች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡

የካፍ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ትናንት ባደረገው ስብሰባ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በሚያስተናግዳቸው ውድድሮች የሚያጫውቱ ዳኞች ጉዳት ቢደርስባቸው የሚከፈለውን የክፍያ ካሳ እንደሚከፍል በካዛብላንካው ስብሰባ አስታውቋል

የተጨዋቾችን ብቃት የሚለካና የሚቆጣጣር "ፊልድ ዊዝ" የተባለ መሳሪያ ለካፍ አባል አገራት በድጋፍ መልክ እንደሚሰጥም በስብሰባው ኮንፌደሬሽኑ አስታውቋል።

የኮንፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እና ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የውድድር ወቅት ላይም ለውጥ አድርጓል

ውድድሩ በ2010 ዓ.ም መጋቢት ወር ጀምሮ ህዳር ወር 2011 ዓ. ም የሚያበቃ ሲሆን የቀጣዩ አመት ውድድር ከታህሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 2011 ዓ.ም እንደሚዘልቅ ካፍ ወስኗል 

እንዲሁም የ2012 ዓ.ም ውድድሮች መስከረም ላይ ተጀምሮ እስከ ግንቦት 2012 ዓ.ም ድረስ የሚቆዩ ሲሆን ይህም ካፍ የውድድሮቹን ወቅቶች ለመቀየር ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው ነው።

 

 

---END---

Published in ስፖርት
Thursday, 11 January 2018 21:33

“የደኃ ፈተና”

                  ነፃነት አብርሃም (ኢዜአ)

ሕፃናት ሲቦርቁ፣ ሲጫወቱና ሲደሰቱ ማየት ማን ይጠላል? ከጎረቤት ልጆች ጋር በሰፈር ሲሯሯጡ መመልከት፤ በንጹህ አንደበታቸው ሲናገሩ መስማት-ማንም! ሐሴቱ ለወላጅ ብቻ ሳይሆን ለመላው ተመልካች ነው። የጨዋታቸው ዑደት እንደየ እድሜያችው ይለያያል። ከፍ ሲሉ ኳስና መሰል ጨዋታቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር ይጫወታሉ። በዚህ ደስታ በሰጡን የልጆች ጨዋታዎች መካከል የተደበቁ፤ ያላወቅናቸው ጥቃቅን ነገሮች በህይወታችን ላይ ሳንካ እንደሚፈጥሩ ግን ልብ ላንል እንችላለን።

መቼም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዑደት ከተፈጥሮ ጋር ይላተማሉ፤ በዚህ መስተጋብርም አዳዲስ ኩነቶችን ያስተናግዳሉ። ደስታ፣ ሐዘን፣ በሽታ… ወ.ዘ.ተ። በሥነ-ሕይወት ሳይንስ የሰው ልጅ ጤናው ሊታወክ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች የትየለሌ ናቸው። ለሕልፈተ ሕይወቱም መንስኤ የሚሆኑ ያልተጠበቁ አጋጣሚዎች ይገጥሙታል። አጋጣሚዎቹ በጤና ላይ ዕክል ፈጥረው በህክምና ሊፈወሱ ወይም ሕይወት ሊቀጥፉ ይችላሉ።

ወደ ቁምነገሬ ልግባ! ወደ ሰፈራችን ልጅ! ታዳጊው እንደ ልጅነቱ መቦረቁን፣ መደሰቱን፣ መጫወቱን እንጂ ጉዳቱን ማንም አላስተዋለም ነበር። የ14 ወይም 15 ዓመት ገደማ የሚገመተው ታዳጊ በአንድ ወቅት ከእኩዮቹ ጋር በሰፈር ውስጥ እግር ኳስ ይጫወታል፤ በመሃሉም ድንገት ወድቆ እግሩ ላይ ጉዳት ይደርሳል። ወላጆቹና ጓደኞቹ ግን ጉዳቱን አላወቁም። ሲውል ሲያድር ጉዳቱ እየባሰ፣ ቁስሉም እያመረቀዘ እግሩ ማበጥ ይጀምራል። ወላጆቹም ችግሩን አውቀው ወደ ሕክምና ይዘውት ሄዱ። እንዳሰቡት ግን ቀላል ሕመም አልነበረም፤ የቁስሉ ኢንፌክሽን በጊዜ ብዛት ወደ ካንሰርነት መቀየሩን ተረዱ። በአፋጣኝ ውጭ ተልኮ እንዲታከም ተነገራቸው። ግን እንዴት? የኑሮ አቅማቸው አይፈቅድም። አገር ወስጥ አይፈወስ ነገር፤ ውጭ ወስዶ ለማሳከም የድኅነት መዘዝ ሆነና ሲቦርቅ፤ ሲደሰትና ሲጫወት ደጅ የተመለከቱት ሕፃን እጃቸው ላይ አለፈ። የደሀ ፈተና!

ሌላም የሰፈራችን ልጅ በሰፈር በተፈጠረ ግጭት እጁን በዱላ ይመታል፤ ነገር ግን በአፋጣኝ ሕክምና አላገኘም። በተመሳሳይ የዚህ ልጅ ጉዳት ወደ ካንሰር ተቀየረ። "በተመሳሳይ ችግርም ሕይወቱ በከንቱ ማለፉን አስታውሳለሁ።" በእነዚህ ሁለቱ ምሳሌዎች የካንሰር በሽታን ምንነት ከተመለከትን በየቤቱ ምን ያህል ገጠመኞች ይኖራሉ? በዓለማችንስ የምን ያህሉ የሰው ልጅ የመኖር ተስፋ መንምኖ፣ ጨልሞ ቀርቷል? የምን ያህሉ ሕይወትስ ብላሽ ሆኗል?

በሕይወት ውስጥ የካንሰር በሽታን የሚያስከትለውን ክፉኛ ቀውስ በቀላሉ መግለጽ ከባድ ነው። ቀዳሚው የሰው ልጅ ገዳይ በሽታ ነው። ለነገሩ ካንሰር ሲባል የምን ያህሎቻችን ውስጠት ነው የሚረበሸው?

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ካንሰር በሰውነታችን ውስጥ "ያለ ምንም ገደብና ቁጥጥር ይባዛል፤ ሌሎች ጤነኛ የሆኑ ሴሎችን በመውረር መደበኛ ሥራቸውን ያስተጉላል፤ ከዛም በሽታው ይከሰታል" ነው። የበሽታው ስርጭት በአልትራሳውንድ፣ በሲቲ ስካን፣ በኤም አር አይ፣ በኤክስሬይና በቦን ስካን የምርመራ ዘዴዎች ማወቅ ይቻላል ይላሉ። ቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምና፣ "ኬሞቴራፒ"፣ "የሆርሞን ቴራፒና"፣ "ባዮሎጂካል ቴራፒ" ደግሞ በዋናነት ለበሽታው የሚሰጡ ህከምናዎች ናቸው። ትንባሆ፣ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማነስ፣ በሄፓታይተስ ቢ እና ሲ መጠቃት፣ የአካባቢያዊ ብክለትና መሰል ችግሮች ለበሽታው መከሰት እንደ ዋነኛ መንስኤ ይወሰዳሉ።

ከመቶ በላይ የካንሰር በሽታዎች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የጡት፣ የቆዳ፣ የሳንባና የመተንፈሻ አካላት፣ የአንጀት፣ የደም፣ የማህጸንና ሌሎች የካንሰር አይነቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2015 ባወጣው መረጃ በተጠቀሰው ዓመት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል። ይህም በዓመቱ ከተከሰቱት ከስድስት ታማሚዎች መካከል አንዱ በካንሰር አማካኝነት የሚከሰት ሞት መሆኑ ነው። 

በየዓመቱ ደግሞ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በካንሰር ይያዛሉ። ሕክምናውን በበቂ ሁኔታ ማግኘት ከተቻለ ከ30 እስከ 50 በመቶ ሕሙማኑን ማዳን እንደሚቻል ይነገራል። ግን ሕክምናውን ማግኘት ቀላል አይደለም። በሪፖርቱ መሠረት ችግሩ በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ እ.ኤ.አ በ2020 በካንሰር የሚሞተው ሕዝብ ቁጥር 10 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይተነትናል። በየዓመቱ በአዲስ የሚያዘው ሰው ቁጥርም ወደ 16 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ለካንሰር በሽታ መንስዔ ከሆኑት አንዱ ትምባሆ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ትምባሆ ከ25 እስከ 30 በመቶ ለካንሰር መንስዔ ነው። የአመጋገብ ችግርና ውፍረትም ከ30 እስከ 35 በመቶ ድርሻን ይይዛሉ። በርግጥ ከ5 በመቶ እስከ 10 በመቶም በዘር ይተላለፋል። በተለያዩ በሽታዎች መጠቃት ከ15 እስከ 20 በመቶ፣ ጭንቀት፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግና ሌሎች ደግሞ 10 በመቶውን እንደሚይዙም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ታክሞ የመዳን ዕድላቸው እንደ ህመሙ ዓይነት፣ ደረጃ፣ ዕድሜና ህክምናው በተሟላ ሁኔታ መስጠት አለመስጠቱ ላይ የተወሰነ ነው። ይኽውም እንደማንኛውም ህመም ማዳን፣ መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል። በቶሎ ከተደረሰበትና በቂ ህክምና ካገኘም ማዳን እንደሚቻል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከፍተኛ የክብደት መቀነስ፣ በሰውነት ላይ አዳዲስ ነጠብጣብ መታየት፣ በአንጀትና በኩላሊት ላይ የህመም ስሜት መሰማት፣ ተከታታይና ደረቅ ሣል  መኖር፣  በሰውነት ክፍሎች (ለምሳሌ በጡት) ላይ ጠጠር ያለ ወይም ላላ ያለ እብጠት መከሰት እንዲሁም ቶሎ የማይድን የጉሮሮ ህመም መከሰት ጥቂቶቹ የበሽታው  ምልክቶች ናቸው።

የካንሰር በሽታ የበለፀጉት አገራት ችግር ብቻ ተደርጎ ይወሰድ እንደነበር ይነገራል። ይሁንና ዛሬ ዛሬ በታዳጊ አገራትም አሳሳቢ ችግር እየሆነ መጥቷል። ይህም ህክምናውን በበቂ ሁኔታ ለማግኘትም ሆነ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ነው ለታዳጊ አገራት ፈተና የሆነው። በታዳጊ አገራት በየዓመቱ በካንሰር ምክንያት ህይወቱን የሚያጣው ህዝብ ብዛት በኤች አይ ቪ ኤድስ ከሚሞተው ሰው በእጥፍ እንደሚበልጥ የጤና ድርጅቱ መረጃ ያመለክታል።

እስኪ ወደ ኢትዮጵያ እንመልከት። በአሁኑ ወቅት የጡት እና የማህፀን ጫፍ ካንሰር በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። የበሽታው ተጠቂዎች ህክምናውን ባለማግኘታቸው ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ ነው። በተለይ ስለካንሰር በሽታ ያለው ግንዛቤም ሆነ መረጃ አነስተኛ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ከድጡ ወደ ማጡ እንዳሸጋገረው ነው የሚነገረው።  የበሽታው ድብቅ ባህሪይም ለመከላከልም ሆነ ለህክምናው ፈተና ሆኗል።

የችግሩን አስከፊነት በመገንዘብ በአገራችን ምን እየተሰራ ይሆን? ምንስ መደረግ አለበት? የሚለው የሁላችንም ጥያቄና መልስ የሚያሻው ጉዳይ ይመስለኛል። የሕብረተሰቡን ችግር ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ ባይቻልም እንኳን መቀነስ በሚያስችል መልኩ የካንሰር ህክምና አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ 5 ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በሚኒስቴሩ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቡድን መሪ ዶክተር ብስራት ደሳለኝ እንደሚሉት፤ በሐዋሳ፣ በመቀሌ፣ በጅማ፣ በጎንደርና በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገነቡት የሕክምና ማዕከላት ለአጠቃላይ ግንባታና የህክምና ቁሳቁስ ወጪ የሚሆን 80 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞ ነው ሥራው እየተከናወነ ያለው።

እንደ ዶክተር ብስራት ገለጻ፤ በአገሪቱ ከአሁን በፊት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ ተወስኖ የቆየውን የካንሰር ህክምና በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው። በአሁኑ ወቅት ከአዳዲሶቹ ማዕከላት ግንባታ ጎን ለጎን የህክምናና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ግብአትን የማሟላት ተግባራትም እየተከናወነ ይገኛል። ማዕከላቱ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው ዶክተር ብስራት የገለጹት።

አገልግሎቱን በተለያዩ አካባቢዎች ላይ መስጠት መቻል በሞት የምናጣቸውን ዜጎች ከመታደጉ ባለፈ ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ውጪ የሚሄዱ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ካላስፈላጊ ወጪና እንግልት ይታደጋል። ወደ ፊትም የችግሩን አሳሳቢነት በመገንዘብ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተመሳሳይ የሕክምና ማዕከላትን የማስፋፋት ሥራ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።

"ለወራት፤ ገፋ ሲልም ለዓመታት በማድፈጥ በዝምታ ሕይወትን ከሚቀጥፍ ገዳይ በሽታ ለመጠበቅ ሁላችንም ለራሳችን ትኩረት ማድረግ ይገባል ባይ ነኝ።" ምልክቶች ከተከሰቱ በአፋጣኝ ወደ ሕክምና ተቋማት በመሄድ ክትትል ማድረግን መዘንጋት የለብንም። ከካንሰር ይጠብቀንማ!!

Published in ዜና-ትንታኔ

አምቦ ጥር 3/2010 በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ400 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የህክምና መድኃኒቶች ተለገሰ።

የተለያየ የህክምና መድኃኒቶችን ገዝተው የለገሱት በአምቦ ከተማ  የሚገኙ ነጋዴዎች፣ የጤናና  የኃይማኖት ተቋማት መሆናቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡

በጽህፈት ቤቱ የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ስራ አስተባባሪ አቶ አለማየሁ አደላ እንዳሉት የተለገሰው መድኃኒት ተፈናቃዮች ወዳሉበት አካባቢ እየተጓጓዘ ነው፡፡

በልገሳው ከተሳተፉት መካከል በአምቦ ከተማ በሆቴል ንግድ የተሰማሩት ወይዘሮ የሺ ቤለማ  "ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ የተፈናቀሉ ዜጎች እስኪቋቋሙ ድረስ የተጀመረውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን" ሲሉ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

"የወገኖች ችግር የሁላችንም በመሆኑ እርዳታውን ሰጥቻለሁ፤ በቀጣይም በሙያዬም ሆነ በገንዘቤ ድጋፌን  እቀጥላለሁ" ያሉት ደግሞ  የግል ኪሊኒክ ባለቤት የሆኑት አቶ ታደለ ገረሙ ናቸው፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን