አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 10 January 2018

አዳማጥር 2/2010 በሥጋ ምርታቸው የተሻለ ዝርያ ያላቸውን እንስሳት በጥናት በመለየትና በማባዛት ጥቅም ላይ ለማዋል ስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ሚንስቴር ገለጸ።

የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚንስቴር ዴኤታ ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ገብረዮሐንስ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገር ውስጥ የተሻለ የሥጋ ምርት ያላቸው የዳልጋ ከብቶች፣ በጎች፣ ፍየሎችና ግመሎችን መለየትና መምረጥ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

በመሆኑም በሥጋ ምርታቸው የተሻሉ የእንስሳት ዝርያዎች ልማት ለማከናወን የሚያስችል በፖሊሲ ማዕቀፍ የተደገፈ ስትራቴጂ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ መገባቱን ተናግረዋል።

"የስትራቴጂው ዓላማ በሥጋ ምርታቸው የተሻለ ዝርያ ያላቸውን የዳልጋ ከብቶች፣ በጎች፣ ፍየሎችና ግመሎች በጥናት እንዲለዩ፣ በአይነት እንዲመረጡ፣ እንዲባዙና ለሕብረተሰቡ ተሰራጭተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው " ብለዋል።

"የሀገር ውስጥ ዝርያ ያላቸው እንስሳት የሚሰጡት የሥጋ ምርት አጥጋቢ አይደለም" ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፣ ከአካባቢው የአየር ፀባይ ጋር የተላመዱ የተሻሉ የሀገር ውስጥ ዝርያዎችን  በሥጋ ምርታቸው ከታወቁ የውጭ ሀገር ዝርያዎች ጋር የማዳቀል ሥራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ለእዚህም የውጭ ዝርያዎቹን በቁም፣ በአባለዘርና በተለያየ መልኩ ወደሀገር ውስጥ በማስገባት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ዘዴዎች በማዳቀል ምርቱን ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

የህግ ማዕቀፍና ስትራቴጂ ዕቅድ መኖሩ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የኢትዮጵያ የወተት ኢንዱስትሪዎች ማቀነባበሪያ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ በላቸው ሁሪሳ ናቸው።

የህግ ማዕቀፉና ስትራቴጂው የታወቁ የሀገር ውስጥ የሥጋ እንስሳት ዝርያቸው እንዳይበረዙ፣ ተመርጠው እንዲያዙና ተባዝተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

ሀገሪቷ ካላት የእንስሳት ሀብት እንፃር የሥጋ ምርቱ ለኢኮኖሚው እያበረከተ ያለው አስታዋፅኦ አነስተኛ መሆኑን አቶ በላቸው ገልጸው አንድ የዳልጋ ከብት 113 ኪሎ ግራም፣ ፍየልና በግ 9 ኪሎ ግራም የሥጋ ምርት በአማካይ እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በውጭ ሀገር ከአንድ ዳልጋ ከብት እስከ 250 ኪሎ ግራም የሥጋ ምርት እንደሚገኝ አመልክተው፣ "ሀገሪቷ ከዘርፉ ተገቢውን ጥቅም እንድታገኝ መንግስት የሥጋ እንስሳት ልማት ስትራቴጂ ቀርጾ ወደ ትግበራ መግባቱ ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ነው" ብለዋል።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተመራማሪና መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ሳይድ በበኩላቸው እንደገለፁት በዘርፉ ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱ ሀብቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ያግዛል።

"የሥጋ እንስሳት አይነት፣ መጠንና ዝርያን መሰረት አድርጎ በምርምር ለመለየት፣ ለማባዛትና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የህግ ማዕቀፉና ስትራቴጂው ቁልፍ የማስፈፀሚያ መሳሪያ ነው" ብለዋል።

በዘርፉ የሚሰሩ የምርምር ማዕከላትና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሥጋ እንስሳት ላይ የሚደረጉ የምርምር ሥራዎችን በባለቤትነትና በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።

በሀገሪቱ 58 ሚሊዮን የዳልጋ ከብቶችን ጨምሮ ከ120 ሚሊዮን በላይ በጎች፣ ፍየሎችና ግመሎች ይገኛሉ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሰመራ ጥር 2/2010 የአፋር ክልል ጤና ቢሮ "ፕሮጀክት ሐረር ኢትዮጵያ" ከተባለ ሀገር በቀል ምግባረሰና ድርጅት ጋር በመተባባር የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ሰዎች ነጻ የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታወቀ።

የከልሉ ጤና ቢሮ እንዳስታወቀው ነጻ የሕክምና አገልግሎቱ ከጥር 4 እስከ 6 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በዱብቲ ሆስፒታል ይሰጣል።

በክልሉ ጤና ቢሮ የሕክምናና ጤና ክብካቤ ዋና የሥራሂደት አስተባባሪ አቶ ሁሴን መሃመድ እንዳሉት፣  በተፈጠሮ የላንቃና የከንፈር መሰንጠቅ ችግር በሰዎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰው ስነ-ልቦናዊ፣ ማህብራዊና ኢኮኖሚዊ ተጽዕኖ ከባድ ነው።

ከዚህ በፊት በክልሉ ችግሩ ያለባቸው ሰዎች ሕክምናው በዘመቻ መልክ በሚሰጥባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተልከው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ይደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሕብረተሰቡ ካለበት የአቅም ውስንነት የተነሳ በዚህ ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ውሱን በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክት ሐረር ኢትዮጵያ ከተባለ ሀገር በቀል ድርጅት ጋር በመነጋገር ሕክምናውን በዘመቻ መልክ በክልሉ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

" በሕክምናው ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የሚመጡ ከ400 በላይ ሰዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል" ያሉት አቶ ሁሴን  ሕብረተሰቡ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በወረዳዎች በኩል ጥሪ መተላለፉን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ሁሴን ገለጻ፣ በሚሰጠው ነጻ የሕክምና አገልግሎት በዱብቲ ሆስፒታል ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ተሳታፊ ስለሚሆኑ የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ምቹ አጋጣሚ ይፈጠራል።

ከዚህ በተጨማሪ ከአንገት በላይ አንደ እንቅርትና መሰል እባጭ ያለባቸውን ሰዎች በቀጣይ የነጻ ሕክምናው አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የምዝገባና የልየታ ሥራዎችን እንደሚከናወኑ አቶ ሁሴን አያይዘው፡፡

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ጥር 2/2010  በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን የሚገኘውን የሰባት  ቤት አገው ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ፌስቲቫል ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ  አቶ ባይነሳኝ ካሳሁን ትናንት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ኃይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘት ያለውን የፈረስ ጉግስ ጨዋታ ፌስቲቫል ከጥር 23/2010ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት ቀናት በተለያየ ዝግጅት ለማክበር ኮሚቴዎች ተቋቁመው እየተሰናዱ ነው፡፡

በባንጃ ወረዳ በሚከበረው ፌስቲቫል አንድ ሺህ የተመረጡ ፈረሰኞች የግልቢያ ትርኢት የሚያቀርቡ ሲሆን የባህላዊ የምግብ ዝግጅት፣ የፎቶ ግራፍ አውደርዕይ ፣ የመስህብ ሃብቶች ጉብኝት፣ ባህላዊ የሙዚቃ ዝግጅትና የፓናል ውይይት ይካሄዳሉ።

የፌስቲቫሉ  መከበርም ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ጨዋታውን በሃገር ውስጥና በውጭ  ሰፊ እውቅና እንዲኖረው በማድረግ የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሻሻል ያለመ መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

በቀጣይም ፌስቲቫሉን በአንድ ማዕከል እንዲከበር ፣ ባህላዊ የፈረስ እርባታና የህክምና ቦታዎችን በማመቻቸት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የቱሪዝም ድርጅት (ዩኒስኮ) በቅርስነት ለማስመዝገብም ታስቧል።

ባህላዊ የፈረስ ጉግስ ጨዋታው እንደ አንድ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን  በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ዋና የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሃይለየሱስ ፋላቴ ናቸው።

የፈረስ ጉግስ ጨዋታውን ዝግጅት  በሃገር ውስጥና በውጭ  በማስተዋወቅ ለቱሪዝም ልማት እድገቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል መሆኑን ጠቁመዋል።

የሰባት ቤት አገው ባህላዊ የፈረስ ጨዋታ ፌስቲቫሉን ክልሉና ዞኑ በመተባበር ሃገር አቀፍ ይዘት ኖሮት እንዲከበር ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

በፌስቲቫሉ ላይም የሀገርና  የውጭ  መገናኛ ብዙሃን እንዲገኙና ባህላዊ ይዘቱን እንደጠበቀ እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የሰባት ቤት አገው የፈረሰኞች ማህበር በ1933 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከ48 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉትም ተመልክቷል።

Published in ማህበራዊ

ባህር ዳር ጥር 2/2010 በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ከተያዘው ወር አጋማሽ ጀምሮ በተለዩ ከ300 በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ለማከናወን  ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለጸ።

በተለዩ ተፋሰሶች ዘጠኝ ሺህ ሄክታር በሚጠጋ መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው  በአርሶ አደሩ ተሳትፎ  ይከናወናል።

በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዳኛው አምሳሉ ለኢዜአ እንዳሉት የማሳ ላይ ዕርከን፣ የተራቆተ መሬትን ከልሎ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የመጠበቅ ተግባር ከሚከናወኑት ስራዎች ይገኙበታል።

ከተያዘው ወር አጋማሽ ጀምሮ ለ30 የስራ ቀናት በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ የሚሳተፍ ከ218 ሺህ በላይ የሰው ኃይል ተለይቶ  ተዘጋጅቷል።

በአሁኑ ወቅትም ከዞን  እስከ ቀበሌ ድረስ ለሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የንቅናቄ መድረኮች እየተካሄደ ይገኛል።

አስተባባሪው እንዳመለከቱት በዞኑ ባለፉት ሰባት ዓመታት በህዝቡ የተደራጀ ንቅናቄ በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 310 ሺህ ሄክታር የተራቆተ መሬት በደን እንዲለብስ ተደርጓል።

ተፋሰሶቹ በማገገማቸው አርሶ አደሩ ለእንስሳት  ዋነኛ የመኖ መገኛ ምንጭ ሆኖ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የተጎዳው አካባቢ በመልማቱና ደርቀው  የነበሩ ምንጮች እንደገና በመመለሳቸው ለመስኖ ልማት፣ ለንብ ማነብ፣ ለእንስሳት እርባታና ማድለብ ስራ አመቺ ሁኔታ መፈጠሩም ተመልክቷል፡፡

" የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የሚያስገኘውን ጥቅም ጠንቅቀን መረዳታችን ለስራው ይበልጥ እንድንዘጋጅ አድርጎናል"  ያሉት ደግሞ የባንጃ ወረዳ አርሶ አደር አበራ ተስፋዬ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት ተፈጻሚ በሆነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራም የተጎዳ ቦረቦራማ መሬት እንዲያገግምና  የእርሻ መሬታቸውም  የአፈር ለምነት እየተሻሻለ እንዲመጣ ያገዛቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በሚጀመረው ተመሳሳይ የልማት ስራም እሳቸውን ጨምሮ ሁሉም የቀበሌው አርሶ አደር ለመሳተፍ ተዘጋጅተው እየተጠባበቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

Published in አካባቢ

ነቀምቴ ጥር 2/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን በተያዘው ዓመት ስምንት የመስኖ ግድቦች ግንባታ ሥራን በማጠናቀቅ  ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ የመስኖ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ  የጥናትና የዲዛይን የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ዮናስ ልመኑ ለኢዜአ እንደገለጹት የመስኖ ግድቦቹ እየተገነቡ ያሉት በመንግስትና በግብርና እድገት ፕሮግራም በተመደበ 81 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በጀት ነው።

በመገንባት ላይ ካሉ የመስኖ ግድቦች መካከል ሁለቱ አዲስ ሲሆኑ ስድስቱ የግንባታሥራቸው ባለፈው ዓመት የተጀመረ ነው።

ግድቦቹን ዘንድሮ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮናስ፣ " ግድቦቹ ተጠናቅቀው ወደሥራ ሲገቡ 1 ሺህ 260 ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 2 ሺህ 813 አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋሉ " ብለዋል ።

አዲሶቹ የመስኖ ግድቦች በዋዩ ቱቃ እና በጉቶ ጊዳ ወረዳዎች የሚገነቡ ሲሆን አምና የተጀመሩት ደግሞ በጉቶ ጊዳ፣ በዲጋ፣ በሊሙ እና በኪረሙ ወረዳዎች በመገንባት ላይ መሆናቸውን አስተባባሪው ገልፀዋል።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ መስኖ ልማት ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ አማኑኤል ኃይሌ እንዳሉት በወረዳው በፈይሳ ቀበሌ የተጀመረው መካከለኛ የመስኖ ግድብ ግንባታ ሥራ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ።

የዋዩ ቱቃ ወረዳ የመስኖ ልማት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ የማነ ታደሰ በበኩላቸው በወረዳው በጊዳ አባሎ ቀበሌ በስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ 157 ሄክታር መሬት ማልማት የሚችል ግድብ እየተሰራ መሆኑንና ዘንድሮ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጥር 2/2010 በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የዓለም ኢኮኖሚ የ3 ነጥብ 1 በመቶ እንድገት ሊያሳይ እንደሚችል የዓለም ባንክ ገለጸ።

እንደ ባንኩ ትንበያ ከሆነ የኢኮኖሚ እድገቱ የሚመዘገብባቸው አገሮች በ2017 ካስመዘገቡት የኢንቨስትመንት፣ የማኑፋክቸሪንግ፣እንዲሁም የወጪ ንግድ እድገት የላቀ ውጤት እያሳዩ በመምጣታቸው ነው።

በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግና በወጪ ንግድ ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የሚቀዛቀዙ ከሆነ ግን የተተነበየው የኢኮኖሚ ዕድገት ላይመዘገብ እንደሚችል ባንኩ እንደ ስጋት አስቀምጧል።

ዕድገቱ ለአጭር ጊዜ የሚታይ ሊሆን እንደሚችል የጠቆመው ባንኩ፤ በረጅም ጊዜ ሂደት የዓለምን ኢኮኖሚ ዕድገት ለማስፋት ከተፈለገ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ገልጿል።

ይህም የሰዎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና በዓለም ደረጃ ድኅነትን ለመቀነስ እንደሚረዳ ነው የዓለም ባንክ የተነበየው።

በተያዘው 2018 የፈረንጆቹ ዓመት የበለፀጉ አገራት ከዚህ ቀደም ያጋጠሟቸውን ቀውሶችና የኢንቨስትመንት ችግሮቻቸውን መፍታት ከቻሉ የኢኮኖሚ ዕድገቱ በሁለት ነጥብ ሁለት በመቶ ያድጋል ተብሏል።

በታዳጊ አገሮች ሸቀጣ ሸቀጦችን ወደ ውጭ የሚልኩ ላኪዎች የንግድ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ ከሆነ በ2018 በነዚህ አገሮች የሚመዘገበው አጠቃላይ ዕድገት በአራት ነጥብ አምስት በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል ተገምቷል።

የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት ጂም ዮንግ ኪም “የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት እያንሰራራ መሄድ የሚበረታታ ቢሆንም ይመዘገባል ተብሎ በተገመተው እድገት ልንኩራራ የሚገባን ጊዜ ላይ  አይደለንም” ይላሉ።      

የባንኩ ትንበያ ለሃገራት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ የሚገልጹት ፕሬዝዳንቱ “ ፖሊሲ አውጪዎች በኢንቨስትመንት፣  ምርታማነትን መጨመር በሚያስችሉ ተግባራት፣ በድህነት ቅነሳና ብልጽግናን ማፋጠን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል።

2018 አገሮች በተደጋጋሚ ሲያጋጥሟቸው ከነበሩ የፋይናንስ ቀውሶች ለመውጣት በሙሉ አቅማቸው የሚሰሩበት የመጀመሪያው ዓመት ሊሆን እንደሚችልም ተገልጿል።

ይህን እውን ለማድረግ ግን የሕግ አውጪዎች የዕድገቱን ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስልቶችን ከመቀየስ ጀምሮ የገንዘብ ፖሊሲያቸውን እስከማሻሻል የሚደርስ ተግባር ሊያከናውኑ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣የሰው ሃብት ልማት ላይ ሰፊ ስራ መስራት፣ ለትምህርት ለጤናና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች ትኩረት መስጠትና የስራ እድል ፈጠራ ላይ ማትኮር የተተነበየውን የእድገት ልኬት ለማሳካት ያግዛል ተብሏል።

እ.ኤ.አ በ2018  በዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ትንበያ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ ከተባሉ አገራት መካከል ጋና፣ኢትዮጵያ፣ኮትዲቯር፣፣ህንድ እና ቻይና በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

ኢትዮጵያ በባንኩ አሀዛዊ መረጃ መሰረት የ8 ነጥብ 2 በመቶ እድገት በማስመዝገብ ከአፍሪካ አገራት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ከሚያስመዝግቡ አገራት ከጋና በመቀጠል በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኮትዲቯር፣ታንዛንያ፣ሴራሊዮን፣ቤኒንና ኬንያ ከጋና እና ኢትዮጵያ በመቀጠል በአፍሪካ የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ያስመዘግባሉ የተባሉ አገራት ናቸው።

Published in ኢኮኖሚ

አርባምንጭ ጥር 2/2010 "ሲፓፕ" የተባለው የኦክሲጂን ማሽን በመበላሸቱ ምክንያት የጨቅላ ህፃናት  የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መቸገሩን የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡

በሆስፒታሉ የጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ተስፋዬ ለኢዜአ እንዳሉት የጤና ተቋሙ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ጨቅላ ህፃናት የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሆስፒታሉ አለጊዜያቸው ለሚወለዱ ህጻናት የኦክስጅን መስጫ " ሲፓፕ " የሚባለው  ማሽን በመበላሸቱ የህክምና አገልግሎቱን ለመስጠት ችግር እንደገጠመው  ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ታፍነው የሚወለዱ ህጻናትን ጭምር የማትረፍ ስራው ፈታኝ እንደሆነባቸው አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

በማሽኑ እስካለፈው ዓመት ድረስ ከ2 ሺህ ለሚበልጡ ጨቅላ ህጻናት አገልግሎቱን በመስጠት የጨቅላ ህጻናትን ሞት በ2005 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ 4 በመቶ ወደ 10 ነጥብ 6 ዝቅ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

የዚህ ማሽን መበላሸት ግን ታፍነው የሚወለዱ ጨቅላ ህጻናትን የማትረፍ ስራ ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ባለፈው ዓመት ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አምስት ሲፓፕ ማሽኖች የተገኘ ቢሆንም የተሟላ መሳሪያ ያልተገጠመላቸው በመሆኑ እስካሁን አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ነው አቶ ሰለሞን የተናገሩት፡፡

ጊዜያቸዉ ሳይደርሱ የተወለዱ ፣ ጡት መጥባት ያልቻሉ ፣ የታፈኑና ሌላም ችግር ያጋጠማቸው ህፃናት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው የገለጹት ደግሞ በሆስፒታሉ የጨቅላ ህፃናት ህክምና ክፍል ባለሙያ ሲስተር ፍሬህይወት ዳኜ ናቸው፡፡

አገልገሎቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚመለከተው ክፍል በትንፋሽ እጥረት ለሚመጡ ህፃናት አስቸኳይ እርዳታ እንዲያገኙ ማሽኖቹ ለአገልግሎት ማመቻቸት እንዳለበትም  ጠቁመዋል፡፡

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አዳሙ ኪሮ በበኩላቸዉ አንዳንድ ጊዜ የህክምና መሣሪያዎች የተወሰኑ ክፍሎች ሳይሟላላቸው የሚመጡበት አጋጣሚ እንዳለና ለዚህም ማሳያው  " ሲፓፕ" የተባሉት ማሽኖች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

" በዚህም  ምክንያት ኦክስጂን ለመወሰድ  በየወሩ አዲስ አበባ በምናደርገው ምልልስ እስከ 160 ሺህ ብር ወጪ እናደርጋለን "ብለዋል፡፡

ማሽኖቹ ተስተካክለው አገልግሎት እንዲሰጡ ከሚመለከተው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የመድኃኒትና ህክምና መሣሪያዎች ዳይሬክቶሬት የህክምና መሣሪያዎች አስተባባሪ አቶ ወንዳፍራሽ ሚሊዮን ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የ" ሲፓፕ" ማሽኖቹ ያልተገጠመላቸውን የአየር መስጫ መሣሪያ  አቅራቢ ድርጅቱ በአስቸኳይ እንዲያሟላ ከስምምነት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

ለአገልግሎት በማብቃትም ችግሩ በቅርቡ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችልም አመልክተዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ጥር 2/2010 የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ምሥረታ አገር አቀፍ ጉባኤ የፊታችን ሰኞ በአዲስ አበባ ይጀመራል።

የአድዋ ፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ ምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ዛሬ ጉባኤውን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

ከሁለት ዓመት በፊት የአድዋ ድልን መሰረት በማድረግ ታሪኩ በተፈጸመበት ቦታ የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝና የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሶቬኒ ዩኒቨርሲቲው በሚገነባበት ስፍራ የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታወሳል። 

ይህንንም ተከትሎ 29ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ሲካሄድ የዩኒቨርሲቲው አስፈላጊነት በሁሉም የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።

በአገር ዓቀፍ ደረጃ የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ በትግራይ ክልል በአድዋ አካባቢ 150 ሄክታር መሬት ተረክቦ የግንባታ እቅድ እያዘጋጀና ከዚሁ ጎን ለጎን  በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠው ሥርዓተ-ትምህርት እየተዘጋጀ እንደሆነ ተጠቁሟል።  

በዩኒቨርሲቲው የጥቁር ህዝቦችን ታሪክ በተመለከተ ምርምር የሚደረግበት ትልቅ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን የታቀደ ሲሆን የማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርትም ይሰጥበታል። በዚህም ደግሞ ከተለያዩ አገራት የመጡ ተማሪዎች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል።

ከሁለት አመት በኋላ ዩኒቨርሲቲው ሙሉ አገልግሎት መሥጠት እንዲጀምር እየተሰራ ስለመሆኑ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ቢተው በላይ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የፊታችን ሰኞ እና ማክሰኞ በሚካሄደው ብሔራዊ ጉባኤ እስካሁን የተሰሩት ሥራዎች ለህዝብ ለማቅረብና ቀጣይ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

በተጓዳኝም መንግሥት ከሚያቀርበው ድጋፍ በተጨማሪ ከሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ድጋፍ ለማሰባሰብም መታሰቡን አቶ ቢተው ገልጸዋል።

ጉባዔ ከሁለት ወር በኋላ ለሚካሄደው የአድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ  ዓለም አቀፍ ጉባኤ ግብዓት  ይሰበሰብበታል ብለዋል።

አድዋ ጥቁር ህዝቦች ነጮችን ድል ማድረግ እንደሚችሉ ኢትዮጵያውያን ያሳዩበትና ከ122 ዓመት በፊት ታሪካዊ ሁነት የተከናወነበት ስፍራ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጥር 2/2010 የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች።

ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ኤክስፖ ላይ እንደምትሳተፍም ተገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መንሱር ቢን ዛይድ አል-ናህያን ጋር በሁለትዮሽና አካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያያታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ግንባታና በተለያዩ መስኮች የምታካሂደውን የልማት ጥረት እንደምትደግፍ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ መንሱር ገልጸዋል።

በዚህ መሰረትም ከጌዶ-ለምለም በረሃ እየተካሄደ ያለው የመንገድ ግንባታ እንዲጠናቀቅና ሌሎች የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ አገራቸው የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ይህንን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ ባለስልጣናት በሁለትዮሽና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ጥልቅና ፍሬያማ ውይይት ማካሄዳቸውን መግለጫው አትቷል።

በተያያዘ ዜና ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ኤክስፖ ላይ እንደምትሳተፍ ተጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሪም አል ሀሽም ጋር መወያየታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መግለጫ ያመለክታል።

ዶክተር ወርቅነህ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት እ.አ.አ በ2020 በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚካሄደው ኤክስፖ ኢትዮጵያ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ ናት።

እንዲሁም አገሪቷ ኤክስፖው እንዲሳካ ከተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች ጋር ተባብራ እንደምትሰራ ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሪም አል ሀሽም በበኩላቸው ኤክስፖው አገራቸውን ከዓለም ማህበረሰብ ጋር ለማስተሳሰር የሚረዳ ነው ብለዋል።

ኤክስፖው ኢትዮጵያ ያላትን ባህል፣ታሪክ፣ወግ ለማሳየትና የኢንቨሰትመንት አቅሟን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ሚኒስትሩ መግለጻቸው በመግለጫው ተመልክቷል።

በተያያዘም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ አቡዳቢ ከሚገኘው ኢግል ሂልስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ዳግላስ ስሞል ጋር ውይይት አድርገዋል::

ኩባንያው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንደሚረዳና በአገሪቷ በቤት ግንባታ እና በተለያዩ የስራ መስኮች መዋዕለ ንዋዩን ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለውና ለዚህም ዝግጁ እንደሆነ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እንዳላት በማስረዳት መንግስት አስፈላጊውን ትብብር እንደሚያደርግ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መግለጫ አመላክቷል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም ኢትዮጵያ ቆንስላዋን እ.ኤ.አ በ2004 በዱባይ የከፈተች ሲሆን፤ ኤምባሲዋን ደግሞ በ2014 በአቡዳቢ ከፍታለች። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ እ.ኤ.አ በ2010 ነበር ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተችው።

የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የንግድ ግንኙነት ከ10 ዓመት በፊት ከነበረበት 45 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር እ.ኤ.አ በ2016 በዓመት ከ809 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን መረጃ ያስረዳል።

Published in ፖለቲካ

ነቀምቴ ጥር 2/2010 በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የነቀምቴ ዲስትሪክት ሠራተኞች በኦሮሚያና በሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ችግር ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉት ወገኖችን ለመደገፍ ከ89 ሺህ ብር በላይ ለገሱ ።

የዲስትሪክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበራ ሚደቅሣ እንደገለጹት   ሠራተኞቹ ድጋፉን ያደረጉት በራሳቸው ተነሳሽነት ከወር ደመወዛቸው እስከ 30 በመቶ በመቀነስ ሲሆን ሙሉ ደመወዛቸውን የሰጡም ይገኙበታል፡፡

ድጋፉ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አለመሆኑን ገልጸው "ተፈናቃዮቹ እስኪቋቋሙ ድረስ ይቀጥላል " ብለዋል።

አቶ አበራ ከዲስትሪክቱ ሠራተኞች የተለገሰውን ገንዘብ ለነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ለአቶ ዓለማየሁ ዴሬሣ በቼክ አስረክበዋል፡፡

ከዲስትሪክቱ ሰራተኞች መካከል አቶ ዋቅጅራ ሮባ በሰጡት አስተያየት " ወገናችን ሲጎዳ እኛ እንደተጎዳን ይሰማናል" ካሉ በኋላ በራሳቸው ፍላጎት ከወር ደመወዛቸው 30 በመቶ በመቀነስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

" ለወገን ደራሽ ወገን ነው " ያሉት ሌላው የዲስትሪክቱ ሠራተኛ አቶ አብደታ ኢተፋ በበኩላቸው ከወር ደመወዛቸው 3ሺህ 500 ብር በመቀነስ መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ከደመወዛቸው 30 በመቶ በመቀነስ ድጋፍ ማድረጋቸውንና  ተፈናቃዮቹ እስኪቋቋሙ ድረስ እገዛቸውን እንደሚቀጥሉ የገለጹት ደግሞ አቶ ጉርሜሣ ገነቲ የተባሉት የዲስትሪክቱ ሰራተኛ ናቸው፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን