አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 01 January 2018

አርባ ምንጭ ታህሳስ 23/2010 በጋሞጎፋ ዞን የከተሞች አስተዳደራዊ መዋቅር በአዲስ መልክ እየተደራጀ መሆኑን የዞኑ ከተማ ልማትና ቤቶች መምሪያ አስታወቀ፡፡

አዲሱ አደረጃጀት በከተሞች የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት በሚያስችል መንገድ ተጠንቶ የተዘጋጀ መሆኑን በመምሪያው  የከተሞች አደረጃጀት ፕላን ዝግጅትና ክትትል ዋና ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እድረ እርኮ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ይህም በከተሞች አስተዳደር ስር የነበረው የክፍለ ከተማ መዋቅር በማስቀረት በምትኩ ከዞኑና ከወረዳ ጋር አቻ በሆነ ቀበሌ መዋቅር እንዲደራጁ ያደርጋል፡፡

አደረጃጀቱ በከተሞች የሚስተዋለውን የመሬት ወረራን ጨምሮ በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዳኝነት የሚሰጥ ልዩ ፍርድ ቤት መዋቅርም መካተቱን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ በከተማ አስተዳደር ከሚመሩ አርባምንጭና ሳውላ ከተሞች በተጨማሪ ጨንቻና ቡልቂ ራስን የማስተዳደር የታዳጊ ከተማ አስተዳደር መዋቅር መፈቀዱን ጠቁመዋል፡፡

"አዲሱ አስተዳደራዊ መዋቅር የተፈቀደላቸው ሁለት ከተሞች ከ100 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ከመሆናቸውም በላይ የክልሉ መንግስት ከተሞችን በአዲስ ለማደራጀት የወጣውን የመመዘኛ መስፈርቶች አሟልተው በመገኘታቸው ነው "ብለዋል፡፡

በዚህ አደረጃጀት ዙሪያ የህዝብ ውይይት እንደሚካሄድና ከተያዘው ወር መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ  ትግበራ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡

የጨንቻ ወረዳ የቀድሞ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እሸቱ እልቶ በሰጡት አስተያየት ጨንቻ ከተማ ከአዲስ አበባ ጋር ተቀራራቢ እድሜ ቢኖራትም ራስ የማስተዳደር መዋቅር ባለመኖሩ የእድሜዋን ያህል ማደግ እንዳልቻለች ተናገረዋል፡፡

አዲሱ አደረጃጀት የህዝቡን የረጅም ጊዜ ጥያቄ በጎ ምላሽ የሰጠ መሆኑን ጠቁመው ይህም መዋቅር የከተማዋን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንደሚያፋጥን ጠቅሰዋል፡፡

የቡልቂ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ባልደረባና  የከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ገነት እንድሪያሰ በበኩላቸው ከተማዋ በራስ አስተዳደር መደራጀቷ  የኢንዱስትሪ ልማቱን ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

"የከተማው የውስጥ ገቢ እንዲያድግና መሰረት ልማቶች እንዲስፋፉ እንዲሁም በየጊዜው የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በቅርበት ለመፍታትም መልካም ሁኔታን ይፈጥራል "ብለዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ታህሳስ 23/2010 የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው የሚጠቀሙበትን መሬት በባለቤትነት ተንከባክበው ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲሰሩ ያነሳሳቸው መሆኑን በጋምቤላ ክልል የማጃንግ ዞን መንገሺ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ በበኩሉ በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ከ19 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ባለቤት ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ አርሶ አደሮች እንዳሉት የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱ በእርሻ ማሳ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ከተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ ይከሰቱ የነበሩ አለመግባባቶችን ያስቀራል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አርሶ አደር አዕምሮ አለሙ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታቸው የሚጠቀሙበትን መሬት በተሻለ ተንከባክበው ምርታማነታቸውን ለማሳደግ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ማረጋገጫው  ባለመሰጠቱና ለመሬት የዞታ ባለቤትነት መብት ባለመከበሩ በማሳ ወሰንተኛ አርሶ አደሮች መካከል አለመግባባቶች ይፈጠሩ እንደነበር አመልክተዋል።

"የተሰጠኝ የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር በእርሻ ማሳዬ ይዞታ ላይ የነበረብኝን የባለቤትነት ስጋት ቀርፎልኛል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ አርሶ አደር መብራብ ሳዶ ናቸው፡፡

አርሶ አደር አለማየሁ ኃይሌ በበኩላቸው "የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ማግኘታችን በማሳችን አካባቢ ያጋጥመን የነበረውን የወሰን ክርክር ከመፍታት ባለፈ ለመሬቱ የተሻለ እንክብካቤ ለማድረግ ያነሳሳል" ብለዋል።

በቀጣይ ባላቸው መሬት የቤተሰባቸውን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በተጨማሪ ለገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት ጠንከረው እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው አቡፕ እንደገለጹት፣ በበጀት ዓመቱ በክልሉ ከ19 ሺህ በላይ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ባለቤት ለማድረግ ታቅዶ ተገባራዊ እየተደረገ ነው።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለ1 ሺህ 200 አርሶ አደሮች ደብተሩ መሰጠቱንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በተለይም የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መስጠት ያስፈለገበት ዋና ዓላማ አርሶ አደሩ የመሬት ይዞታውን በባለቤትነት ስሜት እንዲይዝ ለማድረግ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በእርሻ ማሳው አካባቢ የሚነሱ አለመግባባቶችን በመፍታት ምርታማነትን ማሳደግ እንደሆነም ኃላፊው ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ታህሳስ 23/2010 በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የዓይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በ800 ሚሊዮን ብር ወጪ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ። 

በዩኒቨርሲቲው የኮንስትራክሽን ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ሰመረ ሰይፉ ለኢዜአ እድገለጹት፣ የማዕከሉ ግንባታው እየተከናወነ ያለው በ30 ሺህ ሜትር ስኩዌር መሬት ላይ ነው።

የግንባታ ሥራው በ2008 ዓ.ም መጨረሻ   የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 36 በመቶ ላይ መድረሱንና በቀጣይ ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አመልክተዋል።

በዛምራ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭ እየተገነባ ያለው የካንሰር ሕክምና ማዕከሉ እያንዳንዳቸው ባለስድስት ፎቅ የሆኑ ዘመናዊ ሕንጻዎች እንደሚኖሩትም ኢንጅነር ሰመረ ተናግረዋል።

የዓይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አማኑኤል ኃይለ በበኩላቸው፣ የካንሰር ሕክምና ማዕከሉ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ሲበቃ 300 አልጋዎች ይኖሩታል።

ለከፍተኛ ሕክምና ባለሙያዎችና ተማሪዎች የምርምር፣ የሕክምና፣ የፋርማሲ፣ የቤተሙከራና ሌሎች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት መስጫዎችን አካትቶ እንደሚይዝም አመልክተዋል።

ማዕከሉ ዘመናዊ የጨረር ሕክምና መሳሪያዎችና ሌሎች የተለያዩ ማሽኖች እንዲሟሉለት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር አማኑኤል ገልጸዋል።

በማዕከሉ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት የጥቁር አንበሳና የውጭ ስልጠናቸውን በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር አማኑኤል እንዳሉት ዓይደር የካንሰር ሕክምና ማዕከል ከትግራይ ባለፈ በአማራና አፋር አጓራባች ክልሎች ለሚገኙ ሕሙማን የሚያገለግለ ነው።

"የማዕከሉ መገንባት በተለይ ለካንሰር ምርመራና ሕክምና ወደ አዲስ አበባ በመመላለስ ገንዘባቸውን ይጨርሱ የነበሩ ሕሙማን ያለ ውጣ ውረድ በአቅራቢያቸው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ያደርጋል" ብለዋል ።

በጥቂት ሠራተኞችና በእርዳታ በተገኙ የሕክምና መሳሪያዎች በ2000 ዓ.ም ሥራውን የጀመረው ዓይደር ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት ከ80 በላይ ስፔሻሊስቶችን ጨምሮ ሁለት ሺህ 400 ሠራተኞች አሉት።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት ለአስረኛ ጊዜ ከ4 ሺህ 700 የሚበልጡ ሰልጣኞችን በድህረና ቅድመ ምረቃ የትምህርት መርሃ ግብሮች  እያስተማረ ነው፡፡

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ታህሳስ  23/2010 በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የውሃ አመራጮችን በመጠቀም  እየለማ ባለው ሰብል ላይ የተከሰተውን  የአሜሪካ መጤ ተምች ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

የክልሉ  እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሉው ኡቡፕ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፈው ክረምት የመኸር ሰብል ልማት  ተከስቶ የነበረው ይሄው ተምች በአሁኑ  ወቅት እየለማ   ላይ ጉዳት  እያደረሰ ነው።

ባሮን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ አራት ወንዞች በክረምቱ ሞልተው በመፍሰስ የፈጠሩትን የአፈር እርጥበትና ሌሎችንም የውሃ አማራጮችን በመጠቀም አርሶና ከፊል አርብቶ  አደሮች የበጋ ወቅት ልማት እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

በተለይ ልማቱ በስፋት በሚካሄድባቸው ጋምቤላ፣ አበቦ፣ ላሬ ኢታንግና የጅካዎ ወረዳዎች ተምቹ  መከሰቱን ኃላፊው ተናግረዋል።

ተምቹ በወረዳዎቹ በሰባት ሺህ ሄክታር መሬት በለማ የበቆሎና የማሽላ ሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው "የፀረ- ተባይ ኬሚካል  በመርጭት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው "ብለዋል።

በተጨማሪም አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተምቹን በባህላዊ ዘዴ ከማሳቸውን  በማጽዳት እንዲከላከሉ ባሙያዎች የምክርና የክትትል ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን ዶክተር ሉው አስታውቀዋል።

በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ወለጋ ኡሎክ በበኩላቸው ተምቹን ከፀረ- ተባይ ኬሚካል ይልቅ በባሀላዊ መልኩ መከላከሉ የተሻለ አመራጭ  መሆኑን ገልጸዋል።

ተምቹ በተለይም በበቆሎ ሰብል ሙሽራ ውስጥ  እንደሚደበቅና ይህም የኬሚካል ርጭቱ ተባዩን ስለማያገኘው ባህላዊ የመከላከል ዘዴው ይበልጥ ተመራጭ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

አርሶና ከፊል አርብቶ አደሮች ተምቹን ከሰብሉ ላይ በመልቀምና ከማሳቸው በማጽዳት እንዲከላከሉ ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

የጋምቤላ ከተማ ዙሪያ  አርሶ አደር ቄስ ደጉ ኡከኝ በሰጡት አስተያየት "ባለፈው ክረምት የተከስተው ተምች አሁንም ተከስቶ በሰብሌ ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው" ብለዋል።

ተምቹን ለማጠፋት የግብርና ባለሙያዎች ኬሚካል በመርጨት እያገዟቸው መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ተምቹ ከሰብላቸው ላይ በመልቀም ለመከላከል ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በማሽላና የበቆሎ ሰብላቸውን ላይ የተከሰተውን ተምች ለመከላከል መድኃኒት ቢረጭም ተባዩ እንዳልቀነሰ የተናገሩት ደግሞ የሴት አርሶ አደር  አኬሎ አጆቶ ናቸው።

በጋምቤላ ክልል በተያዘው የበጋ ወቅት የተለያዩ የውሃ አመራጮች በመጠቀም ለማልማት በእቅድ ከተያዘው ውስጥ እስካሁን ከ18 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ ሰብል መሸፈኑን ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in News

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2010 የኢትዮ-ጅቡቲ ስታንዳርድ ጊጅ የባቡር ትራንስፖርት የመንገደኞችና የጭነት አገልግሎት ከታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ስራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ የአገልግሎት ታሪፉንም ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የባቡር ፕሮጀክቱ መሰከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ የተመረቀ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት በርካታ የዝግጅትና የሙከራ ስራዎች እንደተከናወኑ ተገልጿል።

ህዳር 14 ቀን 2010 ዓ.ም ቻይና አሶሴሽን ኦፍ ሬልዌ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ከተባለ ኩባንያ የብቃት የምስክር ወረቀት ማግኘት ችሏል።

የኮርፖሬኝኑ የኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ደረጀ ተፈራ  እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ በርካታ የብቃት ማረጋገጫ ምዘናወችን ካለፈ በኋላ ነው በይፋ ስራ እንዲጀምር የተደረገው።

ይህን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አንድ ሺህ አንድ መቶ የጭነትና ሰላሳ የመንገደኞች ባቡር እንደተዘጋጀም ገልጸዋል።

የአገልግሎት ታሪፉ ተመጣጣኝ ዋጋ እንደተተመነ የተናገሩት አቶ ደረጀ፤ የወጣው ዋጋም ባቡሮቹ ለተጠቃሚው እንደሚሰጡት አገልግሎት እንደሚለያይ አውስተዋል።

ሃላፊው ታሪፉ እንደመጀመሪያ ሙከራ ከለቡ አዳማ፣ ድሬዳዋ ፣ አልሳቤህና ነጋድ ብቻ እንደተዘጋጀ ገልጸው ፤ "በቀጣይ  ከለቡ እስከ ጅቡቲ ባሉት 19 ጣቢያዎችን ባካተተ መልኩ ታሪፉ ይዘጋጃል" ብለዋል።

ከለቡ አዳማ በወንበር ለሚጓዙ 68 ብር፣ በባለ መኝታ ከላይ 91 ብር፣ ከመሃል 125 ብር፣ ከታች 137 ብር እንዲሁም በባለ ልዩ መኝታ ከላይ 171 ብር ከታች 182 ብር እንደሆነ ተገልጿል።

ከለቡ ድሬዳዋ በወንበር ለሚጓዙ 308 ብር፤ በባለ መኝታ ከላይ 410 ብር፣ ከመሃል 564 ብር፣ ከታች 616 ብር እንዲሁም በባለ ልዩ መኝታ ደግሞ ከላይ 769 ብር ከታች 821 ብር መሆኑም ታውቋል።

የጭነት ትራንስፖርት ዋጋ 0 ነጥብ 051 የአሜሪካን ዶላር /በቶን/ በኪሎ ሜትር  ሲሆን፤ የዶላር የምንዛሬ ተመንም ለዚሁ አገልግሎት ብቻ በሚውል መልኩ በ22 ነጥብ 5 ብር እንዲሆን መወሰኑንም አቶ ደረጀ ተናግረዋል።

ከታህሳስ 25 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ጥር 10 ቀን 2010 ዓ.ም አገልግሎቱን ለሚጠቀሙ ደንበኞች ከተገለፀው ታሪፍ የ50 በመቶ ቅናሽ መደረጉንም ገልጸዋል።

ከኢትዮ - ጅቡቲ ባቡር መስመር በተጨማሪ ከአዋሽ ወደ መቀሌ የሚዘረጋው መስመርም በፍጥነት እየተገነባ ሲሆን፤ ለአብነትም ከአዋሽ ወልዲያ ያለው ግንባታ አፈፃፀምም 61 በመቶ እንደደረሰ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይ ጥር 2010 ዓ.ም ከአዋሽ ወልዲያ ባለው የባቡር መስመር የሙከራ ጉዞ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2010 የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር ገበያውን ለማረጋጋት በ10 ክፍለ ከተሞች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ።

በቢሮው የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ወልደሰንበት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት፤ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር በሁሉም ክፍለ ከተሞች ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።

የተቋቋመው ግብረ ኃይል በየአካባቢው ያለውን ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚከታተልና የሚቆጣጠ ሲሆን፤ በተጨማሪም የንግድ ምዝገባ ፍቃድ እድሳትን በሚመለከት የመቆጣጠር ስራ እንደሚሰራም አቶ በላይነህ ጠቁመዋል።

ለህብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች ፍትሃዊና እኩል ተደራሽ እንዲሆኑ በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ውስጥ የተለያዩ ምርቶች እየገቡ እንደሆነም ነው የገለጹት።

በየክፍለ ከተማው በፍትሃዊነት ለመገበያየት የሚያስችል ኩፖን ለነዋሪው መድረሱን የተቋቋመው ግብረ ኃይል እንደሚያጣራ ጠቁመው፤ በዚህ አሰራር ክፍተቶች ካጋጠሙና ማስተካከያ ማድረግ ካስፈለገ ግብረ ኃይሉ እንደሚያስተካክል ገልጸዋል።

ለህብረተሰቡ በሚሰጡት አገልግሎት ህግ ተላልፈው በሚገኙ ነጋዴዎች ላይ አስተዳዳራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተናግረዋል።

አሁን የተቋቋመው ግብረ ኃይል በበዓሉ ምክንያት የሚፈጠሩ የዋጋ ጭማሪዎችን ከማስተካከል ባሻገር የምዝገባና ፍቃድ የመፈተሽ እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን በጊዜያዊነት የማከናወን ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይ የተሻለ ለመስራት እንዲችል የማጠናከር ተግባር  እንደሚከናወን አቶ በላይነህ ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ነቀምቴ ታህሳስ 23/2010  በነቀምቴ ከተማ በገበያው ለቆዳና ሌጦ የሚሰጠው ዋጋ ዝቅተኛ መሆን ስጋት እንዳሳደረባቸው በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ገለጹ።

 ነጋዴዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት የቆዳና ሌጦ ምርት ቢኖርም በገበያ ያለው ተፈላጊነት ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል።

 በቆዳና ሌጦ ንግድ ሥራ ላይ ከተሰማሩ ነጋዴዎች  መካከል  በነቀምቴ ከተማ በኬ ጀማ ክፍለ ከተማ የሚኖሩት አቶ ፈተድን ሁሴን በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ለረጅም ዘመናት በቆዳና ሌጦ ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ሕይወታቸውን ሲመሩ ቆይተዋል።

 ዘንድሮ የታየው የቆዳና ሌጦ ዋጋ መውረድ ኑሯቸውን በአግባቡ ለመምራት እንዳከበደባቸው ተናግረዋል።

 የቆዳና ሌጦ ዋጋ ለትራንስፖርት የወጣውን ወጪ ጭምር የማይሸፍን ከመሆኑ በተጨማሪ ገዥ በማጣት በየመንገዱ የሚጥሉበት አጋጣሚ እንዳለ አስረድተዋል።

 የከተማው ነዋሪ አቶ ፉአድ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት ከዚህ ቀደም  በዚህ ወቅት  ከ40 እስከ 50 ሺህ ቆዳና ሌጦ ሰብስበው ለማዕከላዊ ገበያ ያቀርቡ ነበር ።

 ዘንድሮ 15 ሺህ ቆዳና ሌጦ ገዝተው ቢያከማቹም ተረካቢ በማጣታቸው ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

 በእዚህ ምክንያት ገቢያቸው በመቀነሱ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር እንደከበዳቸው የተናገሩት አቶ ፉአድ፣ የገበያው መቀዛቀዝ  ስጋት ስላሳደረባቸው ባለድርሻ አካላት መፍትሄ እንዲፈልጉ ጠይቀዋል ።

 በሥራቸው ለ15 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረው እንደነበርና ባጋጠማቸው የገበያ ችግር ምክንያት በአሁኑ ወቅት ሠራተኞቻቸውን ከሥራ ማሰናበታቸውን ተናግረዋል።

 የነቀምቴ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት የእንስሳት ቆዳና የቆዳ ውጤቶች የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሰለሞን ሶሩማ እንደተናገሩት በዘንድሮ ዓመት ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው ቆዳና ሌጦ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ ቀንሷል።

 ለነጋዴው የሚቀርበው ምርት ጥራት የጎደለው መሆን፣ የዋጋ መቀነስ፣ ተረካቢዎች በወቅቱ ገንዘብ አለመክፈል ምክንያት የአቅራቢዎች ተስፋ መቁረጥ ለመጠኑ መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውን አመልክተዋል።

 ግብይቱን ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ በቀጣይ ጥራት ያለው የቆዳና ሌጦ ምርት ማቅረብ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

 የቆዳ ፋብሪካዎች አሰራራቸውን የሚያስተካክሉበት ስርዓት እንዲዘረጋ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚሰራም አቶ ሰለሞን አስረድተዋል ።

Published in ኢኮኖሚ

                               አቢብ ዓለሜ (ኢዜአ)

ፊልም እንደ ሌሎች የአገራችን ኢንዱስትሪዎች ሁሉ ሊያድግ ሊመነደግ፣ “እሰይ አበጀህ፣ በርታ አያያዝህ ጥሩ ነው” ተብሎ እየተጓዘ መሆኑን ደፍሮ መናገር አይቻልም። እንደሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎች ሁሉ መመንደግና ማደግ የሚገባው ዘርፍ እንደሆነ ግን ሁሉም ይስማማበታል።

ዛሬ ላይ የፊልም ሰሪዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ በገንዘብ፣ በአቅም ማነስ፣ በቅጅ መብትና በሌሎች ሳንካዎች ተተብትበው ከችግሩ ለመውጣት ትግል ላይ ናቸው። ችግሮች ቢገጥሟቸውም እንኳን በራሳቸው ገንዘብና የሰው አቅም “ለተመልካች ይሆናሉ” ያሏቸውን ፊልሞች ከመስራት አልሰነፉም።

የፊልም ተመልካቹ ተዘውትረው በሚቀርቡ የፊልም ሐሳቦች በመሰላቸቱ አዲስ ሀሳብ ማምጣት ያልቻለ በማለት ትችቱን ከመሰንዘር አልፎ ፊቱን ወደ ውጭ ፊልሞች አዙሯል። ዘንድሮ ለ12ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫል በፈጠረው የውይይት እድል በፊልም ዘርፍ ላይ ያሉ ፈተናዎችን ለይቶ ለማሳየት ሞክሯል።

ፊልሞችን እያወዳደረ የተሻለ የሰሩትን መሸለም፣ ከዓለም አቀፍና ከአገር ውስጥ ፊልሞች ልምድ ልውውጥ በማድረግ የዳበረ ልምድ ማካበት አላማው የሆነው ይህ ፌስቲቫል በየዓመቱ የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ በመውጣት ለፊልሙ እድገት ይበጃሉ ያሏቸውን ሐሳቦች ለውይይት እያቀረበ በተቻለው መጠን መፍትሄ ለማምጣት እየተጋ ነው።

"አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ መንገር እስካልጀመሩ ድረስ የአፍሪካ ታሪክ የቅኝ ገዢዎችን ማንነት የሚያሞካሹ ይሆናሉ" በሚል መሪ ሐሳብ አፍሪካውያን ታሪካቸውን በራሳቸው አንደበት ይተርኩ 12ኛው የፊልም ፌስቲቫል መልዕክቱ ነበር። 

‘ሳንኮፋ የታሪክ አተራረክ ጥበብ’ በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው የፊልም ፌስቲቫል አዘጋጅ አቶ ይርጋሸዋ ተሾመ "በየጊዜው የፊልም ፌስቲቫሎችን ብናዘጋጅም እንኳን  የፊልም ኢንዱስትሪው ይበልጥ እየተፈተነ ነው" ሲል ያስረዳል።

በመሆኑም በፊልም ዘርፉ ላይ የሚታዩ አስቸጋሪ ፈተናዎችን ለመፍታት ፌስቲቫሉ የራሱ የሆነ አወንታዊ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይናገራል። የተለያዩ ጥናቶች በዘርፉ ላይ የተደረጉ ቢሆንም እንኳን የጥናቱን ውጤት ይዞ ለመፍትሔ በመትጋት ተወዳዳሪና ተወዳጅ ማድረግ አልተቻለም።

በፊልም ሰሪዎች፣ ደራስያን፣ ተዋንያን፣ መንግሥትና ፊልም ተመልካቾች መካከል የጋራ መግባባት ተደርሶ ፊልሙን ከወደቀበት ማንሳት የሚቻልበት ዕድል አሁንም አለ። የኢትዮጵያ ፊልም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ መሆን እንዳይችል ያደረጉት የቁሳቁስ እጥረት፣ ያልተደራጀ የፊልም ግብይት ስርዓት፣ በፊልም ሰሪዎችና በመንግሥት በኩል ያለው የላላ ግንኙነት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።

ፊልም መስራት ቀላል ነገር አይደለም፤ ከፍተኛ በጀትና  የሰው ኃይል ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ዓቅም ያለው ፊልም ሰሪ ያስፈልጋል። በአገሪቱ ግን ፊልም ሰሪዎች ሁልጊዜ በገንዘብና ብቃት ባለው የሰው ኃይል እጥረት የሚፈተኑ ሆነዋል። ጥራት ያለው ስራ መስራት ያልተቻለው የፊልም ሰሪዎች የገንዘብ አቅም ውስን በመሆኑ እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። የዚህ ችግር ድምር ውጤት የሚታየው በተራ ቁሳቁስና በተራ አቀራረብ የሚሰሩ ፊልሞች ተመልካቹ ጋር ሲደርሱ ሰለቹኝ በሚልበት ቅጽበት ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት፤ ፊልሙን እንደትልቅ ዘርፍ አይቶ ድጋፍ እያደረገለት አለመሆኑ እርግጥ ጎልቶ የሚጠቀስ ጉዳይ ነው። "ፊልም ማሕበረሰብን ለማስተማር ይጠቅማል ተብሎ አይታሰብም" ብለው የመንግሥትን ድጋፍ “ዝቅተኛ ነው” በማለት የሚወቅሱ የፊልም ባለሙያዎች እየተበራከቱ ነው።

የቅጅ መብት ጉዳይ የኪነ ጥበብ ስራዎች መስራት ከጀመሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ ስሞታ የሚቀርብበት፤ አእምሯዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ቢቋቋምም ግለሰቦች፤ ተቋማትና ድርጅቶች የሰው የፈጠራ ሃብትን ያለ አግባብና ፈቃድ ሲመዘብሩ የሚስተዋል ሀቅ ነው። ይሄ እጣ የፊልሙንም ዘርፍ እየጎዳው ያለ ፈተና ነው።

የኢትዮጵያ ሙዚቃ በውጪ አገሮች በተለይ በአሜሪካ  እየተሸጠ ቢሆንም እንኳን የአገራችን ፊልም ግን አገር ውስጥ የሙዚቃውን ያህል እንኳን በስፋት መሸጥ አልተቻለም። ትምሕርት፤ ዕውቀትና የሙያ ክህሎት ያካበተ የፊልም ባለሙያ አለመኖር ደግሞ ሌላው ችግር ነው። ዛሬ ፊልም ለመስራት ፍላጎት ብቻ በቂ የሚመስልበት፤ ትንሽ ገንዘብ ያለው ሰው ፊልም የሚያዘጋጅበት፤ ከ15 ባልበለጠ ቀናት የፊልም ድርሰት ተጽፎ ለቀረጻ የሚወጣበት ጊዜ ሆኗል።

እርግጥ ነው ተሰጥኦ ለማንኛውም ነገር መሰረት ነው፤ ነገር ግን በትምህርትና በስልጠና ካልታገዘ ሂደቱ የኋልዮሽ ጉዞ ይሆናል። ፍላጎት ያለው ሁሉ ዳይሬክተር፤ የፊልም ጽሑፍ ደራሲ፤ አዘጋጅ፤ የካሜራ ባለሙያ፤ እየሆነ መምጣቱ ደግሞ የፊልም ጥራት ደረጃው እንዲወርድ አድርጓል።

የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሁሉ በየሰፈሩ ካሜራ ይዞ ፊልም ለመስራት የሚሯሯጥ ከሆነ፤ ተዋንያን የነበሩ ሁሉ ድንገት ተነስተው ፊልም ዳይሬክተር “ልሆን ነው” ካሉ፤ ግለሰቦች ሁሉ የፊልም አዘጋጅ ከሆኑ፤ ለእውቅናና ለዝና ብቻ የሚሮጥበት ዘርፍ እንጂ ተወዳዳሪ የፊልም ኢንዱስትሪ መሆን እንደማይቻል እሙን ነው።

ኢትዮጵያ ለውጪ አገር ፊልሞች ትልቅ ገበያ ሆና ሳለ፤ የአገር ውስጥ ፊልሞች ገበያ ደካማ መሆኑ ያነጋግራል። ፊልም ሰሪዎች ሁልጊዜ እንደሚሉት የውጪ አገር ፊልሞች ዘርፉን እየጎዱት ነው። በቅርቡ የተከፈቱ የውጪ አገሮች ፊልሞችን ተርጉመው ለአገር ውስጥ ተመልካች የሚያቀርቡ የሳተላይት ቴሌቪዢን ጣቢያዎች በፊልም ሰሪዎችና በተመልካቹ ላይ ትልቅ ጉዳት እያሳደሩ እንደሆነ በባለሙያዎች በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ይህ መሆኑ ደግሞ የአገር ውስጥ ፊልም ሰሪዎች ተስፋ በማጣት የፊልም ስራውን ለቀው መውጣት ወይም የውጪ አገር ፊልሞች በሚሰሩበት መንገድ እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ። ዘርፉ የሚመራው፤ የሚቆጣጠረው፤ በቅርበት ሆኖ የሚያስተዳድረውና የሚደግፈው ተቋምና የተማረ ባለሙያ ያስፈልገዋል።

መንግሥትም ዘርፉ ካለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ጠቀሜታ አኳያ በቅርበት ሊደግፈውና ፊልምን ለአገር ሁለንተናዊ ብልጽግና መሣሪያነት ሊጠቀምበት ይገባል።

Published in ዜና ሓተታ

አዲስ አበባ ታህሳስ 23/2010 በጥጥ ልማት ላይ የተጋረጡ የግብዓት፣ ፋይናንስና የግብይት ችግሮች አሁንም ሊፈቱ ያልቻሉ የዘርፉ ፈተናዎች እንደሆኑ የጥጥ አልሚዎች ማኅበር ገለጸ።

ዘርፉን በበላይነት የሚመራው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበኩሉ፤ የ15 ዓመቱ የጥጥ ልማት ስትራቴጂ የዘርፉን ችግር "በዘላቂነት ለመፍታት መፍትሄ ይሆናል" ብሏል።  

በጥጥ እርሻ፣ መዳመጫ ፋብሪካና ንግድ ላይ የተሰማሩ ከ100 በላይ አባላትን ያቀፈው የጥጥ አልሚዎች ማህበር በ2009 የሥራ ዕቅድ አፈጻጸምና በ2010 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጫዎች ላይ ጠቅላላ ጉባኤ እያካሄደ ነው።

አገሪቷ ለጥጥ ልማት ምቹ የአየር ንብረት ቢኖራትም በዘርፉ ላይ የተጋረጡ ከግብዓት፣ ከፋይናንስ አቅርቦትና ከግብይት ጋር የተያያዙ ችግሮች በሚጠበቀው ልክ ለማምረት እንቅፋት መሆናቸው ተጠቁሟል።

የማህበሩ አባላት እየተገነባ ያለው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክና የጥጥ ምርታማነት ዕድገት የተጣጣሙ ባለመሆናቸው ለክፍተቱ አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሼህ የሱፍ ዑመር በየወቅቱ ማህበሩ የሚያነሳቸው የዘር አቅርቦት፣ የመድሃኒት፣ የፋይናንስ ችግሮች አሁንም እልባት እንዳላገኙ ገልጸው፤ ከመሬት ጀምሮ አልሚዎች የሚያጋጥማቸው ችግር ካልተፈታ "ዘርፉን ወደሚፈለገው ደረጃ ማድረስ አይቻልም" ይላሉ።

በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመለየት የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚዎች ያሉበት ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት በኩል ተቋቁሞ 12 ቁልፍ ችግሮች መለየታቸውንም ተናግረዋል።

ስለሆነም መንግስት የተለዩትን ማነቆዎች በአፋጣኝ መፍታት እንዳለበት ገልጸው፤ "በአልሚዎች በኩል ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ማህበሩ ጥረት ያደርጋል" ብለዋል።

በጥጥ አምራችነት የተሰማሩት ኢንጂነር ጌታሁን ሐሰን በጥጥ እርሻ ላይ የሚሰሩ ባለሀብቶች ከፋይናንስ አቅርቦት ችግር ባለፈ የጸጥታ፣ የምርጥ ዘር አቅርቦት፣ የኬሚካልና ሌሎች የግብዓት ችግሮችን በመናበብና በመቀናጀት መፍታት ካልተቻለ ዘርፉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።

በርካታ ባለሀብቶችም "ተስፋ እየቆረጡ የጥጥ ማሳቸውን በሌሎች ሰብሎች እየሸፈኑ ነው" ያሉት ባለሀብቱ፤ ከክልል መንግስታት ጀምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ለዘርፉ ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጥጥ አምራቹ አቶ ተወልደ ገብረእግዚአብሄር በበኩላቸው፤ የመድሃኒት፣ የግብይትና ፋይናንስ ችግሮች ሳይፈቱ ጥጥ ማምረት እንደማይቻል ገልጸው፤ "በልማት ባንክና በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ዘርፉ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ በመገንባት ላይ ካሉ ኢንዱስትሪዎች 60 በመቶ የሚሆኑት የጨርቃ ጨርቅ መሆናቸውን አውስተው፤ ለኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ግብዓት የሆነውን የጥጥ ዘርፍ ማጠናከር ግዴታ በመሆኑ በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት እንደሆነም  ተናግረዋል።

በመሆኑም ችግሮቹን በዘላቂነት ለመፍታት በጥናት ላይ ተመስርቶ የተቀረጸ የ15 ዓመት የጥጥ ልማት ስትራቴጂ መጽደቁን ገልጸዋል።

ስትራቴጂው ተግባራዊ ሲሆን የፋይናንስ፣ የግብዓትና ግብይት ችግሮች  እንደሚፈቱም አረጋግጠዋል።

ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የጥጥ ምርት በጥራትና በብዛት ማምረት እንዲቻል የጥጥ እርሻዎችን ማስፋፋትና የተሻሻሉ ዘሮችን ማባዛትና ማሰራጨት ላይ ትኩረት እንደሚደረግም አመልክተዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶችን በማጋለጥ ለልማታዊ ባለሀብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል የአልሚዎች ማህበርን ትብብር ጠይቀዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተቋቋመው የጥጥ ችግር መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ከተለዩ 12 ችግሮች መካከል የአደረጃጅት፣ የድጋፍ፣ የመሬት ሽፋንና ምርትና ምርታማነት መቀነስ፣ የመዳመጫ ፋብሪካዎች፣ የፋይናንስና የግብይት ችግሮች ይጠቀሳሉ።

በአነስተኛ ማሳ ጥጥ አምራች አርሶ አደሮችን ጨምሮ በአገሪቷ እስከ 40 ሺ አምራቾች ሲኖሩ፤ ለ10 ሺዎች በቋሚነት፤ ለ90 ሺ ሰራተኞች ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ ዕድል እንደፈጠሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

Published in ኢኮኖሚ

ዲላ ታህሳስ 23/2010 የጌዴኦን ''ባህላዊ መልክዐ ምድር'' በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የማስመዝገቡን ሂደት ለማፋጠን የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር እንደሚያሰፈልግ ተገለፀ ፡፡

 በጉዳዩ ዙሪያ የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከጌዴኦ ዞን አመራርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሄዷል፡፡

 በውይይት መድረኩ ባህላዊ መልክአ ምድሩን በዩኒስኮ የዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሰራ ካለው የቅርስ ምዝገባ የጥናት ቡድን ሂደቱ ያለበት ደረጃ አስመልክቶ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተካሄዷል፡፡

 የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡቶ አኒቶ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ባለፈው አመት ሰኔ ወር የጥናቱ ውጤት ተጠናቆ ለፌዴራል ቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን እንዲቀርብ ዕቅድ ተይዞ ነበር ፡፡

 ጥናቱ ከሚጠይቀው ጥልቀት የተነሳ ሊዘገይ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

 ቢሮውም ሆነ ሌሎች አካላት የማስመዝገቡን ሥራ በተመለከተ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እየሰሩ እንደሆነ የገለፁት አቶ አቡቶ ''ሂደቱን ለማፋጠን በቅንጅት ልንስራ ይገባል'' ብለዋል ፡፡

 የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው የጌዴኦ ህዝብ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት ባለበት ተዳፋት መልክአ ምድር ላይ የምግብ ዋስትናውን አረጋግጦ በመኖር እና ዛፎችን በመትከል ተፈጥሯዊ ሥነ-ምህዳሩ ሳይጎዳ ለዘመናት እንዲቆይ ማድረጉ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀዋል፡፡

 በዩኒስኮ ከማስመዝገቡ ሂደት ጎን ለጎን ወጣቱ ትውልድ አባቶቹ ጠብቀው ያቆዩለትን ይህንኑ መልክአ ምድር ተንከባክቦ ለትውልድ እንዲያስተላልፍ የማስተማሩ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

 ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት በተፈጥሯዊ ሥነ-ምህዳሩ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወጣቱን በንብ ማነብ እና ሌሎች ግብርናን መሰረት ያደረጉ የስራ ዘርፎች ለማሰማራት ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል ፡፡

 የጌዴኦ ዞን ፀጥታና አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ እንግዳወርቅ ዳካ በበኩላቸው ምዝገባው ሀዝቡ በጉጉት የሚጠብቀው በመሆኑ ሂደቱን ለማፋጠን በጋራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

 በባህል ጥባቃ ማህበር የቅርስ ምዝገባ ጥናት ቡድኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መታሰቢያ በቀለ የዩኔስኮን የአሠራር መመሪያ በተከተለ መልኩ እየሠሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

 ጥናቱ ጥልቀት ያለውና በጥንቃቄ መሰራት ያለበት መሆኑ ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደምሮ ሥራውን እንዳዘገየው አስረድተዋል ፡፡

 እየተካሄደ ያለው ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር መታሰቢያ የሚቀሩት ሥራዎች የጋራ አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

 በመጨረሻም ባለድርሻ አካላቱ በመጪዎቹ ስድስት ወራት ቀሪ ሥራዎችን በጋራ ሰርቶ በማጠናቀቅ ለፌዴራል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን