አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 08 September 2017

መቱ ጳጉሜ 3/2009 የመቱ ከተማ አስተዳደር ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዘመናዊ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሸከርካሪ በድጋፍ አገኘች፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ኃይሉ መኮንን እንደገለጹት ድጋፉ የተገኘው "ኢትዮጵያን ፊውቸር ቺልድረን"  ከተሰኘ መንግስታዊ ያልሆነ በጎ አድራጊ ድርጅት ነው።

በድጋፍ የተገኘው ተሸከርካሪ በአንድ ጊዜ 5 ሺህ ሊትር ውሃ የመያዝና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው።

የከተማዋን ነዋሪ ማህበራዊ አገልግሎት ለማዳረስ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሽከርካሪው ከፍተኛ አስዋጽዎ እንደሚኖረውም አመልክተዋል፡፡

አስተዳደሩ በቀጣይ በከተማ ውበት፣ በጽዳትና በቄራ አገልግሎት እንዲሁም በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከሕብረተሰቡና ከሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ተባብሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ ሳላዲን ሰይድ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ድርጅታቸው የከተማዋን ሁለገብ የልማት እንቅስቃሴና እድገት ከግንዛቤ በማስገባት ተሸከርካሪውን መለገሱን ገልጸዋል፡፡

ድርጅቱ ተሸከርካሪውን ያገኘው "ጃይካ"  ከተሰኘ የጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድዎ ድርጅት መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ለቡታጅራና በደሌ ከተሞች ተመሳሳይ የእሳት አደጋ መከላከያ ተሸከርካሪ ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሳላዲን እንዳሉት ድርጅቱ በተጨማሪ ለመቱ "ካርል ሪፈራል ሆስፒታል" የኩላሊት ማጠቢያ የሕክምና መሳሪ  እንዲሁም ለከተማዋ አገልግሎት የሚሰጥ አምቡላንስና የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪ በድጋፍ እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡

በመቱ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ አሰፋ ዲባባ በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በከተማው የእሳት ቃጠሎ አደጋ  ሲከሰት እሳትቱን ማጥፊያ ተሽከርካሪ ባለመኖሩ በቀላሉ መቆጣጠር ሲያዳግት ቆይቷል፡፡

አስተዳደሩ የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሸከርካሪውን ማግኘቱ ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት ከፍተኛ ጥፋት ሳያስከትል ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል።

የመቱ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ ካሉት የሀገሪቱ ከተሞች አንዷ ናት ፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ጋምቤላ ጳጉሜን3/2009 ወጣቱ ትውልድ ለአገሪቱ የህዳሴ ጉዞ መፋጠን ሊተጋ ይገባል - የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች

ወጣቶ ትውልድ የቀደምት አባቶችን የሀገር ፍቅር ስሜት በመላበስ ለአገሪቱ የህዳሴ ጉዞ መፋጠን መትጋት እንዳለበት ኢዜአ ያነጋገራቸው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ወንድሙ መዝሙር እንዳሉት ወጣቱ ትውልድ የቀደምት አባቶችን የሀገር ፍቅር ስሜት በመላበስ አገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጉዞ ለማፋጠን ሊተጋ ይገባል፡፡

''ቀደምት አባቶች በከፈሉት የህይወት መስዋእትነት የተከበረች ሀገር አስረክበውናል'' ያሉት አስተያየት ሰጪው ''የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ድህነትና ኋላቀርነትን በመዋጋት የራሱን ታሪክ ሊሰራ ይገባል'' ብለዋል፡፡

ሌላዋ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ውቢቱ በቀለ በበኩሏ ''የሀገር ፍቅር ቀንን ስናከብር ባለፈው ትውልድ የተሰራውን ታሪክ እያውራን ሳይሆን የራሳችንን ታሪክ ለመስራት ለመትጋት ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል'' ነው ያሉት፡፡

በተለይ በህዝቦች ሙሉ ተሳትፎ የተጀመረውን ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር በማድረስ የቀደምት አባቶችን ታሪክ ሰሪነት በአሁኑ ትውልድ እንዲደገም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ የጀመረችውን የልማት ጎዳና ለማስቀጠል በሚደረገው ርብርብ ወጣቱ በተሰማራበት የስራ መስክ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ ሌላው የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ አቶ ሀፍቶም ተስፋዬ ነው፡፡

ወጣት እወር ኡሞድ በበኩሉ ሀገሪቱ ከነበረችበት ድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ በምታደርገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ገልጿል፡፡

የሀገር ፍቅር ቀንን ከማሰብና ከማክበር ባለፈ ወጣቱ ትውልድ በተሰማራበት የሥራ መስክ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ የሀገሪቱ ህዳሴ ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝቧል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 በአዲስ ዘመን ቋሚ ስራ ብናገኝ አለያም መንግስት ቶ አሰልጥኖን የስራ እድል ቢፈጥርልን በተለያዩ መስኮች ለመሰማራት ዝግጁ ነን ሲሉ በመዲናዋ የተለያዩ ስፍራዎች የሚሞሩ የወጣት ጎዳና ተዳዳሪዎችን አስታወቁ

በጎዳና ህይወት የተሰማሩ አረጋውያን እንደ ወጣቶቹ ሁሉ መንግስት ማህበራዊ ዋስትናቸውን ጠብቆ ቀሪ ዕድሜቸውን በመጦሪያ? ስፍራ ለማሳለፍ በአዲሱአመት ተመኝተዋል።

ከጎዳና ህይወት መውጣት የሚፈልጉት እነዚሁ ዜጎች ወጣቶች በመሆናቸው አላማ እነዳላቸውና ሰርተው መብላት እንደሚችሉም ይናገራሉ የተማሩም ብዙዎች አሉ፤ከፈጣሪ ጋር አዲስ ዓመት የስራ እንዲሆንላቸው ይመኛሉ።

የአዲስ አበባ መንገዶች ከተለያዩ አካባቢዎች በመጡ የጎዳና ተዳዳሪዎች በነዋሪነት አሁንም እያስተናግዱ ነው።

ባገኟት ቦታ የሚችሉትን የሚሞክሩ የመኖራቸውን ያህል ፣ እጃቸውን ለምፅዋት የሚዘረጉ አለያም ደግሞ ሁሉም ይቅርብን ብለው በትካዜ የተቀመጡ በጎዳናው ይኖራሉ።

በዚህ ጎዳና በስራ አሊያም በቦታ እጥረት ለአመታት የሚኖሩ ጥቂት አይደሉም።

ዘመን በዘመን ሲተካ ከጎዳና ህይወታቸው ለመላቀቅ አቅደው አልሳካ ቢላችውም የዛሬውን ብርድና ሃሩር ችለው ነገን ያልማሉ፣ያቅዳሉ፡፡

ኢዜአ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የመዲናዋ ጎዳና ተዳዳሪዎች ከመነሻችን የሚደግፈን ካገኘን በአዲሱ አመት ራሳችንን ለማሻሻል ቁርጠኞች ነን ይላሉ፡፡

መስራት ባለመቻላቸው ራሳቸውን መደገፍ አቅቷቸው እጅ ብቻ ጠብቆ ማደርን አማራጫቸው ያደረጉ አዛውንቶች ተስፋቸውን በወጣቱ ላይ አድርገዋል።

በአገራችን በተለይም በመዲናችን ተምሮም ሆነ የራሱ ሙያ ኖሮት የመስሪያ ቦታና ግብዓቶች የሚያሟላበት አጥቶ ህይወቱን በጎዳና የሚመራ ሰው አልታጣም፡፡

ሆኖም ህይወት በተስፋ የተሞላች ናትና ካለፈው ተምሮ በተለይ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ሙያን አሳድጎና ሰርቶ ራስን ለመቻል ማቀድና መፍጨርጨር አይቀርም፡፡

ተስፈኞቹ የጎዳና ተዳዳሪዎች <<ባለሙያው በሙያው እንዲሰራ ሙያ የሌለው ባለሙያ እንዲሆን ምርኩዝ በማቀበል መንግስትና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ቢያግዘን የመለወጥ፤ የማደግ ህልም አለን>> ነው የሚሉት፡፡

የ75 አመት ዕድሜ ባለጸጋዋ የአዲስአበባ ከተማ ጎዳና ተዳዳሪ እንደሚሉት መንግስት አንድ ነገር ቢያደርግልን ጥሩ ነው፡፡

" እኔ ግን ደካማና አሮጊት ነኝ እና ስለአዲሱ ዓመት እቅድ እንኳ ብዙ የማወጣው ነገር የለም፤ በበኩሌ መንገስት ቢደግፈን ጥሩ ነው፡፡ ወደ መጦሪያ ቤትም ቢያስጠጋኝ እኔ ፍላጎት አለኝ፡፡ልጅ የለኝ፣ጧሪ ቀባሪ የለኝ እና ቢያነሱኝና ደጋፉ ቢሰጡኝ ፍላጎት አለኝ"ይላሉ


---END---

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 ህግ በመጣስ ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ ህንፃዎች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችን ማስቆም አዳግቶኛል ሲል የአዲስ አበባ አስተዳደር የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን አስታወቀ።

በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ ህንጻዎች ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮችን መመልከት የተለመደ ሆኗል።

የኢትዮጵያ የሕንፃ አዋጅ ቁጥር 624/2001 በክፍል ሁለት ቁጥር 18 አዲስ የተገነባ ህንፃ በዚህ አዋጅ መሠረት መስፈርቱን ማሟላቱ በፍተሻ ካልተረጋገጠና የመጠቀሚያ ፈቃድ ካልተሰጠ በስተቀር ህንፃው ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም ይላል።

የባለሥልጣኑ የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ንዑስ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ሊግዲ የተለያዩ ባንኮች ከህጉ አግባብ ውጪ በጅምር ህንጻዎች ላይ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት።

ማንኛውም አካል የህንጻ መጠቀሚያ ፈቃድ ሳይዝ ውል መዋዋል አይችልም፤ ባንኮቹ ግን በራሳቸው ስምምነት ከውክልና ማስረጃ ዕውቅና ውጪ ህንጻዎቹን በመከራየት አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉት አቶ ሙሉጌታ።

የአንድ ህንፃ ግንባታ ሳይጠናቀቅ በከፊል አገልግሎት የሚሰጥበት አግባብ መኖሩን የገለፁት የባለስልጣኑ የመጠቀሚያ ፍቃድ ንዑስ የስራ ሂደት ተወካይ አቶ አስፋው ተስፋዬ ናቸው።

ይህ የሚሆነው ግን የህንጻው ግንባታ ቆሞ ጊዜያዊ የመጠቀሚያ ፍቃድ ሲሰጠው ብቻ ነው ብለዋል።

ባለሥልጣኑ በከተማዋ አገልግሎት እየሰጡ ለሚገኙ 18 የመንግስትና የግል ባንኮች ግንባታቸው ባላለቀ ህንፃዎች ላይ አገልግሎት መስጠታቸውን እንዲያቆሙ ደብዳቤ መፃፉንም ገልፀዋል።

ከመካከላቸውም አራት የግል ባንኮች ከባለሥልጣኑ ጋር በመነጋገር ዳግም በጅምር ህንፃዎች ላይ ተከራይተው አገልግሎት እንደማይሰጡ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ይሁን እንጂ አሁንም በርካታ ባንኮች ከህግና መመሪያ ውጪ በጅምር ህንጻዎች ላይ አገልግሎት መስጠታቸውን መቀጠላቸውንና ባለስልጣኑም ሊያስቆማቸው እንዳልቻለ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙኒኬሽን ተጠባባቂ ስራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ ባንኩ ግንባታቸው ባልተጠናቀቁ ህንጻዎች ላይ አገልግሎት እንደሚሰጥ አምነው በቀጣይ የሚከፈቱ ቅርንጫፎች በተጠናቀቁ ህንጻዎች ላይ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የአዋሸ ባንክ የማርኬቲንግና የኮሙኒኬሸን ዳይሬክተር አቶ አንዱዓለም ኃይሉም የባንኮቹ ቅርንጫፎችን የማስፋትና ህንጻ የማግኘት ፍላጎት ባለመጣጣሙ በጅምር ህንጻዎች ላይ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ቅርንጫፍ ለመክፈት ስናስብ ለአገልግሎቱ የሚሆን በቂ ህንጻ ስለማናገኝ በግንባታ ላይ በሚገኙት ላይ ለመስራት ተገደናል ሲሉ አስተያየት የሰጡት ደግሞ የአቢሲንያ ባንክ የማርኬቲንግና ኮሙኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ታምሩ ናቸው።

በቀጣይ አገልግሎት የሚሰጡባቸው ህንጻዎች በሚጠናቀቁበት አግባብ ላይ ከባለንብረቶቹ ጋር እንደሚነጋገሩና አዲስ የሚከፍቷቸው ቅርንጫፎችም ሙሉ በሙሉ በተጠናቀቁ ህንጻዎች ላይ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 በአዲስ አበባ የሚካሔደውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ወራት ለማስቀጠል የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን ገለጸ።

ፌደሬሽኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ውስጥ የተጀመረውን የደም ልገሳ ተግባር በመደበኛነት ለማስቀጠል በሁሉም ክፍለ ከተሞች የለጋሾች ማህበር መቋቋሙም ተገልጿል።         

የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ወጣት አባይነህ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጸው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ  በተሳታፊም ሆነ በአገልግሎት አሰጣጡ አበረታች ውጤት እየተገኘበት ነው።      

''የተገኘውን ውጤት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በበጋውም ወራት ማስቀጠል ወሳኝ ነው'' ያለው ወጣት አባይነህ አገልግሎቱን  በመደበኛነት ለማስቀጠል የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም አብራርቷል።     

በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የደም ለጋሾች ማህበር የተቋቋመ ሲሆን የማህበሩ አባላት በየ 3 ወሩ ደም ባንክ በመሄድ የሚለግሱበት ስርዓት መዘርጋቱንም ጠቅሷል።    

ከአካባቢ ጽዳት ጋር በተያያዘም በከተማ ደረጃ የተለዩ 43 ቦታዎችን የማጽዳት፣የማስዋብና ለኀብረተሰቡ የማስረከብ ተግባር መከናወኑን የገለጸው ምክትል ፕሬዝዳንቱ በቀጣይም የየአካባቢዎቹ ጽዳት መጠበቁን መከታተል ከተዘረጋው አሰራር መካከል አንዱ ነው ብሏል።   

ከሰብአዊ ድጋፍ አኳያም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመተባበር ፈቃደኛ ወጣቶች ከራሳቸው ገንዘብ እንዲቆረጥና ለተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች እንዲለግሱ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁማል።    

የኩላሊትና የካንሰር ህሙማን ህክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ገልጾ 200 አባላትን የያዘ ''በኩላሊት መሞት ይብቃ'' የተሰኘ ማህበር መቋቋሙንም ተናግሯል።

ከማህበሩ አባላት ለኩላሊት እጥበት  የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የማዋጣትና የማሳከም ሥራም እንደሚከናወን ነው ያብራራው። 

''የበጎ ፈቃድ ሥራ ክፍያው የህሊና እርካታ ነው ያለው'' ወጣት አባይነህ ለጋሽ ድርጅቶች፣የመንግሥት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ለበጎ ፍቃድ አገልገሎት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሟላት በኩል ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርቧል።  

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶች ንቅናቄና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ የኋላሸት ሰኢድ በበኩላቸው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በበጋውም ወራት ለማስቀጠል ቢሮው ከገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ግብዓቶችን ለማሟላት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በክረምት የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ፣የማጠናከሪያ ትምህርት የመስጠት ፣ የኤች አይ ቪ ምርምራና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በበጋውም ወራት ማከናወን ዋና ዋና ተግባራት መሆናቸውንም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ላለፉት 15 ዓመታት በችግኝ ተከላ፣በትራፊክ አገልግሎት፣በአረጋውያን እንክብካቤ፣በክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት፣ደም ልገሳን ጨምሮ በ13 ዘርፎች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል።  

Published in ማህበራዊ

ጳጉሜን 3/2009 አብሮ የመኖር የቆየ እሴታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ የተመዘገቡ በጎንደር አካባቢ የሚገኙ የአማራና የቅማንት ተወላጆች ተናገሩ።

የአማራና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው በዞኑ 12 ቀበሌዎች የፊታችን መስከረም 7 2009 ዓ.ም ለሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እየተካሄደ ነው።

በጎንደር ከተማ አመድጌ ምርጫ ጣቢያ በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ በመራጭነት የተመዘገቡት የአማራ ተወላጅ ወይዘሮ አበባ አደም “ከህዝበ ውሳኔውም በኋላ ቢሆን የአብሮነቱ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ሙሉ እምነት አለኝ” ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላው የአማራ ተወላጅ የሆነው ወጣት ለምለሙ ተበጀ በበኩሉ በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ የመራጭነት ካርድ መውሰዱን ተናግሮ ህዝበ ውሳኔው የሁለቱም ህዝቦች ህገ-መንግስታዊ መብት በመሆኑ አከብረዋለሁ ብሏል።

“የቅማንት ህዝቦች ቋንቋችን ባህላችን ማንነታችንና የራስ አስተዳደር መብታችን ይከበር ብለው መጠየቃቸው ዴሞክራያዊ መብታቸው ነው” ያለው ወጣት ለምለሙ ህዝበ ውሳኔውን እቀበለዋለሁ ብሏል።

የቅማንት ተወላጅ የሆኑት አቶ ጌትነት አያናው በበኩላቸው “አማራና ቅማንት ለረጅም ዘመናት አብረው የኖሩ የተዋለዱና የጋራ ማህበራዊ እሴት የገነቡ እንደመሆናቸው ህዝበ ውሳኔውም ቢሆን የሁለቱ ህዝቦች የጋራ ስምምነት ውጤት ነው” ብለዋል፡፡

ህዝበ ውሳኔው የሁለቱን ህዝቦች ዘላቂ አንድነትና መተማመን የሚያስቀጥል እንጂ በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያዎች እንደሚናፈሰው አንዱን ተጠቃሚ ሌላውን ተጎጂ ለማድረግ አለመሆኑንም ተናግረዋል።

ወጣት ሙሉነሽ በለጠ የቅማንት ተወላጅ ስትሆን በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ ተመዝግባ የመራጭነት ካርድ መውሰዷን ተናግራ የምዝገባ ሂደቱ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን መመልከት መቻሉዋን ገልጻለች፡፡

የአመድጌ ምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ገመዳ በምርጫ ጣቢያው የአማራም ሆነ የቅማንት ተወላጆች በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ የድምጽ ሰጪነት ካርድ ተመዝግበው እየወስዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አራተኛ ቀኑን በያዘው የመራጮች ምዝገባም 708 ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን ጠቁመው በምርጫ ጣቢያው 989 ነዋሪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የጎንደር ከተማ ምርጫ አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ ነጋሳ እንደገለጹት በከተማው ክልል በሚገኙ ገጠር አካባቢዎች በተቋቋሙ 3 ምርጫ ጣቢያዎች በየጊዜ ሰሌዳው መሰረት የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ ነው።

“በሶስቱ ምርጫ ጣቢያዎች እስከ አሁን 1ሺ 814 ድምጽ ሰጪዎች የመራጭነት ካርድ ወስደዋል” ያሉት አስተባባሪው እስከ ምዝገባው ማብቂያ እለትም 2ሺ 200 ድምጽ ሰጪዎች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 አዲሱን ዓመት ስንቀበል ባለፉት አስር ዓመታት አገሪቷ ለጀመረችው የሠላምና የዕድገት ጉዞ እውቅና በመስጠት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስታወቀ፡፡

ጉባዔው በላከው መግለጫ እንዳመለከተው '' መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው '' በማለት ለመላው ህብረተሰብ መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

ለመጪው ትውልድ  የሚሆን አገር ለመገንባትና ቀድሞ ወደነበርንበት ከፍታ ለመመለስ የጀመርነው ትግል የሚታይና የሚጨበጥ ፍሬ በማፍራቱ ቀጣዩ ዘመን '' ለኢትዮጵያ የከፍታዋ ዘመን " መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

በተጀመረው ጉዞ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የዓለም ዓቀፉን ኀብረተሰብ በተግባር ማሳመን ችለናል ሲል መግለጫው አብራርቷል፡፡

ሆኖም የተገኙትን ድሎች በማስፋት ከድህነትና ከኃላቀርነት ጋር የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ነው ያስገነዘበው፡፡

ለዚህ ደግሞ መሠረቱ ዘላቂ ሠላምና የሕዝቦች መተማመን በመሆኑ ሁሉም ለዚህ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ ነው በመግለጫው የተጠቆመው፡፡

ከፍታው የተገኘው በሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች፤ በመላው ሕዝብና  ሠላም ወዳዶች ብርቱ ጥረት በመሆኑ ምስጋናና አክብሮት የላቀ ነው፡፡

መጪውን ዘመን በአንድነት ወደ ቀድሞ ከፍታ ለመመለስ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ጉባዔው ለኢዜአ በላከው መግለጫ አሰታውቋል፡፡

Published in ማህበራዊ

በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአገሪቱ ያለው የጸጥታ ጥበቃ ሥራ በሶማሊያ የጸጥታ ኃይል ኃላፊነት ሥር መሆን እንዳለበት ተጠቆመ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በመተባበር በአፍሪካ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በአዲስ አበባ እየመከረ ነው።

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ሠራዊት /አሚሶም/ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2007 ጀምሮ በሶማሊያ የተቀሰቀሰውን የጸጥታ ችግር እልባት ለመስጠት ሲሰራ ቆይቷል።

ከመጀመሪያ ጀምሮ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት በውይይት እንዲፈታና በኃይል የሚፈጠሩ ግጭቶችንም እርምጃ በመውሰድ በአገሪቱ መረጋጋት እንዲኖር ለማድረግ አግዟል።

በሌላ በኩል ከአል ቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ የሚጠቀሰውን የሽብር ቡድን 'አል ሸባብን' ለመዋጋት በሶማሊያ ብሎም በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ጥረት ማድረጉ ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅትም በሶማሊያ በፖለቲካው ዘርፍ ለተመዘገቡት አጠቃላይ ውጤቶች የአሚሶምና ሠራዊት የሚያዋጡ አገራት ጥረት የላቀ መሆኑም የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

በአፍሪካ ኅብረት የመንግሥታቱ ድርጅት የዋና ጸኃፊው ተወካይ አቶ ኃይለ መንቆሪዮስ "እነዚህ አካላት ጥረት ባያደርጉ ኖሮ በሶማሊያ አሁን የተገኘው ውጤት አይመጣም ነበር" ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የደህነት ኮሚሽነር አምባሳደር እስማኤል ቼርጓይ በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ በፖለቲካውና በደህነት ዘርፍ የተሻለ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ ከወራት በፊት የመንግሥታቱ ድርጅትና አፍሪካ ኅብረት የአገሪቱ የፀጥታ ጥበቃ ሥራ በሀገሪቱ የጸጥታ አካላት ሥር መሆን እንዳለበት መስማማታቸውን ጠቁመዋል።

ይህም ለአገሪቱ ብሔራዊ (ውስጣዊ) አስተዳደር አጽንዖት ለመስጠት መሆኑን ነው የገለጹት። ይህም ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን የቅንጅት ሥራው በመንግሥታቱ ድርጅትና በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም በሌሎች ባለድርሻ አካላት መካሄድ እንዳለበት አስረድተዋል።

ሶማሊያን አንደገና ለማቋቋም በሚደረገው የረጅም ጊዜ ጥረት ውስጥ የአገሪቱ ዜጎች ተሳታፊ ሊሆኑ እንደሚገባም አምባሳደር እስማኤል ጠቁመዋል።

ያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ በሥራ ላይ ለሚገኘው ለአሚሶም የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ዘለቂ እንዲሆን ለማስቻል ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

አምባሳደር እስማኤል ቼርጓይም ሰላምን ለማስፈን የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ኃብቶችን በበቂ ሁኔታ ለማሟላ ሁሉም አካላት ይበልጥ ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በሌላ በኩል በቻድ ሸለቆ አከባቢ ያሉ አገራት ቦኮ ሃራም የተሰኘውን የሽብር ቡድን ለመዋጋት ወታደሮችን በማሰማራት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም የጋራ ጥረት ቦኮ ሃራምን በማዳከም ቀድሞ በሽብር ቡድኑ ቁጥጥር ሥር የነበሩ ቦታዎች በአሁኑ ወቅት ነጻ ሊወጡ መቻላቸውን አምባሳደሩ ጠቅሰዋል።

በተመሳሳይ የመንግሥታቱ ድርጅት በቀጣናው አገራት እየተሰራ ያለውን ተግባራት በማድነቅ በቀጣይ በቅንጅት ለመሥራት መረባረብ አንደሚገባ የዋና ጸኃፊው ተወካይ አሳስበዋል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሃሴ 3/2009 በበጀት ዓመቱ ሥራ የሚጀምሩ የስኳር ፋብሪካዎች የአገር ውስጥ ፍጆታውን በማሟላት ወደ ውጭ የመላክ አቅም እንደሚፈጥሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ ሥር የሚገኙ የልማት ኮርፖሬሽኖች በኢንዱስትሪ ፓርኮች በሚሳተፉበት ሁኔታ ዙሪያ ዛሬ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት የአገር ውስጥ የስኳር ፍጆታን በማሟላት በበጀት ዓመቱ በቋሚነት ወደ ውጭ መላክ ይጀመራል።

መንግስት በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ስኳር ወደ ውጭ ለመላክ እየሰራ የነበረ ቢሆንም በተፈጠረው የቅንጅት ጉድለት ላለፉት ሁለት ዓመታት ማሳካት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

የመዘግየቱ ችግር የተፈጠረው በተለያዩ አካላት የሚከናወኑ የፋብሪካ ግንባታ፣ የአገዳና መስኖ ልማትና የመሰረተ ልማት ሥራዎች  በቅንጅት ባለመሰራታቸውና አንዱ በጊዜ ገደቡ ሲያጠናቅቅና ሌላው ስራውን ሲያጓትት መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ የአንድ ፋብሪካ የተለያዩ ግንባታዎች በቅንጅት እንዲሰሩ ለማድረግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት የኦሞ ኩራዝ ሁለት ፋብሪካ ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ለማምረት ዝግጁ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካም የአገዳ ልማት ሥራ በመሰራቱ በመጪው ጥቅምት ማምረት ይጀምራል ብለዋል።

ከእነዚህና ከሌሎች ስኳር ፋብሪካዎች በሚገኘው ምርት በተያዘው በጀት ዓመት የአገር ውስጡን ፍጆታ በማሟላት ወደ ውጭ መላክ ይጀመራል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት የገበያ ጥናት ለማድረግ የተወሰነ ምርት ወደ ኬንያ መላኩን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 300 ሺህ ቶን ስኳር ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ጠቅሰው በዚህ ዓመት እንዲገባ የታዘዘው የስኳር መጠን ወደ 50 ሺህ ቶን ዝቅ ማለቱን አክለዋል።

ፋብሪካዎቹ ከውጭ የሚገባውንና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውለውን ስኳር ማምረት እንዲችሉ ተደርገው መገንባታቸውንም ገልፀዋል።

በአገር ውስጥ የሚመረተውን ስኳር ለኢንዱስትሪ በሚውል መልኩ አዘጋጅተው ወደ ውጭ የመላክ ፍላገት ካላቸው ባለሃብቶች ጋርም ተፈራርመናል ብለዋል።

ከስኳር ፋብሪካዎች የሚወጡ ተረፈ ምርቶች ለሌሎች ፋብሪካዎች ግብዓት እንዲሆኑ ለማድረግ ፋብሪካዎቹ ባሉበት አካባቢ የአግሮ ኢንዱስትሪዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ይህም የፋብሪካዎቹን አቅም አሟጦ ለመጠቀም ታስቦበት እየተሰራ ያለ መሆኑን ነው ያብራሩት ሚኒስትሩ።

በውይይቱ ለማህበረሰቡ ፍጆታና ለኢንዱስትሪዎች የሚውል በቂ የስኳር ምርት በአገር ውስጥ በመሸፈን የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚያስቀር በመሆኑ በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበት ተነስቷል።

በ2010 በጀት ዓመት ነባሮቹን ጨምሮ ስምንት የስኳር ፋብሪካዎች ማምረት እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የህክምና ኮሌጅ ለሁለት ቀናት ነጻ የጤና ምርመራ አገልግሎት ሊሰጥ መሆኑን ገለፀ።

የኮሌጁ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነዋይ ፀጋዬ ለኢዜአ እንደገለፁት ኮሌጁ በመድኃኒአለም መሰናዶ ትምህርት ቤት ለሁለት ቀናት አጠቃላይ የጤና ምርመራ አገልግሎት በነጻ ለመስጠት ዝግጅቱን አጠናቋል።

ነገና ከነገ በስቲያ የሚሰጠው የምርመራ አገልግሎት በዋናነት የጉበት ፣ የአይን ፣ የኤች. አይ. ቪ/ ኤድስ ፣ የስኳር ፣ የደም ብዛትና የመሳሰሉትን ያካተተ እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚሁ መሰረት ቅዳሜ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 11 ሰዓት እሁድ ደግሞ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 6 ተኩል ምርመራው እንደሚሰጥና በነዚሁ ቀናት ውስጥ እስከ 2 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች አገልግሎቱን ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

ኮሌጁ ከዚህ ቀደም ነፃ የኤች. አይ. ቪ/ ኤድስ ምርመራ ይሰጥ ነበር ያሉት ዳይሬክተሩ አጠቃላይ የጤና ምርመራ ዘመቻ ሲያካሂድ ግን የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብለዋል።

ለምርመራው 20 ባለሙያዎችና አስፈላጊ መሳሪያዎች እንደተዘጋጁ አቶ ነዋይ አመልክተው ኀብረተሰቡ በየዓመቱ አጠቃላይ የጤና ምርመራ የማድረግ ልምድ ሊያዳብር እንደሚገባም ነው የመከሩት።

ሕብረተሰቡ ሲታመም ብቻ ወደ ጤና ተቋም እንደሚሔድ ገልፀው ይህንን እድል በመጠቀም ኀብረተሰቡ ስለጤናው እንዲያውቅና ራሱን ከበሽታ እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 6

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን