አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Thursday, 07 September 2017

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009  እውቁ የአፈር ተመራማሪ ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ በህክምና ሲረዱ ቆይተው በ61 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

 አስክሬናቸው ከውጭ አገር በነገው ዕለት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የሥራ ባልደረቦችና ወዳጅ ዘመዶቻቸው አቀባበል እንደሚያደርጉላቸው የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር ለኢዜአ ገልጿል።

 የቀብር ሥነ-ሥርዓቱም ቅዳሜ ጳጉሜ 4 ቀን 2009 ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት በመንበረ ፀባዖት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዓለማየሁ ብርሃኑ ገልጸዋል።

 እ.ኤ.አ በ1985 በአፈር ኬሚስትሪ እና ለምነት ከስኮትላንዱ አበርዲን ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል።

 እ.ኤ.አ ከ1985 እስከ 1999 ከፍተኛ ተመራማሪና የምርምር ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል።

 እ.ኤ.አ በ2004 የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ ከ2004 እስከ 2005 የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ፣ ከ2005 እስከ 2010 ደግሞ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪና የግብርና ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

 ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ በአፈር ኬሚስትሪና ለምነት፣ በሰብል ጥናት፣ የአፈር መረጃ እና መሰል ጉዳዮች ላይ ከ75 በላይ ሳይንሳዊ ጽሑፎችንና እና መጽሐፎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አሳትመዋል።

 ተመራማሪው የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ኃብት ጆርናል መስራችና ዋና አዘጋጅ ሆነውም አገልግለዋል።

 በአገር ውስጥና በሌላው ዓለም በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሁለተኛ እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር የሙያ ግዳታቸውን ተወጥተዋል።    

 ፕሮፌሰር ተካልኝ የኢትዮጵያ የአፈር ሳይንስ ሶሳይቲ ተጠሪ ሆነው በሰሯቸውት በርካታ ምርምሮች ከአሜሪካው ባዮግራፊካል ኢንስቲትዩት "የስዊስ ትራንስ-ዲሲፒሊነሪ" ሽልማትና እውቅና አግኝተዋል።

 በ2016 የአፈር ለምነትና የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ላይ ባደረጓቸው ምርምሮች 11 ሚሊዮን የሚሆኑ በአነስተኛ ግብርና ላይ የተሰማሩት አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

 በዚህም የመሬት መሸርሸርን በመከላከሉ ረገድ፣ የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስና የሰብል ምርታማነትን ማሳደግ ላይ የላቀ ሚና ነበራቸው።

 በዚህም "ኖርማን ቦርላውግ" የተሰኘ ዓለም አቀፍ ሽልማት አግኝተዋል።    

 በአገሪቷ በአፈርና የአፈር ለምነት መረጃ አያያዝ ላይ ባበረከቱት የምርምር ውጤት ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል።

 ተመራማሪው እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ ዋስትናና የግብርና ዓለም አቀፍ ኮሚሽነር ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ። 

 በቅርቡም የአፈር ጤናና ለምነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የአምስት ዓመታት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለመንግሥት አቅርበዋል።

 ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ በተለይ የአፈር መረጃ እንዲደራጅ ከማድረጋቸውም ባለፈ፤ አርሶ አደሩ ለምርት የሚጠቀመው ማዳበሪያ የየአካባቢውን አፈር መሰረት ያደረገ እንዲሆን የላቀ ሚና መጫወታቸውን ከእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ ሞሮኮ በሚገኘው አንድ ዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ውስጥ ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ እንደነበሩ አቶ ዓለማየሁ ገልጸዋል።

 ፕሮፌሰር ተካልኝ ማሞ ባለ ትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ። 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009 የዘመን መለወጫን በዓል ምክንያት በማድረግ የሚካሄደው የእንስሳት እርድ በጥንቃቄ እንዲከናወን የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር አሳሰበ።

በበዓሉ እለት የሚከናወኑት የእንስሳት እርዶችን በጥንቃቄ በማድረግ ከቆዳና ሌጦ ዘርፍ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ እንዳይቀንስ መጣር እንደሚገባ ዛሬ በተሰጠው መግለጫ ተመልከቷል።

ቆዳና ሌጦ በባሕላዊ መንገድ ለኅብረተሰቡ ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ በአገሪቷ ለሚገኙ ከ25 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች ዋነኛ ግብዓት በመሆን ለአገሪቷ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ጥሬ እቃ ነው።

የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ  እንደገለጹት፤ አገሪቷ በዘርፉ የውጭ ምንዛሪ እያገኘች ቢሆንም ካላት ሀብተ አኳያ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት አልተሰራም።

በበዓላት ወቅት እንስሳትን ከእርድ በፊት ፤ በእርድ ወቅትና በኋላ በጥንቃቄ በመያዝ የአገሪቷን የውጭ ምንዛሪ ከፍ ለማድረግ መስራት እንደሚጠበቅ ነው ያስገነዘቡት።

"እንስሳት በህይወት እያሉ ተገቢውን እንክብካቤ በማድረግ ጤናቸው የተስተካከለ እንዲሆን፤ በቆዳቸው ላይም ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

በበዓላት ወቅት 70 በመቶ የሚሆነው የእንሳት እርድ የሚከናወነው በቤትና በመንደር ውስጥ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በሌጦዎችና ቆዳዎች ላይ የመቀደድ፣ የመሳሳት አደጋ እንደሚደርስ ገልፀዋል፡፡

የመንደር እርድ በሚከናወንበት ወቅት ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች እንዳይከሰቱ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግም ነው የጠቆሙት፡፡

እንስሳት ከታረዱ በኋላ እስከ ሶስት ሰዓት ባልበለጠ ጊዜ በአካባቢ ለሚገኙ ሕጋዊ ነጋዴዎች በማስረከብ "ከቆዳና ሌጦ ሀብታችን ትሩፋት እናሳድግ" ብለዋል፡፡

 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገሪቷ የቁም እንስሳት ከብቶችን ወደ ውጭ በመላክ ስድስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ሀዋሳ ጳጉሜ 2/2009 በደቡብ ክልል ባለፉት አስር ዓመታተ የከተሞች ቁጥር ከሶስት እጥፍ በላይ ማደጉን የክልሉ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ አስታወቀ ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ክፍሌ ገብረማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት በሚሊንየሙ መጀመሪያ 2000 ዓ.ም ላይ 99 የነበረው የክልሉ ከተሞች ቁጥር አሁን ላይ 427 ደርሷል።

ከተሞቹ በአስተዳደራዊ መዋቅርና በደረጃቸው የሚለያዩ ቢሆኑም ተወዳዳሪና ለኑሮ ተስማሚ እዲሆኑ በፕላን እንዲመሩ መደረጉን ተናግረዋል ።

በክልሉ የከተሞች መስፋፋትን ተከትሎ የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመመለስና የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት መከወናቸውን ተናግረዋል።

በተለያዩ ከተሞች  ከ1999 እስከ 2007 ዓ.ም በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ 8 ሺህ 861 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተገንብተው ለተጠቃሚ መተላለፋቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል ።

"የከተሞችን የአረንጓዴ ገጽታ ለመጠበቅ በተሰራ ስራም በከተሞች በዓል ተሸላሚ የሚሆኑ ከተሞችን ለመፍጠር ተችሏል " ብለዋል ።

ከዚህ ባለፈም የከተሞችን እድገት ተከትሎ በተፈጠሩ የስራ እድሎች 1 ሚሊዮን 8 ሚሊዮን ዜጎች በቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

በተጨማሪም በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በተለያዩ የቤቶች ልማት መርሀ ግብሮች በማህበር፣ በኢንዱስትሪ ፓርክና በግል ይዞታ 4 ሺህ 574 ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል ።

"ባለፉት ሁለት ዓመታት በማህበርና በመምህራን ቤት ልማት ከ1 ሺህ በላይ ማህበራት የተደራጁ ሲሆን 363 የግንባታ ቦታዎች ተዘጋጅተው 147 ቤቶች በግንባታ ላይ ናቸው "ብለዋል።

በማህበር ለሚደራጁና ጥያቄ ለሚያቀርቡ የህብረተሰብ ክፍሎች የግንባታ መሬት ተዘጋጅቶ እንደሚቀርብም ገልጸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ጳጉሜ 2/2009 በምዕራብ ጎጃም ዞን በዘንድሮው የክረምት ወቅት በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተተከለው ከ130 ሚሊዮን በላይ የዛፍ ችግኝ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገለት ነው፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ እንዳለው ችግኙ እንክብካቤ  እየተደረገለት ያለው በተጎዳና በበጋ ወራት የተፈጥሮ ሃብት በተሰራበት 25 ሺህ 450 ሄክታር መሬት ላይ ነው፡፡

የደን መራቆትና መመናመን በአካባቢው እያስከተለ ያለውን ተፅዕኖ ለመቀነስም በየዓመቱ በአርሶ አደሩ የሚተከሉ የደን ችግኞችን ተንከባክቦ የማሳደግ ልምዱ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በክረምት ወቅት ተተክሎ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገለት የሚገኘው የዛፍ ችግኝ የዞኑን የደን ሽፋን ከነበረበት 21 ነጥብ ስድስት በመቶ ወደ 23 ነጥብ ሰባት በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ አቢዮት ብሩ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከተተከለው ችግኝ ውስጥም  ወይራ፣ ዋንዛ፣  ኮሶ፣  ዝግባ፣ ግራርና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ይገኙበታል፡፡

ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ለምነቱ በተሟጠጠ አምስት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ከ50 ሺህ በላይ የዛፍ  ችግኝ ተክለው እያሳደጉ መሆናቸውን የተናገሩት  በሰከላ ወረዳ የሱርባ ቢፈታ ቀበሌ  አርሶ አደር የእኔዓለም በዛም ናቸው፡፡

በዞኑ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት ከተተከለው የደን ችግኝ ከ81 በመቶ በላይ ፀድቆ በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in አካባቢ

ነቀምቴ  ጳጉሜ 2/2009  በምሥራቅ ወለጋ ዞን በዘንድሮው  የክረምት ወቅት ከ300 ሚሊዮን በላይ የእንስሳት መኖ ችግኝ መተከሉን የዞኑ የእንስሳት እና ዓሣ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

 በጽህፈት ቤቱ የእንስሳት መኖ ባለሙያ አቶ ደረጀ ከበደ እንደገለጹት በበጋ ወቅት የሚከሰተውን የግጦሽ እጥረት ለመቋቋም  በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች የእንስሳት መኖ ችግኝ ተተክሏል፡፡  

 በክረምቱ ወራት እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም ከተተከሉት መካከል ሰስባኒያ፣ሉሲኒያ፣ ሮደስና የዝሆን ሣር የተባሉ ዝሪያዎች ይገኙበታል።

 የተከለው ችግኝ  በ19 ሺህ 887 ሄክታር መሬት እየለማ መሆኑን  ጠቁመው አፈጻጸሙም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ18 ሚሊዮን ችግኝ ብልጫ  እንዳለው  ነው ባለሙያው ያመለከቱት።

 ባለሙያው እንዳሉት በዞኑ በእንስሳት መኖ ልማቱ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት 223 ሺህ አርሶ አደሮች መካከል 38 ሺህ ያህሉ  ሴቶች ናቸው፡፡

 በዞኑ በልማቱ እጸየሸታፉ  ካሉት መካከል የጉቶ ጊዳ ወረዳ ጋሪ ቀበሌ አርሶ አደር ያደሣ ኢታና በሰጡት አስተያየት እያጋጠማቸው ያለውን የግጦሽ እጥረት ለማቃለል ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ የመኖ ችግኝ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 ዘንድሮ ደግሞ በግማሽ ሄክታር መሬት ላይ የዝሆን ሣርና ደሾ የተባሉ ዝርያዎች ተክለው እየተንከባከቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም ለከብቶቼ በቂ ቀለብ ለማቅረብ እንደሚረዳቸው ነው የገለጹት፡፡

 በዲጋ ወረዳ የአርጆ ጉደቱ የገጠር ቀበሌ አርሶ አደር ለታ ቱጌ በበኩላቸው በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የእንስሳት መኖ በማልማት  ሁለት የወተት ላሞችን እያረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009 አርባ ስድስት አገሮችን በሞተር ሳይክል ለማቋረጥ ጉዞውን የጀመረው ኦማናዊው አል ባርዋኒ አዲስ አበባ ገብቷል።

 ሞተር ሳይክለኛው የተለያዩ አገሮችን በማቋረጥ በሱዳን በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል።

 ተጓዡ በኢትዮጵያ የኳታር ኤምባሲ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን፤ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2009 ጀምሮ እስካሁን 110 ሺህ ኪሎ ሜትርና 30 አገሮችን  አቋርጧል።

 በቀጣይ ከአራት እስከ ስድስት ወራት ውስጥ  ያቋረጣቸውን አገሮች ወደ 46  ከፍ በማድረግ  አዲስ ክብረወሰን ለማስመዝገብ አቅዷል።

 ሞተር ሳይክለኛው አል ባርዋኒ በሰጠው አስተያየት ጎዞው ጥሩ ቢሆንም አገራቱ ድንበር ላይ ፈታኝና አስቻጋሪ ጎዞ እንዳደረገ ተናግሯል።

 በኢትዮጵያ የተደረገለት አቀባበል የተለየ እንደሆነበት ጠቅሶ አገሪቷን በመጎብኘቱ  ቀደም ሲል የሰማቸው አሉታዊ አመለካከቶች የተሳሳቱ እንደነበሩ ለመረዳት  እንደቻለ ተናግሯል።

 በተለይም አገሪቷ እያደገች መሆኗንና ለማየት  በመቻሉ በቀጣይ ጓደኞቹ አገሪቷን እንዲጎበኙ የራሱን ጥረት እንደሚያደርግ አብራርቷል።

 አል ባርዋኒ ያለውን ልምድና ክህሎት ለተለያዩ  አገሮች ማካፈል እንደቻለ ተናግሮ፤ አብዛኛው የጉዞው  ክፍል አፍሪካን የሚሸፍን መሆኑን ተናግሯል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009 የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባር በማለት ራሱን የሚጠራውን አሸባሪ ቡድን ጨምሮ እንደ ኦብነግና አልሸባብ ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት እንደሚዋጋ የሶማሊያ መንግስት ገለጸ።

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንደገለጸው በጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ካይሬ የተመራው የሶማሊያ መንግስት ካቢኔ ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ራሱን የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር በማለት የሚጠራው አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ላይ የሚያደርገውን እኩይ ተግባር ሶማሊያ እንደምትዋጋ ገልጿል።

 ሶማሊያ የአሸባሪዎች መደበቂያ እንዳትሆን የአገሪቱ መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወስድም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

 በአሚሶም ጥላ ስር በሶማሊያ የተሰማራው የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል በአገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን እየፈፀመ ላለው ጀግንነት የተሞላበት ተልዕኮ ካቢኔው አክብሮቱን ገልጿል፡፡

 በቅርቡ የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የድርጅቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራር የነበረው አብዱልከሪም ሼክ ሙሳ ድርጅቱን በመተው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ይታሳል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደብረብርሃን  ጳጉሜ 2 /2009 ያለፉት አስርት ዓመታት ደብረ ብርሃን ከተማ በኢንዱስትሪና መሰረተ ልማት ዘርፎች እምርታ ያስመዘገበችበት ዘመን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

 የከተማ አስተዳደር በበኩሉ በእነዚህ ዓመታት ከ13 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ 382 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በከተማዋ ተመዝግበው ወደሥራ መግባታቸውን አስታውቋል።

 በከተማው የቀበሌ 08 ነዋሪ አቶ አለማየሁ ወንድወሰን ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከአስር ዓመት በፊት በመሰረት ልማት ዘርፍ ከተማዋ ከአዲስ አበባ ወደወሎና መቀሌ አልፎ የሚሄደው የአስፓልት መንገድና አንድ የብርድልብስ ፋብሪካ ብቻ ነበራት።

 "ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአይነትም ሆነ በቁጥር ብዙ ኢንዱስትሪዎች ከመስፋፋታቸው በተጨማሪ መሰረተ ልማቶች  እየተሟሉ መምጣታቸው ከተማዋ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለሃብቶች ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል" ብለዋል።

 የደብረ ብርሃን ዩንቨርሲቲን ጨምሮ በግልና በመንግስት የተከፈቱ በርካታ ኮሌጆች መኖራቸው የኢንዱስትሪዎችን የሰው ኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለንግድ እንቅስቃሴው መፋጠን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል

 በደብረብረሃን ከተማ ቀበሌ 06 መወለዳቸውንና በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እንደሚኖሩ የገለጹት አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ በበኩላቸው ከተማዋ ከአስር ዓመት በፊት ጥንታዊነቷን እንጂ ዘመናዊነት የማይስተዋልባት ከተማ እንደነበረች አስታውሰዋል

 "አሁን ላይ መንግስት ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚያደርገው ሽግግር ከተማዋ በኢንዱስትሪ ማዕከልነት መሳያ እየሆነች መጥታለች" ሲሉ ገልጸዋል።

 ከዓመታት በፊት ከተማዋን አቋርጦ የሚሄድ መንገድ ብቻ አንደነበራት አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ዋናው መንገድ ደረጃውን ጠብቆ ከመሰራቱ በተጨማሪ ሌሎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ተገንብተው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

 በየአካባው ዘመናዊ ህንጻዎች ብቅ በቅ ማለት እንደጀመሩም ጠቁመዋል።  

 በደብረብረሃን ከተማ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው በበኩላቸው ባለፉት 10 ዓመታት ከ13 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ 382 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መመዝገባቸውን ተናገረዋል።

 በኢንዱስትሪ መንደር ከገቡት 180 ፕሮጀክቶች መካከል በጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ በምግብና መጠጥ  ማቀነባበሪያ፣ በብረታ ብረት፣ በቆዳና ሌጦ፣  በኮንስትራክሽን መሳሪያ ማምረትና ሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ 19  ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገራቸውን አስረድተዋል።

 ዘጠኝ ኢንዱስትሪዎች በመጪው መስከረም ወር ማምረት  እንሚጀምሩ ጠቁመው በአገልግሎት፣ በግብርናና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩት ፕሮጀክቶችም በአጠቃላይ 337 ሄክታር መሬት መሰጠቱን አስገንዝበዋል።

 የከተማዋ እድገት በየዓመቱ እየተፋጠነ በመምጣቱም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 12 ሺህ 866 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለበት ደረጃ ላይ መደረሱን ገልጸዋል።

 በከተማዋ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎም  የሚኖረው ሕዝብ ቁጥር በየጊዜው ከሚገመተው በላይ እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።

 በደብረ በርሃን ከተማ ባለፉት አሥር ዓመታት የተመዘገበውን ውጤት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገርም በአሁኑ ወቅት በፌደራል መንግስት በ106 ሄክታር መሬት ላይ የኢንዱስትሪ ፓርከ ግንባታ መጀመሩንም አቶ ዳምጠው ተናገረዋል።

 የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ አስፋቸው ደስታ በበኩላቸው፣ ከአስር ዓመት በፊት ከአንድ ኪሎ ሜትር በታች የነበረው የከተማዋ የአስፓልት መንገድን በአሁኑ ወቅት ከስድስት ኪሎ ሜትር በላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

 ከእዚህ በተጨማሪም 27 ኪሎ ሜትር የጠጠርና ስምንት ኪሎ ሜትር የኮብል ስቶን መንገድ ግንባታ ሥራ በከተማዋ ውስጥ መካሄዱንና ያለውን የመብራት እጥረት ለመቅረፍ የንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009 በኢትዮጵያ የሚገኙ 12 አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ ጋር ለመደራደር የሚያስችላቸውን ጥምረት ፈጠሩ።

 የጋራ ስምምነት ሰነዱ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መልካም ግንኙነት ለመፍጠርና የተደራጀ ጠንካራ መደራደሪያ ሃሳብ ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል።

 በአገሪቷ ያለውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ለማጎልበት "ወሳኝ ሚና ይኖረዋል" ብለው በፈጠሩት ጥምረት ዙሪያ ዛሬ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

 የመላው ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ዘመኑ ሞላ እንዳሉት፤ ጥምረቱ ዲሞክራሲን ከጽንሰ ሃሳብ ባለፈ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ ሃሳቦች ይስተናገዱበታል።

 በድርድሩ ወቅት እርስ በእርስ በመከባበር፣ በመግባባትና በመቻቻል፣ በእውቀትና በመረጃ የተደገፈ ሀሳብ በማቅረብ "የሃሳብ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያስችላል" ብለዋል።

 በድርድሩ ወቅት የውይይት ጊዜውን ተገቢና አግባብ በሆነ መንገድ መጠቀም አስፈላጊነቱን ያወሱት አቶ ዘመኑ በዚህም የሰጥቶ መቀበል መርህ ትርጉም ያለው ውጤት እንደሚያመጣ እንደታመነበት ገልጸዋል።

 የተደራደሩበትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅ ጨምሮ ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ በሆኑ 12 የመደራደሪያ ሃሳቦች ላይ በስፋት ተወያይቶ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

 የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ  እንደገለጹት፤ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ዜጎች በመረጡት ድርጅት እንዲመሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ መንግስትና ገዥው ፓርቲ ቁርጠኛ መሆን ይኖርባቸዋል።

 የፖለቲካ ተሳታፊዎች በነፃነት በአደባባይ እንዲንቀሳቀሱ፣ የታፈኑ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ፣ በህግ የበላይነት የሚያምን ኅብረተሰብ መፍጠር የሚሉ ጉዳዮች "በድርድሩ ምላሽ እንዲያገኙ እንታገላለን" ብለዋል።

 ፓርቲዎቹ የተጣመሩበት ዋና ዓላማ ለኅብረተሰቡ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ሙሉጌታ፤ "የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ በ2010 በአዲስ አበባ በሚካሄደው የማሟያ ምርጫ  ላንሳተፍ ወይም ገብተን ልንወጣ እንችላለን" ብለዋል።

 የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጫኔ ከበደ፤ "ከህገ መንግስቱ አንስቶ ባሉት አጠቃላይ የህግ አፈፃፀሞች ላይ ለመወያየት የተጀመረው ድርድር አጋዥ ይሆናል" ብለዋል።

 የሰጥቶ መቀበል መርህን ተግባራዊ ለማድረግ ገዥው ፓርቲ የሚያቀርባቸውን መደራደሪያዎች በመቀበል አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረገው ድርድር በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።  

 ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ በመፍጠር ዲሞክራሲን ለማጎልበት አፋኝ የሆኑ ህጎች ካሉ ለማስወጣት፣ መጨመር ያለባቸው ካሉም ለመጨመር ጥምረቱ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

 መኢብን፣ መኢአድ፣ መኢዴፓ፣ መኦህዴፓ፣ ቅንጅት፣ አንድነት፣ አትፓ፣ ኢዴህ፣ ኢዴፓ፣ ኢብአፓ፣ ኢዴአን እና ወህዴፓ ጥምረቱን የመሰረቱ አገር አቀፍ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 2/2009 በአሁኑ ወቅት እየጣለ ባለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የቆቃ ግድብ በመሙላቱ በአካባቢው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ተቋሙ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ የቆቃ ግድብ በመሙላቱ የተነሳ መጠኑ የበዛ ውሃ ወደ ወንዝ እየተለቀቀ በመሆኑ ከግድቡ በታች ያሉና የማይያዙ ገባር ወንዞች አንድ ላይ በሚመጡበት ወቅት ከፍ ያለ ጎርፍ ስለሚያስከትሉ ህብረተሰቡ መጠንቀቅ እንዳለበት በመግለጫው ተመልክቷል፡፡

በወንዙ አካባቢ የሚገኙት የምስራቅ ሸዋ ዞን፣የአዳማና ፈንታሌ ወረዳ፣ አርሲ ዞን፣ መርቲ እና ጀጁ ወረዳዎች ፣ከአፋር ዞን ሶስት በአሚባራ፣ በዱለቻ፣በቡሬ ሙዳይቱ እና በገዋኔ ወረዳዎች የሚኖሩ ሰዎችና የመስኖ ተጠቃሚዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል፡፡

በወንዙ ላይ የሚከሰተውን ከፍተኛ ፍሰት ተከትሎ በወንዙ ዳር የሚገኙ ዛፎች በመውደቅ የወንዙን አቅጣጫ ሊያስቀይሩ ስለሚችሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አቅጣጫውን ሊያሰቀይሩ ከሚችሉ ነገሮችን በማፅዳት አደጋውን መከላከል እንዳለባቸው ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም ቆቃ ግድብ ከመድረሱ በፊት ያሉት ደቡብ ምዕራብ ዞን ኢሉ ወረዳ ልዩ ዞን፣ ሰበታ ፣ ሀዋዝ ወረዳ፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን ፣ ቦራ፣ ሊበን ዝቋላ እና ሎሚ ወረዳዎች በሚዘንበው ከባድ ዝናብ ምክንያት ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰትባቸው ስለሚችል ነዋሪዎቹ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ  በመግለጫው አሳስቧል፡፡

በቆቃ ግድብ ሪዘርቫየር አካባቢ የግድቡ ውሃ ወደ ኋላ እየተስፋፋ በመሆኑ በዙሪያው ያሉ ነዋሪዎች ከግድቡ በመራቅ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አስገንዝቧል፡፡

በተፋሰሱ አካባቢ የሚገኙ አመራሮችና የመገናኛ ብዙሃን እለታዊ መረጃ እንዲያደርሱም ኮሚሽኑ ጠይቋል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን