አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Wednesday, 06 September 2017

አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2009 ለአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ የበለጠ ለማረጋገጥ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዶክተር ተቀዳ አለሙ ገለጹ።

 በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላትና በአፍሪካ ሕብረት የሰላምና የጸጥታው ምክር ቤት 11ኛው ጉባዔ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን ውይይት በተመለከተ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዶክተር ተቀዳ እንደተናገሩት፤ የፀጥታው ምክር ቤት ለአፍሪካ ሰላምና ፀጥታ መረጋገጥ የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማድረግ  ፍላጎት አለው።

ሆኖም ግን በርካታ የሚቀሩ ተግባራት በመኖራቸው ነገ የሚካሄደው ውይይት በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ዋና ትኩረት እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በተለይም የሶማሊያና የደቡብ ሱዳን ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢጋድ ጋር በቅርበት የመስራት እቅድ እንዳለም ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት ለአፍሪካ ህብረት የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግም አንዱ የውይይቱ ትኩረት መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ አገሮችን ወክለው የመጡት የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት አባላትም በአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴስ ኦፍ አሜሪካ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ ሚስስ ሚሸል ሲሶን እንዳሉት ወደ ዚህ የመጣነው በአፍሪካ ያለውን የሰላምና ደህንነት ችግሮች ለመፍታት በተባበሩት መንግስታትና በአፍሪካ ህብረት በተጨባጭ እየተሰሩ ያሉ ሰራዎችን ለማየት ነው።

በተባበሩት መንግስታት የሴኔጋል ቋሚ መልዕክተኛ ሚስተር ፎዴ ሴክ፤ "ውይይቱ የአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ችግሮችን ለመፍታት ወሳኝ ነው" ብለዋል።

Published in ፖለቲካ

አዳማ ጳጉሜ1/2009 የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ለሀገር ገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያካሄደው አንድ ጥናት አመለከተ።

ምክር ቤቱ በጥናቱና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ከፌደራል፣የክልልና የከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ሲያደርግ የነበረው የምክክር መድረክ ዛሬ ተጠናቋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የንቃተ-ህገ መንግስት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አማሃ ንዋይ እንደገለጹት ጥናቱን ማካሄድ ያስፈለገው በበዓሉ አከባበር ዙሪያ መልካም ተሞክሮዎችንና ተግዳሮቶችን በመለየት ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ነው።

በጥናቱ መሰረትም በዓሉ ካበረከተው አስተዋጽኦ መካከል ከፍተኛ የህዝብ መነቃቃት መፍጠሩ፣ልዩነት ውበት ሆኖ እንዲንጸባረቅ ከማድረጉም ባሻገር የእርስ በእርስ መተማመን እንዲጎለበት ማስቻሉ ይገኝበታል።

እንዲሁም በዓሉ የራስን ባህል፣ታሪክና ቋንቋ ጠብቆና ተንከባክቦ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ  ሁኔታ ፈጥሯል።

የክልል ከተሞችን የመሰረተ ልማት ለማስፋፋት ከመርዳቱም ባለፈ ለህዝቦች መቀራረብና አንድነት መጠናከር ብሎም ለሀገሪቱ ገፅታ ግንባታ የማይተካ ሚና ማበርከቱንና ሌሎችንም  ጥናቱ አትቷል።

ጥናቱ በችግርነት ከለያቸው ጉዳዮች መካከልም በዓሉ በሚከበርባቸው አካባቢዎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ዘላቂነት የማረጋገጥ ውስንነት፣ለበዓል አከባበሩ የሚውሉ አንዳንድ ወጪዎችና ሌሎችም ተጠቅሰዋል።

በዓሉን ለማክበር የሚወጣው ወጪ እጅግ በጣም ከፍተኛ ብክነት የሚታይበት መሆኑን ጥናቱ ጠቅሶ በተለይ ለርችት የሚወጣው 5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለቲሸርትና ኮፍያ የሚወጣው ወጪ ምንም ዓይነት እሴት እንደማይጨምር በማሳያነት አቅርቧል።

በመሆኑም እነዚህና ሌሎችንም ችግሮች በማቃለል የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ ጥናቱ ቀጣይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በበኩላቸው እንደገለጹት ጥናቱ በተለይም በዓሉ ለሃገራችን ገጽታ ግንባታና የሕዝቦች እኩልነትና አንድነት መዳበር ያለውን አስተዋጽኦ ያመለከተ ነው ።

በጥናቱ የገኘው ውጤትና በተሳታፊዎች የተሰጡት አስተያየቶች በግብአትነት ተቀምረው ለውሳኔ ሰጪ አካላት እንደሚቀርቡም አመልክተዋል።

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌጳጉሜ1/2009 ተማሪዎች የማንበብ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ አጋዥ የሆኑ ተጨማሪ መፃህፍት ወደ ትምህርት ቤቶች በመላክ ድጋፍ እንደሚያደርግ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ባህታ ወልደሚካኤል ትናንት የተከበረውን የንባብ ቀን ምክንያት በማድረግ እንደገለጹት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የተማሪዎችና የመምህራን የማንበብ ባህል ለማሳደግ ቢሮው ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ሆነው ከሚያገኙት መደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ለንባብ የሚያነሳሱ መፃህፍትን እንዲጠቀሙና ዕውቀት እንዲገበዩ ለማድግ ቢሮው እየሰራ ነው።

ወላጆችም የልጆቻቸውን የንባብ ባህል ከፍ ለማድረግ መፃህፍቶችና ሌሎች የሚነበቡ ፅሁፎችን በማቅረብና በመስጠት ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል።

በአፄ ዮሃንስ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ታዳጊ ወጣት ኪሮስ ታደለ እንዳለችው፣የቤት ስራ በጊዜ በመስራት ትምህርቷን በፕሮግራም በማጥናት መፃህፍት በማንበቧ ከክፍል አንደኛ መውጣቷን ተናግራለች።

ዶክተር የመሆን ህልም አለኝ ያለችው ተማሪ ኪሮስ፣ በትርፍ ሰዓቷ ወንድሞቿና የክፍል ጓደኞቿን በጥናት በማገዝ እውቀታቸውን እንዲጨምሩ እንደምታደርግ ገልጻለች።

በትምህርት ቤቱ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ አቤል ተኽለ በበኩሉ፣ትግርኛ ቋንቋ፤ሳይንስና እንግሊዝኛ የትምህርት ዓይነቶችን ማንበብ እንደሚወድና ጠንክሮ በማጥናት አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

"መምህራን በክፍል የሚያስተምሩኝ ካልገባኝ በመጠየቅ፤የቤት ስራ በመስራትና በማጥናት ከክፍል ጓደኞቼ ጋር ስለምሰራ ለደረጃ እወዳደራለሁ" ብሏል።  

ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚሰጥ የድጎማ በጀት የተለያዩ አጋዥ መጽሐፍትን ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ደሴ ጳጉሜ 1/2009 በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለጤና ተቋማት ከሚያስፈልገው የመደኃኒት አቅርቦት ማሟላት የተቻለው 61 በመቶውን ብቻ መሆኑን የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በጤና አገልግሎትና ግብአት ዙሪያ በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ለሁለት ቀናት በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

በቢሮው የጤና ግብአት አቅርቦትና ስርጭት የሥራ ሂደት መሪ አቶ እድሜዓለም አድማሱ እንዳሉት ቢሮው ባለፈው ዓመት በክልሉ ለሚገኙ ጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት የሚሆን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ መመደቡን አስታውሰዋል።

ይሁንና ክፍያ ከተፈጸመበት ውስጥ ከመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጀንሲና ከሌሎች መድኃኒት አቅራቢዎች ለጤና ተቋማቱ መድረስ የቻለው 61 በመቶ ብቻ ነው፡፡

በግዥና በሌሎች ምክንያቶች የሚፈጠረውን መጓተት በቀጣይ ለማስቀረት ቢሮው በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት 73 በመቶውን የግዥ ፍላጎት ማሟላት ከሚቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሶ የነበር ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፍላጎትና የአቅርቦት ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን አመለክተዋል፡፡

በግብአት እጥረቱ ምክንያት ጤና ተቋማቱ ለሕብረተሰቡ መሰጠት የሚገባቸውን አገልግሎት በሚፈለገው የጥራት ደረጃ እየሰጡ አለመሆኑንም አቶ እድሜዓለም አያይዘው ጠቁመዋል፡፡

እጥረቱ በመድኃኒት ብቻ ሳይሆን በሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦት ላይም እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ አገልግሎቱን ከጤና ተቋማት ሳያገኝ ሲቀር ከግለሰብ ጤና ተቋማት መድኃኒቶችን በውድ ዋጋ ለመግዛት መገደዱንና ይህም የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ መምጣቱን አስረድተዋል፡፡

እንደአቶ እድሜአለም ገለጻ፣ የሕክምና ቁሳቁስና መድኃኒት በዋናነት ከሚያቀርቡ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት በመወያየት ችግሩን ለመፍታት አቅጣጫዎች ቢቀመጡም በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ መምጣት አልቻለም፡፡

የመካነ ሰላም ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ከተማ አብተው በበኩላቸው ከመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጀንሲ የሚቀርብላቸው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ በየወቅቱ እየቀነሰ መምጣቱ በሆስፒታሉ አገልግሎት ላይ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ተናገረዋል፡፡

ዋጋው ከ16 ብር በታች የሆነና ለድንገተኛና ለማንኛውም ሕክምና አገልግሎት የሚውል ፕላስተር ባለመቅረቡ ሕሙማን ከግለሰብ ጤና ተቋማት እስከ 200 ብር ለመግዛት የተገደዱበት አጋጣሚ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

"የማሕበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ቁጥር እያደገ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የመድኃኒት አቅርቦትና ቁሳቁስ እጥረት መፈጠሩ ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ እየሆነ ነው" የሚሉት ደግሞ  የሰሜን ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ ናቸው፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ኤች.አይ.ቪን ለመመርመር የሚያስፈልጉ ብልቃጦችና ኬሚካሎች እጥረት በመኖሩ በመከላከልና በመቆጣጠር ስራው ላይ  ተጽእኖ እያሳደረ ነው፡፡

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ብዙዓየሁ ካሳ  በበኩላቸው "መድኃኒት በዋናነት የሚያቀርበው የመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እያደገ ከመጣው የሕብረተሰብ ፍላጎት ጋር የሚጣጣም አደራጃጀትና አሰራር መዘርጋት አለመቻሉ እጥረቱ እንዲፈጠር አድርጓል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ጤና ተቋማቱ በእጃቸው ያለውን ግብአት በመቆጣጠርና በማስተዳደር በኩል ባለባቸው ክፍተት የሕክምና መሳሪያዎች ብልሽትና የመድኃኒት ብክነት እያጋጠመ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ቢሮው ከላይ የተነሱና ሌሎች ችግሮችን በአዲሱ በጀት ዓመት ለመፍታት ከኤጀንሲው ጋር በመተባበር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚደሰራ አመልክተዋል።

አሰራሩን ቀልጣፋና ፍትሃዊ ለማድረግ በክልል ደረጃ ኤጀንሲውን ያካተተ የአማካሪዎች ቡድን እንደሚቋቋም ጠቁመዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የመድኃኒት አቅርቦት ፈንድ ኤጀንሲ ባልደረቦች በቀረቡት ቅሬታዎች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ጳጉሜ 1/2009 ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲን መሰረት ያደረገው የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ የሀገቱን መልካም ገጽታ በመገንባት በአለም አቀፍ መድረኮች ያላትን ተደማጭነት ማሳደግ እንዳስቻላት የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ለኢዜአ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ግብ ሀገሪቱ ለጀመረችው የሰላም ፣የዲሞክራሲና ልማት ጥረት በገንዘብ፣ በፖለቲካና በዲፕሎማሲ መስኮች ድጋፍ ማግኘት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በሀገሪቱ እየታየ ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት ቀጣይ እንዲሆን ባለሀብቶችን በመሳብ ለግብርናና እሴት ተጨምሮ የሚላኩ ምርቶች ገበያ ለማፈላለግ የሚረዳ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማምጣት ዋና የዲፕሎማሲው አቅጣጫ ነው፡፡

የበርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት ሰላም ለማስከበር ባደረገው ጥረት ውስጥ የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡

ቃለ አቀባዩ እንዳመለከቱት ከኮንጎና ኮሪያ በተጨማሪ ባለፉት አስርት ዓመታት ከላይቤሪያ እስከ ሩዋንዳ ከብሩንዲ እስከ ሱዳን የሰላም አስከባሪ ሀይል ልካለች፡፡

"በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰላም አስከባሪ ሀይል ከሚልኩ ሀገራት ሁለተኛ በአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚዋ ናት ብለዋል"

ይህም ለሀገሪቱ ትልቁ የስኬት ማሳያና ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የሰላም አጋርና የሌሎችን እንባ የምታብስ ሀገር መሆኗን በተግባር ማስመስከሯን ጠቅሰዋል፡፡

"አዲስ አበባ የአፍሪካ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ መዲና ናት የሚባለው እንዲሁ አይደለም "ያሉት ቃል አቀባዩ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ለኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ የባለብዙ መድረኮች ላላት ሚና የሰጣት ዕውቅና ተደርጎ እንደሚወሰድም አመልክተዋል፡፡

በእነዚህና በሌሎችም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ያከናወነችው ተግባራት በአለም መድረክ ተሰሚነቷን በማሳደግ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንድትሆን እንዳደረጋት ጠቁመዋል፡፡

ቃለ አቀባዩ እንዳስረዱት ከወራት በፊት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም የአለም የጤና ድርጅትን በዋና ሊቀመንበርነት እንዲመሩ  የመመረጣቸው ምክንያት በአህጉራዊም ሆነ አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በምታቀርበው ሀሳብ ተጽእኖ መፍጠር በመቻሏ ነው፡፡

"ሀገራችን  በአለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፤  ብዙ ሀገራትም ለእኛ ቢሆን  ብለው እንዲመኙ አድርጓል "ብለዋል፡፡

በአጎራባች ሀገራት መካከል ትብብር ማድረግ የኢፌዴሪ የውጪ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ያመለከቱት አቶ መለስ የሀገራትን ትስስር ለማጠናከር በመሰረተ ልማት የማገናኘት ስራ መከናወኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያን ከኬንያ የሚያገናኝ የአስፋልት መንገድ እስከ ሞያሌ መጠናቀቁን ከሱዳንም ጋር በተመሳሳይ በመተማ በኩል መገናኘት እንደተቻለና ከጅቡቲ ጋር በመንገድም በባቡርም ማስተሳሰር ተችሏል፡፡

ይህም በሀገራቱ መካከል የኢኮኖሚና የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን እንዲጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል እንደ አቶ መለስ ገለጻ፡፡

ኢትዮጵያ ለወጭና ለገቢ ንግድ ከጅቡቲ ጋር ባላት ስምምነት መሰረት የወደብ አገልግሎት እንደምትጠቀም አስታውሰው በተመሳሳይ የሰሜን ምዕራብ አካባቢ ላለው ደግሞ  የሱዳንን ወደብ መጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት በቅርቡ መፈራረሟን አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተደማጭነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሁን ያለው ትውልድና አመራር ለሀገሩ ኃላፊነቱን መወጣትና አምባሳደር እንደሆነ ማሰብ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

 

Published in ፖለቲካ

አዳማ ጳጉሜ1/2009 የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያለበትን የተወዳዳሪነት ክፍተት ለመቅረፍ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ  የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2009 ዓ.ም የሥራ ዕቅድ ክንውንና የአዲሱ በጀት ዓመት የመነሻ ዕቅድ የምክክር መድረክ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተጀምሯል።

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሊዊጃ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት አገሪቱ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ያለባትን የተወዳዳሪነት ክፍተት ለመቅረፍ ኮርፖሬሽኑ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ ይገባዋል።

እንዲሁም ከሀገር ውስጥና ከውጪ የሥራ ተቋራጮች ጋር ተቀራርቦና ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ድርሻ ያለውን የመስኖ ልማት ግንባታን ጨምሮ በሃይል ማመንጫና በህንፃ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የሰው ሃይሉንና አነስተኛ ሀብቱን በማቀናጀት ኮርፖሬሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ የልማት ፕሮጄክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ በጥራትና ወጪን በቆጠበ መልኩ ያለማጠናቀቅ፣ በቂ የሰው ሃይል ያለመኖርና የግብዓት አቅርቦት እጥረት ከተቋሙ ችግሮች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም የወሰን ማስከበር፣ የፋይናንስ አቅርቦት፣ ሂሳብ በወቅቱ ያለማስመርመር፣ የኦዲት ግኝት ሃሳቦችን ተከታትሎ የእርምት እርምጃ ያለመውሰድም የተቋሙ ተጨማሪ ችግሮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኮርፖሬሽኑ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ከፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ጀምሮ በሁሉም መስኮች አቅሙንና ተወዳዳሪነቱን ማጎልበት እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም በግንባታ ኢንቨስትመንት በተለይም በመስኖና የመጠጥ ውሃ፣ በትራንስፖርት፣ በህንፃና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች ተስፋ ሰጪ አፈፃፀም መኖሩን የገለፁት ደግሞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ሃይለመስቀል ተፈራ ናቸው።

በተጠናቀቀው  የበጀት ዓመት የትራንስፖርት መሰረተ ልማት፣ የመስኖ፣ የመጠጥ ውሃና የሕንፃ ኮንስትራክሽን ጨምሮ 183 ፕሮጄክቶች ግንባታ ሲያከናውን መቆየቱን  ዋና ሥራ አስፈፃሚው  ተናግረዋል ።

ከእነዚሁ መካከል 10 መካከለኛና ከፍተኛ የመስኖ ግድቦችን ጨምሮ፣ ንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የስኳር ፋብሪካና የደረቅ ወደብ ፕሮጄክቶች ግንባታ ዓመታዊ አማካይ አፈፃፀማቸው  79 ነጥብ 4 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል።

በግብዓት አቅርቦት፣ የማሽነሪዎች እርጅናና የሰው ሃይል ምርታማነት ማነስ፣ የአመራሩ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ውስንነት ለፕሮጄክቶቹ ወጪ መናርና በተቀመጠላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

በአዲሱ የበጀት ዓመት በአቅርቦት ላይ የሚታዩትን ማነቆዎች ለመፍታት የሰው ሃይሉን በአመለካከት፣ ክህሎትና በአቅም ከማብቃት ባሻገር የማሽነሪና ተያያዥ መሳሪያዎች ጥገናና ግዢ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ።

በበጀት ዓመቱ ኮርፖሬሽኑ ካከናወናቸው ስራዎች ከ975 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ አግኝቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ አሰራር በሚፈቅደው መሰረትም ለመላው ሠራተኞች የሁለት ወር ደሞዝ በስጦታና የአንድ እርከን ጭማሪ ማድረጉን  ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2009 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የአዲሱ በጀት ዓመት የመነሻ ዕቅድ የምክክር መድረክ ላይ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ጳጉሜ 1/2009 በ2010 በጀት ዓመት የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ዕቅዱ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ28 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ አለው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መብራቱ መለሰ እንደገለጹት የ2009 በጀት ዓመት በምግብ፣መጠጥና ፋርማሲቲካል ምርቶች የውጭ ሽያጭ የተገኘው ገቢ ከእቅዱ አኳያ ዝቅተኛ ነበር።

ለአብነትም በመጠጥ ፕሮሰሲንግ ምርቶች ሽያጭ ከ18 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታቅዶ 7 ሚሊዮን ዶላር፣ ከቅባት እህሎች  ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ታቅዶ 16 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በብርዕና አገዳ ከ23 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማግኘት ታቅዶ 15 ሚሊዮን ዶላር ነው የተገኘው።

በአጠቃላይ በዓመቱ የ73 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ማሳካት የተቻለው ግን 51 ሚሊዮን ዶላር ወይም 69 በመቶውን ብቻ ነው።

ያም ሆኖ በአትክልት፤ ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ንዑስ ዘርፍ ኤክስፖርት ረገድ ከእቅድ በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።  የአቅም አጠቃቀም ማነስ፣ የጥሬ ዕቃ ግብዓት ብዛትና ጥራት መጓደል፣ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የጥራት ሰርተፈኬት ችግርና የገበያ መዳረሻ እጥረት ለአፈጻጸሙ ማነስ ምክንያቶች ነበሩ ተብሏል።

በጥሬ እቃ ማነስ ምክንያት ተገንብተው ስራ ያልጀመሩ፣ ስራ ጀምረው ያቋረጡ እንዲሁም ስራ ጀምረውም እስከ 30 በመቶ የማምረት አቅማቸውን የተጠቀሙ ፋብሪካዎች ነበሩ።

ቢራ አምራች ፋብሪካዎች በአገር ውስጥ ካለው ሰፊ ገበያ አኳያ ወደ ውጭ የመላክ ፍላጎታቸው ዝቅተኛ መሆኑንም ዶክተር መብራቱ ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመገንባት ላይ ካሉት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮች በተጨማሪ በርካታ የትኩረት አቅጫጫዎች መቀመጣቸው ተገልጿል።

ከሚላኩ ምርቶች ስብጥር አንጻር በመጭው ዓመት ወደ ሰላሳ የሚደርሱ አዳዲስ ምርቶችን ለማካተት ታቅዷል።

የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬቶችን መተግበር፣የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት፣አዳዲስና ማስፋፊያ የተደረገላቸው አምራች ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ማስገባት፣የኢንዱስትሪና ዩኒቨርሲቲ ትስስርን ማጠናከርና ምርምሮችን ማካሄድ ትኩረት ከተደረገባቸው ነጥቦች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ከነበረበት 57 በመቶ ወደ 69 በመቶ ለማሳደግም ታቅዷል።

በአጠቃላይ ችግሮችን በመለየት በቀጣይ በጀት ዓመት የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲቲዩካል ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ101 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱን ነው የገለጹት። 

በተመሳሳይም በ2010 በጀት ዓመት ከ56 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር መታቀዱ ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ድሬደዋ ጳጉሜ1/2009 በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት አስር አመታት የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን የአስተዳደሩ ጤና ጥበቃ  ቢሮ ገለጸ፡፡

በገጠርና በከተማ ተደራሽ የሆኑት የጤና አገልግሎቶች በሽታን በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ማስቻሉም ተመልክቷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው ለኢዜአ እንዳሉት በአስተዳደሩ ከአስር ዓመት በፊት የነበሩት አንድ ሆስፒታልና ሶስት ጤና ጣቢያዎች በአሁን ሰዓት ያልተጠናቀቀውን ጨምሮ ሆስፒታሎች ወደ ሶስት የጤና ጣቢያዎች ቁጥር ደግሞ 15 ደርሰዋል፡፡

" 34 ጤና ኬላዎች በገጠርና በከተማ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፤ የህክምና ስፔሻሊስቶችና ጠቅላላ ሐኪሞች ቁጥርም  ጨምሯል" ብለዋል፡፡

የጤና ተቋማትና የባለሙያዎች ቁጥር መጨመር የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ መሆኑ የእናቶች ቅድመ ወሊድ ክትትልና ህክምና ሽፋን ከ52 በመቶ ወደ 87 ማሳደግ መቻሉን ዶክተር ሙሉ ቀን ተናግረዋል፡፡

በጤና ጣቢያ የሚወልዱ እናቶች ቁጥርም ከ26 በመቶ ወደ  58 መድረሱን ጠቅሰው የህጻናት የክትባት ሽፋን ከ75 ወደ 96 በመቶ አድጓል፡፡

በፍቃደኝነት የሚሰበሰበው ደም ልገሳ እያደገ መምጣቱ የፈውስ አገልግሎትን  ውጤታማ እያደረገ ከመሆኑም በተጨማሪ በህፃናትና እናቶች ላይ የሚደርስን ጉዳት መቀነስ መቻሉን ነው ዶክተሩ ያመለከቱት፡፡

በድሬዳዋ  በጤናው ዘርፍ ለተገኘው ውጤት የግሉ ሴክተር  አስተዋፅኦ አድርጓል፤  በቀጣይ ከህክምና ፍላጎት መስፋትና ከዘመናዊ የቴክኖሎጂ ህክምና አንፃር ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በአንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ላይ  የሚስተዋሉ የሥነ-ምግባር ክፍተቶች ፣በመድሃኒትና የቤተ-ሙከራ  መቆራረጥና ድንገተኛ በሽታዎችን መቆጣጠር ሌላው ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

የድል ጮራ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሁዲን ረዲ በበኩላቸው ከአራት ዓመታት በፊት በሆስፒታሉ  ለእናቶችና ህጻናት ህክምና ብቻ የሚውል የህክምና ማዕከል ተገንብቶ አገልግሎት መስጠቱ  የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነሱን ተናግረዋል፡፡

"ህብረተሰቡ የተመጠነ ቤተሰብ እንዲመሰርት የተሰሩ ተግባራት ውጤት እያመጡ ናቸው " ብለዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በፊት ገዳይ የነበረውን የወባ በሽታ በጤና ልማት ሠራዊት በመታገዝ መቆጣጠር ተችሏል፤ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ለሚገኝባቸው ነዋሪዎች የሚሰጠው ህክምና ውጤት እያመጣ ነው፡፡

በቀጣይ ከቫይረስ  ነፃ የሆነ ጨቅላ እንዲወለድ በማድረግ የተገኘውን ውጤት ከማጠናከር ጎን ለጎን  መድኃኒት የተላመደ ቲቪን ለመከላከል  ርብርብ ይደረጋል ብለዋል አቶ ሙሁዲን ፡፡                     

"ከስድስት ዓመት በፊት እርጉዝ ሴቶች እቤት  ነበር የሚወልዱት፤ ይህ ሞት ያስከትል ነበር ፤ አሁን ይሄ ተቀይሯል - በተገነቡ ጤና ተቋማት የሚወልዱ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ  መጥቷል"  ያሉት ደግሞ በአስተዳደሩ የዋሂል ገጠር ክላስተር የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተቆጣጣሪ  አቶ ሀሪፍ መሐመድ ናቸው፡፡

የመልካ-ጀብዱ ጤና ጣቢያ የህጻናትና እናቶች ህክምና ባለሙያ ሲስተር ጫልቱ መሀመድ በበኩላቸው የጤና ባለሙያዎች፤የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችና ህብረተሰቡ ተቀናጅተው መስራታቸው በጤናው ዘርፍ ጉልህ ውጤት እንዲመጣ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሣቢያን መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል በህጻናትና እናቶች ክፍል ህክምና ሲከታተሉ የነበሩት ወይዘሮ አይናለም ታደሰ በሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መምጣቱ  ለሶስተኛ ጊዜ በጤና ተቋም  እንዲወለዱ ምክንያት እንደሆናቸው ገልፀዋል፡፡            

 

 

Published in ማህበራዊ

አዳማ ጳጉሜ 1/2009 በአዳማ ከተማ በተለያዩ ሆቴሎች አልጋ ይዞ በማደር ቴሌቪዥን እየሰረቀ ይሰወር ነበር የተባለው ተጠርጣሪ መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የአዳማ ከተማ ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ዋና ሳጅን ወርቅነሽ ገልሜቻ ዛሬ እንደገለፁት ግለሰቡ ከሶስት ወራት በፊት በተለያዩ ሆቴሎች አልጋ ይዞ በማደር ስድስት ቴሌቪዥኖች ሰርቆ እየተሰወረ በፖሊስ ክትትል ሲደረግበት ቆይቷል፡፡

ፖሊስ ፎቶግራፉን አባዝቶ በመበቱኑ ምክንያት ከሶስት ወራት በኋላ ወደ አዳማ ተመልሶ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም ሆቴል በማማረጥ ላይ እንዳለ ህብረተሰቡ በጥርጣሬ ለፖሊስ ባደረሰው ጥቆማ ነሀሴ 20 ቀን 2009 ዓ.ም ተይዟል።

ዋና ሳጅን ወርቅነሽ እንዳሉት ግለሰቡ ከሚያድርባቸው ሆቴሎች ቴሌቪዥኖቹን በትልቅ ሻንጣ ደብቆ በማውጣት  በአዳማ ፣ ሞጆ ፣ ዱከምና ሻሸመኔ ከተሞች ወስዶ እንደሸጣቸው ለፖሊስ የእምነት ቃሉን ሰጥቷል ።

በአዲስ አበባ በፀጉር ማስተካከል ስራ ተሰማርቶ የነበረውና  የተሻለ ስራ ፍለጋ ወደ አዳማ ከመጣ በኋላ ያሰበውን ስራ ማግኘት ባለመቻሉና ሱሰኛ በመሆኑ ወደ ስርቆት  መግባቱን ለፖሊስ መናገሩም ተመልክቷል፡፡

የግለሰቡ የምርመራ መዝገብ ቢጠናቀቅም ፍርድ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው እሰከ አሁን ድረስ ለህግ እንዳልቀረበ ዋና ሳጅን ወርቅነሽ ጠቁመው ፍርድ ቤቶች ስራ ሲጀምሩ እንደሚቀረብ ተናግረዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎች የአልጋ ተከራዮችን ማንነት የሚያረጋግጥ መታወቂያ መያዝና አልጋ ሲለቀቅ ንብረቶቻቸው ባሉበት መሆናቸውን ፈትሸው ማረጋገጥ እንደሚገባቸው ዋና ሳጅን ወርቅነሽ አሳስበዋል ።

 

 

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ ጳጉሜ1/2009 መንግስት በመደበው ተዘዋዋሪ ብድር ተጠቅመው ወደ ስራ የገቡ አንዳንድ የምስራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች ለዘመን መለወጫ  ምርቶቻቸውን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገለጹ።

በዞኑ በተለቀቀው ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ብድር ወጣቶችን በማደራጀት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ማሰማራት መቻሉን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታውቋል።

በዞኑ እነብሴ ሳር ምድር የቅል ሜዳ ቀበሌ  ነዋሪ ወጣት ይታየው ገዜ እንዳለው በተዘዋዋሪ ብድሩ በተፈቀደላቸው ከ300 ሺህ ብር በላይ ከአምስት ጎደኞቹ ጋር በመሆን በዶሮ እርባታ ስራ መሰማራታቸውን ገልጿል።

በዚህም ቀደም ብለው ጫጩት በማሳደግ ከተደራጁ ወጣቶች የአንድ ወር ከ15 ቀን የሆናቸው ከ2 ሺህ በላይ የስጋ ዶሮዎችን በግንቦት ወር በመረከብና በማሳደግ ለዘመን መለወጫ ለሽያጭ ማድረሳቸውን ገልጿል።

በዞኑ መስተዳድር በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርም ምርቱን በቀጥታ ወደ አዲስ አበባ ለመላክ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

አሁን ባለው የገበያ ዋጋ ጥናት መሰረት ከዶሮዎቹ ሽያጭ ከ100 ሺህ ብር በላይ ትርፍ እንደሚያገኙ ያለውን እምነት ገልጿል።

መንግስት በተዘዋዋሪ ብድር በፈቀደላቸው 250 ሺህ ብር ብድር ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን በሰኔ ወር በከብት ማድለብ ስራ መሰማራታቸውን የገለጸው ደግሞ በዚሁ ወረዳ የመርጦለማሪያም ከተማ ኗሪ ወጣት ተስፋ ቢያድግልኝ ነው።

በ2008 ዓ.ም  ከመቱ ዩኒቨርስቲ በማኔጅመንት ተመርቆ ስራ በመፈለግ ላይ እንዳለ በተፈጠረለት የስራ እድል 25 በሬዎችን ገዝተው አስረው በማድለብ ላይ እንደሚገኙ ተናግሯል።

ያደለቧቸውን በሬዎችም ለዘመን መለወጫና ለመስቀል በዓል ገበያ ለማቅረብ በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልጾ ጥሩ ስጋ የያዙና የደለቡ በመሆናቸው ከሽያጩ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚያገኙ ያለውን እምነት ገልጿል።

በሞጣ ከተማ አስተዳደር የቀበሌ 01 ነዋሪ ወጣት ሀያት በሀሉዓለም በበኩሏ ከአምስት ጓደኞቿ ጋር ተደራጅተው ባገኙት 287 ሺህ ብር ብድር በቅርቡ በዶሮ ማርባት ስራ መሰማራታቸውን ተናግራለች።

''ያጋጠመን የካፒታል እጥረት ተቀርፎ ወደ ስራ በመግባታችን ሰርተን በመለወጥ ካለንበት የቤተሰብ ጥገኝነት የመላቀቅ ፍላጎታችንን እንዲያድግ አስችሎታል'' ብላለች።

በቀጣይም በሬዎችን አድልበውና ዶሮዎችን አሳድገው በመሸጥ የወሰዱትን ብድር ፈጥነው በመመለስ በራሳቸው አቅም ለመንቀሳቀስ በመትጋት ላይ መሆናቸውን ሁሉም አስተያየት ሰጪ ወጣቶች ተናግረዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ወጣቶች እና ስፖርት መምሪያ የወጣቶች ማካተት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን አላምሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት በመጀመሪያው ምዕራፍ መንግስት 170 ሚሊዮን ተዘዋወሪ ብድር ለዞኑ ለቋል።

ከተለቀቀው ገንዘብ ውስጥም ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነውን ተደራጅተውና ስልጠና ወስደው ይጠባበቁ የነበሩ 4ሺህ  ወጣቶችን በተለያዩ  የስራ ዘርፎች በማሰማራት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው የስራ ዘርፎች መካከል  በከተማ እና ገጠር ግብርና፣ በኮንስትራክሽን ፣ በምግብና መጠጥ፣ በአገልግሎትና ሌሎች ተያያዥ ዘርፎች መሆኑን አመልክተዋል።

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከልም ከ35 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኮሌጅ እና የዩኒቨርስቲ  ምሩቃንና ትምህርታቸውን በተለያየ ምክንያት ያቋረጡ ወጣቶች መሆናቸው ተገልጿል።

በአዲሱ የበጀት ዓመትም ስራ አጥ ወጣቶች በሚመርጡት የሙያ መስክ በማደረጃትና በማሰልጠን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በተዘዋዋሪ ብድሩና ሌሎች የገንዘብ አማራጮችን በመጠቀም ለ60 ሺህ 235 ዜጎች አዲስ የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 4

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን