አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 05 September 2017

አዲስ አበባ ነሐሴ 30/2009  የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቅርቡ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው 63 ግለሰቦች ከ170 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ የሕዝብ ሃብት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገለጸ።

 የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳ በቁጥጥር ስር የዋሉ 63 የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ተባባሪ ግለሰቦችን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

 ከተጠርጣሪዎቹ መካከል በከተማ አስተዳደሩ ባሉ 12 ተቋማት ስር በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የነበሩ 36 አመራሮች፣ 20 ሙያተኞች እንዲሁም በወንጀሉ ተባባሪ የነበሩ ሌሎች ሰባት ግለሰቦች እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

 ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከከተማው ዋና ኦዲተርና ከሕዝብ በተገኘ ጥቆማ በሙስና ወንጀል በበቂ ሁኔታ በመጠርጠራቸው መሆኑን ገልጸዋል።

 ከነዚህም መካከል በአዲስ አበባ የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ከአመራር እስከ ተራ ሰራተኞች  በጥቅሉ 29 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

 የተጠረጠሩበት ወንጀል ደግሞ "በተሰረዘ ደረሰኝ ክፍያ በመፈጸም ከስምንት ሚሊዮን ብር፣ ከመመሪያ ውጭ ግዥ በመፈጸም ስድስት ሚሊዮን ብር፣ ለማን እንደተከፈለ የማይታወቅ ገንዘብ አምስት ሚሊዮን ብር፣ ያልተመዘገበና ለማን እንደተከፈለ የማይታወቅ 32 ሚሊዮን ብርና በሌሎች ህጋዊ ባልሆኑ ድርጊቶች በጥቅሉ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት አድርሰዋል" በሚል ነው።

 በአንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ሁለት ዋና ስራ አስኪያጆችን ጨምሮ ስድስት ግለሰቦች ለአውቶብሶቹ የማይሆን የመለዋወጫ ዕቃ ከመመሪያ ውጭ ግዠ በመፈጸም ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ሃብት እንዲባክን በማድረግ ወንጀል ነው የተጠረጠሩት።

 ደራሽ ለመርካቶ የሸማቾች የግል ማህበር ደግሞ ያለአግባብ፣ ካለደረሰኝ፣ ያለ ጨረታና ከውል በላይ ክፍያ በመፈጸም፤  ላልተገባ አካል ስራ በመስጠት በመሳሰሉ ድርጊቶች በጥቅሉ ሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህዝብ ሃብት በማባከን አምስት ተጠርጣሪዎች ተይዘዋል።

 የመንግስትን መሬት ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ለግለሰብ በመስጠት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።

 ለአብነትም የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ስር ከ600 ሺህ ብር በላይ ያባከኑ  ስድስት ግለሰቦች፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 አራት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር  በላይ እንዲባክን ያደረጉ ሁለት ግለሰቦች እንዲሁም በዚሁ ክፍለ ከተማ የመሬት ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት  ከ700 ሺ ብር በላይ እንዲመዘበር ያደረጉ አምስት ሰራተኞች በወንጀል ተሳትፎ ተጠርጥረው ተይዘዋል።

 በተመሳሳይ በጉለሌ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩ ግለሰብም አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ጉዳት ያደረሱ የሃሰተኛ ሰነዶችን በመጻፍ ወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል።

 በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ሰባት የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች የልማት ተነሽ ላልሆኑ አምስት ግለሰቦች ህገ ወጥ በሆነ መልኩ ባለ ሶስት መኝታ ቤት ኮንዶሚኒየም በመስጠት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ሃብት በማባከን ተጠርጥረው ነው የተያዙት።

 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሰባት ሰዎች ለጊዜው የጉዳት መጠኑ በመጣራት ላይ የሚገኝ ሃብት እንዲባክን በማድረግ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

 በአዲስ አበበ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት በአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ታገለግል የነበረች ግለሰብ ከ880 ከረጢት በላይ ሲሚንቶ ለግል ጥቅም በማዋል እንዲሁም በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ጉቦ በመቀበልና  የዜጎችን አገልግሎት የማግኘት መብት በመንፈግ የሙስና ወንጀል ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

 በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ውስጥ  አንድ የደረሰኝ አገልግሎት ዳይሬክተርና ሌሎች ሁለት ግለሰቦች ከውል ውጭ ማስታወቂያ በመልቀቅ ከ200 ሺ ብር በላይ መንግስትን በማሳጣት ወንጀል ተጠርጥረው ተይዘዋል።

 ኮሚሽነሩ አያይዘውም ከ64 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ ሃሰተኛ ሰነዶችና ደብዳቤዎች፣ ስም የሌላቸው ካርታዎች፣ የፕላን ስምምነቶች፣ ማህተሞችና በመስሪያ ቤት ብቻ መቀመጥ ያለባቸው ቁሶች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ከዋሉ ግለሰቦች እጅ መያዛቸውን ገልጸዋል።

 "በጥቅሉ በቁጥጥር ስር በዋሉት 63 ግለሰቦች ከ170 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህዝብና የመንግስት ሃብት ተመዝብሯል" ነው ያሉት።

 ምርመራው አስፈላጊውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ፣ ትክክለኛውን ተጠርጣሪ በመለየት በቁጥጥር ስር ለማዋል  ስድስት ወራት መፍጀቱን አመልክተዋል።

 ከፌደራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከ699 በላይ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን ተረክቦ እያጣራ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ "የማጣራት ሂደቱን በማጠናከር ተጠርጣሪዎችን በህግ ፊት ማቅረቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

 'ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ከፍተኛ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ያልዋሉት ተሳትፎ ስላልነበራቸው ነው ወይ?' ተብሎ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ " ለጥርጣሬ ዋናው መለኪያ ማስረጃ ነው፤ ማስረጃ የተገኘበት ማንኛውም ባለስልጣን በህግ ይጠየቃል፣ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከልም 36ቱ ከፍተኛ አመራር  ናቸው" ብለዋል።

 ሙስና ከተፈጸመ በኋላ የሚያደርሰው ተጨማሪ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ "ዋናው ተግባር የሙስና ወንጀል ከመፈጸሙ በፊት የመከላከል ስራ ነው" ብለዋል።

 ህብረተሰቡ መረጃ የመስጠት ባህሉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

Published in ማህበራዊ

ድሬዳዋ   ነሀሴ 30/2009 በሀገር አቀፍ ደረጃ ኤች.አይቪ/ኤድስን እና የቲቢ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተነደፈውን የሦስት ዘጠና መርሀ ግብር ለማሳካት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ።

መርሃ ግብሩን ለማሳካት የሚያግዙ 35 የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበትና ሁሉም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች  እንዲሁም ፖሊሲ አውጪዎችና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተሳተፉበት ዓመታዊ ጉባኤ በድሬዳዋ ዛሬ እየተካሄደ ነው፡፡

ለሦስት ቀናት የሚቆየው አውደጥናት ሲጀመር የኢትዮጵያ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ እንደተናገሩት በመላው ሀገሪቱ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡

በፍቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ምርመራ፣ በፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት አቅርቦት አንዲሁም ቫይረሱ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለማድረግ በቅንጀት የተከናወኑ ተግባራት ፍሬ እያፈሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር አቤ አንዳሉት፣ በ2005 በሀገሪቱ 330 ብቻ የነበሩት የኤች አይ ቪ የምርመራ ማዕከላትና ተቋማት በአሁኑ ወቅት ወደ 1ሺህ 200 አድገዋል።

ተቋማቱም ጥራቱ የተጠበቀ አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው ይደርስ የነበረውን ሞት በ65 በመቶ መቀነስ ተችሏል፡፡

በተገኘው ውጤት በተፈጠረው መዘናጋትና በበጀት እጥረት ምክንያት የተገኙ ውጤቶች ወደ ኋላ እንዳይመለሱ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሦስት ዘጠና መርሃ ግብር  ተነድፏል።

በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተነደፈውን መርሀግበር አቀናጅቶ በመተግበር የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርቡ ተጠናከሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ቲቢና ኤች አይ ቪ በፈጠሩት ቁርኝት በኤድስ መክንያት እየተከሰተ ያለውን ሞት ለማስቀረትና ለቲቢ ሕሙማን ተገቢው ሕክምናና ክትትል የማድረጉ ሥራ በስፋት እየተሰራበት መሆኑን ዶክተር አቤ አመልክተዋል።

በሽታውን በተለማመደ ቲቢ ለታመሙ ሕሙማን ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ በመላው ሀገሪቱ ማዕከላት በመገንባት የተሻለ ሕክምና መሰጠት መጀመሩ ውጤት እያስገኘ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በስድስት ዘርፎች እየቀረቡ የሚገኙት 35 የምርምር ውጤቶች የተሻለ ሥራ ለመስራት የሚያግዙ እንደሚሆኑም አመልክተዋል።

"ምርምሮቹ ለፖሊሲ አውጪዎች እንደግብዓት የሚያገለግሉ በመሆናቸው በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ለመስጠትም ያግዛል" ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው በበኩላቸው፣ በሽታውን የተለመመደ የቲቪ በሽታንና ኤች.አይቪን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተሰሩ ሥራዎች በአልጋ ላይ የነበሩ ሰዎች ጭምር ጤናቸው ተመልሶ በሀገር ልማትና ዕድገት ላይ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡

በሀገር አቀፍ  ደረጃ የተነደፈው የሦስት ዘጠና መርሃ ግብር በድሬዳዋ ለማሳካት የተለያዩ ሥራዎች ቢከናወኑም አሁንም ወደ ምርመራ እንዲመጡ የሚጠበቁ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ማስመዝገብ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ሀገር አቀፉ አውደ ጥናት በተጀመረበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠርና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ተወካዮች በሀገሪቱ ኤች አይ ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በሦስት ዘጠና መርሃ ግብር፣ በቲቢ በሽታ ቁጥጥር እንዲሁም በሁለቱ በሽታዎች ቁርኝት ላይ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተካሄዱ ጥናቶች ቀርበው በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል ፡፡

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ነሀሴ 30/2009 የአርብቶ አደሩን  ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አብዴፓ) አስታወቀ፡፡

 የፓርቲዊ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈጻጸምና የቀጣዩ ዘመን እቅድ ዙሪያ በሰመራ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲያካሄድ የቆየውን  ስብሰባ ትናንት አጠናቋል፡፡

 የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና አብዴፓ ጽህፈትቤት ኃላፊ አምባሳድር ሀሰን አብዲልቃድር በስብሰባው ማጠቃለያ እንደገለጹት ባለፈው በጀት ዓመት የክልሉን መንግስት የሚመራው አብዴፓ ከከፍተኛ አመራሮች እስከ ህብረተሰቡ ድረስ የወረደ የጥልቅ ተሃድሶ ግምገማ አድርጓል፡፡

 በዚህም  ህብረተሰቡን ያማረሩ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

 በተሀድሶው ወቅት በፓርቲዉ አባላት መካከል የተካሄደው  ግምገማ ተከትሎ  አባላትን በስፋት ባሳተፈ አግባብ ድርጅቱን  መልሶ የማደራጀት ስራ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ ተከናውነዋል፡፡

 የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር እንዳመለከቱት በየደረጃው ያለውን አመራር የፖለቲካዊ ብቃቱን ለማሳደግ ብሎም በመንግሰት ፖሊሲና ስትራቴጂ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ይዞ ወቅቱ የሚጠይቀውን በእውቀት ላይ የተመሰረተ አመራር እንዲሰጥ የአቅም ግንባታ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይቷል፡፡

 ይህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና አባላቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ በመታደስ መንፈስ በሙሉ አቅማቸው ወደ ልማት በማዞር የህዳሴ ጉዞውን ለማስቀጠል ተነሳሽነት ፈጥሯል፡፡

መሪው ፓርቲ ፣ህዝቡና መንግስት ተቀናጅተዉ በመንቀሳቀስ በተጠናቀቀው  በጀት ዓመት በመንደር ማሰባሰብ፤ በውሃ ማቆርና መስኖ ልማት እንዲሁም በትምህርትና በሌሎችም የልማት  ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች እንደተከናወኑ መገምገማቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

 በጥልቅ ተሃድሶው ሂደት የተገኙ መልካም ውጤቶችን በተያዘው በጀት ዓመትም  የበለጠ አጠናክሮ በመቀጠል የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ  ከፍተኛ አመራሩ መንግስትና ህብረተሰቡ ይበልጥ ተቀራረበው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አስታውቀዋል፡፡

 በተለይም  የተጀመረው የመንደር ማሰባሰብ፣  የወጣቶች ስራ እድል ፈጠራ፣ ክልሉ የሚያስተናግደው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ዝግጅት፣ የቤትና ህዝብ ቆጠራ እንዲሁም የወረዳና አካባቢ ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቁ ፓርቲው በትኩረት እንደሚሰራም አብራርተዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

አክሱም ነሀሴ 30/2009 ወጣቶች በጥሩ አስተሳሰብ ታንፀው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ህይወትህን ለመምራት የንባብ ባህላቸውን ማሳደግ እንደሚገባቸው ተመለከተ፡፡

 የንባብ ቀንን ዛሬ በንባብ ያከበሩት አንዳንድ የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት  ማንበብ ለብቁ ተወዳዳሪነት፣ለመዝናኛና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ህይወትህን ለመምራት ይረዳል።

 በአክሱም ዩኒቨርስቲ የማናጅመንት ተማሪ ወጣት ማህደር ብርሃነ በሰጠችው አስተያየት  " ማንበብ ማለት ህይወት ነው፣ካላነበብን ቀሪ ህይወታችንን በእቅድ መምራት ያስቸግረናል" ብላለች።

 የሚያነብ ሰው እውቀቱን  በማስፋት የመናገር፣ የመግባባትና የመወሰን አቅሙን ያዳብራል፤ የሚሄድበትና አኗኗሩን በቀላሉ መገንዘብ እንደሚችል ወጣቷ ከራሷ ተሞክሮ ማረጋገጧን ተናግራለች፡፡  

 " ተማሪው  በፈተና ጊዜ ብቻ ነው የሚያነበው፣ለእውቀት ብሎ የሚያነብ ሰው እጅግ አነስተኛ ነው " የምትለው ወጣት ማህደር፣ብዙ መጽሐፍት ቢኖሩም  የማንበብ ባህሉ ገና እንደሆነ ነው ያመለከተችው፡፡

 ማህበረሰቡን የሚለወጠው ንባብ መሆኑን በመግለጽ በአዲስ ዓመት ዋዜማ የንባብ ቀን መሰየሙንና መከበሩን በተለይ ተማሪዎች በቀጣዩ ዘመን  የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያነሳሳቸው ጠቅሷለች፡፡

 " ማንበብ ማለት ተጨማሪ እውቀትን በማግኘት፣ ነገሮችን የማመዛዘንና ችሎታህን በየጊዜው ማሳደግ  ነው " ያሉት ደግሞ የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ ሰናይ መስፍን ናቸው።

 በየቀኑ የተለያዩ ጋዜጦች፣መጽሄቶችና መጽሓፍት በማንበብ ሀገራዊ፣አህጉራዊና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ለመገንዘብ እንደሚያስችል ጠቁመው  ማንበብ ትልቁ የእውቀት ስፍራ  በመሆኑም ማህበረሰቡ በተለይም ወጣቱ የንባብ ባህሉን ማሳደግ እንዳለበት  አመልክተዋል፡፡

 የንባብ ባህል እንዲያድግ  ማህበረሰቡ  የሚያነብበት ቦታ ማስፋፋት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

 በአክሱም ቤተ ንባብ ማዕከል የመጻህፍት ተቆጣጣሪ ወይዘሮ ነብያት በየነ በበኩላቸው " የህብረተሰቡ የንባብ ባህል እያደገ ነው፣ተማሪዎች በትርፍ ሰዓታቸው ሌሎችም  በእርፍት ጊዜያቸው ወደ ማዕከሉ እየመጡ ያነባሉ" ብለዋል።

 በተለይ አዲሱ ተውልድ አንባቢ እንዲሆን በሚደረገው እንቅስቃሴ ደራሲያን፣የሃይማኖት አባቶችና አስተማሪዎች ትልቅ ድርሻ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

 በማዕከሉ የትምህርት፣የመዝናኛና የታሪክ ማጣቀሻ መጽሐፍት በብዛት እንዳሉ ይገኛል፡፡

 " ማህበረሰቡ በተለይ ወጣቱ በጥሩ አስተሳሰብ ታንፀው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ህይወትህን ለመምራት በእቅድ የተመሰረተ የማንበብ ባሀል ሊያዳብር ይገባል"  ብለዋል ወይዘሮ ነብያት።

 የአክሱም ሄሪቴጅ ፋውዴሽን አስተባባሪ አቶ አረፋይኔ ብረሃነ እንዳሉት ደግሞ በከተማው የንባብ ባህልን ለማሳደግ በ25 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲሰ ቤተመጽሐፍት እየተገነባ ነው።

 ወጪው በኢትዮ- ኮሚዩኒቲ ዲቨሎፕመንት ካውንስል በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የተሸፈነ ነው፡፡

 እንደ አቶ አረፋይነ ገለጻ ፣ግንባታው ለንባብ ምቹ አካባቢና ሁኔታ በመፍጠር የንባብ ባህልን ለማሳደግ ያለመ ነው።

 

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ነሐሴ 30/2009 የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ባለፈው በጀት ዓመት ከ 380 ሺህ በላይ እርድ በመፈጸም ከዕቅዱ 76 በመቶውን ማሳካት ችሏል።

 በበጀት አመቱ ከ 53 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ማስቀመጡንና 96 በመቶውን ማሳካት መቻሉን ጠቅሰው የተገኘው ትርፍም ከ2008 ዓ.ም   የ9 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው የድርጅቱ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ንብረት በቃ ተናግረዋል።

 የእቅዱን ያህል ገቢ ማግኘት ያልቻለው ድርጅቱ ከአመቱ አጋማሽ አንስቶ የበግ ዕርድ አገልግሎቱ  በመቋረጡ ነው።

 የድርጅቱ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግብዓት አጠቃቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱም ተነግሯል።

 ድርጅቱ መሻሻሎች ቢኖሩትም አሁንም ፈታኝ ችግሮች እንዳሉበት ጠቁመው ከተመሰረተበትና ካለው ኃላፊነት አኳያ ብዙ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

 የሰራተኛው ክህሎትና አመለካከት በሚፈለገው ደረጃ አለመቀየሩ፣የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በስፋት መኖሩ፣ተቋማዊ ለውጡን ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለማጣጣም ያለው ሒደት አዝጋሚ መሆኑ፣የተወዳዳሪነት አስተሳሰብ ዝቅተኛ መሆን ድርጅቱን ከገጠሙት ችግሮች በዋናነት ተጠቃሾች ናቸው።

እነዚህና በአንዳንድ ሰራተኞች ላይ የሚታየው የከፋ የስነ-ምግባር ጉድለት ተገልጋዮችን ከተቋሙ እንዲሸሹ ያደረጉ ተግዳሮቶች እንደሆኑም ገልጸዋል።

 ድርጅቱ በራሱ ችግሮቹን ለመቅረፍ  ከሚያደርገው እንቅስቃሴ በተጨማሪ የባለድርሻ አካላት እገዛ እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።

 የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በዚሁ እለት 60ኛ ዓመት ምስረታውንና ዓመታዊ የሰራተኞች በዓሉን አክብሯል።

 በተቋሙ ለረጅም ጊዜ ላገለገሉና በስራቸው የላቀ አፈጻጻም ላስመዘገቡ ሰራተኞችና  በዓመቱ ብዙ ግብይት ለፈፀሙ ደንበኞች ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሐሴ 30/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ 10 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርግ ነው።

 ድጋፉ የሚደረግላቸው  የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን የሚከታተሉ፣ በትምህርት ቤት የምገባ ስርዓት ውስጥ የተካተቱ እና የድሃ ድሃ  ተብለው የተለዩ ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።

 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ዛሬ በሰጡት መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በ2009 ዓ.ም የማህበራዊ ፈንድና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ አቋቁሞ እየሰራ ነው ብለዋል።

 በትምህርት ገበታ የሚገኙና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው  ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በተወሰነው መሰረት በምገባ ስርዓት ውስጥ ከሚገኙ 26 ሺህ ተማሪዎች መካከል ችግረኛ ለሆኑ 10 ሺህ ተማሪዎች ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።

 ተማሪዎቹ የደብተርና እስክሪብቶ እንዲሁም የትምህርት ቤት አልባሳት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው የገለፁት።

 ድጋፉ ከጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ እንደሚፈፀም የተናገሩት አቶ ኤፍሬም የድጋፍ አሰጣጡን የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ትምህርት ቢሮ፣ሴቶችና ህፃናት ቢሮ፣ማህበራዊ ፈንድና ሴፍትኔት ኤጀንሲ እንዲሁም የከንቲባው ፅህፈት ቤት እንደሚያስተባብሩት ገልፀዋል።

 ድጋፍ የሚደረግላቸውን 10 ሺህ ተማሪዎች በትምህርት ቢሮ አስተባባሪነት ትምህርት ቤቶቹ መርጠው ማጠናቀቃቸውንም አስረድተዋል።

 ለድጋፉ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን ከአስተዳደሩ፣ከባለሀብቶች፣ከግለሰቦች፣መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚገኝ እንደሆነም ጠቁመዋል።

 ከባለሀብቶችና ግለሰቦች ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው ገንዘብ ባይገኝ እንኳን የከተማ አስተዳደሩ ወጭውን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

 ድጋፉ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልፀው ለዚህም የባለሀብቱና ግለሰቦች ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሀሴ 30/2009 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ 10 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ሊያደርግ ነው።

ድጋፉ የሚደረግላቸው  የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን የሚከታተሉ፣ በትምህርት ቤት የምገባ ስርዓት ውስጥ የተካተቱ እና የድሃ ድሃ  ተብለው የተለዩ ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤፍሬም ግዛው ዛሬ በሰጡት መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በ2009 ዓ.ም የማህበራዊ ፈንድና ልማታዊ ሴፍቲኔት ኤጀንሲ አቋቁሞ እየሰራ ነው ብለዋል።

በትምህርት ገበታ የሚገኙና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው  ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በተወሰነው መሰረት በምገባ ስርዓት ውስጥ ከሚገኙ 26 ሺህ ተማሪዎች መካከል ችግረኛ ለሆኑ 10 ሺህ ተማሪዎች ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።

ተማሪዎቹ የደብተርና እስክሪብቶ እንዲሁም የትምህርት ቤት አልባሳት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ነው የገለፁት።

ድጋፉ ከጳጉሜ 1 ቀን 2009 ዓ.ም እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ እንደሚፈፀም የተናገሩት አቶ ኤፍሬም የድጋፍ አሰጣጡን የከተማ አስተዳደሩ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ትምህርት ቢሮ፣ሴቶችና ህፃናት ቢሮ፣ማህበራዊ ፈንድና ሴፍትኔት ኤጀንሲ እንዲሁም የከንቲባው ፅህፈት ቤት እንደሚያስተባብሩት ገልፀዋል።

ድጋፍ የሚደረግላቸውን 10 ሺህ ተማሪዎች በትምህርት ቢሮ አስተባባሪነት ትምህርት ቤቶቹ መርጠው ማጠናቀቃቸውንም አስረድተዋል።

 ለድጋፉ7ነጥብ5ሚሊዮንብርየሚያስፈልግሲሆንከአስተዳደሩ፣ከባለሀብቶች፣ከግለሰቦች፣መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚገኝ እንደሆነም ጠቁመዋል።

 ከባለሀብቶችና ግለሰቦች ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው ገንዘብ ባይገኝ እንኳን የከተማ አስተዳደሩ ወጭውን እንደሚሸፍን ተናግረዋል።

 ድጋፉ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን ቀጣይነት እንደሚኖረው ገልፀው ለዚህም የባለሀብቱና ግለሰቦች ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ብለዋል።

Published in ማህበራዊ

 አዲስ አበባ ነሐሴ 30/2009 የኢትዮጵያ ግብርና፣ አርብቶ አደር ፖሊሲ ፣ስትራቴጂዎችና ተቋማትን ለውጥ ፍለጋ በሚል ርዕስ የተዘጋጀው መጽሃፍ ለንባብ በቃ። 

 በግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያና አማካሪ ዶክተር ደምስ ጫንያለው የተፃፈውን ይህንኑ መጽሃፍ ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው መድረክ ዛሬ በግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተካሂዷል።

 መጽሃፉ በአስር ምዕራፎች የተከፋፈለ ሲሆን ዘርፉ የሚመራበት አገር በቀል ፖሊሲ አስፈላጊነት ፣ የግብርና ባለሙያዎች ያሉበት ደረጃና ቀጣይ ሚና ፣የልማት አጋሮች በመስኩ ፖሊሲ ላይ ያላቸው ተሳትፎና ችግሮቻቸው የሚሉት ከተዳሰሱ ርእሰ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። 

 መጽሃፉ በተለይ ከዚህ በፊት የሚገባውን ያህል ትኩረት ያልተሰጠውን የአርብቶ  አደር ጉዳይ ማካተቱ ጠቃሚነቱን ይበልጥ እንደሚያጎላው የተናገሩት የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ሁሴን በቀለ ናቸው።   

 ''አገሪቷ ካለችበት የእድገት ደረጃ አኳያ መጽሃፉ ወቅታዊ ነው'' ያሉት አቶ ሁሴን በመስኩ በቀጣይ ውጤታማ መሆን የሚቻልባቸውን ዝርዝር አቅጣጫዎች የሚያመላክት መሆኑንም ነው የተናገሩት።  

 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር እንዳሻው በቀለ በበኩላቸው መጽሃፉ ኢትዮጵያን የግብርና መስክ ፖሊሲ ድክመቱንም ጥንካሬውንም የያዘ መሆኑ የተሻለ ያደርገዋል ይላሉ።  

 መጽሃፉ ለግብርና ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሴክተሮችም ጠቃሚ መንገዶችን እንደሚያሳይ አብራርተዋል። 

 እንደ ፕሮፌሰር እንዳሻው ገለጻ መጽሃፉ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ የሆኑ ሀሳቦችን እንደያዘም ነው የተናገሩት። 

 የመጽሃፉ አዘጋጅ ዶክተር ደምስ ጫንያለው ግብርናን ከእህልና እርሻ ጋር ብቻ አያይዞ የማየት ችግር በስፋት መኖሩን ይገልጻሉ።

 የግብርና  ምርት፣እርሻና የእንስሳት ሀበት ልማት ፣የገበያ ሰንሰለትና ሌሎች በርካታ ነገሮችን የያዘ መሆኑን ማስገንዘብ የመጽሃፉ ዓላማ መሆኑንም አመልክተዋል ።

 ''እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ አገራት አገር በቀል ፖሊሲ ቀርጸው ተግባራዊ እስካላደረጉ ደረስ የእድገታቸው ቀጣይነት ጥያቄ ውስጥ ይገባል'' ያሉት ዶክተር ደምስ መጽሃፉ አገራዊ እውቀት ወሳኝ ሚና እንዳለው ያስረዳል ይላሉ። 

 በየሴክተሩ የሚወጡ ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ምንያህል ተነባቢ ናቸው፣ የግብርና ፖሊሲው አተገባበር ላይ ያሉ ክፍተቶች፣በዘርፉ አማካሪነት ለሚሰሩ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ማሰራት ተገቢ እንዳልሆነ ማስገንዘብም ሌላው የመጽሃፉ የትኩረት ነጥብ  እንደሆነ ነው ያብራሩት። 

 የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቲ በበኩላቸው መጽሃፉ ለፖሊሲ አውጪዎች በግብዓትነት የሚያገልግል መሆኑንም አመልክተዋል። 

 ኢንስቲትዩቱም ለሚያከናውናቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች መጽሃፉን በግበዓትነት እንደሚጠቀም አስረድተዋል። 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሐሴ 30/2009 ኅብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን በማሻሻል ቆሻሻን ወደ ሀብትነት ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ጠየቀ።

ሚኒስቴሩ ከ2010 ዓ.ም አዲስ ዓመት ጋር በተያያዘ በነገው እለት "ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጠበቆች ነን" በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን የአረንጓዴ ልማት ቀን በማስመልከት  መግለጫ ሰጥቷል።

ሚኒስትሩ ዶክተር ገመዶ ዳሌ እንደተናገሩት፤ በየአካባቢው ያለው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ከተሞችን በከፍተኛ ሁኔታ እያቆሸሸና ውበታቸውንም እየቀነሰ ነው።

በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት አሰራር መዘርጋቱን የተናገሩት ዶክተር ገመዶ፤ "ኅብረተሰቡ የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓቱን በማሻሻል ቆሻሻን ወደ ሀብትነት ለመቀየር የሚደረገውን ጥረት መደገፍ አለበት" ብለዋል።

በነገው ዕለት በሚከበረው የአረንጓዴ ልማት ቀን አገሪቷ ለአረንጓዴ ልማት ያላት ጠበቃነትና አለም አቀፍ ተሰሚነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኅብረተሰቡ ከቤቱ የሚወጣውን ቆሻሻ በመለየት ቆሻሻን ወደ ሀብት ለመቀየር እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

ዶክተር ገመዶ፤ አገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የነደፈችው ስትራቴጂም በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጠበቃነት በተግባር ለማረጋገጥ የዘርፍ መስሪያ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ሊናበቡና በእቅዳቸው ውስጥ ሊያካትቱት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት አገሪቷ  ብክለትን የሚቀንሱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሟ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳያል። 

ኢትዮጵያ በተለያዩ መድረኮች በተለይ እያደጉ ላሉ አገሮች ስለ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት በማሳሰብ በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች እንደሆነም አስታውሰዋል።

በዓሉ ቱሉዲምቱ አካባቢ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብና በተያያዥ ሥራዎች እንደሚከበር ተገልጿል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ነሐሴ 30/2009 ኢትዮጵያ ከእንሰሳት ኃብት የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የዘርፉ አካላት በጋራ ሆነው በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራ ሊሰሩ አንደሚገባ ተጠቆመ። 

የኢትዮጵያ የእንሰሳት ጤና ኃኪሞች ማኅበር 31ኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ጀምሯል።

የእንሰሳትና ዓሳ ኃብት ምኒስትር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት አገሪቱ ከአፍሪካ በቀንድ ከብት ብዛት ቀዳሚ ብትሆንም ዘርፉ ለአገሪቱ አጠቃላይ ምርት የሚያበረከተው ድርሻ አነስተኛ ነው።

ለዚህ ደግሞ እንሰሳት በተለያዩ በሽታዎች መጠቃታቸውና ጥራት ያለው የመኖ ተደራሽነት ችግር መኖሩን በምክንያትነት አንስተዋል። 

ችግሩን ለመቅረፍ በዘርፉ ያለውን በተለይም የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ሁሉም የመስኩ ተዋናዮች ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።

በእንስሳቱ ጤና ላይ የሚከሰተውን በሽታ ከወዲሁ ለመከላከልና የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማሟላት ቴክኖሎጂ አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ዘርፉን በዘመናዊ መንገድ ለመምራትና ለማስተዳደር ከማገዝ በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ለመረጃ ቅርብ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል ነው ያሉት።

ዘርፉን ለማሳደግ የሚያስችል የብድር አቅርቦትን ለማሻሻልና በእሴት ሰንሰለት ላይ የተመሰረተ የገበያ መሰረተ ልማትን ለማስቀጠል ቴክኖሎጂዎቹ ጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ለአስር ዓመት የሚቆይና በዘርፉ ተግባራዊ የሚደረግ መሪ እቅድ በማዘጋጀት ከአንሰሳት ኃብት የሚገኘውን ጥቅም  ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ምኒስትሩ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የእንሰሳት ኃኪሞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር በእውቀት ስራው በበኩላቸው ዘርፉ ለአገሪቱ የሚጠበቅበትን ያህል አስተዋጽዖ እያስገኘ አለመሆኑን ማኅበሩ እንደሚያምን ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ የእንስሳት ጤና ችግር ዋነኛ ቢሆንም የመኖ ጥራትና ዘመናዊ ያልሆነው የአረባብ ሥልትም ቀላል የማይባል ችግር እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል።

በተለይም በእንስሳቱ ላይ የሚስተዋሉት የጤና ችግሮች በባለሙያዎቹ እንዲለዩ በማድረግ ዘላቂ እልባት ለመስጠት ማኅበሩ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በቀጣይም ለባለሙያዎቹ ተከታታይ ሥልጠና በመስጠት ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱና የእንስሳቱን ጤና እንዲጠብቁ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በዘርፉ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበርም በመስኩ በቴክኖሎጂ የታገዘ የእንስሳት ርቢና የጤና ክብካቤ እንዲኖር ለማድረግ ማኅበሩ በስፋት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

43 ዓመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ የእንሰሳት ጤና ኃኪሞች ማኅበር ከ100 በላይ አባላት አሉት።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን