አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Monday, 04 September 2017
Monday, 04 September 2017 23:18

የህዳሴው ግድብ

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ ነሃሴ 29/2009 የሥራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠናዎችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት የወጣቶችን ክህሎት ለማጎልበት እንደሚሰራ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከሰባት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ መምህራን በአዲስ አበባ የሥራ ፈጠራ ክህሎትን የማስተማር ስልጠና እየተሰጠ ነው።

ለአራት ቀናት በሚቆየው ስልጠና ከሐዋሳ፣ አዳማ ፣ አርሲ፣ መቀሌ፣ ደብረማርቆስ፣ አክሱምና ባህርዳር የተወጣጡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እየተሳተፉ ነው።

ሥልጠናውን ትምህርት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት  እንዱስትሪ ልማት ድርጅት የሴቶችና ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ትውውቅ ፕሮጀክትና ከሌሎች አጋሮች ጋር አዘጋጅቶታል።

ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚመረቁ ወጣቶች ዘንድ ሥራን ከመፍጠር ይልቅ የመቀጠር ዝንባሌ ጎልቶ ይስተዋላል።

ችግሩ በተግባር የሥራ ፈጠራ ክህሎት የሚያዳብሩበት የትምህርት ስርዓት ባለመኖሩ እንደተፈጠረም ጠቁመዋል።

ወጣቶች በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቆይታቸው የስራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠና ሊያገኙ እንደሚገባ ገልፀው፤ "በእነዚህ ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት የተግባርና የሥራ ፈጠራ ክህሎቶች የሚዳብሩበት እንዲሆን ይሰራል" ብለዋል።

"ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው የሥራ ፈጠራ ክህሎትን የሚያዳብሩ ስልጠናዎችን መውሰዳቸው ተመርቀው ከወጡ በኋላ ከሥራ ጠባቂነት ያላቅቃቸዋል" ያሉት ደግሞ በተባበሩት መንግሥታት እንዱስትሪ ልማት ድርጅት የሴቶችና ወጣቶች ሥራ ፈጠራ ትውውቅ ፕሮጀክት ዳይሬክተር ማቲዮ ላንዲ ናቸው።

ንድፈ ሐሳብ ላይ ብቻ ያተኮሩ ስልጠናዎች መሰጠታቸው ሰልጣኞች የሥራ ፈጠራ ክህሎታቸውን እንዳያዳብሩ እንቅፋት እንደሆነም ተናግረዋል።

"በመሆኑም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተግባር የታገዘ የሥራ ፈጠራ ክህሎት ስልጠናዎች ላይ ትኩረት አድረገው ሊሰሩ ይገባል" ነው ያሉት።

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎትና ኢንዱስትሪ ሊንኬጅ ዳይሬክተር ዶክተር ሺመልስ ረጋሳ በበኩላቸው በተቋማቸው የሚሰጠው ስልጠና በተግባር ላይ ያተኮረና ሥራ ለመፍጠር አቅም የሚፈጥር እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ሰልጣኞች በቆይታቸው በአገሪቱ ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ልምድና ክህሎት እንዲቀስሙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ተግባር በሁሉም የአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስተያየታቸውን አክለዋል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 29/2009 የነሀሴ ወር 2009 ዓ.ም የ12 ወራት ተንከባላይ አማካይ አገራዊ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ7 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታወቀ።

በተመሳሳይ ንጽጽር የምግብ ዋጋ ግሸበት 8 ነጥብ 9 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች ግሽበት ደግሞ በ6 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ  ማሳየቱን ኤጀንሲው ለኤዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።

የነሀሴ ወር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ10 ነጥብ 4 በመቶ ከፍ ማለቱም ታውቋል።

የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ከፍ ማለት ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ መጨመር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም በመረጃው ተብራርቷል።

171 ነጥብ1 በመቶ የሆነው በነሀሴ ወር 2009 ዓ.ም  አጠቃላይ የዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ 115 ነጥብ 5 ከነበረው ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት መመዘኛ  በልጦ መገኘቱም ለአብነት ተጠቅሷል።

በጤፍ፣ ገብስ ፣በቆሎ፣ ስንዴና ማሽላ በመሳሰሉ የምግብ እህሎች ጠንከር ያለ የዋጋ ጭማሪ እንደተመዘገበ የተገለፀ ሲሆን፤ በቅባት እህሎች፣ በአትክልት፣ በጥራጥሬና ድንች በመሳሰሉት ላይ ግን ብዙ ለውጥ አለመታየቱ ተገልጿል።

በልብስና መጫሚያዎች እንዲሁም በቤት እቃዎችና የቤት ማስጌጫ ቁሳቁስ ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ምግብ ነክ ላልሆኑ ቁሶች የዋጋ ግሽበት መጨመር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን አስገንዝቧል።

በሌላ በኩል የአጭር ጊዜ ክስተትን በሚለካው ወርሃዊ የዋጋ ግሽበት ምጣኔ መሰረት፣ የነሀሴ ወር 2009 ዓ.ም የዋጋ ግሽበት ከተመሳሳይ ዓመት ሐምሌ ወር ጋር ሲነጻጸር የ1ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ተጠቁሟል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሃሴ 29/2009 ኢትዮጵያ በህገ ወጥ እርድ ምክንያት በዓመት እስከ 500 ሚሊዮን ብር እንደምታጣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ገለጸ።

ባለድርሻ አካላት በቅንጅት አለመስራትና ኅብረተሰቡ ህገ ወጥ እርድ የሚያመጣውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት በበቂ ሁኔታ አለመገንዘብ እንደምክንያት ተጠቅሷል።

"የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከትናንት አስከ ዛሬ" በሚል ርዕስ ባዘጋጀው የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ ላይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ንብረት በቃ እንዳሉት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ካልሰሩ ህገ ወጥ እርድ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ ይሆናል።

ድርጅቱ  በዓመት ከ 200 ሚሊዮን ብር ያልበለጠ ገቢ እንደሚያገኝና በህገ ወጥ እርድ ምክንያት ደግሞ በዓመት እስከ 500 ሚሊዮን ብር መንግስት እንደሚያጣ ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ከ146 በላይ ህገ ወጥ እርድ የሚከናወንባቸው ቦታዎች እንዳሉ የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፣ በዜጎች ጤናና በአገር ሃብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለመቀነስ የደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ የልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበራት፣ ንግድ ሚኒስቴር፣ የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በቅንጅት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ህብረተሰቡም በአካባቢ ብክለት ምክንያት የሚከሰተውን የጤና መታወክ ለማስቀረትና የሚወድመውን የአገር ንብረት ለማዳን ህገ ወጥ እርድን በመከላከል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት በሁሉም አካባቢ ተደራሽ አለመሆኑ ለህገ ወጥ እርድ መባባስ መንስኤ እንደሆነና ድርጅቱም የራሱ ውስንነት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በሚቀጥለው 2010 ዓ ም የሞባይል ቄራ ወይም ተንቀሳቃሽ ቄራ በማዘጋጀት ኅብረተሰቡ በአቅራቢያው እንዲያሳርድ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

በህገ ወጥ እርድ ዙሪያ ኅብረተሰቡን በየጊዜው አለማስገንዘብ፣ ሚዲያዎች የሚሰሯቸው ዘገባዎች በበዓል ወቅት ብቻ የተወሰኑ መሆንም ለችግሩ መባባስ እንደመንስኤ ተቀምጧል።

Published in ኢኮኖሚ

 

አዳማ ነሃሴ 29/2009 በቢሾፍቱ የሚገኘው የሆራ አርሰዲ ሐይቅና አካባቢው ላይ በግለሰቦች እየደረሰበት ያለውን ጉዳት ለመታደግ ተገቢ ጥበቃና እንክብካቤ  እንዲደረግለት ተጠየቀ፡፡

በየዓመቱ የኢሬቻ በዓል  በደማቅ  ስነ ስርዓት የሚከበርበት ይህ ሐይቅ ጥበቃ  እንዲደረግለት የጠየቁት የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት አባላት ናቸው፡፡

አባላቱ በቢሾፍቱ ከተማ  የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት አንድነት ጉባኤን ባካሄዱበት ወቅት እንደገለጹት ሐይቁ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት ሰብሳቢና የቱለማ አባገዳ በየነ ሰንበቶ በተለይ ለኢዜአ እንዳሉት  የኢሬቻ በዓል በሚከበርበት ሐይቅ ላይ ግለሰቦች ጥፋት እያደረሱበት ነው።

ለመዝናናት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ግለሰቦች ሐይቁ ዳርቻ ላይ በየጊዜው የታሸገ ውሃ መያዣ ላስቲኮችን በመጣልና  ሌሎችንም ባእድ ነገሮችን በመጣል  ስፍራውን እያቆሸሹት ነው፡፡ 

ሐይቁና አካባቢው በቀላሉ እንዳይበከል በመጠበቅ   የሐይቁ ዙሪያ ለኢንቨስትመንት ልማት  እንዳይሰጥ አባገዳ በየነ ጠይቀዋል።

ይልቁን ስፍራው ፕላን ወጥቶለትና በአጥር ተከልሎ ተገቢ እንክብካቤ ሊደረግላት እንደሚገባም  አሳስበዋል።

የሐይቁን ልምላሜ ለማስፋፋት በዘንድሮ ክረምት የዋቄፈቻ እምነት ተከታዮችና አባገዳዎች 40 ሺህ ችግኝ መትከላቸውንም ጠቅሰዋል።

የምክር ቤቱ አባልና የዋቄፈቻ እምነት ተከታዮች ሰብሳቢ ቡላ ሐዬ በበኩላቸው ግለሰቦች ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ላይ ቆሻሻ ከመጣላቸውም በላይ የአልኮል መጠጥ በመያዝ ስፍራውን እያወኩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ስፍራው በአግባቡ ካልተያዘና ጽዳቱ ካልተጠበቀ የኢሬቻ በዓልን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት ሊያደናቅፈው እንደሚችል  ነው ያመለከቱት፡፡

የአካባቢው ነዋሪና  መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ተገቢውን ጥበቃና ከለላ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱ የኢሬቻ በዓል መስከረም 21/2010 ዓ.ም እንዲከበር  መወሰኑን አባገዳው ገልጸው በዓሉ በሠላምና በደማቅ ሥነ ስርዓት እንዲከበር ለማድረግ ከወዲሁ ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ሐይቁን ከጎበኙ በኋላ " የመንግስት ድርሻ የክልሉን ባህልና ታሪክ ማስተዋወቅና ማጠናከር ስለሆነ ታሪካችንንና ባህላችንን በጋራ ለማሳደግ እንረባረባለን " ሲሉ ገልጸዋል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ መለያ አርማ እንደሆነ ጠቁመው በተለይ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ ላይ ግለሰቦች እያደረሱ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት እንደሚሰራ ለአባገዳዎቹ  አረጋግጠውላቸዋል ።

በተለይ ስፍራው በአግባቡ ተይዞና ለምቶ አንዱ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን መንግስት ከአባገዳዎች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፍላጎትና ቁርጠኝነት እንዳለውም ተናግረዋል፡፡   

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው የገዳ ስርዓትን ጨምሮ ሌሎችንም በክልሉ የሚገኙ የባህል እሴቶች በመጠበቅ፣በመንከባከብ፣በማልማትና በማስተዋወቅ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም  ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 29/2009 በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንትነት የሚመራው የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኮሪያ ባህረ ሰላጤ የነገሰውን ውጥረት አስመልክቶ  ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄዳል።

ኢትዮጵያ ነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም የፕሬዚዳትነቱን ስልጣን ከግብጽ ከተረከከበች በኃላ የመጀመሪያውን ስብሰባ የሚያካሄደው ምክር ቤቱ ሰሜን ኮሪያ ትናንት ያደረገችውን የሀይድሮጂን ቦምብ ሙከራ ዋነኛ አጀንዳ አድርጎ እንደሚወያይ ታውቋል።

የአሜሪካ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን አሶሼትድ ፕሬስን ዋቢ አድርጎ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፤ ምክር ቤቱ በሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር መርሃ ግብር ላይ እርምጃ መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይመክራል።

አባላቱ ከዚህ ቀደም በሰሜን ኮሪያ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች በፍጥነት በሚተገበሩበትና አዳዲስ እርምጃዎችን መውሰድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚወያዩም ተጠቁሟል።

የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት የሆኑት ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና አሜሪካ እንዲሁም የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባላት ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ውይይቱ እንዲካሄድ መወሰኑም ታውቋል።

ምክር ቤቱ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ላይ ስብሰባ ሲያደርግ በሳምንቱ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም ዘገባው አስታውሷል።  

የፀጥታው ምክር ቤት ሰሜን ኮሪያ ከአንድ ወር በፊት በጃፓን ላይ ያደረገችውን የባለስቲክ ሚሳኤል ሙከራ ተከትሎ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፤ አገሪቷ ከመሰል ድርጊቶቿ እንድትቆጠብ ማሳሰቡንም ኤቢሲ በድረ ገጹ አስነብቧል።

ሰሜን ኮሪያ ትናንት ያደረገችው የሀይድሮጂን ቦምብ ሙከራ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2006 በኋላ ያደረገችው ስድስተኛው የኒውክሌር ሙከራ መሆኑ በዘገባው ተካቷል።

ሰኔ 2008 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ኢትዮጵያ አፍሪካን ወክላ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆና የተመረጠች ሲሆን፤ ታህሳስ 23 ቀን 2009 ዓ.ም ሥራዋን በይፋ መጀመሯ ይታወቃል።

15 አባል አገራትን ያቀፈው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፤ በአምስት ቋሚ አባል አገራትና በየሁለት ዓመቱ በሚመረጡ አስር ተለዋጭ አባል አገራት የተዋቀረ ነው።

አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝና ሩሲያ የምክር ቤቱ ቋሚ አባል አገራት ናቸው።

ሁሉም የምክር ቤቱ አባል አገራት በየወሩ በመለዋወጥ የፀጥታውን ምክር ቤት በፕሬዚዳንትነት ይመራሉ። 

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር 1967 እስከ 1968 እንዲሁም ከ1989 እስከ 1990 ለሁለት ያህል ጊዜ አገልግላለች።

አሁንም በፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን ለሁለት ዓመታት ታገለግላለች።

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ህዳር 29/2009 ባለፉት አስር አመታት ወደ ጤና ተቋም ሄደው የህክምና አገልግሎት የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር  75 በመቶ መድረሱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

ከአስር አመት በፊት በአመት በጤና ተቋማት  ተመላልሰው ህክምና የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር 20 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 75 ሚሊዮን መድረሱን ነው የሚኒስቴሩ መረጃ የሚያመላክተው።

ለዚህ ውጤት በ2000 ዓ.ም  10 ሺህ አከባቢ  የነበሩ ጤና ኬላዎች ቁጥር  ከ16 ሺህ በላይ መድረስ ፤ የጤና ጣቢያዎች ቁጥር ደግሞ ከ700 ወደ 3 ሺህ ከፍ እንዲልና የሆስፒታሎችም ቁጥርም ከ 93 ወደ  311 እንዲያድግ በመደረጉ መሆኑ ይጠቀሳል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ፕላኒንግ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሱድ መሃመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት የጤናውን ዘርፍ ለማልማት በአራት ምዕራፎች የተከፋፈሉ የ20 አመት ስትራቴጂዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ነው።

ከእነዚህም መካከል  በአስር አመታት ውስጥ የእናቶችና ከአምስት አመት በታች ያሉ ህጻናትን ሞት የመቀነስና ተላላፊ በሽታዎችን የመከላከል ስራ ትኩረት የተደረገባቸው መስኮች ናቸው።

በዚህም የእናቶችና ህጻናት ሞት መቀነስ፤ የኤች. አይ.ቪ ፣ የወባና ሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ስርጭት እንዲሁም  የህብረተሰቡ የአመጋገብ ስርዓት ላይ አያሌ ለውጦች ተመዝግበዋል።

ለተገኘው ውጤት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት የጤና ኬላ፣ የጤና ጣቢያና የሆስፒታሎች መስፋፋት ምክንያት መሆናቸውን ይናገራሉ።

በተጨማሪም ለቅድመ ወሊድ አገልግሎት የጤና ተቋማትን ይጎበኙ የነበሩ እናቶች ቁጥር ከነበረው 61 በመቶ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ መቻሉን ነው የሚጠቁሙት።

በጤናው ዘርፍ ለ15 አመታት ያገለገሉትና በአራዳ ክፍለ ከተማ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳሬክተር የሆኑት ሲስተር ወርቅያንጥፉ ቦጋለ ቀደም ሲል የጤና አገልግሎት ለማግኘት ለቀናት ወረፋ መያዝ የግድ እንደነበር ይናገራሉ።

ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በሰው ኃይል፤ በጤና ተቋማት፣ በጤና አገልግሎት ግብአቶች ላይ በትኩረት በመሰራቱ ህብረተሰቡ በፈለገበት ሰአት አገልግሎቱን እያገኘ መሆኑን ገልጸዋል።

በጤና ባለሙያዎች በኩልም በወቅቱ የነበረው ከ24 ሺህ በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ሙያተኞች ቁጥር አሁን ከ38 ሺህ በላይ፣ ከ16 ሺህ በላይ የነበሩት ነርሶች ከ60 ሺህ በላይ  እንዲሁም ከ2 ሺህ በላይ የነበሩት ሃኪሞች አሁን ከ6 ሺህ 700 በላይ ከፍ ማድረግ ተችሏል።

እነዚህ ውጤቶች ቢመዘገቡም የሰው ኃይል  በተለይም የስፔሻሊስት ሃኪሞች እጥረት በአፈጻጸም ሂደት ያጋጠመ ችግር እንደነበር ተገልጿል።

የህክምና ባለሙያዎች ማህበር አባል የሆኑት ዶክተር የኔነህ ጌታቸው በበኩላቸው የስፔሻሊስት ሐኪሞችን ቁጥር ለማሳደግ አሁንም በትኩረት መሰራት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማሉ።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፖሊሲ ፕላኒንግ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሱድ መሃመድ በበኩላቸው አሁን 1 ሺህ እስፔሻሊስት ሃኪሞች መኖራቸውን በመግለጽ ተጨማሪ በ22 ልዩ ሙያ አይነቶች1 ሺህ 50 እስፔሻሊስት ሃኪሞች በ2010 ዓ.ም ትምህርት ለመጀመር ፈተና ወስደዋል።

የህክምና መሳሪያዎች አስተዳደር ስርአት ጠንካራ አለመሆን፣ ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ከተደራሽነት ጋር አብሮ አለመሄድና ሌሎች በአፈጻጸም ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ ብለዋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ የጤናውን ዘርፍ ሽግግር ዕውን ለማድረግ የጥራትና ሌሎች ችግሮችን ሊፈታ የሚችል የአምስት አመት እቅድ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ይናገራሉ ።

በመሆኑም በከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች ተደራሽነት ላይ ያለውን የሰው ኃይል እጥረት ለመቀነስ የብሔራዊ የስፔሻሊስት ስልጠና ፕሮግራም ተግባራዊ ማድረግ፤ የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን መከላከልና መቆጣጠር ተቋም ማቋቋምና ሌሎች ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ይናገራሉ።

ሚኒስቴሩ በቀጣዩ 2010 ዓ.ም ጥራት፣ የባለሙያ ቁጥር፣ የመሳሪያ አቅርቦትና ሌሎች ላይ ትኩረት አድርገን የምንሰራባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

 

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሀሴ 29/2009 የዓለም የቱሪዝም ቀን"ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል   በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይከበራል፡፡

በዓሉ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከመስከረም 17 /2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት ይከበራል ፡፡

የቱሪዝም ቀን "ቱሪዝም ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል በዓለም ለ38ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ30ኛ ጊዜ ነው የሚከበረው፡፡

በሚኒስቴሩ የቱሪዝም ልማት ዘርፍ  ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መዓዛ ገብረመድህን ዝግጅቱን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ  እንዳሉት የቱሪዝም ቀን  መታሰቢያነቱ  የኢትዮጵያ የቱሪዝም አባት በመባል ለሚታወቁት አቶ  ሀብተሥላሴ ተስፋ እንዲሆን ሚኒስቴሩ ወስኗል።

በዓሉ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም  በማስገንዘብ  ለዜጎች የሥራ እድል መፍጠር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመወያየት እንደሚከበርም ነው የገለጹት።

የቱሪዝም ልማት አካባቢያዊ  ሥነ-ምህዳርን ባማከለ ሁኔታ የሚሰራ እንደመሆኑ ህዝቦች በመስህብ ሃብቶች ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚደረግም ነው ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታዋ።

የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት እ አ አ 1979 በስፔን ቶርምሊኖስ  የዓለም የቱሪዝም  ቀን እንዲከበር በወሰነው መሠረት እ.ኤ.አ ከ1980  ጀምሮ በየዓመቱ መስከረም 17 እየተከበረ ይገኛል።

 

 

Published in ማህበራዊ

ሀዋሳ ነሀሴ 28 /2009 ዓ.ም በደቡብ ክልል ባለፉት አሥር ዓመታት ምርታማነትን ለማሳደግ በተከናወኑ ተግባራት ከግብርና የሚገኘው የምርት መጠን በሦስት እጥፍ ማደጉን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊና የእርሻ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ግርማሜ ጋሩማ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አርሶአደሩ በተሰጠው የክህሎት ስልጠና ታግዞ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን የመጠቀም ልምዱ እያደገ መጥቷል።

በእዚህም በግብርናው መስክ ባለፉት አሥር ተከታታይ ዓመታት በአማካይ ከ8 ነጥብ 6 በመቶ በላይ እድገት ተመዝግቧል፡፡

የክልሉ ግብርና ልማት በአነስተኛ የአርሶአደር ማሳ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶአደሮችን ማሳ በማልማት ግብርናው ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"ከአሥር ዓመታት በፊት አርሶአደሩ ከቤተሰቡ ፍጆታ በተጨማሪ ለገበያ የማምረት ችግር ነበረበት፤ ድህነቱንም አምኖ ይቀበል ስላልነበር አመለካከቱን ለመቀየር ሰፊ ትግል በማድረግ ወደ ምርታማነት እንዲገባ ተደርጓል" ብለዋል፡፡

አብዛኛው የክልሉ አርሶአደር ማሳ ከግማሽ ሄክታር እንደማይበልጥ ያስታወሱት አቶ ግርማሜ፣ የአርሶአደሩን ማሳ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች በግብርናው ዘርፍ የክልሉን ምርት በሦስት እጥፍ ማደጉን ጠቁመዋል፡፡

በእዚህም ከሦስት ዓመት በፊት በክልሉ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደተቻለ ነው የገለጹት፡፡

አቶ ግርማሜ እንዳሉት ከ10 ዓመት በፊት አርሶአደሩ ይጠቀም የነበረው ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ከአምስት መቶ ሺህ ኩንታል በላይ አልነበረም።

በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያና ከ200 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር መጠቀም የሚችልበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በክልሉ በበልግ፣ በመኸርና በመስኖ ከ153 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዓመታዊ ምርት ማምረት የተቻለበት ደረጃ ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።

ባለፉት አሥር ዓመታት የግብርናው መስክ በአማካይ 8 ነጥብ 6 በመቶ እድገት ያሳየ ሲሆን የሰብል ልማቱ ለብቻው በዓመት 11 በመቶ እድገት እየታየበት መሆኑን አቶ ግርማሜ አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ቦሎቄ፣ ጥራጥሬ፣ ሰሊጥና ማሾ በስፋት የሚመረቱ ዋና ዋና ሰብሎች ሲሆኑ በመኸር 30 ሚሊዮን፤ በበልግ 28 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እየተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ድርቅ፣ የዝናብ እጥረት፣ የተባይና የሰብል በሽታ ክስተት እያለም በክልሉ ምርታማነት እያደገ እንደመጣና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ያስመዘገቡ በርካታ ሞዴል አርሶአደሮችንም ማፍራት ተችሏል" ብለዋል፡፡

የሞዴል አርሶአደሮች ሽልማት ከዘጠኝ ዓመት በፊት ሲጀመር 100 ሺህ ብር ሀብት ያስመዘገቡ አርሶአደሮች ተሸላሚ እንደነበሩ አስታውሰው፣ አሁን ላይ አንድ ሚሊዮን ብር ሀብት ያፈሩትን መሸለም እንደተጀመረና ዘንድሮ 20 ሚሊዮን ብር ያስመዘገበ አርሶአደር መኖሩን ገልጸዋል፡፡

እንደአቶ ግርማሜ ገለጻ ከመስኖ ልማት ጋር በተያያዘ ከአስር ዓመት በፊት በመስኖ የሚለማው መሬት ከመቶ ሄክታር የማይበልጠው በአሁኑ ወቅት ከ571 ሺህ 855 ሄክታር በላይ መሬት ማልማት ተችሏል፡፡

በግብርና ሥራው ከራስና ከቤተሰብ ፍጆታ ውጪ ለኢንዱስትሪና ለወጪ ንግድም ታስቦ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለእዚህም በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶአደር ገበያን፣ ኢንዱስትሪንና የወጪ ንግድ ላይ ተመስርቶ እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከውጪ ሀገር የሚመጣውን የብቅል ገብስ ለማስቀረት ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ ጋር በመተባበር  በ14 ወረዳዎች ማምረት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ ዱበና ጎላ ቀበሌ ነዋሪና በመስኖ ልማት የተሰማሩት አርሶአደር ገብሩ አበበ እንዳሉት በመስኖ ልማት በማህበር ተደራጅተው ያላቸውን ስምንት  ሄክታር ማሳ በማልማት ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡

ከዚህም በዓመት 100 ሺህ ብር የተጣራ ገቢ እንደሚያገኙ የተናገሩት አርሶአደሩ በዓመት ሁለት ጊዜ በመስኖ እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላው አርሶአደር አልዬ ሽኩር በበኩላቸው እንዳሉት በመስኖ ልማት ከተሰማሩ ወዲህ በከተማ የመኖሪያ ቤት መስራታቸውንና በአሁኑ ወቅትም በማህበር ተደራጅተው የገበያ ማዕከል እየገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ነሃሴ 29/2009 በትግራይ ክልል የሚገኘው ገንፈል ኮሌጅ በሁለት የትምህርት ዓይነቶች ያሰለጠናቸውን 156 ተማሪዎች ትናንት በደረጃ አራት አስመረቀ፡፡

ኮሌጁ ተማሪዎችን ለሦስት ዓመታት አሰልጥኖ ያስመረቀው በፋይናንስና በጀት እንዲሁም በሀርድ ዌርና ኔትዎርኪንክ የትምህርት ዘርፎች ነው፡፡

በውቅሮ ከተማ በተካሄደው ስነስርዓት ላይ የኮሌጁ ዲን አቶ ገብረዮሀንስ ገብረማሪያም እንዳሉት ኮሌጁ በሁለቱ የሙያ ዘርፎች ተማሪዎችን ማሰልጠን የመረጠው የክልሉ ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና  ቢሮና ኮሌጁ ባካሄዱት የገበያ ጥናት መሰረት ነው፡፡

የእለቱ ተመራቂዎችም በስልጠናው ወቅት የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ስራ ፈጥረው መስራትና የገበያ ክፍተትን መሙላት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብረሀ  ኪሮስ በበኩላቸው የእለቱ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት ሙያ ጠንክረው በመስራት የተሻለች አገር ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ወጣት ኪዳነ ወልደማሪያም በሰጠው አስተያየት በተማረበት ፋይናንስና በጀት የትምህርት ዘርፍ  የግል ስራ ለመስራት ማቀዱን ገልጿል፡፡

የኮሌጁ ስራ እስኪያጅ አቶ መብራህቱ ሀፍቱ እንዳሉት በሚቀጥሉት አምስት አመታት የሙያና ቴክኒክ የትምህርት ዘርፍን ጨምሮ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ለማስተማር እቅድ መያዙን ገልፀዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን