አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 03 September 2017

ሀረር ነሀሴ28/2009 መንግስት ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስናን ለመከላከል የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ በሐረሪ ክልል የሚገኙ የደኢህዴን/ኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ገለጹ።

 አባላቱና ደጋፊዎቹ ይህን ያሉት ደርጅቱ የተመሰረተበትን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል "በስኬት በታጀበ ጉዟችን ወደ ሕዳሴው ማማ" በሚል መሪ ቃል" በሐረር ከተማ ባከበሩበት ወቅት ነው።

በዓሉ በከተማው በሚገኘው አሚር አብዱላሂ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ሲከበር አባላቱና ደጋፊዎቹ እንዳሉት በመንግስት የተጀመረው የጸረ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላቸውን ጥረት ያደርጋሉ።

 በበዓሉ ላይ ከተገኙት መካከል የድርጅቱ አባል መቶ አለቃ  ደበላ ደስታ "የድርጅቱ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል የምናከብረው መላው የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች  የልማት እንቅፋት የሆኑትን ኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ ቃል በመግባት ነው" ብለዋል።

 የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች ከሁከትና ብጥብጥ ምንም ጥቅም እንደማይገኝ ተረድተውና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው በክልሉ በሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ላይ  የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

 ውድ ታጋዮች በከፈሉት መስዋዕትነት  የሕብረተሰቡ የልማት ተጠቃሚነት በየጊዜው እያደገ መምጣቱን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መሊካ አልይ ናቸው።

 "በዓሉን የምናከብረው የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎች አበረታች የልማት ሥራዎችን እጅ ለእጅ ተያይዘን አጠናክረን ለማስቀጠል ቃል በመግባት ነው" ብለዋል።

 አቶ ታሪኩ ሀምቢሶ የተባሉ ሌላው የድርጅቱ አባል በበኩላቸው፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮችን መፍታት የድርጅቱ አባላት አንገብጋቢ ጉዳይ እንደነበር አስታውሰዋል።

 መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ እያደረገው ያለው ጥረት ህዝቡ ያነሳቸው የነበሩ ችግሮች ተቀርፈው መልካም አስተዳድር እንደሲሰፍንና መንግስትና ህዝብ ፊታቸውን ሙሉ ለሙሉ ወደልማት እንዲያዞሩ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል።

 ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ተቀርፈው የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ መንግስት የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመው ለእዚህም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

 የክልሉ የደኢህዴን/ ኢህአዴግ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ነሪ ባደረጉት ንግግር በተለይ ባለፉት ጊዜያት በህዝብ ላይ ቅሬታ የፈጠሩትን የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮች ድርጅቱ ሲታገል መቆየቱን ገልጸዋል።

 በተያዘው ዓመት አጋማሽ የተካሄደውን ጥልቅ የተሃድሶ መድረክ መነሻ በማድረግም በአሁኑ ወቅት ችግሮችን የመፍታትና ልማትን ሊያፋጥኑ የሚችሉ ሥራዎችን መከናወናቸውንና በእዚህም አበረታች ለውጦች እየተመዘገቡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

 ድርጅቱ ሕብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የጀመረውን ፈጣን ልማት የማስመዝገብና ወጣቱን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 ለእዚህም የድርጅቱ አባላትም ሆነ ደጋፊዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከድርጅቱ ጎን በመሰለፍ የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮችን ለመፍታት የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 የደርጅቱ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አስመልክቶ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ስነጽሁፋዊና ኪነጥበባዊ  ዝግጅቶች ለታዳሚው የቀረቡ ሲሆን የእህትና የአጋር ድርጅት ተወካዮች ለደኢህዴን ያለቸውን ድጋፍ በንባብ አሰምተዋል ።

Published in ፖለቲካ

 አዲስ አበባ ነሐሴ 28/2009 የአሸንዳ በዓል የህብረተሰቡን  ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት  እያሳደገ መሆኑ ተገለጸ።

 በአዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ ሴቶች ዛሬ የአሸንዳን የማጠቃላያ በዓል በሚሊኒየም አዳራሽ አክብረዋል።

 "ባህላዊ ሀብታችንን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን እናረጋግጠለን"  በሚል መሪ ቃል በተከበረው የማጣቃላያ በዓል ከፍተኛ የመንግስት  ባለስልጣናትን ጨምሮ ከ20 ሺህ በላይ የህረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 የትግራይ ሴቶች ማህበር ዋና ስራ አስካያጅ ወይዘሮ ዘነበች ፍሳሃ እንደገለጹት የአሸንዳ በዓል ባህሉን ጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውለድ እንዲሸጋገር በመደረጉ ለህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እገዛ አድርጓል።

ለዚህም በዓሉን የሚያከብሩ ሴቶች የሚለብሱት ልብስ  አገር ውስጥ የተመረተ በመሆኑ በሽመናም ሆነ በስፌት የተሰማሩ የህብረተሰብብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረጉን በአብነት አንስተዋል።

 በቀጣይም በዓሉን በዩኒስኮ  ለማስመዝገብና ህብረተሰቡም በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ዕድል ለማስፋት ጥረት እየተደረገ  መሆኑን አብራርተዋል።

 የትግራይ ሴቶች ማህበር አዲስ አበባ ቅርንጫፍ  ስራ አስካያጅ ወይዘሮ ምሕረት ምናስብ ዘንድሮ በአዲስ አበባ ለ15ኛ ጊዜ በተከበረው የአሸንዳ በዓል አንድ ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ገልጸዋል።

 ገንዘቡ በችግር  ምክንያት ከትምህርት ገበታ ለራቁ ህጻናትና ለተገቸገሩ እናቶች እንደሚውልም ተናግረዋል።

 አሸንዳን  ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የኢትዮጵያ ባህሎች   በማበልጸግና ለዓለም በማስተዋወቅ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም ነው ወይዘሮ ምህረት የጠቆሙት፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ ነሀሴ 28/2009 በሀገረ አቀፍ ደረጃ የእናቶችና ሕጻናት ቀን ታስቦ መከበሩ መንግስት ለእናቶችና ሕጻናት ልዩ ትኩረት መስጠቱን ያሳያል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ የጋምቤላ ከተማ እናቶች ተናግሩ።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አኳታ ኡሚዩ አንዳሉት መንግስት ለአዲስ ዓመት አቀባበል በሚያደርገው ዝግጅት ውስጥ የእናቶች ቀን እንዲታሰብ ማድረጉ ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች የሰጠውን የተለየ ትኩረት ያሳያል።

ቀኑ በተለየ ሁኔታ መከበሩ እናቶች ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ግንባታ ያላቸውን ሚና ከማረጋገጥ ባሻገር ትውልዱን በመቅረጽ በኩል ያላቸውን ድርሻ የጎላ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

"የእናትና የልጅ ፍቅር ሁሌም የጸና በመሆኑ አዲስ ዓመትን ለመቀበል ለሚደረገው ዝግጅት የእናቶችና የህጻናት ቀን ተብሎ በሀገረአቀፍ ደረጃ መከበሩ መንግስት ለእኛ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ያሳያል" ያሉት ደግሞ ሌላዋ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኢታይ ወልዱ ናቸው።

"መጪውን አዲስ ዓመት ስንቀበል እናትና ልጅ አንዳላቸው የጠበቀ ግኑኝነት በአዲስ መንፈስና ደስታ እርስ በርስ በመፈቃቀር መሆን አለበት" ብለዋል።

ወይዘሮ ኙጌድ ኡዋሪ በበኩላቸው መንግስት የእናቶችንና ህጻናትን ቀን ማክበሩ ለእነዚህ አካላት በጤናና በተለያዩ መንገዶች ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍና  እክብካቤ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።

ህጻናት በሥርዓት አድገው የወደፊት አገር ተረካቢ በመሆናቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለእናቶችና ሕጻናት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል።

አዲሱን ዓመት ለመቀበል ከነሀሴ 26 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ የተለያዩ ሁነቶች በመንግስት እየተተገበሩ ሲሆን በእዚህም ትናንት ነሐሴ 27 ቀን 2009ዓ.ም  የእናቶችና ህጻናት ቀን ተብሎ መከበሩ ይታወሳል።

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሐሴ 28/2009 የላቀ ውጤት አስመዝግበው የሚመረቁ ተማሪዎችን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ስልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ኢንፎኔት ኮሌጅ ገለፀ።

ኮሌጁ በአካውንቲንግና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በደረጃ አራት ያሰለጠናቸውን 344 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

በመደበኛና በማታ መርሃ ግብር ካስመረቃቸው ተማሪዎች 182ቱ ሴቶች ሲሆኑ ከመካከላቸው 50ዎቹ ኮሌጁ በነፃ የትምህርት ዕድል ያሰለጠናቸው ናቸው።

የኮሌጁ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ገብረሚካኤል እንደተናገሩት የላቀ ውጤት አስመዝግበው በመጀመሪያ ዲግሪና በድህረ ምረቃ የተመረቁት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ኮሌጁ ተጨማሪ ስልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀ ነው። 

ኮሌጁ የራሱንና የሌሎች ኮሌጆች ተማሪዎችን በአሜሪካ ከሚገኝ ዳናስት ከተባለ ድርጅት ጋር በማሰልጠን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ስልጠናው በ30 ተማሪዎች የሚጀመር ሲሆን ዌብነር በተሰኘ ሶፍትዌር በመታገዝ በድረ ገፅ አገር ውስጥ ሆነው ከድርጅቱ ስልጠናውን የሚያገኙ ይሆናል።

ተማሪዎቹ የሚያገኙት ስልጠና አገሪቱ ከውጭ ባለሙያ ለማስመጣት ታወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ ለማስቀረት እንደሚያግዝ ነው አቶ ሰለሞን የተናገሩት።

በሌላ በኩል ኮሌጁ የድህረ ምረቃ ትምህርት ሊጀምር መሆኑን ገልፀው ተመራቂዎች በሚሰማሩበት ሙያ ለአገሪቱ እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኘው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም ተመራቂዎቹ  ያስተማራቸውን ቤተሰብና ኅብረተሰብ በእውቀታቸው እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርቧል።

ኢንፎኔት ኮሌጅ ከተመረሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከ10 ሺህ በላይ ለሆኑ ሰዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሁም ከ5 ሺህ በላይ ለሆኑ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል መስጠቱ ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

ነሐሴ 28/2009 አልሻባብ በሶማሊያ ኪስማዩ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የሀገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ካምፕ ማጥቃቱን ተከትሎ በተወሰደው የአጸፋ እርምጃ በትንሹ 20 ታጣቂዎችን መግደሉንና በርካቶችን ማቁሰሉን የሀገሪቱ ጦር አስታወቀ፡፡

ከሀገሪቱ መከላከያ ኃይል እስማዔል ሳሃርዲድ ታጣቂ ቡድኑ ከኪስማዩ በስተሰሜን አቅጣጫ 30 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቡሎ ጉዱድ የተሰኘ ወታደራዊ ካምፕ የሰነዘረው ጥቃት በሁለቱም ወገን ጉዳት ማድረሱን አረጋግጠዋል፡፡

 አሸባሪ ቡድኑ በተሸከርካሪ ላይ በተጠመደ ቦምብ የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት መሰንዘሩን  ተከትሎ በተከፈተው የተኩስ ልውውጥ 20 ታጣቂዎች መገደላቸውን ተናግረዋል፡፡

ወታደራዊ ካምፑም በቁጥጥራቸው ስር እንደሆነ ይፋ አድርገው በመንግሥት ወታደሮች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

አልሻባብ በበኩሉ በመንግሥት ኃይሎች ላይ ድል መቀዳጀቱንና 25 ወታደሮችን ገድሎ ሶስት ተሸከርካሪዎችንና በርካታ የጦር መሳሪያዎችን መማረኩን ገልጿል፡፡

ወገንተኛ ያልሆኑ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ የቻይናው ዓለም ዓቀፍ ቴልቪዥን ኔትወርክ እንደዘገበው ግን አደጋው ሁለቱም ወገኖች ከተናገሩት  በላይ ነው፡፡

24 የጁባላንድና የመንግስት ወታደሮች ኪስማዩ በሚገኘው ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንም ነው ምንጮቹ የተናገሩት፡፡

ታጣቂ ኃይሉ የሚያደርሳቸው ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረትና የሀገሪቱ ጸጥታ ኃይሎች በደቡባዊ ሶማሊያ የሚያደርጉትን የአየር ጥቃት አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡

በዚህም  በርካታ የታጣቂ ቡድኑ አባላት የተገደሉ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ አካባቢውን ለቀው እየሸሹ መሆናቸውም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

በተባበሩት ምንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ የቆይታ ጊዜው እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደሴ ነሀሴ 28/2009 አማራ ክልል ወባን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተሰራው ሥራ ውጤት በማስገኘቱ በቀጣይ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት እንደሚሰራ የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡

 በክልሉ በሚገኙ ሦስት ዞኖችና አንድ የከተማ አስተዳደር ወባን የማጥፋት መርሃ ግብር ዘመቻ ትናንት በኮምቦልቻ ከተማ ይፋ ተደርጓል፡፡

 የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ወባን ለመከላከል መንግስት፣ የፖለቲካ አመራሩና ባለድርሻ አካላት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሲሰሩ ቆይተዋል።

 የተጠናከረ የኬሚካል ርጭት፣ የአጎበር ስርጭት እንዲሁም ህብረተሰቡ አካባቢውን የመቆጣጠር ሥራ በመስራቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ወባ በክልሉ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ማድረግ ተችሏል፡፡

 በክልሉ በ2005 በጀት ዓመት በወባ የተያዘው ሰው ብዛት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሰው በተያዘው ዓመት ቁጥሩ ወደ 387 ሺህ ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል፡፡

 ዶክተር አበባው እንዳሉት፣ ወባ በክልሉ ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በእጅጉ የቀነሰ ቢሆንም አሁንም ከዋና ዋና የጤና ስጋቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡

 የወባ በሽታን እስከ 2030ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ብሔራዊ የወባ ማስወገድ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

 የዘመቻውን  መርሀ ግበር ወደ ተግባር ለማሸጋገር ዘመቻው በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ ዞንና በደሴ ከተማ አስተዳደር እንደሚጀመር ይፋ አድርገዋል።    

 መርሃ ግብሩ ባለሙያው ወደህዝብ በመውረድ የችግሩን ምንጭ በማድረቅ ዘላቂ መፍትሄ የሚያስቀምጥበት አሰራር የሚዘረጋ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በቢሮው የማሕበረሰብ ጤና አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ተክለሃይማኖት ገብረህይወት ናቸው፡፡

 ዘመቻው በቅርቡ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር በማሰራጨት እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

 የክልሉ ምክርቤት አፈ ጉባኤ አቶ ይርሳው ታምሬ በበኩላቸው መርሃ ግብሩ ውጤታማ ይሆን ዘንድ የሕብረተሰቡ፣ የፖለቲካ አመራሩና የአጋር ድርጅቶች ሚና የላቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 ወባን በማጥፋት አገሪቱ ያስቀመጠችውን ግብ ለማሳካት ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በክልሉ መንግሥት ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 የወባ ስርጭት በክልል በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንስም  በአንዳንድ አካባቢዎች በወባ የሚያዙ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ቁጥር በሚፈለገው መጠን አለመቀነሱን አመልክተዋል፡፡

 "ዘመቻው ለሁለት ዓመታት የሚዘልቅ ሲሆን በእዚህም ቀደም ሲል የነበሩ የወባ መከላከልና መቆጣጠር ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋል" ብለዋል።

 በዘመቻው ተሞክሮዎች ተቀምረው ከፍተኛ የወባ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች ተግባራዊ  እንደሚደረጉም አመልክተዋል።

 በይፋ ማድረጊያ ዝግጅቱ ላይ ከፌዴራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ አመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎችና አጋር አካላት ተገኝተዋል ነው፡፡

Published in ማህበራዊ

 ዲላ ነሀሴ 28/2009 በጌዴኦ ዞን ህዝቡ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየውን የአብሮነት እሴት በማጎልበት በአካባቢው ዳግም የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት በጋራ እየሠሩ መሆናቸውን የሃይማኖትና የባህል መሪዎች ገለፁ ፡፡  

 "መቻቻልና አብሮ መኖር የዳበሩ የህዝባችን ዕሴቶች ናቸው" በሚል መሪ ቃል በዞኑ ሰላም ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡

 በመድረኩ የተሳተፉ የባህልና የሃይማኖት መሪዎች እንደተናገሩት የዞኑ ህዝብ ለዘመናት ያቆያቸውን የመፈቃቀር፣ የመከባበርና ተቻችሎ አብሮ የመኖር እሴቶችን ይበልጥ በማጠናከር በህዝቡ መካከል የተፈጠረውን መሻከር ለማርገብ እየሠሩ ይገኛሉ ፡፡

 የጌዴኦ ብሔር ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት መሪ አባ ገዳ ደንቦቢ ማሮ ቀደም ሲል በአካባቢው የፀጥታ ችግር ተከስቶ እንደነበር አስታውሰዋል።

 ከክስተቱ ማግስት ጀምሮ በባህላዊ ሸንጎዎች፣ በትምህርት ቤቶችና በእምነት ቦታዎች በመገኘት ሕብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ በመስራት መንግስት ችግሩን ለመፍታት ያደርግ የነበረውን ጥረት ሲያግዙ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡

 አባ ገዳ ደንቦቢ እንዳሉት፣ ሠላም የማስፈን ሂደቱ እንዲሳካ ብሎም ዳግም ህዝቡን የሚያቃቅር ድርጊት እንዳይፈጠር ለማድረግ በዞኑ በሚገኙ 525 ባህላዊ ሸንጎዎች ወጣቶችን ስለ አብሮነት እሴቶች በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡

 በቀጣይም ይህን ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት፡፡

 በሲዳማና ጌዴኦ ዞኖች የአማሮና ቡርጂ ወረዳዎች ሀገረ-ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅና የደቡብ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ሊቀ-ጉባኤ አባ ሀብተማርያም ገብረ መስቀል በሀገሪቱ ውስጥ የትኛውም የሃይማኖት ተቋም ፀረ-ሠላም አስተምህሮ እንደሌለው ጠቁመዋል፡፡

 ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው ንፁሀን ዜጎችን ለሁከትና ብጥብጥ የሚዳርጉ ኃይሎችን ለይቶ በማስተማር ከድርጊታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ አባታዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የጀመሩትን ጥረት እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል ፡፡

 የጌዴኦ ዞን የሃይማኖት ተቋማት ጥምረት አባል የሆኑት መጋቢ ምስራቅ ሀጢያ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት የተገኘውን ሰላም ለማደፍረስ እየተንቀሳቀሱ ያሉአካላት መኖራቸውን ጠቁመዋል።

 የእነዚህን ወገኖች እኩይ ተግባር ለማክሸፍ በየቤተ እምነቱ ስለሠላም አስፈላጊነት አፅንኦት ሰጥቶ ለምዕመናን ማስተማር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

 የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው፣ ዞኑ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ተዋደውና ተቻችለው የሚኖሩበት መሆኑን ጠቁመው ፀረ-ሠላም ኃይሎች ይህ እንዲደፈርስ ባደረጉት ጥረት በሰላም ወዳዱ ህዝብ መካከል መቃቃር ተፈጥሮ አንደነበር አስታውሰዋል ፡

 ክስተቱ በዞኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ ጊዜያዊ መቀዛቀዝ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም የሃይማኖትና የባህል አባቶች ከመንግስት ጎን ሆነው ህዝቡን በማስተባበር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ሁኔታው መቀልበሱን አስረድተዋል፡፡

 በአርብቶአደር ጉዳዮች ልማት ሚኒስቴር የሠላም እሴት አስተምህሮ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፍቅር ግርማ ሚኒስቴሩ በሁሉም አካባቢዎች የሠላም አደረጃጀቶችንና ፎረሞችን በማቋቋም የግጭት መንስኤዎችን በመቀነስ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 በዞኑ ባለፈው መስከረም ተከስቶ የነበረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ዘላቂ ሠላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል ፡፡

 በዞኑ እርቀ-ሠላም ለማውረድ በየደረጃው ሲደረጉ የነበሩ የሠላም መድረኮች እንደቀጠሉ ሲሆን ጳጉሜን 02 ቀን 2009 ዓ.ም በሁሉም ወረዳ እና የከተማ አስተዳደሮች የማጠቃለያ ኮንፈረንሶች እንደሚካሄዱ ተመልክቷል።

 በመድረኩ የግጭት መንስኤዎችና የአፈታት መፍትሔዎችን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዲሁም በዞኑ ባለፈው መስከረም ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ተቃቅረው የነበሩ ወገኖችን ወደ እርቀ-ሰላም ለማምጣት በተከናወኑ ተግባራት ላይ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

 ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በእዚህ መድረክ የባህልና የሃይማኖት መሪዎች፣ የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮች፣ ከየወረዳው የተውጣጡ የሚመለከታቸው አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ነሀሴ 28/2009 በአፋር ክልል ለ12ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ዝግጅት የሚከናወኑ የመሰረተልማት ሥራዎች ወጣቶችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

 ድንበር የለሽ የወጣቶች በጎፍቃድ አገልገሎት ቡድን ሰሞኑን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በነበረው ቆይታ ለብሔር ብሔረሰቦች ቀን እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል።

 በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ታረቀኝ አብዱልጀባር እንደተናገረው፣ በክልሉ ከበዓሉ ጋር ተያይዞ  እየተከናወኑ የሚገኙ የመሰረተልማት ሥራዎች የከተማዋን እድገት ከማፋጠን ባለፈ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ናቸው።

 በተለይ ወጣቶች እየተከናወኑ ባሉ ግንባታዎች በተለያዩ ሙያ መስክ በመሳተፍ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ኢኮኖሚዊ ተጠቃሚነታቸውን በማረጋግጥ ላይ መሆናቸውን ተናግሯል።

 ወጣቶቹ ባላቸው የትምህርት ደረጃ ሰርተው ተጠቃሚ ከመሆናቸው በተጨማሪ የሥራ ልምድ፣ የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ተጠቃሚ እየሆኑ ስለመምጣታቸው በጉብኝቱ ወቅት መገንዘባቸውን አብራርተዋል።

 በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሺን የሰመራ እስታዲዮም ግንባታ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አሸናፊ ጸሀዬ አንደተናገሩት፣ በእስታዲየሙ ግንባታ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

 ከዚህ ውስጥ ቁጥራቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአካባቢው ወጣቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

 በእዚህም ወጣቶቹ ገቢ ከማግኘት ባለፈ የሙያ ባለቤት ሆነው ቀጣይ ሕይወታቸውን ለመሳካት ጠቃሚ ልምድ እየቀሰሙ መሆኑን ተናግረዋል።

 የሰመራ ከተማ ነዋሪ ወጣት አህመድ ሳልህ  በበኩሉ እንዳለው፣  በሰመራ ስታዲየም ግንባታ ሥራ በምህንድስና ሙያ ተቀጥሮ ተጠቃሚ በመሆኑን ላይ ነው።

 የተፈጠረለት የሥራ ዕድል በተማረው የሙያ ዘርፍ ያካበተ ልምድና እውቀት ካላቸው ባለሙያዎች ጋር አብሮ የመስራት ዕድል እንደፈጠረለት ገልጾ፣ ይህም ከሚያገኘው የገንዝብ ጥቅም በላይ ለቀሪ ሕይወቱ መሰረት እንደሚሆነው አመልክቷል።

 ለበዓሉ ታስቦ ሥራው እየተፋጠነ ባለው የሰመራ አየር ማረፊያ ግንባታ ፕሮጀክት በጸሐፊነት ሙያ በመስራት ተጠቃሚ መሆኗን የተናገረችው ደግሞ ወጣት ፋጡማ ሙሳ ናት።

 ከዚህ በፊት ሥራ አጥታ እቤት በመዋሏ በትምህርት የቀሰመችው እውቀት ሊጠፋት ተቃርቦ አንደነበር ጠቁማ፣ ያገኘቸው የሥራ ዕድል  ሙያዋን ከማጎልበት ባለፈ የተሻለ ሕይወት ለመምራት መነሳሳት እንደፈጠረባት ተናግራለች።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሐሴ 28/2009 በአካባቢያቸው ከሚገኘው ዕድር የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘታቸው በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የተውጣጡና ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ተማሪዎች ገለጹ።

‘በጄኔራል ዊንጌት አካባቢ በህይወት ሳለን መረዳጃ ዕድር’ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ለ140 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

በመርሃ ግብሩ ረዳት ለሌላቸው አረጋውያን ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ለበርካታ ዓመታት ላገለገሉ መምህራን የዕውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቷል።

ተማሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ከመረዳጃ ዕድሩ ለተከታታይ ሁለትና ሶስት ዓመታት የተለያዩ የመማሪያ ቁሳቁስ፣ የቦርሳና የዩኒፎርም ድጋፍ አግኝተዋል።

ካሳሁን ደሳለኝ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ክፍል ድረስ በአንድ ዩኒፎርም፣ ቦርሳና ባልተሟሉ የትምህርት ቁሳቁሶች መማሩን ያስታውሳል።

በዚህ ሳቢያ ትኩረቱን ትምህርቱ ላይ ማድረግ ባለመቻሉ ውጤታማ እንዳልነበረ ነው የገለጸው።

"ከአራተኛ ክፍል ጀምሮ ግን መረዳጃ ዕድሩ በየዓመቱ ዩኒፎርም፣ ቦርሳና ሌሎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን እያሟላላኝ በመማሬ ውጤቴ በጣም ተሻሽሏል" ሲል ተናግሯል።

የስድስተኛ ክፍል ተማሪው እሱባለው ፈርሻም  የትምህርት ቁሳቁሶች ሳይሟሉለት በመማሩ አራተኛ ክፍልን ደግሟል።

ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ባገኘው ድጋፍ ያለ ሀሳብና ጭንቀት እየተማረ መሆኑን ገልጾ "ከክፍሌም እስከ አስረኛ ባለው ደረጃ ለመውጣት ችያለሁ" ብሏል።

በህይወት ሳለን መረዳጃ ዕድር ከመዋዕለ ህጻናት ጀምሮ እያስተማራት መሆኑን የገለፀችው ደግሞ የአንደኛ ክፍል ተማሪዋ ዕድላዊት ባዱ ነች።

በክፍሏ ካሉት ተማሪዎች አንደኛ ወይም ሁለተኛ እንደምትወጣ ነው የገለፀችው።

የዕድሩ መስራች አባል አቶ ዘርይሁን ክበቡ ከ20 ዓመታት በፊት አንዲት አረጋዊ በጠና ታመው አባል ከሆኑበት ዕድር እርዳታ ሲጠይቁ በወቅቱ የነበረው ደንብ ስለማይፈቅድ ድጋፍ ሳይደረግላቸው ህይወታቸው ማለፉን ያስታውሳሉ።

አዛውንቷ ላይ በተከሰተው አሳዛኝ አጋጣሚ ሳቢያ 'በህይወት ሳለን መረዳዳት አለብን' በሚል መነሻ ዕድሩ መቋቋሙን ገልፀዋል።

ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ የዕድሩ አባላት በየዓመቱ 150 ብር በማዋጣት 'አንድም ልጅ በችግር ምክንያት ከትምህርት ቤት እንዳይቀር ሁላችንም ኃላፊነት አለብን' በሚል ዓላማ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዕድሩ አባላት በሚሰበሰው  ገንዘብ ለችግረኛ ቤተሰቦች፣ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች ለተመረጡና ወላጆቻቸውን በተለያዩ ምክንያቶች ላጡ ተማሪዎች ድጋፍ እንደሚደረግን ነው የተናገሩት።

በተለያዩ የሙያ መስኮች ለበርካታ ዓመታት ላገለገሉ እንዲሁም ለአካባቢ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችም የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራሞች እንደሚዘጋጅ ጠቅሰዋል አቶ ዘርይሁን።

ዕድሩ ረዳት ለሌላቸው አረጋውያን በየዓመቱ የብርድ ልብስና አንሶላ፣ የጽዳት መጠበቂያ ቁሳቁሶችና ለአዲስ ዓመትም የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያበረክት አክለዋል።

የዕድሩ አባል የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ግርማ ሌሎች መረዳጃ ዕድሮች የማህበረሰቡን የእርስ በእርስ መደጋጋፍና ትስስር በሚያጠናክር መልኩ እንዲሰሩ ተሞክሯቸውን እያሰፉ እንደሚገኙ ለኢዜአ ገልፀዋል።

በጄኔራል ዊንጌት አካባቢ በህይወት ሳለን መረዳጃ ዕድር በዓመታዊ የጉብኝት መርሃ ግብር የአገርህን እወቅና ሌሎች ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

"በየአካባቢያችን በሚገኙ ዕድሮች እርስ በእርስ ከተረዳዳን ችግሮችን በቀላሉ መቅረፍ እንችላለን" ያሉት ደግሞ የዕድሩ ሊቀመንበር አቶ አለምነህ ግርማ ናቸው።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ብቻ የሚገኙት 700 የሚሆኑ ዕድሮች ይህን ተሞክሮ ቢተገብሩ ብዙ ለውጥ ማምጣት ይቻላል" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሐሴ 28/2009 የዛሬዋን ኢትዮጵያ ያቆዩትን ደጋፊና ተንከባካቢ ያጡ አረጋውያንን መንከባከብና መደገፍ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነት መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ አስገነዘቡ።

መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል "የዛሬዋን ኢትዮጵያ ለሰሩ ክብር እንሰጣለን" በሚል መሪ ቃል  የሚሊኒየሙን አስረኛ አመት የአረጋውያን ቀን ሀያት በሚገኘው ማዕከሉ አክብሯል።

አፈጉባኤውን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች በማዕከሉ ተገኝተው ቀኑን አክብረዋል።

አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሀገርን የገነቡና ጥሩ ስራ የሰሩ አረጋውያንን በመንከባከብና በመደገፍ በኩል መቄዶንያ ያከናወነውና በማከናወን ላይ ያለው ተግባር  በአርዓያነት የሚጠቀስ መሆኑን ገልፀዋል።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ አብዱልፈታ አብዱላሂ በበኩላቸው በአሉ ለማዕከሉ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን ለመቀጠል ቃላችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።

የማዕከሉ መስራች አቶ ቢንያም በለጠም እስካሁን መንግስታዊ ተቋማት፣የግል ድርጅቶችና ግለሰቦች ላደረጉት  ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡

ማዕከሉ ከመንግሥት፣ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከግለሰቦች በሚያገኘው ድጋፍ  አቅም ያላቸውን ተረጂዎች  በብረታ ብረት፣ በሽመና ፣ በጽዳት፣ በእደ ጥበብና መሰል የስራ ዘርፎች እያሰመራ መሆኑም ታውቋል፡፡

አቶ ተከስተ ብረሃን የተባሉት አረጋዊ  ማዕከሉ እራሱን በራሱ መርዳት እንዲችል ተረጂዎቹ በሚችሉት የስራ ዘርፍ መሰማራት የሚያስችሏቸው  የስራ መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቶ ጌታሁን መኮንን የተባሉት የእድሜ ባለጸጋ ደግሞ  በማዕከሉ እርዳታ ከጎዳና ተነስተው ጤንነታቸውም ተስተካክሎላቸው ለስራ መብቃታቸው ከሞት የመነሳት ያህል እንደሆነባቸው ነው የተናገሩት፡፡

መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለሚያደርገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ድጋፉ ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው የጠየቁት፡፡

ቀኑን ምክንያት በማድረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር  ለማዕከሉ 210 ሺ 500 ብር የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጸህፈት ቤትም 70 ጋቢዎችን ለአረጋውያኑ አበርክቷል፡፡

በዕለቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሃያት አካባቢ ለማዕከሉ  በነጻ በሰጠው ሶስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ 1ሺ 500 አረጋውያን የተጠለሉበት  ጊዜያዊ መጠለያም ተጎብኝቷል።

የሚሊኒየሙን 10ኛ አመት በማስመልከት “መጭው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው” በሚል መሪ ቃል  የሚከናወኑ መርሃ ግብሮች እስከ ጳጉሜ 5/2009 የሚካሔዱ ሲሆን በነገው ዕለትም  የሰላም ቀን ተከብሮ ይውላል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን