አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Saturday, 02 September 2017

ማይጨው ነሀሴ 27/2009 በትግራይ ደቡባዊ ዞን ሶስት ወረዳዎች የተከሰተውን አጣዳፊ  ተቅማጥና ትውከት በሽታ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገለጸ፡፡

በመምሪያው የጤና ልማት ቡድን አስተባባሪ አቶ መሳይ አበበ እንደገለጹት በዞኑ  ራያ አዘቦ ፣ ራያ አላማጣና እንዳመሆኒ ወረዳዎች  በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በአንድ ሳምንት ውስጥ  70 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል፡፡

ሰዎቹ ለመጠጥ የሚገለገሉበት የምንጭ ውሃ በጎርፍ በመበከሉና በንጽህና ጉድለት  ለአተት በሽታ መጋለጣቸውን አመልክተዋል፡፡

በበሽታው የተጠቁት ሰዎች  በማይጨው፣  በአላማጣና መሆኒ ሆስፒታሎች በተዘጋጀው ልዩ  ማዕከላት ተኝተው የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡

ለአካባቢው  ነዋሪ ህዝብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት አስቀድሞ በመሰጠቱ እንዲሁም በጤና ባለሙያዎች ድጋፍና ክትትል ህሙማን ፈጥነው ወደ ጤና ህክምና ቦታ  መጥተው እንዲታከሙ በመደረጉ እስካሁን የከፋ ችግር እንዳላጋጠመ አስተባባሪው ተናግረዋል።

በገጠሩ አከባቢ የሚገኙ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን በየጊዜው በማከምና የግንዛቤ መስጨበጫ ትምህርት መስጠቱን በመቀጠል በሽታውን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንዳለም ተገልጿል፡፡

በበሽታው ተይዘው በአላማጣ ሆስፒታል ተኝተው የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙ  አርሶአደሮች መካካል ወይዘሮ ጄቶ ኩቤ አንዱ ናቸው።

አርሶ አደሩ እንዳሉት፣መንገድ ሲጓዙ ውሃ ጠምቷቸው የምንጭ ውሃን በመጠጣታቸው ምክንያት በበሽታው ተይዘው በቤተሰቦቻቸው ድጋፍ ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ ተናግረዋል።

ወዲያውኑ በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች በተደረገላቸው ህክምና እርዳታ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

ንጉስ ካህሳይ የተባሉት አርሶ አደር በበኩላቸወ ቀደም ሲል በአተት በሽታ ታመው በሆስፒታሉ ህክምና ተደርጎላቸው ካገገሙ በኋላ ወደ አካበቢያቸው ሲመለሱ ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ከበሽታው ለመጠበቅ የውሃ አጋር ይዘው መሄዳቸውን አመልክተዋል።

" ይሁንና የእርሻ መሬቴን እያረስኩ ከዋልኩ በኋላ ወደ ቤቴ ስመለስ ውሃ ጠምቶኝ  የኩሬ ውሃ በመጠጣቴ በድጋሚ ለበሽታው ተዳረኩኝ"  በማለት ገልጸዋል።

አሁን በተደረገላቸው ህክምና ጤንነታቸው መመለሱን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ ነሐሴ 27/2009 በቄለም  ወለጋ ዞን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተከናወኑ የልማት ስራዎች 100 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ  ወይዘሮ ጫልቱ ተረፈ እንደገለፁት የልማት ሰራዎቹን ያከናወኑት 117 ሺህ 599 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ናቸው ።

ወጣቶቹ ከሀምሌ መጀመሪያ ጀምሮ በዞኑ 12 ወረዳዎች ውስጥ ያከናወኗቸው የልማት ስራዎች ከፍተኛ ግምት እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡ 

ችግኝ ተከላ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአቅመ ደካማ አረጋዊያን መኖሪያ ቤቶች ጥገና፣ አነስተኛ ድልድዮች ግንባታ በወጣቶቹ ከተከናወኑት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ 

የሰዮ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ደረጀ ፍቃዱ በሰጡት አስተያየት በወጣቶቹ በተሰጣቸው ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት በግልና አካባቢ ንጽህና አጠባበቅ፣ በቤተሰብ ምጣኔና በግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም  የተሻለ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በላሎ ቅሌ ወረዳ የኩታላ ሉቤ ቀበሌ አቅመ ደካማ የሆኑት ወይዘሮ ረጋቱ ዋከኔ በበኩላቸው በእርጅና ለመፍረስ ተቃርቦ የነበረው መኖሪያ ቤታቸውን ወጣቶቹ እንዳደሱላቸው ገልጸዋል፡፡ 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

ነቀምት ነሃሴ 27/2009 በምስራቅ ወለጋ ዞን በቤት ለቤት አሰሳ ለመጪው አዲስ ዓመት  እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ 78 ሺህ ህፃናት ተመዘገቡ፡፡

በዞኑ ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት የትምህርት ማሻሻያ ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ታየ በንቲ ለኢዜአ  እንደገለፁት በቤት ለቤት አሰሳ በማካሄድ  ከተመዘገቡት ህፃናት መካከል 38 ሺህ 900  ሴቶች ናቸው ።

"ህፃናቱ በመጪው የትምህርት ዘመን በዞኑ 17 ወረዳዎች በሚገኙ 642 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ መርሀ ግብር ትምህርታቸውን ይጀምራሉ " ብለዋል ።

እንደ አቶ ታየ ገለፃ በትምህርት ዘመኑ በዞኑ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሰ ህፃናትን ሁሉ ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ከተያዘው እቅድ እስካሁን 72 በመቶ ማሳካት ተችሏል ።

በቀሪው ጊዜ እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት እንደሚሰራ አመልክተው በተጓዳኝም  ለትምህርት ዘመኑ የሚያገለግሉ 792 ሺህ የመማሪያ መጽሐፍት  መሰራጨቱን ጠቅሰዋል።

እንዲሁም 298 ነባር ጥገና፣ 64 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታና 4 ሺህ 700 አዲስ የተማሪ መቀመጫዎች  መመቻቸታቸውንም አመልክተዋል።

አቶ ታየ እንዳሉት ለትምህርት ልማት ስራው ህብረተሰቡ 131 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ፣  በጉልበትና በቁሳቁስ  አቅርቦት በኩልም 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋጽኦ አድርጓል።

በጊዳ አያና ወረዳ የአያና አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ገመዳ ያዳ እድሜያቸው ለትምሀርት የደረሱ ሕፃናትን ወደ ትምህርት  ቤት ለማምጣት ከወላጆች፣ ከሐይማኖት ተቋማትና ከሃገር ሽማግሌዎች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"ትምህርት የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን በመገንዘብ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሶስት ልጆቼን  ቀድሜ አስመዝግብያለሁ " ያሉት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የላሊስቱ ጉድና ቀበሌ አርሶ አደር በዳሳ ገለታ ናቸው።

በዞኑ በ2010 የትምህርት ዘመን ከ396 ሺህ በላይ ነባርና አዲስ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተመዝገበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉ ይጠበቃል፡፡

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አርባ ምንጭ ነሃሴ 27/2009 በጋሞ ጎፋ ዞን በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የነበሩ 2 ሺህ 30 ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን የዞኑ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የሴቶችና ህፃናት መብት ደህንነት ዳይሬክተር ወይዘሮ ጥጋቧ ሱልጣን ለኢዜአ እንደገለጹት ህጻናቱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ የተደረገው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውስጥ ነው፡፡

"በህገወጥ ደላሎች በመታለል ፣በአቻዎቻቸውና በወላጆቻቸው  የኢኮኖሚ ችግር በመገፋት ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ጉልበት ለሚበዘብዝ ስራ ሲዘዋወሩ የተገኙ ናቸው " ብለዋል ።

መምሪያው ድርጊቱን ለመከላከል በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በጀመረው የተቀናጀ ስራ ህፃናቱ ተይዘው ወደየመጡባቸው ወረዳዎች እንዲመለሱ ተደርጓል።

ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ለህጻናቱ አልባሳት፣ ምግብና የትምህርት ቁሳቁስ እንዲያገኙና መልሶ ለማቋቋም ዞኑ የመንግስት ተቋማት ዓመታዊ በጀት ሁለት በመቶ ተቀንሶ  ለዚሁ አገልግሎት እንዲውል መመቻቸቱን ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ ከቁጫ ወረዳ ሁለት ህገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ተይዘው በፍርድ ቤት እያንዳንዳቸው በአምስት ዓመት እስራትና በ6 ሺህ ብር  እንዲቀጡ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

በዞኑ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ጥበቃ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ካተኔ ካወሌ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ  ድርጊቱ ጎልቶ በሚታይባቸው ቦንኬ፣ አርባምንጭ ዙሪያ፣ ዳራማሎ፣ ጨንቻና ዲታ ወረዳዎች የህፃናት ዝውውር መከላከል ግብረ-ኃይል መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም 62ሺህ 258 የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ተሰጥቷል።

እንደ አቶ ካተኔ ገለፃ ከአካባቢዎቹ ህፃናት ይዞ የሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብ ከቀበሌና ከወረዳ ህጋዊ ደብዳቤ መያዝ እንዳለበት በመወሰኑ የዝውወሩን መጠን በመቀነስ ረገድ የተሻለ ለውጥ እያመጣ ነው፡፡

በቦንኬ ወረዳ የገረሰ ቀበሌ ነዋሪ  አቶ  በላይ በዙ በሰጡት አስተያየት በየአካከባቢው በተናጥልም ሆነ በቡድን ህፃናትን ይዞ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማቸው ለግብረ ሀይሉ በማሳወቅ የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በህገ-ወጥ ደላሎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል ።

በምዕራብ ዓባያ ወረዳ የፉራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገዛኽኝ ገብሬ በበኩላቸው በአካባቢው ህገ-ወጥ የህፃናት ዝውውር እንዳይፈጸም የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

" የከተማ ኑሮ የተመቸ ነው በሚል ትምህርቴን አቋርጨ ከዳራማሎ ወረዳ ወደ አርባምንጭ ብመጣም የጠበኩት ሳይሆን በመቅረቱ ከቤተሰቦቼ ጋር ተቀላቅያለሁ "ያለችው ደግሞ የ13 ዓመቷ ታዳጊ ትእግስት እንታ ናት ፡፡

"በተሰጠኝ ምክርና የትምህርት ቁሳቁስ ታግዤ ትምህርቴን ለመማር ተመዝግቤያለሁም ብላለች ።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሐሴ 27/2009 በእናቶችና ህጻናት ሞት ቅነሳ ዙሪያ የተያዙ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች እየተሳኩ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

የሴቶችና ህጻናት፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ''ክብር ለእናቶች ፍቅር ለህጻናት'' በሚል መሪ ሀሳብ የጤና ተቋማትና ህጻናት መርጃ ማዕከላትን ዛሬ ጎብኝተዋል። 

የቅዱስ ጳውሎስ ፣ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም ክበበ ጸሃይ ህጻናት ማሳደጊያና የሴቶች ማረፊያ ልማት ማህበር በሥራ ኃለፊዎች ከተጎበኙት መካከል ይገኙበታል።  

ኃላፊዎቹ በሆስፒታሎቹ በመገኘት የወለዱ እናቶችን ሲጎበኙ የተወለዱ ህጻናት ታሪካዊና እድለኛ ትውልድ መሆናቸውን የሚያበስር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ ያረፈበት ፖስት ካርድ አበርክተዋል። 

ወይዘሮ ሰላማዊት ነጋ በጋንዲ ሆስፒታል በድንገተኛ ክፍል በተደረገላት እንክብካቤ ያለምንም ችግር ሴት ልጅ መውለድ ችላለች። 

''ልጅ መውለዴ ከአዲሱ ዓመት ጋር መገጣጠሙ የደስታ ስሜት ፈጥሮብኛል'' ያለችው ወይዘሮ ሰላማዊት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊርማ ያረፈበት ፖስት ካርድ ማግኘቷ ይበልጥ  አስደስቶኛል ብላለች።  

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ እንደገለጹት በእናቶችና የህጻናት ሞት ቅነሳ የተያዙ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች እየተሳኩ ነው።

የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ ደሚቱ አምቢሳ በበኩላቸው በመንግስት በኩል ሁሉም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ የተቀመጠው ስትራቴጂ ውጤት የተገኘበት እንደሆነ ገልጸው የጉብኝቱ ዓላማም ስኬቱን ለማስቀጠል መሆኑን ተናግረዋል። 

የመርሃ ግብሩ አካል የነበረው የክበበ ጸሀይ ህጻናት ማሳደጊያ  208 ወላጅ አልባ ህጻናትን ተቀብሎ የተለያዩ ድጋፎችን እየሰጠ መሆኑንም ገልጿል።

መንግስት ከነሃሴ 26 ጀምሮ ባሉት አስር ተከታታይ ቀናት የአገሪቱን እድገት በሚያስቀጥሉ ኩነቶች አዲሱን ዓመት ለመቀበል መርሃ ግብር ማውጣቱ የሚታወስ ነው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 27/2009 የፋትሳል እግር ኳስ ውድድሩ በሚዲያና ኪነጥበባት ባለሙያዎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የጎላ ሚና እንደተጫወተ የውድድሩ ተሳታፊዎች ገለፁ።

ከሐምሌ 14 እስከ ነሐሴ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደው የሚዲያና ኪነጥበባት ባለሙያ ቡድኖች የፉት ሳል እግር ኳስ ውድድር ዛሬ በትንሿ ስታዲየም ፍጻሜውን አግኝቷል።

ውድድሩ 13 ቡድኖች የተሳተፉበት ሲሆን በባምቢስ፣ዳግማዊ ምንሊክ መሰናዶ ትምህርት ቤትና በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ በሚገኙ ሜዳዎች ሲከናወን ቆይቷል።

የዘአናሊስት ቡድን ተጫዋች የሆነው ወጣት ላንተአለም ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገረው፤ ውድድሩ በሚዲያና ኪነጥበባት ባለሙያዎች መካከል ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲዳብር መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።

ቡድኑ በውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፉን የገለጸው ወጣት ላንተአለም፤ "በውድድሩ በቀጣይ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚያደርገንን  ልምድ ከሌሎች ቡደኖች ቀስመናል" ብሏል።

የአርቲስቶች ቡድን ተጫዋች ተዋናይ ፍቃዱ ከበደ በበኩሉ የፋት ሳል ስፖርት ውድድር  ከነበረው የፉክክር ስሜት ባለፈ በባለሙያዎቹ መካከል የወንድማማችነት መንፈስ የፈጠረ እንደነበር ገልጿል።

ልምድ በመለዋወጥና እርስ በእርስ በመማማር ረገድም ውድድሩ የራሱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ተናግሯል።

የዳኛ ውሳኔ አለማክበርን ጨምሮ ሌሎች በውድድሩ ላይ የተስተዋሉ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደላቸው ተግባራት በቀጣይ ሊታረሙ እንደሚገባም አስተያየቱን ሰጥቷል።

"ውድድሩ ከነበረው ፋክክር ባለፈ ከሌሎች ተቋማት የመጡ ባለሙያዎች ጋር ማህበራዊ ግንኙነት እንዲጠናክር አስተዋጽኦ አድርጓል" ያለው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የስፖርት ቡድን አምበል የሆነው ወጣት ተመስገን ኃይሌ ነው።

በሚዲያና ኪነጥበባት ባለሙያዎች መካከል የሚደረገው የፉትሳል እግርኳስ ውድድር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጿል።

በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ለሁሉም ኮሚቴ የቴክኒክ ባለሙያ አቶ አለምነህ ስዩም በበኩላቸው የውድድሩ ዋነኛ ዓላማ የሚዲያና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ጤናቸውን በመጠበቅ ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ ለማድረግ እንደሆነ ተናግሯል።

"ውድድሩም የስፖርት ለሀሉም ጽንሰ ሀሳብን የተከተለ ነው" ብለዋል።

የስነ ምግባር ግድፈት ያሳዩ ተጫዋቾችና ቡድኖች በቀጣይ በሚዘጋጁ ውድድሮች ላይ አስከመታገድ የሚያደርስ ቅጣት  እንደተጣለም ገልጸዋል።

ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ውድድሩን በዓመት ሁለት ጊዜ ለማካሄድ እቅድ መያዙንም ገልጸዋል።

በፉት ሳል እግር ኳስ ወድድር በተካሄደው የፍጻሜ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ቡድን የዲጄዎች ማህበር ቡድንን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችሏል።

ዘአናሊስት ቡድን ደግሞ የአርቲስቶች ቡድንን ስድስት ለሶስት በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

በውድድሩ ከአንድ እስከ አራት ለወጡ ቡድኖች ከተበረከተላቸው የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት በተጨማሪ እንደ ደረጃቸው  ከ15 ሺህ እስከ ስድስት ሺህ ብር ተሰጥቷቸዋል።

ኮከብ ተጨዋች፣ኮከብ በረኛ፣ኮከብ አሰልጣኝና ኮከብ ግብ አግቢ ለሆኑ ተጫዋቾችም የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ቡድን ላሳየው ስነምግባርና ስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫና ሰባት ሺህ ብር ተሸልሟል። 

ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደው የሚዲያና ኪነጥበባት ባለሙያ ቡድኖች የፉት ሳል እግር ኳስ ውድድር 147 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን፤ 28 ቢጫና ስድስት ቀይ ካርዶች ከዳኞች ተመዘዋል።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ነሃሴ 27/2009 ዩኒቨርሳል ሜዲካል ኮሌጅ በነርሲንግ፣ ፋርማሲና በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት በዲግሪና በደረጃ 4 መርኃ ግብር ያሰለጠናቸውን 275 ተማሪዎች አስመረቀ።

በመርኃ ግብሩ ላይ በእንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሲስተር የዛብነሽ ክቤ የጤና ምሩቃኑን ቃለ መሃላ አስፈጽመዋል።

ሲስተር የዛብነሽ ተመራቂዎቹ በትምህርት ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ወደ ተግባር በመቀየር ህብረተሰቡን በመልካም ሥነምግባር እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል።

"በጤና አገልግሎትና በጤና ባለሙያ እጥረት ውስጥ የምትገኘውን ሀገራችንን ካለችበት ችግር አውጥታችሁ ለሕዝቦቿ የተመቸች ሀገር እንድትሆን መረባረብ አለባችሁ" ሲሉም አደራ ብለዋል።

የኮሌጁ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ የኔእህት አሰፋ በበኩላቸው የጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ኮሌጁ የበኩሉን ኃላፊነት  በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ተመራቂዎቹ በቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በጤናው ዘርፍ የሚስተዋለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለመቅረፍ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩም ጠይቀዋል። 

ኮሌጁ ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች 104 በነርሲንግ፣ 102 በፋርማሲ፣ 34ቱ ደግሞ በጤና መኮንንነት በዲግሪ እንዲሁም 27ቱ ሰልጣኞች በነርሲንግ 8ቱ ደግሞ በፋርማሲ ቴክኒሺያን በደረጃ 4 የሠለጠኑ ናቸው።

ዩኒቨርሳል ሜዲካል ኮሌጅ ካለፉት 15 ዓመታት ጀምሮ በጤናው ዘርፍ በተግባርና በንድፈ ሐሳብ የተደገፉ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል።

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 27/2009 የአዲስ አበባ ደምብ ማስከበር አገልግሎት ጽህፈት ቤት በህግ ጥሰት ፈፃሚዎች ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ  ለመንግስት ገቢ ማድረጉን ገለጸ።

አዲስ አበባ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቷ ነዋሪዎቿን በማርካት በ2020 ዓ.ም ከአፍሪካ ጽዱ፣ውብና አረንጓዴ ከተሞች ሞዴል ለመሆን ራዕይ ሰንቃለች።

ከመዲናዋ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በከተማዋ የሚከሰቱ የደንብ ጥሰቶችን ለመከላከል፣ የፀዳችና በማህበራዊ ዑደቷ የተረጋጋች ለማድረግ የደንብ ማስከበር ጽህፈት ቤት በአዋጅ ተቋቁሟል።

ከአራት አመት በፊት የተቋቋመው ይህ ተቋም በተሰጠው የደንብ ማስከበር ኃላፊነት በርካታ የቅጣት እርምጃዎችን ሲያከናውን መቆየቱን የጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ኮማንደር አሳዬ አምባዬ ይገልጻሉ።

በተያዘው ዓመት በህገ ወጥ መሬት ወራራ ማስፋፋትና ህገ ወጥ ግንባታ በተፈጸሙ የደንብ ጥሰቶች ከ 14 ሺህ በላይ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

ደረቅ ቆሻሻ በመንገድና በተከለከሉ ቦታዎች በመጣል፤ ፈሳሽ ቆሻሻን ከጎርፍ መውረጃ ጋር አገናኝቶ መልቀቅ ጋር በተያያዙ ድርጊቶች ከ 5 ሺህ 500 በላይ እርምጃዎችን መወሰዱንም አስታውቀዋል።

በመዲናዋ የእግረኛ ፍሰት ላይ ችግር የሚፈጥሩ የጎዳና፣ የበረንዳ፣ የአሸዋ፣ የአጠናና ሌሎች መሰል ህገ ወጥ የንግድ ተግባራት ላይ ደግሞ ከ 16 ሺህ በላይ የቅጣት እርምጃዎች መወሰዱን አብራርተዋል።

በከተማዋ ህገ ወጥ የእንስሳት ንግድ፣ በተከማቸ ተረፈ ምርትና ተያያዥ ጉዳዮች ደንብ የጣሱ ከ 2 ሺህ በላይ ግለሰቦችም ተቀጥተዋል።

በአጠቃላይ በእነዚህና በሌሎች ዘርፎች ከ 144 ሺህ በላይ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውንና ከእነዚህም መካከል 139 ሺህ የደንብ ጥሰቶች ተጠንተው እርምጃ መወሰዱን ነው የገለጹት።

ድርጊቶቹን በፈፀሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ በተወሰደው የቅጣት እርምጃም ከ 29 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ተደርጓል ብለዋል።

ዘንድሮ በተወሰዱ እርምጃዎች የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸርም ከ 4 ሚሊየን ብር በላይ ብልጫ አለው።

ጽህፈት ቤቱ በሚያከናውናቸው የደንብ ማስከበር ተግባራት በርካታ ችግሮች ሲያጋጥሙት መቆየቱንም ተናግረዋል።

 በአንድ በኩል ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል ጥረት ሲደረግ በሌላ በኩል ህጋዊ ነጋዴዎች በህገ ወጥ ንግዱ ሲሳተፉ እንደነበርና ይህም ለቁጥጥሩ ከባድ ፈተና እንደሆነ ይገልፃሉ።

ህገ ወጥ ነጋዴዎቹ ተደራጅተው በህጋዊ መንገድ ቢሰሩ በመንግስት ቦታ እንደሚመቻችላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን አብዛኞቹ መደራጀት እንደማይፈልጉ ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የሚናገሩት።

በሌላ በኩል የአካል ድብድባ እየደረሰባቸው ለደንብ ማስከበሩ የሚተጉ ደንብ አስከባሪ መኮንኖች እንዳሉ ሁሉ የስራው ባህሪ ለኪራይ ሰብሳቢነት ምቹ በመሆኑ በአፈጻጸም ላይ የሚከሰተው የሰራተኞች የስነ ምግባር ጉድለት ሌላው ፈተና እንደነበር ገልፀዋል።

ጽህፈት ቤቱ የራሱ የዲሲፕሊን ኮሚቴ እንዳለው ጠቁመው ተጨባጭ መረጃ የተገኘባቸው ኦፊሰሮች ላይ ከስራ ማባረር ጀምሮ በህግ እንዲጠየቁ እስከ ማድረግ የሚደርሱ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

 “አገሪቷ ልታድግና ልማቷ ሊረጋገጥ የሚችለው ሁሉም በህጋዊ መንገድ ሲሰራና ለመንግስት የሚገባውን ግብር ሲከፍል ነው” ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ችግሩን ደንብ ማሰከበር ብቻውን ሊፈታው ስለማይችል መላው ህብረተሰብ እንዲተባበር ጠይቀዋል።

ደንብ አስከባሪዎችን በጉቦ ለመደለል የሚሞክሩ አካላትም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሃዋሳ ነሐሴ 27/2009 በዘንድሮው የምርት ዘመን በዋና ዋና ሰብሎች ስምንት በመቶ እድገት መታየቱን የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በመኸር ወቅት የታቀደው 12 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ ታርሶ በተለያየ ሰብል ተሸፍኗል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በእርሻ ልማት ዘርፉ የ2009 አፈጻጸሙንና የ2010 እቅድ ላይ የምክክር መድረክ በሃዋሳ እያካሄደ ነው፡፡

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ እንደገለጹት ስምንት በመቶ የዋናዋናስብሎች ዕድገት የተገኘው ካለፈው ዓመት ምርትጋር ሲነጻጸር ነው

በ2008/2009 ምርት ዘመንም በዋና ዋና ሰብሎች ከ290 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቦ እንደነበር አስታውሰው ዘንድሮ ከአምናው የስምንት ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ ለገበያና ለኢንዱስትሪ ግብዓት ማምረት መጀመሩን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእርሻ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ተስፋዬ መንግስቱ በመድረኩ ገልጸዋል፡፡

በ2008/2009 ምርት ዘመን በዋና ዋና ሰብሎች ከ290 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው ይህም ከአምናው የስምንት ነጥብ ስምንት በመቶ እድገት መሳያቱ አውስተዋል፡፡

በተጨማሪ በመስኖ ልማትም 369 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በ2009/2010 ዘመን የመኸር ወቅት የታቀደው 12 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ሙሉ በሙሉ ታርሶ በተለያየ ሰብል መሸፈኑን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህም በዋና ዋና ሰብሎች 345 ሚሊየን ኩንታል ለማግኘት ታቅዷል፡፡

የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣የተሻሻሉ አሰራሮችን መተግበርና የግብርና ተኮር ልማትም በስፋትና በጥራት መፈጸም የተቻለ ቢሆንም የበቆሎ ሰብልን የሚያጠቃው ተምች የምርት ዘመኑ ፈተና መሆኑን ሚኒስቴር ዲኤታው ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመግታት በተደረገው ጥረትም በተምች ከተጠቃው 621ሺህ ሄክታር መሬት 92 በመቶውን መከላከል መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታው እንዳሉት የአርሶአደር ማሰልጠኛ ተቋማትን ማስፋፋት፣ ባለፉት 3 ዓመታት እየቀነሰ የመጣውን የምርጥ ዘር አጠቃቀም ማስተካከል፣የሞዴል አርሶአደሮችን ቁጥር ማሳደግ፣ የመስኖና የግብርና ገበያ ተኮር ስራዎች ትኩረት የሚያሻቸው ናቸው፡፡

በተያዘው የምርት ዘመን ለማግኘት በእቅድ የተያዘው ግብ ለማሳካት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሚዩኒኬሽን ዳሬክተር አቶ ለማ ቦጋለ በበኩላቸው የበልግ እርሻው በዝናብ መቆራረጥ የተስተጓጎለ ቢሆንም በመኸር ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታሩ በላይ ታርሶ በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የተከሰተውን የአሜሪካን መጤ ተምች ለመከላከል በቅንጅት በመስራት ውጤታማ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሰሽን ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ አብረሃም ሙጬ በሰጡት አስተያየት " በምርት ዘመኑ ዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑ ተግባራት የተሻሉ ናቸው" ብለዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የተመረጡ ስምንት የሰብል ዓይነቶች በኩታ ገጠም መዝራታቸውንና የገበያ ትስስሩን ለማሳደግ የህብረት ስራ ማህበራት ፎረም መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡

የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት እጥረት፣ የሰርቶ ማሳያ ማዕከላት ጥራትና በምርጥ ዘርና የመስራች ዘር አቅርቦት እጥረትን በክልሉ እንደችግር የተነሱ ናቸው፡፡

መድረኩ በሶስት ቀናት ቆይታው በየክልሎቹ እቅድ አፈጻፀም፣በ2010 የመስኖ ንቅናቄ ሰነድና ጠቋሚ እቅዱ ላይ ውይይት የሚያካሂድ ሲሆን የመስክ ጉብኝት እንደሚደረግም ይጠበቃል፡፡

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

አርባምንጭ ነሃሴ 27/2009 የህዳሴው ግድብ ዋንጫ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በተዘዋወረባቸው ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የተሳካ ውጤት ማስገኘቱን የክልሉ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

ዋንጫው በክልሉ ቆይታው ለማሰባሰብ ከተያዘው እቅድ  በላይ አስቀድሞ ማሳካት ከማስቻሉም በላይ በህዝቦች መካከል አንድነትን መፍጠሩም ተመልክቷል፡፡

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው ለኢዜአ እንደገለጹት  ዋንጫው ክልሉ በተዘዋወረባቸው አስር ዞኖችና አራት ልዩ ወረዳዎች አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተሰብስቧል፡፡

ዋንጫውን ገና የሚጠብቁ 3 ዞኖችና ሐዋሳ ከተማ አስተዳደር እየቀሩ አሁን ላይ  አፈጻጸሙ የእቅዱን እጥፍ ብልጫ ያለው ነው፡፡ 

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ብልጫ ያለው ክንውን ማስመዝገብ የተቻለው  የክልሉ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች  ለግድቡ ግንባታ ብዙና አንድ ሆነው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ 

ታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ካስገኘው ገቢ ባሻገር የክልሉን ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦችን የብዝሃነትና የአንድነት እሴቶችን በማጉላት ትስስራቸውን ይበልጥ እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

የባስኬቶ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ደሳለኝ በበኩላቸው በወረዳው ለግድቡ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ በአይነትና በገንዘብ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዋንጫው በልዩ ወረዳው በቆየበት ወቅት የተሰበሰበዉ ገቢ ከ8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የላስካ ከተማ ነዋሪው  አቶ ታምራት ካንኮ  በሰጡት አስተያየት የዋንጫውን አቀባበል ምክንያት በማድረግ ለአራተኛ ጊዜ የወር ደመውዛቸውን  መቆጠብ መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋንጫው ታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ለሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች የተበረከተ ልዩ ስጦታ በመሆኑ ባደረጉት ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በልዩ ወረዳው የጋንቺሬ አካባቢ አርሶ አደር ዳንጎ ባይሳ በበኩላቸው በመንደራቸው ከሌሎች ጎረቤቶች ጋር 10 ሆነው በመደራጀት ለህዳሴው ግድብ ድጋፍ የሚውል አንድ ሰንጋና አምስት ኩንታል የበቆሎ እህል መለገሳቸውን ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ዋንጫ የባስኬቶ ልዩ ወረዳ ቆይታውን  አጠናቆ ነገ ደቡብ ኦሞ ዞን እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን