አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 13 September 2017

አሶሳ መስከረም 3/2010 በአሶሳ በከተማ ምግብ ዋስትና  እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሃ ግብር ተጠቃሚዎች በወቅቱ ክፍያ ባለመፈጸሙ ለችግር መዳረጋቸውን  ተናገሩ።

በከተማዋ የገቢ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆነ የቀጥታ ድጋፉ ተጠቃሚዎችና በአካባቢ ልማት በመሳተፍ ተጠቃሚ የሚሆኑ ነዋሪዎች ተለይተው ወደ ተግባራዊ ሥራ ከተገባ ሁለት ወራት አልፈዋል።

ይሁንና የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች አስካሁን ድረስ ተገቢውን ክፍያ በወቅቱ እያገኙ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ሮማን ወልደገሪማ በመርሀ  ግብሩ ተጠቃሚ  የከተማዋ  ነዋሪዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ  በከተማዋ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገድ ሥራ ማከናወን ከጀመሩ ከሁለት ወራት በላይ ቢያስቆጥሩም እስካሁን ድረስ ሙሉ ክፍያ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

በወቅቱ ካልተከፈላቸው ሥራውን ለረጅም ጊዜ ለማከናወን የሚያስችል አቅም የሌላቸው መሆኑን ኤጀንሲው  ተገንዝቦ  የቀረባቸው ክፍያ  እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

ወይዘሪት አልማዝ ጥላሁን  በበኩሏ፣  ከሁለት ወራት በላይ በደረቅ ቆሻሻ የማንሳት ሥራ ላይ ብትሰማራም በወቅቱ ክፍያ እያገኘች ባለመሆኑ ሥራውን ለመቀጠል እንደምትቸገርና ኤጀንሲው አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቃለች።

ወይዘሮ ማማነሽ መኮንን የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመመረጣቸው ደስተኛ ቢሆኑም ድጋፉ እየተቆራረጠ መሆኑ ለችግር እንደዳረጋቸው ተናግረዋል።

በአሶሳ ከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የልማታዊ ሴፍትኔትና ኑሮ ማሻሻያ ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ እንዳሻው ይግዛው በበኩላቸው፣ ክፍያው በአሰራር ሂደት ባጋጠሙ ችግሮች ምክንያት የዘገየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በየቀበሌው በተዋቀሩ ኮሚቴዎች የተመለመሉ ነዋሪዎች በትክክል ተጠቃሚ መሆን የሚገባቸው ስለመሆኑ ለማወቅ የተካሄደው የማጣራት ሥራ የወሰደው ጊዜ ለመዘግየቱ አንድ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

"ተጠቃሚዎችን በዘላቂነት ማቋቋም የመርሃ ግብሩ ዋንኛ ዓላማ በመሆኑ ከሚያገኙት ገቢ ሃያ በመቶ እንዲቆጥቡ ሁሉም ተጠቃሚዎች የቁጠባ ሒሳብ ደብተር እንዲያወጡ ለማድረግ የወሰደው ጊዜም ለመዘግየቱ ሌላው ምክንያት ነው" ብለዋል፡፡

ኤጀንሲው የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎችን የኑሮ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ከአምስት መቶ ሺህ ብር በላይ ተበድሮ የተወሰነ ክፍያ መፈፀሙን ገልፀዋል፡፡

የተቀረውን ክፍያ ቅድመ ሁኔታዎችን በማጠናቀቅ በቀጣይ ሳምንት ሙሉ ለሙሉ እንደሚፈጸምም አረጋግጠዋል።

የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎችን እስከ ሦስት ዓመት ድረስ በአካባቢ ልማት በማሳተፍና የተለያዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት በቀጣይ ተደራጅተው ራሳችውን እንዲችሉ ለማድረግ ኤጀንሲው በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

የቀጥታ ድጋፍ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በአሶሳ ከተማ ሦስት ሺህ 650 ነዋሪዎች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚዎች ሆነዋል፡፡

ከሦስት ዓመት በኋላ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጨማሪ አምስት ከተሞችን በመርሃ ግብሩ ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙን የገለፁት አቶ እንዳሻው፣ የመርሃ ግብሩ ተግባራዊነት እስኪጠናቀቅ ድረስ 23 የክልሉ ከተሞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናገረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲሰ አበባ መስከረም 3/2010 የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአዲስ አበባ ቄራዎች አገልግሎትን ለማዘመንና ለማስፋፋት የሚያግዝ የ70 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ስምምነት ከፈረንሳዩ የልማት ተራዕዶ ድርጅት በኢትዮጵያ ጋር ተፈራረመ።

በከተማዋ እያደገ የመጣውን የቄራዎች ፍላጎት በጥራትና የአካባቢ ተጽዕኖ በማያስከትል መልኩ የሚያቀርቡ ቄራዎች አናሳ በመሆናቸው አገልግሎቱን ለማዘመንና ለማስፋፋት ስምምነቱ መፈረሙ ተጠቅሷል።

ስምምነቱን የተፈራረሙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ እንደገለፁት የሁለቱ አገራት ወዳጅነት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ  የዘለቀ ነው።

በመሆኑም "ዛሬ የተፈረመው የብድር ስምምነት የሁለቱን አገራት ትብብር የሚያጠናክር ነው" ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው በተለይም በከተማዋ መሰረተ ልማት ግንባታ እና ለነዋሪዎቿ የዘመነ  አገልገሎት ለማቅረብ የሚከናወነውን ሥራ ይደግፋል ብለዋል።

የብድር ስምምነቱ የአዲስ አበባ ቄራዎች አገልግሎትን ለማዘምንና ለማስፋፋት በተያዘው ፕሮጀክት  ጥራቱን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በማከናወን የስጋ ውጤቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲሁም  ከአካባቢ ተፅዕኖ የፀዳ የቄራ አገልገሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቲምስ በበኩላቸው እያደገ የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ የቄራዎች ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም የአዳዲሰ ቄራዎች ግንባታና ማስፋፋያ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአዳዲስና በማስፋፊያ ቄራዎች ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የአሁንና የወደፊት የከተማውን የሥጋ አቅርቦት ፍላጎት ከማርካት ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትርፋማ እንዲሆን ያስችለዋል ያሉት አምባሳደሩ በሥጋ አቅርቦትና በቆዳ ጥራትም ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ እ.አ.አ በ2022 የሚጠናቀቅ ሲሆን ሥራ በሚጀምርበት ወቅት በዓመት ከስምንት መቶ ሺህ በላይ እንስሳትን ለእርድ በማቅረብ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነውን የከተማዋን የሥጋ ተጠቃሚዎች ፍላጎት ማርካት እንደሚችል ተገልጿል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህርዳር መስከረም 3/2010 የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ከማካሄድ ጎን ለጎን በፓርኩ የሚገቡ ባለሃብቶችን የማዘጋጀት ስራ መጀመሩን የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ኪዳኔ ምስክር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት ፓርኩን በዚህ ዓመት መጨረሻ ስራ ለማስጀመር የተለያዩ የግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

እስከ አሁን በተደረገው እንቅስቃሴም የፓርኩ ዲዛይን አለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንዲሰራ የማደረግና የወሰን ማስከበር ስራው መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ለቢሮ፣ ለመመገቢያ፣ ለመኝታ፣ ለመጋዝንና መሰል አገልግሎቶች የሚውሉ 13 ብሎኮችን የያዘ የካምፕ ግንባታ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

እንዲሁም የ9 ኪሎ ሜትር የአጥር ስራ እየተከናወነ ሲሆን እስከ አሁንም 40 በመቶ የሚሆነው ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመዋል።

የካምፑን የውስጥ ለውስጥ የ10 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ መስመርዝርጋታና ሌሎች የመሰረተ ልማቶችን ከ700 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት ለማከናወን የጨረታ ውል መሰጠቱንና መስከረም መጨረሻ ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በፓርኩ ዙሪያ ከሚገነቡ ሰባት የገጠር የሽግግር ማዕከላትም በሞጣ ማዕከል የአጥር ግንባታ ስራ መጀመሩንና ሌሎች ግንባታዎችን ለማስጀመር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም አቶ ኪዳኔ አስታውቀዋል።

ወደ ፓርኩ ቀድመው ለሚመጡ ባለሃብቶችም ለስራ ማስጀመሪያ የሚሆኑ ሰባት ሼዶች እንደሚገነቡም አስረድተዋል።

ከግንባታው ጎን ለጎንም በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት ወደ ፓርኩ ገብተው ማልማት የሚችሉ ባለሃብቶችን ለመመልመል የሚያስችል ሰነድ ተዘጋጀቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በስጋ፣ በትክልትና ፍራፍሬ፣ በቅባት እህሎች፣ በመድሃኒት፣ የወተትና ወተት ተዋጽኦ፣ የማርና ሰም ማቀነባበሪያ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።

የፓርኩ መገንባትም የውጭ ምንዛሬ ከማስገኘት አልፎ ለአካባቢው አርሶ አደር የገበያ ትስስር በመፍጠር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።

የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከ2011 ዓ.ም በኋላ በ1000 ሄክታር መሬት ላይ ሙሉ በሙሉ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም 60 ከፍተኛ 120 አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን የመያዝ አቅም እንዳለው ታውቋል።

ፓርኩ በዓመት 358 ሺህ ቶን ምርት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሃገራት ገበያ በማቅረብ በመጀመሪያው ዓመት ከ14 ቢሊዮን ብር ያላነሰ ያልተጣራ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ኢኮኖሚ

መብራህቱ ይበልህ (መቀሌ  ከኢዜአ)

 የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም የሚል ብሂል አለ ። እንዴት ያስጥል ? ባል ቢሆንም እኮ እሱም አህያ ነው ። አህያ ከመበላት የምትድነው እራሷን ከጅብ ከጠበቀች ብቻ ነው ።

 እኔን የገረመኝ ጅብ ለዘመናት አህያን ሲያሳድድ መኖሩ አይደለም - የቅርቡን የአህያና የጅብ ፍቅር እንጂ  ። በዪና ተበዪ ፣ አጥፊና ጠፊ ፣አሳዳጅና ተሳዳጅ እንዴት ተፋቀሩ ?ይገርማል ። ይባስ ብሎ ደግሞ ቀበሮና በጎች አንድ ጉረኖ ላይ ሲያድሩ አይቼ ደነቀኝ ።

 ምን ዘመን መጣብን ? እንዴት አህያና ጅብ ፣ ቀበሮና በግ ሊፋቀሩ ቻሉ ?ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው ። አይዞን! በምንም ተአምር ፍቅራቸው ዘላቂ ሊሆን አይችልም ። እርስ በርሳቸው መበላላታቸውም አይቀርም ።

 ጉዳዩ እንዲህ ነው ። አይጥና ድመት ሊፋቀሩ የሚችሉት ድመቱን እስኪርበው ድረስ ብቻ ነው ። የአህያና የጅብ የጋራ ቆይታ ደግሞ ጅቡ ወደል አህያውን ለመቦጨቅ አመቺ ጊዜና ቦታ ለመምረጥ ካልሆነ በስተቀር  መበላቱ ግን አይቀርም ።

 በቅርቡ በአማራና በትግራይ  ወሰን  አካባቢ የነበረውን መለስተኛ አለመግባባት ወደ ግጭት እንዲያመራ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም - ጠባቦችና ትምክህተኞች ።

 ግጭት በአግባቡ ማስተናገድ ከተቻለ ከጉዳት ይልቅ ዘላቂ መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ የታወቀ እውነታ ነው ። እነሱ ግን ግጭቱን አቀጣጠልነው ብለው በጋራ ስቀው ነበር ። አለመግባባቱ በሁለቱም ህዝቦች በጎ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሲፈታ ደግሞ አብረው ማላዘን ጀመሩ ።

 ህዝብን እርስ በርሱ ያባሉ መስሎአቸው ሰርግና ምላሽ ዓይነት ሽርጉድ ቢያሳዩንም አብረው እንደማይዘልቁ ግን ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው ። ታዲያ! ሰሞኑን እንዴት አብረው ተሰለፉ? መልሱ ቀላል ነው ።በሬውን ሰርቀው ስጋውን ለመቀራመት ቢሆንም በቆዳው ሽያጭ መጣላታቸው እንደማይቀር ግን እነሱም ያውቁታል ።

ከተፈጠረው አለመግባባት በስተጀርባ  ሁለት የማይጣጣሙ ሃይሎች አብረው ተሰልፈዋል ። ሁለቱም የጎሪጥ የሚተያዩ ፣ አንዱ ለሌላው የማይተኛ ፣ በእርቅና በድርድር ሊፈታ የማይችል መሰረታዊ ቅራኔ ያላቸው ሃይሎች ናቸው - ጠባቦችና ትምክህተኞች ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ይበላላሉ ።

የትምክህት ሃይሎች “ እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል” የሚል መርህ ያነገቡ ናቸው ።አንድ ቋንቋ ፣ አንድ አገር ፣ አንድ የአስተዳደር ስርዓት መኖር አለበት ብለው የሚያምኑ፣ ብዝሃነትን የማይቀበሉና የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የመጨፍለቅ አባዜ የተጠናወታቸው ሃይሎች።

በሌላ በኩል የተሰለፉት ጠባብ ሃይሎች ደግሞ በመከባበር፣ በመፈቃቀርና በመቻቻል ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት የማይቀበሉ በግልባጩ ደግሞ የመገንጠል ጥያቄን በማራገብ የህዝቦችን ሰላም ለማደፍረስ  የቆሙ የጥፋት ሃይሎች አንደሆኑ ይታወቃል ።

የአማራና የትግራይ መንታ ህዝቦች ጠገዴ አካባቢ በግጨው ቀበሌና ዙሪያው የወሰን ጥያቄ ሲነሳ በሰላም እንደሚፈቱት እርግጠኞች ነበሩ ። ሁለቱም የጥፋት ሃይሎች ግን በእሳት ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ አለመግባቱን ወደ ግጭት እንዲያመራና ግጭቱን ያከረሩት መስሎአቸው ድዳቸው እስኪታይ ድረስ ለመሳቅ ሞክረው ነበር ። ሁለቱ መንታ ህዝቦች ግን የሚቀመሱ አልሆኑም ።

አስቀድመው በውስጣቸው መከሩበት ። ምክክራቸውን የጋራ ለማድረግ ደግሞ ባለፈው ሀምሌ ወር መቀሌ ከተማ ላይ  ህዝባዊ ኮንፈረንስ አካሄዱ ። “ የሰይጣን ጆሮ ይደፈን “ በመሀከላችን ውስጥ ግጭት ምን ሲደረግ በማለትም በጋራ ለሰላም ዘብ ቆሙ ። ስለ ሰላም ዘመሩ ። ሁለቱም የሰላም ጠበቆች መሆናቸውም በአቋም መግለጫቸው አረጋገጡ  ።

የሁለቱም ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮችም በኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው ለህዝብ ውሳኔ ተግባራዊነት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ቃል ገቡ ።

ስምምነቱ የሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች ግንኙነትን ያጠናከረ፣ ሰላምና መረጋጋትን ያሰፈነ ህዝበ ውሰኔ መሆኑን የአገር ሽማግሌዎቹ ይገልፃሉ፡፡ በስምምነቱ መሰረትም በጋራ የህዝብ ተሳትፎ ወሰናቸውን የማካለል ስራ አከናወኑና ዘመናትን ያስቆጠረው አንድነታቸው በምንም መልኩ እንደማይሸረሸር አረጋገጡ ።

ስምምነቱ የተፈፀመው ህገ መንግስቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ነው ። በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 48 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት የክልሎች ወሰንን በሚመለከት የሚነሳ ጥያቄ  ካለ  ጉዳዩ በሚመለከታቸው ክልሎች ስምምነት ይፈፀማል ይላል፡፡

በትግራይ ክልል ፀገዴ ወረዳና በአማራ ክልል ጠገዴ ወረዳ ወሰኑ ሳይታወቅ የቆየውን አንድ ቀበሌ ላይ ሁለቱም ክልሎች ሰሞኑን የፈፀሙት የጋራ ውሳኔም  ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈረው አንቀፅ 48ን መሰረት ባደረገ ነው፡፡

በህገ መንግስቱ አንቀፅ 40 ንኡስ አንቀፅ 3  ላይ  መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ  የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት መሆኑ ተደንግጓል፡፡

በህገ መንግስቱ ድንጋጌ መሰረት   መሬት የሁሉም ህዝቦች የጋራ  ንብረት፣ በጋራ የሚጠቀሙበት ሀብት ከመሆን ባለፈ ለየትኛውም ክልል ብቻ  የተተወ  ንብረት አይደለም ማለት ነው፡፡

የትግራይ ፀገዴና የአማራ ጠገዴ በታሪክ አጋጣሚ ግማሹ ትግርኛ ግማሹ ደግሞ አማርኛ ተናጋሪ ሆነ እንጂ  ሁለቱም የማይነጣጠሉ መንታ ህዝቦች ናቸው ። እውነታው እንዲህ ከሆነ የግጨው ቀበሌ የት ነበረ ? የትስ ይሄዳል ? ያው እዛው ነው ። መንታ ህዝቦቹ በመተሳሰብ ፣ በመፈቃቀርና በመከባበር ይጠቀሙበታል - በፍትሃዊነት  ።

ከፀገዴ ወረዳ የተወከሉ የሀገር ሽማግሌ አቶ ካሳዬ ሀፍቱ የመንታ ህዝቦቹ የዘመናት የደም ትስስርና የትውልድ ሀረግ እየመዘዙ የሚሉት አላቸው ።

በ1984 ዓ.ም ለአስተዳደር ይመች ዘንድ በ16 ቀበሌ የሚኖር ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪዎች ነን በማለት በትግራይ ክልል ፀገዴ ወረዳ ሲካለሉ፣ 12 ቀበሌዎች ደግሞ አማርኛ ተናጋሪዎች ነን በማለታቸው  በአማራ ክልል ጠገዴ ወረዳ  አስተዳደራዊ መዋቅር ስር እንዲጠቃለሉ ተደረገ ይላሉ ።

ግጨውና አከባቢው  ደግሞ  በይደር ወሰኑ ሳይካለል እስከ አሁን ድረስ መቆየቱንና የሁለቱም አጎራባች ወረዳ አርሶ አደሮች ሰጪና ከልካይ ሳይኖራቸው ለአመታት በጋራ እያረሱ ሲጠቀሙበት የነበረ ነው፡፡

በትግርኛ አነጋገር “ወፍረ ዘመት” ይሉታል፡፡ ወፍረ ዘመት ማለት ባለቤት ሳይኖረው ሁሉም በየፊናው እየሄደ እያረሰ የሚጠቀምበት መሬት ማለት ነው፡፡

ወሰን ሳይኖረው የሁለቱም ክልል አጎራባች ወረዳዎች አርሶ አደሮች ሲጠቀሙበት የነበረው መሬት  ለአስተዳደርና ለአጠቃቀም  እንዲያመች  በፍጥነት ወሰኑ እንዲካለል የሁለቱም  ወረዳ አገር ሽማግሌዎች መጠየቃቸው ህገ መንግስታዊ መሰረት የያዘ ነው፡፡

በመሆኑም አንድም ወሰኑ ሳይካለል የቆየውን የግጨውና አካባቢው ቦታ ከሁለቱም ወረዳዎች እያንዳንዳቸው 50 ተወካዮችና የአገር ሽማግሌዎችን በመምረጥ አስተዳደራዊ ወሰን በማስቀመጣቸው የአገር ሽማግሌዎችና ተወካዮች ብስለትና አስተዋይነትን ከማድነቅ ይልቅ መኮነኑን ምን አመጣው?

በህገ መንግስቱ መሰረት መሬት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ሆኖ እያለ  ለእከሌ ክልል መሬት ተቆርሶ ተሰጠ፣ እከሌ ክልል ደግሞ ሰፊ የእርሻ ቦታ ወሰደ ብሎ ለቅራኔ ማነሳሳት ለጥፋት ከመጋበዝ ባለፈ ህገ መንግስታዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ያሳያል፡፡

ሲጀመር አስተዳደራዊ ወሰን ባልነበረበት ቦታ ከየት ወደየት እንደሄና እንደተሰጠ  የሚያሳይ ውሀ የሚቋጥር ማስረጃም መረጃም  በሌለው ሁኔታ፣ መካለሉ ኖረም አልኖረም ተጋብቶና ተዋህዶ፣ በጋራም ሰርቶ በሚኖር ወንድማማችና እህትማማች ህዝብ መካከል  አፍራሽ ሀይሎች የሚነዙት አሉባልታ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡

የፀገዴ አገር ሽማግሌ አስተባባሪ አቶ ካሳዬ ሀፍቱ  “የሁለቱም ህዝቦች ጥያቄ የእርሻ ቦታው በጋራ እንጠቀምበት እንጂ መሬት ለክቶ የመቀራመት ጉዳይ አልነበረም” ፡፡

በመሆኑም የአርሶ አደሩ ጥያቄ ከእርሻ ስራው ሳይፈናቀል ህጋዊ የመጠቀምያ እውቅና አግኝቶ በነፃነት እንዲያመርት ነበር ፡፡ የአገር ሽማግሌዎች ያደረጉትም  ይህንኑ ነው ይላሉ፡፡

በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 40 ንኡስ አንቀፅ 4 ላይ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነፃ የማግኘትና ከመሬታቸው ያለመፈናቀል መብታቸው የተከበረ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

ውሳኔው ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ህዝቡን ደስ ያሰኘ መሆኑንም አቶ ካሰዬ ይናገራሉ፡፡

ሁለቱም ርእሰ መስተዳድሮች ለአገር ሽማግሌዎች ውሳኔ ተገዢ መሆናቸውን ስላረጋገጡላቸው አድናቆታቸውን ይገልፃሉ ።

ወሰን የማካለሉ ስራ ዳኛና ሌላ ሶስተኛ አካል ሳይጨመርበት በወንድማማች ህዝቦች መተማመንና መተዛዘን በተሞላበት መንገድ መጠናቀቁ ለጠላቶች በር የዘጋና የዞረ ድምር ሳያስቀር ለአንዴና ለመጨረሻ የተቋጨ አጀንዳ መሆኑን  አቶ ካሳዬ በልበ ሙሉነት ነበር የገለፁት ፡፡

ሌላው የፀገዴ ወረዳ የአገር ሽማግሌ መልአከ ፀሀይ ሙሉ ድረስ  “ውሳኔው ህዝባችንን ያስደሰተ ነው፡፡ ህዝቡ የሚፈልገው ሰላምና አብሮነት ነው፡፡ በውሳኔው ረክተናል ። በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን  እንፈልጋለን “  ይላሉ፡፡

ውሳኔውን ተከትሎ የአየገር ሽማግሌዎቹ በየቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ህዝቡን እንዳወያዩት ነው የሚናገሩት፡፡

በውሳኔው የተከፋ አርሶ አደር አላጋጠመንም ይላሉ፡፡ ሁለቱም መንታ ህዝቦች የጋራ ችግራቸውን በራሳቸው ንቁ ተሳትፎ መፍታታቸው ከማንም በላይ ያስደሰተው ለዘመናት አብሮ የዘለቀው ህዝብ ራሱ ነው ። ችግሩን ለማባባስ ከዳር ሆነው አሉባልታ የሚነዙ ሃይሎች ቢያላዝኑ አይፈረድባቸውም ። ምክንያቱ ደግሞ ለጥፋት መቆማቸው ነበር - ግን ህዝቡ ነቃባቸው ።

የእንጀራ ገመዳቸውና የህልውናቸው ማራዘሚያ ስልት አድርገው የሚያስቡት አሉባልታ ሰሚ አጣ ። ይህ ቦታ ተወሰደብን ፣ ይህ ቦታ ደግሞ ትርፍ አገኘን እያሉ ግጭት የሚፈጥሩበት እድልም ጠቧል ። ያላቸው ብቸኛ እድል ችግሩ ሲፈጠር የሳቁትን ያክል ችግሩ ሲፈታ ደግሞ እርር ድብን ብለው ማልቀስ ብቻ ነው ።

ህዝቡ ግን ከእንግዲህ በኋላ  ’’አደብ’’ ይግዙልን እያለ ነው ፡፡ የሁለቱም ክልል መንግስታትም እየተከታተሉ ልካቸውን እንዲያውቁ ያድርጉልን  ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ሁለቱም ህዝቦች እስከ አሁን መሬቱን በጋራ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፡፡ የሁለቱም  የአገር ሽማግሌዎች የተማመኑበት ዋና ቁም ነገር  አሁንም እንደወትሮው ማንም አርሶ አደር ከእርሻ ቦታው ሳይፈናቀል  የመጠቀም መብቱ እንዲከበር ማድረግ መሆኑ መልአከፀሀይ ይገልፃሉ፡፡

ወሳጅም ሰጪም የለም፡፡ አርሶ አደሩ ኬላ ሳያስፈለግው ያመረተውን ምርት በፈለገው ቦታ እንዲሸጥ የማድረግ ስራ ነው ተፈፃሚ እንዲሆን የጠየቁት፡፡

ህዝበ ውሳኔው ከሁለቱም ክልል የሚመለከታቸው አካላት በተጨማሪ የፌደራል መንግስት የአገር ሽማግሌዎችን ውሳኔ ተቀብሎ እንዲያፀድቀው ከመጠየቅ ባለፈ በህዝቡ አንዳች ግርታም የለም ብለዋል፡፡

የሁለቱም ህዝቦች ፍላጎት ሁለቱም ክልሎች በጋራ ሆነው መሰረተ ልማት እንዲስፋፋላቸው ከመጠየቅ ውጭ  የመሬት ጥያቄ የአርሶ አደሩ ጥያቄ አይደለም ያሉት ደግሞ ሌላ የፀገዴ ወረዳ የአገር ሽማግሌ ተወካይ አቶ ብረሀኑ ተሾመ ናቸው፡፡

የህዝቡ አጀንዳና ፍላጎት ልማትና አብሮነት ነው፡፡ ፀገዴና ጠገዴ የአንድ እናት ልጆች ናቸው፡፡

በመሆኑም ህዝቡ መሀል ገብቶ ሊለያያቸው የሚችል ሀይል አለመኖሩን ባለፈው ክረምት በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው ግርግር በእነሱ ዘንድ አለመከሰቱ ትልቅ የመንታ ወንድማማችነት ማሳያ መሆኑን  በግልፅ አሳይተዋል፡፡

ለወደፊቱም ቢሆን በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን በማጠናከር በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ ለዘላቂ ልማትና አስተማማኝ ሰላም መረጋገጥ አብረው እንደሚሰሩ  የማያጠራጥር ደረጃ ላይ መድረሳቸውን በተግባር አረጋግጠዋል ።

 

 

Published in ዜና ሓተታ

ነቀምቴ መስከረም 3/2010 የጊምቢ ከተማን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረት ለማቃለል በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ለስምንት ዓመታት በመጓተቱ መቸገራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግሩ።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ ቸርነት አስፋው እንደገለጹት የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ በ2002 ዓ.ም ሲጀመር በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ቢባልም እስካሁን ባለመጠናቀቁ በውሃ እጥረት እየተጉላሉ ነው።

ለከተማዋ ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ነባሩ የውሃ ተቋም ከህዝብ ቁጥር ማደግ ጋር ተያይዞ በቂ ባለመሆኑ የከተማዋ ነዋሪ ንፅህናው ያልተጠበቀ የወንዝ ውሃ ለመጠቀም ከመገደዱም ባሻገር በሴቶችና ህጻናት ላይ የሥራ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል።

"ለገጠሩ ሕብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተመቻቸበት በአሁኑ ወቅት የከተማ ነዋሪዎች ከእንስሳት ጋር እየተጋፉ የወንዝ ውሃ ለመጠቀም መገደዳቸው አግባብ አይደለም" ብለዋል።

የውሃ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠናቁ ለውሃ ወለድ በሽታ እየተጋለጡ መቸገራቸውን የገለጹት ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ ወይዘሮ ጌጠ ከበደ ናቸው።

መንግስት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የህብረተሰቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ያስጀመረው ፕሮጀክት በትኩረት ማነስ በመጓተቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው ገልጸው ችግሩ በተለይ በእናቶችና ሕፃናት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉን አመልክተዋል።

የከተማዋ የውሃ አቅርቦት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ፕሮጀክቱ የሚጠናቀቅበት ሁኔታ እንዲመቻች የጠየቁት ደግሞ አቶ እጅጉ ኩሚ ናቸው።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃኔ ታመነ በበኩላቸው   በጊምቢ ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመረው የውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቱን ተናግረዋል።

በተለይ የሥራ ተቋራጭ አቅም ማነስና የግንባታ እቃዎች ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መናር በዋናነት ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከብዙ ድካም በኋላ የፕሮጀክቱ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ቀሪውን ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ 26 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ ፣ የውሃ ማከፋፊያ ቦኖ ፣ የውሃ ማጠራቀሚያ ጋን ግንባታና ሌሎችም ተጓዳኝ  ሥራዎችን ያካተተ መሆኑንም አስታውሰዋል።

ፕሮጀክቱ ሥራ ሲጀምር ከ100 ሺህ ለሚበልጡ የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

በጊምቢ ከተማ ቀደም ሲል የተሰራው የውሃ ተቋም ለ30 ሺህ ህዝብ አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እንደነበር ከዞኑ ውሃ ፣ መአድንና ኢነርጂ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ መስከረም 3/2010 በቢሾፍቱ  ከተማ ከ18 ሺህ የሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች እንዲሰማሩ ተደረገ፡፡

 ለወጣቶቹ  ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስርም ተፈጥሯል።

 የከተማዋ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሉሉ አለሙ እንደገለፁት ወጣቶቹ እንዲሰማሩ የተደረገው ባለፈው በጀት ዓመት ባገኙት ተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ  ድጋፍና በመደበኛ ፕሮግራም ነው።

 በመደበኛው ፕሮግራም  ለ5 ሺህ 470 ወጣቶች ቋሚና ለ11 ሺህ 515 ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን  በተዘዋዋሪ የብድር ገንዘብ  ድጋፍ ደግሞ 1 ሺ 206 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ተደራጅተው ወደ ስራ  እንዲገቡ ተደርጓል።

 ወጣቶቹ ከተሰማሩባቸው የገቢ ማስገኛ መስኮችም የድንጋይ ንጣፍ መንገድ ግንባታ ፣የማዕድን ልማት፣ብረታ ብረትና እንጨት ሥራ፣እንስሳት ማድለብና ዶሮ እርባታ ይገኙበታል።

 አስተዳደሩ የከተማዋ ወጣቶች ያለባቸውን የመልካም አስተዳደር ችግር በመፍታት የተለያየ ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጉንም አቶ ሉሉ አመልክተዋል።

 ከተደረገላቸው ድጋፍ  መካከል በባለሃበቶች አለአግባብ የተያዘ  74 ሄክታር የማዕድን ማምረቻ  ቦታ በመንጠቅ በ95 ማህበራት ለተደራጁ 3 ሺ 349 ወጣቶች መሰጠቱ ይገኝበታል።

 ከ10 ዓመት በላይ በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ 175 የማምረቻና የመሸጫ ሼዶችን በማስለቀቅ ለ103 ማህበራት ማስተላለፉን የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ጠቅሰዋል።

 ያለባቸውን የመንቀሳቀሻ ካፒታል ችግር ለመፍታትም ለ82 አንቀሳቃሾች 18 ሚሊዮን 323 ሺ 231 ብር በብድር ተሰጥቷል።

 የስራ እድሉ ተጠቃሚዎች በእንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የስራ እቅድና የንግድ ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ ከመደረጉም በላይ 91 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል።

 በቢሾፍቱ ከተማ የዜሮ ዘጠኝ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሀሮምሳ አዲሱ በሰጠው አስተያየት መንግስት በቀበሌያቸው በ7 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን የወጣቶች መዝናኛ ማዕከል እሱን ጨምሮ 23 ወጣቶች በቅርቡ ተረክበው የገቢ ምንጭ ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

 "በማዕከሉ የካፍቴሪያ፣የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን፣የስፖርት ማበልጸጊያ፣የስብሰባ አዳራሸና የኢንተርኔት አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ በመስጠት ተጠቃሚ መሆን ጀምረናል" ብሏል።

 ወጣት አርሲት ቃዲ በበኩሏ አምስት ሆነው በመደራጀት በካፍቴሪያ አገልግሎት መሰማራታቸውን ጠቅሳ  ከመንግስት ባገኙት የቡና ማሽን ጨምሮ  በ60 ሺህ ብር ብድር የውስጥ ቁሳቁስ ማሟላታቸውን ገልፃለች።

 መንግስት ለወጣቱ በሰጠው ትኩረት እሰካሁን አምስት የወጣቶች መዝናኛ ማዕከላት አስገንብቶ በማስረከቡ በርካታ የማህበሩ አባላት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገረው ደግሞ የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት ተገኝ አለማየሁ  ነው፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ፍቼ  መስከረም 3/2010 አካባቢያቸው በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ መሻሻል እየታየበት መሆኑን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች ገለጹ።

 የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ከ41 ሺህ  በላይ መዝገቦች ውሳኔ ማግኘታቸውን አስታውቋል።

 የፍቼ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዓለም ባይሳ በሰጡት አስተያየት በዞኑ ፍርድ ቤት በተለይ ከጥልቅ ተሀድሶ ወዲህ ለተገልጋዩ እየተሰጠ ያለው አገልግሎት መሻሻል ታይቶበታል።

 ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤቱ በፍታብሄር ለታየ ጉዳያቸው ውሳኔ ለማግኘት 18 ቀጠሮ መፍጀቱን ያስታወሱት ወይዘሮ ዓለም በቅርቡ ከቤተሰብ ውርስ ጋር ተያይዞ በፍርድ ቤቱ የታየው ጉዳያቸው በአራት ቀጠሮ ውሳኔ ማግኘቱን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

 የደገም ወረዳ ነዋሪ  አቶ ታምሩ አረዶ በበኩላቸው በንብረት ይገባኛል ክርክር በወረዳው ፍርድ የተያዘው ጉዳያቸው በሦስት ቀጠሮ ብቻ እልባት ማግኘቱን ተናግረዋል ።

 " በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለከፈትኩት የፍታብሄር ክስ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ አግኝቻለሁ " ያሉት ደግሞ የገብረ ጉራቻ  ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ብርሃኔ አጋ ናቸው ።

 ከሁለት ዓመት በፊት በወረዳው ፍርድ ቤት ለተመሳሳይ የክስ መዝገብ የታየው ጉዳያቸው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በዘጠኝ ቀጠሮ ለውሳኔ መብቃቱን አስታውሰዋል ።

 ሌላዋ የግራር ጃርሶ ወረዳ ፍርድ ቤት ተገልጋይና የፍቼ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት አስጨናቂ በበኩላቸው በፍርድ ቤቱ ለባለጉዳይ የሚደረገው አቀባበልና አገልግሎት አሰጣጥ እየተሻሻለ መሆኑን ተናግረዋል።

 የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበኩሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዞኑና በ13 ወረዳ ፍርድ ቤቶች ከቀረቡ 44 ሺህ 104 የወንጀልና የፍትሐብሄር የክስ መዝገቦች ውስጥ 41ሺህ 39ኙ ውሳኔ ማግኘታቸውን  አስታውቋል።

 የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት አቶ አብርሃም አበበ እንደገለፁት ውሳኔ ካገኙት መዝገቦች ውስጥ 7 ሺህ 338ቱ የወንጀልና 33 ሺህ 701ዱ የፍታብሄር ናቸው ።

 " አብዛኞቹ የክስ መዝገቦችም በአጭር የጊዜ ቀጠሮ ውሳኔ ያገኙ ናቸው " ብለዋል ።

 ቀሪዎቹ ሦስት ሺህ 15 መዝገቦች ከወረዳ ይግባኝ  የተባለባቸውና ጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው መሆኑንም አቶ አበርሀም ጠቁመዋል ።

 በበጀት ዓመቱ በፍርድ ቤቶቹ ውሳኔ ያገኙ መዝገቦች ቁጥር በ2008 በጀት ዓመት ውሳኔ ከተሰጣቸው መዝገቦች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በ1 ሺህ 255  ብልጫ አለው።

 በበጀት ዓመቱ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ በአቅራቢያው ፍትህ እንዲያገኝ ተዘዋዋሪ ችሎትን በመሰየም ከወረዳ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ለተጠየቀባቸው 1 ሺህ 701  የክስ መዝገቦች  ውሳኔ መሰጠቱንም አቶ አብርሀም አስረድተዋል።

 እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ በተለይ በጥልቅ ተሀድሶ መድረኮች ከህዝቡ የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ በተወሰደ የማስተካከያ እርምጃ በፍርድ ቤቶች የፍትህ አሰጣጥ ሂደት በመሻሻሉ ውሳኔ በመስጠት በኩል የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።

 በፍርድ ቤቶቹ ከተሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች 4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

ደሴ መስከረም 3/2010 በደሴ ከተማ ከኢትዮጵያ ሚሌኒየሙ ማግስት ጀምሮ ከ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል።            

ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በከተማዋ በተሰራው የ483 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። 

በደሴ ከተማ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሰረተ ልማት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጌትነት አልታዬ እንዳሉት ለመንገድ ግንባታው ከአንድ ቢሊዮን 750 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኗል።

በገንዘቡ የአስፋልት፣ የጥርጊያ መንገድ፣ የኮብል ስቶን፣ የገረጋንቲና የድንጋይ ንጣፍ መንገዶች መሰራታቸውን ገልጸው ፣ የዓለም ባንክ ፣ የፌዴራልና የክልሉ መንግስት እንዲሁም የከተማዋ አስተዳደር ለመንገዱ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የተሰሩት መንገዶች የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ ቀደም ሲል መንገድ ያልነበራቸው የከተማዋ አካባቢዎች ለመንገድ ተደራሽ ሆነዋል። 

"የከተማዋ የመንገድ ሽፋን ተደራሽ እየሆነ በመምጣቱ ከ10 ዓመት በፊት የአምቡላንስ፣ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና የእሳት አደጋ ተሸከርካሪዎች የማይገባባቸው አካባቢዎች ሳይቀሩ በአሁኑ ወቅት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል" ብለዋል፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በከተማዋ አንድ ዋና መንገድ ብቻ እንደነበር አስታውሰው  ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ አማራጮችና አገናኝ መንገዶች በመሰራታቸው የከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ እየቀነሰ መምጣቱን አመልክተዋል፡፡

ሕብረተሰቡም ለመንገድ ግንባታው ቦታ በመልቀቅና ደጋፊ ግንብ በመገንባት ያሳየው ተሳትፎ ለስራው ውጤታማነት አስተዋጽኦ እንደነበረው አቶ ጌትነት አስታውሰዋል፡፡

በሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ቀጠና 2 ነዋሪ አቶ ዘውገ መላኩ ለኢዜአ እንደተናገሩት ቀደም ሲል ውስጥ ለውስጥ መንገድ ባለመኖሩ የአምቡላንስ ፣ የእሳት አደጋና ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎች ወደ አካባቢያቸው መድረስ አይችሉም ነበር፡፡

መንገዱ አለመሰራቱ አምሽቶ ለመንቀሳቀስና የማታ ትምህርት ለመከታተል እንቅፋት ከመሆኑም በላይ የሕብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር የቅሬታ ምንጭ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል። 

የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ጽህፈ ቤት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ አድማሴ በሰጡት አስተያየት  በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ብቻ የባጃጅ ትራንስፖርት የሚሰጥባቸው 26 መንገዶች እንዲከፈቱ ተደርገዋል፡፡

በዚህም በከተማ ክልል ውስጥ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

Published in ኢኮኖሚ
Wednesday, 13 September 2017 21:30

የብርሃን አብዮት

Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ መስከረም 3/2010 የፌደራሉ ዓቃቤ ሕግ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የቀድሞ ኃላፊዎችና በስኳር ኮርፖሬሽን የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ኃላፊዎች በነበሩት ላይ ክስ መሰረተ።

አቃቤ ሕግ ዛሬ ክሱን የመሰረተው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ነው።

ክሱ የተመሰረተው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ፈቃደ ኃይሌን ጨምሮ አራት የባልስጣኑ ኃላፊዎች የነበሩና በሙስና ወንጀል ተከሰው በማረሚያ ቤት በሚገኙት የትሕዳር ኮንስትራክሽን ኧርዝ ሙቪንግ ድርጅት ባለቤት ሚሰትር ሚናሺ ሊቪ ላይ ነው።

አቃቤ ሕግ በነዚሁ አካላት ላይ ክሱን የመሰረተባቸው የባለስልጣኑ ኃላፊዎች የአስተዳደሩን የግዥ መመሪያ ተከትለው መስራት ሲገባቸው ከትሕዳር ኮንሰትራክሽንና ኧርዝ ሙቪንግ ከተሰኘው ኩባንያ ባለቤት ጋር ተመሳጥረው በመንግስትና በሕዝብ  ሃብት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው ነው።

እነዚሁ የስራ ኃላፊዎች  ከዚሁ ኩባንያ ጋር በመሆን በቀድሞ ማእድን ሚኒስቴር ተብሎ በሚጠራው፣ በለም ሆቴል 22 ማዞሪያ እስከ  የውሃ መስኖና ኤሌትሪክ ሚኒስቴር ድረስ ለሚካሄደው የመንገድ ግንባታ ውል ሲፈፀም ኩባንያው ሊያሲዝ የሚገባውን የመድን ገንዘብ  ባለማስያዙ ነው።

በተጨማሪም ኩባንያው በ2007 ዓ.ም ጀምሮ ስራውን ሲያቋርጥ ሊመልስ የሚገባውን ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ሳይመልስ በመቅረቱ በመንግስትና በሕዝብ ሃብት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው መሆኑ ተገልጿል።

በዚሁ መሰረትም የቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብት የሚያሰጣቸው ባለመሆኑ ጥቅምት 9 ቀን 2010 ዓ.ም የክስ መቃወሚያ ይዘው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ አዟል።

በተመሳሳይም ለችሎቱ የቀረበው እነ አቶ የማነ ግርማይ የተካተቱበት የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት በአቶ ፈለቀ ታደሰ መዝገብ ክስ የቀረበባቸውን የሰባት ሰዎች ጉዳይ ነው።

ተከሳሾቹ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ውስጥ በተለያየ ቦታ ኃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ ለባቱ ኮንስትራክሽን ተሰጥቶ የነበረውን የደን ምንጠራ ስራ በመንጠቅ  ለየማነ ግርማይ ጠቅላላ ተቋራጭ በተጋነነ ክፍያ ስራውን እንዲያከናውን በማድረጋቸው ነው።

ተከሳሾቹ ክስ የተመሰረተባቸው በአጠቃላይም 95 ሚሊዮን ብር በሚደርስ የመንግስትና የሕዝብ ሐብት ላይ ጉዳት በማድረሳቸው እንደሆነም ፍርድ ቤቱ ክሱን ለችሎቱ በንባብ አሳውቋል።

እነዚሁ ተከሳሾች የዋስትና ሕገ-መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን ፤ የቀረበባቸው ክስ እስከ 25 ዓመት የሚያስቀጣ በመሆኑም በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል፡፡

በዚሁ መሰረት ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የክስ መቃወሚያ ካላቸውም ለጥቅምት 8 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ወስኗል።

የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና በኦሞ ኩራዝ አምስት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ኃላፊዎች በነበሩት ላይ ምርመራውን ማጠናቀቁንና ለዓቃቤ ሕግ መዝገቡን ማስተላለፉን የገለጸ ሲሆን ፤ ፍርድ ቤቱም ክስ እንዲመሰረት ትእዛዝ ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳሬይክተር በነበሩት በእነ አቶ ዛያድ ወልደገብርኤ መዝገብ ስር 13 ሰዎች ላይ  ፖሊሲ ምርመራውን በመጨረሱም መስከረም 12 ቀን ክስ እንዲመሰረት ፍርድ ቤቱ አዟል።

በተመሳሳይም በኦሞ ኩራዝ አምስት የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክት ኃላፊዎች በእነ አቶ መስፍን መልካሙ የክስ መዝገብ ስር ባሉት አምስት ተጠርጣሪዎች ላይም በተመሳሳይ መስከረም 11 ቀን አቃቤ ሕግ ክስ መስርቶ እንዲቀርብም አዟል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን