አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Tuesday, 12 September 2017

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 የአፍሪካ ልማት ባንክ ለኢትዮጵያ እያደረገ ያለው ድጋፍ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የባንኩ የሰባት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ዶክተር ካሌብ ወጋሮ ገለጹ።       

ዳይሬክተሩ ባንኩ ፈንድ እያደረገ የሚገኘውን የሞምባሳ-ናይሮቢ-አዲስ አበባ አስፋልት መንገድ ግንባታና የኃይል ማስተላለፊያን ፕሮጀክቶች ጎብኝተዋል።

ዶክተር ካሌብ ከጉብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈንድ የሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች ለአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እድገት የጎላ ሚና አላቸው። 

''ባንኩ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር በብድርና በስጦታ በማቅረብ 22 ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል'' ነው ያሉት።

ከዚሁ ወስጥ 33 በመቶ ለትራንስፖርት ዘርፍ፣ 19 በመቶ ለኃይል ዘርፍ፣ 16 በመቶ ደግሞ በማህበራዊ ልማት እንዲሁም ለግል ዘርፍ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተሩ ገለጻ በተለይ ኢትዮጵያን ከኬኒያ ጋር የሚያገናኛት የሞምባሳ -ናይሮቢ-አዲስ አበባ የመንገድ ኮሪደር ግንባታ ተጠቃሽ ነው። 

750 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው መንገዱ ከአገረ ማሪያም እስከ ሞያሌ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን ከአዋሳ እስከ አገረማሪያም ደግሞ ግንባታው እየተከናወነ ነው።    

ግንባታው የኢትዮጵያና ኬኒያ የንግድ ግንኙነትን የሚያጠናክርና የሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ግዙፍ ኢኮኖሚ እርስ በእርስ እንዲደጋገፍም ያደርጋል ብለዋል።  

መንገዱ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያን ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር በቀላሉ የሚያገናኝና የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ውህደት የበለጠ ለማፋጠንም ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።   

በኬኒያ በኩል ያለው የመንገዱ ግንበታ የተጠናቀቀ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል ያለውም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ባንኩ ክትትል እንደሚያደርግም ነው ያረጋገጡት። 

በባንኩ ድጋፍ እየተከናወኑ ከኢትዮጵያ ወደ ጂቡቲና ኬኒያ እየተዘረጉ የሚገኙ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችም በተሻለ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።  

''ይህም ሥራው ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ተጫማሪ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝላትና ኢኮኖሚዋ የሚያድግበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል'' ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ብድርና እርዳታ በመጠቀም ከአህጉሪቷ ከናይጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን መረጃዎች ያመለክታሉ።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 በተለያዩ አገሮች የተመደቡ አምባሳደሮች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አሳሰቡ። 

የአመራር አባላቱን የክህሎት፣ የእውቀትና የአመለካከት ችግሮችን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርትና የምርምር ተቋማትን መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ዛሬ ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራር አባላትና ከሚሲዮን መሪዎች ጋር ተወያይተዋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2009 በጀት ዓመት አፈጻጸም የሥራ ግምገማና የ2010 ዕቅድ ላይ መክረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በወቅቱ እንደገለጹት፤ አገሪቷ አሁን ካለችበት የእድገት ደረጃ አኳያ በዲፕሎማሲው ዘርፉ የተፈለገውን ያህል ውጤት አልመጣም።

በተለይ በተቋማት ግንባታ፣ በሰው ሀብት ልማት ስምሪት፣ ክህሎት ያለውን አመራር ከመገንባት አኳያ መከናወን የሚገባቸው በርካታ ተግባራት እንዳሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም በሰው ኃይል በኩል ያሉ የአመለካከት ችግሮችን በመፍታት ሁሉም የአመራር አባል በተመደበበት ቦታ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት መረባረብ እንደሚገባው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም በበኩላቸው፤ በቀጣይ የሰው ኃይል የክህሎትና የእውቀት ውስንነትን ለመፍታት ከፍተኛ ተቋማትና የምርምር መሥሪያ ቤቶችን ለመጠቀም አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።  

"ከውጭ ዲፕሎማሲው በዋናነት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል" ብለዋል።

የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ስኬት በዲፕሎማቶች ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል በተለይ ባለሀብቱ፣ ነጋዴው፣ ምሁራን፣ አርቲስቱ፣ ስፖርተኛውና ሎሎችም ዜጎች ግዴታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።

በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳቡም ረገድ አምባሳደሮቹ ቅድሚያ ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2009 በጀት ስራ አፈጻጸም ከነሐሴ 25 እስከ ጳጉሜን 4 ቀን ድረስ በአዲስ አበባ እና ሐዋሳ ከተማዎች ገምግሟል።

በግምገማው አመራር አባላቱ በአስተሳሰብ፣ በአመለካከት የተለወጡ፣ የተደራጁና በአንድነት የሚንቀሳቀሱ የአገሪቷን የውጭ ፖሊሲ የሚያስከብሩ ተግባራትን በማከናወን ደረጃ ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ ታይቷል። 

 

 

Published in ፖለቲካ

አርባ መንጭ መስከረም 2/2010 በጋሞጎፋ ዞን በክረምቱ ወራት ወጣቶች ባከናወኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 480ሺህ ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ኦፊሰር ወይዘሪት ናርዶስ ሺበሺ እንዳሉት በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ282 ሺህ በላይ ወጣቶች በ23 የልማት መስኮች ተሳትፈዋል፡፡

ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናትና አረጋዊያን ድጋፍና እንክብካቤ፣ የደም ልገሳ፣ የጎልማሶች ትምህርት፣ የከተማ ጽዳትና ውበት ማስጠበቅ ወጣቶቹ ካከናወኗቸው  የልማት ስራዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

ስራዎቹም ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸው ሲሆን 480ሺህ ያህል የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ወይዘሪት ናርዶስ ገልጸዋል፡፡

በጋሞጎፋ የካምባ ወረዳ ነዋሪ አቶ ሽብሩ ሽርኮ አቅመ ደካማ በመሆናቸው በክረምት በተከናወነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቶቹ የምግብና አልባሳት ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

የተጎዳው መኖሪያ ጎጇቸውን ጭምር እንዳደሱላቸው በመጥቀስ ወጣቶቹን አመስግነዋል፡፡

በደንባ ጎፋ ወረዳ የዛንጋ አዋንዴ ቀበሌ ነዋሪው ተማሪ አድማሱ ካሌብ ወላጆቹን በሞት ካጣቸዉ በኋላ የሚያስተምረው ባለመኖሩ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዶ እንደነበር ገልጿል፡፡

በወጣቶቹ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎ የመማሪያ ደብተርና እስክሪቢቶ እንዲሁም ልብስ ጭምር ባደረጉለት ድጋፍ ያቋረጠውን ትምህርት ለመቀጠል መመዝገቡንም ጠቅሷል፡፡

ለጎልማሶች የተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት በክረምት በጎ አገልግሎቱን በማከናወኑ ደስተኛ መሆኑን የተናገረው ደግሞ  የሳውላ ከተማ ነዋሪና በሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በሶሾሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት የሶስተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው የሩቅነህ አውግቸው ነዉ ፡፡

" ሀገር የምታድገው በመንግስትና በህዝብ አንድነት በመሆኑ በጎ አገልጋይ በመሆኔ ነገ በሥራ ዓለምም ተግባሬን በሚገባ እንድወጣ የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማኝ አድርጎኛል" ብሏል ፡፡

የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪና በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ በስነ ህንጻ ጥበብ የሁለተኛ ዓመት ተማሪው አብርሃም ፍቃዱ በበኩሉ "በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፌ ጊዜዬን በአልባሌ ቦታ እንዳላባክን አግዞኛል" ብሏል ፡፡

በደም እጥረት ለሚቸገሩ ወገኖች  ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ደም መለገሱንም ጠቅሷል፡፡

Published in ማህበራዊ

ወልዲያ መስከረም 2/2010 የኤሌክሪክ ሀይል መቆራጥና መጥፋት ስራቸውን በማስተጓጉል ለኪሳራ እየደረጋቸው መሆኑን በወልድያ ከተማ አስተያየታቸውን የሰጡ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለቤቶች አመለከቱ።

ወይዘሮ አቻሽማን ክቡር ለኢዜአ እንዳሉት  ከሁለት ዓመት በፊት ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ባገኙት የብድር ገንዘብ  ያቋቋሙት የእህል ወፍጮ በኤሌክትሪክ ሀይል መቆራረጥና መጥፋት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት አልቻለም ።

በኃይል መዋዥቅ ምክንያትም የወፍጮው መለዋወጫ በየጊዜው እየተቃጠል ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጋቸው መቸገራቸውን አመልክተዋል፡፡

በአንድ ጊዜ ብቻ ለተቃጠለ መለዋወጫ እቃ ግዥ እሰከ 7ሺህ ብር እንደሚያወጡ በመጥቀስ።

"በተጨማሪም የሀይል መቋረጥ ሲያጋጥም በወፍጮ ቋት ውሰጥ የሚቀረው እህል ሀይሉ ተመልሶ እስኪመጣ እስከ ሁለት ቀን የሚቆይበት አጋጣሚ ስለሚኖር ከደንበኞቼ ጋር ቅሬታ ውስጥ እንድገባ እያስገደደኝ ነው " ብለዋል ።

በሀይል መቆራረጥና መጥፋት ስራቸው  በመስተጓጎሉ ወፍጮውን ለማቋቋም የተበደሩትን ገንዘብ በወቅቱ መመለስ እንደተሳናቸውም ጠቁመዋል፡፡

የዳቦ ቤት ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ትርንጎ ወርቅነህ በበኩላቸው ባገኙት 80ሺህ ብር ብድር ያቋቋሙት የዳቦ መጋገሪያ ተቋም በተመሳሳይ ችግር ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንደተሳነው ገልጸዋል።

በተደጋጋሚ ለቀናት በሚያጋጥም የሀይል መጥፋት ሊጋገር የተዘጋጀ ሊጥ ወደ ዳቦነት ሳይለወጥ ለብልሽት እየዳረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል ።

ለህብረተሰቡ በሚሰጡት አገልግሎት ከሚያገኙት ገቢ እዳቸውን ለመክፈል ዳቦውን በእንጨት ለመጋገር መገደዳቸውን ጠቁመው በአንድ ጊዜ ለሚጋግሩት 30 ኪሎ ግራም ዱቄት ለማገዶ ግዥ ከ200 ብር በላይ ወጪ በማውጣት ለኪሳራ መዳረጋቸውንም አመልክተዋል።

"በኤሌክትሪክ ሀይል መጥፋትና መቆራረጥ ከምሰራበት ይልቅ የማልሰራበት ጊዜ ስለሚበዛ ራሴንና ቤተሰቤን መርዳት እየተሳነኝ መጥቷል" ያሉት ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ጥገና የተሰማሩት አቶ ባየው ዓለሙ ናቸው ።

እንደ አቶ ባየሁ ገለፃ በከተማው በተለይ ከሶስት ዓመታት ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ ቢመጣም መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም ።

የሚመለከተው አካል ችግሩን በመረዳት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል ።

በወልድያ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ አቶ ቢምረው ይርጋ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ  ለከተማው የተፈቀደው 12 ሜጋ ዋት ኃይል በዙሪያው ለሚገኙ የገጠር ከተሞች ጭምር የሚሰራጭ በመሆኑ የኃይል አቅርቦቱና ፍላጎቱ አለመጣጣሙ የችግሩ ምከንያት እንደሆነ ነው ብለዋል፡፡

"የምሰሶ መውደቅ፣ ዛፍ ከመስመር ጋር መገናኘት፣ ህብረተሰቡ ከሚገለልበት ቆጣሪ ለሌሎች ኃይል መስጠት፣ የትራንስፎርመር መቃጠል  ደግሞ ለሀይል እጥረቱና መቋረጥ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው " ብለዋል ።

በክረምቱ ወቅት ብቻ 1ሺህ 500 ቆጣሪዎችና አራት ትራንስፎርመሮች በመቃጠላቸው ተቋማቸው ጭምር ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በዋናው መስሪያ ቤት በኩል 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ አንድ ተንቀሳቃሽ ትራንስፎርመር የተፈቀደ በመሆኑ በአንድ ወር ውሰጥ ተተክሎ ችግሩ እንደሚፈታም አመላክተዋል ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከከባህር ዳር ባለ 400 ኪሎ ቮልት ሀይል ተሸካሚ መስመር መዘርጋትና መቻሬ ሜዳ ላይ የሀይል ማሰራጫ ተከላ መጀመሩንም ጠቅሰዋል ።

አቶ ቢምረው እንዳሉት ስራውን በሁለት ዓመታት ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ።

 

 

 

 

Published in ኢኮኖሚ

መስከረም 2/2009 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦች መጣሉን በቢሲ ዘግቧል፡፡

ፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ሙከራን ለስድስተኛ ጊዜ ማድረጓን ተከትሎ አሜሪካ ያቀረበችውን ረቂቅ የማዕቀብ የውሳኔ ሀሳብ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል።

በዚህም መሠረት ትናንት ሰኞ በተደረገ ውሳኔ ሰሜን ኮሪያ ነዳጅ ዘይት እንዳታስገባ እና የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ደግሞ ለውጭ ገበያ መሸጥ እንዳትችል የሚያደርግ ማዕቀብ ተጥሎባታል፡፡

በተጨማሪም ሁሉም ሀገሮች ለሰሜን ኮሪያ ሰራተኞች አዲስ የሥራ ፈቃድ እንዳይሰጡ የሚከለክል እገዳ የተጣለ ሲሆን፥ ይህም በሀገሪቱ ሁለት ዋና ዋና የገቢ ምንጮች ከባድ ጫና የሚፈጥር መሆኑ ተጠቁሟል።

ማዕቀቡም ከውጭ የምታገኘውን የሀይል አማራጭ በማስቆም የኒዩክለር አቅሟን ለማዳከም ነው ተብሏል፡፡

ሰሜን ኮሪያ በ6ኛ የሚሳይል ሙከራዋ የሀይድሮጅን ቦንብ ማስወንጨፏን  ተከትሎ  የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ 

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት አዘዘ።

በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር  ሚኒስትር ዴኤታ በነበሩት በአቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ ሥር ያሉ 16 የሙስና ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ሆኖም ባሳለፍነው ዓርብ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በገንዘብ እና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አማካሪ የነበሩት አቶ ደጉ ላቀው በመካተታቸው ቁጥሩ ወደ 17 አድጓል። ፍርድ ቤቱ በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ እንዲመሰረት አዟል።

ፖሊስ የአቶ ደጉ ጉዳይ በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ ሥር ተጨምሮ እንዲታይ ያደረገበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱም አስረድቷል። በዚሁ መሰረት ተጠርጣሪው እስከ 500 ሚሊዮን ብር ጉዳት ማድረሳቸውን አብራርቷል።

ከአቶ ደጉ በተጨማሪ ሁለት ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ የአቶ ደጉን ቃል አለመቀበሉንም በዝርዝር አስረድቷል። ይህንም በመጥቀስ ለተጠርጣሪዎች ዋስትና እንዳይሰጣቸውና ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቋል።

ይሁን እንጂ ግራና ቀኙን የመረመረው ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትእዛዝ በእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብ  የተካተቱ ተጠርጣሪዎች ላይ  ክስ ተመስርቶ በመስከረም 12 ቀን 2010 ዓ.ም እንዲቀርብ አዟል።

ቀሪ የምርመራ ሥራዎች በተሰጡት 11 ቀናት ውስጥ ጎን ለጎን እንዲከናወኑ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በወይዘሮ ፀዳለ ማሞ መዝገብ ሥር የሚገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች ላይም እስከ አርብ ድረስ ክስ ተመስርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ፖሊስ ተጨማሪ መያዝ ያለባቸው ተጠርጣሪዎች እንዳሉ፣ የፎረንሲክ ምርመራ እና የወጪ ማመሳከሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚቀርቡ ቢያስረዳም በፍርድ ቤቱ ውድቅ ሆኗል።

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ቀጠሮ ሲሰጥ የክስ ማቅረቢያ ቀን ቀንሶ መስጠቱን የገለፀው ፍርድ ቤቱ፤ እስከ አርብ ድረስ የክስ ማቅረቢያ ቀን ተሰጥቷል።

በጋራ የተጣመረው የአቶ ሲሳይ ሃይለሚካኤል እና የአቶ ታምሩ ታደሰ መዝገብን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፤ ፖሊስ ያቀረበው የተጨማሪ የምርመራ ቀን ውድቅ በማድረግ እያንዳንዳቸው በ10 ሺ ብር ዋስ ወጥተው ጉዳያቸው በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ወስኗል።

ፖሊስ "ተጠርጣሪዎችን በዓይን አይቶ በመለየት ምስክርነቱን የሚሰጥ ምስክር አለኝ የቀጠሮ ቀን ይሰጠኝ" ቢልም፤ ፍርድ ቤቱ ፖሊስ  የተጠርጣሪዎቹን ፎቶ በማሳየት ምስክሩን እንዲያስመርጥ ወስኗል።

ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ በማለቱ ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ሐሙስ እንዲወጡ ያዘዘው ፍርድ ቤቱ፤ ተጠርጣሪዎች ከአገር እንዳይወጡም አግዷል።

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ "ከጠጠርና ብረታ ብረት በተያያዘ ከ20 ሚሊዮን ብር ጉዳት አድርሰዋል" በሚል የተጠረጠሩት የእነ አበበ ተስፋዬ መዝገብ በነገው ዕለት እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ አዟል።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የወንጀል ችሎት ዛሬ ጠዋት በዋለው ችሎት የእነ አቶ አለማየሁ ጉጆ መዝገብን ጨምሮ ስድስት መዝገቦችን ተመልክቷል።

 

Published in ማህበራዊ

መቀሌ መስከረም 2/2010 በትግራይ ክልል የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስና  ፍላጎቱን ለማርካት የሚደረገው ጥረት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ  አቶ ልዑል ካሕሳይ ለኢዜአ እንደገለፁት በትግራይ ባለፈው የበጀት ዓመት መልካም አስተዳደርና ፍትህ ከማስፈን አኳያ ጥሩ የሚባል አፈፃፀም ተመዝግቧል፡፡

ቢሮው  በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ከ2 ሚሊዮን 400 ሺህ ለሚበልጥ  ህዝብ የንቃተ ህግ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ፣ አራጣ አበዳሪ፣ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከልን አስመልክቶ የተሰጠው ትምህርት ተጠቅሷል፡፡

እንዲሁም በቢሮው ስር የሚገኘው የወሳኝ ኩነት አደረጃጀት በማጠናከርና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በመስጠት ከ25 ሺህ በላይ አዲስ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተካሂዷል፡፡

ሆኖም በየጊዜው የሚወለዱ ህጻናትን በወሳኝ ኩነት የክብር መዝገብ  ማስመዝገብ ስራ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩ ኃላፊው  ጠቅሰዋል፡፡

ይህም " ስራው የፍትህ ቢሮ ብቻ ተደርጎ በመታየቱና ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው  አለመስራታቸው የፈጠረው ችግር ነው "ብለዋል።

በቀጣይም የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በወንጀልና ፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ጥሩ መሻሻል ቢታይም በይግባኝና ሰበር ጉዳዮች አፈጻጸም ላይ የሚቀሩ  ስራዎች እንዳሉ ነው  አቶ ልዑል ያመለከቱት።

እሳቸው እንዳሉት ቢሮው በየጊዜው የስራ ግምገማ በማካሄድ ችግሮችን ለመፍታት የተጓዘባቸው መንገዶች መልካም ናቸው፤ ሆኖም የመንግስትና ህዝብ ፍላጎት ከማሳካት አንፃር ክፍተቶች እንዳሉና ብዙ መስራትን ይጠይቃል፡፡

ከውሳኔዎች ፍትሃዊነትና  ጥራት አንፃር የነበሩ እጥረቶችን በማስተካከል የህብረተሰቡን የፍትህ ጥያቄ ለመመለስና  ፍላጎቱን ለማርካት የሚደረገው ጥረት በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

በክልል ደረጃ አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮች ተብለው የተለዩትን  የመሬት ወረራ፣ ህገወጥ ግንባታ፣ አስገድዶ መድፈርና አራጣ አበዳሪነት ለመከላከል በትኩረት ይሰራል ተብሏል፡፡

የወንጀል ምርመራ ባለሙያ ምክትል ኢንስፔክተር ልዑል ግርማይ በበኩላቸው "ወንጀለኞችን ተከታትለን በመያዝ፣ድርጊቱን በመመርመርና በማጣራት በጊዜው ወደ ሚመለከተው የህግ አካል እያቀርብን እንገኛለን "ብለዋል።

በእውነት ላይ ተመስርቶ የምስክርነት ቃልን መስጠት ወንጀል እንዳይስፋፋ የሚያግዝ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ   የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አማኑኤል ኪዳኔ  ናቸው፡፡

" የፍትህ አካላት እውነቱን ለማውጣት የሚያደርጉት ጥረት እንቅፋት በሚሆኑ ምስክሮች ላይ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል"ብለዋል፡፡

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ መስከረም 2/2010 አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስባትን ጉዳት ለመቆጣጠር ሳይንሳዊና አስተማማኝ የሆነ የውሃና ሚትዮሮሎጂ መረጃ ስርዓት እንደሚያስፈልጋት የአፍሪካ ህብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽን ገለፁ።

በሚትዮሮሎጂ ላይ ያተኮረው የአፍሪካ ሚኒስትሮች ጉባዔ ( አምኮሜት) የውሃና ሚትዮሮሎጂ አገልግሎት ፎረም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።

የህብረቱን የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነርን ወክለው በጉባኤው የተገኙት ሚስተር ሁሴን ያምቢ እንዳሉት፤ እኤአ ከ1970 ጀምሮ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ አንድ ሺህ የሚደርሱ ጉዳቶች ተመዝግበዋል።

ከእነዚህም መካከል ወደ ሶስት መቶ የሚጠጉት ጉዳቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ እንደተመዘገቡ አስታውሰዋል።

ከሰሃራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በአማካይ ከአስራ አንዱ ስምንቱ በአየር ንብረት ለውጥ በሚከሰት ችግር ምክንያት በድህነት ውስጥ እንደሚገኙ የተናገሩት የኮሚሽነሩ ተወካይ፤ ጉዳቱ በተለይ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የከፋ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በ2016 በኢትዮጵያ ብቻ ስምንት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ መጎዳታቸውንም ለአብነት አንስተዋል።

በመሆኑም አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚደርስን ጉዳት አስቀድማ ለመከላከል በውሃና ሚትዮሮሎጂ አገልግሎት አማካኝነት  "አስተማማኝ የውሃና የአየር ንብረት መረጃ ስርዓት መዘርጋት አለባት" ነው ያሉት።

በአህጉሪቷ እያደገ የመጣው የህዝብ ቁጥርና የከተሞች መስፋፋት በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።

በፎረሙ ላይ የተገኙት የውሃ መስኖና ኤለትሪክ ሚንስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤  በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰት ጉዳት አፍሪካ እያስመዘገበችው ያለውን የኢኮኖሚ እድገት እየተፈታተነው ይገኛል።

የአፍሪካ አገሮች በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስን ጉዳት በተቀናጀ መልኩ ለመቆጣጠር መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

ሚንስትሩ ኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራስፎርሜሽን እቅዷ ላይ ለአየር ንብረት ልዩ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ገልፀው፤ በአገሪቷ እየተተገበረ ያለውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በአገሪቷ የተቀናጀና ዘመናዊ የውሃና ሜትሪዮሎጂ መረጃ ስርዓት ለመገንባት በትኩረት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በፎረሙ ከታደሙ 615 ተሳታፊዎች መካከል ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተወከሉ 35 ሚንስትሮች ይገኙበታል።

Published in ፖለቲካ

ነገሌ መስከረም 2/2010 በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመኸር አዝመራ 72 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን እየተሰራ ነው፡፡

በዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት የግብአትና የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤፍሬም ታደሰ እንደገለፁት በምዕራብ ጉጂ  ከነሐሴ አጋማሽ እስከ ጥቅምት አጋማሽ  ድረስ በአካባቢው የዝናብና የአዝመራ ወቅት ነው ፡፡

ለመኸር የአዝመራ ወቅት በአርሶ አደሩ ከተዘጋጀው መሬት ውስጥ እስከ አሁን12 ሺህ ሄክታር መሬት በአምስት ዋና ዋና የሰብል ዘር መሸፈን ተችሏል፡፡

በበልግ አዝመራ ወቅት በዞኑ በተፈጠረ የዝናብ እጥረት ምክንያት ይገኛል ተብሎ ከተጠበቀው  2 ሚሊዮን ኩንታል ምርት 75 በመቶ መቀነሱን ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡

የመኸሩ ዝናብ  ወቅቱን ጠብቆ በመጀመሩ አርሶ አደሩ ፈጥነው የሚደርሱ የቦለቄ ፣ የስንዴ ፣ ጤፍ ፣ አተርና ሽምብራ  ዘር እንዲጠቀም ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዝ 1ሺህ 500 ኩንታል ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ተከፋፍሏል ።

በስራው 124 ሺህ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ሲሆን 1 ሚሊዮን 450 ሺህ  ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል።

በዞኑ የገላና ወረዳ አርሶ አደር ሁጤሳ ቦሩ በሰጡት አስተያየት ለመኸር አዝመራ ያዘጋጁትን ሁለት ሄክታር መሬት በቦሎቄና በሽምብራ ዘር ለመሸፈን እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በበልጉ ወቅት በዝናብ እጥረት ምክንያት በሶስት ሄክታር መሬት ላይ የዘሩት የጤፍ ፣ የስንዴና የበቆሎ ሰብል ምርት ሳይሰጥ በመጥፋቱ  በአሁኑ አዝመራ ላይ ተስፋ መጣላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር ሂርባየ ሁዴሳ በበኩላቸው በበልግ አዝመራ በዝናብ እጥረት ምርት ሳይሰጥ የቀረውን የበቆሎ ሰብል  በሽምብራ ዘር ለመሸፈን መሬታቸውን ገልብጠው ለማረስ እንደተዘጋጁ ገልጸዋል፡፡ 

"በአካባቢያቸው የተመደበው የልማት ጣቢያ ሰራተኛ የዝናብ እጥረትን በመቋቋም ፈጥኖ የሚደርሱ የጤፍ ፣ የስንዴና የቦለቄ ዝሪያዎች  እንድንጠቀም እያስተማረን ነው "ብለዋል፡፡

በዞኑ በ2009/2010 የምርት ወቅት ለማልማት የታቀደው የእርሻ መሬት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ15 ሺህ ሄክታር   ብልጫ እንዳለው የዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ደብረ ብርሃን መስከረም 2/2010 በሀገሪቱ የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታዎች ተጠናከረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የጸጥታ አካላት ገለጹ።   

በደብረ ብርሀን ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የዞኑ ፀጥታ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባኤ የላቀ አፈጻጸም ላበረከቱ ወረዳዎች የማበረታቻ ሽልማት በመስጠት ተጠናቋል።

ከምክር ቤቱ ተሳታፊዎች መካከል የአሳግርት ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ንጉስ ተስፋ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት አሥር ዓመታት በሀገሪቱ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ሥራዎች በመከናወናቸው በዘርፈ ብዙ እድገቶች ተመዝግበዋል።

እነዚህ እድገቶችና ለውጦች በቀጣይም ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

ኢንስፔክተር ንጉስ አንዳሉት፣ በወረዳቸው በየዓመቱ እስከ 16 የሚደርሱ በቂም በቀል፣ በመሬት ይገባኛል፣ በስካርና በመሳሰሉት ምክንያቶች ይከሰቱ የነበሩ የነፍስ ግድያ ወንጀሎችን የግጭት አስወጋጅ ኮሚቴ ተዋቅሮ በመሰራቱ እንዲቆም ማድረግ የተቻለበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ እንስፔክተር ምንውየለት ጭንቅሎ በበኩላቸው በ2009 በጀት ዓመት ከማህበረሰቡ ጋር በተደረሰ የጋራ ስምምነት ወንጀልን አስቀድሞ በመከላከል በኩል አመርቂ ሥራዎች ተሰርተዋል።

በዞኑ የተመዘገበው ሰላምና መረጋጋት የኢንቨስትመንት ፍሰቱና የንግድ እንቅስቃሴው እየተስፋፋ እንዲመጣ በማድረጉ በተያዘው ዓመት ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝቡን ሰላም ለማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በብቃት አንደሚወጡ  አስታውቀዋል።

የዞኑ ፀጥታና አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድአፍራሽ አባተ በበኩላቸው እንደገለጹት በዞኑ 439 ቀበሌዎች የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጸጥታ ኃይሉ እንቅስቃሴ ላይ ማህበረሰቡ ያበረከተው አስተዋጽኦ በዘርፉ አመርቂ ውጤት እንዲመጣ ማድረጉን አመልክተዋል።

በተጀመረው የ2010 በጀት ዓመትም ከአጎራባች ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ሰላም ለማረጋገጥና ልማቱን ለማፋጠን እንደሚሰራም አቶ ወንድአፍራሽ አመልክተዋል።

የዞኑ ፀጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢና የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ የሺጥላ በ2009 ዓ.ም የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ወረዳዎች ሽልማት ሰጥተዋል።

የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር ለህገመንግስቱ የበላይነትና ለህዝብ የሚቆም ፖሊስ ለመገንባት የተጀመረው ጥረትም ተጠናክሮ አንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች በተለያዩ ደረጃ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቶች መኖራቸውን ገለጸው፣ የውጪና የሀገር ውስጥ  ባለሀብቶች ወደአካባቢው መጥተው ቢያለሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሚኒሻ፣ ከፖሊስ፣ ከፀጥታና አስተዳደር የላቀ የሥራ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ወረዳዎች የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን