አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Sunday, 10 September 2017

ደብረ ማርቆስ ጳጉሜ5/2009 በምስራቅ ጎጃም ዞን ጠቃሚ ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ በኩል ውስንነት እንዳለ ተመለከተ፡፡ 

ነባሩ የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ የልጃገረዶች ባህላዊ ክንዋኔ  በዞን ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በደብረማርቆስ ከተማ በንጉስ ተክለሀይማኖት አደባባይ ትናንት ተከብሯል።

የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ውድ አለም አልማው በበዓሉ አከባበር ስነስርዓት ወቅት  እንደገለፁት በዞኑ  በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ቢኖሩም ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ከማስተላለፍ ረገድ ውስንነት አለ።

ለዚህም ማሳያው ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ ባህል እየተረሳ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

ቀደም ሲል በወጣቱ ዘንድ በዞኑ በድምቀት ይከበር የነበረው ይሄው ክንዋኔ በጥቂት የገጠር ቀበሌዎች ብቻ ተወሰኖ መቆየቱን አስታውሰዋል ።

እነዚህና ሌሎችም አኩሪ  ባህላዊ እሴቶች  በመጠበቅና በመንከባከብ ለትውልድ ማስተላለፍ ይገባል፤ለቱሪዝም ልማት በማዋል ከሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባለፈ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ፋይዳ እንደሚኖራቸውም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

"የእንግጫ ለቀማና የከሴ አጨዳ ክዋኔዎች እስከ መስከረም አንድ ድረስ ጎረምሶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው ልዩ ልዩ ዘፈኖችን በመዝፈን በየቤቱ እየተተዘዋወሩ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልክት የሚያስተላልፉባቸው ናቸው" ብለዋል ።

መጪው ዘመን የእድገት ፣የብልጽግናና የሰላም እንዲሆን ምኞት የሚገለፁባቸውም ነው።

እንደ ወይዘሮ ውድ አለም ገለፃ እንግጫ ለቀማ በወንድ ወጣቶች የሚከወን ሲሆን ከሴ ደግሞ በልጃገረዶች ታጭዶ ከአደይ አበባ ጋር አብሮ ተጎንጉኖ በጭፈራ ታጅቦ ለህብረተሰቡ የሚሰጥበት ክንዋኔ ነው።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው በዚህ  በዓል ስምንት ወረዳዎች ባህላዊ እሴታቸውን ያቀረቡ ሲሆን በቀጣይ ዓመት  ሁሉንም የዞኑ አካባቢዎች በማሳተፍ ይከናወናል ተብሏል።

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም  ቢሮ ምክትል ኃላፊና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ልኡል ዮሐንስ  በበኩላቸው ባህል ለገጽታ ግንባታ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ተጠብቆ ለትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

"እንደ ከሴና እንግጫ የመሳሰሉ ማህበራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ማልማት የዞኑም ሆነ የክልሉ ተግባር ስለሆነ ክልሉም የራሱን ተልኮ ወስዶ የበኩሉን ይወጣል " ብለዋል።

ከተሳታፊዎች  መካከል የእነማይ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ሰርካለም በላይ በሰጠችው አሰተያየት የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ የልጃገረዶች ባህላዊ ክንዋኔ በገጠር የጎላ ባይሆንም አንዳንዴ  የሚከበሩበት ጊዜ እንዳለ ገልጻለች፡፡ 

አሁን ትኩረት ተሰጥቶት በዞን ደረጃ በይፋ መከበሩ ተገቢ መሆኑን ወጣት ሰርካለም ጠቅሳለች፡፡

በጎዛምን ወረዳ የፈንደቃ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሁነኛው ምህረት በበኩላቸው "ይህን የቅርብ ጊዜ ባህላችን እንደተረት እናወራው ነበር፤ አሁን ግን ተረት መሆኑ ቀርቶ ተመልሶ ልጆቻችን እንዲያከብሩት መደረጉ  ተደስቻለሁ " ብለዋል ።

 

 

Published in ማህበራዊ

ማይጨው/አዲስአበባ ጳጉሜ 5/2009 የኢትዮጵያ ቀን በመላው አገሪቱ ዛሬ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት እየተከበረ ነው።

በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ዕለት የኢትዮጵያ ቀን እንዲከበር መንግስት በወሰነው መሰረት በዓሉ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሲከበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ለመላው የአገሪቱ ሕዝብ የመልካም ምኞት መግለጫ ያስተላልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

"መጪው ዘመን የኢትዮጵያ ከፍታ ነው " በሚል መሪ ቃል የኢትዮጵያ ቀን ዛሬ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲከበር በመዲናዋ ዝግጅት ላይ ደግሞ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትን ጨምሮ ተጋባዥ  እንግዶች ይታደሙበታል።

በዓሉ በማይጨው ሲከበር ወጣቱ አባቶች ያስረከቡትን ሀገር በመጠበቅ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን  ማጠናከር እንዳለበት የከተማዋ ነዋሪዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ዛሬ እየተከበረ ያለው የኢትዮጵያ ቀን ምክንያት በማድረግ ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንደገለፁት ወጣቱ ትውልድ ከጥንት አባቶቹ የወረሰውን ሉአላዊ ሀገር ጠብቆ የማቆየት ሀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ።

የከተማው ነዋሪ አቶ አበበ ጓንጉል እንዳሉት ከጥንት ጀምሮ  ጀግኖች አባቶች  ወራሪዎችን  በመመከት ለሀገሪቱ ሉአላዊነት መከበር የከፈሉት መስዋዕትነት የማይረሳና ታሪክ የማይሽረው ነው።

ኢትዮጵያ  ከራሷዋ ድንበር ማስከበር አልፋ እንደ ኮሪያ፣ ሩዋንዳና ደቡብ ሱዳን በመሳሰሉ ሀገራት በሰላም ማስከበር ላይ በመሳተፍ  አለም አቀፍ  ተልዕኮዋን እንደተወጣችም አውሰተዋል ።

"ኢትዮጵያ  ከድርቡሽና ከዶግዓሊ ጦርነት ጀምሮ በተከታታይ የተካሄዱ ወረራዎችን በልጆቿዋ ተጋድሎ መክታ ነፃንቷን ያስከበረች ሀገር ናት" ብለዋል ።

የአሁኑ ትውልድ የአስተሳሰብ ልዩነት ቢኖረውም የሀገሩን ሉዓላዊነት በመጠበቅ  ከአባቶቹ  የወረሰውን አደራ ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታላቅ ተጋድሎ ወራሪዎችን በማሳፈር ነፃነቷን ያስከበረች ሀገር መሆኗን የተናገሩት ደግሞ  ሌላው ነዋሪ መምህር በርሄ በላይ ናቸው። 

"ሀገራችን በንጉሰ ነገስቱ ጊዜ በኮንጎ የሰላም ማስከበርና በደርግ ዘመነ መንግስትም ቢሆን ለዝምባቤ  ነፃነት መከበር የከፈለችው ዋጋ  የልጆችዋ  የጀግንነት መስዋዕትነት ውጤት ነው " ብለዋል ።

"ከደርግ ውድቀት በኋላም  የአሁኑ የሃገር መከላከያ ሰራዊታችን የአፍሪካ ህዝቦችን ጠበቃ ለመሆን በቅቷል"  ያሉት መምህር በርሄ ሰራዊቱ  ኢትዮጵያ የአፍሪካ  ህዝቦች የሰላም ማስከበር ግዳጅን በብቃት በመወጣት አለም አቀፍ ዝና እንዲኖራት ማስቻሉን ጠቅሰዋል፡፡

አዲሱ ትውልድም  ምንም እንኳን የፖለቲካ ልዩነት ቢኖረውም  በሀገሪቱ ያለውን የተመቻቸ ሁኔታ ተጠቅሞ  የሀገሩን  አኩሪ ገድልና ታሪክ በጋራ ጠብቆ ማቆየት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል፡፡ 

ወጣቱ የጀግኖች አባቶቹን ታሪክ ጠበቆ በመከባበር ላይ የተመሰረተ አንድነትን  ማጠናከር እንዳለበት ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

 

 

Published in ፖለቲካ
አዲስአበባ ጳጉሜን5/2009የአዲስ ዓመት የበዓል ገበያ በሸቀጦች ሆነ በበግና ዶሮ የአቅርቦት  ችግር አለመታየቱን ሸማቾች እና ነጋዴዎች ገለጹ። 
 
የዘመን መለወጫ በዓል ገበያ በመዲናዋ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች  ተሟሙቆ በዋዜማው ውሏል። 
 
በአዲስ አበባ ባሉ እንዳንድ የንግድ ስፍራዎች የኢዜአ  ሪፖርተር የበዓል ገበያውን ቅኝት እንደሚያመለክተው  ሴት ዶሮ ከ150 እስከ 250 ብር፣ ወንድ ዶሮ ከ300 እስከ 500 ብር ሲገበያይ  ውሏል።እንዲሁም በግ ከ1 ሺህ 700 ጀምሮ እስከ 6 ሺህ ብር ተሸጧል። 
 
አስተያየታቸውን ሊኢዜአ የሰጡት ነጋዴዎችና ሸማቾች አንደተናገሩት የበዓል ገበያው በአቅርቦት ረገድ ምንም አይነት እጥረት የለበትም።