አርዕስተ ዜና
Items filtered by date: Friday, 01 September 2017

ወልዲያ  ነሀሴ 26/2009 በሰሜን ወሎ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመስኖ ልማት የሚውሉ 36 የውሃ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኑ።

 የዞኑ ግብርና መምሪያ እንዳስታወቀው ተጠናቀው ለአገልግሎት ዝግጁ  የሆኑት የውሃ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቶች አንድ ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት በመስኖ ማልማት የሚችሉ ናቸው፡፡

 በመምሪያው የአነስተኛ መስኖ ግንባታና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አልይ አራጋው እንደገለጹት፣ የተገነቡት ፕሮጀክቶች 70 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው ሲሆኑ በመጪው የበጋ ወራት ለመስኖ ልማት ሥራ ይውላሉ።

 ፕሮጀክቶቹ 18 አነስተኛ ግድቦችና 18 የወንዝ ጠለፋ ሥራዎች ሲሆኑ በዝናብ አጠር አካበቢዎች ያለውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ተብሏል።

 ከአንድ ኪሎ ሜትር ተኩል በላይ ርዝመት ያላቸው የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮችና የእንስሳት ማጠጫ ገንዳዎችም በፕሮጀክቶቹ የተካተቱ መሆናቸውንም  አስገንዝበዋል።

 አቶ አልይ እንዳሉት፣ ፕሮጀክቶቹ 20ሺህ 381 አባውራዎችን በሰብል ልማትና በእንስሳት መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

 የውሃ ማሰባሰቡ ዓላማ ዞኑ ዝናብ አጠር በመሆኑ የመስኖ አማራጭ በመፍጠር ገበሬው በዓመት ሦስት ጊዜ በማምረት ትርፍ ምርቱን ለገበያ እንዲያቀርብ መርዳት መሆኑን ገልጸዋል።

 ከእዚህ በተጨማሪ በዞኑ ብዙ እንስሳት በውሃና በመኖ እጥረት በየጊዜው ስለሚሞቱ እነዚህን ችግሮች የማቃለል ዓላማ እንዳለው አቶ አልይ ተናግረዋል፡፡

 የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት ውሃ የያዙ በመሆናቸው የአትክልትና ፍራፍሬ፣ መስኖ ውሃ አጠቃቀም የሥራ ሂደት በቅርቡ ተረክቦ ልማቱን እንደሚያስቀጥል አያይዘው ተናግረዋል፡፡

 በጉባላፍቶ ወረዳ ቀበሌ 15 የግብርና ተጠሪ አቶ ባየ አየነ በበኩላቸው እንዳሉት ፣ በቀበሌው የግንቦራ ወንዝን በመጥለፍ የተከናወነው ፕሮጀክት በመጭው ዓመት 112 ሄክታር መሬት በማልማት 270 ገበሬዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

 ሕብረተሰቡ ለልማቱ በጥሬ ገንዘብ 146ሺህ 800 ብር ማዋጣቱንም አመልክተዋል፡፡

 የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አሰፌ ፈለቀ በሰጡት አስተያየት መስኖው በመገንባቱ ያላቸውን አንድ ሄክታር መሬት በመጪው ዓመት በድንች፣ በካሮት፣ በበቆሎ፣ ስንዴና ሌሎች ሰብሎች ለማልማት ማቀዳቸውንም ተናግረዋል።

 አርሶአደር አሰፌ እንዳሉት፣ በግንባታው ወቅት የአካባቢው ነዋሪ ከጉልበት በተጨማሪ በነፍስ ወከፍ እስከ 200 ብር አዋጥቷል፡፡

 በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 10 ነዋሪ አርሶአደር ወዳጁ ተሾመ በበኩላቸው ዘንድሮ በተሰራው የወንዝ ጠለፋ ሥራ ከእዚህ በፊት ከሚያለሙት መሬት ተጨማሪ አንድ ሄክታር በመስኖ ለማልማት እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል።

 አካባቢው የበልግ ሰብል አምራች ጭምር በመሆኑ በውሃ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክቱ ያላቸውን ሁለት ጥማድ መሬት በመስኖ ለማልማት ተስፋ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ መኮንን ማሪሁን የተባሉ ሌላው አርሶአደር ናቸው።

 በዞኑ በ2009 በጀት ዓመት የበጋ ወቅት 56 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለምቶ ከ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ደሴ ነሃሴ 26/2009 የደሴ ከተማ አስተዳደር ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች  1ሺህ 394 መኖሪያ ቤቶችን መገንባቱን አስታወቀ፡፡

ከተማ አስተዳደሩና ህዝቡ ቤቶቹን ለመገንባት፣ በቁሳቁስ አቅርቦትና በጉልበት 30 ሚሊዮን ብር የሚገመት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የቤቶችና ገበያ ማደራጃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሉጌታ አመዴ እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተገነቡት እነዚህ መኖሪያ ቤቶች በከተማዋ ስር ባሉ አስሩ ክፍለ ከተሞች አማካኝነት ነው።

አንድ ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ ከእቅድ በላይ መገንባቱን አመልክተው ኅብረተሰቡን በማንቀሳቀስና በፈቃደኝነት በስራው ላይ ማሳተፍ በመቻሉ የተሳካ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በነፃ ለማከፋፋል ከተገነቡት  ቤቶች  ውስጥ 703 መኖሪያ ቤቶችን ከ3ሺህ በላይ የቤተሰብ አባላት ላላቸው አባወራና እማወራዎች  ማስረከባቸውንና  ቀሪዎቹንም በተመሳሳይ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተመልክቷል፡፡

ቤቶቹን ለማስረክብም በጥናት ለተለዩ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ለሚገኝባቸው ወገኖች ፣ ለአካል ጉዳተኞችና ጧሪ ለሌላቸው አረጋዊያን ቅድሚያ የተሰጣቸው መሆኑን አስተባባሪው አስታውቀዋል።

የ80 ዓመት የእድሜ ባለጸጋዋ ወይዘሮ ወርቄ አስፋው በሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ቢለን ጊዮርጊስ አካባቢ በተገነባው  መኖሪያ ቤት ተረክበው መኖር ጀምረዋል።

የድሃ ድሃ በመሆናቸው ከሃያ ዓመታት በላይ በረንዳ ላይ መኖራቸውን አውስተው ከተማ አስተዳደሩ ቤት ሰርቶ በነጻ በመስጠቱ በጎዳና ላይ በዝናብና ፀሀይ መፈራረቅ ይደርስባቸው ከነበረው ስቃይ መላቀቃቸውን ተናግረዋል።

የሆጤ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ  አገሪቱ ብርሃኑ ደግሞ ከ28 ዓመታት በላይ የግለሰቦች ቤት ተከራይተው እስከ 500 ብር በየወሩ ይከፍሉ እንደነበር አስታወሰዋል፡፡

እሳቸውና ባለቤታቸው በቀን ስራ በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ሶስት ልጆቻቸውን ለማስተዳደር ይቸገሩ እንደ ነበር ጠቁመው መንግሥት በገነባው መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌላዋ የሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ነዋሪና የኤች አይቪ ቫይረስ በደሟ የሚገኝባቸው ወይዘሮ መዲና ይመር በበኩላቸው ከ20 ዓመታት በላይ በቀን ስራ ተቀጥረው ከሚያገኙት ገቢ 300 ብር በየወሩ በመክፈል ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ይቸገሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

" አሁን ግን የከተማ አስተዳደሩ ቤት ሰርቶ ስለሰጠኝ ለቤት ኪራይ የማወጣውን ለቤተሰቦቼ ቀለብ ማዋል ችያለሁ" ብለዋል፡፡     

በሰኞ ገበያ ክፍለ ከተማ ነዋሪና  ዓይነ ስውር የሆኑት አስር አለቃ መሐመድ  ሰይድ በግላቸው ከ80ሺህ ብር በላይ በማውጣት አምስት መኖሪያ ቤቶችን በማስገንባት አርአያነታቸውን ያሳዩ ግለሰብ ናቸው።

ተጨማሪ 10ሺህ ብር ገንዘብ ለከተማ አስተዳደሩ በመለገስ የተሻለ ገቢና አቅም ያላቸው ግለሰቦች ወገኖቻቸውን በማገዝና የመደጋገፍ ባህልን እንዲያጎለብቱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ከ2004 በጀት ዓመት ጀምሮ ባስገነባቸው ቤቶች 5ሺህ 383 ቤተሰቦችን የቤት ባለቤት ማድረጉ ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደተመለከተው መኖሪያ ቤቶቹን ገንብቶ ማስረከቡ ምስጉን ተግባር ሆኖ አንዳንዶቹ አካባቢዎች የመጸዳጃ ቤቶች የሌላቸው በመሆኑ ነዋሪዎች መቸገራቸውን አረጋግጧል።

የከተማ አስተዳደሩ ስለጉዳዩ ተጠይቆ በሰጠው ምላሸ  ችግሩን በመገንዘብ የጋራ መጸዳጃ ቤቶች ለማስገንባት ከመንግስትና ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጋምቤላ  ነሀሴ 26/2009 የጋምቤላ ህዝቦች  ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ምክር ቤት  አፈ ጉባኤ አቶ ታኬት አስፋው ድንገተኛ ሞት የተሰማው ጥልቅ ሀዘን ገለጸ፡፡

 የክልሉ መንግስት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው አቶ ታኬት አስፋው ክልሉ ካፈራቸው ታላላቅ የህዝብ ልጆች አንዱና በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና  ህዝቦች መብት መከበር የድርሻቸውን የተወጡ አመራር ነበሩ ።

 አቶ ታኬት አስፋው በህይወት ዘመናቸው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች የሰሩ በተለይም በአራተኛው ምርጫ ዘመን የክልሉን ህዝብ በመወከል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገመንግስታዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

 ከሐምሌ ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ  ህይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የክልሉ መንግስት ምክርቤት ዋና አፈ  ጉባኤ ሆነው  ሲያገለግሉ ቆይተዋል ።

 አቶ ታኬት አስፋው በስነምግባራቸው ምስጉንና የተጣለባቸውን ሃላፊነት ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመግባባት የመፈጸም ባህሪ ያላቸውና ፣ በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን እውቀታቸውን ለህዝብ ጥቅም ለማዋል ሲሰሩ የነበሩ አመራር ነበሩ።

 የክልሉ መንግስት  በመግለጫው እንዳመለከተው አቶ ታኬት የመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች  እንዲፈፀሙና የህዝብ ተጠቃሚነት  እንዲረጋገጥ በሙሉ አቅማቸው ሲታገሉ ያለፉ ታታሪና የክልሉ ህዝብ መቸውንም ጊዜ የማይዘነጋቸው ናቸው።

 በህይወት ዘመናቸው ባከበቱት እውቀትና ችሎታ ከሌሎች የክልሉ አመራሮች ጋር በመሆን የክልሉ ልማት እንዲፋጠን ከሚመዘገበውም ውጤት የህዝቦች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡

 አቶ ታኬት አሁን ከሚመሩት ህዝብና የትግል አጋሮቻቸው በህይወት ቢለዩም  ምስጉን ስራቸውና ራእያቸው መቼውንም ጊዜ የማይረሳና  በተተኪ አመራሮች  የሚፈፀም መሆኑን የክልሉ ህዝብና መንግስት ቃል ይገባሉ ብሏል በመግለጫው፡፡

 የጋምቤላ ህዝቦች  ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአቶ ታኬት አስፋው  ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን በመግለጽ ለቤተሰቦች፣ ለወዳጆችና  ለትግል አጋሮች መጽናናትን ተመኝቷል፡፡

 አቶ ታኬት አስፋው ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጅማ ነሃሴ 26/2009 በጅማ ዞን በወጣቶች የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ10  ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የልማት ስራዎች ተከናወኑ፡፡

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳሁን ጆቢር ለኢዜአ እንደገለጹት የልማት ስራዎቹ የተከናወኑት በ523 ሺህ 502 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት ነው ።

ከተከናወኑት ስራዎች መካከል  የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ጥገና፣ የአነስተኛ ድልድዮች ግንባታ፣የአካባቢ ፅዳትና ውበት ፣በሽታና የትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ይገኙበታል።

በዚህም 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚሆኑ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሆኑ ነው አቶ ካሳሁን  የተናገሩት፡፡

በዞኑ ጉማይ ወረዳ የቶባ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ኑሪያ አማን በሰጡት አስተያየት በደካማ አቅማቸው ለሚኖሩበት ቤት በወር 150 ብር ኪራይ ይከፍሉ እንደነበር ተናግረዋል።

"ወጣቶቹ ገንዘብና ጉልበታቸውን በማስተባበር  የመኖሪያ ቤት ሰርተው ስላሰረከቡኝ ችግሬ ተቃሎልኛል " ብለዋል ።

"ወጣቶቹ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ድልድይ ተሰርተው ለህብረተሰቡ አስረክበዋል" ያሉት ደግሞ በሊሙ ኳሳ ወረዳ የመንደራ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሱልጣን አባዋሪ ናቸው፡፡

በጉማይ ወረዳ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሰማራው ወጣት ተመስገን ጤናዬ በበኩሉ ደም በመለገስና የአቅመ ደካሞችን  ቤት በመስራት የክረምት ወራት በማሳለፉ   የህሊና እርካታ እንደሰጠው ተናግሯል፡፡

ወደፊትም ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው ወጣት ተመስገን ያመለከተው።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ 26/2009 "የሀገራችን ህዝቦች የዘር የሃይማኖትና የብሄር ልዩነትን በማክበር ፍቅርን በማጎልበት የተጀመሩ ሀገራዊ ዕቅዶችን ማሳካት ይቻላል" ባለስልጣናትና የሃይማኖት አባቶች ተናገሩ።

አዲሱን ዓመት በማስመልከት ለ10 ተከታታይ ቀናት ከሚደረጉ ሁነቶች የመጀመሪያው የፍቅር ቀን ክብረ በዓል የተለያዩ የሃይማኖትና የመንግስት ተቋማትን እንኳን አደረሳችሁ በማለት ተጀምሯል።

በዚሁ ወቅት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የተላለፈላቸው የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ ሚኒስትሮች ኢትዮጵያውያን ለብዙ ጊዜያት ይዘውት የቆዩት ፍቅር በአገር ደረጃ በማክበር በዘር በሃይማኖትና በቋንቋ ያለውን ልዩነት የሚያስቀር ነው።

አንድ አገራዊ ስሜት እንዲኖርም በር ይከፍታል ብለዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንዳሉት የሰው ልጅ ህይወት ቀጣይነትና ትርጉም የሚኖረው በመካከላቸን ፍቅር ነግሶ ሲታይ ነው።

ሰው በሌሎች ልዩነቶች ሳይከለል ሰብአዊነትን መሰረት ያደረገ ፍቅርን ለሁሉም ወገኑ መስጠት እንደሚገባውም ነው የገለፁት።

የአረፋን በዓል በማክበር ላይ የሚገኙት የእስልምና ሃይማኖት አባቶች ፍቅር ከፈጣሪ ጀምሮ ለሁሉም የሰው ዘር ሊሰጥ የሚገባ መሆኑን ጠቅሰው በፍቅር መሰጣጣት አገራዊ ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ተወካይ ሀጂ ከድር ሁሴን የፍቅር ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ መከበሩ ዜጎች ህዝባቸውን እንዲወዱና ፍቅርን እንዲረዱ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ዜጋው ሁሉ ከአንዲት ኢትዮጵያ ውጪ ሌላ አገር ስለሌለው አገሩን ሊያፈቅር ይገባልም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቀኑ ከሙስሊሙ የአረፋ በዓል እለት ጋር መገጣጠሙም ታሪካዊ አድርጎታል ብለዋል።

የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የተላለፈላቸው የትምህርት፣ የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች፣ የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትሮችና የፍቅር ቀን በመከበሩ ህዝቡን ለመከባበር የሚያስችልና የተጀመረውን ልማት በህብረት አጠናክሮ ለማስቀጠል ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

ከሁለተኛው ሚሊኒየም ማግስት ያለውን 10ኛ ዓመትና አዲስ አመትን ምክንያት በማድረግ የተጀመረው ኩነት እስከ ጳጉሜ አምስት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን ነገ የእናቶችና ህፃናት ኩነት ይደረጋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2009 ኢትዮጵያ ያስቀመጠችው የኢንዱስትሪ ልማት ግብ ይሳካ ዘንድ በሁሉም ዘርፎች የተሰማሩ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎችን መሳብ እንደምትቀጥል ተገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የቻይና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ልዑካንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ምክር ቤቱ በቻይና ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የሚንቀሳቀሱ ትላልቅ ኩባንያዎች በስሩ ያቀፈ መሆኑን ወይይቱን የተከታተሉት በሚኒስትር ደረጃ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ተናግረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገው ውይይት ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ልማት እስካሁን ያደረገችውን እንቅስቃሴ የሚመለከት ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ የቻይና ኩባንያዎች መዋዕለ ንዋያቸውን በአገሪቷ ውስጥ እንዲያፈሱ የተመቻቸ ሁኔታ በመፍጠር ላይ እንደምትገኝም ገልጸዋል።

አምባሳደር ብርሃነ የልዑካን ቡድኑ አባላትም የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አባሎቻቸውን እንደሚያሳምኑ ቃል ገብተዋል ነው ያሉት።

የቻይና የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙንም አምባሳደር ብርሃነ አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች ፕሬዚዳንት ሁዓንግሮንግ ዛንግ በበኩላቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ማዕከል እየሆነች መጥታለች።

በአገሪቷ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ብዛት ያላቸው የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ባለፉት እምስት ዓመታትም ብዛት ያላቸው የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ በተለይ በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ እየሰራ የሚገኘው 'ሁጂያን ግሩፕ' ኩባንያ ብቻ በቀጣይ ለ15 ሺህ ኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የቻይና ኩባንያዎችን ለመሳብ የሚያደርገው እንቅስቃሴና ኢንቨስት እያደረጉ የሚገኙትንም በቅርበት እያገዘ መሆኑ ይበረታታል ብለዋል።

የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከመንገድ መሠረተ ልማት ጀምሮ እስከ ማምረቻ ኢንዱስትሪ ድረስ በስፋት ገብተው እየሰሩ መሆናቸው ይታወቃል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ጅግጅጋ ነሐሴ26 /2009 መጪው አዲስ ዓመት ድህነትንና ኋላቀርነትን በጋራ ለመዋጋት የተጀመረውን ጥረት የምናጠናክርበት ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ገለጹ።

በጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ ያሉ የእምነቱ ተከታዮች 1 ሺህ 438ኛ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን በጅግጅጋ ስታድየም በመሰብሰብ በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓት ዛሬ አክብረዋል።

በባዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አብዲ መሀሙድ "
የምንቀበለው አዲስ ዓመትም በሀገሪቱ ድህነትንና ኋላቀርነትን በጋራ ለመዋጋት የተጀመረውን ጥራት ይበልጥ አጠናክረን የምንቀጥልበት ሊሆን ይገባል" ሲሉ ገልጸዋል።

በክልሉ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ ሙስሌሙ ሕብረተሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ያለውን ለም መሬት እና ውሃ በማቀናጀት ከፊል አርብቶአደሮቹ በዘመናዊ የእንስሳት እርባታና የእርሻ ሥራዎች በስፋት እንዲሰማሩ በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አብዲራህማን ሐሰን በበኩላቸው እምነቱ በሚፈቅደው መሰረት ህዝበ ሙስሊሙ አቅመ ደካማ የሆኑና ወላጆቻቸውን ያጡ ህጻናትን በማብላት በዓሉን በጋራ ሊያከብር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከበዓሉ ላይ ከተገኙት የእምነቱ ተከታዮች መካከል አቶ ሀቢብ መሀመድ "በዓሉ ቤተሰብ የሚጠያይቅበት እና ዝምድና የሚናጠናክርበት በመሆኑ በብሔራዊ ደረጃ ከተከበረው የፍቅር ቀን ጋር መገጣጠሙ ልዩ ደስታ ፈጥሮብኛል " ብለዋል፡፡

"የኢድ አል አድሃ በዓልን ስናከብር በተለያዩ ምክንያቶች በሕመም ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመጠየቅና እርስበርስ የመረዳዳት ባህልን በሚያጠናክር መልኩ መሆን አለበት" ያሉት ደግሞ አቶ ኢድ ሀጂ አቢብ ናቸው፡፡

እርሳቸውም በዓሉን ከሌሎች ጋር ተሰባስበው በፍቅርና በደስታ እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አቶ ሙስጠፊ ዩሱፍ የጅግጅጋ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ምክንያቶች ወላጆቻቸውን ያጡ ሕጻናት የደስታቸው ተካፋይ እንዲሆኑ በጋር ሆነው እያከበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአረፋ በዓልና የፍቅር ቀን በአንድ ቀን መከበሩ እርስ በእርስ የመተሳሰብ ባህል እየጎለበተ እንዲመጣ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተንግረዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2009 የመንግሥትን ንብረት በመመዝበር የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሥራ ኃላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የፀረ-ሙስና እርምጃው በክልሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ላይም በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል መንግሥት አስታውቋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሶስቱ በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ደረጃ የነበሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ የመምሪያና የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ የድርጅቱ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ደሳለኝ ገብረሕይወት፣ የኮርፖሬት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሲሳይ አባፈርዳ፣ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ፣ የፕላንና ቢዝነስ ዴቬሎፕመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሲራጅ አብዱላሂና የድርጅቱ የፋይናንስ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መላኩ ናቸው።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ እርምጃው መንግሥት በሙስና ላይ የሚወስደው እርምጃ በቁርጠኝነት መቀጠሉን ማሳያ ነው።

የንግዱ ማኅበረሰብም ሆነ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሙስናን አመለካከት እንዲጸየፉ የሚደረግ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የገለጹት ሚኒስትሩ፤ እርምጃውም ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚደረግ ጥረት ነው ብለዋል።

 "በመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት አድርሰዋል" ተብለው የተጠረጠሩበት ዝርዝር ጉዳይ በሂደት እንደሚገለጽም ዶክተር ነገሪ ተናግረዋል።

መንግሥት በሙስና የተጠረጠሩትን ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ከ57 በላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ደላሎችና የግል ባለኃብቶችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።

ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ በፖሊስ ተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ተጠይቆባቸው ጉዳያቸው እየተጣራ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ምርመራቸው ተጠናቆ መዝገባቸው ለአቃቤ ሕግ ተላልፏል።

Published in ማህበራዊ

አዲስአበባ ነሐሴ26 /2009 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ በተፈፀመ የሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 57 የሚሆኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሙያተኞችና ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ፡፡

የፖሊስ ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው የሚገኙ መሆናቸውን ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም ከአስተዳደሩ ዋና ኦዲተር፣ከህዝብ በተገኘ መረጃና ፖሊስ በስፋት ባከናወነው የማስረጃ ማሰባሰብና የምርመራ ስራ መሆኑ ተጠቅሷል።

ከነዚህ አካላት በተገኘው መረጃ በሙስና ወንጀሉ በመጠርጠራቸው በፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ መሠረት መያዛቸውንና ምርመራው የቀጠለ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

ህዝቡም ለፀረ ሙስና ትግሉ መሳካት እያደረገ ያለውን ድጋፍ ኮሚሽኑ አድንቆ በማናቸውም መንገድ መረጃ ማቅረብ እንደሚችል በመግለጫው አብራርቷል።

Published in ማህበራዊ

ሰመራ 26/2009 የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት የእርስ በርስ ግንኙነትንና ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር የጎላ ሚና እንዳለው የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

በፌዴሬሽኑ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ትናንት በአፋር ክልል ሰመራ አካባቢ የጽዳት ስራና ችግኝ ተከላ ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ወጣት ታረቀኝ አብዱልጀባር እንደገለጸው በጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለፉት አስር ዓመታት በክረምትና በበጋ ወጣቱ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ዘንድሮም ከ10 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሰማራታቸውን የጠቀሰው ፕሬዝዳንቱ ይህም ወጣቱ በአካባቢው ሳይወሰን ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ ጭምር እየሰራ ነው፡፡

ወጣቱ በተለይ በተያዘው ዓመት ያከናወነው በጎ ተግባር አንድ እርምጃ ወደፊት ማራመድ ያስቻለ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

በዚህም ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ከ100 በላይ ወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት በኦሮሚያ አዳማና በአፋር ክልል ደግሞ አዋሽ ሰባት ኪሎ አካባቢ ፣ አሚበራና ገዋኔ ወረዳዎች እንዲሁም ሰመራ የተለያዩ የጽዳት ስራና ችግኝ ተከላ አከናውነዋል፡፡

ይህም ወጣቶችን በማቀራረብ እርስ በራስ ከማስተዋወቅና ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት የጎላ ሚና እንዳለው ወጣት ታረቀኝ ገልጿል፡፡

የአፋር ክልል ወጣቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ወጣት አሊ ሀሴን በበኩሉ ከአዋሽ ሰባት ኪሎ ጀምሮ በየአካባቢዉ የክልሉ ወጣቶች ያሳተፈ የጽዳት ስራና ችግኝ ተከላ በማካሄድ ቀጣይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል መሰረት ከመጣል አንጻር አላማው መሳካቱን ተናግሯል፡፡

እንዲሁም 12ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን የሚያስተናግደው የአፋር ክልል ለዝግጅቱ እያከናወናቸው ያሉትን የልማት ስራዎች ለመደገፍ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ምቹ አጋጣሚ መሆኑንም ገልጿል፡፡

የፌዴሬሽኑ አባል ወጣት ፍሬዘር አበራ በሰጠችው አስተያየት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአካባቢ አልፎ ወደተለያዩ ክልሎች ድረስ ዘልቆ በመግባት የተከናወነው የልማት ስራ ወጣቱን ያቀራበና አንድነትን እያጠናከረ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወጣት ኡመር መሃመድ በበኩሉ ወጣቶቹ ከአካባቢያቸው አልፈው አፋርን ለማልማት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለክልሉ ወጣቶች መነሳሳትን የፈጠረና ጠቃሚ ተሞክሮ የተለዋወጡበት መሆኑን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አባላት ቡድን የአፋር ክልል 12ኛውን የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ለማስተናገድ እያከናወናቸው ያሉትን የልማት ስራዎችና ዝግጅት ጎብኝተዋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 5

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን