አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 09 August 2017

አዲስ አበባ ነሃሴ 3/2009 የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት የ22 የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ጉዳይን ተመለከተ።

ፍርድ ቤቱ በቅርቡ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ባለሃብቶችና ደላሎች መካከል ጉዳያቸውን ለማየት ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።

በዚህም ዛሬ ማለትም ነሐሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም የተጠረጠሩበት ወንጀል ዝርዝር ጉዳይ እንዲታይ ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጣቸው 42 ተጠርጣሪዎች በልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።

ነገር ግን ከቀረቡት መካከል ጉዳያቸው በሶስት መዝገቦች ስር የተጠቃለሉ 22 ተጠርጣሪዎችን ብቻ ተመልክቷል።

ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀው ፖሊስ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ዝርዝር የምርመራ ውጤት እንዲያቀርብ ችሎቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ፖሊስ ጉዳዩ ከአዲስ አበባ ውጭና ውጭ አገር ድረስ ስለተዘረጋ አሁንም ያላጠናቀቀው ምርመራ እንዳለው ገልጿል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ግለሰብ ላይ የተጣራ መረጃ አለማቅረቡን ተቃውመዋል።

ደንበኞቻቸውም የዋስትና መብት ተሰጥቷቸው ጉዳያቸውን ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ችሎቱን  ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በጠበቆቻቸውና በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙ ችሎቱ ትዕዛዝ ቢሰጥም ከሁለት ቀናት በፊት አንድ ቀን ብቻ መገናኘት እንደቻሉ ገልጸዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ማረሚያ ቤቱ ጠበቆችና ቤተሰብ ለመጠየቅ የራሱ ህገ ደንብ እንዳለው ገልጾ፤ በዚህም መሰረት ጠበቆች በተፈቀደላቸው ሰዓት አለመከልከላቸውን ለፍርድ ቤቱ መልስ ሰጥቷል።

ፖሊስ ያጣራቸው መረጃዎችንና ተጨማሪ ምስክሮችን ማግኘቱን ጠቁሞ ተጠርጣሪዎቹ የሰነድ ማስረጃዎች ይሰውራሉ በሚል ዝርዝር የምርመራ ውጤቱን ከመግለጽ ተቆጥቧል።

ቀሪ የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን ለማጠናቀቅም ተጨማሪ የ14 ቀናት የምርመራ ጊዜ እንዲፈቀድለት ችሎቱን ጠይቋል።

ችሎቱም የቀሪ ተጠረጣሪዎችን ጉዳይ ከተመለከተ በኋላ በነገው ዕለት የተጨማሪ የምርምራ ጊዜ ፈቃድም ሆነና የዋስትና ጥያቄው ውሳኔውን ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በአንደኛ መዝገብ ስር ከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል አቶ ሙሳ መሃመድ፣መስፍን ወርቅነህ፣ዋሲሁን አባተ የቀረቡ ሲሆን በመዝገብ ሁለት  የቀረቡት ደግሞ መስፍን መልካሙ፣ብርጋዴር ጀኔራል ኤፍሬምና ሚ/ር ጁ ዩኪን ናቸው።

ጉዳያቸው በሶስተኛ መዝገብ ከተካተቱት መካከል አቶ እንዳልካቸው ግርማ፣ ወይዘሮ ሰናይት ወርቁና አቶ በለጠ ዘለለው ይገኙበታል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሃሴ3/2009 ኢትዮጵያ በኤርትራ ድንበር የሚገኙ የሜዳ አህዮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ለዓለም አቀፉ ተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን ልታስመዘግብ መሆኑን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኮንቬንሽኑ አባል የሆኑ የአፍሪካ አገራት በህዳር 2010 ዓ.ም በፊሊፒንስ ለሚካሄደው 12ኛው ዓለም አቀፍ የተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን ዝግጅት በአዲስ አበባ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በውይይቱ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣንን የወከሉት አቶ ካህሳይ ገብረ ትንሳኤ ኢትዮጵያ የኮንቬንሽኑ አባል በመሆኗ፤ በድንበሯ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የዱር እንስሳት ተመዝግበው ልዩ ጥበቃ እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በተካሄደው11ኛው ኮንቬንሽን ኢትዮጵያ  በደቡብ ሱዳን ድንበር የሚገኙ የነጭ ጆሮ ቆርኬ ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።

በቀጣይ ዓመት በፊሊፒንስ ለሚካሄደው 12ኛው ዓለም አቀፍ የተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን በኤርትራ ድንበር የሚገኙ የሜዳ አህዮች ልዩ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የምታስመዘግብ መሆኗንም ተናግረዋል።

የዱር እንስሳቱ በኮንሼንሽኑ መመዝገባቸው፣ አገራቱ ለእንስሳቱ ልዩ ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው መሆኑን አቶ ካህሳይ ተናግረዋል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መዓዛ ገብረመድኅን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በ2002 ዓ.ም የኮንቬንሽኑ አባል ከሆነች ጀምሮ ድንበር አቋርጠው ለሚመጡ እንስሳት ጥበቃ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጠና በዱር እንስሳት ስደት በዓለም ሁለተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንስሳቱን ከሕገ-ወጥ አደን ለመከላከል የኮንቬንሽኑን መሠረታዊ መርሆች በማክበር ከአጋር አካላት ጋር ጥበቃ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ሱዳንና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ለሚንቀሳቀሱ ባለ ነጭ ጆሮ ቆርኬ በመጠለያነት እያገለገለ መሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። 

ዛሬ በተጀመረው  ጉባዔ  ከ42 የአፍሪካ አገሮች የመጡ ባለሙያዎችና ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

12ኛው የዓለም አቀፍ ተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን በመጪው ሕዳር መጀመሪያ በፊሊፒንስ ይካሄዳል።

ዓለም አቀፉ ተሰዳጅ የዱር እንስሳት ኮንቬንሽን በአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች ተፈጥሯዊ ምክንያቶች ድንበር አቋርጠው የሚሰደዱ እንስሳት ጥበቃ እንዲደረግላቸው የሚሰራ ተቋም ነው።

 

 

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ነሃሴ3/2009 የአሮሚያ ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ በሙስና የተመዘበረ ሃብት ማስመለሱን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በሕገ-ወጥ መንገድ የተያዘ ከ319 ሺህ ስኩዌር ካሬ ሜትር መሬት በላይ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ያደረገ ሲሆን፤ ተጨማሪ ከ279 ሺህ ስኩዌር ካሬ ሜትር መሬት በላይ በህገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች የተያዘ መሬት እንዲታገድ ማድረጉን አስታውቋል። 

ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሐሚድ ኪኒሶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኮሚሽኑ በክልሉ በሙስና ወንጀሉ የተሳተፉ ከ600 በላይ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁ አድርጓል ነው ያሉት።

በዚህም 145ቱ ከ6 ወር እስከ 13 ዓመት የእስራት እና ከብር አንድ ሺህ እስከ 213 ሺህ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል ብለዋል።

በዚሁ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሙስና ጋር የተያያዙ 80 ተሽከርካሪዎች የተያዙ ሲሆን፣ 45 መኖሪያ ቤቶችም በምርመራ ሂደት ላይ እንደሆኑ ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በሰበታ ከተማ የቀድሞ ምክትል ከንቲባ እና በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ላይ በነበሩት ግለሰቦች የተመዘበረ ከ19 ሚሊዮን ብር በላይ፣ 35 ሄክታር መሬት፣ እንዲሁም የተለያዩ የሕገ-ወጥ ማስረጃዎችን በመጠቀም በመንግሥት ላይ ጉዳት አድርሰዋል ያላቸውን ሰዎች በቁጥጥር ስር አውሏል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የቀድሞው የሰበታ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጎቤን ጨምሮ በተለያዩ ኃላፊነት ላይ የነበሩ መሃንዲሶች፣ ሠራተኞች፣ ደላሎችና ሌሎች በወንጀሉ ላይ የተሳተፉ አካላት ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹ በሰበታ ከተማ በተገነቡት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል፣ ሕገ-ወጥ የመሬት ይዞታን ማረጋገጥ፣ የሐሰት ካርታ የመስጠት ወንጀሎች ነው የተጠረጠሩት።

ካሳ ለማይገባቸው ግለሰቦች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈል፣ የሐሰት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን በማቋቋም ገንዘብ መውሰድና ሌሎች ሕግ-ወጥ ድርጊት በመፈጸማቸውም ነው የተያዙት።

ምክትል ኮሚሽነሩ ከዚህ በፊት በክልሉ በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የግብርና ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ዘላለም ጀማነህን ጨምሮ በሌሎች ተጠርጣሪዎች ላይ የፍርድ ሂደቱ በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል ብለዋል።

በክልሉ በሙስና ወንጀል የተሳተፉ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ሕብረተሰቡም ሙሰኞችን በማጋለጡ ሂደት የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርግ አቶ ሐሚድ ጥሪ አቅርበዋል።  

 

 

Published in ፖለቲካ

ደብረ ማርቆስ ነሃሴ 3/2009 ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጣቸው የማህበረሰብ አገልግሎቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲው በሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን እነማይ ወረዳ የጯሂት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ የሺመቤት ጓሌ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ከዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁራን በተደረገላቸው የህግ አግልግሎት ድጋፍ በእርሻ ማሳቸው ላይ የነበረባቸውን ክስ በአሸናፊነት አጠናቀዋል።

ለአጎታቸው ለአራት ዓመታት አከራይተው ይጠቀሙበት የነበረውን ግማሽ ሄክታር ማሳ አጎታቸው በመመሳጠር የራሱ ይዞታ አድርጎና ደብተር አውጥቶ ሲከራከራቸው መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይሁንና የዩኒቨርሲቲው ምሁራን በነጻ በሰጧቸው የጥብቅና አገልግሎት ተከራክረው መሬታቸው እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

በዞኑ የስናን ወረዳ ጅገት ቀበሌ ነዋሪ አቶ መከተ ስሜነህ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው በተደረገላቸው የህግ ድጋፍ እናታቸው የሞተችባቸውን የልጅ ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ተቆራጭና የውርስ ሀብት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በእዚህም ለመማር የደረሱ ሁለቱን ልጆችን ትምህርት ቤት አስገብተው በማስተማር ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

"በምዘራው የስንዴ ምርጥ ዘር የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ማሳ ድረስ ተገኝተው ሙያዊ እገዛ ስላደረጉልኝ ተጠቃሚ መሆን ችያለሁ" ያሉት ደግሞ በደብረኤሊያስ ወረዳ የገነቴ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር አግደው ጌታቸው ናቸው።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉሴ ምትኩ በበኩላቸው፣  ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራ በተጨማሪ በጥናት ላይ የተመሰረተ የማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በእዚህም በስምንት ወረዳዎች ለሴቶችና ለአቅመ ደካሞች ነጻ የህግ አገልግሎት፣ የስነልቦናና የንግድ ሥራ ማማከር፣ በዘር ብዜት ለሚሳተፉ አርሶአደሮች የባለሙያ ምክርና እገዛ እንዲያገኙ ማድረጉን ተናግረዋል።

ዶክተር ንጉሴ አንዳሉት፣ በተጠናቀቀው የ2009 በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲው በሰጠው የማህበረሰብ አገልግሎት ድጋፍ ከ12 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

ለማህበረሰብ አገልግሎት ድጋፉም ተቋሙ ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ገልጸው፣ በተጀመረው አዲሱ በጀት ዓመትም የአገልግሎት ሥራው የበለጠ ተጠናክሮ አንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዳማ ነሃሴ 3/2009 ኢትዮጵያ በመስኖ ልማት ያስመዘገበችው ውጤት በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በዘርፉ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደምትገኝ አመላካች ነው ተባለ ።

በአዲሱ ዓመት በመስኖ የሚለማውን መሬት በማስፋትና የተሳታፊ አርሶ አደሮችን ቁጥር በማሳደግ 469 ሚሊዮን ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር አስታውቋል ።

በሚኒስቴሩ የአነስተኛ መስኖ ልማት ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ አወል እንደገለፁት በ2009 ዓ.ም በሁለት ዙር በተካሄደው የመስኖ ልማት 370 ሚሊዮን 592 ሺህ 655 ኩንታል ምርት ተገኝቷል ።

ከሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የሆነው የዓመቱ ክንውን በመስኖ የሚለማውን መሬት ከማልማት ፣ የተሳታፊ አርሶአደሮችን ቁጥር ከማሳደግና ከተገኘው ምርት አንፃር ሲገመገም ከ95 በመቶ በላይ  እቅዱን ማሳካት ተችሏል ።

በዓመቱ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በመስኖ የለማ ሲሆን 7ሚሊዮን የሚጠጉ አርሶአደሮች በዘርፉ ተሳታፊና ተጠቃሚ ሆነዋል ።

በአዲሱ ዓመትም በመስኖ የሚለማው መሬት ወደ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሔክታር በማስፋትና  በመስኖ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ቁጥር 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን በማድረስ 469 ሚሊዮን የአትክልትና ፍራፍሬ  ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ በበኩላቸው በዓመቱ በመስኖ ልማት የተገኘው ውጤት በመሰረተ ልማት አውታሮች መስፋፋትና በፈፃሚው ፣ በአምራቹና በተጠቃሚው የአመለካከት ለውጥ የተገኘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የተገኘው ውጤት በዘርፉ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ በዘርፉ የተያዙ ግቦችን ማሳካት እንደሚቻል አመላካች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''ዘርፉ ያልተቀረፉ ተግዳሮቶች አሉት'' ያሉት የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ልዩ ረዳት አቶ ሰለሞን ዳኜ በበኩላቸው ''ኢትዮጵያ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ተጠቃሚ የሚያደርጋት እምቅ ሀብት ቢኖራትም ከአምራቹ ተጠቃሚነትና ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንፃር ሲገመገም ገና በዳዴ ላይ ያለ ነው'' ብለዋል ።

በአትክልት ፣ ፍራፍሬና የስራ ስር ዘር አቅርቦት ፣ በማዳበሪያ አጠቃቀምና በተቀናጀ የእሴት ሰንሰለት ምርቱ ወደ ገበያ በፍጥነት አለመድረስ ዋነኞቹ ችግሮች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

አምራቹ አንዱን ኪሎ ቲማቲም ከ5 ብር ባልበለጠ ዋጋ እየሸጠ በመሀል ያሉ ሃይሎች ግን አንዱን ኪሎ አዲስ አበባ ላይ 23 ብር በመሸጥ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም የሚያገኙበት የተበላሸ የግብይት ስርዓት መኖሩን አስረድተዋል ።

የሆርቲካልቸር ምርት በብዛትና በጥራት በማምረት ከራሳችን ተርፈን የውጪ ገበያውን መቆጣጠር የምንችልበት እድል እያለን የተቀነባበረና ያልተቀነባበረ የአትክልት ምርት ከውጭ በማስገባት በ2008 ዓ.ም ብቻ 15 ነጥብ 5 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ከውጭ ከሚገባው የተቀነባበረና ያልተቀነባበረ የአትክልት ምርት ቀይ ሽንኩርት ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዝ በተጠቀሰው ዓመት ከሱዳን ብቻ 77 ሺህ 432 ቶን ምርት ወደ አገራችን መግባቱን ገልፀዋል።

በዘርፉ የሚታዩትን ተግዳሮቶች በሙሉ በመፍታት ከዘርፉ ማግኘት ያለብንን ጥቅም ለማስከበር ለመጪዎቹ አስር ዓመታት ስራ ላይ የሚውል የሆርቲካልቸር ልማት ስትራተጂ መዘጋጀቱን ልዩ አማካሪው ተናግረዋል ።

ስትራተጂው ከ10 ዓመታት በኋላ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ፣ በዓለም ገበያ ብቁና ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ማቅረብ ፣ ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥርና ለምግብና ስነምግብ ዋስትና መረጋገጥ የላቀ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችልና ከቀዳሚ አምራችና ላኪ የአፍሪካ አገራት መካከል ተወዳዳሪ የሆነ የሆርቲካልቸር ዘርፍ የመገንባት ራእይ የያዘ ነው ተብሏል ።

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር በ2009 ዓ.ም በአፈር ለምነት ፣ በመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃና በአነስተኛ መስኖ ልማት የተከናወኑ ስራዎች ለመገምገምና በ2010 ዓ.ም እቅድ ላይ ለመምከር በአዳማ ከተማ ከባለድርሻ አካላት በመወያየት ላይ ነው ።

 

Published in ኢኮኖሚ

ወልዲያ ነሃሴ 3/2009 በሰሜን ወሎ ዞን 283ሺ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው የተለያዩ የልማት ስራዎች በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መመሪያ የወጣት ማደራጃና ክትትል የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወርቁ ተፈራ እንደገለፁት በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩት ወጣቶች መካከል 12 ሺህ ያህሉ የዩኒቨርስቲና የኮሌጅ ተማሪዎች ናቸው፡፡

ወጣቶቹ በአሁኑ ወቅት ከ3ሺ ለሚበልጡ ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጡ ሲሆን እስካሁን የ11 አቅመ ደካማ ቤቶችን ጠግነዋል፡፡

እንዲሁም በተራቆቱ አካባቢዎች ከ15 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መትከላቸውንና 178 ሄክታር የጥቁር አፈር መሬትን አርሰው በማጠንፈፍ በሰብል እንዲሸፈን አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም 4ሺ 637 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ በመስመር የመዝራት ተግባር በማከናወን ለአርሶ አደሩ እገዛ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

''ወጣቶቹ በከተማ ጽዳት፣ በቢሮ ስራ፣ የተዘጉ የጎርፍ መፋሰሻ ቦዮችን በመክፈትና በሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ተሰማርተው ማህበረሰቡን እያገለገሉ ይገኛሉ'' ብለዋል።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የ5ኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ገነት መልካሙ በበኩሏ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሳተፏን ገልፃለች፡፡

ዘንድሮም በወልድያ ከተማ ለሙያዋ ቀረቤታ ባለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተሰማርታ አገልግሎት እየሰጠች መሆኑን ተናግራለች፡፡

የ3ኛ ዓመት የሂሳብ ተማሪ ሀብታም ወዳጆ በሰጠው አስተያየት በወልድያ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማጠናከሪያ ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በሀምሌ ወር አጋማሽ የተጀመረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እስከ ነሀሴ ወር መጨረሻ ይዘልቃል፡፡

በሰሜን ወሎ ዞን ባለፈው ዓመት ከ282ሺ በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያየ  የልማት ስራ ማከናወናቸው ታውቋል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ነሃሴ 3/2009 የአፋር ክልል ከ15 ዓመት በታች የታዳጊ ወጣቶች የፕሮጀክት እግር ኳስ ውድድር ከትላንት ጀምሮ በሰመራ ከተማ እየተካሄደ ነው።

ለመጪዎቹ አምስት ቀናት በሚቆየው በእዚህ ውድድር ሰባት ወረዳዎች ተሳታፊ ናቸው።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን ተወካይ አቶ አብዱ ሃሰን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ውድድሩ ከነሀሴ 13 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በጅግጅጋ ከተማ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የኮካ ኮላ ሻምፒዮና በሁለቱም ጾታዎች ክልሉን ወክለው የሚወዳደሩ ተጫዋቾችን ለመምረጥ ነው ።

በተጨማሪም በኮካ ኮላ ፋብሪካ ድጋፍ በክልሉ በሰባት ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው ከ15 ዓመት በታች ታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክት ስልጠና ሂደትን የመገምገም ዓላማ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ አብዱ እንዳሉት፣ በውድደሩ ተሳታፊ ከሆኑ ሰባት ወረዳዎች ውስጥ አምስቱ በሁለቱም ጾታዎች፤ ሁለቱ ደግሞ በሴቶች ብቻ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ከእዚሁ ጎን ለጎን ክልሉ ለታዳጊ ወጣቶች በሰጠው ትኩረት በ13 ወረዳዎች በ12 የስፖርት አይነቶች የፕሮጀክት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

የዱብቲ ወረዳ ፕሮጀክት አሰልጣኝ አብዱ ኢሴ በበኩላቸው፣ በክልሉ በኮካ ኮላ ድጋፍ እየተካሄደ ላለው የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ፕሮጀክት ስልጠና ከውድድር ትጥቅ አቅርቦት ጀምሮ አስፈላጊው እገዛ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አቶ አብዱ ገለጻ ለፕሮጀክት አሰልጣኞችም የዘርፉን ሳይንስ መሰረት ያደረገ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

Published in ስፖርት

አርባምንጭ ነሃሴ 3/2009 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል እንደሚሰሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የጋሞ ጎፋ ዞን ነዋሪዎችና ፖሊስ አስታወቁ ፡፡

በአርባ ምንጭ ከተማ ሴቻ ክፍለ ከተማ የዶይሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ኮራ አያሌው እንደገለጹት ሰላም እንዲረጋገጥ የፀጥታ ኃይሉ በየአከባቢው ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል ፡፡

እሳቸውም ሰላማቸውን ሊያናጉ የሚችሉ ተግባራትን ለፀጥታ ኃይል በመጠቆም የድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡

''የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተገቢው ሰዓት ተነስቷል'' ያሉት አቶ ኮራ አሁንም በአካባቢያቸው የተገኘውን ሰላም ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

''ለልማት መሰረት የሆነውን ሰላም በማረጋገጡ ረገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል'' ያሉት ደግሞ በዞኑ የደምባ ጎፋ ወረዳ ነዋሪ አቶ በላይ በዛብህ ናቸው፡፡

''የሰላሙ ባለቤት እኛው በመሆናችን በአካባቢው ያለውን ሰላም ለማስቀጠል ከፀጥታ አካላት ጋር የጀመርነውን የወንጀል መከላከል ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን'' ብለዋል፡፡

በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ የተሰማራው የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ትግልፍሬ ሙሉጌታ በበኩሉ ወጣቱ በየደረጃው የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ተጠቃሚነቱን የበለጠ ለማረጋገጥ ሰላም በማስፈኑ በኩል የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጾ ወጣቱ ''የጸረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርበታል'' ብሏል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ፖሊስ መምሪያ በበኩሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመታወጁ አስቀድሞ በዞኑ ከግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ጋር ግንኙነት የነበራቸው ፀረ-ሰላም ኃይሎች በአባያና ጫሞ ሸለቆዎች በመስፈር ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጿል፡፡

የመምሪያው ፖሊስ አዛዥ ተወካይና የማህበረሰብ አቀፍ ሥራ ሂደት አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር ፊሊበር ቁጮ ''እነዚህ አካላት ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ለማደፍረስ ህገ-ወጥ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን ጨምሮ በማህበራዊ ሚዲያ አፍራሽ መልእክቶችን ሲያስተላልፉ ነበር'' ብለዋል ፡፡

ይሁን እንጂ ፀረ-ሰላም ኃይሎች አንዳች ተግባር ሳይፈጽሙ በዞኑ የፀጥታ ግብረ-ኃይልና በህዝቡ አንድነት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

''የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳም የዞኑ ፖሊስ ከህብረተሰቡ ጋር የጀመረውን ቅንጅት በማጠናከር ለአካባቢው ሰላም መጠበቅ በትኩረት ይሰራል'' ብለዋል፡፡

Published in ፖለቲካ

ደሴ ነሃሴ3/2009 በደቡብ ወሎ ዞን ከ217 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መተከሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ጥላሁን ሞላ እንዳስታወቁት ችግኙ የተተከለው በተያዘው የክረምት ወቅት ለመትከል ከታቀደው 250 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ ነው፡፡

በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎች ዝናብ ዘግይቶ በመጀመሩ እስካሁን ያልተተከለው 32 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም የተከላ ስራው በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ችግኙ ለየስነ- ምህዳሩ ተስማሚነት ተለይቶ በ48 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ ነው እተተከለ ያለው።

በችግኝ ተከላው 525 ሺህ በላይ ህዝብ የተሳተፈ ሲሆን የተከላ ስራው በተያዘው ሳምንት መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ አስተባባሪው ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተካሄደው የችግኝ ተከላ የዞኑ የደን ሽፋን 12 በመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን ''በዚህ አመት በሚተከለው ችግኝ ሽፋኑን በአንድ ነጥብ አንድ በመቶ ለማሳደግ ያስችላል'' ብለዋል።

በችግኝ ተከላው ከተሳተፉት መካከል በጃማ ወረዳ ቀበሌ 14 ነዋሪ አርሶ አደር በየነ ሽፈራው በሰጡት አስተያየት ባለፉት አመታት በተካሄደው የችግኝ ተከላ ተራቁቶ የነበረውን አካባቢያቸው እያገገመ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዘንድሮም በአንድ ለአምስትና በልማት ቡድን ተደራጅተው የችግኝ ተከላ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልፀው የተከሉት ችግኝ እንዲጸድቅ ጥበቃና እንክብካቤ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በደሴ ዙሪያ ወረዳ ቀበሌ 30 ነዋሪ ወጣት የሺህወርቅ ሙሉጌታ በበኩሏ በችግኝ ተከላ ስራው ዘንድሮ ለ3ኛ ጊዜ  መሳተፏን ገልፃለች፡፡

“ችግኝ መትከል ብቻ በቂ አይደለም” ያለችው የሺህወርቅ “ችግኙ ከተተከለ በኋላ እንዲጸድቅ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል” ብላለች።

ባለፈው ክረምት ከ276 ሚሊዮን በላይ ችግኝ የተተከለ ሲሆን በተደረገው ጥበቃና የእንክብካቤ 70 በመቶ መፅደቁን በግንቦት ወር በተካሄደ የሁለተኛ ዙር ቆጠራ መረጋገጡ ታውቋል።

Published in አካባቢ

ሰመራ ነሃሴ 3/2009 በአፋር ክልል ሁለት ወረዳዎች በደረሰ የመብረቅ አደጋ የስድስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

መብረቁ አራት የቤት እንስሳትንም መግደሉ ታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ከድር አብደላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የመብረቅ አደጋው የደረሰው በክልሉ "ጭፈራ" እና "እዋ" በተባሉ ሁለት ወረዳዎች ነው።

ከትላንት በስቲያ ማታ በእዋ ወረዳ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ድረስ የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በቦሎቶሞና ቤሉ ቀበሌዎች የወደቀ መብረቅ ሁለት ሰዎችና ሁለት የቀንድ ከብቶችን ሲገደል፣ በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል።

በእዚሁ ቀን ጭፍራ ወረዳ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እስከ 3፡00 ሰዓት በጣለው ዝናብ ተገሪ፣ አስኮማና ጭፍራ 01 በተባሉ ቀበሌዎች መብረቅ ወድቆ አራት ሰዎችንና ሁለት የቀንድ ከብቶችን መግደሉን ተናግረዋል።

በተያዘው የክረምት ወራት በክልሉ ከእዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በተለያዩ ወረዳዎች ተደጋጋሚ የመብረቅ  አደጋ መከሰቱንም አቶ ከድር  አስታውሰዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በዱብቲ፣ ኩነባና ጭፍራ ወረዳዎች ተመሳሳይ የመብረቅ አደጋ ደርሶ የሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ በእነዚህ ጊዜያት ወስጥ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመብረቅ ተመተው የሞቱ ሰዎች ቁጥር 13 ደርሷል።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን