አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Tuesday, 08 August 2017

አዲስ አበባ ነሃሴ 2/2009 የአሜሪካ ኤምባሲ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መልምሎ በድረ ገጽ ኮዲንግና ሌሎች ዘርፎች ለአንድ ዓመት ያሰለጠናቸውን 40  ሴት ተማሪዎች አስመረቀ።

 ተማሪዎቹ በስልጠናው ተጨባጭ የኮዲንግ ዕውቀትና የሕይወት ክህሎት እንዲጨብጡ ማስቻሉን ገልፀዋል።

ኤምባሲው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ትኩረቱን በሶፍት ዌር ኮዲንግ ያደረገ ጂ ሲ ሲ ፒ የተሰኘ የስልጠና ፕሮጀክት ቀርፆ በመንግስት መሰናዶ ትምህርት ቤቶች እየተገበረ ይገኛል።

ኤምባሲው ባለፈው ዓመትም በአዲስ አበባ ከሚገኙ አስር ትምህርት ቤቶች ለተውጣጡ 40 የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች ተመሳሳይ ስልጠና ሰጥቶ አስመርቋል።

በዘንድሮው ፕሮግራም ደግሞ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በባህር ዳር፣ በመቀሌ፣ በጅማና በድሬዳዋ ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ከእያንዱ ከተማ 40 ተማሪዎች መልምሎ በድምሩ ለ200 ሴት ተማሪዎች ስልጠና ሰጥቷቸዋል።

ከነዚህ መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 40 ሰልጣኞች ዛሬ ተመርቀዋል።

በኤምባሲው የፕሮጀክቱ አስተባባሪ እመቤት መቆያ እንዳሉት ፕሮጀክቱ ሴቶች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲገቡና ከገቡም በኋላ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘረፍ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ያለመ ነው።

ለ9 ወራት የሚሰጠው ይህ ስልጠና ከኮዲንግ በተጨማሪ በህይወት ክህሎትና በአመራር ስልጠናም ተሰጧቸዋል።

በፕሮግራሙ የተለያዩ እንግዶችን በመጋበዝ የማነቃቂያ ንግግር ሲደረግላቸው መቆየቱም ተመልክቷል።

ኤምባሲው የቅድመ ከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለማበረታታት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም አስተባባሪዋ ተናግረዋል።

ከሰልጣኝ ተማሪዎች መካከል የኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ተማሪዋ ፈትያ አብራር መሰረታዊ የኮምፒዩተር ክህሎት እንዳልነበራት ገልጻ፤ ስልጠናው እርሷና ጓደኞቿ የራሷቸውን ድረ ገጽ ማበልጸግ የሚያስችላቸው ዕውቀት መጨበጣቸውንም አብራርታለች።

ሴት ተማሪዎች በኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቀላሉ ለመፍታት የሚያስችሉ የዲጅታል ቴክኖሎጂዎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝም አብራርታለች።

ከቀለመ ወርቅ ትምህርት ቤት ተመልምላ ስልጠናውን የተከታተለችው ተማሪ ነጃት አህመድ በበኩሏ ስልጠናው ከኮምፒዩተር ኮዲንግ በተጨማሪ በህይወት ክህሎት የተሰጠው ስልጠና ሯሷን ለመግለጽ እንዳስቻላት ገልጻለች።

በተለይም በኮዲንግ ስልጠናው ድረ ገጽ መፍጠርና መረጃ መሰብሰብ የሚያስችል ግንዛቤ እንዳስጨበጣት ነው ያብራራችው።

በሌሎች ከተሞች ስልጠናው ሲሰጣቸው የነበሩ ተማሪዎች በዚህ ወር ውስጥ እንደሚመረቁም ተገልጿል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2009 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ ቁጥር 573/2000 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ምዕራፎች በሰፈሩት 31 አንቀጾች ላይ ባደረጉት ድርድር የማሻሻያ ሀሳቦችንና አዳዲስ አንቀጾችን ማካተታቸውን አስታወቁ።

የፓርቲዎቹ ሚዲያ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብሩ በርሄ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት  በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 በፓርቲዎች አመሰራረት፣ የምዝገባ እንዲሁም የምርጫ ቦርድን ተግባርና ኃላፊነት በሚመለከቱ  አንቀጾች ላይ ተደራድረዋል።

ፓርቲዎቹ ባካሄዱት ድርድር መሰረት የተሻሻሉ ሀሳቦችና አዳዲስ አንቀጾች መካታቸውንም አቶ ገብሩ አብራርተዋል።

የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት የመስራች አባላት ቁጥርን  ከ 1ሺ500 ወደ ሦስት ሺ እንዲሁም ለክልላዊ ፓርቲ  ከ750 ወደ 1 ሺ 500 ከፍ ማድረግ  ከተሻሻሉ አንቀጾች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

"ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የፖለቲካ ስራውን ለማካሄድ በአገር ውስጥ በየትኛውም ቦታ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ሊያቋቁም ይችላል" የሚለው አንቀጽ 17  "በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች  እና ቢያንስ  በአራት ክልሎች  ስድስት ፅህፈት ቤቶች እንዲኖሩት" በሚል ተሻሽሏል።

ክልላዊ ፓርቲዎችም "በክልሎች በሚገኙ 10 በመቶ በሚሆኑ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን እንዲከፍቱ" የሚል አዲስ አንቀጽ መጨመሩም ተገልጿል።

የምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን አቅም ለመገንባት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ፓርቲዎች በማናቸውም ውስጣዊ እንቅስቃሴያቸው የዲሞክራሲ ባህል እንዲያዳብሩ መከታተል የሚያስችሉት አንቀጾች መጨመራቸውን አቶ ገብሩ ተናግረዋል።

"ፓርቲዎቹ ጉባኤ ከማካሄዳቸው 30 ቀን ቀደም ብለው ለቦርዱ ማሳወቅ እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ አንቀጽ እንዲካተትም ተስማምተዋል" ብለዋል።

አንድ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ በሚያዘጋጅበት ጊዜ የአባላት ብዛት፣ ውሳኔ አሰጣጥ እንዲሁም ጉባኤ የሚያካሄድበትን አማካይ ጊዜ በግልጽ መያዝ እንዳለባት የሚያመለክት አዲስ አንቀጽ መካተቱም ተብራርቷል።

"ፓርቲዎቹ ለቢሮ አገልግሎት የሚሆን ቤት ለመከራየት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ማደናቀፍ የተከለከለ መሆኑን የሚደነግግ አንቀጽ እንዲጨመር  ተስማምተናል" ሲሉም ተናግረዋል።

ፓርቲዎቹ ከአንቀጽ 32 ጀምሮ በቀሪዎቹ የአዋጁ ሃሳቦች ላይ ለመደራደርም ለነገ ነሀሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።

ፓርቲዎቹ አንድ አጀንዳ ከአምስት የድርድር መርሃ ግብር በላይ መውሰድ እንደሌለበት የተስማሙ ሲሆን፤ የምዝገባ አዋጁን በሚመለከት ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ መደራደራቸው ይታወቃል።

 

 

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ነሐሴ 2/2009 የደላሎች የተሳሳተ መረጃ እና የምህረት ጊዜው መራዘም በሳዑዲ ያለመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዳይመለሱ እንዳዘናጋቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። በተደረገው ጥረት እስከ አሁን ከ67 ሺህ በላይ ዜጎች ተመልሰዋል

በሳዑዲ ዓረቢያ ያለፈቃድ የሚኖሩ ዜጎችን ለመመለስ የተቋቋመው ብሔራዊ ግብረ ኃይል እስከ አሁን በተከናወኑት ተግባራት ላይ ተወያይቷል።

የጉዞ ሰነድ ከወሰዱት እና ያለመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ  በሳዑዲ ይኖራሉ ተብለው ከሚገመቱት ዜጎች አኳያ የተመለሱት ጥቂቶች መሆናቸውም ተጠቁሟል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የሳዑዲን መንግስት ፖሊሲ በትክክል ያለመረዳትና የደላሎች የተሳሳተ መረጃ ወደ አገር ቤት ሊመለሱ የሚገባቸውን ዜጎች አዘናግቷል።

በሳዑዲ ዓረቢያ አሰሪዎች የሚሰጠው አጉል ተስፋ እና የምህረት ጊዜው መራዘም ዜጎችን እንዳዘናጋቸው በውይይቱ ላይ መነሳቱንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

ዜጎች ባሉበት አካባቢ የጉዞ ሰነድ እንዲያገኙ በተለያዩ የሳዑዲ ግዛቶች ጊዜያዊና ተንቀሳቃሽ ጽ/ቤቶች መከፈታቸውን ያስታወሰው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ፤ የመኖሪያና የሥራ ፈቃድ የሌላቸው ዜጎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ  ጥሪ አቅርቧል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሐሴ 2/2009 የኢትዮጵያ የፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር ለሶማሊያ መልካም ልምድ የሚቀሰምበት መሆኑን  የአገሪቱ መንግስት ልዑክ  አባላት ገለጹ።

በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኙት አባላቱ  ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የየክልሉ ህዝቦች በምክር ቤቱ የተወከሉበትን መንገድ ሶማሊያ እንደ ጠቃሚ ልምድ ትወስደዋለች።

የልዑክ ቡድኑ ከፌደሬሽን ምክር ቤት የስራ ኃላፊዎች ጋር በምክር ቤቱ አወቃቀርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ተወያይቷል።

የአገሪቱ ደቡብ ምዕራብ ክልላዊ መንግስት የኢንፎርሜሽንና ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ሀሰን አብዱራሀማን መሐመድ እንዳሉት የክልሉ ብሔር ብሔረሰቦችና  ህዝቦች የተወከሉበት ምክር ቤት ልምድ ለሶማሊያ ጠቃሚ ነው።

በፌደሬሽን ምክር ቤት  ክልሎች ቢያንስ ካላቸው አንድ ተወካይ በተጨማሪ በአንድ ሚሊዮን ህዝብ አንድ አንድ  ተጨማሪ ውክልና የሚያገኙበት ሁኔታ መልካም የሚባልና ለሶማሊያ ጠቃሚ ልምድ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክር ቤቱ ክልሎች የሚወከሉበት ሁኔታ የውክልና ስርአቱ ፍትሐዊና የህዝቡን ተሰሚነት እንዲጎላ በማድረግ ረገድ ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የሶማሊያ የአገር ውስጥና የፌደራል ዕርቀ ሰላም ሚኒስቴር ቋሚ ፀሐፊና የልዑክ ቡድኑ መሪ አብዱላሂ ሞሐመድ ሀሰን በበኩላቸው የምክር ቤት አባላት የሚወከሉበት ስርአት የህዝቡን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

ከዚህም ሀገራቸው ትልቅ ልምድና ተሞክሮ እንደምትወስድ ነው የልዑክ ቡድኑ መሪ የተናገሩት።

"ሴቶች በፌደሬሽን ምክር ቤት ያላቸው ተሳትፎ በሶማሊያ የሚገኙ ምክር ቤቶች ትምህርት የሚቀስሙበት ነው" ያሉት ደግሞ የሶማሊያ የአገር ውስጥና የፌደራል ዕርቀ ሰላም ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሚስ ፋርቱን ሮብሌ መሐመድ ናቸው።

በምክር ቤቱ ያለው የሴቶች ውክልናና ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በዕለቱ ከተደረገላቸው  ገለጻ መረዳታቸውን አመልክተው በዚህ ረገድ ያለው ተሞክሮም ለአገራቸው ጠቃሚ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ያለው አባተ እንደገለጹት የምክር ቤቱ አወቃቀር የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ነው።

አገሪቷ የምትከተለውን የፌደራሊዝም ስርአት መሰረት አድርጎ የተቋቋመው ምክር ቤት ክልሎች በኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ፣ፖለቲካዊና ሌሎች መስኮች ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻለ ነው ብለዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤትን አወቃቀርና የፌደራሊዝም ስርአቱን አስመልከቶ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ መንግስት ያላትን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

የሶማሊያ መንግስት ልዑክ  ከኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት፣ ገቢ አሰባሰብ፣ ከተማ ልማት፣ግጭት አፈታት፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ልምድ ለመቅሰም  አዲስ አበባ የገባው ትናንት ነው።

የልዑክ ቡድኑ  ለተከታታይ 4 ቀናት በአዲስ አበባ፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በመዘዋወር ተሞክሮዎችን እንደሚቀስም የወጣው ፕሮግራም ያመላክታል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት በአሁኑ ወቅት 153 አባላት ያሉት ሲሆን ከዚህ ውስጥ የሴቶች ድርሻ 33.5 በመቶ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዳማ ነሃሴ 2/2009 በኦሮሚያ ክልል ከዘንድሮ የመኸር አዝመራ 184 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

ዘንድሮ ለማግኘት የታቀደው ምርት ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ30 በመቶ ብልጫ ይኖረዋል ተብሏል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ስለሺ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት  በዘንድሮው የመኸር አዝመራ ከዋና ዋና ሰብሎች 184 ሚሊዮን 600 ሺህ ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

ባለፈው ዓመት የተገኘው ምርት 144 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር አስታውሰው ፣ ዘንድሮ ከ40 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት ለማግኘት የተቀናጀ የግብርና ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት የአርሶአደሩን የግብርና ግብዓት አጠቃቀም በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዕቅዱ ተግባራዊነት የክልሉ መንግስት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር መዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአርሶአደሩ ማሰራጨቱንም ተናግረዋል።

በመኸር አዝመራው ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማልማት የታቀደ ሲሆን እስካሁን ድረስም 85 በመቶ የሚሆነው በዘር ተሸፍኗል።

ከእዚህ ውስጥም አንድ ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በኩታገጠም በመስመር የተዘራ መሆኑን ከኃላፊው ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።

የአገሪቷን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማፋጠን የግብርና ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ስለሺ ገልጸው፣ እያደገ የመጣውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ በግብዓት ለመመገብ ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ትርፍ ማምረት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ የባቴ ገርማማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቃቻ ተሊላ በሰጡት አስተያየት፣ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በልማት ጣቢያ ባለሙያዎች የዕለት ተዕለት ድጋፍና ሙያዊ እገዛ እየተደረገላቸው በሰባት ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ በመስመር መዝራታቸውን ገልጸዋል።

በብተና ሲዘሩ በሄክታር እስከ 40 ኪሎ ግራም ዘር ይጠቀሙ እንደነበር አስታውሰው በቴክኖሎጂ ታግዘው በመስመር ሲዘሩ በአንድ ሄክታር ሰባት ኪሎ ግራም ጤፍ ብቻ መጠቀማቸውን አስረድተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሀሴ 2/2009 በአዲስ አበባ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ  በተደረገ ቁጥጥር ከ134 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ጊዜ ያለፈባቸውና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግቦች ማስወገዱን የከተማው ምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላለል በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጊቶችን የፈፀሙ የ12 የንግድ ድርጅቶች ጉዳይ ወደ ህግ መወሰዱም ባለስልጣኑ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምጸሃይ ጳውሎስ ለኢዜአ እንደገለጹት "ባለስልጣኑ ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ በ4ሺ 15 ተጋላጭ የሚባሉ የምግብና የመጠጥ ድርጅቶች ላይ ክትትል አድርጓል።"

በዚህ መሰረት ከ134 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የስጋ፣ የአትክልትና ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ሌሎች ጊዜ ያለፈባቸውና ለጤና አስጊ የሆኑ ምግቦች ተይዘው እንዲወገዱ ተደርገዋል።

በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉና ጊዜ ያለፈባቸው 73 ሺህ ሊትር ለምግብነት የሚውሉ የታሸጉ መጠጦችም በተደረገው ቁጥጥርና ክትትል ተይዘው እንዲወገዱ መደረጉን ወይዘሮ አለምጸሃይ ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ በ2009 በጀት ዓመት ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒት ሲሸጡ ያገኛቸውን 125 ቸርቻሪ ድርጅቶች ላይ የማስጠንቀቂያ፣ የማሸግና  በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ መስራቱን ምክትል ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

ለባለስልጣኑ ከሰኔ ወር ጀምሮ ከህብረተሰቡና ከህጋዊ የንግዱ ማህበረሰብ 925 ጥቆማዎች የደረሱት መሆኑንና ጥቆማዎቹን መሰረት አድርጎ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዱንም ገልጸዋል።

ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር በመቀላለል ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ድርጊቶችን በፈፀሙ 12 የንግድ ድርጅቶች ጉዳይ ወደ ህግ መወሰዳቸውንም ጠቁመዋል።

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 08 August 2017 21:57

ያልዘሩትን ማጨድ…

Published in ቪዲዮ

መቀሌ ነሀሴ 2/2009 የአልነጃሺ መስጊድና አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሀጂና ዑምራ ተጓዦች ገለፁ፡፡

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የዘንድሮ የሀጂና ዑምራ ተጓዦች በትግራይ ክልል የሚገኘውን አልነጃሺ መስጊድ በመጎብኘትና ፀሎት በማድረግ ዛሬ ከመቀሌ አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮኘላን ወደ ሳዑዲ ተጉዘዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የመጡት ሼክ ያቁብ አባድር እንደገለፁት ወደ ሳዑዲ ቀጥታ በረራ ከማድረጋቸው በፊት ቀደም ሲል በስም በሚያውቁት ታሪካዊው አልነጃሺ መስጊድ ፀሎት ማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ ፈጥሮላቸዋል፡፡

ከነቢዩ መሐመድ የተላኩት የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ኢትዮጵያ ተቀብላ በአልነጃሺ እንዲያርፉ ማድረጓን አስታውሰዋል፡፡

''የአካባቢው ነዋሪም ትላንት ወደ ስፍራው ለደረሱት የሀጂ ዑምራ ተጓዦች ደማቅ አቀባበል በማድረግ ለዘመናት የቆየውን የእንግዳ ተቀባይነት ባህል ዳግም አረጋግጠዋል'' ብለዋል፡፡

ይህን ታሪካዊ ስፍራ በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ለተጀመረው ጥረት የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

''እስልምና ካነሳን አልነጃሺን፣ አልነጃሺን ካነሳን ኢትዮጵያን ማንሳታችን አይቀሬ ነው" ያሉት ደግሞ  ከደቡብ ክልል ስልጤ ዞን የመጡት ሼክ ሸምሰዲን ብአዲ ናቸው፡፡

"አልነጃሺን ማስተዋወቅ ኢትዮጵያ የሃይማኖት መቻቻል ተምሳሌት ስለመሆንዋ ለአለም ማህበረሰብ ማረጋገጥ ከመሆን ባለፈ የቱሪዝም ፍሰቱ  እንዲጨምር አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ መስህቡን የማስተዋወቅ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል ።

አልነጃሺ  ፀሎት አድርሰው ወደ ሳዑዲ መጓዛቸው የቀደምት የእምነቱ ተከታይ አባቶች እሴቶችን ጠብቀው ለማቆየት እንደሚያግዛቸው የገለፁት  ሸኽ ሸምሰዲን  ሃይማኖታዊ መስህቡን በማስተዋወቅ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል ።

የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ፀሐፊ ሼክ መሐመድ ካሕሳይ እንደገለፁት ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የተውጣጡ 540  የሀጂ ዑምራ ተጓዦች በአልነጃሺ ፀሎት አድርሰው ወደ ሳዑዲ ጉዞ ያደርጋሉ ።

"ከእነዚህ ተጓዦች መካከል 270 የሚሆኑት በዛሬው እለት በአልነጃሺ ፀሎት ካደረጉ በኋላ  ከመቀሌ አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመጀመሪያ ጊዜ  ወደ ሳኡዲ ቀጥታ በረራ አድርገዋል " ብለዋል ።

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አባዲ ደስታ በበኩላቸው፣ አልነጃሺ መስጊድ በእስልምና እምነት ተከታዮችና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል ።

ቀደምት የሃይማኖቱ ተከታዮች ወደ መካ መዲና ለፀሎት ሲጓዙ አልነጃሺ መስጊድ ተሰባስበውና ፀሎት አድርሰው ይጓዙ እንደነበር አስታውሰዋል ።

"የአሁኑ ተጓዦችም በስፍራው ያደረጉት ፀሎት የቀደምት የእምነቱ ተከታዮች በጎ ተግባር እንዲቀጥል ያስቻለ ነው " ብለዋል ። 

በአልነጃሺ በኩል የሚደረግ ጉዞ  አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ በመሆኑ የክልሉን የቱሪዝም እድገት ከፍ በማድረግ በኩል የጎላ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

የ1ሺህ 438ኛ ሀጂና ዑምራ ተጓዦች በአልነጃሺ መስጊድ ፀሎት አድርሰው ከመቀሌ ቀጥታ በረራ እንዲያደርጉ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ቀደም ብለው መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

በሰባተኛው ክፍለ ዘመን በሳዑዲ በተቀሰቀሰው የሃይማኖት ግጭት ምክንያት የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች "ወደ ሐበሻ አገር ሂዱ ፤ ህዝቡ ተቀብሎ ያስተናግዳችኋል’’ የሚለውን የነቢዩ መሐመድን  ቃል ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ያረፉበት ስፍራ- አልነጃሺ የቱሪዝም መስህብ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።

Published in ማህበራዊ
Tuesday, 08 August 2017 21:11

ስደተኛው ኢንዱስትሪ

                                መብራህቱ  ይበልህ (መቀሌ ኢዜአ)

ብዙዎቹ  ስደተኛው  ኢንዱስትሪ  ይሉታል። ከአገር አገር፣ ከአህጉር አህጉር ስለሚንከራተት ነበር ስደተኛው የሚል መጠሪያ  የተሰጠው ። የመንከራተቱ ሚስጢር ደግሞ በተመጣጣኝ ዋጋ በቂ የሰው ጉልበትና እውቀት ለማግኘት ነው።

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ከሌላው የማምረቻ ዘርፍ በተለየ መንገድ ከርታታ መሆኑ ይነገርለታል ። ቋሚ ወዳጅ የለውም። ከወቅቱ ጋር አብሮ የሚሄድ ወዳጅን ፍለጋ ባህር አቋርጦ  ምድርን  ሰንጥቆ  የሰው ሀይል ያለህ እያለ የሚንከራተት ዘርፍ መሆኑ ነው።

የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስቱሪ ዓመታዊ ግብይቱ በትሪሊዮን  የአሜሪካን ዶላር መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ ። በዘርፉ የሚንቀሳቀሰው የሰው ሀይልም ከሌላው የማምረቻ ዘርፍ በብዙ እጥፍ ብልጫ ይወስዳል።

በአለማችን በርካታ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ባለቤት ከሆኑ አገሮች መካከል የህንድን ዓመታዊ ግብይት ብንመለከት ዘርፉ ምን ያህል አዋጪና ሰፊ ምጣኔ ሀብት እንደሚንቀሳቀስበት እንገነዘባለን ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ህንድ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በዓመት 150 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶች ለገበያ እንደምታቀርብ ያሳያል። ከዚሁ ውስጥ 40 ቢሊዮን ዶላሩ ወደ ውጭ በመላክ  የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ መሆኑን ያሳያል።

አገሪቱ ካላት የህዝብ ብዛት አንፃርም  ኢንዱስትሪው በእጅጉ የሚያዋጣት ሆኖ ተገኝቷል። 51ሚሊዮን ህዝቧ በጨርቃ ጨርቅና አልበሳት ስራ  ቧሰማራቱን መረጃዎች ያሳያሉ።

ህንድ የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገቢ  15 በመቶ ያህሉን ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት  ኢንዱስትሪ ታገኘዋለች። ከአጠቃላይ አመታዊ ምርቷም  የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፉ ድርሻ አራት ከመቶ ይሸፍናል።

በሚቀጥሉት ሶስት አመታት ደግሞ አመታዊ ግብይቷ  ወደ 230 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ለማድረግ እየኳተነች እንደምትገኝ ድረ ገፆች ያሳያሉ።

አገራችን በዓለም ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ፣ በርካታ ገዢ ኩባንያዎች፣ ብዙ ሚሊዮን የሰው ሀይል ወደ ሚንቀሳቀስበት  የማምረቻ ዘርፍ  ለመቀላቀል  ወገቧን ጠበቅ መንቀሳቀስ ጀምራለች።

በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ከተመረቁት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ የመታጨቱን ብስራት ሰምተናል።

በምረቃው ስነ ስርአት ላይ የተገኙት በሚኒስትር ማዕረግ የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ እቁባይ የማምረቻ ዘርፉን ዋና የኢኮኖሚው ምሰሶ ለማድረግ ስራው እንደተጀመረ አብስረዋል።

ዘርፉን ለመቀላቀል ግን በርካታ እድሎችና ፈተናዎች ጎን ለጎን መቀመጣቸውም ተገልጿል። ከፈተናዎቹ መካከል በብዙ ትሪሊዮን ዶላር የሚንቀሳቅሰውን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ገበያ ሰብሮ ለመግባት መንገዱ አልጋ በአልጋ  አለመሆኑን ዶ/ር አርከበ እቁባይ ያስረዳሉ።

ከተሰራበት፣ከተለፋበትና ወገብን ጠበቅ ተደርጎ ከተገባ ግን ወደ ውድድሩ ለመግባት በርካታ  ፀጋዎችና እድሎች እንዳሉም ዶ/ር አርከበ እቁባይ አስረድተዋል።

በዙሪያው ተመሳሳይና ተመጋጋቢ  ኢንዱስቱሪዎች ማበባቸው የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክን መፃኢ ጊዜ ብሩህ ያደርገዋል።

በውጭ ባለሀብቶች ተገንብተው ወደ ማምረት ምእራፍ እየተሸጋገሩ የሚገኙት የህንድ ኩባንያ  ቮሎሲቲ፣የባንግላድሽ ኩባንያ ዲቢኤል፣አንድ የጣልያን ኩባንያና ቀደም ብሎ የተገነባ ማጋርመንት መቐለ አካባቢ መከተማቸው ፓርኩን እድለኛ ያደርገዋል።

እርሻ ብቻ ሳይሆን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፎችም በኩታ ገጠምና በመደዳ  እየከተሙ በመሆናቸው በርካታ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይነገራል።

ከአዋሽ ሃራ ገበያ መቐለ በመገንባት ላይ ያለው የባቡር ሀዲድም ዘርፉ የሚያመርተውን ምርት በፍጥነት ወደ ወደብ ለማንሳትና ከውጭ የሚመጡ ግብአቶችን በብዛትና በፍጥነት ለማጓጓዝ አመቺ ያደርገዋል ።

መቐለ ከጅቡቱ ወደብ በ600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑም የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አመቺ ያደርገዋል ።  

ዶክተር አርከበ እቁባይ እንዲህ ይላሉ፣ “እርዳታ መለመንና ወደ ሰው አገር ተሰዶ ጉልበትን በርካሽ ዋጋ መሸጥን የመሰለ አሳፋሪ ስራ የለም ። ኢንቨስትመንትን መሳብ ግን የድህነት መገለጫ ሳይሆን ለልማት የቆረጠ መንግስት ማሳያ ነው።”

ሰፊ ኢንቨስትመንትን መሳብ ቀጣዩና ከባዱ የቤት ስራ መሆኑንም  ያስረዳሉ። በተለይም የዳበረ ቴክኖሎጂ ፣ልምድና ካፒታል ያላቸው የውጭ ባለሀብቶችን ማስመጣት የውድድር ብልህነትን ይጠይቃል ባይ ናቸው።

ከመቐለ በ50 ኪሎ ሜትር ርቀት አካባቢ የሚገኙ ከተሞችም  የኢንዱስቱሪ ማእከል የመሆን እድላቸው ሰፊ መሆኑን ይናገራሉ ።ይህንኑ ለማድረግም  ክልሉና የፌደራል መንግስት ዝግጁ መሆናቸውን በመጠቆም።

በዘርፉ የሚሰማራውን የሰው ሃይል የኢንዱስትሪ አስተሳሰብና ቅኝት ያለው ፣ በእውቀትና በክህሎት እራሱን ያዘጋጀ ለማድረግ ውስብስብና ከባድ ፈተና በመሆኑ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባልም ነው ያሉት ዶክተር አርከበ ።

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ አንድ መቶ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል።

የኢንዱስትሪ ልማት ፓርኮች ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስገዶም ለኢዜአ እንደገለፁት የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ  በልዩ ሀኔታ የተገነቡ 15 ሼዶች አሉት። ወደ ስራ ሲገቡ  20 ሺህ ለሚሆኑ ወገኖች  የስራ እድል ይፈጥራሉ ። ሌላ ከተማ መቆርቆር ማለት ነው።

ፓርኩ ውስጥ የህክምና፣የፖሊስ፣የአንድ መስኮት አገልግሎት ማእከል ፣የጉምሩክ፣ንግድና የሌሎች አገልግሎቶች መስጫ ማእከላትና ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ህንፃዎችን ያካተተ መሆኑንም ያስረዳሉ።

በኢፌዴሪ የኢንቨስትመንት ኢጀንሲ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑ አቶ አበበ  አበባየሁ ፓርኩን በሚቀጥሉት አራት ወራት ውስጥ ስራ ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተለይም በዓለማችን የሚታወቁ ሶስት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያዎች ወደ ፓርኩ ለመግባት የሚያስችላቸውን ድርድር በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።

የመቐለ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ሲመረጥ ያለ ምክንያት አይደለም ያሉት አቶ አበበ ለዘርፉ የሚመች የሰው ሀይል መኖሩን በጥናት ተረጋግጧል ይላሉ።

በዙሪያው በዘርፉ ሊሰራ የሚችል ከአንድ ነጥብ አምስት ሚልዮን በላይ የሰው ሀይል መኖሩ እንደተረጋገጠም ያስረዳሉ።

ይህም በመቐለ ዙሪያ እየከተሙ ያሉትን የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች የሚመግብ የሰው ሀይል በመኖሩ ከርታታው ወይም ስደተኛው ፋብሪካ ማረፊያ እንዲያገኝ እስችሎታል።

ፓርኩ በፍጥነት ስራ እንዲጀምር የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ምክትል ርእስ መስተዳድሩ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ ናቸው።

ፓርኩን ሊያውኩ የሚችሉ የውሃና የኤሌክትሪክ እጥረት  በፍጥነት እንዲፈታም የፌደራል መንግስቱ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥያቄ አቅርበዋል።

አብዛኛው የክልሉ ህዝብ ኑሮው ግብርና ላይ የተመሰረተ ቢሆንም 30 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ከተማ ውስጥ ይኖራል።

ፈጣን የሚባል የአዳዲስ ከተሞች መቆርቆርና መስፋፋት ከሚታይባቸው የአገራችን ክልሎች መካከል ትግራይ ግንባር ቀደም ደረጃ እንደያዘችም ይጠቀሳል።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ በፓርኩ ምረቃ ላይ ’’ የትግራይ ክልል ከሌሎች የአገራችን ክፍሎች በተለየ ሁኔታ ከግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ባለፈ ህዝቡም ሆነ የክልሉ መንግስት በአማራጭ የኑሮ መሰረቶች ላይ ትኩረት ሲያደርግ ቆይቷል።በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መፃኢ እድሉ ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር የተቆራኘ እንደሚሆንም ህዝቡ የተረዳው እጅግ ቀደም ብሎ ነው’’ ያሉት ።

የህዝቦች ወደ ከተማ መሰብሰብ ማህበራዊ መሰረተ ልማቶችን ከማቅረብ ባለፈ ለኢንዱስቱሪ ልማት መስፋፋትም የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት ።

ስደተኛው ኢንዱስትሪ ማረፊያውን መቐለ ኢንዱስትሪ  ፓርክ ለማድረግ ተቃርቧል ። የአካባቢው ወጣቶችም በናፍቆት እየጠበቁት ነው ።

Published in ዜና ሓተታ

ጅግጅጋ ነሃሴ 2/2009 በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ15 ሺህ በላይ አርብቶአደሮችን በመንደር ለማሰባሰብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ተፋሰስና መስኖ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮ የመንደር ማሰባሰብ ሥራ ሂደት መሪ አቶ ፈርሃን መሀሙድ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት የመንደር ማሰባሰቡ ሥራ የሚካሄደው በጀረርና ቆረሃ በሚገኙ አራት ወረዳዎች ነው።

የመንደር ማሰባሰቡ ሥራ በአርብቶ አደሩ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

"አርብቶ አደሮቹ በአንድ ማዕከል በመሰባሰብ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን የእርሻ ልማት በማካሄድ ራሳቸውን በምግብ ሰብል እንዲችሉ ይደረጋል " ብለዋል ።

እንደ ሥራ ሂደት መሪው ገለጻ በመንደር ለሚሰባሰቡ አርብቶአደሮች ለግብርና ሥራ አገልግሎት የሚውሉ በ500 ሚሊዮን ብር አራት የመስኖ ተቋማት ተገንብተው ዝግጁ ሆነዋል።

የመስኖ ተቋማቱ 21 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳላቸውና ለልማቱ የሚሆን መሬትም መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ለአርብቶ አደሮቹ በዘመናዊ የግብርና አሰራር ስልጠና ለመስጠትና የገበያ ትስስር የመፍጠር ሥራዎች ለማከናወን አቅጣጫ መያዙን አመልክተዋል።

ከእዚህ ጎን ለጎን በመንደሮቹ የትምህርት፣ የጤናና የንጹህ መጠጥ ውሃ  ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል ።

አርብቶአደሩ የተዘጋጁትን የመሰረተ ልማት አውታሮች በመጠቀም ሕይወቱን በዘላቂነት እንዲቀይር የጎሳ መሪዎችን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየተሰጠ ነው ።

በክልሉ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመንደር የተሰባሰቡ 199 ሺህ ከፊል አርብቶ አደሮች ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን ወንዞችን በመጥለፍ 3 ነጥብ 2  ሚሊዮን ኩንታል በቆሎን ጨምሮ ሰሊጥ፣ ሽንኩርትና ቲማቲም እንዲሁም የእንስሳት መኖ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል።

በክልሉ ባለፉት ዓመታት በመንደር ከተሰባሰቡ አርብቶ አደሮች መካከል በአፍዴር ዶሎ አዱ ወረዳ ለመደጋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሐመድ ኢስማኤል አንዱ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በመንደር ሳይሰባሰቡ እንስሳቶቻቸውን ይዘው ሳርና ውሃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልጆቻቸው የትምህርትና የዘመናዊ ህክምና ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

በመንደር ከተሰባሰቡ በኋላ ከእንስሳት እርባታ ጎን ለጎን በአካባቢው የሚፈሰውን የገናሌ ወንዝ በመጥለፍ አንድ ሄክታር መሬት ላይ ሰብል ማልማት መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በመንደር መሰባሰባቸው የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖሩ ከማድረግ ባለፈ ልጆቻቸው የዘመናዊ ትምህርትና የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መቶ ሺህ ሄክታር የማልማት አቅም ያላቸውና ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ የዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ፣ ዳዋና ወይብ ወንዞች እንዲሁም የስድስት ኃይቆችና የበርካታ ወንዞችና ጅረቶች ባለቤት ነው።

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን