አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Monday, 07 August 2017

አዲስ አበባ ነሃሴ 1/2009''ካፍን በመምራት በእግር ኳሱ አሻራ ያሳረፉትን ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ እውቅና እንዲሰጣቸው ጥረት አደርጋለሁ'' ሲሉ የካፍ ፕሬዘዳንት አህመድ አህመድ ገለጹ።

የአፍሪካን እግር ኳስን ለማሳደግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩም ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አህመድ አህመድ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝታቸውን ጀምረዋል።

ፕሬዝዳንቱ በጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለማሪያም ደሳለኝ ጋር የአገሪቱን እግር ኳስ በሚያሳድጉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ መንግስት እግር ኳሱን ለማሳደግ አብረው ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

ፕሬዝዳንት አህመድ እግር ኳሱን በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ለማሳደግ በጋራ ተባብሮ መስራት አማራጭ የሌለው መንገድ መሆኑን ገልጸው ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከካፍና ከፊፋ ጋር በቅርበት  ለመስራት ማቀዳቸውን ነው የተናገሩት።

አዲሱ ትውልድም የይድነቃቸው ተሰማን አርዓያ እንዲከተልና እግር ኳሱን ለማሳደግ አብረው ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

'' ካፍን በመምራት በእግር ኳሱ አሻራ ያሳረፉትን ክቡር ይድነቃቸው ተሰማን እውቅና እንዲሰጣቸው ጥረት አደርጋለሁ'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ኢትዮጵያ የካፍ መስራች እንደመሆኗ መጠን በሚፈለገው መጠን  አላደገችም፤ ወደ ቀድሞ ክብር ለመመለስ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ መናገራቸውን ውይይቱን  የተከታተሉት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ እርስቱ ይርዳ  ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማስተናገድ የሚችሉ ዘመናዊ ስታዲየሞች እየገነባች መሆኗም አንስተዋል።

የካፍ ፕሬዚዳንትም የአገሪቱ መንግስት ለስፖርቱ በሰጠው ትኩረት የስታዲየሞችን ግንባታ አድንቀው በወጣቶች ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት ይጠበቅባታል ብለዋል።

ካፍ በሚያዘጋጃቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ውይይቶችና ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ እንድትሆንም አህመድ አህመድ መጠየቃቸውን አቶ እርስቱ ይርዳ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የምስራቅ አፍሪካ እግር ኳስ አካዳሚ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ካፍ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም የኢትዮጵያ መንግስት ጠይቋል።

የካፍ ፕሬዘዳንት አህመድ በበኩሉ አካዳሚው ቶሎ ወደ ተግባር እንዲገባ ከመንግስት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰሩም እንዲሁ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ የካፍ አካዳሚንና በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለው የብሔራዊ ስታዲየም የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።

ማዳጋስካራዊ ፕሬዚዳንት አህመድ አህመድ ከስድስት ወር በፊት በአዲስ አበባ በተደረገው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ  ካሜሮናዊው ኢሳ ሃያቱን ተክተው መመርጣቸው ይታወሳል።  

 

Published in ስፖርት

አምቦ ነሃሴ 1/2009 አምቦ ዩኒቨርሲቲ የሰጣቸው ነጻ የህግ አገልግሎት ድጋፍ ሚዛናዊ ፍትህ እንዲያገኙ የረዳቸው መሆኑን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የተቋሙ የህግ ትምህርት ቤት ገንዘብ ከፍለው የግል ጠበቃ ማቆም ለማይችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች እየሰጠ ያለው ነጻ የህግ አገልግሎት ከወጪ እንደታደጋቸውም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። 

ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ዘሀራ ሸረፋ እንደተናገሩት፣ ከባለቤታቸው ጋር ሲጣሉ ባለቤታቸው ከነልጆቻቸው ከቤት እንዳባረሯቸውና ንብረትም እንደከለከሏቸው ገልጸዋል።

ጉዳዩን ወደፈርድ ቤት ወስዶ ለመከታተል የገንዘብ እጥረት እንደገደባቸው የገለጹት ወይዘሮ ዘሀራ፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ በሰጣቸው ነጻ የህግ አገልግሎት ጉዳያቸው ወደፍርድ ቤት መድረሱን ተናግረዋል። 

በዚህም ለልጆቻቸው የትምህርት ቤትና ወርሃዊ ቀለብ የሚሆን ክፍያ እንደተወሰነላቸውና ንብረት ለመካፈልም ጉዳዩ በፍርድቤት ቀጠሮ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

አቶ ሚልኬሳ ፉፋ የተባሉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው "በ2007 ዓ.ም የመኪና አደጋ ከደረሰብኝ በኋላ ክስ ለመመስረት የሚያስችል ገንዘብ ስላልነበረኝ ከነጉዳቴ ቤቴ ተቀምጬ ነበር" ብለዋል።

ይሁንና ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ነጻ የህግ አገልግሎት አደጋው ከደረሰ በኋላ ለሕክምና ያወጡትን ሁሉንም ወጪ የመኪናው ባለንብረት እንዲከፍል የወሰነላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"የዩኒቨርሲቲው የህግ ባለሙያዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ባደረጉልኝ የህግ ድጋፍ በገንዘብ እጦት ላጣው የነበረውን ፍትህ አግኝቻለሁ" ሲሉ አስረድተዋል።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት ጥናትና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲንና የነጻ ህግ አገልግሎቱ ማዕከል አስተባባሪ አቶ ብርሀኑ ሞሲሳ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው የህግ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ዜጎች ፍትህ አንዳይጓደልባቸው የማድረግ ዓላማ ያለው ነው፡፡

በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አቅመ ደካሞችና የህግ እውቀት የሌላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አገልግሎቱን ካገኙ 3 ሺህ 989 ሰዎች መካከልም 63 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።

አቶ ብርሀኑ እንዳሉት፣ በ2009 በጀት ዓመት ዩኒቨርሲቲው የሰበር ማመልከቻ በማዘጋጀት፣ ፍርድ ቤት ጥብቅና ቆሞ በመከራከር፣ ለክስ መልስ በመጻፍ እንዲሁም የህግ መረጃ በመስጠት ለሕብረተሰቡ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

በዓመቱ በህግ ከታዩ ጉዳዮች መካከልም የቤተሰብ ክርክርና የፍቺ ጉዳይ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዝ ሲሆን የመሬትና የንብረት እንዲሁም የውርስ ጉዳይ በቀጣይ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተቋሙ 50 ያህል የፍርድ ቤት ክሶችን ተከራክሮ ማሸነፍ መቻሉንና 10ሩን ወደ ሌላ ጊዜ እንዲሸጋገሩ መደረጉንም አያይዘው ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት ለበርካታ ሰዎች የህግ መረጃ መስጠቱን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

መቱ /ነቀምቴ ነሀሴ 1/2009 የተሰማሩበት የክረምት በጎ ፈቃድ  አገልግሎት  ሌሎችን የመርዳት ባህል እንዲያዳብሩ ያደረጋቸው መሆኑን የበደሌ ከተማ ወጣቶች ገለፁ።

በተመሳሳይ በቄለም ወለጋ ዞን በተያዘው ክረምት 145 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።

በበደሌ ከተማ የአስረኛ ክፍል ተማሪ ነኢማ  ኡመር  እንዳለችው በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና  በአካባቢ ጽዳትና ውበት ሥራ ላይ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።

" በአሁኑ ወቅት የምፈጽመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለእኔ ሌላው ትምህርት ቤት ነው" ያለችው ተማሪ ነኢማ፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የተቸገሩትን የመርዳትና በጎ ተግባራትን የመፈጸም ልምዷን እያጎለበተላት መምጣቱን ገልጻለች።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዓመት የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል ተማሪ መለሰ ጎበና በበኩሉ፣ እየሰጠ ያለው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከፈጠረለት የህሊና እርካታ በተጨማሪ  የሥራ ፍቅር እንዲያድርበት ማድረጉን ገልጿል ።

"እንደወጣትነቴ ለሀገሬና ለወገኔ  የበኩሌን ማድረጌ የህሊና ነፃነት ሰጥቶኛል" በማለትም የሚሰጠው አገልግሎት የፈጠረለትን ስሜት ተናግሯል። 

የበደሌ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ቤኛ በበኩላቸው፣ እንዳሉት ከሐምሌ ወር 2009 አጋማሽ ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የበጎ ፈቃድ ሥራ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ 6 ሺህ 700 ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ወጣቶቹ እስካሁን ከ2 ሺህ በላይ ችግኞችን በመትከል፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመስራት እንዲሁም ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ዳርቻ ማጽዳትን ጨምሮ በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና በቄለም ወለጋ ዞን በተያዘው ክረምት 145 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ ተረፈ እንዳሉት፣ ወጣቶቹ ከሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ የተሰማሩት በደምቢ ዶሎ ከተማ አስተዳደርና በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች ነው ።

ወጣቶቹ በአገሪቱ ከሚገኙ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ናቸው።

"የአካባቢ ጽዳት፣ የችግኝ ተከላና እንክብካቤ፣ የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታና ዕድሳት፣ ሰብል ማረምና መንከባከብ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎችን ማዘጋጀትና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ወጣቶቹ እያከናወኗቸው ካሉ ተግባራት ይጠቀሳሉ "ብለዋል ።

ከወጣቶቹ መካከል ከአዋሳ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀችውና የደምቢ ዶሎ ከተማ ቀበሌ 07 ነዋሪ ተማሪ ኩመሺ ሱራጋ " ሕብረተሰቡን በዕውቀቴና በጉልበቴ በማገልገሌ ደስተኛ ነኝ " ብላለች ።

በዞኑ ላሎ ቅሌ ወረዳ ቀበሌ 01 ነዋሪና ከዳንዲ ቦሩ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዲፕሎማ የተመረቀው ተማሪ ተስፋ በቀለ በበኩሉ በሳምንት ሁለት ቀን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣቱ እንዳለው በቅርቡ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በአካባቢያቸው በሁለት ሄክታር መሬት ላይ የችግኝ ተከላ አከናውነዋል። 

የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ኬኔሣ ጆፌ በበኩሉ በከተማ ጽዳት፣ በተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት፣ የጎርፍ መውረጃ ትቦዎችን በመስራትና በሌሎች መሰል ሥራዎች ላይ እርሱን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን ተናግሯል።

ይህም ከፈጠረለት ውስጣዊ ደስታ ባለፈ በጎ አገልግሎትን ባህሉ እንዲያደርግ መሰረት እንደሚሆነው ጠቁማል። 

በዞኑ ባለፈው ክረምት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሳተፉ ከ141 ሺህ በላይ ወጣቶች 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የልማት ሥራዎችን ማከናወናቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሀሴ1/2009 የአዲስ አበባ ደረጃ "ሐ" የግብር ከፋዮች የግብር መክፈያ ቀን ለተጨማሪ 10 ቀናት ተራዘመ።

በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሰልጣን የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የደንበኞች አገልግሎትና የትምህርት ዳይሬክተር አቶ ቶሉ ፊጤ ለኢዜአ እንደገለጹት ከቀን ገቢ ግምታው ቅሬታ ጋር በተፈጠረው የስራ ጫና እና በግብር ከፋዮች ይራዘምልን ጥያቄ መሰረት ጊዜው ተራዝሟል።

እንደ አቶ ቶሉ ገለጻ "ነጋዴዎቹ እስከ ሃምሌ 30 መክፈል ያለባቸው ቢሆንም ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመመካከር እስካሁን ባልከፈሉ ነጋዴዎች ላይ ቅጣት ከመጣል ይልቅ የመክፈያ ጊዜው እስከ ነሐሴ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም ተወስኗል።"

በከተማዋ ካሉት 59 ሺህ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ውሰጥ እስካሁን ከ48 ሺህ በላይ ያህሉ የከፈሉ ሲሆን ይህም በመቶኛ ሲታይ 82 በመቶዎቹ ዓመታዊ ግብራቸውን መክፈላቸውን ተናግረዋል።

ግብር ከፋዮች አላስፈላጊ ለሆነ ቅጣት ላለመዳረግ ዛሬን ጨምሮ ባሉት ቀናት ውስጥ ግብራቸውን እንዲከፍሉ ባለስልጣኑ ጥሪውን አስተላልፏል።

የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች ደግሞ ከዛሬ ነሐሴ 1 እስከ 30 2009 ዓ.ም ግብር መክፈያ ጊዜ መሆኑን አውቀው በተቀመጠው መርሃ ግብር መሰረት እንዲከፍሉ አቶ ቶሉ ፊጤ አሳስበዋል።

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ነሀሴ 1/2009 በጤናው ዘርፍ የሚያተኩሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ከምርምሮቹ ጥቅም መኖርና አለመኖር ወይም አጥኝዎች ከፖሊሲ አውጭዎች ጋር ተቀራርቦ ባለመስራት በርካታ ገንዘብ ወጪ ሆኖባቸው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ይቀራሉ።

ሚኒስቴሩ እነዚህን ችግሮች በመረዳት ከሁለት ዓመት በፊት"የጥናትና ምርምር አማካሪዎች ካውንስል"  አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አመልክቷል፡፡

በዚሁ ካውንስል ውስጥም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ዬኒቨርሲቲና በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ ተቋማት ተመራማሪዎችና አማካሪዎች ይሳተፉበታል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ የጥናትና ምርምር አማካሪዎች ካውንስልን የመጀመሪያ ጉባኤ ሲከፍቱ እንደገለጹት የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ አገሪቱ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ለማሳካት በጤናው ዘርፍ የሚያተኩሩ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ጥቅም ላይ መዋል ይገባቸዋል።

በዘርፉ የሚደረጉ ጥናትና ምርምሮች ችግሮችን የሚለዩ ፣ መፍትሄ የሚጠቁሙና መፍትሔዎቹም በአግባቡ መፈጸም አለመፈፀማቸው ክትትል ለማድረግ የሚያግዙ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጭዎችና አስፈጻሚው አካል ተቀራርበው የሚሰሩበትን አለም አቀፋዊ ልምድ በመውሰድ በእናቶችና ህጻናት ጤና እና አመጋገብ ስርዓት ላይ ለውጥ ማምጣት ያስችላል።

በአገሪቱ ዱቄትን በአዮዲን ማበልጸግ ያልተለመደና በተመራማሪዎች ዘንድም ልዩነት እንደነበር ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ዱቄትን በአዮዲን አበልፅጎ መጠቀም ለእናቶችና ጨቅላ ህጻናት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው አመልክተዋል።

"በአደጉ አገራት በወሊድ ምክንያት  ከ 100 ሺህ  እናቶች መካከል የሚሞቱት ከ10 በታች ናቸው፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከ 100 ሺህ እናቶች 350 ዎቹ ለህልፈት ይዳረጋሉ። እነዚህ ችግሮች የሚፈቱት የአገልግሎት ጥራቱን ማሻሻል ስንችል ነው" ብለዋል።

በተጨማሪም በአገሪቱ የአምስት ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ ከሚሞቱ ሕፃናት መካከል 42 ከመቶ የሚሆኑት አንድ ወር ለሚሞላ ጊዜ እንኳ በህይወት እንደማይቆዩ ነው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው። 

የአማካሪ ካውንስሉ አበርክቶ

በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህፃናት ዳይሬክተር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ በዚሁ ወቅት እንደገጹት ካውንስሉ መንግስት በቀረፃቸው የእናቶችና ህፃናት ጤና ፣የስነ ምግብ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ በምርምር የተደገፈ ግብዓት እንዲሰጥና እንዲያማክር የተቋቋመ ነው ብለዋል።

አማካሪ ካውንስሉ በስሩ ያሉት ስድስት ቡድኖች እያንዳንዳቸው አንድ ጉዳይ ላይ እንዲያማክሩና ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መግለጫ እንዲሰጡ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።

ህጻናት ለሚደርስባቸው የኢንፌክሽን ህመም ለሰባት ቀናት መድሃኒት ይወስዱ እንደነበርና አማካሪ ካውንስሉ የተለያዩ ጉዳዩችን ተመልክቶ ለሁለት ቀን ብቻ መውሰዳቸው በቂ እንደሆነ አሳይቶናል ብለዋል።

በወሊድ ወቅት በእናቶች ላይ የሚከሰተውን ከፍተኛ የደም መፍሰስ ለመከላከል በጥናትና ምርምር የተደገፈ ግብዓት እንዲያቀርብ ተጠይቆ ለውጦች መምጣቻቸውንም ነው ያስታወቁት።

እነዚህና ሌሎችም ለውጦች የአማካሪ ካውንስሉ የሚሰጣቸውን ግብዓቶች መነሻ በማድረግ የተወሰዱ እርምጃዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ በበኩላቸው የአማካሪ ካውንስሉ መቋቋም ተመራማሪዎችና ፖሊሲና ስትራቴጂ አውጭዎች ተቀራርበው እንዲሰሩ ያግዛል ብለዋል።

በተለያዩ ተቋማት በርካታ ገንዘብ ወጪ ሆኖባቸው ነገር ግን አገልግሎት የማይሰጡ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ስራ ላይ ለማዋል በር ይከፍታልም ነው ያሉት።

የትምህርትና የምርምር ተቋማት ከአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው ችግር ፈቺ  ጥናትና ምርምር የሚያደርጉበትን መንገድ እንደሚያመቻችም ነው የጠቆሙት።

 

Published in ማህበራዊ

ሰመራ ነሀሴ 1/2009 በአፋር ክልል በአዋሽ ፈንታሌና በረሀሌ ወረዳዎች በተያዘው በጀት ዓመት የቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ መርሀግብር በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚደረግ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መሃመድ ሁሴን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በመርሀግብሩ 1ሺህ 500 አርብቶ አደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ።

በመርሃግብሩም አርብቶ አደሮቹ የገንዘብ ብድር ተሰጥቷቸው በአማራጭ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው የኑሮ ለውጥ እንዲያመጡ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

"እንስሳት እርባታ፣ ግብርናና ንግድ አርብቶአደሮቹ ከሚሰማሩባቸው ዘርፎች ተጠቃሽ ናቸው" ያሉት ኃላፊው፣ በየአካባቢያቸው ባሉ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚደረግበት ሁኔታ መኖሩንም ጠቁመዋል ።

አቶ መሀመድ እንዳሉት፣ ሁለቱ ወረዳዎች ባላቸው ዝግጅት፣ የማስፈፀም አቅምና አካባቢያቸው ባለው አመቺ ሁኔታ ለመርሀግብሩ ትግበራ በቅድሚያ ተመርጠዋል።

መርሀግብሩን ለማስጀመር በአሁኑ ወቅት ከክልል እስከ ወረዳ የባለሙያ ቅጥር መካሄዱንና ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅሰዋል ።

መርሀግብሩ የአንድ ዓመት የሙከራ ትግበራ ውጤታማነት ተረጋግጦ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የማስፋፋት ሥራ እንደሚሰራም ኃላፊው አመልክተዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ለመርሀ ግበሩ ማስፈፀሚያ ከክልሉ መንግስት  ሰድስት ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል።

የአዋሽ ፈንታሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባህአባ ሁሴን በበኩላቸው፣ "በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ መርሀግብር የሚታቀፉ አርብቶአደሮች በሚሰጣቸው የገንዘብ ብድርና ስልጠና ተጠቅመው ከተረጂነት እንዲላቀቁ ድጋፍና ክትትል ይደረግላቸዋል" ብለዋል።

ለዚህም የወረዳው አመራር ስራውን በባለቤትነት በመምራት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው፣ በአሁኑ ወቅት በመርሀግብሩ አተገባበር ላይ ከሕበረተሰቡ ጋር ውይይት መጀመሩን አስታውቀዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 1/2009 ሶማሊያ የኢትዮጵያን ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር በተሞክሮነት መውሰድ እንደምትፈልግ አስታወቀች።

የሶማሊያ መንግስት ልዑካን ቡድን ከኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት፣በገቢ አሰባሰብ፣ ከተማ ልማት፣የግጭት አፈታትና የፌደሬሽን ምክር ቤት አወቃቀር ላይና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ልምድ ለመቅሰም ዛሬ አዲስ አበባ ገብቷል።

የሶማሊያ የአገር ውስጥና የፌደራል ዕርቀ ሰላም ሚኒስቴር ቋሚ ፀሐፊ አብዱላሂ ሞሃሙ የተመራ ልዑክ ቡድን በፌደራል ስርዓት አወቃቀር፣ ሂደትና ፋይዳ ዙሪያ ከፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር ተወያይቷል።

ቋሚ ፀሐፊው ከዚህ ቀደም ስለፌደራል ስርዓት ልምድ ለመውሰድ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ ያሁኑ የአገሪቱ የፌደራልና ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተካተውበት ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በሶማሊያ ሽብርተኝነትን  ለመዋጋትና ዘላቂ ሰላም ለማስከበር የፌደራላዊ ስርዓት አስፈላጊ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።

የፌደራል ስርዓት በሶማሊያ ገና ጅምር ላይ መሆኑን የተናገሩት ቀሚ ፀሐፊው፤ የሶማሊያ መንግስት ይህን ስርዓት ለማጠናከር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

"ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው ይህ ልምድ የመቅሰም ጉብኝትም አንዱ ማሳያ ነው" ብለዋል።

ለልዑኩ አቀባበል ያደረጉት የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ውለታው በበኩላቸው በኢትዮጵያ የፌደራል ስርዓት ተግባራዊ መደረጉ  አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ምዕራፍ መክፈቱን አብራርተዋል።

"የፌደራላዊ አስተዳደር ስርዓት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ከ76 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰቦች በሰላምና በአንድነት  እንዲኖሩ አስችሏል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የራሷን የዕድገት ራዕይ በማስቀመጥ  በኢኮኖሚው ዘርፍ አበረታች ወጤት ማስመዝገቧን የተናገሩት አቶ ሙልጌታ ለውጤቱ የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ በስርዓቱ መፈታቱ መሆኑንም አመላክተዋል።

ይሁንና አሁንም 23 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ከድህነት በታች እንደሚኖርና የእነዚህን ዜጎች ኑሮ ለማሻሻል መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአገሪቱ እየተስፋፋ የመጣው የሙስና አመለካከትና ተግባርም ሌላኛው የስርዓቱ ተገዳሮት መሆኑን ጠቁመዋል።

ሶማሊያ ልምድ ልውውጧን ለማድረግ ኢትዮጵያን ምርጫዋ ማድረጓ ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንደሚመልሳት ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

የልዑካን ቡድኑ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት በአዲስ አበባ፣ ትግራይና አማራ ክልሎች በመዘዋወር ተሞክሮዎችን እንደሚቀስም የልዑካን ቡድኑ ፕሮግራም ያመላክታል።

Published in ፖለቲካ
Published in ቪዲዮ

አዲስ አበባ ነሀሴ1/2009 በለንደኑ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የብር ሜዳሊያ ያስገኘው አትሌት ታምራት ቶላ ከዚህ በኋላ ትኩረቱን ከማራቶን ይልቅ በ10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ እንደሚያደርግ ተናገረ።

አትሌቱ ይህን ያለው ከማራቶን ውድድሩ በኃላ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ነው።

በማራቶን ውድድሩ በኬንያዊው አትሌት ኪሩ ኪፕኮረር ተቀድሞ ሁለተኛ የሆነው አትሌት ታምራት በማራቶን የመሳተፍ ፍላጎቱ አነስተኛ እንደሆነ ነው የተናገረው።

አትሌቱ የትናንቱን የማራቶን ውድድር በቀዳሚነት ሲመራ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻ በኬንያዊው አትሌት ሊቀደም ችሏል።

ታምራት ውድድሩን ሲመራ ቆይቶ ወደኋላ እንዲቀር ያደረገው በእግሩ ላይ የነበረ የቆየ ህመም በድጋሚ ስለተሰማው እንደሆነ ገልጿል።

ከቆየ የእግር ህመሙ ጋር ታግሎ በማሸነፍ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ታምራት በቀጣይ አገሩን በሚወክልባቸው ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከማራቶን ይልቅ ትኩረቱ በ10 ሺህ ሜትር እንደሚሆን ነው የተናገረው።

''የእግሬ ላይ ህመም በደንብ ከተሻለኝ ወደ 10 ሺህ ሜትር ነው የማደላው፤ ምክንያቱም በፊትም የምወደው 10 ሺህ ሜትር ነው'' ብሏል።

አትሌት ታምራት ኢትዮጵያ በ10 ሺህ ሜትር እያጣች ያለውን ድል አስመልክቶ ''የወንዶች 10 ሺህ ሜትር የውጤት መቀዛቀዝ እየታየ ያለው በ10 ሺህ ሜትር ላይ የቤት ስራችንን ስላልሰራን ነው'' ሲል አስተያየት ሰጥቷል።

''እነ ሞ ፋራህ የሚያሸንፉት በደንብ ስለሰሩ ነው፣ ስለዚህ ኢትዮጵያም በ10 ሺህ ሜትር ወንዶች በደንብ መስራት አለባት'' ሲል ሀሳቡን ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ አራተኛ ቀኑን በያዘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአንድ ወርቅና በሁለት ብር በደረጃ ሠንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2009 በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ተጨማሪ ሜዳሊያ ታገኝበታለች ተብሎ የሚጠበቀው የሴቶች 1ሺህ 500 ሜትር  የፍጻሜ ውድድር ዛሬ ይካሄዳል።

በለንደን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አራተኛ ቀኑን ይዟል።

ዛሬ ከምሽቱ 5 ሰአት 50 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው ውድድር ገንዘቤ ዲባባ ከፍተኛ የማሸነፍ ቅድሚያ ተሰጥቷታል።

በ1ሺህ 500 ሜትር የፍጻሜው ውድድር 12 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን አትሌት ገንዘቤ ኢትዮጵያን ወክላ የምትሳተፍ ብቸኛ አትሌት ናት።

ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የግማሽ ፍጻሜ የማጣሪያ ውድድር ተሳታፊ የነበሩት ጉዳፍ ፀጋይና በሱ ሳዶ ወደ ፍጻሜው ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ዛሬ ማምሻውን በሚደረገው ውድድር አትሌት ገንዘቤ ዲባባ ከደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ካስተር ሴሜኒያና በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ ከሆነችው ሲፋን ሀሰን ጋር ብርቱ ፉክክር እንደምታደርግ ይጠበቃል።  

ከሁለት ዓመት በፊት በቤጂንግ በተካሄደው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ገንዘቤ ዲባባ አራት ደቂቃ ስምንት ሰከንድ ዘጠኝ ማይክሮ ሰከንድ በማስመዝገብ አንደኛ መውጣቷና የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

ነገ በሚካሄደው የ800 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት መሐመድ አማን፣ በ3ሺህ ሜትር መሰናክል ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ደግሞ አትሌት ጌትነት ዋሌ፣ ታፈሰ ሰቦቃና ተስፋዬ ድሪባ ይሳተፋሉ።

በ10 ሺህ ሜትር የሴቶች ውድድር አልማዝ አያና አንደኛ በመውጣት የወርቅ ጥሩነሽ ዲባባ ሁለተኛ ወጥታ የብር ሜዳሊያ ለአገራቸው አስገኝተዋል።

ትናንት በተካሄደው የወንዶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያ በአትሌት ታምራት ቶላ አማካኝነት የብር ሜዳልያ አግኝታለች።

በ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ አሁን በተደረጉ ውድድሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ 10 አገራት የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ መግባት ችለዋል።

አራተኛ ቀኑን በያዘው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አንድ የወርቅና ሁለት የብር ሜዳሊያ በማግኘት አሜሪካን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ ነሐሴ 7 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል።

Published in ስፖርት
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን