አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 06 August 2017

ድሬዳዋ ሀምሌ30/2009 በድሬዳዋ አስተዳደር የአስፓልት ኮንክሪት መንገዶች ግንባታ መጓተት ለተለያዩ ችግሮች  እያጋለጣቸው  መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ ።

የከተማው መንገዶች ባለስልጣን በበኩሉ መንገዶቹ በሚሰሩበት ሥፍራ ንብረቶችን ለማንሳት የፈጀው ጊዜ ግንባታው በወቅቱ እንዳይጠናቀቅ ምክንያት መሆኑን አስታውቋል።

በከተማው የሳቢያን ጎሮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መብራቱ አየለ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት፣ "ለመንገዱ ሥራ ከተቆፈረው መሬት በፀሐይ ወቅት የሚነሳው አቧራ ለጤና ችግር አጋልጦናል " ብለዋል ።

በተጨማሪም መንገዱ ለተሽከርካሪ አመቺ ባለመሆኑ ለታክሲ ትራንስፖርት ተጨማሪ ክፍያ እንዲከፍሉ እያደረጋቸው መሆኑን ገልፀዋል።

የመንገዱ ግንባታ መጓተት አሁን በክረምቱ ለጎርፍ አደጋ እያጋለጣቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ ነዋሪ ወይዘሮ ዘሀራ ሁሴን ናቸው።

"መንገዱ በመቆፋፈሩና  የውሀ  ማፋሰሻ የተሰራለት ባለመሆኑ ወደ መኖሪያ ቤቴ የሚገባ ጎርፍ ለችግር እየዳረገኝ ነው " ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል ።

በከተማው የታክሲ አሽከርካሪ አቶ ሰለሞን ካሳሁን በበኩላቸው አንዳሉት " የመንገዶቹ ግንባታ በፍጥነት አለመጠናቀቁ በተሽከርካሪና እግረኛ እንቅሰቃሴ ላይ መጨናነቅ በመፍጠር የአደጋ ተጋላጭነት እንዲጨምር አድርጓል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በተለያዩ አቅጣጫዎች የከተማውን መንገድ በተሻለ አስፓልት ለማሳደግ የተጀመረው የአስፓልት ግንባታ ሥራ የነዋሪውን ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግር የሚቀርፍ በመሆኑ በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የሚመለከተው አካል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ።

የድሬዳዋ መንገዶች ባለስልጣን የዲዛይን ዝግጅት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ቢኒያም ታምራት ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ አስተዳደሩ በመደበው 310 ሚሊዮን ብር ወጪ 7 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የተለያዩ የአስፓልት ኮንክሪት  መንገዶች በመገንባት ላይ ናቸው።

ከመንገዶቹ ውስጥ በሰኔ 2007 ዓ.ም በ205 ሚሊዮን ብር የኮንትራት ውል ተፈርሞ  ሥራው የተጀመረውና በከተማው በሁለት አቅጣጫ እየተገነባ ያለው  የ5 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር መንገድ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

የመንገዱ ግንባታ በአሁኑ  ወቅት 59 በመቶ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና መጠናቀቅ ካለበት ጊዜ በአንድ ዓመት መዘግየቱን ገልፀዋል።

መንገዶቹ በሚገነቡበት ስፍራ የነበሩ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የውሃና የስልክ መስመሮችን ካሳ ከፍሎ ለማንሳት ረዥም ጊዜ በመፍጀቱና የተቋራጩ ዝግጅት ማነስ ለግንባታው መጓተት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

ይሁንና ግንባታውን በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ መንገዶቹን ሥራ ለማስጀመር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አቶ ቢኒያም ተናግረዋል ።

ሌላው ፕሮጀክቱ አካል የሆነውና ከራስ ሆቴል እስከ ፈረንሳይ ሆስፒታል አደባባይ እየተገነባ የሚገኘው የ1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ በተቀመጠው የጊዜ ገድብ ውስጠ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

"በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት በአካባቢው አሁን እየታየ ያለወን የትራፊክ መጨናነቅ ያስቀራል" ብለዋል።

እንደ አቶ ቢኒያም ገለጻ በመንገዶቹ ግንበታ ሳቢያ ጎርፍ በነዋሪዎች ላይ ችግር እንዳያስከትል የውሃ መውረጃ ቦዮችን የማጽዳት፣ የጎርፍ አቅጣጫን የማስቀየርና የማፋሰሻ ሥፍራዎች ከፍታ የማሳደግ ሥራ እየተሰራ ይገኛል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2009  የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የሙያ መስኮች በዲግሪና በደረጃ ያሰለጠናቸውን 702 ተማሪዎች አስመረቀ።

 በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ መዓዛ ገብረመድኅን “የሆቴልና ቱሪዝም ልማት ዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል መመራት አለበት” ብለዋል።

 ተማሪዎቹ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ በመሆናቸው ሲመለሱና የባህልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በሚቀላቀሉበት ወቅት አገሪቱ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም እንደሚረዳ ገልጸዋል።

 ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም ዘርፉ ብዙ የሰው ኃይል የሚይዝና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ጉልህ ሚና እንዳለውም ነው የገለጹት።

 ኢንስቲትዩቱ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የሰው ኃይል ማሰልጠን ከጀመረ 48 ዓመታትን አስቆጥሯል።

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 30/2009  የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢሰዴፓ/ 7ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ አካሄደ።

 ጉባዔው ፓርቲውን ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚመሩ አመራሮችን መርጧል።

 ፓርቲው አቶ ሰኢድ ኡመር አሊን ሊቀ-መንበር ሆነው እንዲቀጥሉ፣ አቶ ዘሪሁን አባተ ደግሞ ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ፓርቲውን እንዲመሩ መርጧቸዋል።

 ኢሰዴፓ በአገራዊ ጉዳዮች ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር እንደሚሰራም አስታውቋል። 

 የፓርቲው ሊቀ-መንበር አቶ ሰኢድ ኡመር አሊ፣ "ፓርቲው በ1986 ዓ.ም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶት ለዴሞክራሲ ግንባታ በሰላማዊ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል" ነው ያሉት።

 የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን እንደሚታገሉና ለሀገሪቷ የዴሞክራሲ ግንባታ ከገዢው ፓርቲ ጋር በመተባበር እንደሚሰሩም ነው የተናገሩት።

 ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የሀገሪቷ አካባቢዎች ተከስተው የነበሩ አለመረጋጋቶችን ለመፍታት መንግሥት ያደረገውንና እያደረገ ያለውን ጥረት ፓርቲያቸው እንደሚደግፍም ገልጸዋል።

 የኢትዮጵያ ሰላማዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ከኢህአዴግ ጋር ከሚደራደሩ 17 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ነው።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 30/2009  የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈፃፀም 60 በመቶ መድረሱ ተገለጸ።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የግድቡን የሲቪል የሃይድሮ እና ኤሌክትሮ መካኒካል የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላም ከሁለቱ ተቋራጭ ኩባንያዎችና አመካሪ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር በአሁኑ ወቅት ግድቡ በደረሰበትና በቀጣይ የስራ እንቅስቃሴ ላይ ውይይት አድርገዋል።

የግድቡ የሲቪልና መካኒካል ስራ በበጋ ወቅት እንደነበረው አሁንም በክረምት ወቅት መቀጠሉን ዶክተር ደብረፅዮን ጠቁመው የክረምቱን ስራ ልዩ የሚያደርገው የጎርፉን ሁኔታ አስቀድሞ በመገንዘብ በጥንቃቄ እየተሰራበት መሆኑ ነው  ብለዋል።

ሰራተኛውና ተቋራጮቹ  የግድቡን ስራ በታቀደው ደረጃ በማስኬድ በህዝብና በመንግስት የተጣለባቸውን አደራ በኃላፊነት በመወጣት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ፤ የግድቡ ግንባታ በጥራትና በብቃት እየተከናወነና በአሁኑ ወቅት በዚሁ ፍጥነት ኃይል ወደ ሚያመነጭበት ምዕራፍ በመጠጋት ላይ ነው። '' ኃይል ለማመንጨት አልመን እየሰራን እንደመሆናችን ወደ ቅድመ ኃይል ማመንጨት ለመግባት ስራው በተፋጠነ መልኩ እየተካሄደ ነው'' ሲሉ ዶክተር ደብረፅዮን ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት በመንግስት ደረጃ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር በተገለጸው መሰረት ይህን በተግባር መሬት ላይ ለማረጋገጥ ስራው እየተከናወነና እየታየ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ ዓመት ባለፈው መጋቢት 27 መከበሩ የሚታወስ ነው።

Published in ኢኮኖሚ

መቱ  ሀምሌ 30/2009 በቡኖ በደሌ ዞን በደሌ ከተማ በመደበኛውና በልዩ ፈንድ ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ወጣቶች ራሳቸውን ለመለወጥ እየሰሩ መሆናቸውን ገለፁ።

በተጠናቀቀው በጀት አመት በማህበር የተደራጁ  ከ54 ሺህ በላይ ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉን የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ወጣት ብርሀኑ ታምሩ በበደሌ ከተማ መንግስት በመደበው የወጣቶች ፈንድ ተደራጅተው ወደ ሥራ ከገቡ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡

እርሱ እንደሚለው ከሦስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ባገኙት የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ብድር በልብስ ስፌት ሥራ በመሰማራት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

"ወደ ፊት አቅማችንን  በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር ዓላማ ሰንቀን እየሰራን ነው" የሚለው ወጣቱ፣ ለእዚህም እርሱን ጨምሮ የማህበሩ አባላት ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥራ በማዋል ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

በከተማው የቀበሌ 02 ነዋሪ ወጣት ትዕግስት እንዳለ በበኩሏ፣ ከሌሎች አራት ጓደኞቿ ጋር በመሆን ተደራጅተው በብድር ባገኙት 100 ሺህ ብር በምግብ ቤትሥራ ተሰማርተው ራሳቸውን ለመቀየር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጻለች።

እንደ ወጣቷ ገለጻ የማህበሩ አባላት ወደ ከፍተኛ የንግድ ሥራ በመሸጋገር ለሌሎች ወጣቶች አርአያ የመሆን ራዕይ ይዘው በመስራት ላይ ናቸው፡፡

"ወደዚህ ሥራ ሳልገባ በፊት ምንም ሥራ አልነበረኝም" የምትለው ወጣቷ በአሁኑ ወቅት በወር ከሚያገኙት ገቢ መቆጠብ መጀመራቸውን ትገልጻለች፡፡

የዞኑ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ በፈቃዱ በበኩላቸው እንዳሉት በእዚህ ዓመት የበደሌ ከተማን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ከ51ሺህ በላይ ወጣቶች በ4 ሺህ ማህበራት ተደራጅተው ወደሥራ ገብተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ወጣቶቹ በገጠርና ከተማ ወደ ሥራ የገቡት በመደበኛና መንግስት ለወጣቶች በመደበው ልዩ የገንዘብ ብድር በመታገዝ ነው ።

ወጣቶቹ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ የሙያ ስልጠናዎች እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡

አቶ ግርማ እንዳሉት፣ ወጣቶቹ በመደበኛውና ልዩ ፈንድ ከተመደበላቸው ገንዘብ ውስጥ እስካሁን ከ55 ሚሊዮን ብር በላይ በብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተድርጓል።

በበጀት ዓመቱ በማህበር ተደራጅተው ወደ ሥራ ለገቡ ወጣቶች በዞኑ በመንግስት መስሪያ ቤቶች እየተካሄዱ ባሉ ግንባታዎችና ከአርጆ ዴዴሳ የስኳር ፕሮጀክት ጋር ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር ተፈጥሮላቸዋል፡፡

በዞኑ በተያዘው የ2010 በጀት ዓመትም ከ47 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት ወደ ሥራ ለማስገባት ከወዲሁ የተጠናከረ ሥራ መጀመሩን አቶ ግርማ አስታውቀዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

መቀሌ ሀምሌ30/2009 በመቀሌ ከተማ በወተት ሀብት ልማት ሥራ የተሰማሩ ሴቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገለፁ።

 የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በበኩሉ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።

 በመቀሌ ከተማ ሐውልቲ ክፍለከተማ የምትኖረው ወጣት ሳምራዊት ድምጹ በወተት ሀብት ሥራ  ከመሰማራቷ በፊት በተመረቀችበት የጋዜጠኝነት ሙያ ተቀጥራ ከ3 ሺህ ብር የማይበልጥ ደመወዝ ታገኝ እንደነበር ገልጻለች።

 ተቀጣሪ ሆና ከሁለት ዓመት በላይ እንዳልሰራች ያስታወሰችው ወጣቷ በ2004 ዓ.ም መደበኛ ሥራዋን ሳትለቅ ዶሮ የማርባት ሥራ መጀመሯን ተናግራለች።

 በእዚህም ገንዘብ አጠራቅማ በ2006 ዓ.ም አንድ ላም በ27 ሺህ ብር ገዝታ ወተትና የወተት ተዋፅኦ ምርቶችን ለገበያ የማቅረብ ሥራ መጀመሯን ገልጻለች።

  ወጣት ሳምራዊት እንዳለችው፣ በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ያሏትን ላሞች ቁጥር 17 የደረሱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ700 ሺህ ብር በላይ ካፒታል አስመዝግባለች።

 የተሰማራችበት የወተት ሀብት ልማት ሥራ ውጤታማ እያደረጋት መሆኑን የገለጸችው ሳምራዊት፣ ወጣቶች ሥራ ፍለጋ ወደውጭ ሀገር ከመሰደድ በአካባቢያቸው ያለውን የሥራ አማራጭ ቅድሚያ መፈተሽ እንዳለባቸው አስገንዝባለች።

 በቀጣይ የራሷን የወተት ሀብት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለሟቋቋም አቅዳ በመንቀሳቀስ ላይ መሆኗን የገለጸችው ወጣቷ፣ ሌሎች ወጣቶችም በእዚህ ሥራ በመሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መክራለች።

 በወተት ሀብት ልማት ሥራ ከተሰማሩት መካከል ወጣት ሚሚ ገብሩ በበኩሏ በ2002 ዓ.ም በማርኬቲንግ ማናጅመንት በዲግሪ ተመርቃ ሥራ ስትፈልግ ለሁለት ዓመታት መቆየቷን ተናግራለች።

 ከተመረቀች በኋላም ለሁለት ዓመት ከሦስት ወር ወደ አረብ አገር ብትሄድም ምንም ጥሪት ሳትይዝ ወደ አገርዋ መመለስዋን የገለጸችው ወጣቷ፣ ከቤተሰቦቿ ባገኘችው 20 ሺህ ብር ድጋፍ የወተት ላም ገዝታ ሥራ መጀመሯን ገልጻለች።

 ሥራን ሳይንቁ መስራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የገለጸቸው ወጣት ሚሚ ባለፉት ሁለት ዓመታት 470 ሺህ ብር ካፒታል ለማፍራት መቻሏን ተናግራለች።

 ወጣቶች በአካባቢያቸው ያሉትን የሥራ እድሎችና ምቹ የስራ ሁኔታ ሳይመለከቱ ወደ ውጭ አገር ተሰደው መሄዳቸው አግባብ አለመሆኑንም ተናግራለች።

 በ2008 ዓ.ም አንዲት የወተት ላም በመግዛት ሥራውን እንደጀመሩ የገለጹት ደግሞ በመቀሌ ከተማ የሚኖሩት ወይዘሮ መድህን ወልዱ  ናቸው።

 በአሁኑ ወቅት ሦስት ላሞችና ሁለት ጥጃዎች እንዳሏቸውና በየቀኑም 400 ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 "ሥራው በቀላል ወጪ የሚሰራና ብዙ ድካም የማይጠይቅ ነው" ያሉት ወይዘሮ መድህን፣ ያለባቸው የቦታ ጥበት እንዲፈታ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋለ።

 በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የእንስሳትና አሣ ሃብት የቴክኖሎጂ ሽግግር ንዑስ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ተስፋማሪያም አሰፋ በክልሉ በየዓመቱ እስከ 800 ሚሊዮን ሊትር ወተት የማምረት አቅም እንዳለ ገልጸዋል።

 ይሁንና ሕብረተሰቡ በወተት ሀብት ልማት ሥራ ላይ ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆንና በተለያዩ ምክንያቶች እየተመረተ ያለው ያለው 559 ሚሊዮን ሊተር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

 ቢሮው በክልሉ ያለውን የወተት ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ካለፈው ዓመት ጀምሮ የእንስሳት ሃብት ያላቸውን በመለየትና የተሻሻሉ የወተት ዝርያዎችን በማቅረብ ቁጥራቸውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

 ወጣቶችና ሴቶች ቀደም ሲል በበግና ፍየል ማድለብ እንዲሁም በዶሮና በንብ እርባታ ሥራ ለመሰማራት ይመርጡ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተስፋማሪያም ካለፈው ዓመት ወዲህ በወተትና የወተት ተዋዕኦ ሥራ የሚሰማሩ ወጣቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ሐረር ሀምሌ 30/2009 በሐረር ከተማ በተለያዩ ጊዜያት የእሳት ቃጠሎ በደረሰባቸው የንግድ ቦታዎች በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ የገበያ ማዕከላትን መልሶ የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው  ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱልማሊክ እንደገለጹት፣ የገበያ ማዕከላቱ ግንባታ እየተካሄደ ያለው በከተማው በተለምዶ ሸዋበርና ሲጋራ ተራ ተብለው በሚጠሩ የንግድ ቦታዎች ላይ ነው ።

የንግድ ማዕከላቱ ግንባታ እየተከናወነ ያለውም ቀደም ሲል በንግድ ቦታዎቹ ላይ ንብረታቸው የወደመባቸው ነጋዴዎች ለክልሉ መንግስት ባቀረቡት የመልሶ ማልማት ጥያቄ መሰረት ነው ።

በግንባታ ላይ ያሉት የንግድ ማዕከላት 13 ባለ ስምንት ፎቅ ሕንጻዎች ሲሆኑ በአጠቃላይ ሁለት ሺህ 600 የንግድ ሱቆች እንዳላቸው ታውቋል።

የንግድ ማዕከላቱ ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ መድረሱንና በተያዘው 2010 በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ አቶ አብዱልሃኪም ተናግረዋል።

በግንባታው በመሳተፍ ላይ ካሉት ማህበራት መካከል የሐረር አንድነት ገንዘብና ቁጠባ ማህበር ጸሐፊ አቶ አብደላ ቱሴ እንዳሉት የ11 ሚሊዮን ብር ኮንትራት ውል በመውሰድ 222 ክሎች ያሉት ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ግንባታ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በግንባታ ሥራው ከ100 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ  የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አመልክቷል።

የኮኮብ ሸዋበር የንግድ ቤቶች ሕብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አበራ ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ "በቃጠሎ ጉዳት የደረሰብን 343 ነጋዴዎች በማህበር ተደራጅተን በ27 ሚሊዮን ብር ባለስምንት ፎቅ ሕንጻ እየገነባን ነው " ብለዋል።

በገበያ ማዕከላቱ ግንባታ ሥራ ላይ በአናጺነት ሙያ እየሰራ የሚገኘው ወጣት ሙሉጌታ ሻንበል በበኩሉ፣ በቀን 200 ብር እየተከፈለው በመስራት ላይ መሆኑንና ይህም ተጠቃሚ አንዳደረገው አስረድቷል።

በሐረር ከተማ ሸዋበር፣ ሲጋራ ተራና መብራት ሐይል በተባሉ የንግድ ስፍራዎች በ2003 እና  በ2006 ዓ.ም በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ይታወሳል ።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሐረር ሀምሌ 30/2009 በሐረር ከተማ በተለያዩ ጊዜያት የእሳት ቃጠሎ በደረሰባቸው የንግድ ቦታዎች በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ የገበያ ማዕከላትን መልሶ የመገንባት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው  ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልሃኪም አብዱልማሊክ እንደገለጹት፣ የገበያ ማዕከላቱ ግንባታ እየተካሄደ ያለው በከተማው በተለምዶ ሸዋበርና ሲጋራ ተራ ተብለው በሚጠሩ የንግድ ቦታዎች ላይ ነው ።

የንግድ ማዕከላቱ ግንባታ እየተከናወነ ያለውም ቀደም ሲል በንግድ ቦታዎቹ ላይ ንብረታቸው የወደመባቸው ነጋዴዎች ለክልሉ መንግስት ባቀረቡት የመልሶ ማልማት ጥያቄ መሰረት ነው ።

በግንባታ ላይ ያሉት የንግድ ማዕከላት 13 ባለ ስምንት ፎቅ ሕንጻዎች ሲሆኑ በአጠቃላይ ሁለት ሺህ 600 የንግድ ሱቆች እንዳላቸው ታውቋል።

የንግድ ማዕከላቱ ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ መድረሱንና በተያዘው 2010 በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ አቶ አብዱልሃኪም ተናግረዋል።

በግንባታው በመሳተፍ ላይ ካሉት ማህበራት መካከል የሐረር አንድነት ገንዘብና ቁጠባ ማህበር ጸሐፊ አቶ አብደላ ቱሴ እንዳሉት የ11 ሚሊዮን ብር ኮንትራት ውል በመውሰድ 222 ክሎች ያሉት ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ግንባታ እያካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በግንባታ ሥራው ከ100 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ  የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አመልክቷል።

የኮኮብ ሸዋበር የንግድ ቤቶች ሕብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አበራ ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ "በቃጠሎ ጉዳት የደረሰብን 343 ነጋዴዎች በማህበር ተደራጅተን በ27 ሚሊዮን ብር ባለስምንት ፎቅ ሕንጻ እየገነባን ነው " ብለዋል።

በገበያ ማዕከላቱ ግንባታ ሥራ ላይ በአናጺነት ሙያ እየሰራ የሚገኘው ወጣት ሙሉጌታ ሻንበል በበኩሉ፣ በቀን 200 ብር እየተከፈለው በመስራት ላይ መሆኑንና ይህም ተጠቃሚ አንዳደረገው አስረድቷል።

በሐረር ከተማ ሸዋበር፣ ሲጋራ ተራና መብራት ሐይል በተባሉ የንግድ ስፍራዎች በ2003 እና  በ2006 ዓ.ም በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ይታወሳል ።

Published in News

ሶዶ ኀምሌ 30/2009 በወላይታ ሶዶ ዞን ከ300 ሺህ በላይ ወጣቶች በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸውን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው የወጣቶች ማብቃት ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ሞሊሶ ቶሩ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ወጣቶቹ ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተዋል።

የከተማ ውበት ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤት መጠገን፣ የመንገድ ደህንነት ደንብን ማስከበር፣  የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ወጣቶቹ እየተሳተፉባቸው  ካሉ የሥራ መስኮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ከዚሁ ጎን ለጎን ወጣቶቹ የደም ልገሳ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በሶዶ ኢንፎሊኒክ ኮሌጅ የማናጅመንት ተማሪ ወጣት መስከረም ቡጡ 40 ወላጅ አልባና የጎዳና ተዳዳሪ ልጆችን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ገንዘብ ለማግኘት ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ሕብረተሰቡን የማስተባበር ሥራ እየሰራች መሆኗን ተናግራለች።

"እስካሁንም ሥራውን ለማስጀመርና ለመነሻ የሚሆን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በሕብረተሰቡ ድጋፍ እየተደረገልን ነው" ብላለች።

በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሦስኛ ዓመት የሶሺዮሊጂ ትምህርት ክፍል ተማሪ ዳዊት አበራ በበኩሉ "በበጎ አገልግሎት የተሰማራሁበት የአረጋውያን ቤት ዕድሳት ሥራ የህሊና እርካታ ሰጥቶኛል" ብሏል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 30/2009   የህግ  ታራሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ያገኙትን ስልጠና እና የሙያ ክህሎት ማህበረሰቡን ለመለወጥ  እንዲጠቀሙበት የፌደራል ማረሚ ቤቶች አስተዳደር ጠየቀ፡፡

በማረሚያ ቤቱ የሚገኘው ተስፋ ቴክኒክናሙያ ኮሌጅ ለ13ኛ ዙር በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣በሂሳብ ስራ በደረጃ ሶስት እና አራት እንዲሁም በተለያዩ አጫጭር የቴክኒክ ሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 606 የህግ ታራሚዎችና የማረሚያ ቤት አባላትን አስመርቋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ የተሃድሶ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ዋና ኦፊሰር ግርማ ታከለ  ታራሚዎች የእርምት ጊዜያቸውን ጨርሰው ከህብረተሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ወቅት ባገኙት ስልጠና እራሳቸውንና ማህበረሰባቸውን ከመጥቀም ባለፈ አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡

ያጋጠማቸውን የተለያዩ ችግሮች ተቋቁመው የተሰጣቸውን የቃልና የተግባር ስልጠና አጠናቀው ለምረቃ መብቃታቸውንም  አድንቀዋል፡፡

አቶ ግርማ ተመራቂዎች ከህብረተሰቡ ጋር በሚቀላቀሉበት ወቅት የወንጀልን አስከፊነት ለሌሎች ማስተማር እንዳለባቸው ገልጸው፤ ያገኙትን ትምህርትና የሙያ ክህሎት ይበልጥ ለማሻሻል ጥረት ማድረግ እንደለባቸው ተናግረዋል፡፡

በኮሌጁ በሂሳብ አያያዝ ሙያ የተመረቀው  ፈይራ በቀለ "ከማረሚያ ቤቱ የእርምት ጊዜዬን ስጨርስ በተመረቅኩበት ሙያ ህዝቤንና ሀገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ" ሲል ለኢዜአ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በኮሌጅ ቆይታው ከተሰጠው ስልጠና በተጨማሪ የሙያ ስነ-ምግባር ምን መምሰል እንዳለበት ልምዶችን የቀሰመበት እንደነበርም ጨምሮ ገልጿል፡፡

ኮሌጁ በአጫጭር የስልጠና መርሃግብር ካሰለጠናቸው መካከል በቆዳና ሌጦ ዘርፍ የተመረቀችው ማርታ ገብረህይወት በበኩሏ ኮሌጁ የተለያዩ ግባቶችን በሟሟላት በተግባር የተደገፈ ስልጠና እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው ገልጻለች፡፡ 

ኮሌጁ በዛሬው እለት ካስመረቃቸው 606 ሰልጣኞች መካከል 369 የህግ ታራሚዎች ሲሆኑ ቀሪዎች ደግሞ በማታው መርሃግብር የሰለጠኑ የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ናቸው፡፡

ከህግ ታራሚ ተመራቂዎች መካካልም  አጫጭር የሙያ ስልጠና መርሃ ግብር የተመረቁ 67 ሴቶች ይገኙበታል፡፡

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን