አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Saturday, 05 August 2017

አየለ ያረጋል-ኢዜአ

... ለአስራ ሁለት ዓመታት በተወሳሰበ የምስጢር ገመድ የተገመደ ቤተሰብ በውስብስብ ቅራኔና ጭቅጭቅ ባህር ውስጥ ሲዋኝ ይስተዋላል። ምስጢሩን በሚያውቁም በማያውቁም የቤተሰብ አባላት በቤተሰቡ ሳሎን እየተተወነ። በፍቅር አምድ እንደተመሰረተ የሚወራለት ቤተሰብም በአስራ ሁለት ዓመቷ ልጃገረድ ጥያቄ ቀስ በቀስ እየተቦረቦረ ሄደ። በመጨረሻም የቤተሰቡ ድብቅ ምስጢር ተመዘዘ፤ ዋጋም አስከፈለ። በርግጥ ቤተሰቡን በ'ግልጽነት' መንፈስ ህልውናወን ዳግም መገንባት ተቻለ...

ምሰጢርን አምቆ መያዝ ክፉኛ ይጎዳል፤ ካዋልከው ካሳደርከው ኪሳራ አለው። በግለሰብም፣ ቤተሰብ፣ በስራም ሆነ በማንኛውም ስፍራ ግልጽነት ከሌለ የውሸት ግድግዳ ሲናድ እውነት መውጣቱ አይቀርም። በጥቅሉ"ግልጽነት መልካም ወዳጅነትን ይፈጥራል" ይላል ጸኃፊ ተውኔት አንተነህ ጸጋዬ። "የድሬዳዋ ህዝብ 'ጣጣ የለውም ይባላል፤ ይህ ግን ሰውን ባለመጉዳት ነው። ለዚህም ነው 'ግልጽነት መልካም ወዳጅነት ይፈጥራል' በሚል ጭብጥ ላይ የሚያጠነጥነውን 'ካላአብራክ' ተውኔት የደረስኩት" በማለት ወጉን ይቀጥላል። ይህ ደግሞ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ትልቅ አበርክቶት ያደረገችውን ድሬዳዋ ያስተዋውቃል ባይ ነው።

አሥርት ዓመታት ሊደፍን ነው። በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ስር የተቋቋመው 'ሚሊኒየም የትያትርና የሙዚቃ ቡድን' ከተመሰረተ። ከሁለት ዓመታት በፊት ሁለት ጊዜ ለመድረክ በቅቶ የተቋረጠው የካላአብራክ ተውኔት አንዱ የቡድኑ ልፋት ውጤት ነው። አምስት ተዋንያን ይሳተፋሉ፤ በውጥንቅጥ ምስጢር በተተበተበው በዚህ ተውኔት። በተዋናዮች ተደራራቢ ሙያና ሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ ከመድረክ ገለል ብሎ መቆየቱን አቶ አንተነህ ያብራራል። ካላብራክ ግን ከድሬ/ከዚራ አዋሽን ተሻግሮ ሸገር ላይ ትናንት ተመርቋል። የብሔራዊ ትያትር ታዳሚያንንም አስጨብጭቧል፤ አስፈንድቋል፤ በሐሴት አስጩኋል።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ብሔራዊ ትያትር በባለሙያ ዓቅም ግንባታ ረገድ በጋራ ለመስራት ቀደም ሲል ተዋውለዋል። እናም የካላአብራክ ከዚህ መድረስ የብሔራዊ ትያትር ባለሙያዎች ድጋፍም ነበረበት። የቢሮው ኃላፊ አቶ ሙራድ በደዊ፤ 'ተውኔቱ የስምምነቱ ፍሬ ነው' ይላሉ። በአገር ደረጃም ቢሆን ለኪነ ጥበቡ እድገት ድሬዳዋ ትልቅ ሚና እንደተጫወተችም ያብራራሉ። በትያትሩ ዘርፍ ግን መቀዛቀዝ እንደሚስተዋል አውስተዋል፤ 'ይህ ተውኔት በብሔራዊ ትያትር መድረክ መቅረቡ ለአማተር ተዋናይ ወጣቶች መነቃቃትን ይፈጥራል' ይላሉ። በቀጣይም ሌሎች ለመድረኩ የሚመጥ ተውኔቶችን ለማዘጋጀት መነሳሳትን እንደሚፈጥርም እንዲሁ።

ጸኃፊ ተውኔቱ አቶ አንተነህ በበኩሉ 'ግልጽነት መልካም ወዳጅነት ይፈጥራል' በሚል ጭብጥ ላይ የሚያጠነጥነው የ'ካላአብራክ ተውኔት' "እንግዳ አክባሪነት፣ እንግዳ ተቀባይነት፣ ግልጽነት መልካም እሴትንም በጥቂቱ ያንጸባርቃል" ይላል።

ብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህላዊ፣ ትውፊታዊና ድራማዊ ክዋኔዎችን የማጥናትና የማስተዋወቅ ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም ነው- ብሔራዊ ትያትር ፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ተዋናዮች ብቻ የተዘጋጀ ትያትር ለመድረክ ሲያበቃ የመጀመሪያው መሆኑን ይናገራሉ-የትያትር ቤቱ የትያትር ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አዳፍሬ ብዙነህ። ብቃት ያላቸው አማተር ከያኒያንን ከማስተዋወቅና መነቃቃትን ከመፍጠር ባሻገር፤ ተውኔቱ የኪነ ጥበቡን ዘርፍ ለማሳደግ የራሱ ፋይዳ እንደሚኖረው በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።  

ተውኔቱ ዘወትር ቅዳሜ 11፡ 00 ሰዓት በብሔራዊ ትያትር ለመድረክ ይቀርባል፤ ለአንድ ዓመት ያክል በመድረክ ሊቆይ እንደሚችልም ተጠቁሟል።

የተውኔቱ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ባሳለፍነው ሳምንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን አንጋፋውን የጥበብ አርበኛ አባባ ተስፋዬ ሳህሉን በሕሊና ጸሎት በማሰብ ነበር የተጀመረው።

Published in ዜና-ትንታኔ

አዲስ አበባ ሃምሌ 29/2009  በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የሸማቾች የሕብረት ሥራ ማሕበራት የትርፍ ምጣኔያቸውን ከማሳደጋቸውም በላይ አባላቶቻቸውን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አስታወቁ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ማህበራት አመራር አባላት እንደገለጹት፤ በየዓመቱ የአባላት ቁጥር፣ የሚያቀርቡት ምርት ዓይነትና ብዛት በመጨመር ትርፋቸውን ማሳደግ ችለዋል።

በከተማዋ የሚገኙ ማህበራት የድጎማ ምርቶችን ከማቅረብ ባለፈ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ፣ በመዝናኛ ክበባት፣ በወፍጮ ቤት፣ በዳቦና ልኳንዳ ቤት ስራዎች ላይ ተሰማርተዋል።

ይህም የገበያ ማረጋጋትና ተደራሽነትን ከመፍጠር አኳያ አስተዋጽኦ እንደነበረው ነው የተመለከተው።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት የሕብረት ስራ ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይታገሱ ጠና እንዳሉት፤ ማህበሩ የመሸጫ ሱቆች ብዛት ጨምሯል፤ ለህብረተሰቡ የሚያቀርባቸው የምርት ዓይነቶችን አሳድጓል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የሕብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ሀይሌ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ በየዓመቱ ከሚገኘው ትርፍ የማህበሩን ካፒታል እንዲያድግ ተደርጓል። የማስፋፊያ ስራዎችም እየተካሔዱ ናቸው።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አብዱልበር ደጋ፤ ማህበሩ በተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥ የአባላቱን ቁጥርና ካፒታል በፍጥነት ለማሳደግ መቻሉን ነው የተናገሩት።

የማህበራቱ አመራር አባላት እንደተናገሩት፤ በየዓመቱ ከሚገኘው ትርፍ አባላቱን ተጠቃሚ አድርገዋል። ለአካባቢያቸው ለልማት፣ ለጤና ተቋማትና ለማህበራዊ ጉዳዮች ድጋፎች እያደረጉ ይገኛሉ።

በቀጣይም በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሰማራት ገቢያቸውን ለማሳደግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ነው ያመለከቱት።

ይህም ሆኖ ማህበራቱ የድጎማ ምርቶች የኮታ ማነስና የአቅርቦት እጥረት እንዳጋጠማቸው ነው የገለጹት።

የማህበራቱ አባል ሀጂ  ሸረፋ ዘይኒ በማህበራቸው አመታዊ የትርፍ ክፍፍል በኩል ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

በአዲስ አበባ የህብረት ስራ ኤጀንሲ የማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ግብይት ዋና የስራ ሂደት መሪ አቶ ሙሉሸዋ በቀለ እንዳሉት፤ ማህበራቱ በተለይም እህል፣ ጥራጥሬና ሥጋ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የዋጋ ንረትን ከመከላከል አኳያ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ውጤታማ ያልሆኑ ማህበራትን በመለየት ድጋፍ የሚደረግበት የምዘና ስርአት መዘርጋቱን ጠቁመው፤ ይህም የማህበራቱን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻልና ድጋፍና ክትትል ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በመዲናዋ 141 መሰረታዊ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት እና 10 የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ዩኒየኖች ተቋቁመዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ጅማ ሀምሌ 29/2009 በጅማ ዞን  ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተሰማርተው የተለያዩ የልማት ሰራዎችን እያከናወኑ መሆኑን የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ያህያ አሊዪ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ወጣቶቹ የማጠናከሪያ ትምህርት፣ የከተማ ፅዳት፣ ችግኝ ተከላ ፣ የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት የመሳሰሉ ስራዎችን እያካሄዱ ነው ።

ከዚሁ ጎን ለጎን ደም በመለገስ ተግባር መሰማራታቸውን ተናግረዋል ።

እንደ ምክትል ሀላፊው ገለፃ  ወጣቶቹ ባለፉት 15 ቀናት ውሰጥ 2ሺህ ለሚሆኑ የአቅመ ደካማ ቤቶች ጥገናና የ7 ሺህ 554 ችግኞች ተከላ አከናውነዋል ።

በሊሙ ኮሳ ወረዳ በጎርፍ የተጉዱ መሬቶችን በማስተካከል ስራ ላይ የተሰማራው ወጣት ሙሉጌታ ሸለማ "በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በመሰማራቴ ለአካባቢው ጠቃሚ ስራ በመስራት መንፈሳዊ እርካታ እንዳገኝ ረደቶኛል " ብሏል ።

ሌላዋ የሊሙ ኮሳ ወረዳ ወጣት ሊሙወርቅ ይማም በበኩሏ ለቀበሌዋ ወጣቶች መሰረታዊ የኮምፒዩተር ስልጠና ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደምትገኝ ገልጻለች። 

Published in ማህበራዊ

ነቀምቴ ሃምሌ 29/2009 በቄለም ወለጋ ዞን በተያዘው ክረምት ከ59 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ችግኝ መሸፈኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን አስታወቀ ፡፡

በባለስልጣኑ የቡና ልማት ቡድን መሪ አቶ መኮንን ቆራሣ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ በተያዘው ክረምት በዞኑ የቡና ልማትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ለዚህም በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ከ4 ሺህ በሚበልጡ የመንግስትና የግል የቡና ችግኝ ጣቢያዎች ላይ ከ250 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተው ተተክለዋል።

የተተከሉት የቡና ችግኞች በምርምር ተቋማት የተገኙ፣ በሽታን መቋቋም የሚችሉና ብዙ ምርት ሊሰጡ የሚችሉ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አቶ መኮንን እንዳሉት በዞኑ ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2009ዓ.ም በተካሄደው የቡና ችግኝ ተከላ ከ250 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ ከ59ሺህ በሚበልጥ ሄክታር መሬት ላይ ተተክሏል፡፡

በዞኑ የተዘጋጀው የቡና ችግኝ በአዲስና ነባር የቡና መሬት ላይ የተተከለ ሲሆን፣ በችግኝ ተከላውም ከ84 ሺህ በላይ የዞኑ አርሶአደሮች መሳተፋቸውን አመልክተዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተተከለው የቡና ችግኝ 82 በመቶው መጽደቁን የገለጹት ቡድን መሪው፣ "በአሁኑ ወቅት በዞኑ በሄክታር የሚገኘውን ስድስት ኩንታል ምርት ወደስምንት ኩንታል ለማሳደግ እየተሰራ ነው " ብለዋል፡፡

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፣ በዞኑ በማህበር ተደራጅተው የቡና ችግኝ ማዘጋጀት የጀመሩ ወጣቶች ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል፡፡

በማህበር ተደራጅተው የቡና ችግኝ በማዘጋጅ ተጠቃሚ ከወኑ ወጣቶች መካከል በላሎ ቅሌ ወረዳ የዶጋሎ ዱሙጋ ቀበሌ ወጣቶች ማህበር  ሊቀመንበር ወጣት ጫላ ደበላ በችግኝ ዝግጅት ስራ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጿል።

ወጣቱ እንደገለጸው ባለፈው ክረምት የማህበሩ አባላት 31 ኪሎ ግራም የቡና ዘር ዘርተው በዘንድሮው ክረምት ከ85 ሺህ በላይ የቡና ችግኝ ለማፍላት ችለዋል።

ከነዚህ ውስጥ 68 ሺህ 500 ችግኞችን ለገበያ በማቅረብ ከ27 ሺህ ብር በላይ ማግኘታቸውንም ወጣት ጫላ ገልጿል። 

16ሺህ500 የቡና ችግኞችንም በግል ማሳቸው ላይ መትከላቸውን ገልጾ፤ ዘንድሮም 40 ኪሎ ግራም የቡና ዘር ዘርተው በመንከባከብ ላይ መሆናቸውን አስረድቷል፡፡

በወረዳው የኩታላ ሉቤ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ደምሴ ታደሰ በበኩላቸው በግል ማሳቸው ላይ ካዘጋጁት የቡና ችግኝ ለራሳቸው ከመጠቀም ባለፈ 23ሺህ 500 የቡና ችግኞችን ለገበያ አቅርበው 9 ሺህ 400 ብር ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ከበደ ታሲሳ በበኩላቸው በተያዘው ክረምት ሦስት ሺህ የቡና ችግኞች መትከላቸውን ተናግረዋል።

በቄለም ወለጋ ዞን ከ302 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና ልማት መሸፈኑን የዞኑ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለሥልጣን መረጃ ያመለክታል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ሽሬ እንዳስላሴ ሀምሌ 29/2009 በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት የማእከላዊ እዝ  የሰራዊት አባላት በትግራይ ሰሜናዊ ምእራብ ዞን በመካሄድ ላይ ባለው የችግኝ ተከላ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

በዞኑ ከ18 ሚሊዮን በላይ አገር በቀል ችግኞች በፓርኮችና በተፋሰሶች እየተተከሉ ነው፡፡

የሰራዊቱ አባላት በችግኝ ተከላው በመሳተፍ ላይ ያሉት “አረንጓዴ አካባቢ የመፍጠር ጉዳይ የኛም ጉዳይ ነው” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡

የዞኑ የተፈጥሮ ሃብት አስተባባሪ አቶ ሃብተስላሴ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት የሰራዊቱ አባላት በዞኑ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች  ፈልተው የተዘጋጁ ከ10 ሚሊዮን በላይ አገር በቀል ችግኞች ወደ ተከላ ጣቢያዎች በራሳቸው ተሽከርካሪ አጓጉዘዋል፡፡

የሰራዊቱ አባላት ችግኞችን ከማመላለስ በተጨማሪ በተከላውም በንቃት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

ከሐምሌ 15 ቀን ጀምሮ በዞኑ በላእላይና ታህታይ አዲያቦ ወረዳዎች በታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ስም በተሰየሙት ስድስት ፓርኮች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተክለዋል።

እንዲሁም በዞኑ በእረፍት ላይ የሚገኙ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትተማሪዎችና የዞኑ ነዋሪ ህዝብ በዚሁ የችግኝ ተከላ ስራ በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡

እስካሁን ባለው እንቅስቃሴም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ያመለከቱት አስተባባሪው ተከላው እስከ ሀምሌ 30 ቀን ይቀጥላል።

በችግኝ ተከላ ወቅት አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የሰራዊቱ አባላት መካከል ሻለቃ እሱባለው ተፈራ እንደገለፀው   ችግኝ ከመትከል ባሻገር ለእድገቱ ትኩረት በመሰጠት ውሀ ለማጠጣትና ለመንከባከብ  ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

”ከተከልኩዋቸው አሥራ አምስት ችግኞች ቢያንስ አስራ ሁለቱን ለማሳደግ ጥረት አድርጋለሁ” ያሉት ደግሞ ሻምበል ግርማይ አለምሰገድ ናቸው።

እንዲሁም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የሦስተኛ ዓመት የኮምፒውተር ኢንጂኔሪንግ ተማሪ ዮናስ ታፈረ “አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት አረንጓዴ አካባቢ መፍጠር ስለሚያስፈልግ በችግኝ ተከላው በንቃት እየተሳተፍኩኝ ነኝ” ብለዋል።

“ጀግኖች ሰማእታት ባረፉባቸው ተራራዎች ተገኝቼ ችግኝ በመትከሌ ክብር ይሰማኛል ያለችው” ደግሞ በዲላ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ሳይንስ ተማሪ ትርሓስ ገብረመድህን ናት።

በዞኑ በክረምቱ ወቅት በስድት ወረዳዎች በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስቴር በተሰየሙት በአሥራ ስድስት ፓርኮችና በተለያዩ ተፋሰሶች ከ18 ሚሊዮን በላይ አገር በቀል ችግኞች እየተተከሉ ናቸው።

በዞኑ ባለፈው ክረምት ከተተከሉት አሥራ ዘጠኝ ሚሊዮን ችግኞች መካከል ስልሳ ከመቶዎቹ መፅደቃቸውን በተደረገው ጥናት ማረጋገጥ ተችሏል።   

 

Published in አካባቢ

ደሴ ሃምሌ 29/2009 ከአንድ መቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን በክረምት ተቀብሎ ተግባር ተኮር ትምህርት እየሰጠ መሆኑን ወሎ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ስዊድን አገር ከሚገኘው ካርልስታድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የትምህርት መርሀግብር ተጠቃሚ የሆኑት ተማሪዎች ከደቡብ ወሎ ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር ከሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ናቸው።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥፎ ሳይንስ ዲን ዶክተር መንገሻ አየነ እንዳሉት ተማሪዎቹ የላቀ ውጤት ያስመዘገቡና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርቱን እየሰጠ ያለው ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ትምህርቱን እየተከታተሉ ከሚገኙት ተማሪዎች ውስጥ 52ቱ ባለፈው ዓመት መማር የጀመሩና ቀሪዎቹ ዘንድሮ አዲስ ወደ መርሀግብሩ የተቀላቀሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዶክተር መንገሻ እንዳሉት፣ የትምህርት መርሀግብሩ በእንግሊዝኛ፣ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስናና ሒሳብ የትምህርት አይነቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።

ይህም ተማሪዎቹ በ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የማድረግ ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ  የራሳቸውና የአገራቸውን ስም ሊያስጠሩ የሚችሉ ምሁራን የማፍራት የረጅም ጊዜ ዓላማ እንዳለው አመልክተዋል።

እርሳቸው እንዳሉት አሁን በትምህርት ላይ ከሚገኙት ተማሪዎች መካከል 41ዱ ሴቶች ናቸው።

እንደ ዶክተር መንገሻ ገለጻ፣ ካርልስታድ ዩኒቨርሲቲ ባለፈው ዓምት ለትምህርት መርሀግብሩ  ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የመማሪያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዘንደሮ ዓመትም ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን በመቀጠል ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ቁሳቁሶችን ማስረከቡን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በተግባር የማስተማር ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን በመላክ እንዲያስተምሩ በማድረግ ላይ መሆኑም ገልጸዋል።

በተያዘው ክረምት ለተማሪዎቹ የተግባር ትምህርት እየሰጡ ያሉት የኢትዮጵያ፣ የስዊድንና ዜግነት ያላቸው መምህር ዮሐንስ ወልደሰንበት "መርሀግብሩ በአደጉ አገሮች በስፋት የሚሰራበት ሲሆን ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና አለው" ብለዋል።

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ዕድል ካገኙ ተማሪዎች መካከል ከቃሉ ወረዳ ደጋን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ኡስማን አሊ የሚሰጥን ትምህርት ለወደፊት ጥሩ መሰረት እንድንይዝ የሚያደርግ ነው ሲል ተናግሯል። 

በተለይ ትምህርቱ በተግባር የተደገፈ መሆኑ በትምህርት ቤታቸው ከሚሰጠው የሚለየው መሆኑን ነው የጠቆመው።

በደሴ ከተማ ከሚገኘው ካራ ጉቱ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣችው ተማሪ ሀያት መሐመድ በበኩሏ ፣ በትምህርቷ 98 ከመቶ አማካይ ውጤት በማምጣት የትምህርት ዕደሉ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለች ገልጻለች።

በትምህርት እድሉ ከምታገኘው ዕውቀት በተጨማሪ እርስ በርስ ልምድ ለመለዋወጥና ያለችበትን ደረጃ ለማወቅ እንደሚያስችላት ገልጻለች፡፡

Published in ማህበራዊ

ጎባ ሃምሌ 29/2009 በባሌ ዞን ውርጭና ድርቅን ተቋቁመው የተሻላ ምርት የሚሰጡ ከ19 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ተተክለው እንክብካቤ እየተደረገላቸው ነው፡፡

በዞኑ ቡና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን የቡና ልማት ባለሙያ አቶ ወንዶሰን ነጋ ለኢዜአ እንደገለጹት የቡና ችግኞቹ የተተከሉት በዞኑ ካለፈው ሚያዝያ እስከ ሰኔ ወር 2009 የጣለውን የበልግ ዝናብ በመጠቀም ነው፡፡

ችግኞቹ ከጅማና መቻራ የግብርና ምርምር ማዕከላት የተገኙና “ሞካ“ እና ”ዴሱ” የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን ጨምሮ 12 የተለያዩ ዝሪያዎች ናቸው፡፡

ለልማቱ አመች በሆኑ ዘጠኝ ወረዳዎች በ7 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተተከሉት የቡና ችግኞች ውርጭና ድርቅን ተቋቁመው በሄክታር 12 ኩንታል ምርት የሚሰጡ ናቸው፡፡

ለተተከሉት የቡና ችግኞች በአርሶና አርብቶ አደሩ እንክብካቤ እየተደረገላቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የልማት ጣቢያ ሰራተኞችም በቅርበት ሆነው በልማቱ ለተሰተፉ ከ30 ሺህ ለሚበልጡ አርሶና አርብቶ አደሮች ስለ ቡና ችግኝ ተከላና እንክብካቤ የሙያ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።

በዞኑ በቡና ልማት የሚሳተፉ  አምራች አርሶና አርብቶ አደሮች ከዘርፉ የሚያገኙት ጥቅም እያደገ በመምጣቱ ለቡና ልማት የሚደረገው እንክበካቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ፡፡

በዚህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተተከለው 18 ሚሊዮን የቡና ችግኝ ውስጥ 85 በመቶ መጽደቁን በማሰየነት አንስቷል፡፡

በቡና ልማቱ ከተሰተፉ የደሎ መና የማኘቴ ቀበሌ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ማህሙድ አብደላ እንደተናገሩት በዘንድሮው የተከላ ወቅት በ2 ሄክታር መሬታቸው ላይ የተሻሻሉ የቡና ዝርያ ችግኞችን በመትከል በመንከባከብ ላይ ናቸው፡፡

በየዓመቱ የሚያዘጋጁትን የቡና ችግኝ ለሌሎች አርሶ አደሮች በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናግረዋል ፡፡

ሌላው  የቀበሌ አርሶ አደር ቃሲም መሮ  በበኩላቸው በቡና ችግኝ ልማት መሳተፋቸው ከሰብል ልማት በተጨማሪ የገቢ ምንጭ እየሆናቸው ነው።

በባሌ ዞን ከ46 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ልማት የተሸፈነ ሲሆን በየዓመቱ እስከ 15 ሺህ ቶን ምርት እንደሚሰበሰብ ከዞኑ የቡና ሻይና የቅመማ ቅመም የግብይት ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Published in ኢኮኖሚ

ሃምሌ 28/2009 በሩዋንዳ በተደረገው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝደንት ፖውል ካጋሜ ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፋቸውን የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በፕሬዝደንታዊ ምርጫው ሶስት ዕጩዎች የተወዳደሩ ሲሆን ፓውል ካጋሜ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን ያሸነፉት ድምጻቸውን ከሰጡት የሃገሪቱ ዜጎች 98 ነጥብ 6 በመቶ ድምፅ በማግኘት መሆኑን ነው የምርጫ ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው።

እስካሁን በተደረገው ቆጠራም ፖል ካጋሜ 5 ሚሊዮን 433ሺ890 ድምጽ/98.66%/ ሲያገኙ ተፎካካሪያቸው ፊሊፕ ምፓይማና 39ሺ620 ድምጽ/0.72%/ እና ፍራንክ ሃቢኔዛ 24ሺ904 ድምጽ /0.45%/ አግኝተዋል፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ ፕሬዝደንታዊ ምርጫውን ያሸነፉት ካጋሜ ለቀጣይ ሰባት ዓመታት ሃገሪቱን በፕሬዝደንትነት የሚመሩ ይሆናል፡፡  በአሁኑ ሰዓትም በመላ ሃገሪቱ የሚገኙ የካጋሜ ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለጹ ናቸው።

ላለፉት 17 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የ59 አመቱ ፕሬዝደንት ካጋሜ ሩዋንዳ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እንድታስመዘግብ አድርገዋል በሚል የሃገሪቱ ዜጎች ይደግፏቸዋል።

አንዳንዶች በተለይም በውጭ የሚኖሩ የሃገሪቱ ዜጎች በካጋሜ አስተዳደር ደስተኛ አለመሆናቸውንና ብርቱ ተቃዋሚዎች እንዳይኖሩ ማስፈራሪያ እንዳለ ይገልጻሉ፡፡

በተለይም እ.ኤ.አ በ2015 የተሻሻለው የሃገሪቱ ህገ-መንግስት የፕሬዝደንት ስልጣንን በማራዘም ለካጋሜ እ.ኤ.አ እስከ 2034 በምርጫ በማሸነፍ ስልጣን ላይ መቆየት እንዲችሉ እድል የሰጠ ነው የሚል ከተቃዋሚዎቻቸው በኩል ይተቻሉ፡፡

ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ከምርጫ ውጤቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር በሃገሪቱ የተጀመረው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የበለጸገች ሩዋንዳን ለመፍጠር እተጋለሁ ብለዋል፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ

Published in ፖለቲካ
Saturday, 05 August 2017 15:02

አዝጋሚው ስጦታ

ሀብታሙ ገዜ -ድሬዳዋ ኢዜአ

በህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ያመጣል የተባለው የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ መጓተት መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የህክምና ባለሞያዎችና ነዋሪዎች ይጠይቃሉ ። ለግንባታው መጓተት የተለያዩ ምክንያቶች የሚጠቅሰው የጤና ቢሮ በበኩሉ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥረቱ ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው ይላል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ ቁጥር 30ሺህ በሚገመትበት ከ5 አስር ዓመታትት በፊት ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ይገለፃል - የድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል። አሁንም ድረስ ግማሽ ሚሊየን ለሚሆነው ህዝብና ለተጎራባች የምስራቅ ኢትዮጵያ ህዝብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ከህዝብ ቁጥር መጨመር፣ከበሽታው ዓይነትና መጠን መበራከት ጋር ተያይዞ ጫና ውስጥ የወደቀው አንድ ለእናቱ የሆነው የድሬዳዋ ድል ጮራ ሆስፒታል ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት፣ ጽዱና ምቹ የህክምና ማዕከል ሆኖ ለመቀጠልና በህክምና ዘርፍ ጥናትና ምርምር  ለማካሄድ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ አዲስ ሆስፒታል መገንባት  የዘመናት ትልቅ ጥያቄ ሆኖ ብቅ አለ ።

ታዲያ! የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለእነዚህ መሰረታዊ ጥያቄዎች መፍትሄ ያመጣል የተባለለት የሚሊኒየሙ ስጦታና ማስታወሻ የሆነ አዲስ ሪፈራል ሆስፒታል ለመገንባት በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እንቅስቃሴ ጀመረ። በ2002 ዓ.ም በ10ሺህ ካሬ መሬት ላይ ባለ ስድስት ፎቅ ህንፃ ግንባታ ጀመረ።

በ142 ሚሊየን ብር ውል ተፈርሞ በአራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ሆስፒታል በተለያየ ጊዜ በዲዛይን መቀየር ፣ ከቁጥጥርና ክትትል ማነስ፣ ከኮንትራክተሮች አቅም ውሱንነትና ተዛማጅ ችግሮች ጋር ተያይዞ ግንባታው እየተጓተተ በህዝቡም በህክምና ባለሞያዎች ዘንድም ቅሬታ እንደፈጠረ አሁን ላይ ደርሷል ።

የድል ጮራ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙህየዲን ረዲ አዲሱ ሆስፒታል በተያዘለት የጊዜ ገደብ ቢጠናቀቅ ኖሮ የሚታየውን ጫናና መጨናነቅ አይፈጠርም ነበር ይላሉ ።

"ወደ ድል ጮራ ሆስፒታል ከተጎራባች ክልሎች፣ ከጅቡቲና ከሶማሌ ላንድ ጭምር ሪፈር ተብለው በርካታ ሰዎች ይመጣሉ ። የአገልግሎት ፈላጊው ህዝብ ቁጥር ከአቅም በላይ በመሆኑ እየጠበቅን ያለነው የሆስፒታሉን መጠናቀቅ ነው ። ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠትም ብቸኛው መፍትሄ ግንባታውን ማጠናቀቅ ነው "የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልፃሉ ።

የአቶ ሙህየዲን ሃሳብ የሚጋሩት ደግሞ የመልካ ጀብዱ ነዋሪ አቶ አብዲ ሙሜ ናቸው ። መንግስት ለገጠርና ከተማ ህዝብ በየቀበሌው የጤና ተቋማትን አስፋፍቷል ።  በመልካ ቀበሌ  የተጀመረው ሆስፒታል ግንባታ መጀመር ህዝቡን ያስደሰተ ቢሆንም ማጠናቀቅ ለምን እንዳልተቻለ ግን  እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ይገልፃሉ ። "ግንባታው ቆሞ ቀር ሆኗል ። መንግስትስ ቢሆን ለምን ዝም ይላል" ሲሉም ይጠይቃሉ ።

የቀድሞ የድሬዳዋ ጤና  ቢሮ ሐላፊ ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ ሆስፒታሉ በህክምናው አገልግሎት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣና የሚሊኒየሙ ታላቅ ስጦታ ለማበርከት የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው ግንባታውን ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ጥረት፣ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ አብዱላሂ  ለግንባታው መጓተት ዋናው ምክንያት የዲዛይኑ ሶስትና አራት ጊዜ መለዋወጥ ነው ይላሉ።

ሆስፒታሉን ለማዘመን የተደረገው የዲዛይን ለውጥ ተጨማሪ በጀት ፣ ተጨማሪ ጊዜና  እውቀት ጠይቋል። "የተጀመሩ ግንባታዎች በማፍረስ ተግባራዊ የተደረገው አዲሱ ዲዛይን  ወጪው በእጥፍ እንዲጨምር አድርጎታል ። የሆነው ሆኖ ግን ግንባታው በሚቀጥለው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ምክር ቤቱ ቁጥጥሩን ያጠናክራል" ብለዋል ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና  ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሙሉቀን አርጋው በበኩላቸው የሆስፒታሉ ግንባታ መጓተት ብዙ ምክንያቶች አሉት ባይ ናቸው ። ከኮንትራክተሮች አቅም ውሱንነት ባሻገር የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣  የዲዛይን መለዋወጥ፣ ቀደም ሲል  ዲዛይኑን የሰራው አካል ከስራው መውጣት፣ ግንባታውን የሚከታተሉት አካላትና ተቋማት መለዋወጥ ጥቂቶቹ ናቸው ይላሉ ።

የመጀመርያው ዲዛይን ለህክምና አስፈላጊ የሆኑ የኤሌክትሮ መካኒካል ስራ ሙሉ በሙሉ ያካተተ አልነበረም ። ይህንኑ ለማካተት ተጨማሪ ጨረታ ማውጣት ፣ 66 ሚሊየን ብር በጀት መመደብና አዲስ ኮንትራክተር መቅጠር ጠይቋል ።

ከዚህ በተጨማሪም ህንጻው በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታገዘና ለህሙማን አመቺ ለማድረግ አዲስ ዲዛይን መስራት አስፈልጎ ነበር ይላሉ ።

በአሁኑ ጊዜ የግንባታው በጀት 323 ሚሊየን ብር ደርሷል ። ከታቀደ አስር ዓመት ግንባታው ከተጀመረ ደግሞ ሰባት ዓመት የሞላው ይኸው ሆስፒታል በሶስት ኮንትራክተሮችና በአንድ አማካሪ ድርጅት አማካኝነት ስራው እያዘገመ ነው ። የህንጻ ግንባታው 74 በመቶ ተጠናቋል ። የሲቪል ስራው ግን በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት እየተጓተተ ነው ።

የኤሌክትሮ መካኒካል ስራው 94 በመቶ ቢጠናቀቅም የኮንትራት ውሉ በመጠናቀቁ የህንፃ ተቋራጩ ላባከነው ጊዜ የገንዘብ ቅጣት እየከፈለ መሆኑን ዶክተር ሙሉቀን ገልፀዋል።

በ198 ሚሊየን ብር ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረውና እስከ አሁን ባለው ወጪው 323 ሚሊየን ብር የደረሰው የድሬዳዋ ሪፈራል ሆስፒታል በመጪው ሚያዚያ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ እየተሰራ ይገኛል።

ሆስፒታሉ በተባለው ጊዜ ከተጠናቀቀ በአካባቢው የማይገኙ አዳዲስ የህክምና አገልግሎቶች በቅርበት ማግኘት ያስችላል ። በጥራት ደረጃም እሴት ለመጨመር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ። ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ጋር በማስተሳሰር ደግሞ ብቁ ባለሞያዎችን ለማፍራትና በጤናው ዘርፍ ምርምርና ጥናት ለማከናወን ይረዳል የሚሉት የጤና ቢሮ ሃላፊው ዶክተር ሙሉቀን አርጋው አብርክቶው የጎላ ይሆናል።

በድሬዳዋ አስተዳደር ህዝብ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የሚሊኒየሙ ስጦታ የሆነው ይኸው ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታው ከዳር ደርሶ ለታሰበለት ዓላማ እንዲውል ጥብቅ ክትትል ማድረግ ያስፈልገዋል ። በዚህ ፕሮጀክት ላይ የተስተዋለው መዝረክረክ፣ የቅንጅት ችግር ፣ አላስፈላጊ ወጪና የጊዜ ብክነት በሌሎች ተቋማት የግንባታ ሂደት  ላይ እንዳይደገም ካለፈው መማርና ለዘላቂ መፍትሄ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል ።

 ከዚህ ጎን ለጎን ግንባታው በሚጠናቀቅበት ወቅት በፍጥነት አገልግሎት እንዲጀምር ከወዲሁ የህክምና መሳሪዎች የማሟላት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የህክምና ባለሞያዎችና ነዋሪዎች የሚሰጡትን አስተያየት ሰምቶ እውን ማድረግም ብልህነት ይሆናል።

በአጠገባችን  ሀረር ከተማ ህይወት ፋና ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ1 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ የሚያስገነባው ስፔሻላይዝድ የመማሪያና የሪፈራል ሆስፒታልና የካንሰር ማዕከል ግንባታ በተቀመጠለት ጊዜና በጀት ተጠናቆ ለአገልግሎት ተቃርቧል ። ድሬዎችም ከዚሁ መማር አለባቸው ። የጎረቤታቸው ሀረርን መልካም ተሞክሮ በመጋራት ፕሮጀክቶች በእቅድ ተጀምረው ባስቀመጡት የጊዜ ገደብ ውስጥ ማጠናቀቅ የማይችሉበት ምክንያት የለምና ይበርቱ እንላለን ።

Published in ዜና ሓተታ

ባህር ዳር ሃምሌ 29/2009 በአማራ ክልል የተጀመረው ሀሰተኛ ማስረጃን የማጋለጥና የማምከን ተግባር ወጥ አሰራር ተዘርግቶለት ሊተገበር እንደሚገባ የፌዴራልና የክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽኖች ጥምረት ጉባኤ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የ2009 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ዕቅድ አፈጻጸምን የሚገመግም መድረክ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

የጉባኤው ተሳታፊና የኦሮሚያ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሀሚድ ኪሚሶ እንዳሉት፣ ችግሩን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማስወገድ በፌዴራል ደረጃ ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ይገባል።

ክልሎች በተናጠል በሚያደርጉት ትግል ብቻ ሀሰተኛ ማስረጃን በመከላከልና በመቆጣጠር የሚፈለገውን ያህል ለውጥና ውጤት ማምጣት እንደማይችልም ተናግረዋል።

በሀሰተኛ ማስረጃ መገልገልን ለመከላከልና ተግባሩንም ለማምከን የአማራ ክልል የተሻለ ሥራ መስራቱን የገለጹት ደግሞ የትግራይ ክልል ፀረሙስና ኮሚሽን የምርመራና ክስ የሥራ ሂደት ኃላፊ አቶ ኃጎስ ወልደዋህድ ናቸው።

"በሀሰተኛ ማስረጃ መገልገል በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ውስጥ በማስገባትም ሌሎች ክልሎች ከአማራ ክልል ልምድ በመውሰድ ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፀረሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አየሁ በበኩላቸው፣ በጉባኤው ከተለያዩ ክልሎች ጠቃሚ ልምዶችና ተሞክሮዎች ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

የአማራ ክልል የሀሰተኛ ማስረጃን ለመከላከል አመራሩን አቀናጅቶ የሄደበት ርቀት ክልሎች በቀጣይ ለሚያከናውኑት የፀረ ሙስና ትግል ምሳሌ ከመሆን ባለፈ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል።

በጉባኤው በክልላቸው የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆነ የመጣውን ሀሰተኛ የትምህርት፣ የመንጃ ፈቃድና የብቃት ምዘና ማስረጃ ለማስቆም የሚያስችል ግብዓት አንዳገኙም ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዝጋለ ገበየሁ፣ ለጉባኤው ባቀረቡት ሪፖርት ሀሰተኛ ማስረጃን ለመከላከል የክልሉ መንግስት አጣሪ ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሚገለገሉ ግለሰቦች ራሳቸውን እንዲያጋልጡ በተሰጠው የአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 506 የመንግስት ሠራተኞች ራሳቸውን ማጋለጣቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሀሰተኛ ማስረጃ የሚገለገሉ ግለሰቦችን ሕብረተሰቡ እንዲያጋልጥ በየመስሪያ ቤቱ የአስተያየት መስጫ ሳጥኖችና ነጻ የስልክ መስመር በማዘጋጀት ጥቆማ የመቀበል ሥራ እየተከናወነ ነው።

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ለሀገር ልማት ትልቅ እንቅፋት በመሆኑ ሁሉም ክልሎች ቅንጅታዊ በሆነ አሰራር ድርጊቱን የመከላከልና የማምከን ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባ አቶ ዝጋለ አስገንዝበዋል።

በፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባር አውታሮች ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ሻሚቦ በበኩላቸው፣ "ሀሰተኛ ማስረጃን ወጥ በሆነ መልኩ ለመከላከል በቀጣይ በስትራቴጂክ ዕቅዱ ትኩረት እንዲሰጠው ይደረጋል" ብለዋል።

የ2009 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ዕቅድ አፈጻጸምና የመልካም አስተዳደር ሪፖርትም ቀርቦ በጉባኤው ተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል።

Published in ፖለቲካ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን