አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Friday, 04 August 2017

አዲስ አበባ ሃምሌ 28/2009 በአፍሪካ የተከሰተውን አዲሱን መጤ የአሜሪካ ተምች ለመከላከል ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ፡፡

የአፍሪካ ህብረት የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽን በአህጉሪቷ የተከሰተውን አዲሱን የአሜሪካ መጤ ተምች በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የህብረቱ ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ቶማስ ክዌሲ ኳርት፤ "እንደበቆሎ፣ ሩዝ፣ ስኳር፣ እንዲሁም በአትክልት እና በጥጥ ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለውን አደገኛ ተባይ ለመከላከል ዓለም ዓቀፉ ማህበር ከጎናችን ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

የአሜሪካ መጤ ተምች ከ80 በላይ በሚሆኑ የሰብል ዝርያዎች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከመሆኑም ባሻገር በአንድ ሌሊት እስከ 100 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ሰብሎችን የሚያጠቃ አውዳሚ ነው።

ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገሮች ሥርጭቱ እንደሚሰፋ የገለጹት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ እስካሁን ከ25 በላይ በሚሆኑ የአፍሪካ ህብረት አባል አገሮች ላይ እንደተከሰተ አመልክተዋል።

በመሆኑም ይህንን ፈጣንና አደገኛ መጤ ተምች ለመከላከል መገናኛ ብዙሃን ችግሩን እንዲያሳውቁ፣ እንዲሁም ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ፈጣኑንና አውዳሚውን መጤ ተምች እንዴት መቆጣጠርና መቀነስ እንደሚቻል በሚደረገው ጥረት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ያስፈልጋል።

እንደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ኡጋንዳ ያሉ አገሮች የራሳቸውን የመከላከል እርምጃ በመውሰድ መልካም እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር፣ ተምቹ ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እንዲሰሩ መረጃዎችን ማድረስ፣ አመራር አባላትን ቁርጠኛ ማድረግ፣ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትን ማበራከት እንዲሁም የአፍሪካ የእርስ በርስ ግንኙነትን ማጠናከር በቀጣይ የሚሰራባቸው አቅጣጫዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የህብረቱ የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ጆሴፋ ሳኮ በበኩላቸው፤ "በአህጉሪቱ ችግሩን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት ላይ በትኩረት ይራል" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ፈጣን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም መረጃዎች በፍጥነት እንዲደርሱና የቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲከናወኑም ይደረጋል።

በአለም እርሻና ምግብ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ክልል አስተባባሪ ዶክተር ፓትሪክ ኮርማዋ ድርጅታቸው በአህጉሪቷ የተከሰተውን መጤ ተምች ለመከላከል ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ድርጅቱ አርሶ አደሮችን የማስተማር፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያመጣውን ተጽዕኖ በመፈተሽ አስፈላጊ መረጃዎችን እየሰበሰቡ መሆኑንም አስረድተዋል።

Published in ኢኮኖሚ

 

አዲስ አበባ ሐምሌ 28/2009 ህብረተሰቡ ሰላሙን ጠብቆ አገሪቱ የተያያዘችውን የመካከለኛ ገቢ ራዕይ የማሳካት ርብርብ አጠናክሮ  እንዲቀጥል የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ10 ወራት በሥራ ላይ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ጽህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው ሳምንታዊ መግለጫ እንዳስታወቀው የአንዲት አገር ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በሠራዊት ቁጥር ብዛትና በአዋጅ እንዳልሆነ መንግሥት በጽናት ያምናል።

ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተልዕኮ መሳካት ህብረተ ሰቡ የጎላ ድርሻ እንደነበረውም ነው በመግለጫው የተመለከተው፡፡

በቀጣይም ህዝቡ የሰላም ባለቤትነት ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩ እንደተረጋገጠ  ተገልጿል፡፡

በአንዳንድ አካባቢዎች ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር ከሚቻልበት ሁኔታ ላይ መደረሱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው፡-

 

             የዘላቂ ሰላማችን ዋስትናና ተጠቃሚ  ህዝባችን ነው!

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ለ10 ወራት በሥራ ላይ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ወስኗል። ምክር ቤቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአዋጁን የ10 ወራት አፈፃጸም በመገምገም ነበር። በመሆኑም ለአዋጁ መደንገግ መነሻ የነበሩ ሁኔታዎች መቀልበሳቸውን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች አንዳንድ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም በመደበኛው የህግ አግባብ መቆጣጠር የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠሩን፣ ከሁሉ በላይ ለአዋጁ ተልዕኮ መሳካት ዓይነተኛ ሚና የተጫወተው ህዝባችን የሰላም ባለቤትነት ሚናውን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችለው ምቹ ሁኔታ መኖሩን ለማረጋገጥ ችሏል።

አዋጁ የተደነገገበት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝብ ያነሳቸው የነበሩትን ህጋዊና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ጽንፈኛ ኃይሎች የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ ለማራመድ ወደ ነውጥና ግርግር በመቀየር ሲያካሂዱት የነበረው አፍራሽ እንቅስቃሴ እጅግ አደገኛና በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር ሥራ መግታትና መቆጣጠር አስቸጋሪ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደነበር ይታወሳል። ከአዋጁ በፊት ዜጎች በሰላም ወጥተው በሰላም ለመመለስ የሚሳቀቁበት፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ፍጹም የተገፈፉበት፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚታወቁበት የመከባበርና የመቻቻል ዕሴት በጸረ ሰላም ሃይሎች ህገወጥ ድርጊት የመሸርሸር ዝንባሌ የታየበት ነበር። ሁኔታው በዚያው ቢቀጥል ኖሮ በአንዳንድ አገሮች የታየው ዕልቂት በአገራችን ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና አልነበረም።

አዋጁ ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ የዜጎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ ሳይታወክ ፣ የንግድና የኢንቨስትመንት ተቋማትም ያለአንዳች ስጋት ስራቸውን ማከናወን ችለዋል።  በሁከትና ብጥብጡ የተሳተፉ አካላት በፈጸሙት የወንጀል ክብደት ልክ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ ተችሏል። በርካታ  ህገወጥ የጦር መሳሪያዎችንም መቆጣጠር ተችሏል። በአመጽ ተግባር ከተሳተፉት እጅግ የሚበዙት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሱ የተደረገ ሲሆን ይህም መንግሥት ለህዝብ ያለውን ተቆርቋሪነትና ወገንተኝነት ያረጋገጠበት ሌላው ህዝባዊ ተግባር ነበር። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወቅትም ተጠርጣሪ ቢሆን እንኳ አንድም ዜጋችን ሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ለማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ እንዲቋቋም ተደርጎ  በተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ ይታዩ የነበሩ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችል አካሄድ ከመጀመሪያው ተዘርግቶ ሥራው በግልጽነት ተከናውኗል።

አዋጁ በሥራ ላይ እያለ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎችን የማስፈጸም አቅም የሚያጠናክሩ ተከታታይ ሥራዎች መሰራታቸውም ሌላው ስኬት ነው። በተለይም የክልል የጸጥታ አካላት በሂደት የየአካባቢያቸውን የጸጥታ ሁኔታ በራሳቸው አቅም ለማስጠበቅ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲገነቡ መደረጉ ዛሬ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ከመደበኛ የጸጥታ ሥራችን አቅም በላይ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህንንም ጎን ለጎን ማረጋገጥ ተችሏል።

በመንግሥት የተያዘው የጥልቅ ተሃድሶ ዕቅድ ከበላይ አመራሩ ጀምሮ እስከታችኛው ህብረተሰብ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲወርድና ህብረተሰቡ ሲያነሳቸው የነበሩ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመለየትና በተቀመጠው አቅጣጫ ከራሱ ከህዝቡ ጋር በመሆን ለመፍታት የሚያስችል ምቹ መደላድል ለመፍጠር ማስቻሉም ሌላው ሊጠቀስ የሚገባው ጉዳይ ነው።

በአጠቃላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ መሆን አገራችን የተያያዘችው የልማትና የሰላም አቅጣጫችን እንዳይደናቀፍ ማድረግ አስችሏል። ይህ ደግሞ ያለ ህዝባችን ንቁ ተሳትፎና የባለቤትነት ሚና የተገኘ አይደለም። የአንዲት አገር ሰላም ለዘለቄታው የሚረጋገጠው በሠራዊት ቁጥር ብዛትና በአዋጅ እንዳልሆነ መንግሥታችን በጽኑ ያምናል። የሰላሙም ተጠቃሚ በዋነኛነት ራሱ ህዝቡ ነውና።

በዚህ አጋጣሚ መላው ህዝባችን፣  በየደረጃው ያሉ የመስተዳደር አካላት እና የጸጥታ ሃይሎቻችን የአገራችንን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስጠበቅ ለከፈሉት መስዋዕትነት የኢፌዴሪ መንግሥት አድናቆቱን መግለጽ ይወዳል።

በአገራችን አሁን ያለው ሰላም ህዝብ በየደረጃው የሚያነሳቸውን የልማት፣ የተጠቃሚነትና የመልካም አስተዳደር አጀንዳዎቻችንን ለማስቀጠል ምቹ ዕድል የሚፈጥር ነው። በመሆኑም መንግሥት ከህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እያካሄደው ያለውን የተሃድሶ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት መንግሥት ሊያረጋግጥላችሁ ይወዳል።

መላው የአገራችን ህቦች፦ ከእንግዲህ ለአፍታም ቢሆን ሳንዘናጋ ሰላማችንን እየጠበቅን ሙሉ ትኩረታችንን ህዝባችንን በየደረጃው ተጠቃሚ በሚያደርገው ፈጣን ልማታችን ላይ በማድረግ አገራችን የተያያዘችውን የመካከለኛ ገቢ ራዕይ የማሳካት ርብርባችንን አጠናክረን እንድንቀጥል መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሐምሌ 28/2009 በአበባ ከተማ አስተዳደር የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በተጠናቀቀው በጀት አመት ባከናወነው የመረጃ ማጥራት ስራ ከ3 ሺ ካሬ ሜትር በላይ መስሪያ ቦታዎችና  ከ100 በላይ  ሼዶች በህገ-ወጥ ግለሰቦች ተይዘው ማግኘቱን አስታወቀ።

በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙትን የመስሪያ ቦታዎችና ሼዶች የማስመለስ ስራ ማከናወኑንም ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዴና ሃይለስላሴ ለኢዜአ እንደገለፁት ለመስሪያ ተብለው ለኢንተርፕራይዞች የተዘጋጁ ቦታዎችና ሼዶች ከኤጀንሲው እውቅና ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ ተይዘው ተገኝተዋል።

በቀጣይም ከመስሪያ ቦታዎች ጋር ተያይዘው የሚታዩትን ህገ-ወጥ ተግባራት የመከታተል፣ የመቆጣጠርና መረጃ የማጥራቱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።

ቁጥራቸው ውስን ይሁን እንጂ የተሰጣቸውን የመስሪያ ቦታ በአግባቡ ተጠቅመው ሀብትና ንብረት አፍርተው መስሪያ ቦታውን ለኤጀንሲው ተመላሽ ያደረጉም መኖራቸውን አቶ ግዴና ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም በህገ-ወጥ መንገድ የመስሪያ ቦታዎችን የያዙ ኢንተርፕራይዞችን በማጋለጥ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል በተጠናቀቀው በጀት አመት ኤጀንሲው ለ3 ሺ 214 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ ቦታ መስጠቱንና 8 ሺ 752 አንቀሳቃሾችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት አመትም ከመስሪያ ቦታ ጋር በተያያዘ 10 ሺ ዜጎችን  ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰቡን ነው አቶ ግዴና ያስረዱት።

የተጠቃሚዎች የአመለካከት ክፍተት፣ የመስሪያ ቦታ መረጣና የመስሪያ ቦታዎችን በህገወጥ መንገድ ለሌሎች አካላት ማስተላለፍ የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውም ነው የተገለጸው።

Published in ኢኮኖሚ

ኢዜአ ሃምሌ 28/2009 በህዝብና በመንግስት ሀብት ላይ የሚፈፀመውን ሙስና ለመከላከል የቁጥጥርና ክትትል ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለፁ።

የምክር ቤቱ አባላት ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት መንግስት በሙሰኞች ላይ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በሙሰኞች ላይ እርምጃ መውሰድ ህዝቡ በሰፊው የሚጠብቀውና ምክር ቤቱም ሲሰራበት እንደቆየ በሰጡት አስተያየት ጠቅሰዋል።

መንግስት እየወሰደው ላለው እርምጃ የዋና ኦዲተር የኦዲት ምርመራ ውጤቶችና የምክር ቤቱ የቁጥጥርና ክትትል ሥራም ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል።

እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በመንግስት ተቋማት የሚያደርጉትን የቁጥጥርና ክትትል ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል። 

የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰቢ አምበሳደር መስፍን ቸርነት እንደተናገሩት በገዥው ፓርቲ ውስጥ የመነጨውን የፀረ ሙስና ትግል ለማስቀጠል ምክር ቤቱ የቁጥጥርና ክትትል ሥራውን ያጠናክራል ብለዋል።

በሙሰኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ በጥልቀትና በብስለት እንዲቀጥል የህዝቡም የምክር ቤቱም ፍላጎት እንደሆነ ገልፀዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ካሚል አህመድ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በተጠርጣሪ ሙሰኞች  ላይ እየተወሰደ ላለው እርምጃ  የምክር ቤቱ ጥረት ጭምር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

“ማንም ሰው ከህግ በላይ አይደለም” ያሉት አቶ ካሚል በሙስና ተዘፍቆ የተገኘ ማንኛውም አካል በህግ ፊት ቀርቦ እንዲጠየቅ ጠንከራ የቁጥጥርና ክትትል ሥራ  እንሰራለን ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ተዋበች ላንቃሞ በበኩላቸው የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

ማህበረሰቡ የሙስናን ወንጀል ፈጻሚዎችን በማጋለጥና በመጠቆም መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንዲያግዝ ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚአብሔር አርአያ እንዳሉት በህዝብና በመንግስት ሀብት ላይ ጉዳት ያደረሱ ሙሰኞች በህግ እንዲጠየቁ በመጪው የሥራ ዘመን ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ይደረጋል።

ይሄም መንግስት የጀመረው ጠንካራ የፀረ ሙስና ትግል እንዳይቀለበስ ያግዛል ብለዋል።

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ብንቱ ቀዋሬ በበኩላቸው የሙስና ሰንሰለቶችን ለመበጣጠስ ማህበረሰቡ ሙሰኞችን አጋልጦ ሊሰጥ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት መንግስት በሙሰኞች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃ የጥልቅ ተሃድሶውን ጥንካሬ እንደሚያሳይም አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸካይ ስብሰባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ የአቶ ዓለማየሁ ጉጆን ያለመያዝና ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

በዛሬው ዕለት በቁጥጥር ስር የዋሉት የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ የአቶ ዓለማየሁ ጉጆ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዛይድ ወ/ ገብርኤልን ጨምሮ በሙስና ተጠርጠረው የታሰሩት የመንግስት ባለስልጣናት፣ ባለሀብቶችና ደላሎች ቁጥር 50 ደርሰዋል።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                     

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሃምሌ 28/2009 በህዝብና መንግስት ገንዘብ ምዝበራ ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች ቁጥር 50 መድረሱን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አስታወቀ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ ጌታቸው አምባዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የቀድሞው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤልና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ይህም በሙስና ተጠርጥረው የተያዙትን ሰዎች ወደ 50 እንዳሳደገው ገልጸዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና ካለፈው ሐምሌ ወር አንስቶ የመሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመሆን እየሰሩ የነበሩት አቶ በቀለ ንጉሴም ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው የ2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የመጀመሪያ አስቸኳይ ስብሰባው የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆን ያለመከሰስ መብት በአብላጫ ድምጽ አንስቷል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ጌታቸው አምባዬ መንግስት በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት እንዲታይ እያደረገ መሆኑን በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

ከተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች ጋር የጥቅም ትስስር በማድረግ በሙስና ወንጀል ስለተጠረጠሩ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት እንዲታይ ለማስቻል ምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸውን እንዲያነሳ ተጠይቋል።

ግለሰቡ የሚኒስቴሩን የፋይናንስ አስተዳዳር ሥርዓት የግዥ ኤጀንሲ ተቀባይነት ያላገኘ አንድ የውጭ ኩባንያ ያለምንም ጨረታ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ውል እንዲፈፀም አድርገዋል።

ኩባንያው ስራውን ሙሉ በሙሉ ሳያጠናቅቅ እንዳጠናቀቀ ተደርጎ ሙሉ ክፍያ እንዲከፈለው በማድረግ ወንጀል መጠርጠራቸውንም አክለዋል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ።

በተጨማሪም ኩባንያው ስራውን አጠናቆ የጨረሰ በማስመሰል ለሁለተኛ ጊዜ በሚኒስቴሩ ህንጻ 7ኛ እና 8ኛ ፎቅ ያለምንም ውልና ያለ ጨረታ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወጪ ውል ፈፅሞ እንዲገባም አድርገዋል።

ኩባንያው ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸው ስምንት ተሽከርካሪዎች የተቋሙ ውል ከተጠናቀቀ በኋላ ከባንክ ብድር እንደተወሰደባቸው አመልክተው፤ ብድሩ ሊሰጥ የቻለው ለኩባንያው ስራ ለ18 ወራት እንደተራዘመለት በማስመሰል መሆኑን ነው የተናገሩት።

በአገር ውስጥ ወይም በአዲስ አበባ ለሚያከናውኗቸው የቤት ግንባታዎች የሚያገለግል እስከ 500 ሺህ ብር የሚደርስ ጉርሻ በመቀበል መጠርጠራቸውም ተጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ ለሚሰራው የአይቤክስ ፕሮጀክት ያለ ጨረታ በአራት ሚሊዮን ዶላር ለሌላ የውጭ ኩባንያ እንዲሰጥ ማድረጋቸውንና፤ በዚህም የኩባንያው ተወካይ በነበሩ ግለሰብ ጋባዥነት ከመላ ቤተሰባቸው ጋር በአሜሪካ ለአንድ ወር ጉብኝት እንዳደረጉ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በኩባንያው ተወካይ አመቻችነት በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉና ሙሉ ወጫቸው እንዲሸፈን መደረጉን የሚያሳይ የሰው ምስክርና የሰነድ ማሰረጃ መኖሩን ጠቅላይ ዓቃቤ ህጉ አመልክተዋል።

በመሆኑም ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት እንዲያልቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ምክር ቤቱ የአቶ አለማየው ጉጆ ያለመከሰስ መብትን በአብላጫ ድምጽ እንዲነሳ ወስኗል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሐምሌ 28/2009 ተባይና በሽታን የመከላከል አቅም ያላቸውን 48 የሰብል ዝርያዎች ማግኘቱን የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ዝርያዎቹ እስከ ሃያ በመቶ የምርት ብልጫ የሚያስገኙ ሲሆኑ የዳቦ ስንዴ፣ቲማቲም፣የፈረንጅ ሽንኩርት፣ቃሪያና ሌሎች የሰብል ዝርያዎች በምርምሩ  ከተሻሻሉት መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የተሻሻሉትን የሰብል ዝርያዎች አስመልክቶ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዛሬ ለጋዜጠኞች  መግለጫ ሰጥቷል።

የኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ድሪባ ገለቲ እንደተናገሩት በበጀት አመቱ ኢንስቲትዩቱ አርባ ስምንት  የሰብል ዝርያዎች ማሻሻሉን ጠቁመዋል።

ከእነዚህ መካከል ሁለት የቴምርና ሁለት የጠጅሳር ዝርያዎች ኢንስቲትዩቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በምርምር ያገኛቸው መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሰብል ዝርያዎቹ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለአግሮ ኢንዱስትሪው ግብዓትን በመጨመርና የውጭ ምንዛሬ ወጪዎችን በማስቀረት  በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል ብለዋል።

በተጨማሪም የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ በማዘመን የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ነው ዶክተር ደሪባ በመግለጫቸው የተናገሩት።

አዳዲስ ዝርያዎች ከነባሩ ዝርያዎች በሄክታር ከአስር እስከ ሃያ በመቶ የምርት ብልጫ ያላቸው ተባይ፣ በሽታና የውሃ ዕጥረትን መከላከል የሚችሉ መሆናቸውን ዶክተር ድሪባ ተናግረዋል።

 

መቀሌ ሐምሌ 28/2009 በትግራይ ክልል የዝናብ መቆራረጥ በሚታይባቸው ወረዳዎች ወባ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው።

በክልሉ ጤና ቢሮ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ዮሐንስ ገብረሐዋሪያ በክልሉ ቆላማ ወረዳዎች ወባ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት የትንኝ መራቢያ ቦታዎችንና ረግረጋማ አካባቢዎችን የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

የጤና ኤክስቴንሽንና የልማት ቡድኖች ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው የወባ መራቢያ የሆኑትን ቦታዎች በመለየትና የኬሚካል ርጭት በማካሄድ የተጠናከረ የመከላከል ሥራ በማካሄድ ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

እንደ አቶ ዮሐንስ ገለጻ ሕብረተሰቡ በየሳምንቱ የጽዳት ዘመቻ በማካሄድ ሳርና ቅጠሎችን አጭዶ ለእንስሳት ቀለብ የሚሆነውን ከመለየት ባለፈ ለወባ መራቢያነት የሚሆኑ አረሞችን ነቅሎ በማስወገድ ላይ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በወባ መከላከያ ዘዴዎች ላይ በየቀበሌው ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዘ ሰው ሲያጋጥምም ወደጤና ተቋማት ሄዶ አስቸኳይ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያደርግ አሰራር መመቻቸቱን አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል።

በክልሉ ለወባ ተጋላጭ የሆኑ ከ20 በላይ ወረዳዎች የሚገኙ ሲሆን የልማት ቡድኖችና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር በበሽታው የተያዘ ሰው ወደ ሕክምና እንዲሄድና መድኃኒት በአግባቡ እንዲጠቀም የማድረግ ሥራ እያከናወኑ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪ በየቤቱ በመሄድ የኬሚካል ርጭት ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በጠንቋ አበርገለ ወረዳ የጭላ ከተማ ነዋሪና የጤና ልማት ቡድን አባል የሆኑት ወይዘሮ ብርሃን ገብረእግዚአብሔር ወባ ከአምስት ዓመት በፊት በአካባቢያቸው በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ያደርስ እንደነበር አስታውሰዋል።

"በየሳምንቱ የጽዳት ዘመቻ በማካሄድ በሽታው ጉዳት ሳያደርስብን መከላከል ችለናል" ያሉት ወይዘሮ በርሃን፣ በሽታውን በመከላከል በኩል የልማት ቡድኖችና የጤና ባለሙያዎች እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በቃፍታ ሁመራ ወረዳ ማይተመን ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጉዕሽ ብርሃነ " ቀደም ባሉት ዓመታት የወባ በሽታን ለመከላከል በቅንጅት ባለመስራታችን በሽታው የብዙ ሰው ሕይወት አጥፍቶብናል" ብለዋል።

"በተለይ በእርሻ ሥራ ከተሰማራነው አብዛኞቻችን በረሃ ላይ ውጭ ስንተኛ በከፍተኛ ሁኔታ በወባ በሽታ እንጠቃ ነበር" ሲሉም ገልጸዋል።

አቶ ጉዕሽ እንዳሉት፣ በአሁኑ ወቅት የሕክምና ባለሙያዎች በሰጡን ትምህርት መጠለያ በመስራት፣ ቤታቸውን መድኃኒት በመርጨትና የአልጋ አጎበር በመጠቀም በወባ የሚጠቃ ሰው ቁጥር በአካባቢያቸው እየቀነሰ መጥቷል።

የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ወይዘሪት አበባ ግርማይ በበኩሏ "ማይተመን እና ቆራሪት በተባሉ ቀበሌዎች ከሕዝቡ ጋር ተቀናጅተን በመስራታችን በጤና ዘርፍ ለውጥ እየመጣ ይገኛል" ብላለች።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሃምሌ 28/2009 የአገርና ሕዝብን ሃብት ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉና ሥልጣናቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ሙሰኞችን በማጋለጥ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢዜአ ሪፖርተር በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተመለከተ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አነጋግሯል።

ወጣት የምስራች ገብረየስ ፣ አርቲስት ዮሃንስ በላይ እና ወጣት ሐና ደርቤ በሰጡት አስተያየት ሙሰኞችን በማጋለጥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በየአካባቢው በሙስና ተግባር ውስጥ የተዘፈቁትን ወንጀለኞች በማጋለጥ ለፍትህ እንዲቀርቡ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነትም አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል።

አቶ ዮሃንስ ኪዳኔ በበኩላቸው የሙስና ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ አስተማሪ መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል።

መንግስት በጥናት ላይ ተመስርቶ በሙስና የተጠረጠሩትን የሥራ ኃላፊዎችና ባለሀብቶች መያዝ መጀመሩ የሚያበረታታ መሆኑን የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎቹ፤ መንግስት ህብረተሰቡን ከወረዳ ጀምሮ በየደረጃው የሚያሰቃዩ ኃላፊዎችን በመመልከት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።

የመንግስትና የህዝብ ሀብትን በሙስና በመመዝበር ወንጀል የተጠረጠሩና በቁጥጥር ሥር የዋሉ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች ቁጥር 48 መድረሱ መገለጹ የሚታወስ ነው።

Published in ፖለቲካ

ጎንደር ሐምሌ 28/2009 በሰሜን ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሕብረተሰቡ ለትምህርት ሥራ መጠናከር ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ፡፡

በመምሪያው የመረጃ ዕቅድ ሀብት ማፈላለግ የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ በየነ መረሳ ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ በዞኑ 20 ወረዳዎች የሚገኙ 160 ሺህ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለትምህርት ሥራው ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

ሕብረተሰቡ በትምህርት ዘመኑ በጥሬ ገንዘብ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ያዋጣ ሲሆን በጉልበትና በቁሳቁስ ያደረገው ድጋፍም ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው፡፡

በዞኑ የትምህርት ሥራው እንዲጠናከር ሕብረተሰቡ ባደረገው ተሳትፎ እያዳንዳቸው 40 ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ 841 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በ51 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገንባት በትምህርት ዘመኑ ተከስቶ የነበረውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ማቃለል ተችሏል፡፡

ለተገነቡት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችም አንድ ሺህ 572 የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮች ሕብረተሰቡ ባዋጣው ገንዘብ ተገዝተው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ መደረጉን ነው አቶ በየነ የገለጹት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሕብረተሰቡ 11 የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር እንዲሁም 22 ቤተ-መጻህፍት፣ ስድስት ቤተ-ሙከራዎች፣ 99 መጸዳጃ ቤቶችን በመገንባትና የ124 ትምህርት ቤቶችን አጥር በማጠር ተሳትፎ ማድረጉ ተገልጻል፡፡

የበየዳ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰውነት ውባለም እንደተናገሩት በወረዳው ሕብረተሰቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በጉልበት ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ለትምህርት ሥራው ድጋፍ ድጋፍ አድርጓል፡፡

በሕብረተሰቡ ተሳትፎም 35 ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችና 19 የመምህራን መጠለያዎች  ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ነው የገለጹት፡፡

የተማሪ ወላጆች ባደረጉት የ277 ሺህ ብር የገንዘብ መዋጮ ሁለት የተማሪ መመገቢያ ክፍሎችና አንድ ቤተ-መጻህፍት መገንባታቸውን የገለጹት ደግሞ  በወረዳው የድል ይብዛ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጌታቸው ወረታ ናቸው፡፡

በትምህርት ቤቱ የወላጅ መምህራን ሕብረት (ወመሕ) አባል የሆኑት አቶ መብራቴ ካሳዬ በበኩላቸው፣ ትምህርት ቤቱ ያለበትን የገንዘብና የትምህርት ግብአት አቅርቦት እጥረት በመፍታት በኩል ሕብረቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ የመማሪያ ክፍል ጥበት ችግሮችን ለማቃለልም ሕብረቱ በትምህርት ዘመኑ የወረዳውን ሕዝብ በማስተባበር  የበኩሉን ጥረት ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

Published in ማህበራዊ

ነገሌ ሐምሌ 28/2009 በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ጉጂ ዞን መሬት ወስደው ግንባታ ያላካሄዱ ስድስት ባለሀብቶችን ፈቃድ መሰረዙን የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አብዱረህማን ፈጂ እንዳሉት ፈቃዱ የተሰረዘው ባለሀብቶቹ መሬት ወስደው እስከ ስድስት ዓመት ምንም አይነት ግንባታና ልማት ባለመጀመራቸው ነው፡፡

''በባለሃብቶቹ ተይዞ የነበረ 8 ሺህ 957 ሄክታር መሬትም ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል'' ብለዋል፡፡

መሬቱ ለባለሀብቶቹ ከስድስት ዓመት በፊት የተሰጠው ለግብርናና ለኢንደስትሪ ስራ አገልግሎት ዘርፎች እንዲውል እንደነበርም ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡

ከባለሀብቶቹ ተነጥቆ ወደ ባንክ የገባው መሬት በዞኑ ለሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች ተሰጥቶ የተረፈውን ለሌሎች ልማታዊ ባለሀብቶች ለማከፋፈል በእቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ግንባታ ጀምረው አገልግሎት ሳይሰጡ ለአራት አመት ያህል ለቆዩ 30 ባለሀብቶች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

በምእራብ ጉጂ ዞን 554 ሚሊዮን 535 ሺህ ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 384 ባለሀብቶች በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ባለሀብቶቹ በዞኑ ወደ ስራ የገቡት በግብር፣ በአገልግሎትና ኢንደስትሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንደሆነ ባለሙያው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል፡፡

ባለሀብቶቹ በዞኑ ለኢንቨስትመንት ስራ በወሰዱት 15 ሺህ 767 ሄክታር መሬት ወደ ስራ በመግባታቸው ከ11 ሺህ 900 ለሚበልጡ ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ከባለሃብቶች መካከል ወይዘሮ ሂሩት ብርሀኔ በሰጡት አስተያየት በምእራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ ለግብርና ኢንቨሰትመንት የተረከቡትን 314 ሄክታር መሬት  ለአራት አመት ያህል ሳያለሙ በማስቀመጣቸው መነጠቃቸውን ገልፀዋል፡፡

ባለሀብቷ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ ወደ ልማት ለመግባት ስምምነት ቢፈራረሙም በተለያየ ምክንያት እስካሁን ወደ ስራ ባለመግባታቸው ፈቃዳቸው ተሰርዞ መሬቱ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን