አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Wednesday, 02 August 2017

ሰመራ ሐምሌ 26/2009 በአፋር ክልል ለ2010 ዓ.ም የተመደበው በጀት ክልሉ ከሀገሪቱ እድገት ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆኑን ያሳያል ሲሉ የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ ገለጹ፡፡

በጀቱ የአርብቶአደሩን የድርቅ ተጋላጨነትና ድህነትን ለሚቀንሱ የልማት ሥራዎች ይበልጥ ትኩረት ማድረጉም ተመልክቷል።

የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ አሚና ሴኮ እንደተናገሩት፣ ምክርቤቱ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን በየዓመቱ የሚመድበው በጀት እያደገ ነው፡፡

ለተጀመረው የ2010 በጀት ዓመት ምክር ቤቱ ያጸደቀው 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ18 በመቶ ብልጫ መኖሩን ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ይህም "በሃገሪቱ እየተመዘገበ ከሚገኘው ተከታታይ እድገት ክልሎች ፍትሃዊ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የሕብረተሰብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ መንግስት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያመላክት መሆኑን ነው ምክትል አፈ ጉባኤዋ የተናገሩት።

ምክር ቤቱ ያጸደቀው በጀት በዋናነት የአርብቶአደሩን የድርቅ ተጋላጭነትና ድህነትን መቀነስ ለሚያስችሉ እንደ ውሃ፣ ትምህርት፣ ጤናና ተያያዥ የማህበራዊ ልማት ዘርፎች ትኩረት የሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ውሃን ማዕከል ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ ሥራ ለማከናወን እንዲሁም የሕብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጀቱ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ወይዘሮ አሚና አንዳሉት፣ በጀቱ የሕረተሰቡን ተሳትፎና ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላትን በክህሎት የማብቃት ሥራው የበለጠ ይጠናከራል፡፡

የምክር ቤት አባላት በተለይ ቋሚ ኮሚቴዎች በአስፈጻሚ አካላት ላይ ከዕቅድ ጀምሮ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ክትትል፣ ቁጥጥርና ድጋፍ በማድረግ በኩል የሚስተዋልባቸውን ክፍተት ለማረምም በበጀት ዓመቱ በትኩረት ይሰራል።

እንደአስፈላጊነቱ ፈጣን የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ የሕዝብ ውክልናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የሚደረግ መሆኑን ወይዘሮ አሚና ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ አህመድ መሃመድ በበኩላቸው፣ የተመደበው በጀት የሕብረተሰቡን ቀዳሚ የልማት ፍላጎት ታሲቢ ባደረገ መልኩ መደልደሉን ገልጸዋል፡፡

በተለይ እንደ ውሃ፣ ትምህርትና ጤና ተቋማት በበጀቱ ትኩረት ከተሰጣቸው የመሰረተ ልማት ሥራዎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

አቶ አህመድ እንዳሉት፣ የተመደበው በጀት ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው አግባብ ሥራ ላይ እንዲውል ተገቢ የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎች ይከናወናሉ።

ከዚህ በተጨማሪ ተጠሪነታቸው ለምክር ቤቱ የሆኑ  ተቋማት ውስን የመንግስት ሃብትን ለብክነትና ለምዝበራ እንዳይጋላጥ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ አንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሃምሌ 26/2009 ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ባለመስራታቸው በኢትዮጵያ የእብድ ውሻ በሽታን የመከላከል ተግባር የሚፈለገውን ውጤት እንዳላስገኘ ተገለጸ።

ችግሩን በአግባቡ ለመከላከል ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስገንዝቧል። 

ኢንስቲትዩቱ በሽታውን ለመከላከል መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ አውደ ጥናት ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።  

የእብድ ውሻ በሽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ 55 ሺህ ሰዎችን የሚገድል ሲሆን በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ስርጭቱ የከፋ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።  

በኢትዮጵያም በየዓመቱ 2 ሺህ 700 ሰዎች በበሽታው ለህልፈት እንደሚዳረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ።

በሽታውን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራት ቢከናወኑም የሚፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አልተቻለም። 

በሽታውን ከእምነት ጋር በማያያዝ ቶሎ ወደ ህክምና ተቋም አለመሄድ፣የኀብረተሰቡ ንቃተ ህሊና አለመዳበርና የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅት ማነስ በሽታውን ለመቆጣጠር ፈተና እንደሆኑም ይነገራል። 

በኢንስቲትዩቱ የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ኬዝ ቲም አስተባባሪ ዶክተር አሰፋ ደሬሳ ለኢዜአ እንደገለጹት በአገሪቱ በሽታውን ለመከላከል በላብራቶሪ ምርምርና ክትባት የታገዙ ሥራዎች ቢከናወኑም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ሊገኝ አልቻለም።     

በአገር አቀፍ ደረጃ ከሁለት ዓመት በፊት ውሾች እንዲከተቡ የሚያስገድድ ሕግ ቢወጣም ተግባራዊ አለመሆኑ በሽታውን በሚፈለገው ደረጃ መቆጣጠር አልተቻለም፡፡

ለዚህም ለሕጉ ተፈጻሚነት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ  እንደሚገባ አመልክተዋል።  

''በአዲስ አበባ በቀን ቢያንስ አምስት ሰዎች በእብድ ውሻ ተነክሰው ለህክምና ወደ ኢንስቲትዩቱ ይመጣሉ'' ያሉት ዶክተር አሰፋ በዓመት እስከ 1 ሺህ 500 ሰዎች በበሽታው እንደሚጠቁና ህክምና እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።      

በተለይ እድሚያቸው ከ 15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በአብዛኛው በበሽታው የሚጠቁ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።    

በቅረቡ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ ከ 230 ሺህ እስከ 300 ሺህ ውሾች እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ ባለቤት ያላቸው፤ 70 በመቶ ደግሞ ባለቤት የሌላቸው ናቸው።    

እንደ ዶክተር አሰፋ ገለጻ ጥናቱን መነሻ በማድረግ 70 በመቶ የሚሆነውን ውሻ በመከተብ የሰዎችን በበሽታው የመያዝ መጠን ወደ ዜሮ ለማውረድ ስትራቴጂ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል።      

ኢንስቲትዩቱ ላለፉት 60 ዓመታት ክትባት በማምረትና በማሰራጨት፣ዘመናዊ ህክምና እንዲኖር በማድረግ የራሱን አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን አብራርተዋል። 

አገልግሎቱን ወደ ክልሎች ተደራሽ ለማድረግም በደቡብ፣ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልሎች ላይ የላቦራቶሪ አገልግሎት አቅም ማሳደግ የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል። 

አስተባባሪው እንዳሉት ኀብረተሰቡ በበሽታው ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋትም የበሽታውን መንስኤ፣ ስርጭትና መቆጣጠሪያ መንገዶች ላይ ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል።   

በየጤና ተቋማቱ ወጥ የሆነ አሰራር መዘርጋት፣ዘመናዊ ክትባት ማቅረብ፣ባለሙያዎችን ማሰልጠን፣ በቀጣይ የሚተገበሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ አውደ ጥናት ላይ በአዲስ አበባ የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች፣የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሐምሌ 26/2009 በጣና ሀይቅ ብዝሃ ህይወት ላይ አደጋ የደቀነውን "እምቦጭ አረም" ለማጥፋት መንግስት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ምሁራን አሳሰቡ።

መንግስት በበኩሉ የክልሉን ሃሳብ በመደገፍ እምቦጭ አረምን ማጥፋት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሀይቁን ከጥፋት ለመታደግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃና መሬት ሃብት ልማት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ እንዳሉት፣ በጣና ላይ የተከሰተው አደገኛ አረም በአጭር ጊዜ በፍጥነት ተስፋፍቶ ሀይቁን ሊያጠፋው ስለሚችል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የመከላከሉን ስራ ሊያከናውን ይገባል።

አረሙን በአስቸኳይ ማጥፋት ካልተቻለ ሃይቁ በደለል ተሞልቶ የጣና በለስን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ብሎም የታላቁን ህዳሴ ግድብ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ጠቁመዋል።

 ዶክተር ጌቴ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት መስጠትና የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ ስርዓት በሚገባ ተጠንቶ ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር ከበደ ጫኔ የጣና ሃይቅ አደጋ ላይ መውደቅ በግድቡም ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ መንግስት የእምቦጭ አረምን አገራዊ ስጋት አድርጎ ማየት አለበት ብለዋል።

የእምቦጭ አረም ከጣና አልፎ ጭስ አባይ አካባቢ እንደታየ ጠቁመው፤ የህዳሴውን ግድብ ህልውና በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሃይቁ ላይ የተከሰተውን አረም ለማጥፋት መንግስት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

የአካባቢ ጥናትና ምርምር በማድረግ እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር የብዝሃ ህይወት ሃብቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል ከወዲሁ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙሴ ያዕቆብ እና በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት ዶክተር ሚናስ ህሩይ መንግስት ለአካባቢ ጥበቃ ስራዎች የሚሰጠውን ትኩረት ማጠናከር እንደሚኖርበት ተናግረዋል።

“ጣና በዙሪያው ከሰው ጋር ንክኪ ስላለው በደለል እየተሞላ ነው፤ በእምቦጭ አረምም እየተጠቃ ነው፣ በመሆኑም መንግስት ጉዳዩን አገራዊ ጉዳይ አድርጎ መውሰድና መስራት አለበት” ብለዋል።

የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጣና ላይ የተከሰተውን አደገኛ አረም ለመከላከል የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅድ መነደፉንና ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ከባህር ዳርና ከጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን አረሙን በዘላቂነት ማጥፋት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለዚህም የተለያዩ አገራት የተጠቀሙበትን ልምድ በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙ ሚኒስትሩ ጠቅሰው፤ በጊዜያዊነት ኅብረተሰቡን በማስተባበር የመመንጠር ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የፌደራል መንግስት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት አረሙን ለማጥፋት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

"እምቦጭ አረምን ማጥፋት የሚችል የቴክኖሎጂ አማራጭ ከየትም ይምጣ እንጠቀማለን፤ መንግስት የሀይቁን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታም አለበት" ብለዋል።

በመጀመሪያ የመንግስትና የህዝብ አጀንዳ መሆን እንዳለበት የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የክልሉ መንግስት በስፋት እየመከረበት ያለ አጀንዳ  በመሆኑ የፌደራሉ መንግስትም እንደሚወስደው ተናግረዋል።

Published in አካባቢ

አዲስ አበባ ሃምሌ 26/2009 በ2010 በጀት ዓመት ለታላቁ የህዳሴው ግድብ ከህብረተሰቡ 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የ 2009 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትና የ 2010 ዓ.ም እቅድ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ጽህፈት ቤቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከህብረተሰቡ በቦንድ ግዢ፣ በልገሳና በሌሎች ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች አንድ ነጥብ ስምንት ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ አንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወይም የእቅዱን 72 በመቶ አሳክቷል።

በዚህም ከአገር ውስጥ ቦንድ ግዢና ልገሳ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር፣ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ 129 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከልዩ ልዩ የገቢ ማስገኛ መርሃ ግብሮች ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሩጫ፣ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት፣ የህዳሴው ችቦ፣ የሥነ ጽሁፍ ምሽትና ሌሎችም ፕሮግራዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ መነሳሳት የተፈጠረባቸው ሁነቶች መሆናቸው ተገልጿል።

የመንግስትና የግል ሰራተኞች ለግድቡ ከተሰበሰበው ገንዘብ ላይ ከፍተኛው ድርሻ ያበረከቱ ሲሆኑ፤ ነጋዴውና ባለሀብቱ ቃል በገባው ልክ ድጋፍ አለማድረጉም በመድረኩ ተገምግሟል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶም የመንግስትና የግል ሰራተኞች ተሳትፎ ከአራት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ሲደርስ፤ የዲያስፖራው ተሳትፎ ደግሞ ከ783 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

በዚህም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት መጋቢት 2004 ዓ.ም ጀምሮ ከህብረተሰቡ የተሰበሰበው ገቢ መጠን ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንን በዚህ ወቅት እንዳሉት በህብረተሰቡ ፍላጎት ልክ የማነሳሳቱ ስራ ቢሰራ ከዚህ የበለጠ ገቢ መሰብሰብ ይቻል ነበር።

ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው የአደረጃጀትና አመራር ስርዓት ከኅብረተሰቡ ፍላጎት አኳያ በቂ እንዳልሆነ የተናገሩት አቶ ደመቀ፤ ይህንን የሚያስተባብረው አመራር የማደግ ጽኑ ፍላጎት ካለው ኅብረተሰብ ጋር በፍጥነት መንቀሳቀስ አለበት ብለዋል።

አመራሩ የህዳሴው ግደብ የሚገነባው በራሳችን የፋይናንስ ምንጭ መሆኑን በመረዳት የገንዘብ ማሰባሰብ ስራውን አዳዲስና ሳቢ የሆኑ ሆነቶችን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡን የበለጠ ማንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል።

የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረ ስላሴ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የህዳሴው ግድብ ግንባታ ከ 58 በመቶ በላይ ደርሷል።

በ2010 በጀት ዓመት ለግድቡ በቦንድ ግዢ፣በልገሳና በሌሎች የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ አጠቃላይ የሀብረተሰቡን ተሳትፎ አሁን ካለበት 10 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወደ 11 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በቦንድ ግዢ፣ከታላቁ ሩጫ፣ልገሳና ሌሎች የገቢ ማስገኛዎች በ2010 በጀት ዓመት ለግድቡ ገቢ የሚሰባሰብባቸው ፕሮግራሞች መሆናቸውን በእቅድ ትውውቅ መድረኩ ተገልጿል።

የህዳሴውን ዋንጫ አቀባበል ሲደረግ እንዲሁም በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ ያለው ተሳትፎ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ግድቡን የመንግስት ሰራተኞች፣ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን፣የውጭ አገር አምባሳደሮች፣ተማሪዎች፣የመከላከያ ሰራዊት አባላትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በድምሩ ከ28 ሺህ በላይ ሰዎች ጎብኝተውታል።

ግድቡ በደለል እንዳይሞላና የአገልግሎት ጊዜውን ለማራዘም የግድቡ ተፋሰስ የሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከ19 ሚሊዮን በላይ የሰው ሃይል የተሳተፈበት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ የጉልበት ዋጋ  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎችንም ተሰርተዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

አዲስ አበባ ሐምሌ 26/2009 በሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰሩ ጥናቶች የሕዝቡን ትክክለኛ አስተያየት ከማንጸባረቅና ተገቢውን መረጃ ከመስጠት አኳያ ጉድለት እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አዘጋጅነት የተካሄደው የሚዲያና የኮምዩኒኬሽን ፎረም ትናንት ተጠናቋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደገለፁት የህዝብ አስተያየት ጥናቶቹ በናሙና አመራረጥና በመጠይቅ አሞላል ጉድለት ይታይባቸዋል።

የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለጹት፤ የህዝብ አስተያየት ጥናቶቹ አርሶ አደሩን፣ ምሁሩን፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የህብረተሰብ አካላትን ማካተትና ገለልተኛ መሆን ይኖርባቸዋል።

በህዝብ አስተያየት ጥናቶቹ የሚስተዋሉ ችግሮች የሚያስከትሉትን አገራዊ ጉዳት በመገንዘብ ችግሮቹን ማስተካከል እንደሚያስፈለግም ነው ዶክተር ነገሪ ያሳሰቡት፡፡

ፎረሙ በ"ሚዲያ ሪፎርሙ" መነሻ ጽሁፍ ላይም  ተወያይቷል።

ሪፎርሙ መገናኛ ብዙሃንና ኮምዩኒኬሽን ይዘት፣ ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እንዲሁም  ዘርፉን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታና ከህዝቡ ፍላጎት ጋር ለማጣጣም የሚያስችል መሆኑ  በውይይቱ  ተገልጿል።

የኪነ ጥበብ ዘርፎችን ጨምሮ የህዘብና የግሉ መገናኛ ብዙሃን  በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ሚዛናዊ  መረጃ በማድረስ ረገድ አገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን እንዲያሳድጉ ይረዳልም ተብሏል።

በመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት መሪነት የሚካሄደው ሪፎርም  ፅህፈት ቤትና ኮሚቴ ተዋቅሮለት ሰነድ የማዘጋጀት ስራው ከተጀመረ ሶስት ወራት አስቆጥሯል።

አስፈላጊ ሰነዶችን የማዘጋጀት ስራው በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

Published in ፖለቲካ

አዲስ አበባ ሃምሌ 26/2009 የአርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) የቀብር ስነ ስርዓት በአዲስ አበባ መንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ቤተሰቦቻቸው፣ አርቲስቶችና  አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል።

አባባ ተስፋዬ በመባል የሚታወቁት አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው በተወለዱ በ93 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል፡፡

አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ በቀድሞው የባሌ ክፍለ ሃገር ልዩ ስሙ ከዶ በተባለ ስፍራ ሰኔ 20 ቀን፣ 1916 ዓ.ም ከአባታቸው ኤጀርሳ በዳኔ እና ከእናታቸው ዮንዢ ወርቅ በለጤ ተወለዱ።

አባባ ተስፋዬ የልጅነት የትምህርት ጊዜያቸውን በጎባ ከተማ መከታተል ጀምረው ቤተሰቦቻቸው በስራ ምክንያት ወደ ጊኒር በመቀየራቸው ትምህርታቸውን በጊኒር ቀጠሉ፡፡

ከዚያም ወደ ሃረር በመሄድ የፈረንሳዮች ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን ተከታለው፥ በ14 ዓመታቸውም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡

ከዚያም ከአዲስ አበባ ባህልና ቲያትር አዳራሽ በተዋናይት ተቀጥረው የተለያዩ ተውኔቶችን ተጫውተዋል።አባባ ተስፋዬ በፋሽስት ጣልያን ወረራ ወቅት ወላጆቻቸውን ልጅ እያሉ ማጣታቸው የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ወላጆቻቸው በጦርነቱ በመሞታቸው አያታቸው አቶ ሳህሉ ያሳደጓቸው ሲሆን አባት ሆነው ያሳደጉኝ አቶ ሳህሉ ናቸው፤ አቶ ኤጀርሳ በዳኔ ቢውልዱኝም የአባቴ ስም በሳህሉ እንዲጠራ ነው የምፈልገው በማለት በመግለጻቸው ምክንያት ያሉት ቃል ፀንቶ አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ  በሚል መጠራት ችለዋል፡፡

የበርካታ ሙያዎች ባለቤት አርቲስት ተስፋዬ የመድረክ መሪ፣ ተዋናይ፣ ሙዚቀኛ፣  ትርኢት አቅራቢ፣ ድምፃዊ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋች፣ የውዝዋዜ አሰልጣኝ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ደራሲና ተረት ነጋሪ ነበሩ።

በገና፣ ክራር፣ መሰንቆ፣ አኮርድዮንና ትራምፔት ከሚጫወቷቸው የሙዚቃ መሳሪያዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በድምጻዊነት ደግሞ "ዓለም እንደምን ነሽ ደህና ሰነበትሽ ወይ" እና "ፀሃይ" የተሰኙ ዘፈኖቻቸው በአድማጮች ዘንድ ተወዳጅ ናቸው።

‘ብጥልህሳ’፣’ ነው ለካ’ ፣ ‘ጠላ ሻጯ’ በድርሰት ያበረከቷቸው ተውኔቶች ሲሆኑ አራት የተረት መጻሕፍት ለልጆች አበርክተዋል።

ከአዲስ አበባ ባህልና ቲያትር አዳራሽ በኋላም በብሔራዊ ቲያትር ሰርተዋል

ሀ ሁ በስድስት ወር፣ የኤዲፐስ ንጉስ፣ አሉላ አባ ነጋ፣ ዳዊትና ኦርዮን፣ ኦቴሎ፣ አስቀያሚዋ ልጃገረድ እና ስነ ስቅለት ደግሞ አባባ ተስፋዬ የተጫወቱባቸው ተውኔቶች ናቸው።

አርቲስት ተስፋዬ በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ፥ የልጆች ጊዜ የሚል ፕሮግራም በመቅረጽ ለልጆች በሚጠቅም መልኩ አባታዊ ምክራቸውን ሲያቀርቡም ቆይተዋል።

"ደህና ናችሁ ልጆች የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች እንደምን አላችሁ ልጆች። አያችሁ ልጆች የኢትዮጲያ ቴሌቭዥን የልጆች ግዜ ዝግጅት ክፍል እናንተን ለማስደሰት ልክ በሰአቱ ይገኛል። እናንተስ ዝግጁ ናችሁ? " በሚል አባባ ተስፋዬ በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን የልጆች ግዜ ፕሮግራም ላይ ዝግጅታቸውን ማቅረብ ሲጀምሩ የሚያሰሙት ንግግር በተመልካቾች የሚረሳ አይደለም።

በ1950ዎቹ በነበረው የኮሪያ ጦርነት ለኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቃ ሠራዊት ልዩ ልዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን በኮሪያ በመገኘት ካቀረቡት አንዱ የነበሩት ተስፋዬ ሳህሉ የአሥር አለቃነት ማዕረግ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

በሳምንቱ መጨረሻ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪዎቹን በማስመረቀበት ወቅት ኮሌጁ ለአባባ ተስፋዬ በኪነ ጥበብ ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ አይዘነጋም።

በትዳር ሕይወታቸውም አንድ ልጅና አምስት የልጅ ልጆችን አፍርተዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ሐምሌ 26/2009 መንግስት የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል የምርምር ማዕከላትንና አስፈላጊ መሳሪያዎችን   በማሟላት ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ተመራማሪዎች ጠየቁ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው ስድስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ማህበር ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢዜአ ሪፖርተር የጉባኤው ተሳታፊ  ኢትዮጵያውያን የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ተመራማሪዎችን በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ዙሪያ አነጋግሯል። 

የሰላም ቅሪተ አካልን ያገኙት ተመራማሪ ፕሮፈሰር ዘረሰናይ አለምሰገድ እንደገለጹት በቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ጥናቶች የተገኙ ቅሪተ አካላትን ለመንከባከብ የሚያስችሉ መሳሪዎች ውስን ናቸው።

አሁን ያሉት መሳሪያዎች በአገሪቷ የሚገኙ ቅሪተ አካላት ምርምርና እንክብካቤ ለማድረግ በቂ እንዳልሆኑ ገልጸው መንግስት በዚህ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

በጀርመን ቱቢንገን ዩኒቨርስቲ የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ተመራማሪው ዶክተር ዮናታን ሳህሌ በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚውሉ ማዕከላትን መገንባት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ምርምር በማድረግ የተገኙ ቅሪተ አካላትን የሚያከማቹና ለቀጣይ ጥናትና ምርምር ዝግጁ የሚያደርጉ ማዕከላት ግንባታ በስፋት መከናወን እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

በሄብሪው ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ተገኑ ጎሳ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘርፉ በሚደረጉ ምርምሮች የሚገኙ ቅሪተ አካላት እየጨመሩ መምጣታቸውንና ለነዚህም የሚሆን ቦታ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በቅሪተ አካላት ላይ በሚደረጉ ምርምሮች የድንጋይ ቁሳቁስ፣ የሰውና የእንስሳት ቅሪት አካላት በቁፋሮ በስፋት እየተገኙ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለእነዚህ ቅሪተ አካላትና ቅርሶች ማስቀመጫ የሚሆን የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደሚያስፈልግና መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና እንክባካቤ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ እንዳሉት በቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ላይ ለሚደረግ የጥናትና ምርምር ተግባር የሚውሉ ማዕከላት ግንባታና መሳሪያዎችን የማሟላት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በባለስልጣኑ ግቢ ውስጥ የሰው፣የእንስሳትና የእጽዋት ቅሪተ አካል ምርምር ማከናወኛ ቤተ ሙከራ ተገንብቶ  ስራ ላይ መዋሉንም ገልጸዋል።

ቤተ ሙከራው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ተመራማሪዎች ለሚያደርጓቸው የጥናት ምርምር ስራዎች በማዕከልነት እያገለገለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የቤተ ሙከራው መገንባት በቂ እንዳልሆነ ገልጸው የሰው ዘር አመጣጥ ሙዝየም ለመገንባት የዲዛይን ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሚገነባው ሙዝየም ቅሪተ አካላትን ከማሰባሰብ ባለፈ የምርምርና ጥናት ስራዎች የሚከናወኑበት እንደሚሆን ነው አቶ ዮናስ ያብራሩት።

ቅሪተ አካሉ ደህንነቱ እንዲረጋገጥ የሚያደርገው የሲቲ ስካን ማሽንና ሌሎች ለምርምርና እንክብካቤ የሚያገለግሉ መሳሪዎች በቤተ ሙከራው እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በ 2009 ዓ.ም ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ሌሎች መሳሪያዎች ግዢ እንደተከናወነ አስታውሰው መሳሪያዎቹ በአሁኑ ወቅት በቤተ ሙከራው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የመሳሪያዎቹ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ከግዥ ይልቅ  በውሰት የመጠቀም ስራ መካሄዱንም ተናግረዋል።  

ኢትዮጵያ በቅሪተ አካል ምርምርና ቅድመ ታሪክ ጥናት ከ12 በላይ ቅሪተ አካላት ተገኝተውባታል።

Wednesday, 02 August 2017 22:17

መንታ ህዝቦች

ተካ ጉግሳ /ኢዜአ/

ሁለቱም ከአንድ ማህፀን የተገኙ ፣ በአንድ አብራክና አምሳል የተፈጠሩ መንታዎች ናቸው። ወንድማማቾችና እህትማማቾች የሆኑት መንትያዎቹ የውዲቷ ሀገር እምዬ ኢትዮጵያ ልጆች ናቸው - የአማራና የትግራይ ህዝቦች ።

ለጋራ እናታቸው ፍቅርና ክብር ሲሉም በጋራ ደማቸውን አፍስሰዋል ። አጥንታቸው ከስክሰዋል።ውድ ህይወታቸውንም ገብረዋል ። ከሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ጋር በመሆን ደርቡሽ ገባ ሲባል ጎንደር ላይ በጀግንነት ተፋልመዋል ።እናታቸውን ጣሊያን እንደወረራት ሲሰሙ አድዋ ላይ ተሰባስበው አስደማሚ ገድል በመፈፀም አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ህዝቦችን በሙሉ አኩርተዋል ።

የቅርቡን ታሪክ ብቻ ብንመለከት እንኳ አምባገነኑን የደርግ መንግስት ለመጣል በተደረገው ትግል በአንድ ምሽግ ውስጥ ውለው እያደሩ ፣ የደፈጣና የቆረጣ ስልቶች እየቀየሱ ፣ ወደማጥቃት እርምጃ የተሸጋገሩትና ዳግም ላይመለስ የደመሰሱት ለጋራ ዓላማ በጋራ የተሰለፉ ህዝቦች ናቸው ።

ለአንድ እናት አብረው የሞቱና በአንድ ጉድጓድ አብረው የተቀበሩ ጭምር የአማራና የትግራይ ህዝቦች አብረው ለዘመናት የነበሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ናቸው ። አሁንም ቢሆን የጋራ ጠላታቸውን በጋራ በመለየት ፀረ ድህነት ትግላቸውን አጧጡፈው በልማት ጎዳና ወደፊት በመገስገስ ላይ ይገኛሉ ።

ታዲያ! የሰይጣን ጆሮ ይደፈንና በቅርቡ ይህን ለዘመናት ተፈቃቅረው ተቻችለውና ተዋደው በጋራ ለሃገራቸው ልማትና እድገት ሲሰሩ የነበሩ እነዚህን መንታ ህዝቦች በመካከላቸው ነፋስ ለማስገባት አልተሳካላቸውም እንጅ ድብቅ አጀንዳ ያነገቡ ሃይሎች ሞክረው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለነገሩማ አንዳንዴ እግር ከእግር ጋርስ ይጋጭ የለ? በአንዳንድ አካባቢዎች ንፋሱ የገባው ግን በህዝቦች ችግር ሳይሆን ስውር አጀንዳ አንግበው የስልጣንና የጥቅም ፍላጎታቸውን ለማሟላት የትምክህትና የጠባብ ሃይሎች በረጩት መርዝ ነበር ።

በፀረ ሰላምና ፀረ አንድነት ሃይሎች የተጠነሰሰው ሴራ ቆስቋሽነት ባለፈው ዓመት ተከስቶ በነበረው ያለመግባባት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ክስተቱ የአማራንና የትግራይ ህዝቦችን ክፉኛ አበሳጭቷል። ምን ሲደረግ በመካከላችን ንፋስ ይገባል የሚል መነጋገሪያ አጀንዳም ሆኖ ሰንብቷል ።

ጊዜአዊ ግጭቱን የፈጠረው ቁርሾ በዘለቄታው እንዲፈታ ለማድረግ በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ የአገር ሽማግሌዎች እንቅስቃሴ የጀመሩት ከሁለት ወራት በፊት ነበር ። የሰሜን ጎንደርና የትግራይ ምእራባዊ ዞን ሽማግሌዎቹ ደግሞ ለሰላም ጥረት የቀደማቸው አልነበረም ።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ለማደስ ፣ ወደነበረበት ለመመለስና የበለጠ ለማጠናከር የሃገር ሽማግሌዎቹ ከሁለቱ አካባቢዎች የህዝብ ተወካዮች ለውይይት ጠርተዋል። ቀዳሚው ውይይት በሳንጃ ከተማ ነበር ።  አንደኛው ተነስቶ ጠቡ የተነሳው እንደዚህ ነው ሲል ሌላው ደግሞ እኛ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ነን። ድሮም ቢሆን ተጣልተን አናውቅም  ሲል ሁኔታውን የገረማቸውን የሁለቱም ህዝቦች አንድነት ይበልጥ መቆራኘቱን ለማስረዳት የፈለጉ የአካባቢው አዛውንት ተነሱና እንዲህ አሉ።

"እናንተ ሰዎች አማራና ትግራይ ወንድማማቾችና እህትማማቾች ናቸው አትበሉ’’ ሲሉ ተሰብሳቢው በሙሉ ደነገጠ ። ሰላም ፈልገን ለውይይት ስንሰባሰብ እንዲህ የሚሉት አነጋገር ምን ይሉታል ብሎ ያጉረመረመም ነበር ። አዛውንቱ ግን ምን ለማለት እንደፈለጉ አስቀድመው ያውቃሉና ሃሳባቸው ቀጠሉ ።

"አንዲት እናት በየሁለት ወይም በየአራት አመቱ ስትወልድ በሚወለዱት ልጆች መካከል የእድሜ መበላለጥ ስላለ ልዩነት ይታይባቸዋል። የትግራይና የአማራ ህዝቦች ግን እንደዚህ አይደሉም። በአንድ ቀን የተረገዙ ፣ በአንድ ቀን የተወለዱ መንታ ህዝቦች ናቸው "  በማለት አንዱ የበላይ አንዱ ደግሞ የበታች ሳይሆን የእምዬ ኢትዮጵያ መንታ ልጆች መሆናቸውን አሰመሩበት ። ሁሉንም ያግባባ አስደማሚ ንግግር ነበር ።

በዞን ደረጃ የተጀመረው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በክልል ደረጃ ይበልጥ ለመቀራረብ፣ አንድነታቸውን ለማጎልበትና በጋራ ጠላታቸው ዙሪያ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የሁለቱም ክልሎች የሃገር ሽማግሌዎች በቅርቡ በመቀሌ ከተማ ሲመክሩ ሰንብተዋል። 

እንግዳ ተቀባይ የሆነው ኢትዮጵያዊ ባህላችን በእነዚህ መንታ ህዝቦች መካከልም በጉልህ  ታየ። የአማራ ህዝብ ተወካዮች መቀሌ ላይ ወደሚካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ሲመጡ ከዳንሻና ወልቃይት እስከ ዋጃና አላማጣ ድረስ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው። ሁለቱም ህዝቦች ተሳሳሙ፣ተቃቀፉ፣ በናፍቆት እንባም ፍቅራቸውን ገለፁ።

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን በደጉዓ ተምቤን የሚገኘው ከሁለቱም መንትያ ህዝቦች አብራክ የወጡት እህት ድርጀቶች የነበሩበትና የኢህአዴግ የዘመቻ መምሪያ ማእከልንም ጎብኝተው አዳራቸውን መቀሌ አደረጉ ።

"የሁለቱም  ህዝቦች አንድነት የቆየ መሆኑን ታሪክ ያስረዳል።አንድነቱ እንዴት ነው ቢባል በትግራይ ችግር ሲፈጠር የአማራ ህዝብ ቶሎ ይደርስለታል፤ የአድዋ ወረራ አንዱ አብነት ነው። በአማራ ችግር ሲፈጠር የትግራይ ህዝብ ቶሎ ይደርስለታል ለዚህም የደርቡሽ ወረራ ሌላው አብነት ነው’ ብለዋል ከትግራይ የተወከሉት መልአከፀሃይ ተሻለ ገብረሚካኤል።

ከአማራ ክልል የተወከሉ አቶ ሞላ መኮንን  ሃሳባቸውን እንዲህ ይገልጻሉ "እኛ ያነሳሳን ትውልድን የማዳን ጉዳይ ስለሆነ ነው። በወቅቱ የተከሰተው ግጭት ወደ ሌላ እንዳያመራ ስለምንሰጋ ነው። ምክንያቱም ጦርነት ከዚህ በፊት አይተነዋል።ከሁከትና ከብጥብጥ የሚገኝ ትርፍ ስለሌለ ትርፍ የሚገኘው በሰላም ብቻ መሆኑን ስለተረዳን ነው"በማለት ነበር ያስረዱት፡፡

በጉባኤው ላይ የሁለቱም ክልሎች ርእሰ መስተዳድሮች የሁለቱም ህዝቦች አንድነት በደም በአጥንት የተገነባ መሆኑን በሚገልፅ መልኩ የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱ እንደገለጹት በአማራና በትግራይ ህዝቦች መካከል የነበረው ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የደመቀው ደርግን ለመዋጋት በረሃ ከወጡት ድርጅቶች መካከል በኢህአፓ የነበሩት ሃይሎች ‘ ደርግን ማሸነፍ ተራራን በገመድ እንደመጎተት ነው’ ፣ ‘ፖለቲካና ኮረንቲ በሩቁ ‘ እያሉ ወደ ከተማ በሚመለሱበት ወቅት ደርግ በከተሞች ወጣቱን በቀይ ሽብር ሲጨፈጭፍ "ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው’’ እያሉ በወቅቱ የነበረው ጨለምተኝነት በአሸናፊነት በተወጡበት ወቅት ነበር ብለዋል።

የአገሪቱን ሰላም፣ ልማትና እድገት የማይመኙ ሃይሎች ያገኙትን ቀዳዳ በመጠቀም ህዝብ ለህዝብ ለማጋጨት ሁሌም እንደሚሰለፉ የተናገሩት ርእሰ መስተዳድሩ " እነሱ በሚፈጥሩት ችግር ሳንንበረከክ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ በማጠናከር ያደጉ አገሮች የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ሁሌም መገስገስ ይኖርብናል" ብለዋል።

አያይዘውም "ሽማግሌዎቹ በራሳችሁ ተነሳሽነት እኛ ማድረግ የነበረብን ትልቁ ጉዳይ አልማችሁ፣ሁላችንም አንቀሳሳቅሳችሁ የህዝቦች ግንኙነት እንዲጠናከርና የህዝብ ጥቅም እንዲከበር ላደረጋችሁት ጥረት ደግሜ ታላቅ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ’’ ሲሉ አስረድተዋል።

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው  በበኩላቸው የትግራይና የአማራ ህዝቦች ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ በጠንካራ የደምና የአጥንት ገመድ ተሳስሮ መቆየቱን ተናግረዋል።

"የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነቶች የሚያሻክሩ ችግሮችን በመፍታት አንድነትን ማጠናከር፣በህዝቦች መካከል ትክክለኛ መረጃ እንዲኖር አንዱ ህዝብ ለሌላው በጎ አመለካከት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል።ምክንያቱም የጥላቻ ዘርን በመዝራት የፍቅር አዝመራን መሰብሰብ አይቻልምና " ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኝነቱን ለማጠናከር የሃገር ሽማግሌዎቹ የጀመሩትን ጥረት አቶ ገዱ አድንቀው የሽማገሌዎቹን በጎ ጅምር ዳር ለማድረስ የሁለቱም ክልሎች አመራሮች የየድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በህዝቦች መካከል በደምና በአጥንት የተገነባው ታሪካቸው ይበልጥ እየተጠናከረና እየደመቀ እንዲሄድ ሽማግሌዎቹ ዘር እየዘሩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ገዱ ጅምሩ ቀጣይነት እንዲኖረውና ወደ ምክክር መድረክ እንዲሸጋገር አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።

ኮንፈረንሱ "የትግራይና የአማራ ህዝቦች አብሮ የመኖር ወርቃማ እሴቶችና ታሪካዊ ዳራ’’ በሚል ርእስ ፅሁፍ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ ትምህርት ክፍል ዶክተር ሃይሌ ሙሉቀን ባቀረቡት ፅሁፍ የመጀመሪያው ውይይት ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ታሪክ መንግስታት ቢቀያየሩም ህዝቦችዋ ተጋጭተው እንደማያውቁ ሙሁሩ አውስተው ከቅርብ አመታት ወዲህ እየተከሰቱ ያሉትን ችግሮች አመራሮቹ በሰከነ መንፈስ ሊያዩዋቸው ይገባል ብለዋል።

"የዲሞክራቲክ ብሄርተኝነት ግንባታና የፌዴራል ስርዓት አስፈላጊነት በኢትዮጵያ " በሚል ርእስም የአርብቶ አደርና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር በነበሩት በአቶ ካሳ ተክለብርሃን ለውይይት የሚሆን መነሻ ሃሳብ ቀርቧል።

አቶ ካሳ ተከለብርሃን በዚሁ ወቅት ካነሷቸው ጉዳዩች መካከል ፡-

-የትግራይና የአማራ ህዝቦች ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትፈጠር የጎላ አስተዋፅኦ ማድረጋቸው፣

- የህወሓትና የብአዴን ግንኙነት ከሁለቱም ህዝቦች የወጡ መሆናቸው ህዝቦቹም ለዘመናት የቆየና በደም የተሳሰረ አንድነት ያላቸው መሆኑን

- ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና የአገሪቱን የወደፊት እጣ የሚወስን ህገመንግስት በዚች አገር እንደኖር ሁለቱም ህዝቦች የጎላ አስተዋፅኦ ማደረጋቸውን አስረድተዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በሁለቱም ክልሎች የሚከሰቱ አንዳንድ ግጭቶች በዋነኛነት መቆጣጠር ያለባቸው የሁለቱም ክልላዊ መንግስታት ናቸው ያሉት ደግሞ የህወሓት ነባር ታጋይ አቶ ስብሓት ነጋ ናቸው።

"በትግራይ ክልል የሚፈጠር ችግር በዋነኛነት ተጠያቂው ህወሓት/ኢህአዴግ ሲሆን በአማራ ክልል ለሚፈጠረው ችግርም ብአዴን/ኢህአዴግ ነው’’ ብለዋል አቶ ስብሓት፡፡ ምክንያቱም ሁለቱም ብሄራዊ ድርጅቶች በዋነኛነት ክልሎቹን የህዝቦችን እኩልነት ባማካለ እየመሩት ስለሆነ በአካባቢያቸው ያሉትን ማናቸውም እንቅስቃሴ የመከታተልና የመቆጣጠር ሃላፊነትና ግዴታ ስላለባቸው መሆኑ ነው።

በመሆኑም የችግሩን ምንጭ ማውጣትና በሱ ላይ መታገል አለብን ያሉት አቶ ስብሃት ምንጩን ትተን ወደ ጅረቱ ብንገባ በቀላሉ ልናደርቀው አንችልም ሲሉ ተናግረዋል ። 

ከኮንፈረንሱ በኋላ ተሳታፊዎቹ ያገኙትን ግንዛቤ አስመልክቶ ከሰሜን ጎንደር ምስራቅ በለሳ በህዝብ የተወከሉት አቶ ስፋፌ ተመስገን በሰጡት አስተያየት በህዝቡ ለሚነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች የየአካባቢው መስተዳድሮች ፈጣን ምላሽ ባለመስጠታቸው እድሉን ፀረ ሰላም ሃይሎች ሊጠቀሙበት ችለዋል ብለዋል።

"የሚታገሉን የኢትዮጵያን እድገት የማይመኙ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ብቻ ሳይሆኑ ጠባብነት፣ ትምክህትና ኪራይ ሰብሳቢነት ጭምር ናቸው’’ ያሉት ደግሞ ከሰሜን ጎንደር ትክል ድንጋይ ወረዳ የተወከሉት ወ/ሮ ጥላነሽ ማሞ ሲሆኑ በሰሜን ጎንደር የገንዘብ ሰነዶች ሳይቀሩ እንዲቃጠሉ መደረጉን አስረድተዋል።

ከትግራይ ምእራባዊ ዞን ከሑመራ ከተማ ህዝብ የተወከሉት አቶ ስዩም ኪዳነ በበኩላቸው አንድነታችን በደም የተገነባ መሆኑን ሳያውቁ ሁከትና ብጥብጥ ፈጥረው ሊለያዩን የሞከሩት ዛሬም ሆነ ነገ የማይሳካላቸው መሆኑን ደጋግመን ልንነግራቸው ይገባል ብለዋል።

ከሰሜን ጎንደር ዓዲ አረቃይ ወረዳ የተወከሉት አቶ ሞላ ጫቅሌ በበኩላቸው ነውጠኞች ከፈጠሩት ሁከት በተጨማሪ በየአካባቢው ያሉት አመራሮች የህዝብን ችግር በወቅቱ ባለመፍታታቸው የተፈጠረ መሆኑን አውስተው የሁለቱ ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች ጉዳዩን በጥልቀት በማየት አስተማሪ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ሲሉ አስረድተዋል።

"የመስተዳድር አካላት ከጠነከሩ እያንዳንዱን ችግር ፈጣሪ ከህዝብ ነቅለን ለማውጣት የሚያዳግተን የለም። በጠራራ ፀሃይ ስለተፈፀመ በየትኛው ቦታ ምን እንደተሰራ በግልፅ እናውቀዋለን ፤በዓዲኣርቃይና አካባቢው ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው ብአዴን ነው፣ በማይፀብሪና አካባቢው ለተነሳው ችግር ደግሞ ተጠያቂው ህወሓት ነው’’ በማለት አሁንም አመራሩ ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ቄስ ባይለየኝ አለማየህ ከሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ የመጡ ናቸው ። በሁለቱም ክልሎች ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች የተሰራበት ኮንፈረንስ መሆኑን አውስተው ለዘመናት የቆየውና በደም የተሳሰረው የሁለቱንም ህዝቦች አንድነት ዘላቂ ለማድረግ ኮንፍረንሱ የደረሳቸው ድምዳሜዎች ወደ ህብረተሰቡ ማውረድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከወልዲያ ከተማ በህዝብ የተወከሉ ወይዘሮ ብርሃኔ አያሌው እንደገለጹት  "በዚህ መድረክ ያገኘሁት ነገር የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ልዩነት በቋንቋ ብቻ ነው ። የተለየ ጥቅም ያለው የለም። መድረኩ ለህዝቡም ለአመራሩም የቤት ስራ የሰጠበት ነበር። ይህ ችግር በአስቸኳይ ተፈቶ ህዝቡ ወደ ልማት ስራው እንዲገባ መደረግ አለበት ።  ትስስራችንና ፍቅራችን  አጠናክረን የወጣንበት መድረክ ነው የሚል እምነት አለኝ’’ በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል ።

ከመቀሌ ሓድነት ክፍለከተማ በህዝብ የተወከሉት አቶ በየነ ይልማ እንደገለጹት በሽማግሌዎች ተነሳሽነት የተጀመረው ጥረት ቀጣይነት እንዲኖረው በየደረጃው የተወከልን ይበልጥ መስራትና ሌላ ችግር እንዳይፈጥር የበኩላችን መጫወት ይኖርብናል ብለዋል።

በባህላዊ የግጭት አወጋገድ ስርዓትና በአፍሪካ ያሉት ተሞክሮዎች ምን እንደሚመስሉ ከደቡብ አፍሪካና ከሌሎች የአህጉሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በመተባበር ጥናትና ምርምር በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተጀምሯል።

በዩኒቨርሲቲው በዘረፉ ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉት መካከል የስነህዝብ ጥናት ተቋም ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶክተር ክንፈ አብርሃና በዩኒቨርሲቲው የህግና ስነመንግስት ኮሌጅ ዲን አቶ ገብረህይወት ሓዱሽ ናቸው።

በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በግጭት አፈታትና ግጭቱን አስቀድሞ በመከላከል በኩል ከጅምር ያለፈ ጠንካራ ሥራ አለመሰራቱን ዶክተር ክንፈ አመልክተዋል፡፡

"አንድ ነገር በዘላቂነት የሚፈታው ደግሞ ዋናው ምንጩን በማድረቅ ነው። ይህም በሌላ ሳይሆን በእንደዚህ አይነት ውይይት ነው ምንጩን ማወቅና ማድረቅ የምትችለው። ስለዚህ ዋናው ምንጩ ምን ነበር፣ በዚህ ላይ ዋናው ተዋናይ የነበረው ማን ነው፣ሰዉን ካወቅክ ለመቅጣት ብቻ ላይሆን ይችላል። ግን አስተሳሰቡ ከምንድነው የመነጨው የሚለውን በማወቅ ከዋናው ምንጩ መድረቅ አለበት’’ ብለዋል ።

የሀገር ሽማግሌዎች በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል የነበረውን መልካም ግንኙነት ለማጠናከር ያደረጉት ጥረት በማህበረሰቡናበመንግስት ምስጋና ሊቸረው እንደሚገባ የጠቆሙት ደግሞበዩኒቨርሲቲው የህግና ስነ መንግስት ኮሌጅ ዲን አቶ ገብረህይወት ሓዱሽ ናቸው፡፡

"ባህላዊ የግጭት አፈታት ጎጂና ተጎጂን በማገናኘት የማስታረቅ ስራ የሚሰራበት በመሆኑ አሸናፊም ተሸናፊም የሌለበት ነው" የሚል አስተሳሰብ አላቸው ።

 በተጨማሪም በሕብረተሰቡ መካከል የሚታዩ ግጭቶች በአጭሩ እልባት እንዲያገኙ ስለሚያደርግ እንደ ዴንማርክና ፖላንድየመሳሰሉት አገራት ከዘመናዊው ግጭት አፈታት ጎን ለጎን እየተጠቀሙበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያልተበረዘና ያልተከለሰ የግጭት አፈታት ልምድ እንደሚኖራቸው ጠቁመው፣ ከፍተኛየትምህርት ተቋማት እነዚህን ልምዶች ቀምረው ለአገር ጥቅም ማዋል እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ኮንፈረንሱ መግባባትና ፍቅር የታየበት ፣ በህዝቦች መካከል ጥላቻና መቃቃር የሚባል ነገር አለመኖሩን በተግባር የታየበትና በህዝቦች መካከል ቅራኔ ለመፍጠር የሚራወጡትን አደብ እንዲገዙ የተጠየቀበት የሰላም መድረክ በመሆኑ ጠቀሜታው የላቀ ነበር ።

በኮንፈረንሱ ማጠቃለያም ተሳታፊዎቹ ባለ አስራ አንድ ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጡ ሲሆን ቀጣይ የሰላም ተልእኮ ለማስፈፀም በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ቃል በመግባት ተስማምተው ተለያይተዋል ።

 

 

 

Published in ዜና ሓተታ

አዳማ ሐምሌ 26/2009 በምስራቅ ሸዋ ዞን  እስካሁን 110 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የፅህፈት ቤቱ የእቅድ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ጎሳ ወርቁ ለኢዜአ  እንደገለፁት በዘር የተሸፈነው መሬት በምርት ወቅቱ ይለማል ተብሎ ከታቀደው ከ439 ሄክታር  ውስጥ ነው። 

የታረሰው መሬት በበቆሎ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ፣ ምስርና ባቄላ ዘር የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል ።

ለዚህም 336 ሺህ 506 ኩንታል ማዳበሪያና 15 ሺህ ኩንታል ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ነው ያብራሩት።

በምርት ወቅቱ  በሰብል ልማት እየተሳተፉ ካሉ 163 ሺህ 372 አርሶ አደሮች ውስጥ 26 ሺህ 830ዎቹ  ሴቶች ናቸው።

ባለሙያው እንዳሉት በምርት ወቅቱ ከሚለማው አጠቃላይ መሬት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የሉሜ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በቀለ ጣፋ በሰጡት አስተያየት በተያዘው መኸር እርሻ ሶስት ሄክታር ማሳቸው ላይ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ገብስና ሽንብራ ለማልማት አቅደው እየሰሩ ነው።

እስካሁን የማሳ ዝግጅት ስራ አጠናቀው ሁለት ሄክታር የሚሆነውን በማሽላና በቆሎ ዘር መሸፈናቸውን ገልፀዋል።

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ሐምሌ 26/2009 በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዩንየኖች ለውጭ ገበያ ከላኩት የግብርና ምርት ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ገቢ መገኘቱን  የክልሉ ሕብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው የግብይት ትስስር ባለሙያ አቶ አማረ አደመ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ገቢው የተገኘው ራስ ጋይንት፣ ፀሐይ፣ መተማ፣ ግዮንና ዘንባባ የተባሉ ዩኒየኖች ወደ ውጭ ከላኩት 27 ሺህ 390 ኩንታል ሰሊጥና ነጭ ቦሎቄ እንዲሁም የማር ምርት ሽያጭ ነው።

ምርቱ የተላከው ለቻይና፣ ህንድ፣ እንግሊዝ፣ ኖርዌይ፣ ፓኪስታንና ጣሊያን ገበያዎች መሆኑንም ጠቁመዋል።

የራስ ጋይንት ዩንየን ሥራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ፈንታሁን  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዩኒየኑ ከ14 ሺህ ኩንታል በላይ ነጭ ቦሎቄ ለውጭ ገበያ ማቅረቡን ተናግረዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም 30 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ የቦሎቄ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ  ማቀዱን ነው የገለጹት።

የፀሐይ ዩንየን ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ በበኩላቸው፣ ዩኒየናቸው ወደ ውጭ ከላከው 8 ሺህ 550 ኩንታል የሰሊጥ ምርት 985 ሺህ ዶላር ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።

ዩንየኑ ወደውጭ የላከው የምርት መጠን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በሁለት ሺህ 330 ኩንታል፤ ገቢው ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው።

Published in ኢኮኖሚ
Page 1 of 2

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን