አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452
Items filtered by date: Sunday, 13 August 2017

አዲስ አበባ ነሃሴ 7/2009 የቱሪዝም አባት በመባል የሚታወቁት የአቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ  የቀብር ስነ ስርዓት  ዛሬ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጸመ።

አቶ ሃብተስላሴ  ኢትዮጵያን የ13 ወር ፀጋ (ሰርቲን መንዝስ ኦቭ ሰንሻይን) በሚል መጠሪያ በማስተዋወቅ ለቱሪዝም እድገት ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ነበሩ፡፡

አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ ከአባታቸው ፊታውራሪ ታፈሰ ሃብተሚካኤል እና ከእናታቸው ሙላቷ በላይነህ በአዲስ አበባ ከተማ በ1919 ዓ.ም ነበር የተወለዱት።

በተወለዱ በሁለት አመታቸው ወደ ግሪክ ያቀኑት ሃብተስላሴ ታፈሰ፤ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ተምረዋል፡፡

በመቀጠልም በግብጽ ቪክቶሪያ ኮሌጅ ለሁለት አመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፤ በ1950 እ.ኤ.አ ወደ አሜሪካ በመሄድ ከካልተን ኮሌጅ በአለምአቀፍ ግንኙነትና በስነ መንግስት አስተዳደር መስክ ተመርቀዋል።

እ.ኤ.አ በ1954 ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰው የመጀመሪያውን የቱሪዝም ድርጅት አቋቁመዋል።

በድርጅቱም ከረዳት እስከ ዋና ዳይሬክተርነት ደረጃ በማገልገል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲኖራት  የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

አቶ ሀብተስላሴ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው የሰሩ ታላቅ የቱሪዝም ሰው እንደነበሩ የቀድሞ የኢፌደሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስና የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ወልደ ማርያም  ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ  የቱሪዝም አባት በመባል የሚታወቁት እኚህ ታላቅ ሰው፤ ባጋጠማቸው የስትሮክ በሽታ በባልቻ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ነሃሴ 4 ቀን 2009 ዓ.ም በተወለዱ በ91 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።

ስርዓተ ቀብራቸውም ቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም አድናቂዎቻቸው በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል፡፡

አቶ ሀብተስላሴ በቱሪዝም ዘርፍ ላደረጉት አስተዋፅኦ በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የወርቅ ኒሻን የተበረከተላቸው ሲሆን በርካታ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ የሶስት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን 4 የልጅ ልጆችንም አይተዋል፡፡

 

 

 

 

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 7/2009 የኦሮሚያ ክልል የተሻለ ስነ ምግባር፣ እውቀትና ክህሎት ያለው ቀጣይ ትውልድ ለመገንባት ለበጎ ፈቃደኝነት ትኩረት መሠጠቱን ገለጸ።

በኦሮሚያ ልማት ማህበር አዘጋጅነት በክልል ደረጃ የበጎ ፈቃደኝት ቀን ተከብሯል፤ በጎ ፈቃደኝነትን ወጥነት ባለው መልኩ ማስኬድ የሚያስችል የአሰራር ማኑዋልም ይፋ ሆኗል።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በበጎ ፈቃደኝነት የተሻለ ስነ ምግባር እንዲሁም እውቀትና ክህሎት ያለው ትውልድ ለማፍራት እየተሰራ ነው።

በጎ ፈቃደኝነት ወጣቶች ያላቸውን ብሩህ አዕምሮ በእውቀት ገንብተው ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች እንዲተጉ ከሚያደርጉ ተግባራት መካከል ዋነኛው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከዚህም ባለፈ ተግባሩ ወጣቶች ወገናቸውን እያገዙ ራሳቸውንም ወደፊት ለሚጠብቃቸው የበለጠ ኃላፊነት እንዲያዘጋጁ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት በክልሉ በጎ ፈቃደኝነት ቀጣይነት ባለው መልኩ ሲሰጥ እንዳልነበረ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ በቀጣይ ወጣቶች ተግባሩን በመደበኛነት እንዲወስዱት ይደረጋል ብለዋል።

ለዚህም ራሱን የቻለ የአሰራርና የአደራጃጀት ማኑዋል መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤና የኦሮሚያ ልማት ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው ማህበሩ እስካሁን በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን ወጣቶችን በበጎ ፈቃደኝነት ሲያሰማራ ቆይቷል ብለዋል።

እንዲያም ሆኖ በዓለም ላይ ያሉ ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አገራት ተወዳዳሪ ሆነው መውጣት የቻሉት በጎ ፈቃደኝነትን በአግባቡ ስለተጠቀሙበት እንደሆነም ተናግረዋል።

ይህንኑ ዓለም ዓቀፍ ልምድና በአገር ውስጥ ያለውን ተሞክሮ በመቀመር የክልሉ ወጣቶች በበጎ ፈቃደኝነት ታንጸው ባህልና ማንነታቸውን ጠብቀው ለትውልድ እንዲያስተላልፉ ለማድረግ እየተሰራም ነው ብለዋል።

አቶ አበዱላ እንዳሉት አሁን አሁን በተወሰኑ ወጣቶች ዘንድ ጫት መቃም፣ ሲጋራ ማጨስና መጠጥ ቤት መገኘት የዘመናዊነት መገለጫ እየሆነ መጥቷል።

በጎ ፈቃደኝነት እነዚህንና መሰል ችግሮችን አልፈው አገራቸውንና ሕዝባቸውን የሚያከብሩና ከሌሎች ጋርም በሰላም አብረው መኖር የሚችሉ ወጣቶች መፍጠር የሚያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።

በማህበሩ አነሳሽነት እስካሁን በክልሉ በአካባቢ ጥበቃና በችግኝ ተከላ የተሻለ ስራ መሰራቱንም አቶ አባዱላ አስረድተዋል።

ማህበሩ እስካሁን በክልሉ በተበጣጠሰ መልኩ ሲሰጥ የቆየውን በጎ ፈቃደኝነት ወጥነት እንዲኖረው ለማድረግ ማኑዋል መዘጋጀቱን የገለጹት ደግሞ አቶ ጀማል አባሶ የኦሮሚያ ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

በ1985 ዓ.ም ማህበሩ ከተመሠረተ ጀምሮ ከ6 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ አባላትን ያፈራ ሲሆን እስካሁን ከ3 ቢሊየን ብር በላይ በማውጣት  ሶስት ሺህ ፕሮጀክቶች ማሰራቱንም ተናግረዋል።

Published in ማህበራዊ

አዲስ አበባ ነሃሴ 7/2009 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን አቻው ጋር ባደረገው የቻን ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ 1 ለ 1 ተለያየ።

ዋሊያዎቹ በ2018 ኬኒያ ለሚካሄደው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና ከሱዳን አቻው ጋር ዛሬ በሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ያደረገው የማጣሪያ ጨዋታ 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። 

ዋሊያዎቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ  የተሻለ እንቅሰቃሴ ቢያደርጉም ኳስን ከመረብ ማሳረፍ ግን  አልቻሉም።

በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ  በሱዳን ብሔራዊ ቡድን ጫና ውስጥ የገቡት ዋሊያዎቹ በቀላሉ ግብ ሊቆጠርባቸው ችሏል። ሰይፈዲን መኪ ሱዳንን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ከመረብ ማሳረፍም ችሏል።  

ተጋጣሚዎቹ  በተደጋጋሚ ወደ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መረብ ላይ አደጋ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሙከራዎች ሲያደርጉ ነበር።

ይሁን እንጂ የፋሲል ከነማው ተጫዋችና በብሔራዊ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈው አብዱራሃማን ሙባረክ የአቻነቱን ግብ ከመረብ በማሳረፍ ዋሊያዎቹን አቻ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ90 ደቂቃ ጨዋታ የሚቀረው ሲሆን ወደ ሱዳን አቅንቶ በሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ ለቻን ዋንጫ ለማለፍ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

ለዋሊያዎቹ ጨዋታው ከሜዳቸው ውጭ እንደመሆኑ መጠን ውጤቱን ለመለወጥ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

በመሆኑም ይህንን ውጤት መለወጥ ከቻሉና በደርሶ መልስ በድምር ውጤት የሚያሸንፉ ከሆነ ኢትዮጵያ በቻን ውድድር በቀጥታ የምትሳተፍ ይሆናል።

ጨዋታውም በመጪው ቅዳሜ በሱዳን የሚከናወን ይሆናል።

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የሚመሩት ዋሊያዎቹ በግብ ጠባቂነት ጀማል ጣሰው፣አብዱልከሪም መሃመድ፣ ደስታ ዮሐንስ፣ አንተነህ ተስፋዬና አስቻለም ታመነን በተከላካይነት አሰልፈዋል።

በአማካይ ስፍራ ሙሉዓለም መስፍን፣ ታፈሰ ሰለሞን፣ አዲስ ግደይ፣ ጋዲሳ መብራቴ እንዲሁም አብዱራሃማን መሐመድና ጌታነህ ከበደን በአጥቂነት ተጠቅመዋል።

 

 

 

Published in ስፖርት

አዲስ አበባ ነሃሴ 7/2009 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መቶ ሺህ የሚሆኑ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች አገር ውስጥ መግባታቸውን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ።

በሌላ በኩል በዚሁ በጀት ዓመት ከ4 ሺህ 500 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል።

በኢትዮጵያ ከተሽከርካሪ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳሬክተር አቶ ካሳሁን ኃይለማሪያም ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በሀገሪቱ እየተመዘገበ ካለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አንጻር  እየተስፋፋ ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰትና የመሰረተ ልማት ግንባታ ለተሽከርካሪ ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያት ነው።

"በመሆኑም በኢትዮጵያ የተሽከርካሪ ቁጥር በአማካይ በአመት በ11 በመቶ እያደገ ይገኛል" ብለዋል።

በሀገሪቱ አሁን ያለው አጠቃላይ የተሽከርካሪ ቁጥር ከ850 ሺህ በላይ መድረሱንም ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከተሽከርካሪ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የዜጎችን ለትራፊክ  አደጋ የመጋለጥ እድል ለመቀነስ መንግስት ዘርፉን የማዘመንና የግንዛቤ መፍጠር ስራዎችን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ላለፉት ሶስት ዓመታት ህይወታቸውን በትራፊክ አደጋ የሚያጡ ዜጎች ቁጥር በ10 በመቶ እያደገ እንደነበር ጠቁመው፤ "በበጀት ዓመቱ ይህን አሃዝ ወደ 4 ነጥብ 4 ዝቅ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል።

በ10 ሺህ ተሽከርካሪ 53 የሞት አደጋ ለማድረስ ግብ ቢቀመጥም አሁን 54 ሰው መሆኑን በመጥቀስ ብዙ መስራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ለዚህም በዘርፉ የተጀመሩ ዘመናዊ አሰራሮችን በማስፋት የትራፊክ ቁጥጥሩን የማጠናከሩ ስራ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል ። 

የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥን፣ ምዝገባና ፈተናን እንዲሁም ሌሎች የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በ95 ሚሊዮን ዶላር የኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሰራሩ ለትራፊክ አደጋ መጨመር አስተዋጽኦ የሚያደርገውን የመንጃ ፈቃድ አሰጣት ስርአት ግልጽነት እንዲኖረው ለማድረግ ይረዳልም ተብሏል።

"ይህም ህጋዊ ያልሆነ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥን ከማስቀረቱም በላይ  በፌዴራልና በክልሎች መካከል የተናበበ  አሰራር አንዲኖር ያስችላል" ሲሉ ተናግረዋል።

 

Published in ኢኮኖሚ

ሙገር ነሃሴ 7/2009 ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ በኤሌክትሪክ ኃይል ማጣትና መቆራረጥ መክሰሩንና ሊዘጋ የሚችልበት ሁኔታ ላይ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አካሉ ገብረህይወት ለኢዜአ እንደተናገሩት ሙገር ያለው ዋናው የሲሚንቶ ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሚደርስበት ጉዳት ምክንያት ካለው አቅም ከግማሽ በታች እያመረተ ነው፡፡

በታጠቅ ፋብሪካው ደግሞ በዚሁ በኤሌክትሪክ ኃይል ዕጦትና መቆራረጥ ምክንያት በአንድ ወፍጮ ብቻ የሚሰራ በመሆኑ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እየከሰረ ይገኛል ፡፡

ለሙገር ከተዘረጋው መስመር ለአካባቢው ነዋሪዎች በመሰጠቱና የነዋሪዎቹ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥና ሲመጣ በሚከሰት መቆራረጥና ያልተመጣጠነ ኃይል ወደ ፋብሪካው መግባት ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ያደረጉት ጥረት እንዳልተሳካላቸውም ነው ኢንጂነር አካሉ የተናገሩት፡፡ 

የኢንተርፕራይዙ የኢንጂነሪንግ ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ ኢንጂነር አብደና መኮንን እንደገለጹት በተለይ የፋብሪካው የአንዳንድ ዕቃዎች መለዋወጫ በቀላሉ የማይገኝ በመሆኑ ረጅም ጊዜ ለመቆም ይገደዳል፡፡

ከሁለት ነጥብ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የፋብሪካውን ጥሬ ዕቃ የሚያቀርበው ኮንቬየርም እንዲሁ በኤሌክትሪክ ምክንያት ጉዳት ደርሶበት ፋብሪካው ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ ከግማሽ በታች በሆነ አቅሙ ሲሰራ እንደነበር የገለፁት ደግሞ የኢንተርፕራይዙ የጥሬ ዕቃ አቅርቦትና ማምረቻ መሳሪያ ጥገና ቡድን መሪ ኢንጂነር ግርማ ባጫ ናቸው፡፡ 

የክሊንከር ምርት ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ ኢንጂነር አበራ ነጋሽ በበኩላቸው በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራጥ ምክንያት ማቃጠያ መሳሪያው ላይ  ጉዳት  እንደሚፈጠር ጠቅሰው ለዚህ መሳሪያ አነስተኛ ጥገና ለማድረግ ማሽኑ እስኪቀዘቅዝ ድረስ ሦስት ቀን እንደሚያስጠብቅ ይናገራሉ፡፡   ጠግኖም ሥራ ለማስጀመር ደግሞ ከ12 እስከ 18 ሰዓት ሊፈጅ እንደሚችል ነው የሚጠቁሙት፡፡   

የኢንተርፕራይዙ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አካሉ ታጠቅ የሚገኘው የድርጅቱ የሲሚንቶ መፍጫና ማሸጊያ ፋብሪካ “ከተመሰረተበት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን በኤክትሪክ እጦት በግማሽ አቅሙ እየሰራ ነው” ብለዋል፡፡

የፋብሪካው ሦስተኛ የምርት መስመር አካል የሆነው የታጠቅ ፋብሪካ ሲመሰረት እያንዳንዳቸው አራት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይልየሚፈልጉ ሁለት ወፍጮዎች ሲኖሩት የተሰጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ግን ከአንድ ወፍጮ በላይ ማንቀሳቀስ የሚያስችል እንዳልሆነ ነው ያመለከቱት፡፡

እርሳቸው እንደሚሉት በዚህ ምክንያት ፋብሪካው የተገነባበትን የብድር ገንዘብ እንኳን መክፈል  አልቻለም፡፡

የታጠቅ ፕላንት የጥገና ቡድን መሪ ኢንጂነር ዳንኤል አጥላው እንደሚሉት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ድርጅት የተጨማሪ ክፍያ ጥያቄዎችን ከማቅረብ የዘለለ አገልግሎት አልሰጣቸውም፡፡

ወፍጮዎቹ በዓመት ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ ሊፈጩ የሚችሉ ቢሆንም እስካሁን በግማሽ አቅም ብቻ እየተሰራ መሆኑን ተናግረው አንደኛው ወፍጮ ባለመስራቱ ብቻ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ እድል መፍጠር እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

የኢንተርፕራይዙ ዋናሥራ አስኪያጅ፤ ችግሩን ለመፍታት በድርጅቱ ሥራ አመራር ቦርድ ሳይቀር ፓርላማውም እንዲያውቀው የተደረገ ቢሆንም መፍትሄ ባለመገኘቱ የሚመለከታቸው ሁሉ መስሪያ ቤቱን ከመዘጋት እንዲታደጉት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለኢንተርፕራይዙ የታጠቅ ፕላንት ተጨማሪ ኃይል ለማቅረብ የጀመረውን መስመር የመዘርጋት ሂደት በተለይም በተለያዩ ቦታዎች የተተከሉ ፖሎች ባሉበት መቆማቸውንና የኤሌክትሪክ መስመሮቹም ተበጣጥሰው በየሜዳው መቅረታቸውን ኢዜአ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ምላሽ እንዲሰጥ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡

 

 

Published in ኢኮኖሚ

ሰመራ ነሃሴ 7/2009 በአፋር ክልል ጉሊና ወረዳ ትናንት በደረሰ የመብረቅ አደጋ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የወረዳው ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን አሊ ቡቶ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአደጋው ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በአምስት ሰዎች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡

በወረዳው ሀሌገርቦ ቀበሌ ልዩ ቦታው ያፊኦ በተባለ ቦታ ላይ ትናንት ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ በወደቀ መብረቅ ባልና ሚስትን ጨምሮ የአራት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው አምስት ሰዎችም በአካባቢው በሚገኝ የጤና ተቋም ህክምና እየተከታተሉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በአካባቢዉ በነበሩ አንድ የቀንድ ከብትና ፍየል በመብረቁ መሞታቸውን ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡

በተያዘው የክረምት ወራት በአፋር ክልል ከእዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ በተለያዩ ወረዳዎች ተደጋጋሚ የመብረቅ  አደጋ መከሰቱንም የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ቀደም ሲል መግለፁ ይታወሳል፡፡

ባለፉት ሦስት ሳምንታት ውስጥ ጭፈራ፣ እዋ፣ ዱብቲ፣ ኩነባና ጭፍራ ወረዳዎች ተመሳሳይ የመብረቅ አደጋ ደርሶ የ13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ተወካይ አቶ ከድር አብደላ በማሳያነት መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

በአጠቃላይ በእነዚህ ጊዜያት ወስጥ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በመብረቅ ተመተው የሞቱ ሰዎች ቁጥር የአሁኖቹን ጨምሮ 17 ደርሷል፡፡

 

Published in ማህበራዊ

በባህር ዳር ከተማ በቀበሌ 04 በብሄራዊ ሎተሪ የባህር ዳር ቅርንጫፍ አካባቢ ትናንት ምሽት የተጣለ ቦምብ በሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የከተማው ፖሊስ መመሪያ አስታወቀ።

በድርጊቱ የተሳተፉ አካላትን ለመያዝ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የመምሪያው ኃለፊ ኮማንደር ዋለልኝ ዳኘው ለኢዜአ እንደገለፁት አደጋው ትናንት ከምሽቱ 1፡ 50 አካባቢ መድረሱን ተናግረዋል።

በደረሰው አደጋም በጉዞ ላይ የነበሩ ወንድና ሴት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት በመድረሱ በባህር ዳር ፈለገ ህይወት ሪፈራል ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ህብረተሰቡን ለማሸበር ድርጊቱን የፈፀሙ አካላትን በቁጥጥር ስራ በማዋል በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግም በፀጥታ አካላት ሰፊ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ድርጊቱም የባህርዳርን ሰላም ለማደፍረስና ልማቷን ለማደናቀፍ ፍላጎት ባላቸው ፀረ ሰላም ሃይሎች በሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍና በተባባሪዎቻቸው የተፈፀመ ሳይሆን እንደማይቀር ጠቁመዋል።

ሐምሌ 23ቀን 2009 እና ነሐሴ 3 ቀን  2009 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ተመሳሳይ የቦምብ ጥቃት ለመፈፀም በሂደት ላይ የነበሩ 4 ተጠርጣሪዎችም በፀጥታ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ ኮማንደሩ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይም ሐምሌ 30 ቀን 2009 በፔዳ መስመር ቦምብ ያፈነዱ 3 ዋና የድርጊቱ ተሳታፊዎችና ሁለት ተባባሪ አካላት በፀጥታ ሃይሉ ብርቱ ጥረት በቁጥጥር ስር በማዋል ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የከተማዋን ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ የፀጥታ አካላት ለሚያደርጉት ጥረት ህዝቡ ጥፋተኞችን በማጋለጥ የተለመደ ትብብሩን ማድረግ እንደሚገባው ኮማንደር ዋለልኝ አሳስበዋል።

Published in ማህበራዊ

ድሬዳዋ ነሃሴ 7/2009 ሴቶች በልማት ቡድን ተደራጅተው እያስመዘገቡ የሚገኘውን ውጤታማ ሥራ ከማስቀጠል ጎን ለጎን ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን የመደገፍ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ተናገሩ፡፡

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም የአራት ቀናት ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ትናንት በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሯል፡፡

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ደሚቱ ሃምቢሣ በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በ2009 በጀት ዓመት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የህፃናት መብትና ደህንነት ለማስከበር በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል፡፡

በተለይ ''በመላው የሀገሪቱ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በልማት ቡድን የተደራጁ በርካታ ሴቶች ካሉበት ድህነት ተላቀው በምጣኔ ሃብት ሽግግሩ ውስጥ እያበረከቱ የሚገኙት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው'' ብለዋል፡፡

በቁጠባ ያሰባሰቡት በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብም በሴቶች የብድርና ቁጠባ ተቋማት አማካኝነት ለሌሎች ሴቶች የሥራ ዕድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በመጪው ዓመትም እየጎለበተ የሚገኘውን የሴቶች ሁለንተናዊ ተሣታፊነትና ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ሴቶች በልማት ቡድኖች ተደራጅተው እያስመዘገቡ የሚገኙትን ውጤታማ ሥራ ከማስቀጠል ጎን ለጎን ለችግር የተጋለጡ ህፃናትን በመደገፍ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፍራት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከርም ሌላው ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለችግር የተጋለጡና በጎዳና ላይ የሚገኙት 12 ሺ 700 ህጻናት ማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ተደርጎላቸው ለመጪው ህይወታቸው ተስፋ እንዲሰንቁ የተከናወነው ስራ ተስፋ ሰጪ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል፡፡

መድረኩ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው በአስተዳደሩ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከልና ለማስቆም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተለይ መምህራንና የእምነት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና የጤና ባለሙያዎችን ያካተተ የህዝብ ንቅናቄ ሥራ በመፍጠር የተከናወነው ተግባር ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

''ለ2ሺ 800 ሴቶች የ112 ሚሊዮን ብር ብድር በመስጠት በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል፤ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ ቆጥበዋል፤ ለሌሎችም የሥራ እድል እየፈጠሩ ናቸው›› ብለዋል፡፡

እንደ ከንቲባ ኢብራሂም ገለጻ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በማፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣  በከተማ ግብርና፣ በንግድና በመንግስታዊ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ለ12ሺ 300 ሴቶች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

የድሬዳዋ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሀመድ በበኩላቸው ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች ማቆያና ማገገሚያ እንዲሁም ለአደጋና ለችግር ለተጋለጡ ህጻናት  ማቆያ የሚውሉ ባለ አንድ ፎቅ መንታ ህንፃዎች በ13 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የህንጻዎቹ ግንባታ በመጪው ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በዘርፉ ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

የሁሉም ክልሎችና የሁለቱም ከተማ መስተዳድሮች የ2009 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃጸም ሪፖርቶች ለመገምገም ትናንት የተጀመረው ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ለአራት ቀናት ይቆያል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም በድሬዳዋና በሐረሪ ክልል በሴቶችና ህፃናት ላይ የተከናወኑ ተግባራትን የሚጎበኙ ሲሆን በ2010 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ መሪ እቅድ ላይም ይወያያል፡፡

Published in ማህበራዊ

ጅማ ነሃሴ 7/2009 በጅማ ዞን በዘንድሮው ክረምት ከ188 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኝ መተከሉን የዞኑ ቡናና ሻይ ግብይት ባለስልጣን ጽህፈት ቤት ገለፀ ።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሉባባ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት ችግኙ የተተከለው በ47 ሺህ 382 ሄክታር መሬት ላይ ነው፡፡

የተተከለው የቡና ችግኝ በተገቢው ሁኔታ እንዲፀድቅ በአርሶ አደሮች እንክብካቤ እየተደረገለት ነው፡፡

ባለፈው አመት ከተተከለው ከ186 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ  የቡና ችግኝ  90 በመቶ መፅደቁን ምክትል ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

የጎማ ወረዳ ነዋሪ  አቶ ሳቢቁ አባመጫ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮው ክረምት የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ መሠረት በማድረግ በግል ይዞታቸው ላይ በተሻሻለ መንገድ የቡና ችግኝ መትከላቸውን ተናግረዋል፡፡

የቡና ችግኙን 60 በ 60በየሆነ ስፋትና ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፍር፣ ጸሃይ በማስመታት፣ የቡና ገለባ ከአፈር ጋር በማዋሃድና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም ተከላውን እንዳካሄዱ አስረድተዋል።

የሊሙ ኮሳ ወረዳ ነዋሪው አቶ አህመድ ኡመር በበኩላቸው የቡና ችግኙን በዘመናዊ መንገድ  በመትከል  የቡና ምርታቸውን ለማሳደግ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አመታት ከተከለው የቡና ችግኝ ተስፋ ሰጭ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በጅማ ዞን ከሚገኙ 15 ከፍተኛ ቡና አምራች ወረዳዎች11 ወረዳዎች ጥራት ያለው ቡና ወደ ውጭ እየላኩ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በዞኑ ከሚካሄደው የግብርና ስራ 90 በመቶው የቡና ልማት መሆኑ ታውቋል፡፡

Published in ኢኮኖሚ

ባህር ዳር ነሃሴ 7/2009 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በሚሰጡት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ  የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡

በከተማው ግንቦት 20 ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አትክልት ሙሉ እንደተናገሩት ግድግዳው ሳጣራ፣ ጣራው ፕላስቲክ የሆነው መኖሪያ ቤታቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች የቆርቆሮ ክዳን ቤት ተሰርቶላቸው “ከችግሬ ተላቅቄያለሁ”ብለዋል ፡፡

በቁልቋል ሜዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ6ኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ልቅና መንግስቱ በበኩሏ “በበጎ ፈቃደኞች የሚሰጠኝ የማጠናከሪያ ትምህርት የእንግሊዘኛ ቋንቋ የመናገር ችሎታየን እንዳሻሽል እያገዘኝ ነው” ብላለች።

በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አማካኝነት  በነጻ በመማር ላይ መሆኑን የገለጸው የ7ኛ ክፍል ተማሪው ሃብታሙ ውብሸት በቀጣዩ የበጋ ወቅት በመደበኛው ፕሮግራም ለሚማረው ትምህርት “መሰረት እንድይዝና በትምህርቴ ተወዳዳሪ እንድሆን ያስችለናል” ብሏል።

“የምሰጠው የሂሳብ ትምህርት ተማሪዎች ተጨማሪ ዕውቀት እንዲያገኙ ያግዛል” ያለው ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የመካኒካል ኢንጅነሪንግ ተማሪና የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪው በጎ ፈቃደኛ ምስጋናው አባት ነው።

የእረፍት ጊዜውን የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን በማገዝ ተጨማሪ ዕውቀት እንዲያገኙ በማድረግ እያሳለፈ መሆኑን ገልጿል፡፡

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ጉዳይ ቢሮ የወጣቶች ስራ ፈጠራና ስልጠና ባለሙያ አቶ ብሬ ወንዴ እንደገለፁት እስካሁን 2 ሚሊዮን የሚጠጉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

ወጣቶቹ እየተሳተፉ ያሉት በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በመንገድ ጥገና፣ በችግኝ ተከላ፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመጠገን፣ በሰብል ልማትና እንክብካቤ፣ በጤናና በሌሎች የግብርና ስራዎች ነው።

በተለይ በትምህርት ዘርፍ  107 ሺህ 527 ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተከታተሉ ሲሆን 590 ሚሊዮን የሚጠጋ ችግኝ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ በተሰራባቸው አካባቢዎች መትከላቸውንም ጠቅሰዋል።

እስካሁን በተከናወነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራውም ከዩኒቨርሲቲ፣ ከኮሌጅ፣ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡና ሌሎች ወጣቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ታውቋል።

 

Published in ማህበራዊ
Page 1 of 3

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን